ስለ ቅድመ
ምርመራ ስናወራ ሃሳቡን በጠንካራ ሁኔታ ተግባራዊ ያደረገው የደርግ መንግስት ሳይጠቀስ አያልፍም፡፡ ከዚያ በፌት በነበረው ጊዜ ‹ንጉሥ
አይከሰስ ሰማይ አይታረስ› የሚለው አስተሳሰብ በስፋት ስለሚታመንበት ንጉሡን ከሚያወድስ እና የንጉሡን ፈቃድ ከሚያሟላ የህትመት
እና የብሮድካስት ስራዎች ውጪ ለመስራት ሃሳብ አልነበረም፡፡ የደርግ
መንግስት የንጉሡን ስርዓት ካስወገደ በኋላ ደግሞ የቅድመ ሳንሱር ጉዳይን ጠበቅ ባለ በሕግ ደንግጎ ቀረበ፡፡ ሳንሱር ሳይደረጉ መፅሃፍት
አይታተሙም፡፡ ሌሎች የህትመት ውጤቶችም የሚያስተላልፉት መልዕክት ስርዓቱ የሚደግፈውን ርዕዮተ ዓለም ፅንሰ ሃሳብና አስተሳሰብ ብቻ
ነበር፡፡ በሃገራችን ባይታተምም ውጭ ሃገር የታተሙ ከስርዓቱ ጋር የሚፃረር ወይም የሚተች መልእክት ያለውን መፅሃፍ/የህትመት ውጤት
ለማንበብ እንኳን አይቻልም፤ ወይም እንደ ሰረቀ ሰው ተደብቀው ነበር የሚያነቡት፡፡
ከደርግ ቀጥሎ
የመጣው የኢህአዴግ መንግስት ደግሞ የህትመት ነፃነት ያስፈልጋል በሚል ቅድመ ምርመራም ክልክል እንደሆነ አወጀ፡፡
አንቀፅ
29.3 ሀ/ ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን››
ይህን ህግ
መሰረት በማድረግም በሬድዬና ቴሌቭዥን ደረጃ የታየ ለውጥ ባይኖርም ብዙ የግል ሃሳብ የሚንፀባረቅባቸው ጋዜጦችና መፅሄቶች ተፈለፈሉ፡፡
ለ97 ሃገራዊ ምርጫም እነዚህ የግል የህትመት ውጤቶች ህብረተሰቡን በማንቃት እና የሃራቸው ፖለቲካ ጉዳይ ያገባኛል ብለው እንዲያስቡ
በማድረግ ረገድ አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢህአዴግም በምርጫው ውጤት እና በህዝቡን ስሜት ተደናግጦ ይመስላል ከ97 ምርጫ በኋላ
በሰበብ አስባቡ ጋዜጠኖችንና አዘጋጆችን ማሰር እንዲሁም ለራሱ የሚመች ለትርጉም የማይመች እና ከፕሬስ ጋር የተያያዙ ህጎችን ማውጣት
እና ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው፡፡