Friday, November 30, 2012

የጉዞ ማስታወሻ የቀሰቀሰው የጉዞ ማስታወሻ ከታሪካችን ታሪክ ምጸቶችና ቁጭቶች ጋር!


በፍቅር ለይኩን

የበፍቄ የጉዞማስታወሻ4 ዓመታት በፊት ከአንድ አማርኛን አቀላጥፎ መናገርና መፃፍ ከሚችል በእጅጉ ካስደነቀኝ ሰው ጋር ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተጉዤ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለሁለተኛው ድግሪ ማሟያ የሚሆነውን የምርምር ጽሑፍ የመጀመሪያዎቹ የሙስሊም እምነት ተከታዮች በነቢዩ መሀመድ ትዕዛዝ ወደ አክሱም ግዛት ያደረጉትን ስደት ዋቢ በማድረግ፡-

አክሱማውያን በወቅቱ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር የነበራቸውን ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ለመመረቂያ የሚሆነውን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ከአሜሪካዋ የሜኔሶታ ግዛት ከመጣ አንድ አሜሪካዊ ነጭ ጎልማሳ ጋር የኢትዮጵያችንን የጥንታዊ፣ የማእከላዊና የቅድመ ዘመናዊ ታሪክና ሥልጣኔ እምብርት የሆኑትን ሰሜናዊ ከተሞቻችንን አብረን ተጉዘን ለማየት ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡

ምንም እንኳን በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ Department of History and Heritage Management/በታሪክና በቅርስ አስተዳደር የትምህር ክፍል፡- ታሪክ፣ አርኪዮሎጂና ቅርስን ባጠናም ስለ ታሪካችንም ሆነ ስለ ቅርሶቻችን በዓይን አይተን፣ በእጆቻችን ዳሰን ምስክርነት ለመስጠት ትምህርቱ ተግባራዊ ድጋፍ የታገዘ ባለመሆኑ ከቃል የዘለለ እውቀት ለማግኘት አልታደልንም ነበር፡፡ አሁንም ድረስ በአብዛኛው በቃል ትምህርት ላይ የተደገፈው የዩኒቨርስቲው የትምህርት ሥርዓት ለዚህ ዕድል እንድንበቃ ሁኔታዎችን የሚያመቻች አይደለም እናም እውቀታችን ፊደል ዘመምነት ሚያጠቃው ነበር ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡

ይህ አሜሪካዊ የጉዞ ወጪዬን በሙሉ ሸፍኖልኝ በመጽሐፍ ብቻ ማውቃቸውን የትናንት ታሪኮቻችን፣ ዓለምን ጉድ ያሰኘውን ሥልጣኔያችንና ቅርሶቻችንን ሕያዋን ምስክሮችን በዓይኔ ለማየት በመቻሌ ራሴን እንደ ትልቅ ዕድለኛ ነበር የቆጠርኩት በወቅቱ፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እንኳን አክሱምን፣ ላሊበላንና ጎንደርን ቀርቶ በዚህ በቅርባችን የሚገኙትን ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶቻችንን ስለ መጎብኘት ማውራት የቅንጦት ያህል እንዳይቆጠርብኝ በሚል አንዳች አሉታዊ ስሜት ውሰጤን ተጫነው፡፡

የጉዞ ማስታወሻ፤ ሥልጣኔ ወደላይ እና ወደታች



አክሱም ከአዲስ አበባ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ያውም በመኪና፣ ያውም ያንን ጠመዝማዛ መንገድ ለተጓዘ ሰው አንድ ሺሕ ነገር መጠበቅ አያስገምተውም፡፡ ጥያቄው ‹በምስል እና በተንቀሳቃሽ ምስል ያየነውን፣ ተጽፎ ያነበብነውን በአካል ሲያዩት እንዳሰቡት ይሆናል ወይ?› ነው፡፡

ከመቐለ ወደ አክሱም ስንጓዝ ውቕሮ (ከጠበቅናት በላይ የደመቀች ከተማ)፣ አዲግራት፣ አድዋ (ከጠበቅናት የደበዘዘች) ከተማን አቆራርጠናል፡፡ አድዋ ከተማ ጦርነቱ የተደረገበት ተራራ ሥር የባንዲራ መስቀያ እና የመታሰቢያ ጽሑፍ የተጻፈበት እምነበረድ ነገር መኖሩን በመኪናው ፍጥነት አስተውያለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰሞን ብዙ ተወርቶለትና ገንዘብ ተሰብስቦለትም የነበረው የአድዋ ተራራ ላንድማርክን ፍለጋ ዓይኔን ወደላይ ባንከራተትም ማየት አልቻልኩም፤ አብረውኝ የነበሩትን የአገሬው ሰዎችም ብጠይቃቸው የሚያውቁት ጉዳይ የለም፡፡

አክሱም ከተማ የዕድሜዋን ያክል አይደለችም፡፡ ጎስቋላነቷ ገና ከደጃፏ ያሳብቃል፡፡ እንዲያውም አካባቢውን የምታውቀው ወዳጃችን እንዳጫወተችን ከሆነ ከፎቅ አቅም እንኳን አብዛኛዎቹ የተገነቡት ከ2000 ወዲህ ነው፡፡ ማረፊያችንን ካመቻቸን በኋላ ወደአክሱም ሐውልቶች መጓዝ ጀመርን… አዲሱ የአክሱም ከተማ እና አሮጌው የተያያዙ ናቸው ከአዲሱ ወደአሮጌው የጥቂት ደቂቆች የእግር ጉዞ በማድረግ ይደረሳል፡፡ ያቺው ወዳጃችን ‹‹የአሁኗ አክሱም የበፊቱ አክሱም ላይ ነው የተገነባችው›› የሚባል አባባል እንዳለ ነገረችን፤ ቢቆፈር ከስር የሚወጣ ጥንታዊ ከተማ አይጠፋም በሚል ዓይነት፡፡ ጥቂት እንደተጓዝን ፊት ለፊታችን አየነው - አክሱምን ቆሞ አየነው፣ የአክሱም ሐውልቶችን ቆመው አየናቸው፡፡


ከተተከለ ጀምሮ እንደቆመ ያለው የአክሱም ሐውልት ትንሽ በመዝመሙ መወጠሪያ በአንድ ጎን ተደርጎለታል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከሮም በፊታውራሪ አመዴ እና ሌሎችም ትግል የመጣው፣ እንደታጠበ ዓይነት አዲስ መልክ ይዞ በግርማ ሞገስ አጠገቡ በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ቆሟል፡፡ ሌላኛው እና ትልቁ የሚባልለት ደግሞ ከአዲሱ ጥቂት ሜትሮች ፈቀቅ ብሎ ተሰባብሮ ተኝቷል፡፡ ተሰባብሮ የተኛው ውፍረቱ ሲያዩት ከሁለቱም እጅግ የገዘፈ እንደሆነ ያሳብቃል፡፡ የቆሙት ሐውልቶች በጥቂት ስኩዌር ሜትሮች ስለታጠሩ መጠጋት አይቻልም፡፡ ከወደቀው አክሱም ስር ዋሻ ነገር አለ፡፡ የዋሻው ኮርኒስ ላይ ያሉት ግዙፍ አለቶች እንዴት እንደተቀመጡ የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ሰዎች ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡

Thursday, November 29, 2012

እንሄዳለን - አትሄዱም




ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በህዳር ወር የመጨረሻ ቀኖች ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ‹ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በማለት የሚጠራቸው ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተዘዋወሩ ይጨፍራሉ፣ ይዘፍናሉ ይደሰታሉ፤ ቀኑም ከዎነኛ የሕዝብ በዓላት እንደ አንዱ ተቆጥሮ በከፍተኛ ትኩረት ሲከበር ይውላል፡፡ ነገር ግን ከዘፈኑ እና ከጭፈራው በተቃራኒ ከነዚህ ሕዝቦች ጉያ የወጡትና ‹ጫካ ቤቴ› ያሉት የእነሱ ልጆች ‹‹ቤተሰቦቻችን አብረውት ከሚጨፍሩት ሕዝብ ጋር አብረን መኖር አንፈልግም፤ መገንጠልን እንሻለን!›› በማለት ነፍጥ አንግተው ትግል እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ነው The Ethiopian Paradox - የኢትዮጵያ አያዎ::

ሀገር ከወዴት?

የሀገር አፈጣጠር (State Formation) ምሁራን አን ወጥ ስምምነት ላይ ካልደረሱባቸው የህብረተሰብ ግንዛቤዎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ሀገር በመልካም ፈቃድ እንጅ በጉልበት ሊፈጠር አይችልም፤ ከተፈጠረም እደገና ፈርሶ በአዲስ ልክ መገንባት አለበት የመለው ሀሳብ በአንድ በኩል ሲቀርብ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አይ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ልንወቅሰው አንችልም ሀገር በተለያዩ መንገዶች (by Hook or Crook) ልትፈጠር ትችላለች፡፡ ታሪክ እንዳሳየንም ሀገሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደማይገነቡ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት የGiuseppe Garibaldiዋ ጣሊያን፣ ‹ሀገራችን መገንባት ያለበት በBlood and Iron ነው› ብሎ የገነባት የOtto von Bismarck ጀርመን፣ የአንድነት ማህበሩን ለቆ መውጣት አይቻልም በማለት በጉልበት አንድነቷ የፀደቀላት የAbrham Lincolnዋ አሜሪካንን መጥቀስ ይቻላል ሲሉ ሀሳባቸው ይሰነዝራሉ፡፡ እንግዲህ አነዚህን ሁለት የተራራቁ ሀሳቦችን ማቻቻል ነው የሀገር ግንባታ ዋነኛ አላማ፡፡

መገንጠል እንደ መብት

የሀገሮች መኖር መሬት ላይ እውነታ ቢሆንም የተለያዩ ምሁራን መገንጠልን እንደ መብት በማየት ነገር ግን ለመገንጠል መሟላት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ፡፡ ይሄንም ተንተርሶም ሁለት መሰረታዊ የመገንጠል መብት ህልዮቶች (Theories) ይቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው መገንጠልን እንደ መፍትሄ (Remedial Secession) የሚመለከተው ህልዮት ሲሆን፤ የዚህ ሀሳብ ደጋፊ ምሁራን እንደሚሉትም የአንድ ሕዝብ መገንጠል በሀገሪቱ ላለው ችግር እንደ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ከሆነ እና ይህ ተገንጣይ ክፍል ተነጥሎ ጉዳት እየደረሰበት ያለ (A continuing injustice and gross Human Right violation) ከሆነ መገንጠል አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ይላሉ፡፡ የሁለተኛው ህልዮት አቅራቢ ምሁራን ግን የመገንጠል መብት ራሱን ችሎ የቆመ መብት (Primary Right) ሲሆን ፤ አንድ ሕዝብ መገንጠል ከፈለገ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይህ ቀዳሚ መብቱ ሊከበርለት ይገባል የሚሉ ናቸው፡፡

ሕገ መንግስቱስ

Cass Sunstein የተባሉ የሕገ መንግስት ምሁር “Constitutionalism and Secession” ባሉት ፅሁፋቸው የመገንጠል መብትን በሕገ መንግስት ደረጃ መቀበል ከሕገ መንግስታዊነት (Constitutionalism) ጋር የሚጋጭ ሀሳብ እንደሆነ ሲያስቀምጡ  ‹‹በታላቅ መርህ የሚመራ ዲሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ለመመስረት በብዙሃኑ (Majorities) የሚወሰንን ውሳኔን መቀበል ይኖርብናል፣ ነገር ግን  ውህዳኑ (Minorities) የመገንጠል መብት ካላቸው የብዙሃኑን ውሳኔዎች አንቀበልም በማለት የእንገነጠላለን ጥያቄ አቅርበው ውሳኔውን ሊያኮላሹት ይችላሉ፤ እንዲሁም የመገንጠል መብታቸውን እንደ ጥቅም መጠየቂያ (Bargaining tool) ሊጠቀሙበት ይችላሉ›› ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እንደ Allen Buchanan ያሉ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የመገንጠል መብትን በሕገ መንግስት ገደብ በማበጀት መብቱ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው የሚል ሀሳብ ይቀርባሉ፡፡ የዚህ ሀሳብ ደጋፊዎች ማጠናከሪያቸውን ሲሰነዝሩ፤ መብቱ በሕገ መንግስት ደረጃ ተቀባይነት ማግኝቱ ዜጎች የራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው እንዲከበርላቸው ያደርጋል ብሎም ወደ ሀገሪቱ መቀላቀል የሚፈልግ ሌላ ግዛት ይሄን ሕገ መንግስታዊ መብት እንደ ዋስትና ተጠቅሞ ሀገሪቱን መቀላቀል እንዲችል ያደርገዋል በማለት ነው፡፡  
ኢትዮጵያዊ የመገንጠል ሀሳብ

ባለፉት ሀያ ዓመታት በኢትዮጵያ ግሎ እና ገኖ ሲያነታርክ የከረመ ሀሳብ ዝርዝር ብታዘጋጁ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠልን የሚያክል ግዝፈት የነሳ ሀሳብ በቀዳሚነት ሊኖራችሁ ይከብዳል፡፡ የሀሳቡ አቀንቃኞች ጉዳዩን ወደ ፖለቲካዊው ተወስኦ (Political Discourse) ያስገቡት በ ‹ያ ትውልድ› አቢዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በዋናነት በኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር (ጀብሃ) ኤርትራን ነፃ የማውጣት እንቅስቃሴ የተጀመረው የእንገነጠላለን ጥያቄ፤ በኤርትራ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ሻዕቢያ) ተጠናክሮ በመቀጠል፤  ከሰሜኑ የሀገራችን ጫፍ ተነስቶ ቀስ በቀስ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ሕወሃት) በመጀመሪያ ማንፌስቶው ‹ትግራይን ከኢትዮጵያ ነፃ አወጣለሁ› ብሎ እንዲያውጅ አደረገው፡፡ በዚህ ያላቆመው ጥያቄ በአስገራሚ ሁኔታ ወደ መሀከላዊ የሀገሪቱ ክፍል ዘልቆ ከሀገሪቱ ሕዝቦች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘውን የኦሮሞ ሕዝብን ገንጥለን ነፃ እናወጣዋለን የሚለውን የኦሮሞ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ብቅ አለ፤ ጥያቄው በዚህ አላበቃም  ይልቁንም ወደ ምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በመሄድ ኦጋዴንን ነፃ አወጣለሁ የሚሉ ሀይሎች እንደ እንጉዳይ ፈሉ፤ አፋርም ‹እኔም አይቅርብኝ› በሚል ‹እገነጥልሃለሁ› የሚሉ ልጆቹን ወደ ጫካ አሰማራ፡፡ 

ለብዙሃኑ ተገንጣይ ሀይሎች እንደ ምክንያት የሚቀርበው ጉዳይም የታሪክ መዛባት ነው፤ በተለይም በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጊዜ የተከናወኑ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ እንቅስቃሴዎች ያስከተሏቸው ክስተቶች፡፡ ብዙሃኑ ተገንጣይ ሀይሎች ‹በማዕከላዊው የአቢሲኒያ መንግስት የቅኝ ግዛት ተፈፅሞብናል፤ ይሄም ቅኝ አገዛዝ በዋነኛነት ስር የሰደደው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነው› ሲሉ እንደ ኤርትራ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ያሉት ሀይሎች ደግሞ ‹አፄ ምኒልክ ለአውሮፓ ሃይል አሳልፈው ሰጥተውናል› በማለት ጉዳዩን ‹ከሽያጭ› ጋር ያያይዙታል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ በህወሃት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ዙፋን ላይ ሲወጣ ኤርትራ ‹ተገንጥያለሁ› ብላ ስንበት አቀረበች፤ ሄደችም፡፡ በኤርትራ መገንጠል ማግስት የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስትም የመገንጠል መብት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ (As a primary Right) በሕገ መንግስት መፈቀድ አለበት የሚለውን ህልዮት በመቀበል በዝነኛዋ አንቀጽ 39 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ፡

 ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያለው መብት በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው::››  

በማለት ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ (Unconditionally) ተገንጥሎ የራሱን ሀገር መመስረት እንደሚችል ‘አበሰረ/ አረዳ’፡፡ ይሄም የኢፌድሪን ሕገ መንግስት የመገንጠል መብትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚፈቅድ ብቸኛው  የጊዜያችን የዓለም ሕገ መንግስት አደረገው፡፡

የፌደራሉን ሕገ መንግስት ተከትለው የወጡት የዘጠኙም ክልሎች ሕገ መንግስቶች በተመሳሳይ ቃላት በአንቀፅ 39 የመጀመሪያ ንዑስ አንቀፅ ላይ ከፌደራሉ ሕገ መንግስት በበለጠ እና ከረር ባለ መልኩ፡ 

‹‹የ … ብሄር/ ብሔረሰብ/ሕዝብ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያለው መብት በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡›› 
በማለት እጅግ የሰፋ መብትን ‘unconditionally’ እና ‘with no restriction’ የሚሉ መረን ዘለል ቃላትን ተጠቅመው በመስጠት የጉዳዩን አነታራኪነት ጫፍ አስነኩት፡፡ 

The Nuclear Option

ብዙ ኢትዮጵያዊያን በተለይም አንድነትን በማንኛውም መንገድ የሚያፈላልጉ (Ultranationalists) ኢትዮጵያዊያን የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ይሄን የተለጠጠ መብት መስጠቱ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን አንድነት ባለመፈለጉ ነው፤  መጀመሪያ በትግል አጀማመራቸው ወቅት መገንጠልን እንደ ዓላማ ይዞ የተነሳ ፓርቲ የሀገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ እንደማይፈልግ ግልጽ ነው፤ የኤርትራን መገንጠልም ያለምንም ዝግጅት እና ቅድመ ሁኔታ መፍቀዱ የዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋሙ መገለጫ ነው፡፡›› በማለት በሕገ መንግስቱ የተሰጠው የመገንጠል መብት ኢትዮጵያን የሚበታትን የጥፋት አማራጭ (The Nuclear Option) እንደሆነ፤ ‹‹የመብት ጉዳይ ቢሆን እዚህ መብት ላይ ርቆ ከመሄድ ይልቅ አንድ የሚያደርገንን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት መስራት ይቻል ነበር፡፡›› እያሉ የመገንጠል መብትን በእጅጉ ይፀፉታል፡፡

እፀ በለሰ፡ የሚታይ እንጅ የማይበላ ፍሬ

ሌሎች ደግሞ መብቱ መኖሩ መልካም ነው፤ ነገር ግን መብቱ የሚታይ እንጅ የማይበላ ነው በማለት ሕገ መንግስቱን ተቀብለው ኢህአዴግን ይጠላሉ፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የመገንጠል መብትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ መብት ማስቀመጡ የሚታይ ነገር ቢሆንም፤ ይሄን መብት እናራምዳለን ብለው የተነሱ ሀይሎች ‹በሀገሪቱ ጠላነት ተፈርጀን ከፖለቲካ ሜዳው ተባረናል፤ እኛ የምንታገልለት ሕዝብም አፈናው በርትቶበታል›፤ ብለው ሮሮቸውን ያሰማሉ፡፡ እነዚህ ሀይሎች ድምዳሜያቸውን ሲሰጡም ‹በሕገ መንግስቱ የተቀመጠው የመገንጠል መብት ጥቅም ላይ የማይውል ከሆነ፤ ከዛሬ ነገ ይህ መብት ይከበርልኛል ብሎ ለመብቱ የሚታገለውን ሕዝብ ማሳዘን ስለሚሆን፤ ከመብትነቱ ቢፋቅ ይሻላል› በማለት ተስ ቢስነትን የሚያመላከት ሀሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ እውነት መብቱ እንዲህ ሩቅ ነው? ብለን ስንጠይቅ፤ አብዛኞቹ ይሄን መብት ለማስከበር ‹ዱር ቤቴ› ያሉ ፓርቲዎች በህገወጥነት መፈረጃቸው ማስተዋላችን መልሳችን አዎንታዊ እንዲሆን ሊያስገድደው ይችላል፡፡ 

ኢህአዴግ ሲመልስ - ‹አይ ይሄ መለስ አይሆንም› ሲባል

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹ለምን መገንጠል መብትን በሕገ መንግስት ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ተደረገ› ተብለው በተደጋጋሚ ሲጠየቁ የሚጡት አንድ ምላሽ ነበር፡፡ ‹‹ደርግ በወደቀ ማግስት ከሶማሌ ክልል የመጡ ተወካዮች በሉ አስከፊውን ስርዓት ስላስወገዳችሁልን እናመሰግናለን፣ አሁን እኛንም እንደ ኤርትራ አሰናብቱን አሉን፡፡ እኛም ትንሽ ሰከን በሉ እስኪ፤ በግዴታ እኛ ጋር ቆዩ አንላችሁም፡፡ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ስትኖሩ በደል የሚደርስባችሁ ከሆነ የመገንጠል መብታችሁን የሚቀበል ሕገ መንግስት እናዘጋጃለን ብለን ተመሳሳይ ጥያቄ የነበራቸውን ሕዝቦች  በዚህች አንቀፅ መለስን›› ይላሉ፡፡ 

ኢህአዴግ በተደጋጋሚ በተለያዩ ሰነዶቹ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሲሰጥ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 39 ኢትዮጵያን እንደ ዮጎዝላቪያ ከመበታተን ያዳነ መልዓክ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ ለዚህም ምክንያቱን ሲያቀርብ ‹‹በአንቀፅ 39 ላይ ሁለት መሰረታዊ መብቶች አሉ እነዚህም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት (Internal Self Determination) እና የመገንጠል መብት (External Self Determination) ናቸው፡፡ አንድ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ብሔር ወይም ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ (ምንም እንኳን የሶስቱን ቃላቶች ልዮነቶች ፓርቲው ባያመለክትም) የመጀመሪያው መብቱ ካልተከበረለት ሁለተኛውን መብት እንዲጠቀምበት መፍቀድ ዋነኛ የመፍትሄው አካል ነው፤ ይሄም ሕዝበች በፍቃዳቸውና በፍላጎታቸው የፌደሬሽኑ አካል እንዲሆኑ አስችሏቸዋል›› በማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ተችዎች ሲተቹ፤ ለሶማሌ ሕዝብ ተወካዮች የተሰጠው ‹እስኪ ቆይታችሁ በስርዓቱ ችግር ከደረሰባችሁ መገንጠል ትችላላችሁ› የሚል መልስ ለምን ለኤርትራስ አልቀረበላትም? እንዲሁም ዛሬ እንደ ሶማሌ ባሉ ክልሎች ብዙ የመገንጠልን ዓላማ ያነገቡ ፓርቲዎች ‹እባካችሁ መብታችን እንጠቀምበት› ብለው ሲጠይቁ ለምን ያኔ ቃል እንደተገባላቸው መብቱን ወደ መሬት አልወረደላቸውም? በማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ኢህአዴግ ‹‹አንቀፅ 39 ላይ ሁለት መሰረታዊ መብቶች አሉ እነዚህም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት (Internal Self Determination) እና የመገንጠል መብት (External Self Determination) ናቸው፡፡ አንድ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ‹ብሔር› ወይም ‹ብሔረሰብ› ወይም ‹ሕዝብ› የመጀመሪያው መብቱ ካልተከበረለት ሁለተኛውን መብት እንዲጠቀምበት መፍቀድ ዋነኛ የመፍትሄው አካል ነው፡፡›› ብሎ መከራከሪያውን ቢያቀርብም፤ ተችዎች በበኩላቸው በዚህ ሀሳብ ላይ ሁለት መሰረታዊ ህፀፆችን እንዳሉ ያስቀምጣሉ፡፡

አንደኛው ሕገ መንግስቱ መገንጠል መብት ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው (Unconditional) ሕገ መንግስታዊ መብት እንደሆነ ያስቀምጣል እንጅ የውስጥ መብት ረገጣን (Injustice) እንደ ቅድመ ሀኔታ አያስቀምጥም፤ ይሄም ኢህአዴግ እንደሚያስቀምጠው እንደ ዋስትና የተቀመጠ መብት ብቻ ሳይሆን፤ መረን የለቀቀ የመብት እደላ ነው ይላሉ፡፡ 

ሁለተኛው ፓርቲው በሚያስቀምጠው የጉዳዩ ትክክኛነት ማረጋገጫ (Justification) ላይ የሚቀርበው ትችት ደግሞ፤ ‹የፌደራላዊ ስርዓት ተገንጣይ ሀይሎችን ከአንድነት ሀይሎች ጋር አስተሳስሮ ህልውናን ማስጠበቅ ሆኖ እያለ የመገንጠል መብትን መፍቀዱ ፌደራላዊ ስርዓቱን ቅልጥሙን መስበር (A Shoot in the Foot) ነው› የሚል ነው፡፡

ታዲያ መፈትሄውስ?

ግማሹ ሀይል የመገንጠል መብት በሕገ መንግስት መፈቀዱን ‹እነዚህ ገንጣይ-አስገንጣዮች ጉድ ሊያደርጉን እኮ ነው› እያለ፤ ይህች ‹መዘዘኛ› አንቀፅ እያለ ጉዳዩን ይፀየፈዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ‹ዋ! በኋላ እዚሁ ጎልተናችሁ እንዳንሄድ› እያለ የመገንጠል መብትን እንደ ‹ማስፈራሪያ› በየቦታው ይመዛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለረጅም አመታት የመገንጠል ጥያቄን አንግበው የነበሩ ሀይላት ሳይቀር (በከፊልም ቢሆን) ‹እንነጋገር፣ እንወያይ፤ ተፈራርቶ እና ተፎካክሮ ሀገር አይገነባም› እያሉ ነው፡፡ 

እናም ጉዳዩን ከመፀየፍ እና እንደ ማስፈራሪያ እየመዘዙ ከመነታረክ ባለፈ፤ እነዚህ የተለያዩ ሀይላት ወደ መሀል መጥተው በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸው መልካም ነው፡፡ መንግስትም ሕገ መንግስቱን እንደ አይነኬ ቅርስ በመቁጠር ስለ ጉዳዩ መጥፎነት ሲነሳበት ‹ያለፈውን ስርዓት ናፋቂ› እያለ፤ መብቱን የሚጠይቁ ሀይላት ሲነሱ ደግሞ ‹ጠባቦች፣ አንዴ በሕገ መንግስት የተፈታን ችግር እያነሱ የፖለቲካ ትርፍ ማጋበስ የሚፈልጉ የትርምስ ሀይላት›  ብሎ መፈረጁን ትቶ፤ ‹እሽ እንነጋገር› ማለት መቻል ይኖርበታል፡፡ ያኔ የህዳር ወሩ ፌሽታ እና ደስታም እውነት ይሆናል፤ ነገር ግን እኛ የማንግባባ ከሆነና እርስ በራሳችን የምንጠቋቆም ከሆነ፣ የኛን ችግር ከእኛ ውጭ ማን ይፈታልናል? ፌሽታውስ ታህሳስ ወርን እንኳን በቅጡ ሊሻገር ይችላልን?

Wednesday, November 28, 2012

የሰሞኑ ጦማሮች እፍታ


ማሕሌት ፋንታሁን

በኢትዮጵያ የሚገኙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በባለፈው ዓመት 246,360 የነበረው በአሁኑ ዓመት በአስገራሚ ፍጥነት 839,580 መድረሱንና ነገር ግን ካለን የሕዝብ ብዛት ሲነፃፀር 0.95 ፐርሰንት ያክሉ ብቻ ተጠቃሚ እንደሆነና ከዚህም ውስጥ የገዢው ፓርቲ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች እንደሚበዙ - ከሌሎች ሃገራት ጋር በማነፃፀር ያስነበበን ኢትዬ ቼንጅ የተሰኘ ጦማር ነው፡፡ ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

አብዪአዲ የሚገኘውና በጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ስም ተሰይሞ የቆየው የሁለተኛ ደረጃ /ቤት ስያሜው ተቀይሮ በመለስ ዜናዊ ስም እንዲሰየም መወሰኑን ታማኝ ምንጮች ማስታወቃቸውን የገለፀው ይኸው ኢትዮ ቼንጅ ጦማር ሲሆን የተጻፈው በኢየሩሳሌም ስዩም ነው፡፡ “በደርግ ዘመን የተሰራውና በራስ አሉላ ስም ተሰይሞ 9-10 ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ 2002 . ጀምሮ የት/ቤቱን አቅም ለማሳደግ በሚል 11-12 መማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ አዋጥተው ሥራው መከናወኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል። ግንባታው ተጠናቆ ባለፈው ነሐሴ ወር ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ እንዳለ አቶ መለስ በማለፋቸው ፕሮግራሙ መሰረዙን ሲታወቅከሁለት ሳምንት በፊት በተከናወነው የምረቃ ሥነ-ስርአት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በስፍራው እንደተገኙ ማወቅ ተችሎዋል።” ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

ይሄው ጦማር ባሳለፍነው እሁድ ኅዳር 16/2005ዓ.ምን አንድነት ፓርቲ አዘጋጅቶት በነበረው ፕሮግራም ላይ የውይይቱ አቅራቢ እና የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ‹የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታና የወደፊት የትግል አቅጣጫ› በሚል አርዕስት ያቀረቡትን ጽሑፍም አስነብቦናል፡፡ ሙሉው እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡


ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ሁለት የሃገራችን ከፍተኛ የጦር አመራሮች፤ የመከላከያ ሚኒስቴሩ አቶ ሲራጅ ፋጌሳ እና ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ኢንቨስትመንትን ለማስተዋወቅ በሚል ምክንያት መሄዳቸውን በተመለከተ መግለጫ ሳይሰጥ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚገኙ የሚያወራው ኢትዮ ሴንተር ጦማር ነው፡፡ ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

“ለሕሊና እስረኞች የሚሟገተው ፍሪደም ናው (‘Freedom Now’) የሚባለው ድርጅት የእስክንድር ነጋን ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያላግባብ የታሠሩ ሰዎችን ጉዳይ ለሚያጠናው ግብረኃይል ማቅረቡ ታወቀ።” የሚለን ፊንፊኔ የተሰኘ ጦማር ነው፡፡ በተጨማሪም ግብረ ኃይሉ በቀረበለት መመልከቻ ላይ በመጭው ሚያዝያ ውሣኔ እንደሚሰጥ እንደሚጠበቅም ገልጧል።

የመጨረሻዎቹ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል ለመጓዝ ተዘጋጅተዋል::130,000 ኢትዮጵያውያን ይሁዲዎች ወደ እስራኤል ይበራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው:: በማርች 2014 ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው ይህ ኦፕሬሽን የኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ ምዕራፍ መዝጊያ ተደርጎ ታስቧል::” የሚለን ደግሞ የሚኒሊክ ሳልሳዊ ጦማር ነው፡፡ AFPን ጠቅሶ ያቀረበውን ሙሉ መረጃ እዚህ ላይ ያገኙታል፡፡

እዚህ የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ደግሞ በፍቃዱ ኃይሉ የመቀሌ የአንድ ቀን ቆይታውን ‹የጉዞ ማስታወሻ፤ መቐለን በአንድ ቀን› በሚል ርዕስ ያስነበበን ሲሆን ስለ መቐሌ ከተማዋና ዝቦቿ፣ የአፄ ዮሓንስ ቤተ መንግሥት፣ የሰማዕታት መታሰቢያ እና ሙዚየም በአንድ ቀን እንደታዘበው ያቀረረበበት ነው፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡