Tuesday, October 9, 2012

ስደትና ፍቅር



በሰለሞን አብርሃም (ከአውሮጳ)

የአንድ አገር መንግስት ለዜጎቹ እረኛ እንደማለት ነው። እረኛ መንጋውን ይጠብቃል መንግስትም ዜጎቹን ይጠብቃል። ነገር ግን እኛ መንግስት ቢኖረንም ጠባቂ የሌለን ሕዝቦች ከሆንን ዓመታት ተቆጠሩ። እረኛ የሌለን መንጋ ከሆንን በርካታ አሥርት ዓመታት አለፉ። መንግስቶቻችን እረኛነታቸው ባሕሪያቸው አልነበረምና አውሬነቱ እያሸነፋቸው ከመንጋው ያማራቸውን እየመረጡ ሲያርዱ፣ ሲበሉ ኖሩ። አውሬዎቹን የተመለከቱና የሰሙ ኢትዮጵያውያንም ከመንጋቸው እየተለዩ ወደምድር ተበተኑ። ከመንጋው የተለየ ደግሞ መጨረሻው ጥፋት ስለሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየዱሩ አለቁ፣ በየመንገዱ ባከኑ፣ በባእድ አውሬዎች ተበሉ። የእረኛ ያለህ እያሉ የሌሎችን ባዕዳን ጠባቂዎችን አድኑን እያሉ ለመኑ። የስደት ኑሮን እንደስኬት ቆጥረው መኖር ጀመሩ።

መንግስታቶቻችንን ሲሸሹ ለዘላለም ያለፉትን አምላክ ነፍሳቸውን በሰላም ያሳርፍልን። በተለያዩ የዓለም አገራት ተበትነን በዘር፣ በጎሳ፣ በመንደር፣ በከተማ፣ በአመለካከት፣ በአስተሳሰብ፣ በትምህርት ደረጃ ተቧድነን ለምንኖረውም አምላክ በቸርነቱ ይጠብቀንና በሰላም ወደመንጋችን እንድንቀላቀል ይርዳን። ለአሁኑ እስቲ ከስደተኛው አበሻ የፍቅር ሕይወት ሒደት በጎ በጎውን እንታዘብ፤ ደግ ደጉን በጨረፍታ እንዳስ።

በስደት ኑሮ አበሻው ቡድን ቡድን መስርቶ ተሰባስቦና ተነጣጥሎ፣ ተዋዶና ተጠማምዶ በሰፊው የስደት ምድር ይኖራል። ኢትዮጵያዊው በሚኖርበት አገር ላይ ብዙ አነስተኛ ድርጅቶችን ይመሰርታል። አነስተኞቹም ድርጅቶች ለመሰነጣጠቅ ምክንያት አያጡም። ምክንያታቸው መኮራረፍን መሠረት ያደረገው የአበሻዊ የአስተሳሰብ ባሕል ሲሆን ከነዚህ ድርጅቶች አኩርፈው የሚወጡት ግለሰቦች ደግሞ ሌላ ጥቃቅን ማሕበራትን መስርተው ይኖራሉ። ኢሕአዴግ የአነስተኛና ጥቃቅን ማኅበራት ማደራጀትን ልምድ የወሰደው በስደት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይመስላል። ያገር ቤቶቹና በስደት ላይ ያሉት ማኅበራት ልዩነታቸው ብዛታቸው አይደለም። ልዩነታቸው አስገባሪያቸው ነው። ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራቱ በአገር ቤት ሲሆን ለኢሕአዴግ ይገብራሉ።  በስደት ያሉት ደግሞ ግብራቸውን የሚያስገቡት ለራሳቸው ነው። እነዚህ ቡድኖች በስደት በሚገኙ አበሾች በየስርቻው ተመሥርተው በብዛት ይገኛሉ።

የሚመሠረቱበት ዓላማ ምንም ቢሆን በወረቀት ያሰፈሩት መርሓቸው እና በግብር የሚያራምዱት ተግባራቸው የአብዛኞቹ ተመሳሳይ ነው። በወረቀቶቻቸው ላይ እኩልነት ፍቅርና አንድነት ሲሰበክ በአንድነት ተሰባስቦ መታገል ደግሞ ይሞገሳል። በተግባር ግን በተቃራኒው ተፈራርተው፣ ተጠማምደውና ተነጣጥለው ይጓዛሉ። በሰው ምድር ላይ በየቦታው ተመሥርተው እርስ በርሳቸውእባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብዓይነት ኑሯቸውን ሲገፉ ይኖራሉ።

ካገርህ ስትሰደድ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ብለህ ሊሆን ይችላል። የሚያገባህ ከሆነ ከነዚህ ማኅበራት ቀረብ ወደሚልህ ሄደህ እንድትመዘገብ ትመከራለህ። ከዚያም ትሄድና አባል ትሆናለህ። ያኔ ታዲያ የምታሞግሰውና የሚያሞግስህ ታገኛለህ ማለት ነው። የማኅበራቱ ሥራ ከዚህ ስለማያልፍ ያንተም ሥራ በማኅበሩ ልክ ይሆናል። እርስ በርስ ለመሸነጋገያ በተመሠረተ አነስተኛ ማኅበር ውስጥ ከተካተትክ ከማኅበሩ አባላት መወደድን ታተርፋለህ። በዚያችው በማኅበሩ ጉድጓድ ውስጥ ትገባና በጉድጓዷ ስፋት ልክ ማሰብ ትጀምራለህ። የምታዋጣት ሳንቲምና ለስብሰባ የምትመድበው ጊዜ እኔ ላገሬ እንዲህ ነኝ እያልክ እንድትሸልል ያደርግሃል። ይህ አንዱ የስደት ጊዜህን የምታሳልፍበት ኑሮህ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሌላው ኑሮህ ከአበሻው ማኅበረሰብ ጋር ባንድነት መኖር ይሆናል። ዝም ብሎ መኖር። ልደት፣ ዓውደ ዓመት፣ ማኅበር እያልክ መገናኘትና አንድ ላይ እንጀራ መብላት፣ አንድ ላይ ማውራት፣ ከቦታ ቦታ እየተንሸራሸሩ ከሥራና ከትምህርት የተረፈ ጊዜህን ማሳለፍ፣ ከአገር ልጅ ጋር ፍቅርን መቅጨት። ይህን ስታደርግ የስደት ጊዜን ሳይታወቅ ሽው እንዲል ያደርገዋል ማለት ነው።

ከነዚህ ክንውኖች ውጭ ከሆንክ ደግሞ ከአበሻው የኑሮ ጉድጓድ ተገልለሃል ማለት ነው። ከዚያም ወይ የራስህን ጉድጓድ ትቆፍራለህ ወይ ወደተለያዩ ጉርጓዶች ጎራ እያልክ ለመላመድ ትጥራለህ። እንደምንም ብለህ ወደ አንዱ ከተጠጋህ የምታየው የአበሻው ኑሮና ፍቅር ሊመስጥህና ጭንቀትህን ሊያጠፋልህ ይችል ይሆናል። ግን የስደት ነገር ምኑም እውነት እንደሌለው የተገነዘብክ ዕለት ችግር ይመጣብሃል። ላይችል አይሰጥ ይሆንና አትቀውስ ይሆናል እንጂ የአበሻው የስደት ምሽግ የሚጠይቅ አዕምሮ ላለው ሰው ለመሸከም ይከብዳል።

ስደተኛው ፍቅር

ስዕሉ የተገኘው ከthecollegecrush.com ነው::
በስደት ዓለም አብሮ መኖርና አብሮ መብላት የአበሻዊነት ባሕሪ ነው። አበሻ ይዋደዳል ብንልም ስደቱ  አበሻዊነት ፍቅርን ሲፈታተነው ይታያል። መፈታተን ብቻም አይደለም፤ እንዲያውም እንዲህ ማለትም ይቻላል፤ ስደተኛው ፍቅር ወደሆድ አይወርድም፣ ወደ አንጀት አይዘልቅም፣ ልብን አይዳስስም፤ እንዲያው ከአፍ አያልፍም። ስደተኛው ፍቅር ባንደበት ይተረካል፣ በምላስ ይቀመሳል፣ በከንፈር ይሳማል፣ በአዞ እንባ ይታጀባል። በቃ እንዲህ እንዲህ ሲኮን ይኖራል።

ለጥገኝነት መሳካት የተፈጠረ ታሪክን መሠረት አድርጎ መኖር የተለመደበት የስደት ዓለም ለፍቅር አይመችም። አንዷ ተመችታህ ፍቅር ልመስርት ብለህ ብትጠጋ ስለመፈጠርህ ዕውቅና ሊሰጡህ የማይፈልጉ የፍቅር ጎሰኞች ይገጥሙህና የፍቅር ቋንቋህ አይደለም ለፍቅር ሰው ለመሆንህ ማረጋገጫ እንዳልሆነ አፋዊ ባልሆነ ድርጊት ሲገልፁልህ የገባህበት ጉድጓድህ ይደብርሃል፣ ኢትዮጵያዊነትህ ያስጠላሃል።  አንዳንዴ ከሌላ አገር ዜግነት ካለው ሰው የሚመሠረት ፍቅር ከኢትዮጵያዊ በላይ ሲደላ ይታያል።

ተሰደህ በፍቅር የምትኖር ከመሰለህ የዋህ ነህ ማለት ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ፍቅር ሊይዝህ አይችልም ማለት አይደለም። ፍቅርን ልትቀበል ግን ትቸገራለህ ወይም ደግሞ ፍቅር ልትሰጥ ትቸገራለህ ማለት ይሆናል። ፍቅርን ለብቻህ ትጫወተዋለህ ስለሆነም ተጋጣሚ የሌለው አታካች ጫወታ ይሆንብሃል። እያባበልክ ወይም እየተባበልክ የምትሰጠው ወይም የምትቀበለው ፍቅር ይሆንብሃል።

ማፍቀርህ ከማንነትህና ከምንነትህ ጋር ይያያዛል። እራስህ የማታስታውሰው ማንነትህ በኩራዝ ብርሃን ይበረበራል፣ ምንነትህ ባለህ የመኖርና የማኖር አቅም ይወሰናል። አንተም የአፍቃሪህን በዋዛ አትለቃትም። ማንነቷንና ምንነቷን ለማወቅ ትተጋለህ። የዘር ማንዘር ብርበራውን አልፈህ ብትገኝ ደግሞ ሌላ የማይታለፍ ፈተና ይጠብቅሃል።

ይህ ማለት ምን ማለት መሰለህ? አንተ ባጋጣሚ ከተዋወቅካት ሴት ጋር ፍቅር ሊይዝህ ይችላል። የመጀመሪያውን ፈተና ማለፍህ ለፍቅርህ ዋስትና አይሆንም። ፍቅርህ ተቀባይነት እንዲያገኝ የምታሟላውን ማሟላት ይጠበቅብሃል። የስደትን ፍቅር ለመኮምኮም አሁንም ሁለተኛውን ማሟላት ያለብህን አሟልተህ ተገኘህ እንበል፤ የወደድካት ልጅ አንተን ሳይሆን ያሟላኸውን ነገር ስለወደደች ፍቅርህ ተጋጣሚ የሌለው ልፋት ይሆንብሃል ማለት ነው።

አንተ ዛሬ ፍቅር ለመመስረት ያሟላኸውን መስፈርት አስበልጦ የመጣ ሌላ ሰው ፍቅረኛህን የማይወስድበት ምክንያት አይኖርም። አንተም ገዛሃት፣ እርሱም ሻል ያለ ዋጋ መድቦ ይገዛታል። ይህ ውድድር ከአገርቤቱ የሚለየው የዚህኛው ምድር እሽቅድድም የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የወረቀትም በመሆኑ ነው። የወረቀትም ብቻ አይደለም አንዳንዴም የዜግነትም ሲሆን ይታያል።

እሷ የምትሸጥ ሆና እንዳይመስልህ በመኖሪያ ፍቃድና በዜግነት የምትቀባበሏት። እሷንና ቤተሰቦቿን የተጫናቸውን የኑሮ ሸክም ለማቃለል ምርጫ ስለማይኖራት ነው። ስለዚህ ነው አታካች ጫወታውን እንኳን በትዕግስት ችለህ ብትዘልቅ ማባበሉን የማትዘልቀው። እየለመንክ እያባበልክ አፍቅሪኝ እያልክ መኖር? ከባድ ሥራ ይሆንብሃል።

ከምዕራቡ ዓለም ከሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ ትኖራለህ እንበል። በዚህ ትልቅ ከተማ ላይ እንደምትኖር ማኅበራዊ ግንኙነት ለመፍጠር በከፈትከው አንድ የኢንተርኔት መረብ ላይ ትጠቅስና የመረቡ የምታገኘውን በረከት መቋደስህን ትቀጥላለህ። ነገር ግን የምትኖርበት ከተማ በሰዎች ላይ ልዩነት ማምጣት የሚጀምረው ሳትውል ሳታደር ይሆናል። በውጭ አገር በመኖርህ አገር ቤት በሚኖሩት ሴት ወገኖችህ ላይ ለውጥ ማምጣት ይጀምራል። ሴት ከሆንሽም እንደዚሁ።

በቀላል ሰላምታ የሚጀመረውን ግንኙነት ለማስጨረስ ከቆረጥክ መጨረሻው ፍቅር እንዲሆን ትጋበዛለህ። የምትጠቀምበት የማኅበራዊ ግንኙነት ገጽ ላይ ፎቶህ እንኳን አለመኖሩን ስትረዳ ፍቅሩ ካንተ ሳይሆን ከምትኖርበት አገር ወይም ከተማ የመነጨ መሆኑን ስትገነዘብ በሐዘን ትወጋለህ።

ይህ ከሩቅ የምትፈጥረው ግንኙነት የአገር ቤቶቹ ወገኖቻችን ውጭ አገርን አክብዶ ከማየት ከሚመጣ የማኅበረሰባችን ሁለንተናዊ ችግር የመነጨ ይሆናል ትልና የችግሩ ምንጭ ‹‹ወያኔ›› ነው ብለህ በደፈናው ለማለፍ ትደፍርና ታልፈዋለህ። ነገር ግን እዛው አጠገብህ በምትኖርበት አገር ላይ ካሉት  ወይም እንዳንተው ተሰደው ከሚኖሩት ወገኖችህ ተመሳሳዩ የፍቅር ግብዣ ሲደረግልህ ስትመለከት ነገሩ ስር መስደዱን ትገነዘባለህ።

ማለቂያ የሌለው ችግራችን የት ድረስ እንደደረሰና ኢትዮጵያዊነት በየፈርጁ ወደማጡ እየገባ እንደሆነ ትረዳለህ። ድህነት ምን ያህል ማንነትን እንደሚቀይር፣ ክብርን እንደሚያስረሳ፣ ፀጋን እንደሚገፍ ታያለህ።

አብሮህ ተሰዶ የስደቱ ገፈት ቀማሽ ከሆነ ሰው ነዋያዊ የፍቅር ግብዣ በአብዛኛው በሁለት መልኩ ሊቀርብልህ ይችላል። አንዱ አንተን ሳይሆን የመኖሪያ ፍቃድህን ለፍቅር የሚጠይቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚያልፈው ጊዜ፣ የሚነጉደው ዕድሜ አማራጭ ሲያሳጣ በስተርጅና ሙሽርናን ለመሸሽ የሚፈጠር ፍቅር ይሆናል። ስለዚህና ለመጥቀስ ስለሚያታክቱ ብዙ ጥቃቅን ምክንያቶች የስደት ፍቅር ፍቅርነቱ ተነክቷል፣ ኃይሉን አጥቷል፣ ፀጋውን ወይም መንፈሳዊ ስጦታውን ተገፏል።

የስደት ፍቅር ከጀርባው ያዘለው አታካች ዝባዝንኬ ስላለ ነገሩ ቢሰምርም እንኳን መንገዳገዱ አይቀርም። ፍቅሩ ሰርቶ፣ ልጅ አፍርቶ ቢቀጥልም እንኳ መቃሰቱ አይቀርም። ፍቅሩ ደርጅቶ በልጆች ቢደምቅም እንኳን ጥያቄ በአዕምሮ መጫሩ አይቀርም።

ብቸኝነቱን፣ ብርዱንና ጨለማውን ለመቋቋም ከዚህ የተሻለ አማራጭ ስለማይኖር የስደት ሕይወት በቅርብ ካገናኘችህ ከአንዷ ጋር ትጣመራለህ። ወይ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ወይ ደግሞ በሥራ ቦታ። ስደት ሲጀመር አብዝቶ ስለሚከፋ ክፉ ዘመንን በጋራ ለማለፍ ፍቅር ጥሩ ምሽግ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ጊዜውን ለመግፋት ብቻ ፍቅርን ተገን ታደርግና ካገኘሃት ጋር ትዋደዳለህ። አብራችሁ ሰርታችሁ ማደር ትጀምራላችሁ። ወልዳችሁ ትከብዳላችሁ።

እንደአገር ቤት ቢሆን በዚህ መሐል በአንተ ወይም በእሷ ላይ ለሚፈጠር ችግር እርስ በርስ እየተጋገዛችሁና እየተሳሰባችሁ ማለፍ የግድ ነው። በስደት ሲሆን ግን እንደዛ አይሆንም። በመሃል ከደኸየህ? ሥራ አጥ ሆነህ ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ተከልክለህ የተቸገርክ ከሆነአይዞህ፤ እኔ አለሁልህ› የምትል ሴት ከስንት አንድ ነች - በስደት ዓለም።

ስለሆነም የነገር ኃይል ይበረታብሃል። ለልጆችህ ብለህ የምትችለው ነገር ቢሆንም ብዙ አሰልቺ የትዳር ሕይወት እንድታሳልፍ ስደቱ ያስገድድሃል። ያጣኸውን ሥራ ወይም የመኖሪያ ፈቃድ እያማረርክ እንደባል ሳይሆን እንደተላላኪ እየተሽቆጠቆጥክ እንድትኖር ይፈረድብሃል።

ይህ የሚሆነው በስደት ውስጥ ሴቶቹ ከፍተው አይደለም፤ ተመሳሳዩንና የባሰውን ድርጊት ወንዶቹም በሴቶቹ ላይ ሲያደርጉት ነው የኖሩት። ነገር ግን ሴቶቻችን ቻዮች ስለሆኑ ችግሩን በመቻል እንዳልተፈጠረ ያደርጉታል። ስለሆነም የስደት ፍቅር በየትኛውም መስፈርት ለማንም አይመከርም።

የመኖርያ ፍቃድ ሲኖርህ የሚያገባህ አታጣም። የሚያፈቅርህ አታጣም የውሸት ቢሆንም። የመኖሪያ ፈቃድ ሲኖርህ ምንም ያህል ክፋተኛ ብትሆን፣ ምንም ያህል ሱሰኛና ለኑሮ የማትስማማ ብትሆንልጅን መውደድ ከነንፍጡ ነውብላ እንደ ልጅ ቆጥራህ የምትሸከምህ ሴት አታጣም።

ለመከራ የተፈጠሩ የሚመስሉት ሴት እህቶችህ የሚሸከሙት የአረብን ክፋት ብቻ አይደለም። የሚሰቃዩት በአረብና በባዕድ ወንድ ብቻ አይደለም። የነዓለም ደቻሳን በደል አይተን በቁጭት የምንብሰለሰል እኛም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሴቶቻችን ሸክም ነን። የተቸገረ ቤተሰብ ከጀርባዋ የተሸከመች ሴት ለቤተሰቧ ትጨነቃለች። ስደት አልሰምርላት ያለች ሴት ስለራሷ ትጨነቃለች። በዚህ ላይ ደግሞ የስደቱ የውሸት ሕይወት ሲታከልባት ሕይወቷን የከፋ ያደርገዋል። ከክፋት ደግነት እንደሚቀል የምናውቅ እኛ ስንጨመርበት ደግሞ ይታይህ።

እንደምታውቀው መሪ፣ ነፃ አውጭ፣ ሸፋች ወንድ የሆነባት አገር ናት ኢትዮጵያ። የሚያሳዝነው ታዲያ ወንዶች ይህን መሆናቸው አይደለም፤ ኢትዮጵያችን የወንድ አገር በመሆኗ ምክንያት ያልተበላሸ ነገር አለመኖሩ እንጂ። እዚህም በስደት ሁሉን አዋቂ ወንድ ነው። ፖለቲከኛና ለአገሬ ሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት እታገላለሁ የሚል አንድ ወንድ በአደባባይ የሚሰብካቸው ስብከቶች እቤቱ ውስጥ  የሉም። በየሚዲያው፣ በየስብሰባው፣ በየቡና ቤቱ የሚደሰኩራቸው የእኩልነት ዲስኩሮች እቤቱ አልዘለቁም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው ወንድ ሁሉ የሰዎችን መብት ማክበር ከጓዳው እንደሚጀምር የረሳ ነው።

በየፓልቶኩና በየሚዲያው ሰለ አገር እንጨነቃለን የሚሉት ወንዶቻችን ስለጓዳቸው ነፃነትና ዴሞክራሲ አስበው አያውቁም። ይህም ስለሆነ በየስብሰባውና በየውይይት መድረኩ የምናገናቸው እነሱኑ ብቻ ነው። ይህ የአገር ቤት የወንዶች ተፅዕኖ በስደቱም ውስጥ ሳይቀየር እንደ እንጀራችን ተከትሎን ስለመጣ ፍቅርን ጨምሮ ያልተበላሽ ነገር ጥቂት ነው።

ያልጠረጠረ ተመነጠረ

ሌላው አበሻዊ የስደት ፍቅርን አታካች የሚያደርገው ጥርጣሬ ነው። እንደ አበሻዊነትህ ለአቅመ አዳም የደረሰች ወገንህን መግባባት መብትህ ነው። ልትወዳትም ትችላለህ። ከዚህ አልፎ ለመሄድ ከፈለግህ እንደፖሊስ መታወቂያዋን ማየት ፍርድ ቤት ከመቆም ያድንሃል። ፍቅር ለመጠየቅ ባካል ባይነ ስጋህ የምታየው ዕድሜዋ በቂ ከመሰለህ ወደማትከፍለው ችግር ለመዝለቅ ቆርጠሃል ማለት ነው። አለበለዚያ በትህትና መታወቂያ መጠየቅ ይኖርብሃል። ከሃያ ምናምን ዓመት ወጣት ቆንጆ ጋር ፍቅር ጀመርኩ ብለህ ወደቤቷ ሸኝተሃት የልብህን ደስታ ወደ አካላትህ እያሰራጨህ  ወደቤትህ ስትራመድ ዕድሜዋ ለምንም ያልደረሰች ሕፃን በማታለል ሕግ ጥሰሃል የሚል ክስ ይዞልህ ፖሊስ በርህ ላይ ሊጠብቅህ ይችላል። ስደት የሴቶቹን ዕድሜ በሁለት ይከፍለዋል። አንተ ባይነ ስጋ ስታይ የምታውቀውንና መንግስት የሚያውቀውን።

ልደታቸው ሁለት ነው። እትብታቸው የተቀበረበት አገር ላይ የሚከበረው ልደታቸውና በሰው አገር ሲኖሩ ያስመዘገቡት ስደት ነክ የሆነው የልደት ቀን።

የስደት ዕድሜዬን እርሳው ብላህ ፍቅርህን ብትቀጥል እንኩዋን እንደ ግንቦት ሰባትና ኦነግ ፖለቲካ ምድር ለምድር ፍቅርህን እንድትዘረጋ ግድ ይልሃል። ስለፍቅራችሁ ማንም ማየትም ሆነ መስማት አይኖርበትም። ምን ይታወቃል አንተን የወደደች አንዲት ቆንጆ ወይም እሷን የጠላት አንድ ስደተኛወንጀል ሲሰራ እያየ ዝም ያለየሚለውን ሕግ ፈርቶ ቢጠቁምብህስ። ስለዚህ የወደደ ሰው ፍቅር ለመጀመር የአፍቃሪውን መታወቂያ በገሃድ ጠይቆ ማየት ወይም በድብቅ በጨረፍታ የትውልድ ዘመኗን ማየት ሕግ ጥሰሃል ከመባል ያድናል።
አብሮ መኖርና ትዳር ለመመስረት ካሰብክ ደግሞ ማወቅ ያለብህ እድሜዋን ብቻ አይደለም። አንድ አይነት ቋንቋ እያወራችሁ፣ አንድ ዓይነት ምግብ እየበላችሁ፣ አንድ ዓይነት ዓውደ-ዓመት እያከበራችሁ ፍቅራችሁን መቅጨታችሁ አገራችሁን አንድ አያደርገውም። አገራችሁ አንድ ባይሆንም ችግር አይኖረውም ነገር ግን ከመገረም ለመዳን ቀድሞ ማወቁ አይከፋም። ስለዚህ ዜግነቷም አንተ ካልጠበቅከው አገር ሊሆን ስለሚችል መታወቂያዋን ማየት ወሳኝ ነገር ነው። ልትፈራረም ማዘጋጃ ቤት ሄደህ ዜግነቷ ኤርትራዊ ወይ ሶማሊያዊ ነው ሲሉህ ዓይንህ እንዳይፈጥ ቀድመህ ማወቁ አይከፋም።

ለዕድሜዋና ለዜግነቷ ብቻ እንዳይመስልህ መታወቂያ ማየት ያለብህ። አንተ እያቆላመጥክ የምትጠራው ስሟም ሌላ ሊሆን ይችላል። የተዋወቀችህ እናትና አባቷ ያወጡላትን የምትወደውን ስሟን ነግራህ ሊሆን ይችላል። አንተ ከስሟ ምንም የለህ ከፍቅሯ እንጂ። ግን አንድ መጠይቅ ቀርቦልህ ልትሞላ ብትፈልግ የሚስትህ ሙሉ ስም ከሚለው መጠይቅ ስር ምን ልትሞላ ነው? ያንን ከመሙላትህ በፊት መታወቂያዋን መጠየቅ ያስፈልግሃል። ያኔ ታዲያ ከዚህ በፊት ጠርተኸው፣ ሰምተኸውና ለማቆላመጥ የማያመች አዲስ ስም ታገኝ ይሆናል። እንዲያም ሲገጥምህ ምን ይደረጋል ብለህ አዲሱን ስሟን እንደዳቦ ስም ቆጥረህ ማለፍ ነው።
ይህን ሁሉ ነገር ስታይ ሌላም ጥርጣሬ በሆድህ ሊፈጠር ይችላል። ብዙ ብዙ ጥርጣሬ።
---
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው (oldkale7@gmail.com) ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment