ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ!
ሠላም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!? እንዴት ነዎት? ያስታውሱ ከሆነ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ
ከፊሉ የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች ‘ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ’ በሚል ርዕስ:
“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎትን የተለያዩ የመንግስት አካላት
የሕገ መንግስታችንን ድንጋጌዎች እየጣሱ ነውና እርስዎም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 74/13/ መሠረት ሕገ መንስቱን የማስከበርና የማክበር
ግዴታ ስላለብዎት ሕገ መንግስቱን ያክብሩ” በማለት አንዲት
አጭር ደብዳቤ ፅፈንልዎት ነበር፡፡
ድንገት በተለያዩ ምክንያቶች የጻፍንልዎትን ደብዳቤ ካላነበቡት ወይም ማስታወስ ካልቻሉ
ዛሬ ይሄን ማስታወሻ ስለምንፅፍልዎት ግለሰቦች አንድ ሌላ ማስታወሻ እንስጥዎ፡ ከ6ወራት በፊት /በሚያዚያ 2006 ዓ.ም/ ሶስት ጋዜጠኞችንና ስድስት ጦማሪያንን ‘ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን
በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ጠርጥሬያችኋለሁ’ በማለት መንግስትዎ ልማታዊ ርምጃ (አብዮታዊ ርምጃ እንደሚባለው) ወስዶ ነበር፡፡
እኛም የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች የዚህ ‘ልማታዊ ርምጃ’ ሰለባ የሆንን ግለሰቦች ነን፡፡
በርግጥ ከሁለት ዓመታት በፊት ‘ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስቱን’ ያስከብሩልን በማለት ጥያቄ ያቀረብንልዎት ግለሰቦች ‘ከ6ወራት
በፊት ሕገ መንግስቱን ለመናድ ሞክራችኋል’ በማለት መንግስትዎ ሲያስረን
ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ጠይቀን ሕገ መንግስቱን ለመናድ በመሞከር ወንጀል ተጠርጥረን ስንታሰር እስሩ በጣም ግራ አጋብቶን ነበር፡፡
በዚህ ያልቆመው መንግስትዎ ክሱን ‘ሕብረተሰቡንና ሀገሪቱን ለማሸበር አቅዳችኋል ሞክራችኋል አሲራችኋል…’ በማለት ወደ ‘ሽብርተኝነት’
ያሳደገው ሲሆን እርስዎም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳብዎትን ሲሰጡ ስለተመለከትንዎ ትንሽ ቅሬታ ይዘን መጣን፡፡
በቅድሚያ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በትንሹ ብናስረዳዎት ቅሬታችንን ለመረዳት ያስችልዎታልና
አንዳንድ ጉዳዮችን እንንገርዎት፡፡
ይሄን ማስታወሻ በምንፅፍልዎት ወቅት ከታሰርን ከ 200 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፣ነገር ግን
ጉዳያችን ገና በቅድመ ክስ (Pre Trial) የክርክር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም መንግስትዎ እንኳን
ለእኛ ለተከሳሾች ለከሳሽ አካልም ግልፅ ያልሆነ ክስ በማቅረቡ ነው፡፡ ይሄንንም ስንል ልትፈፅሙት ነበር የተባለው ‘የሽብርተኝነት
ድርጊት’ ሳይጠቀስ ‘በቃ የሽብርተኝነት ድርጊት ልትፈፅሙ ነበር’ በማለት በጨበጣ ስለመጣብን ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንግዲህ የብዙ ድብደባ፣ ዛቻ እና ስድብ ሰለባዎች ከሆንን በኋላም
የቀረበው ይሄ ክስ ነው ከ6 ወራት በኋላም ተከሳሾች ከሳሾቻችንም
ሳንረዳው በየቀጠሮው እየታሸ ነው የሚገኘው፡፡ ‘የተፋጠነ ፍትህ’ ሕገ መንግስትዊ መብት ነውና የተፋጠነ ፍትህ ይሰጠን፣ እርስዎም
ይሄን ሕገ መንግስታዊ መብት ያክብሩ እያልንዎት አይደለም ‘ሕገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ’
በማለት ‘ጥፋት የሚያሳምን’ ( አንዱ የዚህ ደብዳቤ ጸሃፌ ጦማሪ ጥፋት ብሎ አንዲፈርም የተገደደው ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ
ህገመንግስቱ ይከበር ማለቴ ጥፋት ነው ብሎ መሆኑ መንግስትዎን መልክ ግልጽ አድርጎ ያሳያል) መንግስት አለዎትና ይህ ጥያቄ አንደሚበዛብዎት
እናውቃለን፡፡
ይልቁንም ቀላልና ግልፅ ቅሬታን ነው ይዘን የመጣነው፡፡ ይሄውም የኢፌድሪ ሕገ መንግስት
በአንቀፅ 20/3/ ላይ
‘የተከሠሡ ሰዎች[…] በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር
[…]መብት አላቸው::’
በማለት የደነገገ ሲሆን፣ ይሄንን ሕገ መንግስታዊ መብትም ማንኛውም የመንግስት አካል እንዲሁም
ግለሰብ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እርስዎና መንግስትዎም በተደጋጋሚ ‘ሕገ መንግስቱ ሳይሸራረፍ እናስከብራለን’
ይላሉና ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የምታውቁት ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ከታሰርን ወዲህ ስለእኛ የእስር ጉዳይ በተጠየቁባቸው
ጊዜያት ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ ‘ፍርድዎትን’ በተደጋጋሚ ሲሰጡ ታዝበናል፡፡ እናስረዳዎ፡- ሐምሌ 12/2006 ዓ.ም
በሰጡት ጋዜጣሚ መግለጫ ላይ ስለእኛ እስር ጉዳይ ለቀረበልዎት ጥያቄ ሲመልሱ፡-
‘ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት ውስጥ አንዴ
ከገቡ በኋላ ብሎገር ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ ማለት ዋጋ የለውም’
በማለት ብዙ ነገሮችን ተናገሩ፡፡ ይሔውልዎት ስህተትዎ፡-
- የክሳችን ዋነኛ ጭብጥ በሃገር ውስጥ ‘የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም ‘የሽብርተኝነት’ ተግባራትን ለመፈጸም አሲረዋል፡ አቅደዋል… የሚል እንጂ፣ እርስዎም እንደሚሉት ‘ሰንሰለት’ ምናምን አይደለም፣
- እሺ አሸባሪዎችም ይበሉን፣ ነገር ግን ሕገ መንግስቱ እንደሚደነግገው በፍርድ ቤት ‘ጥፋተኝነታችን’ እስሚረጋገጥ ቢጠብቁስ ምናለበት? ይህ የሚያመለክተው እርስዎም እነደማእከላዊ መርማሪዎች ነፃ ሆኖ የመገመት (presumption of innocence) መብታችንን እያከበሩልን እንዳይደለ ነው፡፡
ይሄ ነገር የሆነው በድንገት ሊሆን ይችላል ብለን
ዝም ብንልም እርስዎ ግን በድጋሚ ጥቅምት 6/2007 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባል ለቀረበልዎ ጥያቄ
ሲመልሱ፡-
“የብሎገር ጭምብል
አጥልቆና በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሸሽጎ ከተከሳሽነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ሽብርተኝነትን መዋጋታችን ይቀጥላል…” እያሉ እርስዎ ያሉትን የብሎገር ጭምብል አውልቀውና ተሸሸጉበት ያሉትን የጋዜጠኝነት ሙያ
መሸሸጊያ አፍርሰው ባንዴ ‘የአሸባሪነት’ ካባ ደረቡልን፡፡
ክቡር ጥቅላይ ሚኒስቴር፣ እያልን ያለነው የአንድ ሰው ‘አሸባሪነት/ወንጀለኝነት’ የሚረጋገጠው
በፍርድ ቤት እንደሆነ ሕገ መንግስቱ ደንግጎ እያለ፣ እርስዎ ግን ነፃ ሆኖ የመገመት መብታችን ወደ ጎን ብለው እንደ ከሳሽም እንደ
ፈራጅም በመሆን ‘አሸባሪዎች’… እያሉን ይገኛሉ ነው፡፡
ምናልባት ‘ስራ አስፈጻሚው ከሳሽ ነውና እኔም የስራ አስፈጻሚው አካል መሪ ስለሆንኩ የፈለኩትን
አስተያየት የመስጠት መብት አለኝ’ ብለው ከሆነ፣ ሕገ መንግስቱን የማክበር ጉዳይ ‘ርስዎን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ላይ የተጣለ ግዴታ
ነው፡፡ እርስዎ ‘L’e’tat, c’est moi’ ይሉት አይነት የራስ ግምት ውስጥዎ ከሌለ በስተቀር እንዲህ በግልፅ እየጠየቅንዎት
‘ሕገ መንግስትቱን አላከብርም’ በማለት ገና ዋነኛ ክርክሩ እንኳን
ያልተጀመረ ክስን (ዋነኛ ክርክር ካለው) መሠረት በማድረግ ከዚህ በኋላ እኛን ‘አሸባሪዎች’ አይሉንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ይህን ተመሳሳይ ምላሽ “በእርግጠኝነት አሸባሪ ናቸው” በሚል ቃና ለቢቢሲ ለኢንቢሲ ለመሳሰሉት አለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማትም መስጠትዎን ሰምተናል፡፡
ሌላው ልናስታውስዎ የምንፈልገው ጉዳይ እንደኛ አይነት የተራገበ( በሰፊው በታወቀ የአደባባይ)
የፍርድ ጉዳይ ([un] popular case) ላይ የመንግስት አካላት አስተያየት (say) ያለውን ተፅእኖ እንዲያስቡት ነው፡፡
እርስዎ በምክር ቤት ቀርበው የአሸባሪነት ፍርድ ከበየኑብን (አሁን እያደረጉት እንዳሉት) ፍርድ ቤትም ሆነ ሌሎች የመንግስትዎ አካላት
ምን ሊያስቡ እንደሚችሉ አስተውለውታልን?!
ይሄን ሁሉ ስንልዎ እንዲያው ሕጉን ያክብሩልን ለማለት ያክል ነው እንጅ፣ ከሽብርተኝነት
ጋር የሚያገናኘን ቅንጣት ያክል እውነት /A segment of fact/ እንደሌለና የሰው ልጆች መልካምና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸው
ከመመኘትና ለአገራችን ያገባናል ከማለት ያለፈ ሕይወትም ፍላጎትም እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን እርስዎና መንግስትዎም ያውቁታል፡፡
ነገር ግን ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ጨዋታውን በግድ ካልተጫወታችሁ ተብለናልና እየተጫወትን ነው፡፡ የአሁኑ ጥያቄያችን ግን
በጣም ቀላል ነው፣ ጨዋታው ገና በደንብ እንኳን ሳይጀመር ውጤቱን እይወስኑት ነው፡፡
እርስዎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ደረጃ በወጡ ሰሞን አብዛኞች የዚህ ማስታወሻ
ፀሃፊዎች መጠነኛ ለውጥና ማሻሻዎች ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ሰንቀን “The First 100 Days” ወዘተ እያልን ብዙ ጠብቀንዎት
ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በሚበልጥ ግዜ እንደተመለከትንዎ ግን ተስፋችን ፍሬ ሊያፈራልን አልቻለም፡፡ አሁንም አዲስ ተስፋ ሰንቀን
ግን ፡- “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እባክዎትን ሕገ መንግስቱን ያክብሩ!
የእኛንም መብት ያክብሩልን” እንላለን፡፡
‘’የብሎገር ካልሲ
አድርጎ፣ የጋዜጠኝነት ጫማ ተጫምቶ የሽብረተኝነት ሰንሰለት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሕገ መንግስቱን ያክብሩልኝ ማለት ዋጋ የለውም!’’
በማለት ተስፋችን ዋጋ እንደማያሳጡት ተስፋ አለን፡፡
ከአክብሮት ጋር
ጦማርያን ጋዜጠኞች
ዘላለም ክብረት ኤዶም ካሳዬ
ናትናኤል ፈለቀ ተስፋለው ወ/የስ
በፍቃዱ ሃይሉ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ
አጥናፍ ብርሃኔ
አቤል ዋበላ
ማህሌት ፋንታሁን