Saturday, October 6, 2012

የመለስ ሞት ለምክር ቤቱ ምኑ ነው?የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀ የፊታችን ህዳር 29 ዓ.ም 17ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከብራል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ካየቻቸው ቀዳሚ ሕገ መንግስቶች በተሻለ መጠን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚቸረው እና የሀገሪቱ የበላይ ሕግ፤ ከያዛቸው አንቀፆች መካከል የመንግስቱን አይነት የሚደነግገው ክፍል በአንቀፅ 45 ላይ ምክር ቤታዊ ዲሞክራሲ (Parliamentarian Democracy) እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ አያይዞም የተዘረጋው ስርዓት ፌደራላዊ እንደሆነና፤ ይሄም አወቃቀር በ9 ክልሎች እና በአንድ ፌደራል / ማዕከላዊ መንግስት የተደለደለ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

እንዲሁም የፌደራሉ ምክርቤት ሁለት የተለያዩ አካላትን ያቀፈ እንደሆነ ገልፆ፤ እነዚህም አካላት ዋነኛ ተግባሩ ሕግ ማውጣት የሆነውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ዋነኛ ተግባሩ ሕገ መንግስቱን መተርጎም የሆነውን የፌደሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡

በማስከተልም ከሁለቱ የፈደራሉ ምክር ቤቶች አንዱ የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹…የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ነው›› በማለት የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ 2 ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሰረት የፊታችን ሰኞ መስከረም 28/2004 ዓ.ም የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀ ወዲህ ለ4ኛ ጊዜ የተመረጠው ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን ይጀምራል ማለት ነው፡፡

አሁን ሥራ የሚጀምረው ምክር ቤት ከቀዳሚዎቹ ምክር ቤቶች የሚለየው ባለፉት 4 ምክር ቤቶች አባል የነበሩት እና በምክር ቤቱም ጉልህ ሚና የነበራቸውን  የቀድሞውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሳያካትት መከፈቱ ይሆናል፡፡ መለስ ለምክር ቤቱ፣ ምክር ቤቱ ለአቶ መለስ ምን እና ምን ነበሩ?

ምክር ቤቱ ያለ መለስ፤  ምን ሆነ?

በኢፌድሪ ሕገ መንግስት መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሉበት ዋነኛ ግዴታዎች መካከል ‹‹ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግስት ሰለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት ዕቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖርት ማቅረብ›› አንዱ ነው፡፡ አቶ መለስም በ17 ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው (የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀበት ጊዜ ወዲህ) ይሄን ተግባር ሲያከናውኑ ነበር፡፡ ነገር ግን የጤናቸው ሁኔታ ጥሩ አይደለም ተብሎ ከአደባባይ ከጠፉበት ካለፈው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ህልፈታቸው በመንግስት እስከ ተነገረበት የነሃሴ ወር አጋማሽ ድረስ ከዚህ ተግባራቸው ርቀው ነበር፡፡ 

በዚህም መሰረት በሕገ መንግስቱ የተቀመጠው እና አስገዳጅ የሆነው የምክር ቤቱ የስራ ማጠናቀቂያ  ሰኔ ሰላሳ ሊከበር አልቻለም ነበር (የእንግሊዘኛው የሕገ መንግስቱ ቅጅ አንቀፅ 58 ንዑስ ቁጥር 2 The annual session of the House shall … end on the 30th day of the Ethiopian month of Sene በማለት አስገዳጅ እንደሆነ ይነግረናል)፡፡ ምንም እንኳን ምክር ቤቱ የሥራ ጊዜየን ያራዘምኩት ከእርሳቸው መታመም ጋር በተያያዘ አይደለም ቢልም፡፡ አቶ መለስ የሌሉበት ምክር ቤት የምክር ቤቱን የሥራ ዘመን ማጠናቀቂያ ሕገ መንግስቱ ካስቀመጠው ቀን በላይ በማራዘም፤ የሕገ መንግስት ጥሰት ፈፅሟል ይላሉ የቀድሞው የኢትዩጵያ ፕሬዘደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፡፡ 

ሌላው ምክር ቤቱ ያለ መለስ ምን የተለየ ነገር አደረገ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኝው በምክር ቤቱ የ17 ዓመት ታሪክ ውስጥ የአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ሁለት ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ሁለቱንም ጊዜ ባሳለፍናቸው ሶስት ወራት ውስጥ ነው ያካሄደው፡፡ የመጀመሪያው የቴሌኮምንኬሽን አዋጁን ለማፅደቅ፣ በሀምሌ ወር 2004 ዓ.ም አጋማሽ ሲሆን፤ ሁለተኛውን ደግሞ መስከረም 11/2005 ዓ.ም የአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ለማፅደቅ ነበር፡፡ ይሄም ምክር ቤቱ ከመለስ በኋላ ምነው አስቸኮለው? እንድንል ይጋብዘናል፡፡

Economics 101ን ማን ያስተምራል?

አቶ መለስ ዜናዊ በሞት በመለየታቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ብቻ ሳይሆን አስረክበው ያለፉት፤ የምክር ቤቱን የመሪነት ሚናም ነው፡፡ መለስ በምክር ቤት ውስጥ በምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ አብዝተው ተከራካሪ እና ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሰጭ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በተለይም በሶስተኛው ሀገር ዓቀፍ ምርጫ የተቃዋሚዎች ቁጥር በእጅጉ ከፍ ማለቱን ተከትሎ፤ መለስም የሚጠየቁት ጥያቄ እና ፈተናቸው በዛው ልክ ከፍ ብሎ ነበር፡፡ 

በሀገሪቱ የኑሮ ውድነት አሳሳቢ እየሆነ ነው፣ የዋጋ ግሽበትም ጣሪያ ነክቷል መንግስትዎ ምን ሊያደርግ አስቧል? ተብለው ሲጠየቁ፡፡ ማብራሪያቸውን የሰዋሰው ግድፈት በማረም ‹‹Fiscal እንጅ Physical አይደለም›› በማለት ይጀምሩ ነበር ኢኮኖሚስቱ መለስ፤ ለትዝብት በሚዳርግ መልኩ፡፡ አስከትለውም አዳም ስሚዝን ምክር ቤት ውስጥ እንደ እማኝ በመጥራት ‹‹የነፃ ገበያ መርሆዎችን አልጣስንም፣ ስሚዝንም አላስከፋንም፣ የኢትዮጵያ ገበሬም ስሚዝን አንብቦ ባያውቀውም በፖሊሲዎቻችን አስተዋውቀነዋል›› እያሉ ማስተማር ከዘወትር የምክር ቤት ተግባሮቻቸው አንዱ ነበር፡፡ 

ስለ ፍላጎት እና አቅርቦት ግንኙነት ትንታኔ በማቅረብ መንግስታቸው በኢኮኖሚው ላይ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ እንዳልሆነና ተጠያቂዎቹ ‘አለማቀፍ ህብረተሰብ’፣ እንዲሁም ‘የመንግስት ሌቦች’ ናቸው እስከማለትም ይደርሳል የመለስ የምጣኔ ሀብት ምክር ቤታዊ ገለፃቸው፡፡

ስለ ምጣኔ ሀብት በምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ ከማብዛታቸው የተነሳ፤ ማብራሪያቸውን በቴሌዚዥን በቀጥታ የሚመለከተው ህዝብ በቅርቡ በኢኮኖሚክስ ዲፕሎማ ወይም የምስክር ወረቀት ማግኝቱ አይቀርም ተብሎ ይቀለድም ተጀምሮ ነበር፡፡ 

እንግዲህ መለስ ከዚህ በኋላ ኢኮኖሚክስ በምክር ቤት ያስተምሩ ዘንድ የህይወት ህግ አልፈቀደም፡፡ አዲሱ ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የአቶ መለስን ቦታ ተክተዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም የመለስን የምክር ቤት ትምህርት ይቀጥሉበታል (አላማየ የመለስን ውርስ ማስቀጠል ነው ማለታቸውን ልብ ይሏል) ወይስ አይቀጥሉበትም?  የሚለው በጊዜ ሂደት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡

በፓርላማው ብቸኛ ተቆጭ

አቶ መለስ በምክር ቤቱ ተገኙ ማለት ምክር ቤቱ ሞቅ ያለ ድባብ አለው፣ ማለትም ሌላው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ መለስ በምክር ቤት ሲገኙ ‘ከተቃዋሚ ፓርቲዎች’ እስከ ‘ተራ ወንጀለኞች’፣ ‘ከአለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች’ እስከ ‘አለማቀፍ የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች’፣ ‘ከኢህአዴግ አባላት’ እስከ ‘መንግስት ሰራተኛው’ ድረስ መለስ የማይወርፉት አካል አልነበረም፡፡ 

‘ቆሻሻ’፣ ‘ያበዱ ውሾች’፣ ‘ኪራይ ሰብሳቢ’፣ ‘የመንግስት ሌባ’፣ ‘እነ ጭር ሲል አልወድሞች’ ወ.ዘ.ተ እያሉ የስድብ መአት የሚያዥጎደጉዱት መለስ፤ ማንንም አካል ከመገላመጥ አይመለሱም ነበር፡፡ ይሄም አንዳንዶች የሰውየውን ስብእና በመጥፎ መልኩ እንዲመለከቷቸው አድርጓቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ የአመራር አባል እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክር ቤት አባል የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹አቶ መለስን እንዴት ያስታውሷቸዋል?›› ተብለው በአውስትራሊያው SBS ራዲዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመለስሱ ‹‹አቶ መለስን የማስታውሳቸው በፓርላማው ውስጥ ብቸኛው ተቆጭ እንደነበሩ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የመለስ የምክር ቤት ቆይታ ውርስ ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም በምክር ቤት እንዴት ይሆናሉ? ጊዜ ጌታ ነው መልሱ፡፡

‹‹ሳቃቸው መች ያስተኛል››

መለስን በምክርቤት የዋሉ እለት ምክር ቤቱ ከፍጥጫም ባለፈ ሳቅ እና ተረት ልማዱ ነበር፡፡ ከኤዞፕ እስከ አለቃ ገብረ ሀና ተረቶች በመለስ እያነሱ የምክር ቤት አባላትን ሲያስፈግጉ ነበር የሚውሉት፤ መለስ፡፡ በየመሃሉ የሚጥሏቸውም ቃላት ከማስከፋት አልፈው አንዳንዴ ፈገግም ያሰኛሉ፡፡ ባጭሩ መለስ በምክር ቤት የተገኙ እለት የምክር ቤት አባላት ሳቂታዎች ነበሩ፡፡ 

በምክር ቤቱ እንቅልፋቸውን በመተኛት ታዋቂ የነበሩ አንድ የምክር ቤት አባል ‹‹ምንድነው; ምክርቤት የገቡት ለመተኛት ነው እንዴ›› ተብለው ሲጠየቁ፡፡ ‹‹ኢጭ እንተኛስ ብንል ሳቃቸው መች ያስተኛል›› አሉ ተብሎ እስከ መቀለድም ተደርሷል፡፡ አቶ ሃይለማርያም እኒህን ‘እንቅልፋም’ አባል ከእንቅልፍ እየቀሰቀሱ ያማርሯቸዋል ወይስ ‘በሰላም እንዲተኙ’ ይፈቅዱላቸዋል? ጊዜን ማየት መልካም ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment