Wednesday, October 31, 2012

የፍርሐት ዘመን

ማሕሌት ፋንታሁን

በሕይወታችን የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ከመከወን እንድንቆጠብ ለራሳችን ስንነግር ወይም ውስጣችን ሲሰማው የፍርሐት ስሜት ተሰማን ልንል እንችላለን፡፡ የፍርሐትን ምንጭ በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ፍርሐታችንን የምናምንበት፣ ምክንያቱም ከራሳችን የመነጨ ድክመት በሚሆንበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድርጊቱን በመፈፀማችን ሊደርስብን ይችላል ብለን የምናሰላው አግባብ ያልሆነ ጉዳት/በደል በማሰብ ድርጊቱን ከመፈፀም ስንቆጠብ ነው፡፡

ከላይ እንዳልኩት የለት ተለት እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ ምንጫቸው ከሁለት አንዱ ወይም ከሁለቱም የሆነ ፍርሐት ሊያሳድሩብን የሚችሉ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያጠነጥነው በአሁን ሰዓት በሀገራችን የሚታየውን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሐሳብን የመሰንዘር፣ የመወያየት፣ የመሳተፍ እና የመተቸት ፍርሐትን ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በተጠቀሰው የፍርሐት ምንጭ የሚከሰተውን ነው፡፡

ተማሪዎች

ተማሪዎች ስል ዕድሜያቸው ለአቅመ ማገናዘብ ከደረሱት ጀምሮ ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት ዕድሉ ያላቸው ወይም ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሚገቡ ወይም በግል ኮሌጅ ገብተው የሚቀጥሉና ውጤታቸው ትምህርታቸውን የማያስቀጥላቸው ሲሆኑ ሁሉንም የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ትምህርታቸውን የቀጠሉትም ያልቀጠሉትም በደረጃቸው ሥራ የመያዝ እና ራሳቸውን ለማኖር የመጣር ግዴታ አለባቸው፡፡ ሥራ ለማግኘት ደግሞ ያልተጻፈው ሕጋችን በኢሕአዴግ መጠመቅን ይጠይቃል፡፡ ሥራ አጥ ሆኖ ኢሕአዴግን መቃወም ወይም ስህተቶቹን እየነቀሱ መተቸት የማይታሰብ ነው፡፡ ይህን ጠንቅቀው ስለሚያቁ  ተማሪዎች ቀደም ብለው አባል ወይም በደጋፊነት መዝገብ መስፈርትን እና የሚፈለገውን ሟሟላት ሌላው ተግባራቸው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ዋናው ነገር እንጀራ ነው፡፡ ምናልባትም ከተደላደሉና የትም ተቀጥረው የመሥራት ዕድላቸው የሰፋ ሲሆን ወደራሳቸው ሊመለሱ የሚችሉ ቢሆንም በጣም ኢሕአዴግ በሆኑ ቁጥር ጥቅማ ጥቅሞቹም በዛው ልክ ስለሚጨምሩ እዛው ሰምጠው የሚቀሩ ይበዛሉ፡፡ ለዚህም ነው በብዙ መጽሐፍት ያነበብነውን የሀገራቸውን ፖለቲካ የሚተነትኑ እና የራሳቸው የሆነ አቋም ያላቸው ተማሪዎች ማየት ሕልም የሆነብን፡፡
ሠራተኞች

ደረጃው ይለያይ እንጂ የመንግሥት የሆኑም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በግልፅ ሐሳባቸውን ለመሰንዘር አይደፍሩም፡፡ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የኢሕአዴግ አባል ወይም ደጋፊ የሆኑ ሰራተኞች የሚያገኙትን እድገትና የተለያዩ ዕድሎች በማየት ሌሎች ገለልተኛ ሆነው የነበሩ ሠራተኞች አባል እንዲሆኑ ይገደዳሉ፡፡ ሁሉም ሰው የሚሠራው ለለውጥ እና ለዕድገት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ለዚህም ለውጥ እና ዕድገት የሚያስገኘውን መንገድ አልቀበልም ብለው በራሳቸው ሐሳብ የፀኑ ብዙዎች በነሱ መያዝ ያለበት የኃላፊነት ቦታ ለቦታው በማይመጥን ሰው እንደሚያዝ በተደጋጋሚ የምንሰማው ስሞታ ነው፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከተመሰረቱበት ዋና ዓላማ ጎን ለጎን መንግሥቱን የሚመራው ፓርቲን ዓላማ የማስፈፀም ኃላፊነትም ያለባቸው ይመስላል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኢሕአዴግ ፓርቲ ጽ/ቤት የሚመስሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በፓርቲው  ያለው መዋቅር እና አሠራር አባል በሆኑ (ያው አብዛኞቹ አባል ናቸው) ሠራተኞች በመሥሪያ ቤቱም ተፈፃሚ ነው፡፡ የ1 ለ 5 የውይይት አደረጃጀትን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲውን የሚመለከቱ ስብሰባዎች በሥራ ሰዓት ቢካሄዱም ችግር የለውም፡፡ 
መንግሥታዊ ያልሆኑ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሠራተኞችም አባል መሆን ላይጠበቅባቸው ይችል ይሆና እንጂ መንግሥትን መቃወም እና መተቸታቸው በአሠሪዎቻቸው አይወደድላቸውም፡፡ ምክንያቱም አሠሪዎች ከመንግሥት ጋር መነካካት አይፈልጉም፡፡

አሠሪዎች

ከላይ አሠሪዎች ከመንግሥት ጋር መነካካት አይፈልጉም ብያለሁ፡፡ አባል ወይም ደጋፊ መሆን ሥራዎችን እንደሚያፋጥን እና ከመንግሥት ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ ሁሉ እንግልት እንደማይኖርባቸው ስለሚያውቁ ብዙ አሠሪዎች አባል ወይም ደጋፊ ይሆናሉ፡፡ ወይም ከዳር ሆነው የሚመለከቱ ይሆናሉ፤ ግን አይቃወሙም ወይም አይተቹም፡፡ ስለሆነም ሠራተኞቻቸው አባል ቢሆኑላቸው እሰየው ነው፤ ተቃዋሚ ወይም የሚተቹ ባይሆኑ ግን ምርጫቸው ነው፡፡ ባጠቃላይ ከመንግሥት ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባት ስለማይፈልጉ መንግሥት የሚያስደስተውን ነገር ቢያደርጉ ይመርጣሉ፡፡

ባለሀብቶች

በድህነት ወይም በአቅም ማነስ ምክንያት ብቻ መንግሥትን ለመደገፍ የምንገደድ ቢመስለንም በሚገርም ሁኔታ ይህን ፍርሐት ገቢያቸው ከፍተኛ የሆኑ ባለሀብቶችም ይጋሩታል፡፡ ዓላማቸው ባላቸው ሀብት ላይ ሌላ ሀብት መጨመር ስለሆነ ምንም ቢሆን ከመንግሥት ጋር ተስማምቶ መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ከመንግሥት ትዕዛዝ ባይቀበሉም (የተቀበሉም ሊኖሩ ይችላሉ)፤ ለተቃዋሚ ድርጅች እና ፓርቲዎች ንብረታቸውን ባለማከራየት፣ መንግሥትን የሚተቹ ማንኛቸውም ዓይነት ሥራዎችን ስፖንሰር ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ባለመርዳት እና በመሳሰሉት ድርጊታቸው ፍርሐታቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡   

እንግዲህ ማን ቀረ? ዋና ዋናዎቹን ጠቀስኩ እንጂ ይህ ዓይነቱ ፍርሐት ያልገባበት ቦታ የለም፡፡ አብዛኛው ዜጋ በሀገራችን የፖለቲካ ጉዳይ መወያየት፣ መሳተፍ እና መተቸትን እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ ሐሳቡን በአደባባይ ቢናገርም ቢወያይም መንግሥትን የማያስከፋውን እየመረጠ ነው፡፡  የመንግሥት መ/ቤት ደጅ ሳንረግጥ መኖር አለመቻላችን ባልከፋ ነገር ግን ጉዳያችን በአግባቡ እንዲፈፀም ደግሞ የመንግሥት ወዳጅ መሆን እንደመስፈርት መጠየቁ፤ ካልሆንን የሚደርስብን እንግልት እና በደል ተደማምረው የፍርሐታችን ልክ መድረሻ በማሳጣት የመንግሥት አጎብዳጅ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ሲጠሩን አቤት ሲልኩን ወዴት ሆኗል ነገሩ፡፡ የመንግሥትን ስህተት በግልፅ የሚናገር፣ የሚወያይ፣ የሚተች፣ የሚቃወም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነና በነዚህ ሰዎች ዙሪያ ያለ ሰው ደግሞ መንግሥት ወዳጅ አይደለም፡፡ ወዳጅ ካልሆነ ደግሞ መንገዱ ቀና አይሆንም፡፡ ይህ እንግዲህ በሕገመንግሥቱም ሆነ በማናቸውም የኢሕአዴግ ሕጎች ያልተጻፈ ነገር ግን ዜጎችን አግባብ ወዳልሆነ የፍርሐት ቀጠና እየወሰደ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም የአባላት ቁጥር ያለመጨመር እና እንቅስሴዎች መቀዛቀዝ ምክንያት አንዱ ይሄ ነው፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ሲያካሂዱ የሚገኘው ሰው በጣም ጥቂት ነው፡፡ አብዛኛዎቹን ኢሕአዴግ በሰበብ አስባቡ አባል ያደረጋቸው ሲሆን፤ የቀሩት ደግሞ ስብሰባው ላይ ቢገኙ የሚደርስባቸውን ነገር በማሰብ እና በመፍራት ብቻ አይገኙም፡፡

ይህን ስጋት እና ፍርሐት አስወግደው በራሳቸው ሐሳብ ብቻ በመመራት መንግሥትን እየተቃወሙ እና እየተቹ የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁመው እስካሁን ያሉ ጥቂቶች ቢኖሩም ብዙዎቹ እስር ቤት እና በስደት ናቸው፡፡ የተለያዩ ማኅበራዊ አውታሮች ላይ የምናያቸውን መንግሥትን በግልፅ የሚተቹ ጽሑፎች እና አስተያየቶችን አይተን  ጸሐፊው ወይም አስተያየት ሰጪው ከኢትዮጵያ ውጪ እንደሆነ መታሰቡም ሀገር ውስጥ ያለውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ፍርሐት በግልጽ ያሳያል፡፡ አንዳንዴም ከሀገር መውጣት እንደፈለገ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከአሠሪ ወይም ከመንግሥት ሰው ከሚደርስ ማስጠንቀቂያ ወይም ማስፈራሪያ በተጨማሪ የጸሐፊው ቤተሰብ፣ ጓደኛ ወይም የቅርብ ሰው ነኝ ባይ ምክር፣ ማስፈራሪያ እና ተግሳፅ ሊያስተናግድ ግድ ይለዋል፡፡ ከኛ ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ያለው ሰው አጋጥሞን እንኳን በግልጽ ሊያወራን ቢሞክር ‹ተልኮብኝ ይሆን› በሚል ጥርጣሬ እንጂ በሙሉ ልባችን ለማውራት ፍርሐት አለብን፡፡ በፌስቡክና ሌሎች ማኅበራዊ አውታሮች ራሳችንን ገልጸን የተሰማንን እና የምናቀውን ሐቅ ለማውራት እንፈራለን፡፡ ሌላም ሌላም ብዙ ፍርሐቶች አሉብን፡፡

ምክንያቱም እንፈራለን፡፡

ግራ የሚያጋባ የወቅቱ ሐቅ! ማብቂያውን እናፍቃለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment