Wednesday, October 3, 2012

የሴቶች ወጪ <=> የወንዶች ገቢ



ሴቶች በዝግመተ ለውጥ ካለመቆጠር ወደ መቆጠር ከመቆጠርም አልፈን ‹ከስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት አለች› የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ተፈጥሮና ባህላችን ተደማምረው አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የሴትና የወንድ የሆኑ ነገሮች እንዲለዩ ሆነዋል፡፡ የሥራ ዘርፍ፣ የትምህርት ዘርፍ፣ አለባበስ፣ አነጋገር፣ አካሄድ፣ አጻጻፍ፣ ባሕሪ፣ አመለካከት… ሁሉም የሴት እና የወንድ የሚባሉ አሏቸው፡፡ ጥልቅ የመመራመር ክህሎትን በሚጠይቁ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ ሴቶች የተቀረነውን ወክለው የተቀመጡ እንጂ እንደወንዶቹ እራሳቸውን ብቻ ወክለው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹የመጀመሪያው የወንድ ጄኔራል› የሚባል ነገር ሰምተን አናውቅም፡፡ ‹በመጀመሪያ ወደጠፈር የተጓዘው ወንድ› ሲባል ልንሰማም አንችልም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያውኑ ወደ ጠፈር የመጓዝ ተግባር እና የጦር አዛዥነት ሥራ የወንድ ብቻ ተደርጎ ስለሚቆጠር እና በዘርፉም የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶቹ ጋር ሊነፃፀር የሚችል ስላልሆነ ነው፡፡

በአገራችን ከተለመዱና የወንዱ ተግባር ተደርገው ከሚቆጠሩ ነገሮች አንዱ ወጪዎችን የመሸፈን ኃላፊነት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ‹ሴትማ አትከፍልም› እየተባለ የከፋይነት ሥራ የወንድ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ማኅበረሰባችን ለወንድ የወጪ ሸፋኝነት ኃላፊነት ሲሰጥ በውስጥ ታዋቂነት ጥሮ ግሮ በሚያፈራው ኃብት የሚመሰርተውን ቤተሰብ የማስተዳደር ሥራ ከሱ እንደሚጠበቅ ይረዳዋል፡፡ ስለዚህም በተሰማራበት ዘርፍ ጠንክሮ በመሥራት ገቢውን ማሻሻል የሕይወት ዘመኑ መመሪያው ይሆናል፡፡ ከሴት የሚጠበቀው ጥሩ ሚስት እና እናት እንድትሆን ነው፡፡ የራሷ ገቢ የምታገኝበት መተዳደሪያ ወይም ሥራ ያላት ብትሆንም እሰየው ነው፤ ባይኖራትም ግን ችግር የለውም፡፡ እንዲኖራት አትገደድም፡፡

ወንድየው ወደፊት ለሚያገባት ሚስቱና በጋራ ለሚያፈሯቸው ልጆች ማስተዳደር እንዲችል ገቢውን ለማሳደግ እና ኃብት ለማፍራት ተግቶ ይሠራል፡፡ ‹ቤት ሳይኖረኝ› ‹ቋሚ ሥራ ሳልይዝ› ‹ጥሩ ደሞዝ ሳይኖረኝ› የሚሉ ወንዶች እንጂ ሴቶች እምብዛም አይደሉም፡፡ ባጭሩ ማኅበረሰባችን ለሴቶችና ለወንዶች ብሎ ሁለት የተለያየ የተግባር መንገድ አስቀምጦልናል፡፡ በሴቷ መንገድ የሚገኙ ወንዶች  እንዲሁም በወንዱ መንገድ የሚገኙ ሴቶች ቢኖሩም በአብዛኛው ሴቱም ወንዱም በተመደበለት መንገድ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ይህ አመዳደብ ወንዶችን የሴቶች የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሆነው በበላይነት እንዲመሩን ያደርጋቸዋል፡፡ እኛ ሴቶችም በአብላጫ ድምፅ ያፀደቅንላቸው ይመስላል፡፡

የዩንቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ከሴት ጓደኞቼ ጋር እራት እንብላ ብለን የካፌ ምግብ ትተን በከተማው ወደሚገኝ ሬስቶራንት ከሄድንባቸው ጊዜያቶች በአብዛኛው ለማለት ባልደፍርም ሒሳባችን በማናውቀው ሰው ተከፍሏል እንባል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ግብዣው ሲደጋገምብን ነገሩ ጣመንና እራሳችን ስንከፍል መበሳጨት ደረጃ ደረሰን ነበር፡፡ የሚከፍልልን እንደማናጣ በመተማመን ምንም ሳይኖረንም ወጥተን እራት እስከማዘዝ የደረስንበት አጋጣሚም እንዲሁ ትንሽ አልነበረም፡፡


በሥራ ዓለም ያለች አንድ ወዳጄ ስታጫውተኝ ከጓደኞቿ ጋር በእረፍት ቀናቸው የሚጋብዛቸው ወንድ ለማግኘት ፕሮግራም እንዳለበት ሰው ዘንጠው፣ ረፈድፈድ ሲል ተያይዘው ይወጡና መጋበዝ የሚፈልጉበት ሬስቶራንት ወይም ሆቴል አካባቢ ያለ ካፍቴሪያ ይቀመጣሉ፡፡ መቼም  ከሦስት ወይም ከአራት ሴት ቢያንስ አንዷ በእረፍት ቀን ደውሎ ‹ምሳ ልጋብዝሽ› የሚል አድናቂ አታጣምና  የተደወለላት ሴት ያለችበትን ቦታና ከጓደኞቿ ጋር እንደሆነች በማሳወቅ መምጣት እንደሚችል ትነግረዋለች፡፡ ይመጣና እዛው ሻይ ቤት ቆይተው ምሳ ሰዓት ሲደርስ ‹የት እንብላ?› ሲባል ያው በቅርብ የሚገኘው ሬስቶራንት ወይም ሆቴል ይመረጥና  ያሻቸውን ይበላሉ ያማራቸውን ይጠጣሉ፡፡ ከፋዩ የታወቀ ነው፡፡ ጋባዡን ያመጣችው ሴት ከጎኑ ከሌሎቹ በተለየ ቀረብ ብላ የመቀመጥ የውዴታ ግዴታ አለባት፡፡ ሊጋብዝም አይደል! ይህ ሰው በድጋሜ ላግኝሽ ብሎ ላይደውልላት ቢችልም ግድ አይሰጣትም፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ አይደል የሚባለው ለሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የሌላ ጓደኛቸው አድናቂ ወይም አዲስ የሚገኝ ስፖ (ስፖንሰር ተቆላምጦ ሲጠራ) አይጠፋም፡፡ ይህ ሁኔታ በጠንካራ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ የፍቅር ሕይወት ስትጀምር ወይም ትዳር እስክትይዝ ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡

ከወዳጄ የሰማሁትን በምሳሌነት ጠቀስኩ እንጂ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሌሎች በቁጥርና በዓይነት የበዙ ታሪኮች ያደባባይ ሚስጥር መሆናቸው የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ እንዲያውም አንባቢ ቢያንስ አንድ ከዚህ ጋር የተያያዘ እውነተኛ ገጠመኝ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአስተያየት ቢያሰፍረውም ደስ ይለኛል፡፡

ሴቶች ፍቅረኛ ከመያዛቸው በፊት ‹በስፖንሰር የመዝናናት እና ወጪን መሸፈን› መርሕ ላይ የተመሰረተ ኑሮ ለምደው፥ ፍቅረኛቸውን ወይም የትዳር አጋራቸውን በሚመርጡበት ወቅት ምርጫ ውስጥ የሚያስገቡት ወንድ ከስፖዎች ያልተናነሰ ወጪያቸውን ሊሸፍን የሚችለውን ነው፡፡ ከጓደኛቸው ያልተናነሰ ኑሮ ለመኖር ከመሻት ወይም የተሻለ ከመመኘት እና ቤተሰብን ለማስደሰት ያላቸውን ፍላጎት ለሟሟላት በዕድሜ በጣም ከሚበልጧቸው፣ ከውጭ አገር ዜጎች እና ባለትዳር ከሆኑ ጋር የፍቅር ግንኙነት ይጀምራሉ፡፡ ‹ሴቶች ፍቅረኛቸውን የሚመርጡበት ዋነኛው መስፈርት የኃብት መጠን ነው› የሚል ትችት ከወንዶች በተደጋጋሚ የሚሰነዘረውም ለዚህ ይመስላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚመሰርቱት የፍቅር ጓደኝነት ወይም ትዳር ሴቶችን በቀጥታ የወንዶች የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶቹ ወጪያቸውን በራሳቸው ችለው ለመኖር ስለማይችሉ ባያምኑበትም ለወንዱ ትእዛዝ እና ፍላጎት ተገዝተው እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡

በርግጥ ለሴቶች እንዲህ ዓይነት ባሕሪ ማሳየት ማኅበረሰባችን ከፍተኛውን ሚና ቢጫወትም በተለይ በጉዳዩ ላይ ተዋናይ የሆኑት ወንዶችና ሴቶች ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም፡፡ በዋነኝነት ግን ከወንዱና ከሴቱ ተጠያቂው ማነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ጉዳዩን እንደማውራት ቀላል አይደለም፡፡ ከዶሮና ከእንቁላል ማን ቀድሞ ተፈጠረ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ወንዶች ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን ተጠቅመው በሚያገኙት ገቢና ኃብት በመጠቀም አብራቸው የፍቅር ጊዜ ለማሳለፍ የምትፈቅድ ሴት እስክትገኝ ድረስ ያለመሰልቸት ሴቶችን ለማዝናናት ሲያውሉት ምንም አይመስላቸውም፡፡ ገቢያቸው እራሳቸውን ለማዝናናት የማይፈቅድላቸው ሴቶችም ወጪያቸውን ሸፍነው ሊያዝናኗቸው ፈቃደኛ በሆኑ ወንዶች ይደለሉና በስፖንሰር የመዝናናት መስመር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ገንዘቡን ለዚህ ተግባር የሚያውል ወንድ ባይኖር ሴቷ በዚህ መስመር አትገኝም፤ እንዲሁም ገንዘብ የማያማልላት ሴት ብትኖር ኖሮ  ወንዱ የፈለጋትን ሴት ለማግኘት ገንዘቡንና ሃብቱን ባልተማመነ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የችግሩ መንስኤ ‹ሴት ናት›፣ ‹ወንድ ነው› ብሎ ለመፍረድ የሚከብድ የሚሆነው፡፡ እንዲያውም በመሀል ቤት የሴትና የወንድ የፍቅር ግንኙነት ወደ ‹ነፃ ገበያ›ነት እንዳይጠጋ ስጋት አለኝ፡፡

ስለዚህም ወንዶች ገንዘባቸውንና ኃብታቸውን ተማምነው ሴቶችን ለማጥመድ የሚያደርጉትን ጥረት እና ወጪዎችን መሸፈናቸውን በመተው እኛ ሴቶች የራሳችንን ወጪ መቻል እንዳለብን እንድናስብ ቢያደርጉ፤ ሴቶች ደግሞ ‹እቤት ከመዋል› ብለን ብቻ መሥራታችንን ትተን ገቢያችን ወጪያችንን እንዲችልልን የተቻለንን ሁሉ ጥረት ብናደርግ፣ ፍላጎታችንን ከገቢያችን ጋር ብናመጣጥነው እና ዓላማ ኖሮን ለምንመሠርተው/ለመሠረትነው ኑሮ በኢኮኖሚ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረግ ብንጀምር እንዲሁም የራሳችን የሆነ አቋም ቢኖረን ወደፊት ብዙ ለውጦችን እናያለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የአሁን ዘመን ወጣት ሴትና ወንዶች የመጪው ትውልድ ወሳኝ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነንና፡፡

በመጨረሻም፣ ይህ ጽሑፍ የማይወክላቸው ጥቂቶች እንዳሉ ሳላስታውስ አላልፍም፡፡

No comments:

Post a Comment