Wednesday, October 15, 2014

የዞን9 ጦማርያኑ እና የወዳጅ ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

 #FreeZone9bloggers #Ethiopia

የዞን9 ጦማርያኑ እና የወዳጅ ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

ከሁለት ወር ቆይታ በኋላ በነሶልያና ሽመልስ የሽብር ወንጀል የክስ መዝገብ ልደታ ፍርድ ቤት የቀረቡት ስድስቱ የዞን9 ጦማርያን እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ቀጠሮ ችሎቱ ከ20 ቀን በኃላ እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተጠናቀቀ። 

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው የተከሳሽ ጠበቆች ክሱ ላይ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ አቃቤ ህግ አይቶ ምላሽ እንዲሰጥበት የተቀጠረ ሲሆን በዚያም መሰረት ለተከሳሽ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ አቃቤ ህግ የፅሁፍ ምላሽ ሰጥቷል ። 

ፍርድ ቤቱም የጠበቆችን የክስ መቃወሚያ እና የአቃቤ ህግን ምላሽ መርምሮ በክሱ ሂደት ላይ ብይን ለመስጠት ለተጨማሪ ሃያ ቀን ለጥቅምት 25 ቀጠሮ ሰጥቷል። 

በተጨማሪም የሴት ተከሳሾችን በጓደኛና በቤተሰብ አለመጎብኘት ተከትሎ ያቀረቡትን አቤቱታ እንዲያስረዳ የማረሚያ ቤቱ እንዲገኝ ጥሪ ቢደረግም አለመገኘቱን እና በፓሊስ በኩል ምላሽ ይዞ መቅረቡን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በሚቀጥለው ቀጠሮ የማረሚያ ቤቱ ሃላፌ እንዲገኙ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። ነገር ግን ሴት ተከሳሾች በተለይ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳየ የመጎብኘት መብት መሰረታዊ መብታቸው በመሆኑ 20 መቆየት እንደማይገባ በመጠየቃቸው ፍርድ ቤቱ የሴት ተከሳሾችን የጉብኝት መብት አስመልክቶ ለማየት ለጥቅምት 11 አጭር ቀጠሮ ሠጥቷል ። 

በዛሬው እለት ነጭ በመልበስ የተገኙት ተከሳሾች በመልካም ፈገግታ እና በጠንካራ መንፈስ የነበሩ ሲሆን በፈገግታ ወዳጅ እና ጓደኞቻቸውን ሰላም ሲሉ ተስተውለዋል። 

በመጨረሻም የሚቀጥለው ቀጠሮ ለጥቅምት 25 የተወሰነ ሲሆን የሴት ታሳሪዎችን የጉብኝት መብት ጥያቄ አስመልክቶ በጥቅምት 11 ችሎቱ ቀድሞ ይሰየማል ተብሎ ይጠበቃል።

የዞን9 ጦማርያን የክሱን ፈጠራነት፣ የጦማርያኑን እና ጋዜጠኞቹ በመአከላዊ ምርመራ ያለፉበትን የመብት ጥሰት እያስታወስን የፍትህ ስርአቱ የሚታማበትን የፓለቲካ መጠቀሚያነት ክስ ወዳጅ ጋዜጠኞችን እና ተከሳሽ ጦማርያንን በነፃ በማሰናበት ፍርድ ቤቱ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሚጠቀምበት ተስፋ እናደርጋለን።

Tuesday, October 14, 2014

የህግ የበላይነት፣ የፓለቲካ ምህዳር እና ሰብአዊ መብት - የጸረ ሽብር ህጉ ሲገመገም

PDF
“ጋዜጠኝነትን እና የፖለቲካ ድርጅትን ሽፋን በማድረግ የሀገሪቱንና የሕዝቦቿን ሰላም ለማደፍረስ ከሚያስቡና ከሚፈልጉ ‘ሀይላት’ ጋር ግንኙነት በማድረግ የተለያዩ  የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር አውለናቸዋል።“ 
ይህ መግለጫ (መልስ) የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 ከወጣበት ከነሀሴ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ጋዜጠኞችና በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው የፖለቲካ ምህዳሩን የተቀላቀሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ከታሰሩ በኋላ በመንግስት አካላት የሚሰጥ የተለመደ አባባል ነው። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መስከረም 2007 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥም ከጋዜጠኛ እስከ ፖለቲከኛ (political personalities)፣ ከሀይማኖት መሪዎች እስከ ጦማሪያን፣ ከታጣቂ ወታደሮች እስከ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች... በዚሁ አዋጅ አማካኝነት ‘ሽብርተኝነታቸው ተረጋግጦላቸዋል’ ወይም ‘ይረጋገጥባቸው ዘንድ ፍርዳቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።’ ለመሆኑ ይህ ከ14 ዓመት ህፃን[1]  እስከ 80 ዓመት አዛውንት[2]  በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የሚያስቀጣው፣ ይህ ከጉምቱ ምሁራን እስከ ገበሬዎች ድረስ የሚያስረው... ሕግ በተጨባጭ ስፋትና ጥበቱ ምን ያህል ይሆን? ለታሪካዊ ጥያቄዎች ያለው ምልከታስ?  በሀገሪቱ ስላለው የዲሞክራሲ ሁኔታስ (The state of Democracy) ምን ይነግረናል? ስለ ጨቅላው የኢትዮጵያ ፌደራሊዝምስ ከፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ተግባራዊነት አንፃር ምን ይታየናል? ወ.ዘ.ተ. የሚሉትን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በመሬት ላይ ያሉ የሕጉ እውነታዎችን በመመርመር (Fact investigation) ምልከታዎቹን (Implications) በዚህ ፅሁፍ ለማየት ሞክረናል።

የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ
ዓለማቀፉ የፀረ-ሽብር ውጊያ (The Global War on Terror) በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቡሽ <We will not tire, we will not falter> ንግግር ከታወጀ ጀምሮ በተለያዩ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ሀገሮች በሽብርተኝነት ዙሪያ ያላቸውን የሕግ ማዕቀፍ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ኢትዮጵያም የዓለማቀፉ የፀረ-ሽብር እንቅስቃሴ አካል መሆን አለብኝ በማለት እንዲሁም ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ እና ድርስ አደጋ (clear and present danger) ደቅኗል በሚል መነሻ የፀረ-ሽብር ሕግ አርቅቃ ለፓርላማ አቀረበች።
ረቂቁ በቀረበበት ወቅት የተለያዩ  አካላት (የፓርላማ አባላት፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ጋዜጠኞችና የጋዜጠኛ ማኅበራት ወ.ዘ.ተ.) ረቂቅ ሕጉ ሰፊ የሽብርተኝነት ድርጊት ትርጉም ይዟል፣ ‘ማወቅ ሲገባው’፣ ‘አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት’ የመሳሰሉት የሚሉ ለትርጉም ክፍት የሆኑ የወንጀል አይነቶችን አካቷል፣ ለፖሊስና ለደህንነት አካላት እጅግ የተለጠጠ ስልጣን ይሰጣል፣ እንደ የዋስትና መብት ያሉ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ይነፍጋል፣ የሥነ ስርዓት እና የማስረጃ ሕጎችን በማቅለል ወንጀለኝነትን የማስረዳት ሸክምን ከዓቃቤ ሕግ ወደ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ያሸጋግራል (shifting burden of proof) ወ.ዘ.ተ. የሚሉ ትችቶችን ቢያቀርቡም፤ ‘እነዚህን የሕጉን ክፍተቶች የተለያዩ  የመንግስት አካላት ላልተገባ ጉዳይ ሊያውሏቸው ይችላሉ’፣ ‘ተቃውሞን እና የመናገር ነፃነትን ወደ ወንጀልነት ያሸጋግራል’ የሚሉ ስጋቶችን በጊዜው ቢያነሱም ሕጉ በፓርላማ ከመፅደቅ ያገደው ነገር አልነበረም።
በሕጉ ዙሪያ የሚቀርቡ ብዙና የተለያዩ  ትችቶች ቢኖሩም ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የዚህ ፅሁፍ ዓላማ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ በተጨባጭ የትኞቹን የሕብረተሰብ ክፍሎች እያጠቃ ነው? ስለ አጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታስ ምን ያመለክተናል? የሚሉትን ጉዳዮችን መዳሰስን ዓላማ ያደረገ ነው።

(ማስታወሻ: - በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚጠቀሱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊ ቀጠሮ ወይም ክስ ተመስርቶባቸው በመደበኛ ቀጠሮ ላይ ያሉ ናቸው።)

የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አተገባበር
የፀረ- ሽብርተኝነት ሕጉ ከመውጣቱ በፊት እንዲሁም ከወጣ በኋላ የሚቀርቡበትን ትችቶች የመንግስት አካላት ምላሽ ሲሰጡበት: -
“ሕጉን ቃል በቃል የገለበጥነው ከAmerican Patriotic Act እንዲሁም ከእንግሊዙ የTerrorism Act ነው። እኛ ጋር ሲመጣ ለምን ትችት እንደሚቀርብበት ሊገባን አልቻለም።” የሚል ነው።  መንግስት እውን ቃል በቃል ገልብጦታልን? የሚለውን ጥያቄ ለመረዳት እንችል ዘንድ የአንዲት እንግሊዛዊት እና የአንድ አሜሪካዊ ታሪክን በማቅረብና በማነፃፀር ትግበራው ላይ ፍተሻ እናድርግ።
እንግሊዛዊቱ Kate Kaplan በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ Mathematicsን በMajorነት Computer Scienceን ደግሞ Minor በማድረግ ትምህርቷን የጨረሰች ስትሆን፤ በተለያዩ  መስሪያ ቤቶችም ከምረቃዋ በኋላ በስራ ዓለም ያሳለፈች ናት። በስራ ዓለምም በData Expertነት Specialize አድርጋለች። ከስራዋ ጎን ለጎን ደግሞ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም እንደርሷ ሁሉ ለሀገራቸው መሻሻል የሚተጉ ጓደኞችን ለማፍራት የቻለች ሲሆን፤ ከእነዚህ ወዳጆቿ ጋር በመሆንም በተለያዩ  ጉዳዮች ዙሪያ የምትጦምር ነች። ንባቧን እና ግንዛቤዋን ለማዳበር ይረዳት ዘንድም በተለያዩ  ርዕሶች ዙሪያ የተፃፉ ፅሁፎችን ከድረ-ገፆች ላይ በመገልበጥ ታነባለች። በIreland Republic ዙሪያ ጥያቄ ያለውን IRA የተባለ ፓርቲ ፕሮግራምም ለማንበብ Laptop ላይ ገልብጣ አስቀምጣለች። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች የእንግሊዝ የፀጥታ አካላት እርሷንና የማኅበራዊ ሚዲያ ጓደኞቿን ሰብስቦ  ያሰራቸው ሲሆን ‘የሽብርተኝነት ተግባራትን ሊፈፅሙ ሲሉ ያዝኳቸው’ በማለት ክስ መስርቶባቸዋል። የክሱ ማስረጃ ሁነው ከቀረቡ ሰነዶችም አንዱ Kate ግንዛቤ ለማግኘት በማሰብ ከድረ-ገፅ የገለበጠችው እና ማንም ሰው በድረ-ገፁ አድራሻ ገብቶ ሊያነበው የሚችለው የIRA የፖለቲካ ፕሮግራም ነው። Kateና ጓደኞቿም ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። የእንግሊዝ Terrorism Act ደግሞ የተወነጀሉበት አዋጅ ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ Andrew Martin በአሜሪካው New York University የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር ሲሆን ከስራው ጎን ለጎን ደግሞ የDemocratic Party የአመራር ክበብ ውስጥ ተሳትፎ አለው። ከፖለቲቻ ስራው ጋር በተያያዘም የተለያዩ  ሰነዶችን የሚያገላብጥ ሲሆን ከእነዚህ ሰነዶች አንዱ ደግሞ ስለ አሜሪካው Black Panters Party የሚገልፅ ሰነድ ነው። በስልጣን ላይ የነበረው የRepublican Party Andrewን ከሽብርተኛ ድርጅት ከሆነው Black Panters Party ጋር ግንኙነት አለው በማለት አሳስሮ የአምስት ዓመት ፍርድ ፈርዶበት በአሁን ሰዓት እስሩን እየገፋ ይገኛል። የRepublican መንግስት በአቶ Andrew ላይ ፍርድ የበየነበት የAmerican Patriotic Act አንቀፆችን በመጠቀም ነው።

እነዚህን ሁለት ጉዳዮች የጠቀስነው የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉን ቃል በቃል ገለበጥኩባቸው የሚላቸው ሀገሮች አሜሪካና እንግሊዝ የሽብርተኝነት ክሶች እስከምን ድረስ ይደርሳሉ? የሚለውን ጉዳይ ለማየት ሳይሆን ሕጉ ቃል በቃል ተገለበጠ በተባለባቸው ሀገሮች የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ሰዓት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን እየተጠቀመበት ባለው አግባብ ቢጠቀሙ ምን ሊፈጠር እንደሚችል  ለማሳየት ሲባል፣ በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሳ በቃሊቲ የምትገኘውን ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁንን በKate Kaplan፣ እንዲሁም በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ተከሶ አምስት ዓመት ተፈርዶበት እስሩን እየገፋ የሚገኘው መምህር በቀለ ገርባን በAndrew Martin በመተካት ማህሌት እና በቀለ ላይ እየሆነ ያለው ነገር የኢትዮጵያ መንግስት ‘ምዕራባውያንም ተመሳሳይ የህግ ማዕቀፍ ነው ያላቸው’ በማለት እያቀረበው ያለውን ማስተባበያ ምን ያህል በአተገባበሩ የተሳሳተ እንደሆነ በቀላሉ ያሳያል።

 ጦማርያን እና ሰላማዊ ፖለቲከኞችን በመፃፋቸው እና ለሀገራቸው መልካም ነገርን በማሰብ ፖለቲካ ውስጥ የገቡ ግለሰቦችን የሚያስር - የሚከሰው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንጂ በሌላ ዓለም ማግኘት ከባድ ነው። Kateና Andrew ‘ሽብርተኛ’ የሚባሉት በኢትዮጵያ እንጂ በአሜሪካ ወይም በእንግሊዝ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ታዲያ ቃል በቃል ከምዕራቡ ዓለም የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጎች ‘የተገለበጠው’ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ እንዴት ቢሰራ ነው ሁሉንም የሕይወት መስመሮች ‘በሽብርተኝነት’ ሊፈርጅ የቻለው?

“የሽብርተኛ ፍለጋና ምርመራው ሂደት “
የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ በተግባር እንዴት ነው እየሰራ ያለው? የሚለውን ጥያቄ መመለሳችን ከላይ የጠየቅነውን ቀዳሚ ጥያቄ ይመልስልናል። እንዲህ በአጭር ምሳሌ እንመልከት:-
‘ሀሰን፣ ሀያት እና ከድር በፖሊስ (በደህንነት ኃይል) ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኘ ወንጀል ሊፈፅሙ ሲሉ ተያዙ’ ተብለው ታሰሩ። አሰራሩ እንዲህ ይቀጥላል:-
  1. በብሔራዊ የመረጃና የደህንነት ኃይል በቁጥጥር ስር ይውላሉ። በተለያዩ  የደህንነት ‘እስር ቤቶች’ ላልተወሰነ ጊዜ (ከ6 ወር በላይ በደህንነት ቢሮ የቆዩ ሰዎች አሉ) ከከፍተኛ ድብደባ እና ስቃይ ጋር ይቆያሉ። በአብዛኛው ፍርድ ቤትም ሆነ ቤተሰብ ያሉበትን ሁኔታ አያውቅም።
  2. በደህንነት ‘እስር ቤቶች’ የነበራቸውን የፈተና (ordeal) ጊዜ ከጨረሱ በኋላ ለፌደራል ፖሊስ ተላልፈው ይሰጣሉ። የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ‘ማረፊያ ቤት’ በማረፍም ‘የምርመራ’ ጊዜያቸውን ይጀምራሉ። የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ባለው ‘የፀረ-ሽብር ዲቪዚዮን’ አማካኝነት ባሉት ከ20 በላይ መርማሪዎችም ‘ምርመራው’ ይጀመራል። በዚህ የምርመራ ወቅትም እጅግ ኢሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶች ይፈፀምባቸዋል። የተጠረጠሩበትን ‘የሽብርተኝነት ድርጊት’ እስኪያምኑ ድረስም መከራና ስቃያቸው ይቀጥላል። በዚህ ሁኔታ እስከ አራት ወራት ለሚቆይ ጊዜ ይቆያሉ (እስከ ስምንት ወራት በማዕከላዊ የቆዩ ሰዎች አሉ)።
  3. በአብዛኛው ‘የሽብርተኝነት ወንጀል ፋይሎች’ ላይ እንደሚታየው በነሀሰን፣ ሀያት እና ከድር ጉዳይ ላይም ፖሊሲ በቂ ማስረጃ ስለማይኖረው ‘ማስረጃ’ እዛው በወንጀል ምርመራ  ዘርፍ መርማሪዎች ይዘጋጃል። እንዴት?

ሀ. ድብደባና ስቃዩን በማጠናከር ከሶስቱ ተከሳሾች አንዱን (ለምሳሌ ከድርን) በጓደኞቹ በሀሰን እና በሀያት ላይ ምስክር እንዲሆን (Accomplice witness) በማስገደድ ፖሊስ የሰው ማስረጃ ይፈጥራል። ከድርም ከክሱ ይወጣል።

ለ. ፖሊስ የፈለገውን ቃል በመፃፉ ሀስን እና ሀያት እንዲፈርሙ ያስገድዳቸዋል። ቃላቸውንም ‘በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕግ አንቀፅ 27(2) መሰረት በነፃ የተሰጠ’ ይለያል።

ሐ. ምናልባትም ሀሰን እና ሀያት ‘ቃላችንን በድብደባ ያለፈቃዳችን ነው የሰጠነው’ በማለት በፍርድ ቤት በክሱ ሒደት ወቅት እንዳያስተባብሉት ፖሊስ ስጋት ካደረበት እዛው በወንጀል ምርመራ  ዘርፍ ማረፊያ ቤት (ማዕከላዊ) እያሉ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕጉ አንቀፅ 35 መሰረት ‘አሸባሪነታቸውን’ አምነው ቃላቸውን እንዲሰጡ ያስደርጋል። በፍርድ ቤት የካዱ እንደሆነ ወደ ማረፊያ ቤት ሲመለሱ ሌሊቱን ሙሉ ከባድ ስቃይ ይጠብቃቸዋል።

መ. ካስፈለገም ‘የሀሰት ምስክሮችን ያሰለጥናል’፣ የወንጀል የሀሰት ሰነዶችን ያዘጋጃል። ወ.ዘ.ተ.

  1. ፖሊስ ‘ምርመራውን’ በዚህ መንገድ ካጠናቀቀ በኋላ ምርመራውን ለፍትህ ሚኒስትር ይልካል። የፍትህ ሚኒስትርም አስፈላጊውን ‘ፖለቲካዊ ግምገማ’ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ካደረገ በኋላ አራት አቃብያን ሕጎችን (አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ፣ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው፣ አቶ ዘውዱ በቀለንና አቶ ሰውበሰው አድማሱን) ላቀፈው የፀረ-ሽብርተኝነት case team ያስተላልፋል። አቃብያነ ሕጎቹም የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ላይ ከተደነገጉት አስር (10) ወንጀሎች በአንዱ ወይም ከዛ በላይ ክስ ያቀርባሉ።
  2. በመጨረሻም የሀሰንና የሀያት ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ይቀርባል። አቃቤ ሕግ ከድርን የሰው ማስረጃ አድርጎ  ያቀርባል። የሀሰንና የሀያትን ለፖሊስ ወይም ለስር ፍርድቤት ተገደው የሰጡትን የተከሳሽነት ቃል በሰነድ ማስረጃነት ያቀርባል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ እና 19ኛ ወንጀል ችሎቶች ካሏቸው ዳኞች[4] ሶስቱ በጉዳዩ  ላይ ይሰየሙና ፍርድ ይሰጣሉ። ከድር ምስክር በመሆን ነፃ ይወጣል። ሀሰንና ሀያት ደግሞ ‘አሸባሪነታቸው’ ተረጋግጦባቸው ይፈረድባቸዋል። (በነገራችን ላይ አሁን ባለው አሰራር የፍርድ ሂደቱ ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል)
ይህ ‘የሁሉም’ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ መሰረት የተከሰሱ ሰዎች ጉዳይ አካሄድ ነው። በዚህም መንገድ ዜጎች ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ገለል እንዲሉ ይደረጋሉ። ምክንያቱም እነሱ ‘ኢትዮጵያዊ አሸባሪዎች’ ናቸውና። የእነዚህን ኢትዮጵያውያን አሸባሪዎች ማንነት ማወቃችን የሽብርተኝነት ትግሉን ምንነት እና የሀገሪቱን ጉዞ በጉልህ ያሳየናልና እስኪ ፍተሻ እናድርግ።

‘መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ፌደራሊዝም’
 “ደርግ በወደቀበት ሰዓት በሀገሪቱ አስራ ሰባት (17) የሚሆኑ የታጠቁ ሀይላት ነበሩ። ይህም ዜጎች በደርግ ስርዓት የተከፉ ምን ያህል ወገኖች እንደነበሩ አመላካች ነው።” በማለት ኢህአዴግ ስልጣኑን ከደርግ በተረከበበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በተደጋጋሚ ያስረዳል።
ኢህአዴግ አያይዞም የተለያዩ  ቡድኖችን መከፋትና ብሶት ለመቀነስና እስከ መጨረሻውም ለማስወገድ የፌደራል ስርዓት እንዲዘረጋ፤ ይህ የፌደራል ስርዓትም ‘ሀገሪቱን እንደ ዩጎዝላቪያ ከመሆን የታደጋት ፍቱን መድኃኒት’ እንደሆነ ይገልፃል።
ደርግም ከወደቀ ሩብ ምዕተ ዓመት እየሆነው ነው፤ የኢትዮጵያም የፌደራል ስርዓት ሀያኛ ዓመቱን ይዟል። እውን ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች ምን ያህል መሻሻል አሳይተዋል? የፌደራል ስርአቱስ ከቃላት ባለፈ ምን ያህል እውነተኛ ለውጥ አምጥቷል?  የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን እና ሕጉ ተግባራዊ የሆነባቸውን ቡድኖች ማንነት ማየቱ ለጥያቄዎቻችን መልስ ለመስጠት  ይሆናልና እስኪ እንመልከት።
በአሁኑ ወቅት ገዥውን ስርዓት ለመገዳደር በማሰብ ‘ፋኖነትን’ የመረጡ ቡድኖች የደርግ ጨካኝና አምባገነን ስርዓት ሲወድቅ ከነበሩት የታጠቁ ሀይሎች ቢበልጡ እንጂ አያንሱም። የአሁኖቹን ታጣቂዎች ከደርግ ወቅቶቹ የሚለያቸው፣ የአሁኖቹ ‘በአሸባሪነት’ የተፈረጁ መሆናቸውን ነው።

ይህ ፅሁፍ በተፃፈበት ወቅት ክስ ተመስርቶባቸው በቀጠሮ ላይ የሚገኙ አስር የተለያዩ  የክስ መዝገቦችን ብናይ መልሳችን ግልፅ ይሆንልናል።
“የጋምቤላ ክልል አሁን ባለው የፌደራል ስርዓት ምንም ዓይነት ጥቅም እያገኘ አይደለም። ለዚህም መፍትሄው ስርዓቱን በኃይል ማስወገድ ነው።” በሚል መነሻ አምስት (5) የተለያዩ  ቡድኖች መሳሪያ አንስተዋል። ከነዚህም አምስት (5) ፓርቲዎች መካከልም በአቶ ሙድ ጎይባሬ የሚመራው የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ጋር በተገናኘ 11 ሰዎች ማለትም
  1. ኡቺሚ አፐይ ኡቻላ
  2. ኡማን ኡድሉቻም
  3. ኡቻን ኡድላ ኦፒዮ
  4. ኡመድ ኡጁሉ ኡማን
  5. ኝበዲ ኡባንግ ኡጃቶ 
  6. ኦፒዮ ቹር ኡባንግ
  7. ኡመድ ኡቶ ኡማን
  8. ኡፐዶካ ኡቱን ኝግየው
  9. ታደሰ ኡዱጊ ቲፋ
  10. ኡማን ኡካይ ኡኩችና
  11. ኦኬሎ ኡበር ኡቻን
በፌ/ዓ/ህ/መ/ቁ 322/06 በቀን 18/07/06 በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 3 (1, 2 እና 3) መሰረት ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ ጋህነንም የሽብርተኛ ድርጅት እንደሆነ በክሱ ተመልክቷል። ከጋምቤላ ሳንወጣ አሁን በቅርቡ ደግሞ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት በአቶ ኦኬሎ አኳይ ኡቻላ እንደሚመራ በክሱ ከተመለከተው የጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋዴን) አባላት ናችሁ ተብለው የተከሰሱ ሰባት ግለሰቦችን እናገኛለን። እነርሱም
  1. ኦኬሎ አኳይ ኡቻላ
  2. ዴቪድ ኡጅሉ ኡባንግ
  3. ኡቻን ኦፒዮ ኡሞድ
  4. ኡማን ኝክየው ኡድሉ
  5. ኡጅሉ ቻሞ ኡኮይ
  6. ኦታካ ኡዋር ኡጋላና
  7. ኡባንግ ኡመድ አቦላ ናቸው።
በቀን 04/10/2006 ዓ.ም. በፌ/አ/ህ/መ/ቁ 508/06 በቀረበባቸው በዚህ ክስ ጋዴን የሽብርተኛ ድርጅት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ክሱም በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ 4 ላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በመተላለፍ እንደሆነ ተገልጿል።
እስኪ ወደ ሌላ ክልል እንለፍ። በኮለኔል አለበል አማረ እንደሚመራ የሚነገርለትን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረትን (አዴሀህ) እናገኛለን። የፌደራል አቃቢ ሕግ በመዝገብ ቁጥር 071/06 በቀን 28/12/05 ባቀረበው ክስ ‘ግንቦት ሰባት ከተባለ አሸባሪ ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኦዴሀህ የተባለ ‘ሽብርተኛ ድርጅት’ ጋር አባል በመሆን ሲንቀሳቀሱ ያዝኳቸው’ ያላቸውን 10 ሰዎች በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ 7(1) መሰረት ከሶ እናገኛለን። ግለሰቦቹም
  1. ማስረሻ ታፈረ ወ/ገብርኤል
  2. ሻለቃ አለምነው አየለ ነጋሽ
  3. ብርቁ አዲሱ ውቡ
  4. ታደሰ መንግስቱ በላይ
  5. የፀዳው ካሴ አሉላ
  6. አወቀ ደስታው ምህረቴ
  7. መሀመድ ግዛቸው ፋንታው
  8. ቴዎድሮስ ሀይሌ
  9. ታደሰ በለጠ
  10. ታደሰ ባዩ  ገበየሁ ናቸው።
ወደ ኦሮሚያ ክልል ተጉዘናል። ባለፉት 20 ዓመታት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ናችሁ በሚል እጅግ በጣም ብዙ ኦሮሞዎች ታስረዋል፣ ተሰደዋል ወይም ተገድለዋል። ይህ ሁኔታ አሁንም በሰፊው ቀጥሏል። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ክሱ ‘ራሱን ኦነግ ብሎ ከሚጠራው ‘ፀረ-ሰላም’ ሀይል ውስጥ አባል በመሆን...’ ከሚለው የተለመደ የክስ ቃል  በተለየ መንገድ ‘ራሱን ኦነግ ብሎ ከሚጠራው ‘አሸባሪ’ ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን...’ ወደሚል መቀየሩ ብቻ ነው። ምስጋና ለፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ይሁንና። ለዚህም ጥሩ ማሳያ ይሆኑን ዘንድ ሁለት የአቃቢ ሕግ መዝገቦችን እንጠቅሳለን።
በ22/07/2006 ዓ.ም. በፌ/ዓ/ሕግ/መ/ቁ 376/06 በመሰረተው ክስ
  1. ደልዴሳ ዋቆ ጃርሶ
  2. ገልገሎ ጉዮ ቦሩ
  3. ዋርዮ ጣጤሳ ጉዮ
የተባሉ ግለሰቦች የኦነግ አባል በመሆን ‘የሽብርተኝነት ድርጊቶችን’ ሲፈፅሙ ይዣቸዋለሁ’ በማለት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን አንቀፅ 3(1 እና 2) እንዲሁም አንቀፅ 7(1) በመጥቀስ ክስ መስርቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የፌደራል ዓቃቢ ሕግ በቀን 11/2006 ባቀረበው ‘የሽብር ወንጀል’ ክስ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩት
  1. አብዲ ከማል የሱፍና
  2. ቶፊቅ ረሽድ ዩያ
‘የአሸባሪው’ ድርጅት የኦነግ አባላት በመሆን የሽብር ተግባራትን ልትፈፅሙ ስትሉ ተይዛችኋል’ ተብለው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ 7(1) ተጠቅሶባቸው ክሳቸውን በማረፊያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ። በ2006 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ከተለያዩ  የክልሉ ዩኒቨርስቲዎች (ከሀሮማያ፣ ከጅማ፣ ከወለጋ... ዩኒቨርስቲዎች) የተያዙ ተማሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ  የክልሉ አካባቢዎች (ከወለጋ፣ ከሞያሌ ወ.ዘ.ተ.)ተይዘው የታሰሩ ዜጎች በኦነግነት ተጠርጥረው በፌደራል የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) የሚገኙ ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ቀን ድረስም ክስ ሳይመሰረትባቸው ከአራት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ በወንጀል ምርመራ ዘርፍ ‘ማረፊያ ቤት’ ውስጥ ይገኛሉ።
በድጋሚ ወደ ሀገሪቱ የምዕራብ ጫፍ እንጓዝ፤ ‘አሸባሪው’ ቤሕነንን እናገኛለን - የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ። በአቶ አብዱል ወሀብ መሀዲ  የሚመራው ቤሕነን “የክልሉ ነዋሪዎች ኢህአዴግ ከዘረጋው ስርዓት ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም። መፍትሔውም ስርዓትቱን በሀይል ማስወገድ ነው።” በሚል መነሻ ነፍጥ ያነገበ ፓርቲ ነው። በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ‘የሽብርተኛ ድርጅት’ ከመባል ግን አልተረፈም። የፌደራል አቃቢ ሕግ በ19/12/2006 ዓ.ም. ባቀረበው ክስ
  1. አብዱልከሪም አብዱሰመድ አብዱልቃድር
  2. ሀዎጃ ሚነሳ አጉር
  3. ኢላቅ ኢብራሒም ዓሊ (ዕድሜ 17)
  4. አዴላ ጃባለ ንምር
  5. አብዲ ሀሚዝ ፈረንሳ
  6. ፋተልሙላ አጣሂር አከሶ
የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀፅ 7(1) በመጥቀስ ከላይ የተዘረዘሩትን ስድስት ግለሰቦች ‘የአሸባሪው የቤሕነን አባል ናችሁ በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።
ሰሜን ኢትዮጵያ ጫፉ ላይ ነን። በስልጣን ላይ የሚገኘው ‘ኢህአዴግ’ ትግሉን የጀመረበት የትግራይ ክልል ውስጥ። ‘ገዢው ስርዓት ለትግራይ ሕዝብ አመጣልሃለሁ ያለውን ዴሞክራሲና ፍትህ ማምጣት አልቻለምና ስልጣን በቃው’ በማለት የተነሳው ዴሞክራሲያዊ ሕዝቢ ምንቅሳቀስ ትግራይ (ዴሕምት) ደግሞ ከትግራይ ክልል የተገኘው ‘አሸባሪ’ ድርጅት ነው። የፌደራል ዓቃቢ ሕግ በ
  1. ብሎፅ ገ/ፃድቃን
  2. ነጋሌ ብርሃኑ
  3. ሹማይ ተበጀ
ላይ ባቀረበው ክስ ‘የአሸባሪው’ ዴሕምት አባል በመሆን የተለያዩ  የሽብር ተግባራትን ሊፈፅሙ ሲሉ ይዣቸዋለሁ በማለት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን አንቀፅ 7(1) በመጥቀስ ክስ መስርቶባቸዋል።
በዘጠኙም የፌደራል ክልሎች ‘አሸባሪ’ ድርጅቶችን መፈለጋችንን ቀጥለናል፤ ማረፊያችንም ኦጋዴንያ ሆኗል። የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ 25 መሰረት በሽብርተኛ ድርጅትነት ከሰየማቸው 5 ድርጅቶች ውስጥ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ኦጋዴንን ነፃ ለማውጣት እየታገለ የሚገኘው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) አንዱ ሲሆን፤ የፌደራል አቃቢ ሕግም በየጊዜው ‘የአሸባሪው’ የኦብነግ አባላት ናችሁ በማለት እጅግ ብዙ ክሶችን በኦጋዴን ተወላጆች ላይ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ ክስ አቅርቦ ‘ፍርዳቸውን’ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
እስኪ በዓላማ ደረጃ ብሄር ተኮር ከሆኑት ‘የሽብርተኛ ድርጅቶች’ ሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያ ‘የሽብርተኛ ድርጅቶች’ እንለፍ።

የግንቦት ሰባት ንቅናቄ “በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሰላማዊ መታገያ መንገዶችን በሙሉ  ስላፈናቸው፤ ‘በማንኛውም አይነት’ የመታገያ መንገዶች ትግል እናደርጋለን።” በማለት አቋሙን ካላወቀ በኋላ ‘ይሔማ ዋና አሸባሪ ድርጅት ነው’ በማለት በመንግስት ከተሰየመ ወዲህ ትልልቅ የፖለቲካ ስብዕናዎችን ጨምሮ  ብዙ ግለሰቦች ከዚህ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ‘የሽብርተኝነት ድርጊቶችን’ ለመፈፀም በማቀድ፣ ማሴር፣ መሰጋጀትና ማነሳሳት ወንጀሎች ተከሰው ወደ እስር ቤት ወርደዋል፤ ወይም በሌሉበት ተፈርዶባቸዋል። ይሔው ጉዳይ ቀጥሎ ይሕ ፅሁፍ በተፃፈበት ወቅት እንኳን በፌደራል ዓቃቢ ሕግ በ13/12/05 በቀረበ ክስ
  1. ዘመኑ ካሴ በእውቄ
  2. አሸናፊ አካሉ አበራ
  3. ደህናሁን ቤዛ ስመኝ
  4. ምንዳዬ ጥላሁን ለማ
  5. አንሙት የኔዋስ አለኸኝ
  6. ደሳለኝ አሰፋ ወንድማገኝ
  7. ም/ኢ/ር ሙልየ ማናየ ረታ
  8. ጠጋው ካሳ እንየው
  9. ይህዓለም አካሉ አበራ
የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 4,  5 እና 8 ተጠቅሶባቸው ‘በአሸባሪነት’ ተከሰው ፍርድ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር (ኢሕአግ) ወደተባለ ‘የሽብርተኛ ድርጅት’ አልፈናል። በክስ ሒደር ላይ የሚገኙ ሁለት መዝገቦችንም እናገኛለን። የመጀመሪያው በፌ/ዓ/ሕ/መ/ቁ 033/06 በቀን 28/12/05 በ
  1. ፀጋው አለሙ ተካ
  2. ዋሲሁን ንጉሱ ገብሬ
  3. ጎዳዳው ፈረደ ማሞ
  4. ማማይ ታከለ በየነና
  5. ተገኝ ሲሳይ መንገሻ
ላይ የቀረበ ‘የአሸባሪው’ ኢሕአግ አባል የመሆን ክስ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ የፌደራል ዓቃቢ ሕግ በክስ መዝገብ ቁጥር 174/06 በ02/11/06 ባቀረበው ክስ
  1. አስማማው ደሴ ጣሰው
  2. መብራታይ ይርጋ ተስፋዬ
ላይ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀፅ 7(1) በመጥቀስ ‘በሽብርተኝነት’ ክስ አቅርቧል።

በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የሀገሪቱን የአስተዳደር ስርዓት ከአሀዳዊ (Unitary) ወደ ፌደራል መንግስ ሲቀይር እንደ ምክንያት የጠቀሰው ዋነኛ ነገር ለታሪካዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠትን፣ በአለፉ ስርዓቶች የተከፉ የተለያዩ  ወገኖችን የከፊል ራስ ገዝነት (Semi-Autonomous) የሆነ ስልጣን በመስጠት ‘ቁስላቸውን መሻር’ ወ.ዘ.ተ. የሚሉ ሀሳቦችን ሲሆን ለእነዚህ ሀሳቦች መፈፀምም በዘጠኝ ክልሎች የተዋቀረ እና በዋናነት ዘውግን መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓትን ዘርግቷል።
ገዥው ፓርቲ “ሕገ-መንግስቱ የፌደራል ስርዓት በመዘርጋት ጭቆናን ታሪክ አድርጓል፤ የብሔሮችን ጥያቄም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልሷል።” በማለት በተደጋጋሚ ቢገልፅም ከላይ ባየናቸው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የመሬት እውነታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ዘጠኝ ክልሎች በስድስቱ ውስጥ ማለትም፥ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች በብሔር ደረጃ የተቋቋሙ ‘ነፃ አውጪዎች’ በአሸባሪነት ተሰይመውና ተፈርጀው አይተናል።

በፌደራል ስርዓቱ ከተቋቋሙት ክልሎች 2/3ኛዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መከፋታቸውን የሚገልፁ  ታጣቂ ሀይሎች ያሏቸው ሲሆን በጣም የሚያሳስበው ደግሞ እነዚህ ሀይሎች ‘በአሸባሪነት’ የተፈረጁ መሆናቸው ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት አልከሸፈምን? መሳሪያ አነሳ የተባለን ፓርቲ ሁሉ ‘የሽብርተኛ ድርጅት’ እያሉ መፈረጁስ ተገቢ ነውን? አሁን በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ስልጣን የጨበጠው በመሳሪያ ነውና፣ የደርግ ስርዓት አሁን ያለው አይነት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ ኖሮት ቢሆን ኢህአዴግ ‘አሸባሪ ድርጅት’ መባሉ እውን ነበር። በዚህ ሂደት ገዢው ቡድን ከቀጠለ ‘ደርግ በወደቀበት ወቅት 17 የታጠቁ ሀይላት ነበሩ’ እንደሚባለው ኢህአዴግ ከስልጣን በሚወርድበት ወቅትስ ስንት ‘የሽብርተኛ ድርጅቶች’ ይኖሩ ይሆን?
ዞን9 ይህንን ጽሁፍ ለማጠናከር የተጠቀምንበትን ከላይ ያለውን መረጃ አንኳን ብንወስድ ዘጠኝ የተለያዩ ቡድኖች ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን በዚህ አጭር ጽሁፍ ውስጥ በሂደት ላይ ያሉ የክስ ሂደቶች ቁጥር እንኳን 58 ተከሳሾችን ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህ እኛ ማስረጃውን ማግኘት ያልቻልንባቸውን የክስ ሂደቶች እና ቀድሞ የተቀጡ ያለቁ ፋይሎችን እና ክልል ላይ የተደረጉ “የፍርድ ሂደቶቸን” አይጨምሩም፡፡  
(ማስታወሻ:  - በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር የተጠቀምንባቸው 10 የሽብርተኝነት ክሶች በሙሉ ከነሀሴ 2005 እስከ ነሀሴ 2006 ዓ.ም. ድረስ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በፌደራል አቃቢ ሕግ የቀረቡ ሲሆኑ፣ ይህ ፅሁፍ በተፃፈበት ወቅትም ሁሉም መዝገቦች በቀጠሮ  ላይ የሚገኙ ናቸው። )

‘It’s IslamoPhobic’?
ዓለማቀፉ የፀረ-ሽብርተኝነት ትግል ትኩረቱን በዋነኛነት የሙስሊሙ ዓለም ላይ ማድረጉ በተችዎች ዘንድ ‘የፀረ-ሽብርተኝነት ትግል ሳይሆን የተያዘው ኢስላምጠልነት (Islamophocia) ነው’ እስከመባል ደርሷል። ኢትዮጵያም የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ስታፀድቅ በገዥው ስርዓት የተሰጠው ምክንያት “የፀረ-ሽብርተኝነት ትግላችንን ለማሳደግ ያስችለን ዘንድ የህግ ማዕቀፋችን ማሳደግ አለብን፤ ይሔም ከዓለማቀፉ እውነታ ጋር ለመራመድ ያስችለናል።” የሚል ነው።

ታዲያ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ በውጤቱ እንዴት ሆነ? ብለን ተጨባጭ ምሳሌዎችን እያነሳን መመልከቱ ጉዳዩን ግልፅ ሳያደርገው አይቀርምና እስኪ እንመልከት።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ኢስላምን (Ummah) ከኢትዮጵያዊነት ጋር አንድ ላይ ይዞ በሀገሩ ለመኖር ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ትግል አድርጓል፡ ‘የአሞራ ቤቱ ከዋርካ፣ የኢስላም ሀገሩ መካ’ ልባል አይገባኝም’ በማለት ለመብቱ መከበር ብዙ ደክሟል። ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በወጣበት ወቅትም በብዙሀን ዘንድ የመብት መከበር ጉዳይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈታል የሚል ተስፋ ተሰንቆም ነበር። ኢትዮጵያ በሕገ-መንግስቷ የሁሉንም ሀይማኖቶች እኩልነት በማወጅ፣ መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገባም ብላ በመደንገግ የተሰነቀውን ተስፋ አለመለመችው። በተግባር ደረጃ ግን ከተለያየ የሀይማኖት ሰዎች ዘንድ መንግስት በሀይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እየገባ ነው፣ እጁን ከሀይማኖታችን ላይ ያንሳልን። ወ.ዘ.ተ. የሚሉ ጥያቄዎች በየጊዜው እየተነሱና በመንግስት አካላት እየታፈኑ ዘልቀዋል።
የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ሁኔታ በዚህ ጥያቄ በመጠየቅ እና በመንግስት አካላት ጥያቄዎችን በመደፍጠጥ ነገሮች ሲመላለሱ ከቆዩ በኋላ ሙስሊሙ ሕብረተሰብ መሰረታዊ ጥያቄዎቹን በመወከሉት ልጆቹ አማካኝነት በተደራጀ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ  አቀረበ። እነዚህ ወኪሎችም መንግስት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን መፍትሄ ለማግኘት ጥያቄያቸውን ይዘው ከመንግሰት አካላት ጋር ሲደራደሩ ቆዩ፡፡
በአጋጣሚ ሆኖ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ጥቅም ላይ በሰፊው መዋል በጀመረበት ወቅት ላይ ነበርና ‘የሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ’ የሙስሊሙን ጥያቄዎች ለተለያዩ  አካላላት በሰላማዊ መንገድ ያቀረበው። እንግዲህ ከዛን ጊዜ ወዲህ ነው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ መበርታት የጀመረው።
ሕጉ ጥቃቱን የጀመረው የፌ/ዓ/ሕግ በክስ መዝገብ ቁጥር 122/05 በ19/02/2005 ዓ.ም. 
  1. አቡበከር አህመድ ሙሐመድ
  2. አህመዲን ጀበል
  3. መከተ ሙሄ መኮንን
  4. ካሚል ሸምሱ ሲራጅ
  5. በድሩ ሁሴን ኑርሁሴን
  6. ያሲን ኑሩ ኢሳ
  7. ሳቢር ይርጉ ማንደፍሮ
  8. መሀመድ አባተ ተሰማ
  9. አህመድ ሙስጠፋ ሀቢብ
  10. ሙራድ ሽኩር ጀማል
  11. አቡበከር አለሙ ሙሔ 
  12. ኑሩ ቱርኪ ኑሩ
  13. ባህሩ ዑመር ሽኩር
  14. ሙኒር ሁሴን ሀሰን
  15. ሰዒድ አሉ ጀውሀር
  16. ዩሱፍ ጌታቸው
  17. ሙባረክ አደም ጌቱ
  18. ካሊድ ኢብራሒም ባልቻ
  19. አብዱረዛቅ አክመል ሀሰን
  20. አሊ መኪ በድሩና
  21. አብሩራህማን ኡስማን ከሊል
ላይ የፀረ-ሽብር ሕጉን አንቀፅ 3 (1, 2, 4 እና 6) እና አንቀፅ 4 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በማለት ክስ ባቀረበበት ወቅት ሲሆን በክሱም ‘የሙስሊሞች የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ’ የተባለ ‘የሽብርተኛ ድርጅት’ በመመስረት’ በማለት ‘ኮሚቴውን’ ‘የሽብርተኛ ድርጅት’ በማለት ሰይሞ ሌሎች ሙስሊም ጋዜጠኖችንና የሀይማኖት ሰዎች ‘የሽብርተኛ ድርጅቱ’ አካላት በማድረግ ክስ አቅርቦ በሒደት ላይ ይገኛል።
በጣም አስደንጋጡ እና አሳዛኙ ጉዳይ ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙ በሰፊ ድጋፍ ይወክሉኛል በማለት የመረጣቸውን ሰዎች ‘አሸባሪ’ በማለት የመሰረቱትን ኮሚቴ ደግሞ ‘የሽብር ድርጅት’ ከማለት ባለፈ በአጠቃላይ ሙስሊሙ እያደረገ ያለውን ሰላማዊና በአፍሪካ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴዎች ትልቅ ስኬት እና አብነት እንደሆነ Rene Lefortን ጨምሮ ታላላቅ ምሁራን እየገለፁት ያሉትን እንቅስቃሴ በመንግስት አካላት ከአለማቀፉ የሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ለማገናኘት እየተደረገ ያለው ሙከራ፣ ሙስሊሙን የኢትዮጵያዊነት ጠላት አድርጎ የመሳል ሁኔታ (ባንዲራ አቃጠለ ወ.ዘ.ተ. እያሉ)... ወ.ዘ.ተ. መኖሩ ነው። የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በቀጥታ እያጠቃ ነው ብለን ለመደምደም ‘የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ’ አባላት መታሰር ብቻ በቂ ሊሆን አይችልምና ተጨማሪ ማስረጃዎችን መፈለግ ያሻል። ስለዚህም እነሆ: -
የፌደራል ዓቃቢ ሕግ በመዝገብ ቁጥር 225/06 በ25/09/06 ዓ.ም. ባቀረበው ‘የሽብርተኝነት’ ወንጀል ክስ ‘የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ከተባለ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላችሁ’ በማለት
  1. ኤልያስ ከድር ሽኩር
  2. ሙባረክ ከድር ሀሰን
  3. ቶፊቅ መሀመድ ዑመር
  4. ፈይሰል አርጋው ኡመር
  5. አብዱልመጅድ አብዱልከሪም
  6. እስማኤል ሙስጠፋ ሀሰን
  7. ሬድዋን አብደላ አህመድ
  8. አንዋር ሱልጣን መሀመድ
  9. አብዱላዚዝ ፋቱደን በድሩደን
  10. ዳፋር ደጋ ሀሰን
  11. ፋሩቅ ሰዒድ አብዶ
  12. መሪማ ሀያቱ ዑመር
  13. መሀመድ ዓሊ ሀሰን
  14. መሀመድ አይለየን ገማ
  15. አቡበክር ሰልማን ሙላና
  16. ሙዓዝ ሙደስር አወል
የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 7(1) ተጠቅሶባቸው ክሳቸውን በእስር ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ በየ/ፌ/ዓ/ሕ/መ/ቁ 216/06 በተከፈተ ሌላ ክስ
  1. አብዱልአዚዝ ጀማል አብዱ
  2. ጅብሪል ይመር አበጋዝ
  3. ስዑድ ሙሳ ሁሴን
  4. ሀያት አህመድ ረዲ
  5. ሳላሀዲን ሙሀመድ አህመድ
የተባሉ ግለሰቦችም የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 7(1) ተላልፈዋል፤ ‘ራሱን የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በማለት ከሰየመው የሽብርተኛ ድርጅት ጋርም ግንኙነት አላቸው’ በማለት ተመልክቷል።
በዚህ ብቻ አያበቃም። የፌደራል ዓቃቢ ሕግ በመዝገብ ቁጥር 164/06 ባቀረበው ‘የሽብርተኝነት ድርጊት ወንጀል’ ክስ ደግሞ
  1. አህመድ ኢድሪስ ገበየሁ
  2. አንዋር ኡመር ሰዒድ
  3. ሷሊህ መሀመድ አብዱ
  4. አደም አራጋው አህመድ
  5. አብዱራህማን እሸቱ መሀመድ
  6. ኢብራሒም ሙሔ ይማም
  7. ዑመር ሁሴን አህመድ
  8. ይመር ሁሴን ሞላ
  9. ሙባረክ ይመር አየለ
  10. እስማኤል ሀሰን ይመር
  11. ከማል ሁሴን አህመድ
  12. አብዱ ሀሰን መሀመድ
  13. አህመድ ጀማል ሰይድ
  14. ሙሀመድ ዩሱፍ መሀመድ
ላይ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀፅ 3(1)፣ (6) እና (7) በመጥቀስ የአሸባሪነት ክሶችን አቅርቦባቸዋል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ሙስሊም ሆኖ መታሰር የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን አንቀፆች የሚያስጠቅስ እስኪመስል ድረስ ሕጉ የሙስሊሙን ሕይወት አክብዶታል። የታሪካዊ ጭቆናዎች ሰለባ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም አሁን ደግሞ ‘የሽብር ምህዳሩን’ አጣቦት ይገኛል። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ተግባራዊነት እና ሰለባ እያደረጋቸው ያሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ስንመለከት ‘ሕጉ ኢስላም ጠል (Islamo-Phobic) ነው’ እንድንል ያደፋፍረናል። አሁን ለዚህ ጽሁፍ ማጣቀሻነት ሲባል የተጠቀምንባቸውን የክስ ፋይሎች ስንመለከት አንኳን 48 ሙስሊሞች በተለያየ የክስ ፋይል ተከሰው እናገኛለን፡፡
(ማስታወሻ: ሁሉም በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር የተጠቀሱ የክስ መዝገቦች በቀጠሮ  ላይ ያሉና የመጨረሻ ፍርድ ያላገኙ መሆናቸውን ልብ ይሏል።)

ዴሞክራሲን ‘ያንበረከከው’ ሕግ 
 ኢህአዴግ ስልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሲወደስባቸው ከነበሩት ተግባራት ዋነኞቹ ነፃ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ፈቃድ መስጠቱ እና ለነፃ የፕሬስ ተቋማት እውቅና መስጠቱ የሚጠቀሱ ናቸው። በሒደት በተለይም ምርጫ 97ን ተከትሎ ግን ገዢው ፓርቲ ነፃ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የግል ፕሬሱን በመያዶች ሕግ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ እንዲሁም የፕሬስ አዋጅ በማውጣት ገዢው ፓርቲ የተወደሰባቸውን ተግባራት አንድ ባንድ መደፍጠጥ ጀመረ። ከሁሉም አስከፊውና ሁሉንም ከመንግስት መዋቅር ውጭ ያሉ ተቋማትን በአንድ ላይ ዝም ያስባለው እና ትንሽ እንቅስቃሴ በታየ ቁጥር ብቅ  ያለ ወደ እስር የሚወረውረው በ2001 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ነው።

በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ የወሰኑ ግለሰቦች ‘ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አድርጋችኋል’ በሚል ምክንያት (pretext) የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የተመዘዘባቸው እና እስከ እድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው እንደ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ ያሉ ግለሰቦች በፊተኛው ረድፍ እናገኛለን። የጋዜጠኝነት የሙያ ግዴታቸውን እየተወጡ እያሉ በመሀሉ ‘አሸባሪዎች’ ናችሁ ተብለው በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የተወነጀሉትን እንደ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬ ያሉ ጋዜጠኞችን እናገኛለን። ክሳቸው በሒደት ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን ጉዳይ መመልከታችን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ማንን ለማጥቃት የተመዘዘ እንደሆነ በግልፅ ያስረዳናል።

የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ብዙም ባልተለመደ መልኩ ፖሊስ በመጀመሪያ በመደበኛ የወንጀል ሕግ አግባብ መሰረት ‘ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱንና ሕገ-መንግስቱን በሀይል ለማፍረስ በመሞከር ወንጀል ሙከራ’ ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት ስድስት ጦማሪያንንና (ማለትም በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ ዘላለም ክብረት እና አቤል ዋበላ) እንዲሁም ሶስት ጋዜጠኞችን (ማለትም አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬና ተስፋለም ወ/የስ) ከሶ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ ቢሔድም የመደበኛው የወንጀል ሕግ ስነስርዓቶች አልተመቹትምና የሁሉም ማጥቂያ ወደሆነው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ጉዳዩን በመውሰድ እና ጦማሪ ሶልያና ሽመልስን በመጨመር በ10 ተከሳሾች ላይ በቀን 09/11/2006 በፌ/ዓ/ሕ/መ/ቁ 05/07 በተዘጋጀ ክስ “ግንቦት ሰባት የተባለ የሽብርተኛ ድርጅትን መመሪያ በመቀበል፣ ኦነግ የተባለ የሽብርተኛ ድርጅትን መመሪያ በመቀበል እንዲሁም በክሱ ላይ ስሙ ያልተጠቀሰ (ምናልባትም ዞን 9) የሽብርተኛ ድርጅትን በማቋቋም ‘የሽብርተኝነት ድርጊቶችን’ (ድርጊቶቹ የትኞቹ እንደሆኑ በክሱ አልተጠቀሰም) ለመፈፀም ሲያሴሩ፣ ሲያቅዱ፣ ሲዘጋጁና ሲያነሳሱ ተይዘዋል።” በማለት ክስ አቅርቧል። የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉም የተለመደውን ጋዜጠኞችን የማሰር ሒደቱን አጠናክሮ በመቀጠል ብዙም ያልተለመደውን ጡመራንም (Blogging) አካቶ፣ በነፃነት የተደራጀ ማንኛውም ዓይነት ስብስብ ‘የሽብርተኛ ስብስብ ነው’ ወደ ሚል አስደንጋጭ ደረጃ ከፍ አድርጎታል።

ምናልባትም በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች ላይ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የማይደርስ የሚመስለው ካለ ቀጣዮቹ ተጠቂዎች (victims) ጥሩ ማስረጃዎች ይሆኑታል። የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን፥ ሰንዓ ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው በተሰጡበት ቅፅበት ከተለያዩ  ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ አባላትን በሽብርተኝነት ድርጊት ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት ፖሊስ አስሮ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት አብርሀ ደስታ ከአረና ለፍትህና ለነፃነት የፖለቲካ ፓርቲ፣ ሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ ከአንድነቱ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የሺዋስ ወንድማገኝ ከሰማያዊ ፓርቲ በማሰር በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አማካኝነት ከሶ  ይህ ፅሁፍ በተፃፈበት ወቅት ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ማረፊያ ቤት አስሯቸው ይገኛል። በተጨማሪም ቀደም ብለው ተከሰው በፌደራል የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) የሚገኙትን አቶ አፍሪካ ከበደ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌስ) እንዲሁም አቶ ታምራት ታዬ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አብረን ስናየው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በሀገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙትን ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠላትነት በመቁጠር ከሁሉም ፓርቲዎች የተለያዩ ግለሰቦችን የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ሰለባ (booty) አድርጓል።
በአጠቃላይ ለዴሞክራሲ ማደግ ዋነኛ መሰረቶች የሆኑትን ነፃ ፕሬስ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ነፃ ስብስቦችንና ተቋማትን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ድል አድርጓቸዋል። ዴሞክራሲንም አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ቦታ የሌለው ሀሳብ እንደሆነ በተግባር (by implication) ተበይኗል።

የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ የበላይነት (Rule of Anti-Terrorism Law)

የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ እያዳረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ከነሰለባዎቹ ማንነት በዚህ ፅሁፍ ማቅረባችን የችግሩ መነሻና መድረሻ ሕጉ ነው በሚል አይደለም። ይልቁንም የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የአምባገነንነት መገለጫ (An epitome of dictatorship) ነው ወደሚል አቅጣጫ ስለሚያመራንም ጭምር ነው። ከሕጉ ጀርባ ዴሞክራሲያዊ ሕልምን የመጨፍለቅ ዓላማ ያለው አካል መሳሪያ ሆኖ የቀረበ አዋጅ ነው።
ሕጉ የማያንኳኳው ቤት አይኖርም። ከሕጉ ‘ባለቤት’ ውጭ። በአፈፃፀሙም ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት ከሳሹ መንግስት በፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ አማካኝነት መክሰስ ይችላል ወደሚል የፍርድ ቤት ትርጉም ደርሰናል። ከሕጉ አፈፃፀሙ ይከፋል። የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ‘ወንጀሉ እኮ ሽብር ነው’ በሚል አስገራሚ ምክንያት ወደጎን ተደርጓል። አቃቢ ሕግ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ እያቀረባቸው ያሉት ክሶች በሙሉ በመደበኛው የወንጀል ሕግ የተሸፈኑ ቢሆንም ‘ጉዳዩ  እኮ ሽብርተኝነት ነው’ በሚል የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አድማሱን በማስፋት መብቶቸን ለመጣስ የተለየ የህግ ማእቀፍ በመፍጠር ግዳይ መጣሉን ቀጥሎበታል።
በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ 36(1) ላይ እንዲህ ተደንግጓል: -
“ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማናቸውም ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም የአሰራር ልማድ በዚህ አዋጅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።”
ይህ ተራ አዋጅ አይደለምና ከላይ በአዋጁ አንቀፅ የተገለፀው ‘ማናቸውም’ የሚል ቃል በእርግጥም ሕገ-መንግስቱንም ይጨምራል። ከሕገ-መንግስት የበላይነት ወደ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ የበላይነት የተሸጋገረች ኢትዮጵያ! በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ እየተመራችም የ2007 ዓ.ም. አምስተኛውን ሀገራዊ ‘ምርጫን’ ‘ፍትሀዊና ሰላማዊ’ በሆነ መንገድ ለማከናወን ደፋ ቀና እያለች ሲሆን ጥያቄው ደግሞ ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ‘የሽብርተኛ ድርጅትነት’ ይረጋገጥ ይሆን? የሚለው ነው።
_______________________________________________________________________________________________________________________ 

[1] በሰኔ 2006 ዓ.ም. ከሞያሌ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አባላት ታፍኖ ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ የሚገኘው የ14 ዓመት ልጅ ሲሆን። ፖሊስም ‘የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ከተባለ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለህ’ በማለት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀበት በእስር ላይ ይገኛል።


[2] ከፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የመጀመሪያ ሰለባዎች አንዱ የሆኑት አቶ ፅጌ ገብረማርያም አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አባት ሲሆኑ፤ ልጃቸውን ለመጠየቅ ወደ እንግሊዝ ሀገር በሔዱበት ጉዳይ ‘ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አድርገዋል’ ተብለው የ8 ዓመት ፍርድ በተፈረደባቸው ወቅት የ80 ዓመት አዛውንት ነበሩ።

[3] ይሄን ስምን ቀይሮ አንድን ጉዳይ የማቅረብ አካሄድ የወሰድነው William Easterly የተባሉ ምሁር ‘The Tyranny of Experts’ ባሉት መፅሐፋቸው Uganda ውስጥ የደረሰን የአካባቢ ውድመት America, Ohio ውስጥ እንደደረሰ አድርገው ለአንባብያን ይገባ ዘንድ ካቀረቡበት አካሄድ ነው።

[4] የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ በአሁኑ ወቅት ካሉት 20 ችሎቶች ውስጥ ሁለቱ፣ ማለትም አራተኛ እና አስራ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎቶች ‘በፀረ-ሽብርተኝነት’ ሕጉ አማካኝነት የሚቀርቡ ክሶችን የሚመለከቱ ሲሆን በችሎቶቹ የሚሰየሙት ዳኞችም በየጊዜው ይቀያየራሉ። ነገር ግን በችሎቶቹ በቋሚነት ተሰይመው ‘የሽብርተኝነት’ ክሶችን እየተመለከቱ ያሉት ዳኞች ባህሩ ዳርቻ፣ ብስራት ተህልቁ፣ ቀናቴ ሆና፣ ሸለመ በቀለ፣ ወ.ዘ.ተ.