Monday, March 28, 2016

ዞን ዘጠኞች ዳግሞ ወደ ፍርድ ቤት

(Zone 9 Update)

ሚያዚያ 17/2006 በድንገት ከያሉበት ተይዘው የታሰሩት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች በሐምሌ 08/2006 የተፃፈ ክስ ሐምሌ 11/2006 ‹ስለ ፀረ-ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3/2/ እና 4 ተላልፋችኋል› በሚል ክስ ቀርቦባቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ክስ ከቀረበባቸው አስር ግለሰቦች መካከል አምስቱ ሐምሌ 01/2007 በድንገት ከሳሽ ክሱን አንስቻለሁ በማለቱ ከእስር የወጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ አምስት ግለሰቦች ላይ ግን ከሳሽ የመሰረተውን ክስ ቀጥሎበት ያቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ጉዳዩን የያዘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት መርምሮ በጥቅምት 05/2008 በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፉ ብርሃኔ እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ‹የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳይገባቸው በነፃ ይሰናበቱ› በማለት ብይን የሰጠ ሲሆን፤ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት የቀረበበትን ክስ ወደ መደበኛው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 256/ሀ/ በመቀየር ክሱን እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡

በተሰጠው ውሳኔ መሰረትም ነፃ የተባሉት የዞን ዘጠኝ አባላት ከእስር የተለቀቁ ሲሆን በመደበኛው ወንጀል ሕጉ መሰረት ክሱን እንዲከላከል የተወሰነበት በፍቃዱ ኃይሉ በሃያ ሽህ በር ዋስትና ከእስር ተለቋል፡፡ ነገር ግን ‹በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ› በማለት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በታህሳስ 04/2008 የተፃፈ ይግባኝ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ይግባኝ አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ከሳሽ በፅሁፍ አለኝ ያለውን ቅሬታ በቃል ሰምቶና የተከሳሾቹን ምላሽ በማዳመጥ ለነገ መጋቢት 20/2008 ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምን ሊከሰት ይችላል?

በነገው የፍርድ ቤት ውሎ ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ የጨረሰ ከሆነና ‹ተጨማሪ ማስረጃ አያስፈልገኝም› የሚል ከሆነ ሶስት የተለያዩ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

የመጀመሪያው ነገር ‹የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው› በማለት የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማፅናት የተከሳሾቹን ነፃነት ማስጠበቅ ነው፡፡

ሁለተኛው ሊከሰት የሚችለው ጉዳይ ደግሞ ከመጀመሪያው በተቃራኒ የከሳሽ ቅሬታን ተቀብሎ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ‹ተከሳሾቹ ክሳቸውን እንዲከላከሉ› የሚል ውሳኔ በመስጠት ተከሳሾቹን ዳግም ወደ እስር ቤት መመለስ ነው፡፡

ሶስተኛው የሚጠበቀው ጉዳይ የስር ፍርድ ቤት 2ኛ ተከሳሽን በፍቃዱ ኃይሉን የሚመለከት ሲሆን፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሰረት አንድ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይ በተመሳሳይ ጊዜ በሁለት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ክሱን ሊከታተል ስለማይገባ ከሕግ አግባብ ውጭ በፍቃዱ ላይ የቀረበውን ይግባይ ውድቅ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማፅናት ይህ በመናገር ነፃነት ላይ የተሰነዘረን ጥቃት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ይሰጠዋል የሚል ተስፋ አለን፡፡

Friday, March 25, 2016

የኛ ኦማር አፊፊዎች የት ናቸው?በላይ ማናዬ

ኦማር አፊፊ (Photo: ahl-alquran.com)
ኦማር አፊፊ በለበሰው የፖሊስ የደንብ ልብስ ኩራት ይሰማዋል፤ ፖሊስነቱን ይወደዋል፡፡ በተለይ በሚከፈለው ደመወዝ እና በደህንነቱ ምክንያት ስራውን አብዝቶ ይፈልገው ነበር፡፡ ኦማር አፊፊ ግብጻዊ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1981 (ልክ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ወደ ስልጣን ሲመጣ) በ16 አመቱ ወደ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ገባ፡፡ ኦማር በፖሊስነት ስራው ለማህበረሰቡ አንዳች ነገር እንደሚያበረክት አምኗል፡፡

ሆኖም ወጣቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የደንብ ልብሱን ለብሶ ወደ ሰፈሩ ሲሄድ የሰዎች እይታ ተቀየረበት፡፡ ተንከባክበው፣ ሲያጠፋ መክረው ያሳደጉት የሰፈሩ ሽማግሌዎች ሳይቀር የፖሊስ ልብሱን ለብሶ ሲያዩት ከመቀመጫቸው ተነሱለት፡፡ ኦማር ድርጊቱ ከአክብሮት ይልቅ ፍርሃት ያዘለ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
‹‹መንግስት ማንም ዜጋ ፖሊስን እንዲፈራ በመፈለግ በዚያ ሁኔታ ቀርጾታል፡፡ ፖሊስ በህብረተሰቡ ዘንድ አሸናፊነት (ተፈሪነት)ን አስርጹዋል›› ይላል ኦማር አፊፊ፡፡ ሁሉም ፖሊሶች ህዝብን የሚበድሉ እንዳልሆኑ ቢያውቅም ኦማር ለፖሊስነት ካለው አክብሮት ጋር የህዝቡ ምላሽ ደስ አላለውም፡፡ ኦማር በዚህ ስሜት ሁለት አመት እንደሰራ በሦስተኛ አመቱ ላይ አንድ ለየት ያለና ህሊናውን የሚፈታተን ነገር ገጠመው፡፡

Monday, March 21, 2016

የመካከለኛው አውሮጳ ክፉ መንፈስ

(Scepticism and Hope በሚል ርዕስ የተሰበሰቡ 16 መጣጥፎች ውስጥ  The Ghosts of Central Europe የሚል ርዕስ ያለውን በLajos Grendel የተጻፈ ጽሑፍ አቤል ዋበላ እንደሚከተለው ተርጉሞታል።)

ላጆስ ግሬንድል  እንደጸጻጻፈው፣
አቤል ዋበላ እንደተረጎመው

ባንድ ወቅት ስሎቫኪያዊው የክፍሌ ተማሪ  ሀንጋሪያዊ ቢሆን ኖሮ ራሱን በመስኮት እንደሚወረውር ነገረኝ፡፡ በምን ምክንያት እንደዚህ ሞኛሞኝ  ጸባይ እንደሚያሳይ ስጠይቀው ሲያጉተመትም እና ሲያጉረመረርም ቆይቶ በመጨረሻ ሀንጋሪያዊ መሆን የሚያስጠላ ነገር እንደሆነ ከአፉ አመለጠው፡፡ ልክ እንደሆነ ሲገለጥልኝ የጋመው ንዴቴ በድንገት በረደ፡፡ ሀንጋሪያዊ መሆን የሚያስጠላ ነገር ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ቼካዊ፣ ስሎቫካዊ፣ ሩማኒያዊ፣ ጀርመናዊ፣ ይሁድ፣ ሩሲያዊ ወይም ጂፕሲ እንደመሆን የሚደብር ነው፤ ይህን የምለው ኢስቶኒያዊ፣ ላቲቪያዊ ወይም ሉቲኒያዊ ላለማለት ነው፤ ቺቺኒያውያን ወይም በአዘርባጃን የተከበቡትን አርመኒያውያንን ጭራሽ አልጠቀስኩም፡፡

ከራሴ ጋር በሐሳብ ስጫወት . . . ስሎቫኪያዊ ብሆን ምን እሆን ነበር ብዬ አሰብኩኝ፡፡ ስሎቫኪያዊ ብሆን ኖሮ  በታሪክ መስመር ተንከባልዬ እስከ 1993 ጠብቄ  በመጨረሻም  የራሴው ሀገር የሀገርነት ሰርተፊኬት በአንዳንድ የውጪ ሀይሎች መልካም ፈቃድ ላይ እንዳልተመሰረተ  ከመረዳቴ በፊት ሀንጋሪያውያን እና ቼኮችን ይቅር ለማለት አልችልም ነበር፡፡ ቼካዊ ብሆን ኖሮ አባቶቼና አያቶቼ በጣም በሚዘገንን ጭካኔ ጋርደው ከትውልድ መንደራቸው ያካለቧቸውን  ሶስት ሚሊዮን ጀርመናውያንና የእነርሱን ዘር ማንዘር ብቀላ በመፍራት እኖር ነበር፡፡ ፖላንዳዊ ብሆን ኖሮ  እንደስዊዝ አይብ ቤቴን በተደደጋጋሚ ቆርሰው የተካፈሉትን ሁለቱን ሁሉንቻይ ጎረቤቶቼን ሩሲያውያን እና ጀርመናውያን መርሳት አልችልም ነበር፡፡ ይሁድ ብሆን ኖሮ በጀርመን ጦር አብዛኞቹን የምወዳቸውን፣ ዘመዶቼን፣  ጓደኞቼን እስኪሞቱ ድረስ በጭስ የመታፈናቸውን እውነታ እንዴት ይቅር ማለት እችላለው?  ጂፕሲ ብሆን ኖሮ በቀን መቶ ጊዜ ልተወው ብስማማም የቆዳዬ ቀለም ከመገኛዬን ማጋለጡ አልቀረም፡፡ እንግሊዞች አይሪሾች ላይ የሰሩትን፣  ፈረንሳዮች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ባልሆኑ ዜጎቻቸው ላይ ያደረጉትን እና እነዚህ ሁለቱም በየቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ ያደረጉትን ህልቆ ማሳፍርት (ad infinitum) በመዘርዘር  መቀጠል እችላለው፡፡

ዛሬ ብሔርተኛ፣ ፀረ-ሴማዊ እና ዘረኛ መሆን  በትሁት ማኀበረሰብ ዘንድ ምስጋና ይደረሳቸውና የተለመደ አይደለም ፡፡ ምንም እንኳን አሁንም ይህ የአህጉር ክፍል የሚያንባርቁ እና የሚደሰኩሩ አክራሪ ብሔርተኛነትን የሚያቀነቅኑ ትጉኃንን እያስተናገደ ቢሆንም ይህ እውነታ በሁለቱም በመካከለኛው አውሮጳ እና በባልካን  በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የጨቃላ ትናንሽ ሀገሮች ቀውሶች ኋላቀር ንትርክ  ወይም በምርጥ አገላለጽ የበጥባጭ ህጻናት ተንኮል አዘል ቧልት  የሚመስለው ከምዕራብ ሲታይ  ሊሆን ይችላል፡፡ በተፈጥሮ ስሜታዊ የሆኑት ሀገር በቀል የመካከለኛው አውሮጳ ዜጎች ግን  ምን ያህል ትንሽ ብቻ እንደገባቸው ተረድተው በበቂ ሁኔታ ሊገረሙ አይችሉም፡፡ እርግጥ ነው አልገባቸውም፡፡ ግን እነርሱ እራሳቸው ምዕራቡ ዓለምን በትክክል ስላልተረዱት ብቻ ሳይሆን፣ በነጻነት ከቦታ ቦታ መጓጓዝ ባለመቻላቸው፣ ውስጣዊ ጥልቅ ስሜቶቻቸው ሳይቀር በመንግስት ቁጥጥር ስር በመዋላቸው አሁን አሁን የእነርሱ የትውልድ ሀገር የምድር እምብርት እንደሆነች ወደማመን መጥተዋል፡፡ እናም አሁንም ያ በትክክል የሆነው ነው፡፡

Monday, March 7, 2016

የስድስት ሰዓት ሴት ተጠያቂዎችበማሕሌት ፋንታሁን

ጥቂት ስለ ቃሊቲ የሴቶች መቆያ እና ማረሚያ ቤት

የማይቻል ነገር እንደሌለ በተግባር ለማየት ከሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዱ የእስር ቤት ሕይወት ነው። እስር ቤት እንገባለን የሚል እሳቤ በአይምሯችን ውስጥ ስለማይኖር በአብዛኛው ከተለመደው የኑሮ ዑደት (መወለድ፣ ማደግ፣ መማር፣ መሥራት፣ ማግባት፣ መውለድ፣ ማደርጀት እና መሞት) እና ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተን ነው የግል አቋማችንን የምንቀርፀው። "ከሰው ጋር መተኛት አልወድም/አልችልም፤ እንቅልፍ አይወስደኝም"፣ "ስፕሪስ ሳልጠጣ መዋል አልችልም"፣ "የቀዘቀዘ ምግብ አልወድም"፣ "ሲጃራ ሳላጨስ መኖር አልችልም"፣ "በቀን ቢያንስ ሁለት ፊልሞችን ካላየሁ አልደሰትም"፣ "እከሊትን/እከሌን ሳላይ መዋል አልችልም"፣ "ጨለምለም ካላለ ወደ ቤት መግባት አልወድም"፣ "መብራት ካልጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም" እና የመሳሰሉ የማይለወጡ የሚመስሉን አቋሞቻችን ፈተና ውስጥ የሚወድቁት የእስር ሕይወትን ‹ሀ› ብለን ስንጀምር ነው። ብዙ አልችልም ብዬ የማስባቸውን ነገሮችን ችዬ ስለወጣሁበት ስለ ቃሊቲ የሴት እስረኞች ግቢ ጥቂት ልበላችሁ።

በቃሊቲ እስር ቤት ግቢ ውስጥ ከሚገኙት 8 ዞኖች ሁለቱ የሴት እስረኞች የሚኖሩበት ነው። በአንደኛው ዞን በቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሴቶች  በሌላኛው ደግሞ የተፈረደባቸው ሴቶች ይኖሩበታል። ልዩ ጥበቃ ወይም  የቅጣት ቤት የሚባሉ ቤቶች አሉ። ወይም በተፈለገበት ሰዓት ይሠራሉ። ለምሳሌ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከማንም እስረኛ ጋር እንዳትገናኝ 5ት ሰው ብቻ የሚኖርበት የቅጣት ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው። ISISን በመቃወም ከተጠራው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ሚያዚያ ወር 2007 የታሰሩ ሴቶች ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ ለብቻቸው በተሠራላቸው ቤት ይኖሩ ነበር።

በቀጠሮ ዞን ደግሞ 5 ቤቶች ያሉ ሲሆን በፍርደኛ ግቢ 6 ቤቶች አሉ።አንድ ቤት ውስጥ ከ 40 እስከ 120 እስረኞች ይኖራሉ። ቀጠሮ ግቢ ከአንዲት አነስተኛ ሱቅ በስተቀር ሌላ ምንም ስለሌለ የተለያዩ ነገሮችን ለመገበያየት  እና ፀጉር ቤት ለመጠቀም  ፍርደኛ ግቢ መሄድ ግድ ይላል። ቤተሰብ መጠየቂያ ቦታው የፍርደኛ ግቢን አቋርጦ የሚገኝ ቦታ በመሆኑ፤ በቤተሰብ መጠየቂያ ሰዓቶች (ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2:30 እስከ 6:00 ከሰዓት ከ7:30 እስከ 10:00 እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ከ2:30 እስከ 6:00)፤ ቀጠሮ ክልል የሚገኙ እስረኞች ከፍርደኛ ክልል ማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ይችላሉ።  በቀጠሮ እና ፍርደኛ ክልል መሐል 200 ሜትር ገደማ ርቀት ያለው ሲሆን በየግቢዎቹ በር እና ማማዎች ላይ ጠባቂ ፓሊሶች አሉ። ዞኖቹ (ቤቶቹ)  ከአስተዳደር ጀምሮ በእስረኞች በተመረጡ የእስረኛ ኮሚቴዎች ይመራል። በየቤቱ ለሊት የሚደረግ ጥበቃ አለ። ሮንድ ይባላል። እያንዳንዷ እስረኛ ተራዋ በደረሰ ቀን ለሁለት ሰዓት ከሌላ አንድ እስረኛው ጋር ይጠብቃል። ከለሊቱ 5:00 ሰዓት እስከ 7:00 እና ከ7:00 ሰዓት እስከ 9:00 ሮንድ ተረኞች የሚጠብቁበት ሰዓት ነው።  የእስረኞች ቆጠራ በቀን ሁለቴ ይካሄዳል። የጠዋት ገቢ ፓሊሶች ከጠዋቱ 12:00 ላይ፤ 11:30 ላይ ደግሞ የማታ ገቢ ፓሊሶች ቆጥረው ይረከባሉ።

የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች

ከላይ የጠቀስኳቸው የእስረኛ "መብቶች" እኛ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ጋር ሲደርስ ቅንጦት ይሆናሉ። እንኳን በውናችን በሕልማችንም አናስበውም። "ይቺም ቂጥ ሆና ለሁለት ተከፈለች" ዓይነት ነገር ነው። ያም መብት ተብሎ  ተሸራርፎ  ሲሰጠን እና ስንከለከል "All animals are equal but some are more equal" የሚለው አባባል ትዝ ይለኛል። የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ማለት በሽብር ወይም በአመፅ ማነሳሳት የሚል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በቀጠሮ ክልል ሆነው የሚከታተሉ ወይም ተፈርዶባቸው ፍርደኛ ክልል ያሉ ሴቶች ማለት ናቸው። ስያሜው የመጣው ከቤተሰብ ጋር ከምንገናኝበት ሰዓት የተወሰደ ነው። የምንጠየቀው 6 ሰዓት ላይ ብቻ ሲሆን እኔ በቆየሁባቸው ጊዜያት ከ10 ደቂቃ እስከ 30 ደቂቃ ለሚሆን ቅፅበት ነበር። የመጀመሪያዎቹ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ለ5 ደቂቃ ብቻ ይገናኙ እነደነበር ሰምቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪም የምንጠየቀው  በቅርብ ቤተሰቦች ብቻ ነው። ያለንበት ዞንም ሆነ ቤት በኮሚቴነት መመረጥም መምረጥም አንችልም። ሮንድ ጥበቃ እኛን አያካትትም። ፍርደኛ ግቢ ሄዶ መገበያየት ይናፍቀናል። ቢበዛ የ6 ሰዓት ተጠያቂ ያልሆነ (ኖርማል) እስረኛ እንድንልክ ቢፈቀድልን ነው። ሆኖም ግን አስጠጪ እስረኞች ሰበብ ፈልገው የሚላኩትን ኖርማል እስረኞች ለአሸባሪ ይላላካሉ የሚል ክስ ስለሚያቀርቡባቸው፤ የሚላክልን ማግኘት እስቸጋሪ ነው።


ክሊኒክ እና ፀጉር ቤት ለመሄድ ስንፈልግ ለብቻችን አጃቢ ተመድቦልን ነው። የምትመደብልን አጃቢ ፀጉር ቤት ውስጥ ገብታ ተሰርተን እስክንጨርስ ጠብቃ ይዛን ትመለሳለች። ይሄ ሲገርመን የሆነ ጊዜ ላይ ፓሊሶች የሚሰሩበት ፀጉር ቤት እንድንጠቀም መመሪያ ተላለፈ። ይህ መመሪያ ከተላለፈ በኋላ የሆነ ቀን ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ፀጉር ቤት ለመሄድ ጠይቃ፤ አጃቢዋ እየወሰደቻት የተላለፈውን መመሪያ ስትነግራት  "እኔ እስረኛ ነኝ። ለምንድነው የፓሊስ ፀጉር ቤት የምሰራው? ይቀራል እንጂ!" ብላ ፀጉሯን መሠራቱን ትታ ተመለሰች። እስክትወጣ ድረስም በአቋሟ እንደፀናች ነበር። ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬም የሚደርስብንን መገለል በመቃወም ፀጉሯን በመላጨት መልዕክት አስተላልፋአለች።