Tuesday, October 16, 2012

የታክሲ ሰልፍ መጀመሪያውና መጨረሻው



ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ወደቦሌ ለመሄድ አራት ኪሎ የተገኘ ሰው እጅግ ረዥም ሰልፍ ለመሰለፍ ይገደዳል (የጥቅምት 6/2005 ሰልፍን በፎቶው እና ቪዲዮው ይመልከቱ!) የቦሌ ታክሲ ለመጠቀበቅ ከተሰለፉት ሰዎች ፊት ለፊት ስምሪታቸው በፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደጉራራ የሆኑ ታክሲዎችም ተሰልፈው የሚቀድሟቸው ታክሲዎች እስኪሞሉ ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ ይህ የአዲስ አበባ ታክሲ የሰሞኑ አጀንዳ ነው፤ እንኳን ደህና መጣችሁ፡፡


የታክሲ ስምሪት ጉዳዮች

የታክሲ ስምሪቱ በ2004 መባቻ እንደወጣ የተደሰቱም የተበሳጩም ነበሩ፡፡ የስምሪቱ ጉዳይ ሁለት ዓመት ተጠንቶበታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ስድስት ያክል መስመሮች ስምሪት ሳይመደብላቸው መቅረታቸው የሚታወስ ክስተት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የታክሲ ስምሪቱ ወዲያው እንደተተገበረ የተዘበራረቁ ነገሮችን ለማስተካከል በሚል በሁለት ወር ውስጥ ማሻሻያዎች ወጥተው ተተግብረዋል፡፡

የታክሲ ስምሪቱ ክፍያን በልምድ ሳይሆን በኪሎ ሜትር እንዲሆን አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ማሻሻያው ደግሞ ታክሲዎች የተሰማሩበትን ቦታ ታሪፍ ፊትለፊት እንዲለጥፉ የሚያስገድድ ነበር፡፡ ሁሉም አልተተገበሩም፤ እንዲያውም አንዳንድ ተሳፋሪዎች ታሪፎቻቸውን (እስከ መደባደብ በሚደርስ ትግል) ለማስከበር ቢሞክሩም ቀስበቀስ ሁሉም ተስፋ እየቆረጠ ወደበፊቱ የልምድ አሠራር ተመልሷል፡፡ ሌላው እያቆራረጡ መጫን በስምሪቱ ወቅት የተከለከለ ቢሆንም አስፈጻሚ ባለመኖሩ እሱም በድሮው አሠራር ቀጥሏል፡፡

እነዚህ የስምሪቱ ቅጥያ አገልግሎቶች አልተተገበሩም፡፡ ለመሆኑ ስምሪቱስ ማምጣት የነበረበትን የትራንስፖርት እጥረት ቀርፏል፤ ወይም ለመቅረፍ የተወሰነ አስተዋፅዖ አድርጓል? - ጥያቄያችን ነው፡፡

ሲሳይ ፋንታዬ ለአምስት ዓመታት የታክሲ ሾፌር ሆኖ ሠርቷል፡፡ የታክሲ ስምሪት የታክሲ እጥረቱን አባብሶታል ብሎ ያምናል፡፡ ባነጋገርኩት ወቅት በምሳሌ የነገረኝ እንዲህ በሚል ነበር፤ ‹‹ታፔላ ቢኖርም ባይኖርም ለውጥ የለውም፤ እንዲያውም… ከቦሌ ተነስቼ ወደሜክሲኮ እሄዳለሁ እንበል፣ ሜክሲኮ ስደርስ ስምሪት ከሌለብኝ ወደጦር ኃይሎች ሊሄዱ የተሰበሰቡ ሰዎች ከገጠሙኝ እነርሱን እዚያ አደርሳለሁ፡፡ በዚህ መንገድ ሰው የበዛበትን ቦታ ያማከለ አሠራር መሥራት ይቻላል፡፡››

ሲሳይ የተናገረው እውነት ነበር፤ በፎቶው ላይ የሚታዩት እና ታክሲ ጥበቃ ከተሰለፉት ሰዎች ፊትለፊት የተሰለፉት ታክሲዎች በየጎደለበት አቅጣጫ ቢንቀሳቀሱ ኖሮ ይህ አይከሰትም ነበር፡፡ እነዚህ አራት ኪሎ ላይ የተሰለፉት ታክሲዎች በበፊቱ አሠራር ቢሆን አጭርም፣ ረዥምም እየጫኑ ፈረንሳይ ደርሰው እጅግ ተሰብስቦ የሚጠብቃቸውን ሰው ትንሽ መፍትሔ ይሰጡት ነበር፤ የስምሪት ጣጣ ባይኖርባቸው፡፡

የስምሪቱ ሌላው ችግር ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ መሆኑ ነው፡፡ የስምሪቱን አቅጣጫ የሚያወጡት የታክሲ ማኅበራቱ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የታክሲ ማኅበር የራሱ አቅጣጫ/ዞን ውስጥ ያሰማራል፡፡ ለምሳሌ ፀሐይ እና አዲስ ሕይወት ከሽሮሜዳ እስከ ሜክሲኮ፣ ከአራት ኪሎ በፈረንሳይ እስከ ጉራራ ድረስ አቅጣጫቸው ነው፡፡ ሆኖም እዚህ አቅጣጫ ላይ (እንደዕለታዊ ሁኔታዎች ሊለያይ ቢችልም) በጥቅሉ ከሽሮሜዳ እስከሜክሲኮ የሚሰማራ ታክሲ ከአራት ኪሎ ወደፈረንሳይ ከሚሰማራ ታክሲ ይልቅ ያተርፋል፤ ወይም ብዙ ገቢ ያገኛል፡፡

ስለዚህ ታክሲዎች የማኅበራቱ አስተባባሪዎችን በገንዘብ በመደለል የሚፈልጉት መስመር ላይ ብቻ ለረዥም ጊዜ ወይም ለሁል ጊዜ እንዲመደቡ ያደርጋሉ፡፡ ከላይ ባነሳነው ምሳሌ፣ ሁሌም ከሽሮሜዳ ሜክሲኮ የሚሰማራ ታክሲ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህንን ታክሲ ለመጥቀም ደግሞ ሌሎቹ በፈረንሳይ መሰማራት ስለሚኖርባቸው (ወይም በሜክሲኮ ለመሰማራት ከሚፈጅባቸው ጊዜ የላቀ ርዝመት በመፍጀት) ተጎጂ ይሆናሉ፡፡

የታክሲ ሥራ ያዋጣል?

በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና ብዙ የታክሲ ባለንብረቶች ታክሲዎቻቸውን እየሸጡ መሆኑን ያትታል፡፡ ለምን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የመጀመሪያው ጉዳይ የሚሆነው ሥራው ‹ያዋጣል ወይስ አያዋጣም?› የሚለው ነው፡፡

ቀደም ሲል የጠቀስነው ሾፌር ‹‹አያዋጣም›› ባይ ነው፡፡ ‹‹እንዲያውም፤ የታክሲ ሥራ ከባለንብረቱ ይልቅ ለሾፌሩ ያዋጣዋል›› ይላል፡፡

የታክሲ ባለንብረት በየቀኑ ከሾፌሩ የሚቀበለው 120 (አሁን 150 ሆኗል) ብር ነው፡፡ ይሄ 120 ብር በወሩ ቀናት ሲባዛ 3,600 ብር ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ በየወሩ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን እነ‹ቴስቲኒ› (በባለሙያው አጠራር) በ2000 ብር፣ ባትሪ በ400ብር - ስድስት ወር ያገለግላል፣ ጎማ እስከ2000 ብር አውጥቶ መቀየር እና ብልሽትም ከገጠመው ማሠራት የባለንብረቱ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ወጪ መሸፈኑ እንኳን ሊያተርፍ እንዲያውም የሚያከስር እየሆነ እንደሆነ ባለንብረቶችም እየተናገሩ ነው፡፡

ከ5 ዓመት በፊት ‹ቴስቲኒ› በ250 ብር ማስቀየር ይቻል ነበር፣ ባትሪ በ400 ብር እና ጎማ እስከ 500 ብር ማስቀየር ይቻል ነበር፤ አሁን ግን የታክሲ ሥራን የመለዋወጫዎቹ ዋጋ የማይቀመስ ስላደረገው፣ ከሥራው የሚወጡ እንጂ ወደሥራው የሚገቡ ባለንብረቶችን ማግኘት እያከበደ መጥቷል፡፡

የታክሲ ሾፌሮች ከ350 ብር እስከ 400 ብር የወር ደሞዝ ይኖራቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ታፔላ ከተጀመረ ወዲህ ከዕለት ገቢያቸው ላይ በአማካይ እስከ 50 ብር እየያዙ ይወርዳሉ፡፡ ይህ መጠን በፊት በአማካይ 150 ብር እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ የቀነሰው ገቢያቸው እንጂ ቅጣቱ እንዳልሆነ እና በጣም እንዳማረራቸው ያነጋገርኳቸው የታክሲ ሾፌሮች በሙሉ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ለሾፌር የሚከፍሉት ከ900 እስከ 1100 ብር ነው፣ ብዙ ጫና የለውም፣ አልፎ አልፎ ጥቅማ ጥቅሞችም አይጠፉትም… ይህንን አስመልክተው የመንግስት መሥሪያ ቤት ውስጥ ለመቀጠር እየተፍጨረጨሩ ያሉ ሾፌሮችም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየን የታክሲ ሥራ ለሾፌሩም፣ ለባለንብረቱም ከዕለት ዕለት መክበዱን ነው፡፡

የተሳፋሪው ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የታክሲዎች የማስተናገድ አቅም እጅግ እያጠረ መጥቷል፡፡ በፊት በግፊያ ታክሲ ውስጥ ለመግባት ይደረግ የነበረው ትንቅንቅ አሁን የማይሞከርበት ደረጃ እየደረሰ ስለመጣ ተጠቃሚው ሰልፍን እንደመፍትሔ ወስዶታል፡፡ ሜክሲኮ /ቡናና ሻይ አካባቢ/ የተጀመረው የታክሲ ጥበቃ ሰልፍ በየአካባቢው እየተስፋፋ ነው፡፡ ሰልፉ የተጠቃሚውን ጨዋነት ያሳያል፣ ነፍሰጡሮች እና አዛውንትን ከሌሎች እኩል እንዳመጣጣቸው እንዲስተናገዱ ያደርጋል፤ በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜያዊ ችግርን የመቀበያ መንገድ እንጂ መፍትሔ ሊባል ፈፅሞ አይችልም፡፡

አሁን ሰልፉም ቢሆን መጀመሪያውና መጨረሻው (ጫፍ ለጫፍ) መተያየት የማይችልበት ደረጃ እየደረሰ ስለሆነ ጠዋት ሥራ ለመግባት ያሰበ ሰው ተራው እስኪደርሰው ሲጠብቅ አይውልም፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው ክፍል /መንገዶች እና ትራንስፖርት ባለስልጣን/ ዘላቂ እርምጃ ዛሬውኑ /ሳይቃጠል በቅጠል/ መተግበር ካልጀመረ ወደማይወጣበት አዘቅት እኛንም ራሱንም መውሰዱ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment