Friday, December 1, 2017

የመረራ ክስ ምን ይነግረናል?

በዘላለም ክብረት

በሰዎች የእድገት መሰላል በተለምዶ ‹ሃያዎቹ› (twentysomethings) የሚባለው የዕድሜ ክልል እጅግ ወሳኝ እንደሆኑ ብዙ ጥናት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሰዎች ከልጅነት ጊዜያቸው ወደ ጉልምስና የሚሸጋገሩበት ጊዜ መሆኑም ነው የወሳኝነቱ መነሻ፡፡ ይሄን ወሳኝ የዕድሜ ክልል ገና ሲጀምረው በ21 ዓመቱ ወደ እስር የተወረወረው አፍላው ወጣት መረራ ጉዲና ከ7 ዓመታት እስር በኋላ የዛኔው የደርግ ምክትል ፕሬዝደንት ፍስሃ ደስታ ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ የኢትዮጵያ አብዮትን ለተወሰነ የታሪክ ወቅት አብረን ስንመራ ቆይተን ዛሬ አብዮታችን የላቀ ዘላቂ ድል ሲጎናፀፍ የደስታው ተካፋይ እንድትሆኑ በምህረት ፈተናችኋል›› ብለው መስከረም 02፣ 1977 ከሌሎች መቶ የሚሆኑ የፖለቲካ እስረኞች ጋር ሲለቀቅ ዕድሜው 28 ደርሶ ነበር፡፡ ወሳኞቹ ‹ሃያዎቹ› እንደዋዛ በእስር አለፉ፡፡ የደርግን አብዮታዊ ድግስ ለማድመቅ ‹በምህረት› ከእስር የተፈታው መረራ፤ ይህ ከሆነ ከ32 ዓመታት በኋላ ተመልሶ ‹ሃያዎቹን› ወዳሳለፈበት ወህኒ ከተወረወረ ይሄው አንድ ዓመት ሞላው፡፡ በእነዚህ 32 ዓመታት ውስጥ ያቋረጠውን ትምህርት አጠናቆ፣ ብዙዎችን አስተምሮ፣ እንዲሁም ‹ታሟል› የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከበሽታው ያገግም ዘንድ የቻለውን ሁሉ፤ በመሰለው መንገድ አድርጓል፡፡ ለዚህ ልፋቱ ክፍያው እስር መሆኑ ደግሞ አሳዛኙ የአገሪቱ ምሥል ማሳያ ነው፡፡

መረራ ጉዲና

መረራ አሁን እስር ቤት ነው፡፡ መረራ የታሰረበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ መረራ ላይ ከቀረቡበት ሦስት ክሶች አንዱን ከነማስረጃው ዘርዘር አድርገን በማየት የክሶቹን መነሻና ዓላማ ለመመልከት ብንሞክር የመረራን ንጽሕና የበለጠ ለመረዳት እንዲሁም መረራን ለማሰር የተሄደበትን ረጅም ርቀት እንረዳለን፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ሦስት የተለያዩ ክሶችን ያቀረበ ሲሆን የመጀመሪያው ክስ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ እንዲህ እንደዛሬ የሁሉም የፖለቲከኛ እስረኞች የክስ መነሾ ከመሆኑ በፊት ለብዙ የፖለቲካ እስረኞች የእስር ምክንያት ሁኖ የኖረው በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 238 ላይ ‹‹ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ መሞከር›› ተብሎ የተደነገገው ነው፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹በአጠቃላይ በአለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲካሔዱ የነበሩትን ተቃውሞዎች ሁሉ አስተባብሯል›› ተብሎም ነው ክስ የቀረበበት፡፡ ሁለተኛው የዶ/ር መረራ ክስ ከአስር ወራት ትግበራ በኋላ ለተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ መነሻ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚያጣቅስ ሲሆን፤ ዶ/ር መረራ ‹በጥቅምትና ሕዳር 2009 አውሮፓ በነበሩበት ወቅት ቤልጅየም ውስጥ አዋጁን በመጣስ ‹‹ከአሸባሪዎች ጋር ተገናኝተዋል›› የሚልም ነው የክሱ ፍሬ ነገር በአጭሩ፡፡ ‹‹ሕገ-መንግስቱን የሚያከብር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ብቻ ነው ለአገሪቱ መድኅን የሚሆናት›› እያለ የፖለቲካ ዕድሜውን ለገፋው መረራ ጉዲና ‹‹ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ሞክረኻል›› ብሎ ክስ ማቅረቡ የከሳሾን ማንነት ከማሳየት ባለፈ በትንተና ጊዜ ሊጠፋበት የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ በሁለተኛው ክስ ላይ ‹ተጣሰ› የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተሻረ ወራት ቢያልፉትም ዶ/ር መረራ ግን ያለምንም ሕጋዊ መነሻ አስከአሁን ድረስ የተሻረው አዋጅ ተጠቅሶ የቀረበበት ክስ የዋስትና መብቱን አስከልክሎት በእስር ላይ ይገኛል፡፡