በጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤
ከዝዋይ ማረሚያ ቤት
(ከኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ የተወሰደ)
‹‹ይህንን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች መወያየት ክልክል ነው፡፡›› በማለት በተንጎላጀጀ ድምፅ ጠባቂው
ተናገረ፡፡ ቀጠል አደረገናም ‹‹መነጋገር የምትችሉት ስለቤተሰብ ጉዳዮች ብቻ ነው›› በማለት ተናገረ፡፡ ይህን ከላይ ያለውን ሐሳብ
የሚመለከት ማንኛውም አንባቢ፣ ጉዳይ የተፈፀመው እዚህችው እማማ ኢትዮጵያ ሰማይ ስር ባሉ አጃኢበኛ እስር ቤቶች፣ ቤተሰብ መጠየቂያው
እንደሆነ መጣራቱ አይቀርም፡፡
ይሁንና በመግቢያው ላይ ያለው ጽሑፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ ‹እናት› ከተሰኘውና እ.ኤ.አ. በ1906
ከታተመው የስመ ጥሩው ሩስያዊ ደራሲ ማክሲም ጎርኪይ ታሪካዊ ልቦለድ ገፅ 102 ላይ ነው፡፡ የዛሬ 108 ዓመት አካባቢ ማለት ነው፡፡
አቤት ርቀቱ!... ይህ ርቀት ግን ለእኛ ምንም ማለት ያልሆነ ይመስላል፤ ለምን? ቢሉ ዛሬም ይህንንና ይህን የመሳሰለውን አስፍተን
እየሠራን እንገኛለን፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች እየተጓዝን ያለነው የቁልቁለት ሩጫ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል፡፡
የነገሮች ሁሉ መድረሻ እስር ቤቶች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ‹ጠበቅ ያለ እርምጃ፣ የማያዳግም እርምጃ፣
የማስወገድ እርምጃ፣…› ወዘተ የሞሉ ከሕግ መርሕዎች ሳይሆን ከጥላቻ ፖለቲካ የሚመነጩ ፀያፍ አነጋገሮችን በሕዝብ የመገናኛ ዘዴዎች
ሲተላለፉ እየሰማን እየታዘብን ነው፡፡ ቃል በቃል ‹ቀይ ሽብር ይፋፋም› ብሎ ማወጅ የቀራቸው የሕግም የግብረገብም ሚዛን ያልወጣላቸው
ቀረርቶች በተለይ በእስር ቤት የምንገኝ ኢትዮጵያውያንን እየሰበሰቡን ይገኛሉ፡፡
በኢ.ቴ.ቪ. የአብዮታዊ እርምጃ ፕሮግራሞች በቀረቡ ማግስት አሁን በዝርዝር ብለው የብዙ ቤተሰቦችን
ስሜት ሊያሸማቅቁ የሚችሉ ሰቆቃና እንግልቶች በአስደማሚ ስልት ተቀናብረው ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ እስኪ የተወሰኑትን እንይ፡፡ ማንኛውም
ታሳሪ ቤተሰብ በቅርብ ሊጎበኘው በሚችለው እስር ቤት ይታሰር የሚለው ሕግ የተሻረው በእኛ ላይ ነው፡፡ ዝዋይ የአገራችን ‹ሳይቤሪያ
ግዞት› ማለት ናት፡፡ ቤተሰብ ያን ያህል የበርሃ ጉዞ አቋርጦ የእኛዋ ሳይቤሪያ ሲደርስ በአድካሚና ግብረ-ገብ በጎደለው ፍተሻ መከራውን
ማየቱ አንሶ ጆሮ ግንዱ ላይ በቆሙ የቤተሰብ አገናኞች ቤተሰባዊ ገመናውን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ሕፃናት ልጆች ወላጆቻቸው አንድ ላይ
ሆነው ናፍቆታቸውን መወጣት አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶቹ ሲዘናጉልን ልጆቻችንን አቅፈን እንስማለን፡፡ ይህ ከሆነ ቁጣና ዘለፋው
ምንም አይደለም፡፡ ግን በሁኔታው ሕፃናቱ ክፉኛ ይበረግጋሉ፣ የእኛ ስጋት ይጋባባቸዋል፤ በዚህም መንፈሳቸው እርብሽብሽ ብሎ ወደቤታቸው
ይመለሳሉ፡፡