Monday, December 29, 2014

አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ከወዴት አለ?


በላይ ማናዬ
 በታላቁ መጽሐፍ የተጠቀሰ አንድ ታሪክ ላይ አንዲት እናት ልጇን በጓደኛዋ ስለመሰረቋ እናነባለን፡፡ ይህቺ እናት ልጄን ተሰረቅኩ ብላ ወደ ጠቢቡ ሰለሞን አቤት ትላለች፡፡ ጠቢቡ ሰለሞንም ሁለቱን ሴቶች ተሰረቀ ከተባለው ህጻን ጋር ተያይዘው እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡ ጠቢቡ ንጉስ ሰለሞን እውነተኛ እናት የትኛዋ እንደሆነች ለማወቅም የራሱን የምርመራ ዘዴ ሲጠቀም እናስተውላለን፡፡ በዚህም ሁለቱ ሴቶች የተካሰሱበትን ጉዳይ ሰለሞን በጥበብ ትክክለኛ ዳኝነት ሰጥቶ ያሰናብታቸዋል፡፡ ህጻኑም እውነተኛ እናቱን ያገኛል፡፡ ይህ ፍትህ የተሰጠው ከብዙ መመላለስ በኋላ አልነበረም፤ አፋጣኝና ትክክለኛ ፍርድ ነበር የተሰጠው፡፡
 እንደ ጠቢቡ ሰለሞን በአንድ ጀንበር በጥበብ ተከሳሽንና ከሳሽን ሰምቶ ትክክለኛ ውሳኔ የሚሰጥ የዳኝነት አካል እንዲኖረን በባዶ የምመኝ ሰው አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ማነኛውም ተከሳሽ የተከሰሰበት ጉዳይ ተጣርቶ በፍጥነት ውሳኔ እንዲሰጠው፣ ፍትህ እንዲያገኝ እፈልጋለሁ፡፡ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል ይባላል፡፡ ትክክለኛ አገላለጽ ነው፡፡ እውነትም በሀገራችን በዚህ አገላለጽ መሰረት ውሳኔ ተጓትቶባቸው፣ ፍትህ የተነፈጉ ብዙዎች ናቸው፡፡
 ማክሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2007 . በእነ እስማኤል ኑርሑሴን የክስ መዝገብ 1 አመት 6 ወር በላይ በእስር ሲሰቃዩ የቆዩ 12 ተማሪዎች እና 1 መምህር በመጨረሻ ብይናቸው ሲሰማ የሆነው ‹‹የዘገየ ፍትህ እንደተነጠቀ ይቆጠራል›› የሚለውን አባባል ያስረገጠ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት ክስ የተበየነው 6 ወር እስር ብቻ ነበር፤ በእስር የቆዩት ግን 1 አመት 6 ወር ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየን ተከሳሾቹ አፋጣኝ ፍትህ ባለማግኘታቸው ብቻ ተጨማሪ አንድ አመት እስርን በግፍ አሳልፈዋል ማለት ነው፡፡ በእነ እስማኤል ኑርሑሴን የክስ መዝገብ ያለአግባብ ከተፈረደባቸው ጊዜ በላይ በእስር ያሳለፉት ሰዎች ከጅግጅጋ፣ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከባህር ዳር፣ ከጅማ፣ ከደሴ፣ ከሐዋሳና ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ተለቅመው የታሰሩ 12 ሙስሊም ተማሪዎችና 1 አስተማሪን የተካተቱበት ነበር፡፡ በአጠቃላይ የተጓተተው ክስ ሂደት ብይን ለማግኘት 18 ወራትን ወስዷል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ደግሞ ተከሳሾቹ በእስር ላይ ነበሩ፡፡ በግንቦት 2005 . ክስ የተመሰረተባቸው እነዚሁ ተማሪዎች በተለያዩ ሰበባ-ሰበቦች ምክንያት ችሎቱ እየተጓተተ በመቆየቱና የፍትህ ስርዓቱ የዜጎችን መብት ማስከበር በማይችልበት ደረጃ በመኮላሸቱ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ እንኳ ክሳቸው ከሚያስፈርድባቸው በላይ በእስር እየቆዩ መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ሲያሳስቡ ቆይተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሰሚ ጆሮ አላገኙም ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለረጂም ጊዜ ተስተጓጉለዋል፡፡ ሊሰሩት የሚችሉት ነገር ሁሉ ተደናቅፎ መቆየቱም እሙን ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ፍትህ አገኙ ወይስ ተነፈጉ?
በነገራችን ላይ አፋጣኝ ፍትህ ማግኘት መሰረታዊ መብት (The right to speedy trial) ነው፡፡ በህግም ጥበቃ ያለው መሆኑን በተለያዩ ሀገራት ህጎች ተደንግጎ ይታያል፡፡ በአሜሪካ (The Sixth Amendment to the U.S. Constitution) በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ በእርግጥም አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ከድሮ ጀምሮ የነበረ መሰረታዊ መብት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በእንግሊዝ በንጉስ ሄነሪ ሁለተኛ (1154–1189) ጊዜ እንግሊዛውያን አፋጣኝ ፍትህ ማግኘት እንዳለባቸው በህግ ተደንግጎ ነበር፡፡ 1215 .. ደግሞ ንጉሱ በእጁ የሚገኙ የፍትህ ጥያቆችን ማዘግየት እንደማይችል በማግና ካርታ (Magna Charta) በግልጽ ደንግጎ ነበር፡፡ ይህ ፍትህን በአፋጣኝ የማግኘት መብት በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ላይ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 37 ላይ ‹‹ፍትህ የማግኘት መብት›› ሲገልጽ እንኳ አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብትን በተመለከተ የሚለው ነገር የለም፡፡ ብዙ ዜጎች በህግ ጥላ ስር ውለው ክስ ተመስርቶባቸውም ይሁን ክስ ሳይመሰረትባቸውየፍትህ ያለህእያሉ በየእስር ቤቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች የፍርድ ቤት ውሳኔው ራሱ ፍትሃዊ ነው በማይባልበት ሁኔታ እንኳ አፋጣኝ ብይን (‹‹ፍትህ››) ሲሽቱ ቢታይም የፍላጎታቸው ሲሞላላቸው አይታይም፡፡
 ባለፈው ሚያዝያ 17 ቀን 2006 . ለእስር የተዳረጉት የዞን 9 ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች እንሆ ከታሰሩ 8 ወራት አልፈዋል፡፡ እስካሁንም ግን ክሳቸውን በውል አላወቁትም፡፡ ክስ ሳይመሰረትባቸው በምርመራ ሰበብ ወራትን አሳልፈው፣ ክሱ ተመሰረተ ከተባለ ጀምሮ የተመሰረተው ክስ እንዲሻሻል በሚል ሌላ ሰበብ እስካሁን ክሳቸው ምን ላይ እንዳረፈ በግልጽ አልታወቀም፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን ጦማሪዎቹና ጋዜጠኞቹ በእስር ላይ ናቸው፡፡ ከቀናት በፊት እስረኞቹ በሚገኙበት ቂሊንጦ እስር ቤት ተገኝቼ በጠየኳቸው ጊዜ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስና ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ በዋናነት አፋጣኝ ‹‹ፍትህ›› ማግኘት እንደሚሹ ነበር በአንክሮ የነገሩኝ፡፡ ናትናኤል ፈለቀ ይህን በተመለከተ፣ ‹‹ትክክለኛ ፍትህ አገኛለሁ የሚለው ተስፋዬ በጣም መነመነ ነው ነገር ግን ቢያንስ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥ እሻለሁ፡፡ ክሳችንን በውል ሳናውቀው ወራት ተቆጥረዋል፤ የሚታይ ጠብ የሚል ነገር እያየን ግን አይደለም›› ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስም በተመሳሳይ፣ ‹‹ፍትህ መጠበቁ ሞኝነት አንደሆነ ይገባኛል ውሳኔው ምንም ይሁን ምን ግን አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥ እፈልጋለሁ›› ብሎ ነበር፡፡ ዳሩ ግን አሁን ባለው የተንዛዛ አሰራር ፍርድ ቤት መኖሩ፣ ዳኞች መሰየማቸው ብቻ ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ አያደርጋቸውም፡፡ የፍትህ ተቋማት የስርዓቱ አገልጋዮች በሆኑበት ሀገር አፋጣኝ ፍትህ ቀርቶ በተንዛዛው ሂደት ውስጥ አልፎም ቢሆን ትክክለኛ ፍትህን ማግኘት ቅዠት ይሆናል፡፡ ስለሆነም ዜጎች ፍትህ ያገኙ ዘንድ አጠቃላይ ስርዓቱን የመቀየር ወይም የማረቅ ትልቅ ስራ ይጠይቃል፡፡