Showing posts with label journalism. Show all posts
Showing posts with label journalism. Show all posts

Monday, September 19, 2016

ማኅበራዊ ሚዲያው እና የመንግሥት ስጋት



በተስፋዬ ዓለማየሁ

የማኅበራዊ ሚዲያውን አጠቃቀም በተመለከተ ተከታታይ ዘመቻዎች እና ማጥላላቶች በተለያዩ ግዜያት በሕትመት ሚዲያው ሳነብ፣ በብሮድከስት ሚዲያውም ሳደምጥ ቆያቻለሁ፡፡ እነዚህን የአጠቃቀም ጉድለቶች ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች ታዲያ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስመለከታተቸው ነው የሰነበትኩት፡፡ ምክንያቱም መሰል ፈራጅ ዘጋቢ ፊልሞች በሕትመት ሚዲው ላይ ይሠሩ እና ጠንከር ያለው እርምጃ ይከተል ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በመጀመሪ የኮረኮረኝ ጽሑፍ "ከማኅበራዊ ሚዲያው በስተጀርባ" በሚል ርዕስ በሪፖርተር ገዜጣ ላይ ከወጣ በጣም ቆየት ብሏል፡፡  የጽሑፉ ዋና ዓላማ የነበረው ከማኅበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታ ‹በስተጀርባ ያለውን አደጋ ነው ማመመልከት› ነበር፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅም በሚገባ አስረጅ ምሳሌዎችን አስቀምጠው ጠቀሜታውንም ለመዳሰስ ሞክረው ጽሑፋቸውን ቢያበቁም፣ ከዚያ በኋላ በተከታታይ እንዲሁ በተለያዩ ግዜያት ቅኝታቸው ማኅበራዊ ሚዲያው ከጥቅሙ ባሻገር ጉዳቶቹ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን አንብቤያለሁ፡፡ እርግጥ ነው በተነሱት ሐሳቦች ዙሪያ የማኅበራዊ ሚዲያው፣ በዋነኛነትም ፌስቡክ ከጥቅሙ በዘለለ ባሉት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ላይ መሠረታዊ ልዩነት ከጸሐፊዎቹ ጋር የለኝም፡፡ "የጥላቻ ንግግሮችን ማስተላለፊያ ነው"፣ "አሉባልታ ማሰራጫ ነው"፣ "የሠራ ግዜን ይሻማል"፣ "በቅርባችን ካሉ ወዳጅ ጓደኞቻቸችን ጋር ይለያየናል"፡፡ ሌሎችም የፌስቡክ እንከኖችን እያስታወስን መዘርዘር አንችላለለን፡፡
  
ማኅበራዊ ሚዲያው ግን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ልንዘነጋው አይገባም፡፡ የማኅበራዊ ሚዲውን ችግሮች ማሳየቱ ለተጠቃሚው አጠቃቀሙን እንዲፈትሽ ስለሚያደርጉ መልካም ሊባል ቢሆንም፡፡ ችግሮቹን ማጉላቱ ላይ ግን አልስማማም፡፡ ከሚጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ለራሳችን በጣም ተስማሚ የሆኑ ችግሮች አይጠፉምና በአግራሞት ወይም በድንጋጤ "ይህማ የእኔም ችግር ነው" የምንለው እና ለችግሩም ተጋላጭ እንደሆንን፣ በደንብ እንዲሰማን የሚያደርጉን ማሳያዎች ስለሚዘረዘሩ ሊያሸማቅቁን ይችላለሉ፡፡ ይህንን ስሜት ከመፍጠር ተሻግረው ግን በሕትመት ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ የሚተላለፉት መልዕክቶች ውጤታቸው  (ኢፌክታቸው) ምን ያህል እንደሆነ ትዝብቱን ለየግላች ልተወውና፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ንበማስተዋል መጠቀም የሚለው ምክር ላይም እንስማማና፣ ፌስቡክ በአሁኑ ሰዐት ሁነኛ አማራጭ ሚዲያ እንደሆነ ለማሳየት የሚከተለውን እጽፋለሁ፡፡

መነሻ፤ በአገራችን የሕትመት እና የብሮድካስት ሚዲያ ሁኔታ ወፍ በረር ቅኝት

በአገራችን ውስጥ ያለት የብሮድካስት እና ሕትመት ሚዲያዎች ከሚጠበቅባቸው አንፃር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በአግባበቡ እያገለገሉን አይደለም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ልንደረድር እንችላለለን፤ የጋዜጠኞች ብቃት ማነስ፣ የጋዜጠኞች የሥነ ምግባር ጉድለት፣ የጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለቤቶች የፖለቲካ ፍላጎት እና አመለካከከት፣ የገበያው ትርፋማነት እያልን በርካታ ምክንያቶችን ብንደረድርም "የእናቴ መቀነት…" ከመሆን አይዘልም፡፡  ምክንያቱም በእነዚህ ሰበቦች ወይም ችግሮች ውስጥ እንኳን የጋዜጠኝነት መርሖዎችን ለማክበር ከመሞከር ይልቅ ሲጥሷቸው በግልጽ ይስተዋላሉ እና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ጠንከር ባሉ ሁሉን ዐቀፍ ተሳትፎ እና ውይይት በሚፈልጉ አገራዊ፣  ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም በዕኩል ደረጃ አያሳትፉም አያገልግሉም፡፡ አብዛኛዎቹ የአገራች ሚዲያዎች በጣም የተካኑባቸው እና የሚሽቀዳደሙባቸው ዘገባዎች በጣም ለስለስ ያሉ ማኅበራዊ፣ የመዝናኛ እና የስፖርት፣ የኪነ ጥበብ፣ የፊልም እና የፋሽን ጉዳዮች ናቸው፡፡

Tuesday, April 5, 2016

ተመስገንን በጨረፍታ

በማሕሌት ፋንታሁን

መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ተቋማት ጋር ማቆራኘት ሳያስፈልገው የጻፈው ጽሑፍ ብቻ ተጠቅሶበት የተከሰሰ እና የተፈረደበት ብቸኛ ጋዜጠኛ ነው - ተመስገን ደሳለኝ። በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተመሠረተችው ፍትህ ጋዜጣ ጥቂቶቹን የግል ሕትመት ሚዲያ ውጤቶች የተቀላለችው በ2000 ነበር። ከምርጫ 97 በኋላ የተከሰተውን የግል ሚዲያ እጥረት አሳስቦት እና የበኩሉን ለመወጣት ብሎ ነው ፍትሕን ለመመሥረት የተነሳሳው። ፍትሕ ጋዜጣ ሕትመት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2004 ሐምሌ ወር (ላይ እስክትታገድ ድረስ) ድረስ ከዓመት ወደ ዓመት የሕትመት ብዛቷ እየጨመረ መጨረሻ አካባቢ እስከ 35ሺ ኮፒ ትታተም ነበር።


ማንኛውም ዓይነት ቅድመ ሳንሱር እንደሌለ በሚደነግገው ሕገመንግሥት መተዳደር ያለበት ፍትሕ ጋዜጣን የሚያትመው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ የሐምሌ 13/2004 ዓም እትም ላይ ስለ መለስ ዜናዊ የተጻፈ ዜና ካልወጣ እንደማያትሙ አሳወቁ። ይህን የሰማው ተመስገን እያረጉ ያሉት  ቅድመ ሳንሱር መሆኑን፣ ይህ ደግሞ በሕገመንግሥቱ የተከለከለ መሆኑን ከገለጸላቸው በኋላ የታዘዙትን 30ሺ ኮፒ ካተሙ በኋላ እንዳይሰራጭ ከፍትሕ ሚኒስቴር በተላለፈ ትዕዛዝ መሠረት ማገዳቸውን እና የታተመው ጋዜጣም መወረሱን በደብዳቤ ገለፁ። ለ30ሺ ኮፒ ሕትመት፣ ለጸሐፊዎች የሚከፈል እና ለተለያዩ አስተዳደራዊ  ወጪዎች የወጣው ገንዘብ ወደ100ሺ ብር የሚጠጋ ከስሯል። ነሐሴ 2 ቀን  2004 ክስ እንደተመሠረተበት ፋና ዜና ላይ እንደሰማ የሚናገረው ተመስገን፣ በዜናው እንደሰማውም በቀጣይ ቀጠሮ ነሐሴ 9 ቀን 2004 ፍ/ቤት ቀረበ። በ2003 እና በ2004 በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በወጡ 5ት ጽሑፎች ሦስት ክስ እንደቀረበበት ተነግሮት የዋስትና መብቱንም ተነፍጎ የዛኑ ቀን ወደ እስር ቤት ገባ። ለስድስት ቀናት በቃሊቲ ጨለማ ቤት ከቆየ በኋላ ባልተጠበቀ ሰዓት እና ምክንያቱ ሳይነግው  ነሐሴ 16/2004 ከእስር ተለቀቀ። በኋላ ሁላችንም እንደሰማነው ከእስር የተለቀቀው ክሱ ተቋርጦለት መሆኑን ነው።