Saturday, April 27, 2013

“የተዘነጉት እስረኞች” እና የተዘነጋው የቤተሰቦቻቸው ስቃይ


ላለፉት አራት ዓመታት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቅዳሜ እና እሁድ የሄደ ሰው ወጣቷን ናርዶስን ሳያገኝ አይመለስም፡፡ ናርዶስ ገና የ20 ዓመት ወጣት እና በኪያሜድ የመጀመሪያ ዓመት የነርሲንግ ተማሪ ናት፡፡ ናርዶስ ዘሪሁን በየሳምንቱ  ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የምትመላለሰው በ‹‹አሸባሪነት›› ‹በእነብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ› ከተከሰሱት 36 ሰዎች መካከል ዕድሜ ልክ የተፈረደባትን እናቷን ልትጎበኝ ነው፡፡ እነዚህ እስረኞች ሚያዝያ 16/2001 አመሻሹ 12 ሰዓት አካባቢ ነበር ሁሉም በያሉበት በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡ እኛም 4ኛ ዓመታቸውን ለማሰብ ተሰባስበን ወደቃሊቲ ማረሚያ ቤት በተለይ እማዋይሽ ዓለሙን ለመጠየቅ ሄደን ነበር፡፡ እንደተለመደው ናርዶስንም አገኘናት እና ብዙ ነገሮችን አጫወተችን፡፡

ናርዶስ ትረካዋን  የጀመረችው እናቷን እና ሌሎችም በተመሳሳይ መዝገብ ተከሰው የተፈረደባቸውን ሰዎች አያያዝ ነበር፡፡ ‹‹ሳስበው የተረሱ ያህል እየተሰማኝ ነው፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሚዲያዎች ስለነሱ አይደለም እያነሱ ያሉት፡፡ በእናቴ ክስ የታሰሩት ከ30 ሰዎች በላይ ናቸው፡፡ አንድ ሰሞን ከይቅርታ ጋር በተያያዘ ስማቸው እየተነሳ ነበር አሁን ግን ሁሉ ነገር የተረሳ ይመስለኛል›› በማለት የእስሩ ሕመም ለታሳሪዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ግን የሚረሳ ዓይነት አለመሆኑን ነገረችን፡፡

‹‹ሚያዝያ 16፣ አርብ ቀን ነበር ሁሉም የተያዙት›› በማለት ሲታሰሩ የነበረውን ጠቅላላ ሁኔታ በማስታወስ ትጀምራለች፡፡ ‹‹ለአንድ ሰው የመጡ የማይመስሉ ብዙ ሲቪል የለበሱ እና የፌዴራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች መሳሪያቸውን አቀባብለው ነበር ወደቤት የገቡት፡፡ ስልካችሁን አጥፉ ወደማንም እንዳትደውሉ አሉን፡፡ የብርበራ ማዘዣ ይዘው ነበር፤ ‹ቤት ልንፈትሽ ነው የመጣነው እማዋይሽ ዓለሙ በቁጥጥር ስር ውለሻል› አሏት ቤት ፍተሻው እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ቀጥሏል፡፡ ቀኑ አርብ ነበር፤ እናቴ ደግሞ እስከ 12 ሰዓት ትጾም ስለነበር ከሥራ ወደቤት እንደገባች ‹ምግብ ስጡኝ› እያለች እያለ ነበር ፖሊሶች የገቡት ስለዚህ ምግብ ሳትበላ ውላ ነው ወደ እስር ቤት የወሰዷት፡፡ ከዚያ በኋላ አራት ወራት ያክል ዓይኗን አላየነውም ነበር፤ ትሙት ትኑር የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡  ደግነቱ በሌላ ጉዳይ ታስራ በተፈታች ሴት አማካይነት መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ‹አንቺ ደህና ከሆንሽ ሽሮ እና ጎመን ሰርተሸ አስገቢልኝ፤ እኔ ደግሞ ደኅንነቴነን የባናና ማስቲካ ወረቀት እልክልሻለሁ፡፡ ደኅና ካልሆንኩኝ ግን ያ ነገር ይቀራል› ብላ ላከችብኝ፡፡ ከዚያ እኔም ሽሮ እና ጎመን ሠርቼ በመላክ፣ እሷም የባናና ወረቀት በመላክ ደኅንነታችንን የሚገልፅ መልዕክት እንለዋወጥ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ሰዓት እኛ በሌለንበት ጉዳያቸው ፍርድቤት ይታይ ነበር፡፡›› በማለት ጉዳያቸው በኢፍትሐዊ መንገድ በመንግሥት እንደተያዘ አጫውታናለች፡፡

Friday, April 26, 2013

#Ethiopia: የስደተኛው ማስታወሻ ከአውሮፓ


(ክፍል ፪)

ናፍቆት

እስክትመጪ ያልኩሽ ስትመጪ ከምትደናገሪ ቀድመሽ እንድትዘጋጂ ብዬ ነው፡፡አንቺ ብቻ ሳትሆኚ ማንም ለመሰደድ የሚቋምጥ ሁሉ እስኪሰደድ የስደትን እውነተኛ ገፅታ ይወቅ ለማለት ነው! እስኪመጣ ይወቅ! እስክትመጣ ትወቅ! እስኪመጡ ይወቁ! ስለ አውሮፓ አእምሯችሁ የሚነግራችሁ ወሬ ውሸት ነው።ስለአውሮፓ ሰዎች የሚነግሯችሁ ሃሰት ነው። አትመኗቸው፤ እወቁና ራሳችሁ  ፍረዱ፤ እወቁና ተዘጋጅታችሁ ወደ አውሮፓ ለማለትም ጭምር ነው፡፡

ከአገርሽ እንደወጣሽ ብዙ ፈተና ይጠብቅሻል። አንዱ ፈተና ናፍቆት ነው። የማይናፍቅሽ ነገር የለም፤ አንተ ብቻ ነህ የምትናፍቀኝ አንተን ካገኘሁ ምንም አይናፍቀኝም የምትይውን አነጋገርሽን የምታፍሪበት እዚህ መጥተሽ ያቺ ለማየት የምተፀየፊያት ሽሮ ከሁሉ በላይ ስታሳሳሽ ነው። አምርረሽ የጠላሽው ወይም እጅግ የሰለቸሽ ሁሉ እየፀፀተሽ ይናፍቅሽ ይጀምራል። የምትወጃቸውንማ ማናገር እስኪያቅትሽ ድረስ ሲቃውን አትችይውም። ቤተሰብሽን፣ ጓደኞችሽን ስታናግሪ ያኔ እኔን ከተለያየን ከሶስት ሳምንት በኋላ ስደውልልሽ እንደሆንሽው ትሆኛለሽ። ናፍቆት አንደበትሽን ይሸብበዋል፣ ናፍቆት ቃልሽን ያጠፋዋል፣ ናፍቆት አልቃሻ ያደርግሻል። ስለዚህ መለስ ቀለስ የምትይበትን የስደት መንገድ መምረጥ ይኖርብሻል።

እኔን ናፍቆት እንዴት እንዴት እንዳረገኝ ልንገርሽ፦ እንደገባሁ ትውልደ ፓኪስታን ከሆነ አንድ ጎልማሳ ላይ የተከራየኋት ጠበብ ያለች ቤት ነበረችኝ። ረከስ ያለችውን መርጬ ነበር የተከራየሁት። ሳሎን እና ኩሽና የጋራ ሲሆን መኝታ ቤት እና ሽንት ቤት የግል ነበር። ከዚህች ቤቴ በተቃራኒው የከተማው ክፍል የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ ለመድረስ ከአንድ ሰአት በላይ እጓዝ ነበር።

ጉዞው ረጅም ቢሆንም ለውጪው ዓለም አዲስ በመሆኔ ምክንያት በየመንገዱ የማየው ትዕይንት የጉዞውን ርዝመት እንዳይታወቀኝ አድርጎኝ ነበር። ሁሉም ነገር ይገርመኝ ስለነበር አንዱን አይቼ ሳልጨርስ ሌላው እየተተካ እንዲችው እየተቁለጨለጭኩ ነበር የምመላለሰው። ጠዋት ጠዋት በምድር ውስጥ ባቡር ላይ ተጠቅጥቀውና ተኮራርፈው ከሚጓዙት ፈረንጆች ውስጥ ጋዜጣ የማያነብ ሰው ማግኘት ይከብዳል። ይህን ሳይ ባቡሩንም፣ አንባቢውንም፣ ጋዜጣውንም እመኛለሁ። አገሬ ላይ እንዲህ አይነት ትዕይንት መቼ ይሆን የማየው እያልኩ። ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደ ልደታ በምድር ውስጥ ባቡር እየሄድኩ እለታዊዋን አዲስ ነገር ጋዜጣን እያነበብኩ ብጓዝ፤ ማይጨው አደባባይ ወርጄ መስመር ስቀይር ከባቡሩ ጉርጓድ መውጫ በር ላይ እንደ ስሙ የዘመነውን አዲስ ዘመንን ገዝቼ ወደ ልደታ ለመሄድ ስሸጋገር እያልኩ እመኝ ነበር። (ይህን እየተመኘሁ ትምህርት ቤት ደርሼ ኢሜሌን ስከፍት አንዱ ወዳጄ አንድ መልዕክት አስቀምጦልኝ አገኘሁ። የሰላም ያርገው ብዬ ብከፍተው ‘ዘጓት’ ይላል፤ የምድር ውስጥ ባቡሩን ብንሰራው እንኳ ጋዜጣውን ርሳው ማለቱ ነበር።)

#Ethiopia: የአበሻው ማስታወሻ ከአውሮፓ


(ክፍል፩)

እነዚህ የግል ማስታወሻዎች ናቸው፡፡ለግለሰብ የተጻፉ፡፡ተወዳጅ ባይሆኑም እንኳን አንዳንድ የስደተኛ ታሪኮች አያጡም፡፡ከስደት ጅማሬየአንስቶ እስከ ገጠመኞቼ ድረስ ያለውን በተከታታይ ላጫውታሁ እሞክራለሁ፡፡፡ሲጀመር

‘ትልቁን ነው መያዝ ያለብህ!’ ቁጣ ባዘለ ድምፀት ተናገረች።

‘ትንሿንም የምይዘው ይሁንልሽ ብዬ ነው’ አልኳት ረጋ ብዬ።

‘ታዲያ የቱን ልትተው የቱን ልትይዝ ነው? ይሄም፣ ይሄም፣ ያም፣ያም ሁሉም ይጠቅምሃል’ አለች ወደ ልብሶቹ፣ መፅሃፎቹ፣ ስጦታዎቿና እህቷ ለመንገደኛ ብላ ወዳዘጋጀችው ስንቅ ተራ በተራ እያመለከተች።

‘አንቺና እህትሽ በሎንችና የሚሰደድ ሰው አይታችሁ ስለማታውቁ አልፈርድባችሁም ግን ሁሉንም አልይዝም፣ ልያዝም ብል መያዝ አልችልም’ አልኳትና የምይዛቸውን ጥቂት ልብሶች በሃሳቤ መምረጥ ጀመርኩ።

 ‘መኪና አይደል እንዴ የሚሸከመው? ካልሆነልህም መንገድ ላይ ብትጥለው ይሻላል’አለች በእንባ በተጋረዱ አይኖቿ እያየችኝ።

‘መኪኖቹ ስለሚፈጥኑ ከሰው ውጪ ከባድ ነገር መጫን አይፈልጉም’ በየመንገዱ ችግር ሲከሰት አይደለም እቃ ሰው እያወረዱ እንደሚጥሉ ብነግራት የባሰ ሃሳብ ውስጥ እከታታለሁ ብዬ ስለሰጋሁ  ነበር እንዲህ ያልኳት።

Tuesday, April 9, 2013

#Ethiopia: የአለም ዋንጫው ለኢትዮጵያ ምኗ ነው?


በጌታቸው ሺፈራው

በአሁኑ ወቅት የአገራችን ወጣት  ትኩረት የሚሰጠው ነገር እግር ኳስ ሆኗል፡፡  ወጣቱ ለእግር ኳስ ብቻ የሚሰጠውን ትኩረትም አንዳንዶቹ የስርዓቱ ወጣቱን የማደንዘዣ ስልት ውጤታማነት ማረጋገጫ አድርገው ይወስዱታል፡፡ በአገራችን በአሁኑ ወቅት ከማይታገዱት የውጭ ጣቢያዎች መካከል የቀሩት የእግር ኳስ ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም አሁን አሁን ሥርዓቱ ‹‹ያመነው ፈረስ›› አደጋ ላይ እየጣለው ይመስላል፡፡  ለይስሙላህም ሰንደቅ ዓላማ መከበር ሳይጀምርና ካድሬዎች ሰንደቅ ዓላማ ሲያዩ ይደነግጡ በነበረበት ወቅት  ጀምሮ  ወጣቱ ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ የሚገኘው አዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ብዙዎቹ ሥርዓቱ የማይፈልገው ‹‹የአገር ፍቅር ያለው አዲስ አበባ ስታዲም ብቻ ነው›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡ 

የአፍሪካ ዋንጫውና የኢትዮጵያውያን  

ኢትዮጵያውያን ለሶስት ዐሥርት ዓመታት ተለይተውት የቆዩትን የአፍሪካ ዋንጫ በተቀላቀሉበት በዚህ አመት ኳስ ወጣቱ ደነዘዘበት ከሚባለው ‹‹እግር ኳስ›› በላይ  ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ የብሔራዊ ቡድናችን ተሳትፎ ኢትዮጵያን በርሃብ ለሚያውቋት አፍሪካዊያንና የዓለም ሕዝብ አዲስ የአጨዋወት ዘይቤ፣ የደጋፊ ስሜትና ድምቀት እንዲሁም ሊረሳ ተቃርቦ የነበረውን ሰንደቃችን አሳይተዋል፡፡ ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያም በደቡብ አፍሪካ የተገኙት ደጋፊዎቻችን ድምፃቸውን ለማሰማት ሞክረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ድምፃችን ታፍኗል ያሉትም ሆነ የአገራችን ፖለቲካ ምኅዳር ተጠርቅሞባቸው በጥገኝነት የሚገኙት ተቃዋሚዎች  ብሔራዊ ቡድናችንን ከመደገፍ ባሻገር ለጊዜው መንግሥት ሊዘጋው ባልፈለገው ዲ ኤስ ቲቪ በኩል የኢትዮጵያውያንን ድምፃቸው ሳይታቀብ አሰምተዋል፡፡ መንግሥት ብሔራዊ ቡድናችን  የአቶ መለስን ቲሸርት ለብሶ  የአፍሪካን ዋንጫ ለአቶ መለስ መታሰቢያ ያደርገዋል  በሚል ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም የእነማንዴላዋ አገር ላይ ከካድሬነት ይልቅ ነጻነትን  ከደጋፊዎቻቸው የተማሩት ተጫዋጮቻችን  የደቡብ አፍሪካ ሜዳ በእብይተኝነታቸው አሸንፈው ተመልሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ብሔራዊ ቡድናችን በመጀመሪያዋ ጨዋታ ነጥብ አስጥሎ ይዟት የወጣውን የባለፈው ዓመትን ሻምፒዎን ዛምቢያ ያልተናነሰ ሽንፈት ደርሶበታል ለማለት ይቻላል፡፡

የአለም ዋንጫውስ?

ጥቋቁሮቹ አናብስቶች በአፍሪካ የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ ያላትና የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫን ያስተናገደችውን ደቡብ አፍሪካን በአገሯ ነጥብ አስጥሎ፣ ቦትስዋናንና ማዕከላዊ አፍሪካን አሸንፎ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያውን  በሁለት ነጥብ ልዩነት እየመራው ነው፡፡ በዚህ አካሄዱ ወደ ብራዚል  የሚጓዝበትን አጋጣሚ እያሰፋ ነው፡፡ ይህ ከመሠረትነው፣ አንዴ ዋንጫውን አንስተን ስንሳተፍበት ከቆየነው የአፍሪካ ዋንጫ በእጅጉ የተለየ መድረክ ነው፡፡ ይህ 20ኛው  የዓለም ዋንጫ 2006 ዓ/ም ከሰኔ መጨረሻ እስከ ሐምሌ መጀመሪያ  በብራዚል ይካሄዳል፡፡ የዓለም ዋንጫው ኢሕአዴግ 100% (ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል) ለማሸነፍ ከሚፈልገው የ2007 ምርጫ የሚቀድመው ለወራት ያህል ብቻ ነው፡፡ 

ብዙ ሳይታሰብበትም ቢሆን በአፍሪካ ዋንጫ የተቃዋሚዎቻችን ድምፅ፣ የሕዝባችንና የእግርኳሳችን ውበት፣ የደጋፊዎቻችን ድምቀት  ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም አስገራሚና የማይረሳ ትዕይንትና ትዝታ ሆኖ አልፏል፡፡  የዓለም ዋናጫ ዐሥራ አምስት ያህል ወራት ይቀሩታል፡፡ በአፍሪካው ዋንጫ ብዙም ሳያስቡበት ያን ያህል ድምፅ ማሰማት የቻሉት ተቃዋሚዎቻችንና ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዓለም ዋንጫ  ከዚህ የተሻለ ዝግጅት አድርገው ሊጠባበቁት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ከምንም በላይ ብራዚል ድምፃቸውን ለሚያሰሙት ኢትዮጵያውያን አመች ትመስላለች፡፡ አፍሪካ ውስጥ ከሚኖረውን ወደደቡብ አፍሪካ ካቀናው   ዲያስፖራ ይልቅ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የአገራችን ሕዝብ ወደ ኳሷ አገር ብራዚል ለማቅናት ይቀናዋል፡፡ ዲያስፖራው እስካሁን ገንዘብ ለማሰባሰብ ወይንም ለስብሰባ ተወካዮቹን በእየአህጉሩ ሲልክ ከነበረው በተቃራኒ ራሱ አገሩን ወክሎ ወደ ብራዚል ለመሄድ  የሚያስችለውን ዕድል ብራዚል አዘጋጅታለታለች፡፡  የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ ዋንጫም በላይ ለማየት የሚያጓጓ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካ ዋንጫ የተሻለ እንዲመርጡት ያደርጋል፡፡ በዚህ መድረክም ኦባንግ ሜቶ ወይንም ታማኝ በየነን ሳይጠብቁ ኢትዮጵያውያን  ከደቡብ አፍሪካዎቹ ደጋፊዎቻችን የተማሩትም እና ጊዜ ገዝተው ያጠናከሩትን ሰላማዊ የትግል ስልት ለዓለም ሕዝብ እንደሚያቀርቡ የሚያጠራጠር አይሆንም፡፡ 

Monday, April 8, 2013

#Kenya፤ ከነጻነት እስከ ነጻ ምርጫ (#Ethiopia)



ጎረቤት ሀገር ኬንያ እ.አ.አ በ1963 ዓ.ም ነበር ከእንግሊዝ ቀኝ አገዛዝ ነፃ የሆነችው፡፡ በቀጣዩ ዓመት ኬንያ ራስዋን የቻለች ሪፐብሊክ ሆና ስትቋቋም የነፃነት ትግሉን እና የኬንያ አፍሪካ ብሔራዊ ኅብረትን (ካኑ) ይመሩ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ* (የአሁኑ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አባት) የኬንያ የመጀመርያ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ ምክትላቸው ደግሞ የአሁኑ ተሰናባች ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ አባት ኦጊንጋ ኦዲንጋ** ነበሩ፡፡
ኦዲንጋ የኬንያ የመጀመርያ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር ያገለገሉት፡፡ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው የኬንያ ሕዝቦች ሕብረት የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም የኬንያታን ሥልጣን መገዳደር ጀመሩ፡፡ ጆሞ ኬንያታ ለነፃነት ትግል አጋራቸው ብዙም ክፍተት መስጠት አልፈለጉም፡፡ በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እያደገ ሂዶ እ.አ.አ በ1969 ዓ.ም. በኪሲሙ ግዛት ሕዝብ በተሰበሰበበት የተከሰተ የሁለቱ መሪዎች ‹እንኪያ ሰላምታ›ን ታክኮ በተፈጠረ ሁከት ሰዎች ከሞቱና ከቆሰሉ በኋላ ኦጊንጋ ኦዲንጋ ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት በእስር እንዲያሳልፉ ተገደዱ፡፡
 
እ.አ.አ በ1978 እስኪሞቱ ድረስ ኬንያን ለመምራት የምዕራባውያኑን ድጋፍ ያገኙት ኬንያታ ፊታቸውን ወደ ምስራቅ ያዞሩት ኦዲንጋ ላይ ሙሉ የፖለቲካ እና የሥልጣን የበላይነት ወስደው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከኩኩዩ ቤተሰብ የሆኑት ኬንያታ የ14 ዓመት ሥልጣናቸውን በሞት ሲነጠቁ የተኳቸው ከካለነጂን ጎሳ የሆኑት ዳንኤል አራፍ ሞይ ይሁኑ እንጂ በሕይወት ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ግን ቤተሰባቸውን በሀብት አንበሻብሸዋል እንዲሁም የኩኩዩ ጎሳን የቁጥር የበላይነት ወደ መንግሥት ተቋማት ሥልጣን የበላይነትም አምጥተዋል ተብለው ይከሰሳሉ፡፡

ሥልጣን በእጃቸው የወደቀላቸው ሞይ ቀስ በቀስ ኬንያታ ሲገነቡ የቆዩትን ሥልጣንን በብቸኝነት መቆጣጠርን እና ተቃዎሚዎቻቸውን የማፈን ልምድ እያዳበሩ ሄደው እ.አ.አ 1982 ኬንያ በአሀዳዊ ፓርቲ (ካኑ) የምትተዳደር ሀገር እንደሆነች በይፋ አሳወጁ፡፡

የሞይ የሥልጣን ዘመን ለኬንያውያን ከቀኝ ግዛት በኋላ የነበረ አስከፊ ወቅት ነበር፡፡ ዜጎች ስለራሳቸው ሀገር መረጃ ለማግኘት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በነበሩትን መገናኛ ብዙኃን ላይ እምነት ስላልነበራቸው ዜናዎችን የሚያገኙት ከቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት እና የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮን ከመሰሉ ምንጮች ነበር፡፡ እ.አ.አ 1978 በተደረገ ምርጫ ሥልጣን የያዙት ሞይ እ.አ.አ በ1983 እና 1988 ሁለት ምርጫዎችን የራሳቸው ፓርቲ ካኑ ካቀረባቸው እጩዎች ጋር ተወዳድረው አሸንፈዋል፡፡ የ1988ቱ ምርጫ መራጮች ድምፅ የሰጡት በሚስጥር ሳይሆን ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተለየ ኮሮጆ ተዘጋጅቶ መራጮች ድምፃቸውን መስጠት ለሚፈልጉት ተወዳዳሪ የተለየ የተራ ሰልፍ ተሰልፈው ነበር፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ዜጋ ለማን ድምፁን መስጠት እንደሚፈልግ ገና ሰልፉን ሲመርጥ ይታወቃል ማለት ነበር፡፡

Monday, April 1, 2013

#Ethiopia: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም (ሁለት)


በዳዊት ተ. ዓለሙ*

ባለፈው ሳምንት በወጣው የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል የተቃዋሚ ፓርቲዎች የድርድር አቅም ዋና ዋና አላባዎች የተነሱ ሲሆን ተከታዩ እና የመጨረሻው ክፍል ተከትሎ ይቀርባል፡፡

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው የቅቡልነት ደረጃ

የተቀዋሚ ፓርቲዎች በማህበሰቡ ውስጥ የሚኖራቸው የቅቡልነት (legetimacy) ደረጃ ፋላጎቶችን የማስታረቅና የማህበረሰቡን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመንቀስ፣ የፖለቲካ አጀንዳ በመቅረጽና ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ላይ የተመሰረተ ነው:: በተለምዶ ፓለቲካ ፓርቲዎች በሚያራምዱት ርዕዮተ አለም ላይ ተመስርተው በሚነድፉት የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ የሚወክሉትን የማህበረሰብ ክፍል ፍላጎቶች ያንጸባርቃሉ:: በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን በብሔር ብሔርተኛነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደመብዛታቸው፣ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው የሚያንጸባርቁት ፍላጎቶች በአንድ የተወሰነ ብሔር ፍላጎት የተገደበና ማህበራዊ መሰረታቸውም እንወክለዋለን የሚሉት ብሔር አባላት ብቻ ናቸው:: ህብረ-ብሄራዊ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች በግልጽ ማህበራዊ መሰረታቸውን ያለዩና በፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው ያስቀመጡት ፍላጎቶች ሃሳባዊነት(utopia) የተላበሰና በሃገሪቱ ካሉ ከማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመነጩ አይደሉም::

ከላይ እንደተመለከተው በሰው ኃይል አመዳደባቸው፣ አደረጃጀትና አሰራራቸው የጥቅመኝነት ግንኙነት የሰፈነበት በመሆኑ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሃከል ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ሁሉም ፓርቲዎች የሚያንጸባርቁት ማህበራዊ መሰረቶቻቸው እየጠበበ ሂዶ በፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉትን ሙሁራንparty-based elites’ ሆኗል:: ስለዚህም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረቶቻቸው የጠበበ በመሆኑ ህልውናቸውን የማስጠበቅ ከፍተኛ ፈተና ተጋፍጠዋል፤ ተቋማዊ አቅማቸውን የሚያዳብሩበትን እድል አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፤ የተቃውሞው ፖለቲካ ካለበት  የችግር አዙሪኝ መላቀቅ አቅቶታል:: ይህም ያላቸውን የመደራደር አቅማቸውን እጅግ በጣም የወረደ እንዲሆን አድርጎታል::