Saturday, May 13, 2017

ሐሳቤን በመግለጼ የለወጥኩት…?

በበፍቃዱ ዘ ኃይሉ

"ለምን ትጽፋለህ?" በይፋ "በብዕር ታጋይ" ከሆንኩ ወዲህ በተደጋጋሚ የሚገጥመኝ ጥያቄ ነው። አንዳንዶች፣ ዓላማዬን ለማወቅ፤ ሌሎች፣ መራር ጦሱን እንዳልጎነጭ ለማሳሰብ ነው ይህን መጠየቃቸው። እኔም ለገዛ ራሴ ተመሳሳይ ጥያቄ፣ በተደጋጋሚ ማቅረቤ አልቀረም። የምጽፈው ለውጥ ለማምጣት ነው። ‘ምን ዓይነት ለውጥ አመጣ[ለ]ሁ?’ የሚለውን ወረድ ብለን መልስ እናገኝለታለን።

ከዚያ በፊት ግን ከእስር ቤት አሾልኬ ከኔ በፊት ካወጣኋቸው ቁዘማዎቼ በአንዱ ላይ «ለምን እጽፋለሁ?»  በሚል ንዑስ ርዕስ ያሰፈርኩትን በድጋሚ ላካፍላችሁ፦

“ጆርጅ ኦርዌል «ገንዘብ ለማግኘት» ከሚደረግ ጥረት ውጪ ጸሐፍት የሚጽፉባቸውን «አራት ትላልቅ መግፍኤዎችን» እንደዘረዘረ አንድ መጽሐፍ ላይ አነበብኩ፡፡ እነዚህ መግፍኤዎች ከተራ ጉራ (‘sheer Egoism’ ማለትም ጎበዝ መስሎ ለመታየት፣ ስለራስ እንዲወራ፣ ወይም ከሞት በኋላ ለመታወስ ለመሳሰሉት) ከመጻፍ ጀምሮ እስከ ፖለቲካዊ ዒላማ (Political purpose ወይም ዓለምን ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ የመግፋት ዕቅድ) ድረስ ሊዘልቁ ይችላሉ። ሌሎቹ መግፍኤዎች ለጥበባዊ ግብ (aesthetic enthusiasm ማለትም ዋጋ የሚሰጡትንና ሰዎች እንዲሰሙት የሚፈልጉትን ነገር በጥበባዊ አቀራረብ የማጋራት ጉጉት)፤ ለታሪካዊ ጥቅም (historical impulse ወይም ስለታሪክ እውነቱን የመለየትና ለወደፊቱ የማስቀመጥ ግብ) የሚደረጉ የምኞት መጻፎች ናቸው፡፡

“የእኔም የመጻፍ አባዜ (ልበለው?) ከእነዚህ የኦርዌል መግፍኤዎች አንዱ ወይም ከፊሉ ወይም ሁሉም ወይም ማንኛውም ሊሆን ይችላሉ፡፡ ወይም ደሞ ነብይ መኮንን በግጥም እንዳለው «ስለሚያመኝና መጻፍ ስለሚያክመኝ» ይሆናል፡፡ እንድ ነገር ግን አምናለሁ፡፡ የቮልቴርን አፍ ተውሼ እምነቴን ልናገር፦ «we can, by speech and pen, make men more enlightened and better» (በንግግር እና ብዕር ሰዎች የነቁና የተሻሉ እንዲሆኑ ማድረግ እንችላለን፡፡)”

‘ጽሑፍ ለለውጥ’(?)

ጸሐፊነት - በተለይ የትችት ጸሐፊነት በሁለት በኩል በተሳለ ቢላዋ እንደመጠቀም ነው። ሌሎችን በሚተቹበት መሥፈርት መልሶ መተቸት ይመጣል። ይህ የጸሐፊነት መንታ ስለት ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የበረታ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ‘ጸሐፊነት’ ቀላል ነው። ነገር ግን እንደሕትመት ሚዲያ የአንድ ወገን የሐሳብ ፍሰት የሚስተናገድበት አይደለም። በማኅበራዊ ሚዲያ አንድ ሰው ለጻፈው አንድ አከራካሪ ሐሳብ እልፍ ምላሽ ይቀበላል። ሌላው ቀርቶ፣ ዛሬ ዛሬ መደበኛው ሚዲያ ላይ ለተስተናገደ አንድ ሐሳብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ (እንደሐሳቡ ሸንቋጭነት) ብዙ ምላሾችን ማንበብ የተለመደ ነው። ይህ ትክክለኛው የሕዝባዊ ተዋስኦ (discourse) ባሕሪ ነው። ከተቻለ - እውነት፣ ካልተቻለ - ስምምነት በዚህ ዓይነቱ የሐሳቦች ፍጭት ነው የሚወለደው።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መጻፍ ስጀምር ያሰፈርኳቸውን በርካታ ሐሳቦችን አሁን ሌላ ሰው ጽፏቸው ባይ በተቃራኒው የምሟገታቸው ዓይነት ሁነዋል። ይህ የምኮራበት ተራማጅነት ነው። በዓመታት የጦማሪነት ሒደት ውስጥ በእጅጉ የለወጥኩት የመጀመሪያው ሰው እኔን - ራሴን ነው።

በፊት፣ በፊት በሐሳቤ የመጣውን ነገር ሁሉ እንደወረደ ነበር የምጽፈው። ነገር ግን በወቅቱ እርግጠኛ የሆንኩባቸው ሐሳቦች በቀላል መከራከሪያ ፉርሽ ሲደ:ረጉብኝ፣ ሁሌም ለምጽፈው ጉዳይ ተቃራኒ ሞጋች ሐሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳልወድ በግዴ ማገናዘብ ጀመርኩ። ከመጻፌ በፊት ስለምጽፈው ነገር የማውቀው ምን እንደሆነ? የምቃወመው/የምደግፈው [ለ]ምን እንደሆነ? ራሴን መጠየቅ፣ በቅርብ የማገኘውን መረጃ ማገላበጥ እና ሙሉ እርግጠኛ ላልሆንኩባቸው ሐሳቦች አንባቢ እንዲሞላልኝ ክፍተት መተው ጀመርኩ። ይህ ሒደት የትኛውም ዩንቨርስቲ  በቀላሉ የማያስተምረኝ ራስን ደግሞ፣ ደጋግሞ የመቅረፅ ሒደት ነው። ሐሳቤን በመግለጼ ያገኘሁት ትልቁ ትሩፋቴ ይኸው ነው።

‘ጽሑፍ ለነውጥ’(?)

የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ በሃይማኖት፣ ብሔር እና ፖለቲካ ጉዳዮች "የጥላቻ መድረክ" እንደሆነ ብዙዎች ይገምታሉ። ነገር ግን እውነታው ተቃራኒውን እንደሆነ ነው አንድ ጥናት የሚጠቁመን። በኦክስፎርድ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ከ2007 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው "የጥላቻ" ወይም "አደገኛ" ንግግሮች አንድ በመቶ እንኳ አይሞሉም። ይልቁንም ከአጥኚዎቹ አንዱ የሆኑት Iginio Gagliardone እንደሚገልጹት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ትልቁ ችግር ‘ለቅራኔ መሔድ’ (going against) ነው።

አጥኚው እንደሚሉት “Statements that go against are statements attacking another speaker or a specific group by belittling, provoking, teasing them maliciously, or explicitly threatening them.” («‘ለቅራኔ መሔድ’ የሚለው ምደባ ውስጥ የሚገቡ ንግግሮች ሌላኛውን ተናጋሪ ወይም ቡድን የሚያንኳስሱ፣ በነገር የሚሸነቁጡ፣ በሐሰት የሚወነጅሉ፣ ወይም ደግሞ በዛቻ የሚያስፈራሩ ናቸው።») የሐሳብ ነጻነትን የሚያፍነው መንግሥት ብቻ አይደለም። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰበሰበው ማኅበረሰብ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚያፍንበት መንገድ ይህ ‘ለቅራኔ የመሔድ’ ልንለው የምንችለው ባሕል ነው።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ‘ለቅራኔ መሔድ’ የሚያጠፋው ሁለት ነው፤ ፩ - ራሱን ለቅራኔ ሒያጁን ከሌሎች ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ እንጂ ለተዋስኦ የሚበጅ ሐሳብ እንዳያበረክት ያደርገዋል፣ ፪ - ለቅራኔ የተሔደበትን ጸሐፊ በውይይቱ እንዲቀጥል ወይም ከውይይቱ እንዲማር ተጨማሪ ዕድል አይሰጠውም። ለቅራኔ መሔድ የመጨረሻ ግቡ የተለየ ሐሳብ ያለውን ማባረር እና ተመሳሳይ ሐሳብ የሚያራምዱ እርስ በርስ የማይዳረሱ (mutually exclusive) ብዙ ክበቦችን መፍጠር ነው።

እያንዳንዱ ችግር መፍትሔ ያስተምራል። ከላይ የጠቀስኩትን ‘ለቅራኔ መሔድ’ አጉል ልመድ በአጭሩ ለመክላት ‘በጨዋነት በመጻፍ፣ ከሰዎች እና ቡድኖች ይልቅ ሐሳቦች ላይ በማተኮር፣ ትችቶች ሲጻፉ የሚተ:ቸውን አካል ሳይቀር ለመልስ እና ለውይይት ተሳታፊ የሚሆንበትን ዘለፋ አልባ አጻጻፍ ስልት መከተል’ ይቻላል።

‘ጽሑፍ ለእስር’(?)

ሁለት ግዜ ታስሬያለሁ -- መጀመሪያ ለ18 ወራት ዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ በጻፍኩት "በሽብር ተጠርጥሬ"፣ ቀጥሎ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ላይ ባወራሁት "የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን አጥላልተሃል" ተብዬ። ሁለቱንም የታሰርኩት ሐሳቤን በነጻነት በመግለጼ ነው። እነዚህ ክስተቶች መጻፍ እንደዋዛ ስጀምር ወደ አላሰብኩት አቅጣጫ ሕይወቴን ቀይሰውታል። ነገር ግን እስሬ የመጣው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ጥቅም ሳላውቅ ወይም በቅጡ ሳላጣምም ቢሆን ኖሮ ዝም ልል እችል ነበር። ነገር ግን ከላይ እንደገለጽኩት የጽሑፎቼ የመጀመሪያ ተጠቃሚ እኔው ራሴ ነኝ። በራሴ መጨከን አልችልም።

ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ማለት ለኔ መተንፈስ እንደማለት ነው። ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦች፣ ዓለም በጥቅሉ በተፈጥሮ ላይ የምትሠለጥነው ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ሲቻል ብቻ ነው። ሐሳብ በነጻነት የማይገልጹበት ፀጥታ እንጂ ሠላም የለም፤ ኩርፊያ እንጂ እርቅ የለም፤ ድንቁርና እንጂ ዕውቀት የለም።

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት ለዘላለም ይኑር!

ስለራስ መብት መሠለፍ

በዘላለም ክብረት

አምስት ዓመት ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ከአንድ ኢትዮጵያዊ አማካኝ ዕድሜ ወደ አንድ አስረኛ ገደማ መሆኑ ነው፡፡ የሕይወትን አንድ አስረኛ ዕድሜ ከሚመስሉ ወዳጆች ጋር ለአንድ ‹‹መልካም ነው›› ብዬ ለማስበው ተግባር መሰለፍ ዕድልም፤ ዕዳም ነው፡፡ የውጥኑ መሳካት ዕድሉ ሲሆን፤ መክሸፉ ደግሞ ዕዳው ነው፡፡ በተለይ እንደኛ አገር መንግሰት ዜጎቹን ‹‹እኔኑ ካልመሰላችሁ›› እያለ በሚያሳድድበት አገር፤ ትንንሽ የደቦ ውጥኖች ሲከሽፉ እያየ ላደገ ሰው የመክሸፍ ስጋት ጋር ሁሌም መኖር የዕየለት እውነታ ነው፡፡

ዞን ዘጠኝን ስንመሰረት ሁሉም የሚሰጋው የመሳደድ፣ የመታሰር፣ ሲብስም ከፍ ያለው ሞት ድረስ የሚያስኬድ መንገድ እንደጀመርን እኔን ጨምሮ የአብዛኞቻችን ስሜት ነበር፡፡ ስጋቱን ሁሉ የሚያጠፋ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ሁሌም ራሴን በመጠየቅ ግን ስጋትን አባርር ነበር፤ ‹‹ሌሎች ሰዎች ለፍተው ባስረከቡኝ ዓለም እንዲሁ ኖሬ መሞት እንዴት ይቻለኛል?›› የምትል ጥያቄ፡፡ ለዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ፤

‹‹እኔም የድርሻዬን መሞከር አለብኝ›› የሚል የሁልጊዜም ሐሳብ ነው፡፡

ይህ ማለት ያለውን ፈተና ማቃለል አይደለም፡፡

ዞን ዘጠኝ ከአምስት ዓመታት በፊት ሲመሰረት የነበረው የነፃ ሐሳብ ገበያ ከሦስት ዓመታት በፊት ለእስርና ስደት ስንዳረግ ከነበረው ገበያ በእጅጉ የተሻለ፣ እንዲሁም ሰፊና ርካሽ ነበር፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በታሰርንበት እና ለስደት በተዳረግንበት ወቅት የነበረው የአገራችን የሐሳብ ገበያ ዛሬ ካለው (አለ ከተባለ) የሐሳብ ገበያ እጅግ ርካሽና ሸማችን የማይጎዳ ነበር፡፡ እያንዳንዱ አዲስ ቀናት የበለጠ ጭቆናን እና የበለጠ ስጋትን ይዘው የሚመጡ እንደሆኑ ማየት የአምስት ዓመታት ትዝብት ነበር፡፡ በዋናነት በስርዓቱ ፍፁም የስልጣን ቀናኢነትና ‹‹የሚቃወመኝ አይኑር›› ባይነት፤ ማሕበራዊ ሚዲያዎች ለሁሉም ሰው እኩል የጋራ ዕድል የሚፈጥሩ የሐሳብ ገበያ ሕግ (rules of engagement) የማይገዛቸው መድረኮች በመሆናቸው ምክንያት፤ እንዲሁም የማሕበራዊ ድረ ገፆች ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣት ማሕበራዊ ድረ ገፆች የሚታሰበውን ያክል የገንቢ ውይይት መድረኮች እንዳይኖሩ አድርጓቸዋል ብል ይህ ድምዳሜ የእኔ ብቻ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን እንደኛ ላለ ሁሉም ነገር በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር ለሚዳክር አገር፤ ሐሳብ ያለው ሁሉ ወጥቶ ሐሳቡን የሚሸጥበት፤ እንዲሁም ከገበያ ያገኝውን የሚገዛበት ትንሽ ቀዳዳም መገኝቱ ደግሞ ትልቅ ዕድል ነው፡፡

ዞን ዘጠኝ በስርዓቱ የተከፈተችለትን ትንሽ ቀዳዳ ትንሽ የተደራጀ በሚመስል መልኩ፤ መሪ እና ተመሪ የሌለበት መዋቅር በመጠቀም ሐሳብን ለገበያ ለማቅረብ የተደረገ ትንሽ፤ ነገር ግን የሚያድግ ሙከራ ነው፡፡ ሁላችንም የምንጽፍበት ምክንያት ብዙና የተለያየ ነው፡፡ እኛ ያገኝነውን እድል ያላገኙ ዜጎች ወደፊት እንዲመጡ ለማስቻል የሚጽፍ ይኖራል፤ የመጻፍ ሱሳችንን ለማብረድ የምንጽፍ እንኖራለን ወዘተ፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ከማንም ምንም ሳንጠብቅ በበጎ ገብነት (voluntarily) መስራታችን ትልቁ ስኬት አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ ለገዥው ሥርዓት የራሱን ሕገ መንግስት እንዲከብር ነበር ዋነኛ ጥያቄያችንና የሥራዎቻችን መሰረት፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ድምፅ ራሱን በሰከነና በሚያግባባ ሁኔታ ይገልፅ ዘንድ ፍላጎታችን ነበር/ነውም፡፡

በዚህ ሁሉ ጊዜ ከመንገድ ላይ ታፍኖ ከመደብደብ ጀምሮ ራሳችንን ሳንሱር እንድናደርግ በመንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲዛትብን ‹‹ይህችም ሥራ ተብላ ሊያስሩን? አያደርጉትም›› በሚል የራስ ሽንገላና ቸልተኝነት አልፈናል፡፡

‹‹ግን መጻፉ ምን ይጠቅማል?››

የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ በተለይም መፃፍ ጦስ ይዞ በሚመጣበት በእኛ አይነት ያልታደለ አገር ይህ ጥያቄ አሁንም አሁንም መላልሶ የሚነሳ ነው፡፡ ብዙ መልስ ከብዙ አቅጣጫ መምጣቱም ያየነው የታዘብነው እውነት ነው፡፡ ‹‹የምጽፈው የድምፅ አልባው ሕዝብ ልሳን ለመሆን ነው›› ሲባል በብዛት እሰማለሁ/አነባለሁ፡፡ ይህ ግን ራስን የሕዝብ ተጠሪ አድርጎ መሾም ከመሆኑም ባለፈ፤ አሩንዳቲ ሮይ እንደምትለን "እንዳይናገር የተሸበበ እንጅ ድምፅ አልባ የሚባል ሕዝብ በሌለበት - 'There's really no such thing as the 'voiceless'. There are only the deliberately silenced, or the preferably unheard"፤ የሌለውን ለመወከል መሞከር ነው የሚሆነው፡፡ ለእኔ የመጦመር/መፃፌ ዋነኛ መነሻ የራሴው ድምጽ መታፈኑ ነው፡፡ በሌላ አባባል የምጽፈው ለሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ሳይኮሎጅስቶች ‘Therapeutic Writing’ ከሚሉት ጋር የተቀራረበ፤ ነገር ግን ይሄኛው ራስን በራስ የማከም ሒደት ነው፡፡ የውስጤን የመታፈን ሕመም በመጻፍ የማክምበት፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያቴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዝነኛ እየሆነ ከመጣው ‘Write for Right’ ጋር የተቀራረበ ምከንያት ነው፡፡ ስለመብት መፃፍ፡፡ ስለራሴ መብት፡፡ ሁለቱን አያይዤ ስጠቀልለው ስለራሴ መብት በመጻፍ ራሴን ማከም የመጻፌ ዋነኛ መግፍኤ ነው፡፡

ስለ መብት መጻፍ

‹‹መብት›› በጣም በተደጋጋሚ የሚነገርለት የሚጻፍለት ጉዳይ ነው፡፡ አማርኛው (ከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት) መብትን ‹‹ሙሉ የትዕዛዝ ሥልጣን፣ ሙሉ ሹመት ሙሉ ሥልጣን፣ ተሹሞ ማዘዝ ከኹሉ በላይ መሠልጠን›› ብሎ ነገሩን ወደሌላ ይወስደዋል፡፡ እኔ መብት እያልኩ ስጽፍና ስኖር በራሴ ላይ መሰልጠኑን ማለቴ ነው፡፡ በራሴ ፍላጎት ላይ “Your liberty to swing your fist ends just where my nose begins” በሚሉት ብሒል ላይ ተመስርቼ፤ የማንንም አፍንጫ ሳልነካ እጄን መዘርጋቱን ነው ‹መብት› ብዬ የምጽፍለት፤ የምኖርበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ላይ ነው መንግስት ጣልቃ ገብቶ ‹‹መብትህን እኔ ሰፍሬ ካልሰጠውህ›› የሚለው፡፡

በእስር ወቅት ለምርመራ ተጠርቼ በቀረብኩበት የመጀመሪያው ቀን አንዲት መርማሪ ‹‹መብት ››የሚባለው ጉዳይ ምን ድረስ እንደሆነ ያ(ስ)ረዱኝን መጥቀሱ እዚህ ላይ ተገቢ ነው፡፡ መርማሪዋ፤ ‹‹ስማ አንተ አንድ ግለሰብ ነህ፡፡ ይሄን ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ እኛ የሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ደሕንነት ነው የሚያሳስበን፡፡ ለሰማኒያ ሚሊዮኑ ሕዝባችን ሲባል የአንተ የአንድ ሰው መበት መጣስ የሚያሳስበን ጉዳይ እንዳይመስልህ፡፡ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ልናደርግ እንችላለን፡፡›› አሉኝ፡፡ ከባድ ዛቻ ነው፡፡ ግን ደግሞ መንግስት ስለዜጎቹ ምን እንደሚያስብ ገላጭ እውነት፡፡ እንግዲህ ስለመብት መጻፍ ያልኩት ይሄኑ ነው፡፡ ሰው በመሆኔ ያገኝሁትን ክብር (privilege) ራሱን ‹‹የሌሎች መብት አስከባሪ ነኝ›› ብሎ ከሾመ ቀማኛ ለመጠበቅ መጻፍ፡፡ ሰው በመሆኔ ብቻ ያገኝሁትን መብት ማንም የማንንም ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል ምክንያት አይንጠቀኝ ነው የመጻፌ መነሻና መድረሻ፡፡

ነገር ግን ቀላል ቢመስልም፤ ስለመብት መጻፍ ከብዙ አቅጣጫ ይፈትናል፡፡ የእስር ቤት ወዳጆቻችን እያሾፉ ‹‹ጦማሪ ነኝ እያላችሁ ከግድግዳ ጋር ከምትላተሙ፤ ለምን እንደ ሰው አፏግራችሁ (ተቅለስልሳችሁ እንደማለት ነው) አትኖሩም? ምን አደከማችሁ?›› ከሚሉት ጀምሮ፤ ‹‹የጻፈ ሁሉ ከጀርባው ተልዕኮ አንግቧል›› እያለ በእየዕለቱ ደንብሮ እስከሚያስደነብረው መንግስት ድረስ በየደረጃው የመጻፍን ሐጢያትነት በክፉና በበጎ የሚነግሩ በዙሪያችን ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጭቆናና ግፍ የሕይወታችን አካል ሁኗልና እሱን ተቃውመን መጻፍ አማራጭ ያላገኝንለት መንገድ ነው፡፡ መንገዱ የት እንደሚያደርሰን ማየት ደግሞ ለጊዜ የተሰጠ የቤት ሥራ ነው፡፡

የአምስተኛ ዓመት ማስታወሻ…

‹ዞን ፱ የጦማሪዎች እና አራማጆች ስብስብ› ከተመሠረተ እነሆ አምስት ዓመቱ ዛሬ ሞላ፡፡ አምስት የተስፋ እና የስጋት ዓመታት ሔዱ፡፡ ብዙ ጊዜ፣ የተለያዩ ቦታዎች እንደሚነገረው ስብስቡን ለመመሥረት ያነሳሳን ተስፋ ነው፡፡ አዎ በይነመረብ ላይ ብቻ እንተዋወቅ የነበርነውን ዘጠኛችንን ያሰባሰበን ይህ ተስፋ ነው፡፡ ስብስቡ ከተመሠረተ በኋላ ታዲያ፣ ብዙ ጊዜ የበለጠ የሚያነሳሱ፣ አንዳንዴ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጡ እውነታዎችን ተጋፍጠናል፡፡

ያለፉትን ዓመታት መለስ ብለን ስናስታውሳቸው፣ በኢትዮጵያ ስለ ዜግነት ግዴታቸው እና ስለ መብታቸው እምቢ ባዮች የሚጋፈጧቸውን ፈተናዎች ከራሳችን ልምድ በመነሳት በአጭሩ ማካፈል አግባብ መስሎ ተሰማን፡፡

ሐሳብን በነጻነት በማስተናገድ ረገድ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዓለማችን አስቸጋሪ ከሚባሉት አገራት አንዷ መሆኗ እሙን ነው፡፡ እኛ ግን፣ አሁንም አሁንም እያነሳን የምንጥላቸው ጥያቄዎች፤ ‹እንዳሰቡት የሚጽፉ ጦማሪዎች ሕይወት በዚህች አገር ምን ይመስላል? የዴሞክራሲ አራማጆች የለት ተለት ፈተናቸውን እንዴት ነው የሚጋፈጡት?  ለምንድን ነው እያንዳንዱ ቀን ካለፈው ቀን የከፋ እየሆነ የሚመጣው? ለምንድን ነው የምንጽፈው? ጽሑፎቻችን አንባቢዎቻችን ላይ ምን ለውጥ አመጡ?› የሚሉ ናቸው፡፡

የየግል ጥረቶቻችን አሰባስበን ለመሥራት ጉዞ ስንጀምር፣ ሕልማችን ራሳችንን በስርዓት ማነፅ እና ማበልፀግ ነበር፡፡ ስለአገራችን ይበልጥ ማወቅ እና ዕውቀታችንን ማስፋት፡፡ ለዚህ ነው፣ የጡመራ እና አራማጅነት ስብስባችን ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች እኛው ራሳችን ነን የምንለው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በእኛ እርምጃ የተነሳሱ ወጣቶችን ንግግር/ጽሑፍ ስንሰማና ስናነብ - ደስታችን ወደር ያጣል፡፡ ሌሎችን እያነሳሱ የግል ፍላጎትን እንደማሟላት ያለ አስደሳች ነገር ጨርሶ የለም፡፡

የጦማር መድረካችንን ስንመሠርተው፣ ትልማችን የነበረው እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ትልቅ አገር ቀርቶ በትንንሽ ማኅበረሰቦች ሳይቀር ነባሪ የሆነውን ልዩነት የሚያስተናግድ ብዝኃ-ዕይታ የተሞሉ መጣጥፎችን ለማስተናገድ ነበር፡፡ ታዲያ ትልማችን ግቡን መታ? ባንድ ድምፅ የምንናገረው “ኧረ በፍፁም” ብለን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በከፊል - የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠሩት ሰዎች ለሐሳብ ገበያ እንቅፋት በመሆናቸው ነው፤ ከፊል ምክንያቱ ደግሞ እኛው ራሳችን አቅማችንን ሁሉ አሟጠን መሥራት ባለመቻላችን ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ጥቂትም ቢሆን ባደረግነው ጥረት ኩራት ይሰማናል፤ ዋናው ቁም ነገር አሁንም ቢሆን ከሞከርነው በላይ ለመሥራት ፍላጎቱ ያለን መሆኑ ነው፡፡

ጡመራ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ራስን በራስ የማከም ሚና አለው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ “ስለሚያገባን እንጦምራለን” የሚለው መፈክራችን በራሱ ይህንን ጡመራ በሕወታችን ያለውን ሚና ያሳያል፡፡ ስለ መብታችን ይገድደናልና እንጦምራለን፡፡ እኛ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ይህንን ተፈጥሯዊ እና አብሮን የተወለደ ሐሳባችንን የመግለጽ መብታችንን መገፈፋችን ስለሚያሳስበን እንጦምራለን፡፡ መጦመር እና ስለ መብቶቻችን መናገር የገዛ ራሱን ሕግ ማክበር በተሳነው አገረ-መንግሥት ውስጥ መኖር የሚያመጣውን ሕመም ስለሚያክምልን እንጦምራለን፡፡ በዚህ አባባላችን፣ ጡመራ ለጤናማ ማኅበረሰብ ፀር ለሆነው ጭቆና ማከሚያ መድኃኒቱ ነው፡፡

ጡመራ ሰፊ የወዳጅነት እና የመደጋገፍ የግንኙነት መረብ እንድንፈጥር ረድቶናል፡፡ እርስ በርስ በመወዳጀት እና በመገናኘታችን፣ የተቀናጀ የቡድን ሥራ አቅምን መረዳት ችለናል፡፡ ይህ ልምድ እንዲስፋፋ ነው ለአገራችን የምንመኝላት፡፡

መሰባሰብ እና መቧደን ግን ችግር አያመጣም ማለታችን አይደለም፤ ስበስቦች በአገዛዙ ዒላማ ውስጥ በቀላሉ ይገባሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ የጨቋኞች ዋና ጠላት የተደራጀ ጥረት እና ምክንያታዊ ሙግት/ትግል እንደሆነ አስተምሮናል፡፡ ትምህርቱን ማግኘታችን አበርትቶናል፡፡ ከእናንተ አንባቢዎቻችን የተቀበልነው ፍቅር እና ድጋፍም - እንዲሁ - በየቀኑ እያነሳሳን ቁስላችንም በቀላሉ እንዲሽር ረድቶናል፡፡

ዛሬ ላይ፣ ከጡመራ ባሻገር በሌሎች የአራማጅነት ኃላፊነቶች ተጠምደናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት - እኛ ስለ መብታችን የሚገድደን ዜጎች - እጅ ለእጅ ከተያያዝን እና ጥረታችንን ካጣመርን ለውጥ እንደምናመጣ ያለን እምነት ፅኑ ነው፡፡ ይህ ተስፋ እና እምነት ነው - በአምስተኛ ዓመታችን መታሰቢያ ዕለት ሁላችሁም የዞን ፱ ጦማር ተከታታዮች ለዚህ የጋራ ግባችን የበኩላችሁን እንድታበረክቱ የምንጋብዛችሁ፡፡

5 Years Down the Road…

It has been five years since the establishment of Zone 9. Five years of hope and melancholy. As it was said for many times in many places, hope triggered us to establish the collective. The hope of nine optimist Ethiopians who happened to get together online. Since the establishment of the collective, we passed through many, oftentimes inspirational and sometimes frustrating realities.

Looking back to the bygone years, we find that it’s imperative to reflect on a life of a dissident in the present days Ethiopia and, the optimism and bummer we experienced.

It’s needless to say that, the current Ethiopia is one of the most dangerous places in the globe for free ideas. Rather, what is to be like living in such precarious place as a blogger who speaks what s/he thinks? How can an activist grapple with such daily downers?  Why every new day appears to be worse than the previous day? Why we’re writing and how it impacted our readers? These are some of the questions we’re struggled to answer every now and then.  

When we began this journey of collectivizing our individual effort, we were looking for disciplining and helping ourselves. Helping ourselves by knowing our country more and widening our horizon of knowledge. That’s why we always say that the foremost beneficiaries of our little effort are - we the members of the collective. However, when we heard/read from other fellow Ethiopians about how much they’re inspired by what we did - we rejoice. Nothing is as ecstatic as fulfilling self-interest while being a reason to inspire others.

We start blogging aimed at creating an independent platform that hosts multi-views and multi-perspectives, which naturally exist in every community, let alone in a country as big as Ethiopia. Was that a successful endeavor? Roaring no. This happened partly, because those in power are hostile to the revered market of ideas and partly because we failed to deliver our promises—because we were not working as much as our energy. However, we’re proud of every little effort exerted to realize a civilized discourse in our collective and we’re committed to scale it up further.

Blogging was playing such a therapeutic role on each of our lives. Our motto “we blog because we care” well sum what we’re referring the therapeutic role. We care about our rights so that we blog. The fact that we along with fellow Ethiopians are dispossessed of those natural rights and our inherently embedded rights are jeopardized triggered us to blog. Speaking about our rights eases the pain of living under a state which couldn’t care less about respecting its own law. In this sense, blogging was helping us in grappling with this menace of life - oppression.

Blogging enabled us to create a wide network of friendship and company. By networking each other and beyond, we learn the essential lesson of group work and collective effort. That’s what we dreamed for our country.

On the down side, a collective effort appeared to be prone for targeting by the regime and surrogates alike. This was an essential lesson for us that knowing the foremost enemies of tyranny are collective effort and moderate engagement. Learning the lesson makes us stronger. Counting the love and solidarity from many of you inspired us to everyday, and optimism heals our wounds.

Currently, we’re vastly engaged with activism responsibilities beyond blogging. Still, our hopes of bringing betterment within collective effort and direct engagement will succeed if we, citizens who care about our own rights, hold hand in hand. It is in this optimism that we, on our fifth anniversary, make calls to Zone 9 fellow followers to contribute pieces of writing to this end.