Wednesday, October 24, 2012

የእነርሱ እና የእኛ ሕዳሴ
የሐዲስ ዓለማየሁን “ጉዱ ካሣ”፣ የበዓሉ ግርማን “አበራ”፣ የዳኛቸው ወርቁን “አደፍርስ” ማን ይዘነጋቸዋል? እንኳን ‘ፍቅር እስከመቃብር’ን፣ ‘ከአድማስ ባሻገር’ን እና ‘አደፍርስ’ን ያነበቡ ቀርቶ ያላነበቡም ያውቋቸዋል፡፡ እነዚህ ገጸ ባሕርያት የሚታወሱት ከዘመናቸው ባፈነገጠ ማኅበራዊ ሃያሲነታቸው ነው፡፡

እነዚህን ገጸ ባሕርያት ወደኋላ ዞር ብለን የፈጠሯቸውን ደራሲያን ስናስብ ደራሲያኑ በየገጸ ባሕሪዎቻቸው አንደበት ማኅበረሰቡን በነገር አለንጋ ይገርፉታል፣ በምክንያት ይሞግቱታል፡፡ ያኔ እነዚህ እና ሌሎቹም ጸሐፍት ይህንን አሉ፤ ዛሬ እና የዛሬዎቹስ?

እዚህች’ጋ ሌላው የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ባለፈው ሣምንት የጠየቃትን ጥያቄ መልኳን ቀይሬ ላንሳትና፣ እንደው ለመሆኑ (ከዚሁ ከልቦለድ ዘርፍ ሳንወጣ) በአለፉት አምስት፣ አሥር ወይም ሀያ ዓመታት ውስጥ እጅግ ተወደደ አነጋገረ፣ ልቤ ውስጥ ቀረ የምንለው መጽሐፍ አለ? ከላይ የጠቀስናቸውን ገጸ ባሕርያት ያክል ያመራመረን፣ ያነጋገረን፣ የሚታወሰን ገጸ ባሕሪ አለ? - ለኔ የለም፡፡

ጥያቄውን በልቦለድ ብቻ አነሳሁት እንጂ፣ ከአንድ ወዳጄ’ጋ ከዚህ ቀደም በመሰል ሐሳቦች ዙሪያ ስናወራ፤ እስኪ የ60ዎቹን ዘመን ወጣቶች እና የአሁኖቹን እናወዳድር ብለን በሁሉም ዘርፍ ሞክረን ነበር፡፡ ያኔ የነበሩ ወጣት ደራሲያኖችን እና ገጣሚዎቻችንን ጠቃቀስን እና አሁን ላይ መጣን… ከበውቀቱ ስዩም እና ምናልባትም እንዳለ ጌታ ከበደ በላይ መሻገር አልቻልንም፡፡ እነአፈወርቅ ተክሌ፣ እነእስክንድር ቦጎሲያን እና ወዘተን… ጠቃቀስን እና የነርሱ እኩያ ይሆናሉ ብለን ተስፋ የምንጥልባቸውን ሰዓሊዎች ማፈላለግ ጀመርን፣ ይሄ ነው ልንነው የምንችለው ሰው አልመጣልንም፤ ሌላው ቀርቶ የሙዚቃ ባንድ እና ዘፈን ዘርፍ ውስጥ መጣን፣ የበፊቶቹን ኦርኬስትራ ቡድኖች የሚተካ፣ ወይም ሁሌም ልብ የሚያሸብሩትን ዘፈኖች እና ዘፋኞች ይተካል ብለን የምንጠራው ዘፋኝ አልነበረንም… ምናልባት እጅጋየሁ ሽባባው… ተባባልን፡፡ ከጋዜጠኞችም ለማወዳደር ሞካክረን ነበር፣ እነ ጳውሎስ ኞኞን፣ እነ ታደሰ ሙሉነህን የሚተካ ቀርቶ ተስፋ የሚጣልበት ጋዜጠኛ አለ?

በየጊዜው በናፍቆት የምንጠብቀው የጋዜጣ ወይም የመጽሔት አምድ/አምደኛ፣ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ትዕይንት፣ ልባችን እስኪጠፋ በጋራ የምናደንቀው ወጣት ባለሙያ ወይም ጀግና… ብቻ በጥቅሉ ምንም የለንም፡፡

ችግሩ የኛ አለማወቅ ነው፣ ወይስ አማተሮቹን ከአንጋፋዎቹ ጋር ማወዳደራችን የሚል ጥያቄም ተከስቶብኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ እነዚህን የምናደንቃቸውን አንጋፋ ባለሙያዎች የምናደንቅላቸው የወጣትነት ሥራዎቻቸውን እንጂ አሁን በስተርጅና የሠሯቸውን (ያውም ካሉ) አለመሆኑን ሳስብ ችግሩ የእውነት የወቅቱ የፈጠጠ ችግር መሆኑ ታሰበኝ እና እንድንነጋገርበት ይዤው መጣሁ፡፡

ኢትዮጵያ እንዴት ሰለጠነች?

ለውይይታችን ማጠናከሪያ፣ ኢትዮጵያን የማዘመን ሙከራዎች በየመንግሥታቱ መሞካከራቸውን እያስታወስን ከነዚህ ውስጥ ዐብይ ለውጥ ያስከተሉትን ጥንታውያን የዘመናዊነት እንቅስቃሴዎች እና የሀያኛውን ክፈለዘመን እርምጃዎች እያየን ዘንድሮ ላይ እንደርሳለን፡፡

 1. የአክሱም ስልጣኔ
  ከክርስቶስ ልደት በፊት 400 ዓመት አስቀድሞ የተጧጧፈው የአክሱም ስልጣኔ እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን ለመዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአክሱም ስልጣኔ ስር መሠረት እና ውርሱ በቅጡ አይታወቅም፡፡ እስካሁንም ድረስ ቆመው ከሚገኙት እና አምልኮተ-መራባትን ያመለክታሉ ከሚባሉት ሀውልቶች በቀር ለትምህርትነት የሚበቃ፣ ወይም ከዚያ ዘመን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ትውፊታዊ ቁምነገር አለ ለማለት የሚያስደፍር ግኝት የለም፣

 2. የዛግዌ ስልጣኔ
  የአክሱም ስልጣኔ መውደቅን ተከትሎ የኢትዮጵያ የጨለማ ዘመን ለ200 ዓመታት ነገሠ፡፡ ከዚያም በመራ ተክለሃይማኖት አማካይነት የዛግዌ ስልጣኔ ተጀመረ፡፡ የዛግዌ ስልጣኔ ክርስትናን በማስፋፋት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ትሩፋቱም የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስትያናት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ትውፊታዊ ትምህርት ናቸው፡፡ የዛግዌ ዘመነ መንግስት ከአክሱም ስልጣኔ በተሻለ ሃይማኖት ቀመስ ቢሆኑም ጽሑፎች ተጽፈው ለቀጣዩ ትውልድ የተላለፉበት የመጀመሪያው ዘመን ነው ማለት ይቻላል፣

 3. ሰሎሞናዊ ስልጣኔ
  ይሄንኛው የስልጣኔ ዘመን የአክሱም ዘመን ቀጣይ እና ሰሎሞናዊ ቤተሰብ ነን በሚሉ ነገሥታቶች የተመራ የስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ የዚህ ዘመን መጨረሻ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ዘመን ለቅርስነት ያስመዘገባቸው ነገሮች የሉም ማለት ይቻላል (የዘመነ መሳፍንት ቤተመንግሥታትም ቢሆኑ በዚህ ዘመን መሐል የተፈጠሩ የመከፋፈል ታሪኮች ናቸው፤) ሆኖም የአሁኒቷ ኢትዮጵያ የአሁኑን ቅርጿን የያዘችው በዚህ የስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን አውሮጳውያን አፍሪካን ሲቀራመቱ ኢትዮጵያውያን ግን በእምቢተኝነት ራስ ገዝ አስተዳደር የፈጠሩበት ይህ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ የተሠሩት ሥራዎች ኢትዮጵያን ከዘመናዊነት ጋር በማስተዋወቁ ረገድ መንገድ ጠራጊዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ በዚህ ዘመን ባቡር፣ ዘመናዊ ትምህርት፣ የጤና ብሎም የባንክ አገልግሎቶች እና ወዘተ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ተዋውቀዋል፣

 4. የድኅረ ጣሊያን ኃይለሥላሴ ስልጣኔ
  በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚኖራቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አብዛኛውን ኢትዮጵያን የማዘመን ሥራ የሠሩት ከጣልያን የአምስት ዓመት ወረራ በኋላ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሚያዝያ 27/1933 ንጉሡ ከስደት ሲመለሱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የ‘አዲስ ዘመን’ እንቅስቃሴያቸውን ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ከሙሉ ፊውዳላዊ አስተዳደር በከፊል አላቀዋታል፣ በብሔር እና ሃይማኖት “መቻቻል” ላይ መጠነኛ ሚዛን እንዲሰጥ በሚል ሕገ መንግሥታቸውንም አሻሻለዋል፣ ፓርላማው ለሕዝቦች በመጠኑ የተከፈተውም በዚሁ ዘመን ነው፣ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ተስፋፋ፡፡ ከዚያም በላይ እስከአሁኑ የአባይ ግድብ፣ የቁጠባ ቤቶች (ኮንዶስ)፣ የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ እና ወዘተ መሠረታቸው የተጣለው በዚህ የስልጣኔ ዘመን ነበር፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን የተፈጠረው የትምህርት እና የአንባቢነት ፋሽን በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸውን ዘመን አይሽሬ ጠበብት ለመፍጠር በቅቷል፣

 5. የማርክሲስት ስልጣኔ
  የዚህ ዘመን ስልጣኔ ባለቤቶች የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ወጣቶች ሲሆኑ፣ ወደማርክሲዝም የመራቸውም በዘመኑ ለነበረው ፊውዳላዊ አስተዳደር የነበራቸው የመረረ ጥላቻ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ለተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም (ማርክሲዝም/ማኅበረሰባዊነት) ነገር ግን በተለያየ ቡድን ተቧድነው ሲቆራቆዙ የነበረበት ዘመን ሲሆን፣ ለሁለት አሥርት ዓመታት በዘለቀው መቆራቆዛቸው ሳቢያ ‘ሰብኣዊ-ዘመናዊነት’ የጎደለው ዘመነ ስልጣኔ፣ ነገር ግን በተለይ መንግሥታት ከሃይማኖታዊ ጥገኝነት የተላቀቁበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘመን መጀመሪያ ላይ ተስፋ ፈንጥቆ የነበረው መሃይምነትን የመቅረፍ ‹የመሠረተ ትምህርት› ዘመቻም፣ በዘመኑ መጨረሻ ላይ ጠውልጎ ነበር፤ ሕዝቦች ለፖለቲካዊ ተሳትፎ የነበራቸው ጉጉት በፍራቻ መቀመቅ የወረደውም በዚህ ዘመን ነው፣

 6. የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስልጣኔ
  የማርክሲስትን የስልጣኔ ዘመን (በአገራችን) ተክቶ የመጣው የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስልጣኔ አጀማመሩ ላይ ለካፒታሊዝም የቀረበ ቅይጥ ኢኮኖሚ መር ስልጣኔ ለመሆን ቢሞክርም፣ የኋላ ኋላ ሶሻሊስታዊ ዴሞክራቲክ ኢኮኖሚ መር የሚመስል የስልጣኔ ዘመን ሆኗል፡፡ ዘመኑን በይፋ ‘የሕዳሴ ዘመን’ ብሎ ለመጥራት በመንግሥት የታወጀ ሲሆን፣ በተለይ ለአንደኛ ደረጃ (አውራ) መንገዶች እና ሕንጻ ግንባታ ትኩረት የሰጠ የስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመንም፣ ልክ እንደ ማርክሲስታዊው የስልጣኔ ዘመናችንም ሁሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊው የስልጣኔ ዘመን ለሰብኣዊ ልማት ምንም ትኩረት ያልሰጠ፣ ትምህርት ከጥራት ይልቅ በቁጥር የተመዘነበት እና በአስተዳደሩ ርዕዮተ ዓለም አስፈጻሚነት የተከረከመ ትውልድ ከማፍራት በላይ ያልተጋ ዘመን ነው ለማለት የሚያስደፍር ትውልድ ተፈጥሯል፡፡

በየዘመናቱ የከፋፈልናቸውን የስልጣኔ መስመሮችን ተከትለን ስንመለከት፥ ለሰብኣዊ ሀብት ልማት (ዕድገት) ትኩረት የሰጠው የድኅረ ጣልያን ኃይለሥላሴ ዘመን ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሁን ያለንበት ዘመን “የሕዳሴው ዘመን” እየተባለ በአስተዳደሩ እየተጠራ ነው፡፡ እውነት ሕዳሴ ማለት የግንብ ብቻ ነው?

የእነርሱ ሕዳሴ

የኢትዮጵያ መንግሥት “ሕዳሴ” የሚለውን ቃል የኮረጀው ከአውሮፓጳውያን “Renaissance” ይመስላል፡፡ ሬኔሳንስ በፍሎረንስ፣ ጣልያን ተጀምሮ በመላው አውሮጳ መስፋፋት የቻለ እና ከ14ኛው እስከ 17ኛው ክፍለዘመን የዘለቀ “የባሕል እንቅስቃሴ” ወይም የባሕል አብዮት ነው፡፡

የእነርሱ ሬኔሳንስ በመካከለኛው ዘመን እና በአሁኑ ዘመን መካከል የስልጣኔ ሽግግር ድልድይ በመሆን አገልግሏል፡፡ የዚህ ሬኔሳንስ ዋነኛው መሠረቱ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ፍልስፍና፣ ሥነ ስዕል፣ ሥነ ፖለቲካ እና ሌሎችም ላይ የዘመናዊነት መልክ ለማላበስ የተካሔዱት ክርክሮች የአስተሳሰብ አብዮቶች በማፍለቅ አውሮጳውያንን ግንባር ቀደም የስልጣኔ ቀዳጅ አድርጓቸዋል፡፡

የእኛ “ሕዳሴ” ግን በቀለበት መንገዶች እና በ“ሰማይ ጠቀስ” ሕንጻዎች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የቀለበት መንገዱን አጠቃቀም እና የሕንጻዎቹን አጠቃቀም እንኳን በአግባቡ የማያውቅ እና ቢያውቅም የማያከብር ብዙሐን አፍርቷል፡፡ የትምህርት ፖሊሲውም በበኩሉ ብዙሐኑን ተከራክሮ የሚያሳምን የሐሳብ ሊቅ ሊፈጥር ቀርቶ የሥራ ማመልከቻ በተስተካከለ ሰዋሰው መጻፍ የማይችል የዲግሪ ምሩቅ እያፈራ ነው፣ ሚዲያው እንኳን ሊያስተምር እና አርኣያ ሊያኖር ወይም ሊያቀርብ ቀርቶ “ወሮ በሎች” ልላቸው የምፈቅደው ሰዎች መናኸሪያ ሆኗል፡፡

አሁን ያለንበትን ዘመን ስንታዘበው፥ አንድም አያቶቻችን ባኖሩልን የኩሩነት፣ የጨዋነት እና የሥነ ምግባር መመሪያ ሳንታነፅ አሊያም ሉላዊነት (globalization) ዘልቆን ከሰለጠኑት ዓለማት እኩል በሐሳብ ሳንራመድ - እንዲሁ የባከንን ትውልድ ሆነን መቅረታችን ያሳስበኛል፡፡ የዚህ ብክነት መፍትሔው - መማር እና ማንበብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እንደ ትውልድ የትምህርት ዕድሉንም ሆነ እውነተኛ ለውጥ አጎናፃፊ ትምህርት ወይም የሚለውጥ ንባብም ሆነ ማንበቢያ በማጣት እየተሰቃየን እንደሆነ ሳስብ ደግሞ ስለራሳችን አዝናለሁ፡፡

1 comment:

 1. I like your style, language, depth and simplicity very much. Thank you for this inspirational piece, brother.
  Best,
  Girma D.

  ReplyDelete