በዘላለም ክብረት
አፍሪካ ከበደ ገና በአስራዎቹ የዕድሜ መጨረሻ ላይ ያለ ወጣት ነው፡፡ በጣም ተስፈኛ ነው፡፡ ሁሌም ለውጥ እንደሚመጣ መናገር ይወዳል፡፡ ለምን ስሙ ‹አፍሪካ› እንደተባለ ሲጠየቅ ደጋግሞ ወደ መምህር አባቱ ይጠቁማል፡፡ አባቱ ስድስት ልጆች እንዳላቸውና የመጀመሪያዋን ዓለም፣ ሁለተኛውን አፍሪካ፣ ሦስተኛውን ኢትዮጵያ፣ አራተኛዋን ኦሮሚያ፣ አምስተኛዋን ወለጋ እንዲሁም ስድስተኛዋን ደግሞ ሊሙ ብለው ስም እንዳወጡላቸው ለጠየቀው ሁሉ ፈገግ እያለ መናገር አይሰለቸውም፡፡ አፍሪካ በወጣትነት ዕድሜው የትውልድ ከተማው የምስራቅ ወለጋዋ ሊሙ ወረዳ፣ ገሊላ ከተማ ውስጥ የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መሆን ብዙ መዘዝ በሚያስከትልበት አገር አፍሪካ በተስፋ ጽሕፈት ቤቱን በራሱ ያቋቋመው ‹የአካባቢው ሰው አማራጭ እንዲኖረው› በሚል ሐሳብ እንደሆነና፤ ከፓርቲው የማረጋጋጫ ፈቃድ ተቀብሎ በጽሕፈት ቤቱ ጊቢ ውስጥ የኦፌኮን አርማ የያዘ ሰንደቅ ዓላማ ከክልሉና ከብሔራዊው ሰንደቅ ጎን የሰቀለ እለት በወረዳዋ የተፈጠረው ትርምስን እያስታወሰ ፈገግ ይላል፡፡ ‹‹አፍሪካ የመረራን ባንዲራ ሰቀለ›› በሚል የወረዳው አመራሮች ተሰብስበው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተወያይተው ለጥቂት ቀናት ከታሰረ በኋላ በፓርቲው ጥረት ተፈቶ ወደስራ እንደገና አንደተመለሰ ይናገራል፡፡ ‹‹የእኛ ጽሕፈት ቤት መክፈት በወረዳው አመራሮች ለሚበደሉ ሰዎች ትልቅ ተስፋ ሁኖ ነበር›› ይላል አፍሪካ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የመንግስት ሰራተኞች አለቆቻቸውን ‹‹አላሰራም የምትሉን ከሆነ አፍሪካ ጋር ሒደን እንሰራለን›› እያሉ ያስፋራሩ ነበር ይላል፡፡
ለአፍሪካ የፓርቲው መኖር ትልቁ ትርጉሙ ለዜጎች ተስፋ መስጠቱ ነበር፡፡ ከዚህ ተስፋ ጀርባ ደግሞ አንድ ስምን ደጋግሞ ያነሳል፤ መረራ ጉዲና፡፡ ‹‹ዶክተር ጋር ከደወልኩ የማንፈታው ችግር አልነበረም፡፡ የታሰሩ አባላቶቻችን በአንድ ስልክ ወዲያው ነበር የምናስፈታው›› ይላል መረራን እያወደሰ፡፡ በርግጥም አፍሪካ በወጣትነቱ ተስፋ ስለሰጡት ጎልማሳ መረራ ጉዲና አውርቶ አይጠግብም፡፡
የሦስት ጨቋኞች እስረኛ
መረራ ከ21 ዓመታት በፊት በሚያዚያ 1988 የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስን (ኦብኮ) ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር ሲመሰርቱ የሚጓዙት መንገድ ረጅም እና አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አልገመቱም ማለት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ከነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አንፃር እንዲሁም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የኢሕአዴግ አካሔድ ትዝብታቸው ነበር ለዚህ ድምዳሜያቸው መሰረቱ፡፡