Wednesday, April 29, 2015

የ365 ቀናት ፈተና እና ተስፋ - የአንድ ዓመት ማስታወሻ

ከዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች
ጊዜው በጣም ይነጉዳል፡፡ ሀላፊነት የማይሰማው ስርዓት የገዛ ዜጎቹን ዕድሜ በእሳት ይማግዳል፡፡ ሚያዚያ 17/08/2006 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንድንውል የተደረግነው ስድስት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኞች ይሔው ከታሰርን ድፍን አንድ የእስር አመት ቆጠርን፡፡ መለስ ብለን ስናየው አጭር በሚመስለው ዓመት ውስጥ የሆነውንና የታዘብነውን ጠቅለል አድርገን ለማካፈል እንሞክራለን፡፡ይህ የእኛ ገጠመኝ እና ትዝብት፣ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚከብደው መንግስት እስካለን ድረስ የነበረ እና የሚኖር ስለሆነ የሁሉም ‹የኅሊና እስረኛ › ገጠመኝ እና ትዝብት ሊሆን እንደሚችል አስታውሱልን፡፡
‹እንዳይችሉት የለም . . .›
ከያለንበት ቦታ በዘመቻ መልክ ተይዘን የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (በተለምዶ ‹ማዕከላዊ›) በገባንበት ቅፅበት ነበር ሥርዓቱ እንዴት እንደሚሰራ ከውስጡ መመልከት የጀመርነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ስርዓቱ ውጪ ሆነን ከምናውቀው የባሰ እንጂ የተሻለ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ለምርመራው የተያዝነውን ‹‹ተጠርጣሪዎች ›› የሚያቆዩባቸው ክፍሎች መሰረታዊ የሆነውን ሰብዓዊነትን ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገቡ እና ሕግ የማያውቃቸው ይመስላሉ፡፡ ተዘግተው በሚውሉና በሚያድሩ ክፍሎች ውስጥ ተበታትነን ታጉረን በቀን ሁለቴ (ለአስር ደቂቃዎች) መፀዳጃ ቤት እንድንሄድ(ተፈጥሮን በቀጠሮ እንድንቆጣጠር ) እንገደድ ነበር፡፡ ‹የፀሃይ ብርሃንም› በቀን አንዴ ለአስር ደቂቃ እንቃመስ ነበር፡፡ይህምየሚሆነው የእኛን ‹መብት› ለማክበር ታስቦ ሳይሆን በአሳሪዎቻችን ‹በጎ ፈቃድ› ነው፡፡ ክፍሎቻችን ውስጥ ሆነን የሰማናቸውና ያየናቸው በታሳሪዎች (inmates) የሚወሩት እና በገዛ አይናችን የምንታዘባቸው የሰቆቃ ታሪኮች ብቻ ናቸው፤ ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ‹‹እመን››በሚል የማይቀጣ የለም፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ እረፍት ብርቅ ነው፤ የካቴና ድምፅ በተቅጨለጨለ ቁጥር ‹‹ማነው ባለተራ›› የሚል ጭንቀት ሁሉንም ሰው ሰቅዞ ይይዛል፡፡ የትኛው ተረኛ ወደ ‹ምርመራ› ክፍል ተወስዶ ይደበደብ ይሆን? የሁሉም እስረኛ ጥያቄ ነው፡፡
ሁላችንም ለጥያቄ ‹ምርመራ› ክፍሎች ውስጥ በተመላለስንባቸው ጊዜያት ሰብአዊ ክብራችንን እንድንዘነጋ እንገደድ ነበር፡፡ ፀያፍ  ስድቦችን የመርማሪዎቻችን አፍ መፍቻ የሆኑ ይመስል ከንፈራቸው ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡ጥፊ፣ ካልቾና ስፖርታዊ ቅጣቶች የእለት ቀለቦቻችን ነበሩ፡፡ ሴቶች ሊደረግልን የሚገባ ጥበቃ ቀርቶ ሴትነታችንን መቀጣጫ የሚያደርግ አበሻቃጭ (abusive) ‹ምርመራ› ተደርጎብናል፡፡ ‹የምርመራ› ስዓቱ ገደብ የለውም ጠዋት፣ ከሰዓት፣ ማታ እና ሌሊት ሊሆን ይችላል፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ከእንቅልፍ ተቀስቅሶ ወደ ‹ምርመራ› ክፍል መወሰድ እና የደንቡን ተደብድቦ መምጣት የተለመደ ነው፡፡ ለነገሩ ማዕከላዊ የቆየ ሰው የሚታሰርባቸው ክፍሎች የተፈጥሮ ብርሃን የማያስገቡ እና ለ24 ሰዓታት በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ ብርሃን የማያገኙ በመሆናቸው መምሸት እና መንጋቱን እንኳን ለማወቅ በፖሊስ መነገርን ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሶስት የእስር ወራት በዚህ ሁኔታ አሳለፍን፡፡

‹የመርማሪዎችን› አካሄድ በመመልከት በጋራ የተረዳነው አንድ ነገር ቢኖር የተጠረጠርንበት ተጨባጭ ወንጀል ወይም ማስረጃ ያልነበረ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም መጀመሪያ ‹በተጠረጠርንበት› ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአመፅ እና በዛቻ ለማፍረስ እና ማኅበረሰብ ሚዲያን ለአመጽ ለመጠቀም የመሞከር ወንጀል ወይም ኃላ በተከሰስንበት የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም የማሴር፣ የማነሳሳት፣ የማቀድ፣ የመዘጋጀትና የመሞከርን ወንጀል ከእኛው አፍ (በሃሰትም ቢሆን) በጉልበት ለመስማት ‹የመርማሪዎቹ› ቁርጠኝነት ወደር ያልነበረው መሆኑን ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ቤታችን፣ ቢሮአችን፣ ኮምፒውተሮቻችን ፣ስልኮቻችንና ቃላችን ሁሉ ተፈትሾ የተገኘው ማስረጃ እንኳንስ ክስ ሊያቋቁም ቀርቶ የተገላቢጦሽ የእኛን ንፅህና የሚመሰክሩ ሆኑ፡፡ ይሁን እንጂ ሕግ የማይገዛው አሳሪያችን ከ15 ዓመት እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል ክስ አቀረበልን፡፡ጉዳዬን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደሞ በምርመራው ወቅት አንድም ቀን የሽብር ተግባር እና አላማቸውን በማስፈጸም የተከሰስንባቸው ድርጅቶች አንዳቸውም አለመጠቀሳቸው ነው ፡፡
ክሱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት (ወንዶች ወደ ቂሊንጦ ሴቶች ወደ ቃሊቲ) ተላክን፡፡ ማረፊያ ቤቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሚንስትሮች ምክር ቤት ያወጡላቸው መተዳደሪያ አዋጅና ደንብ ያላቸው ሲሆን፤ ነግር ግን የሚገዛቸው ያልተፃፈ ሌላ ደንብ ነው፡፡ በተለይ ሴቶችን የሚያሳድረው የቃሊቲው የአዲስ አበባ የሴቶች የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ገና ለገና ‹በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠርን› በመሆናችን ብቻ አግላይ አያያዝ በማድረግ የቀደመ ልምዱን ተግብሮብናል፡፡ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች / ታራሚዎች በተለየ ሁኔታ የጠያቂዎቻችንን ስም ዝርዝር እንድንፅፍ በማስገደድ መብታችንን ሲገድብብን፣ የምንጠየቅበትን ሰዓትም በአዘቦት ቀን ከአስር ደቂቃ እና ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ከ30 ደቂቃ እንዳይበልጥ አድርጓል፡፡ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ብናቀርብም የማረፊያ ቤቱ አስተዳደር ‹ችግር የለም› በማለት እውነታውን በግልጽ ሲክድ ፍርድ ቤቱም ተባብሮት አጽንቶታል ፡፡ ፍትህን የሕግ የበላይነት ከፖሊስ እጅ እንዳጣነው ሁሉ በአያያዝ ረገድ ከማረፊያ ቤቱም ደጃፍ ልናገኘው አልቻልንም፡፡
ፍ/ቤቱ ‹እንደተጠርጣሪ› ለማረፊያ ቤቶቹ ያስረከበን በአደራ አቆዩልኝ ብሎ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱና የመብት ረገጣው ዋነኛ ተዋናዮች የሚመለከቱንግን ግን በጦር ሜዳ እንደማረኩት ግዳያቸው ነው ፡፡ እኛም በዚህና መሰል ለደህንነታችን ምንም አይነት ዋስትና በማይሰጥ አያያዝይህንን የመአት ዓመት ችለን አንድ ዓመት አስቆጥረናል፡፡
ምን ያሟግተናል?
በግልፅ የአሳሪያችንን መልካም ፈቃድ በወገንተኝነትና በታማኝነት በሚያገለግሉ ግለሰቦች የሚመሩትን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ‹የወንጀል ምርመራ ቡድን› እና በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ‹ገለልተኝነት› ተሸማቀን ስናበቃ የተጋፈጥነው አንበሳውን  የፍትህ ስርዓታችንን ነው፡፡
ወንጀልን ሊያቋቁም የሚችል ምንም አይነት ማስረጃ በሌለበት በወንጀል መጠርጠራችንና መከሰሳችን ከሁሉም ቀዳሚው በደል እንደሆነ ይሰማናል፡፡ ነገር ግን ስለፍትህ አውርተናል ጠይቀናል ተከራክረናልና የኖርንበትን ታላቅ አላማ እኛው ፈልገን የፍትህ በርን እያንኳኳን እንገኛለን፡፡ ‹‹ለምን ተጠረጠርን?›› ‹‹ለምንስ ተከሰስን?›› ብለን ፍትህን ከመሻት ራሳችንን ሳናቅብ የቀረበብን ክስ እንደ ክስ ሊቆም የማይችል እንደሆነ ሕጋዊና ሙያዊ መቃወሚያ አቅርበን ፍርድ ቤቱም ‹ተቀብዬዋለሁ ግን አልተቀበልኩትም› በማለት ልንረዳው ያልቻልነውን ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ከእስራችንም በፊት የምንታወቅበትን የአገሪትዋን ህግ በመጠቀም መብቶቻችንን የመጠየቅን ሂደት አጠናክረን የምንገፋበት ተቋማቱ ገለልተኛ ናቸው ብለን ስለምናምን ሳይሆን ከተቋማቱ ጀርባ ላለው ፍትሕ እና ህግ የበላይነት ያለንን ቁርጠኛነት ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡

ከሳሻችን አለኝ የሚለውን ‹ማስረጃ› በከፊል ከእኛ ከተከሳሾች ደብቆ እንኳን የተባለውን ‹ማስረጃ› ለማድመጥ የአንድ አመት ጊዜ መጠበቅ ነበረብን፡፡ የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል መባሉን ከሳሻችን እንደሚያውቅ ብናውቅም እኛ ግን የዘገየውን ‹ፍትሕ› እንኳን ለመጠየቅ የሚያስችልትዕግስት አላጣንም፡፡
አሁንም ፍትሕ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዓይነተኛ መለያ ቀለም ነው ብለን እናምናለን፡፡ ፍትሕ ይኖር ዘንድ ገለልተኛ ተቋማት መኖራቸው ደግሞ የግድ ነው፡፡ ተቋማት ለተቋቋሙበት ዓላማ ከመኖር ይልቅ ታማኝነታቸውን ለስርዓቱ ሹማምንት ማድረግ ሲጀምሩ ፍትሕ አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ይገባል፡፡ ፍትሕ እኛ በታሰርንባት ኢትዮጵያ ይሕ ፈተና እንደገጠማት ይሰማናል፡፡ እንግዲህ የኛ ተስፋና ጥበቃም ከዚህ እውነት የሚመነጭ ነው፡፡
ወንጀላችንን ፈልገን ማግኘት አልቻልንም በህግ ፊት ንጹህ ነን ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ይሕ ንፅሕናችን መቼና እንዴት እንደምንፈታ አይነግረንም፡፡ አንድ ነገር ግን እርግጠኞች ነን፡- እውነት ከኛ ጋር መሆኗን፡፡

በተስፋ የሚያቆመን . . .
እኛን ከአገራችን ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም የዴሞክራሲ ቤተሰብ ጋር ያስተሳስረናል ብለን የምናምነው ዕሴት ሐሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነት ላይ ያለን ፅኑ እምነት ነው፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን ያለምንም ጣልቃ ገብነትና ፍርሃት መግለፅና መደማመጥ ሲችሉ አገራችንን ጨምሮ በዓለማችን ያሉ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መቅረፍ የሚችሉ ሀሳቦችና መነሳሳቶች መፍጠር ይችላሉ የሚል እምነት ከመታሰራችንበፊትም ይሁን በኋላ በውስጣችን አለ፡፡ የታሰርነውም ይህንን ተፈጥሮአዊ ነፃነታችንን ለመጠቀም ሙከራ ማድረግ ስንጀምር ነው፡፡ በየትኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ እውነትን ለጉልበተኞች መናገር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እኛም ሐሳባችንን በነፃነት ስለመግለፅ እየከፈልን ያለነው ዋጋ የማይከብደን የነገይቱ ኢትዮጵያ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ የተሻለች ትሆናለች የሚል ተስፋ በማድረጋችን ነው፡፡

የሚያበረታን . . .
የመታሰራችንዜና ከተሰማ ጀምሮ ብቻችንን አልታሰርንም፡፡ ብዙዎች አኛን ከከለለን አጥር ውጪ አብራችሁን ታስራችኋል፡፡ ስለዚህ የእስርቤት ጌጥ የሆኑት የመረሳትና ተስፋ የማጣት ስጋቶች እንዳይጎበኙን ያደረገንና በብርታት ያቆመን የእናንተው በእሳት የተፈተነ አብሮነት ነውና ሁላችሁም ምስጋና ይገባችኋል፡፡
እምነታችን እዳ ሆኖባችሁ ከታሰርንበት ደቂቃ አንስቶ የመንፈስም፣ የአካልም ዕረፍት ሳያሻችሁ እየደከማችሁ ላላችሁ ቤተሰቦቻችን፣ በፈተናችን ሰዓት ሕመማችንን አብራችሁ ለታመማችሁ ወዳጆቻችን (friends indeed)፣ ከታሰርንበት ጊዜ ጀምሮ ንፅህናቸንን ተረድታችሁ ጉዳያችንንእንደ ጉዳያችሁ እየተከታተላችሁ ላላችሁ እና የመንፈስ ድጋፋችሁ ላልተለየን አገር በቀል እና አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን፣ ሰብአዊነትናየዴሞክራሲ ተቆርቋሪዎች ስለድካማችሁ ምስጋናችን የበዛ ነው፡፡ የማረፊያ ቤት ቆይታችን አዲስ አይነት የህይወት ልምድ የምናገኝበትናየምንማርበት ይሆን ዘንድ አብራችሁን በማረፊያ ቤት የነበራችሁ/ያላችሁ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እናንተም ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡ እንዲሁም ይህን በሕግ አግባብ ያልተመሰረተ ክስ በሕግ አግባብ እንዲቋጭ ያላሰለሰ ጥረት እያረጋችሁ ያላችሁት ጠበቆቻችንና ሌሎቻችሁም. . . ምስጋናችን ከልባችን የፈለቀ ነው፡፡ ሁላችሁም የምንበረታው በእናንተ ነውና እጅግ በጣም እናመሰግናለን፡፡

#Ethiopia  #FreeZone9Bloggers  #FreeEdom  #FreeTesfalem  #FreeAsemamaw 

Tuesday, April 28, 2015

ስቃይና መብት ጥሰት -አጥናፍ ብርሃኔ

አጥናፍ ብርሃኔ 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ
- ሳጅን ምንላድርግልህ
-ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( የሽፋን ስም )
- ኢንስፔክተር አሰፋ
- ም/ሳጅን መኮንን
- ኢንስፔክተር ገብሩ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 17 እስከ ሃምሌ 11 /2006 አም

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ በተለይ ቢሮ ቁጥር 5.፣ 32

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- ታደሰ የተባለው መርማሪ ፓሊስ ያለምንም ምክንያት ምርመራ ክፍል ውስጥ እያነቀኝ በተደጋጋሚ “እውነቱን የማትናገር ከሆነ ሽባ ነው የምናደርግህ ፣ እኛ ለግለሰብ መብት አንጨነቅም” በማለት በጥፊ ሲደበድበኝ ነበር

- ሳጅን ምን ላድርግልህ የተባለ መርማሪ “ጦማር ምን ማለት አንደሆነ ተናገር” ሲለኝ ጦማር ማለት መጻፍ ነው ብለውም ፡።፡።”ምህጻረ ቃል ነው እያንዳንዷ ምጻረ ቃል ምን ማለት አንደሆነች ካልተናገርክ አንላቀቅም” በማለት ከግርግዳ ጋር እያጋጨ ደብድቦኛል፣ ከግርግዳ ማጋጨት ብቻም ሳይሆን ረጅም ሰአት ከአቅሜ በላይ የሆነ የአካል አንቅስቃሴ እየሰራሁ የተመረመርኩ ሲሆን ምራቁን እየተፋብኝ አጸያፊ ስድብ ሲሰድበኝ ነበር፡፡

- ግንቦት ወር ላይ ሳጅን ምን ላድርግልህ የተባለው መርማሪ “ ኢህአዴግን ለምንድነው ተችታችሁ የምትጽፉት ?” “ከአገር ውጪ የምትሄዱት የመንግሰትን ስም ለማጥፋት ነው አንጂ የአባይ ግድብ ቦንድ ለመግዛት አይደለም” በማለት እጄን ወደላይ አድርጌ አንድመረመር አንዲሁም ጆሮዬን እየጎተተ በጥፌ ሲደበድበኝ ውሏል፡፡ ከዚህ ቤት ደንቁረህ ነው የምትወጣው በማለትም ያስፈራራኝ ነበር፡፡ እየተፋብኝ አጸያፊ ስድብ እየተሰደብኩ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ተፈጽሞብኛል፡፡

- በሰኔ ወር ኢንስፔክተር አሰፋ የሚባለው መርማሪ ሌሊት 6 ሰአት አካባቢ ጠርቶኝ አላማችሁን ካልተናገርክ ጭለማ ቤት ነው የምትገባው በማለት ከማስፈራራቱም በላይ ሌሎች እስረኞች ሲደበደቡ እና ሲጮሁ ሲያለቅሱ በማሰማት እነደነሱ አንዳትሆን በማለት ዛቻ ተፈጽሞብኛል።

- ሰኔ ወር ላይ ኢንስፔክተር ገብሩ የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ በመግባት ወረቀት ጽፈሃል የሚል በውል በማላውቀው ምክንያት ከሌሎች እስረኞች ለይቶ በተኛሁበት በተደጋጋሚ ከባድ የእርግጫ ደብደባ ፈጽሞብኛል። ሲደበድበኝም ህዝብ ልታጫርስ ነው እያለ ነበር፣ አስካሁንም የዛን ቀኑን ድብደባ ምክንያት ነው ያሉትን ነገር አላውቀውም፡፡

- በማእከላዊ ቆይታዬ 4በ4 በሆነች ክፍል ውስጥ በቀን ሁለቴ ብቻ ለ15 ደቂቃ ወደውጪ በመውጣት ከአስር ሰው ጋር ተቆልፎብኝ ታሬያለሁ ፡፡ የመጸዳዳት እድልም ቀኑን ሙሉ አልነበረኝም ፡፡ በየቀኑ ከባድ የአካል አንቅስቃሴ መስራት የምርመራው አካል ነበር፡፡

- በሃምሌ ወር ከምሽቱ 2.30 አካባቢ ሳጅን ምንላድርግልህ ፣ ም/ሳጅን መኮንን እና ሌላ የማላውቀው መርማሪ በመሆን ጭንቅላቴን በሃይል ከግንብ ጋር በማጋጨት እና የኮምፒውተር ኬብል በማሳየት አንደምገረፍ በመንገር ሳጅን ምንላድርግልህ የተባለው መርማሪ ፓሊስ የጻፈው የእምነት ቃል ላይ በግዳጅ አንድፈርም ተገድጃለሁ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው 

ስቃይና መብት ጥሰት - አስማማው ሐይለጊዬርጊስ

አስማማው ሐይለጊዬርጊስ 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ ስማቸው የማላውቃቸው ማንነታቸውን ለመናገር ፍቃደኛ ያልሆኑ አራት መርማሪዎች እና መርማሪ ጽጌ መርማሪ መኮንን አብተው

ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 17 እስከ ሃምሌ 11 /2006 አም 

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ላይ

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- ከአንድ ወር ከአስራም አምስት ቀን በላይ የተፈጥሮ ብርሃን የሌለው በጨለማ ክፍል ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ታስሬያለሁ

- የቀለም አብዮት ልታመጣ ነው የወጠንከው በሚል ስለቀለም አብዬት እቅድ ተደጋጋሚ ተጠይቄያለሁ፡፡

- ስታሰር ከመንገድ ላይ የታፈንኩ ሲሆን ምንም አይነት ጥያቄ አንድጠይቅ አልተፈቀደልኝም፡፡ የእስር ትእዛዝ አላሳዬኝም ፣ የእስር ትእዛዝ አሳዬኝ ብዬ ብጠይቅም መልስ አልተሰጠኝም፡፡

- ባለብኝ የወገብ ህመም የተነሳ ወንበር አንዲገባልኝ ብጠይቅም ለ65 ቀናት ከፍተኛ ህመም ስር ሆኜ ቆይቻለሁ ፡፡ አካላዊ ጤንነት የመጠበቅ መብቴ ተነፍጓል፡፡

- “የአንተ ነገር አልቆለታል ፡፡ነጻ ሰው ነኝ ማለት አትችልም ወንጀልህን ተናዘዝ” የሚል ረጅም ሰአት ማስፈራሪያ ደርሶብኛል

- የሙያ ባልደረቦቼን ውብሸትን ታዬን እና ሌሎች ታራሚዎችን መጠየቄን አንደወንወጀል ተቆጥሮ ለምን ጥሩ ታራሚዎችን አትጠይቀም በሚል ከፍተኛ ተሳልቆ ደርሶብኛል፡፡

- በር በሌለው መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም የተገደድን ሲሆን በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ጸሃይ ብርሃን አገኝ ነበር ፡፡

- ስድብ መሳለቅ ያንተ ነገር ያለቀለት ጉዳይ ነው በማለት ከፍተኛ ስፓርት አንድሰራ እና የዞን9 አባል ነኝ ብዬ አንዳምን ከፍተኛ ማሰቃየት ደርሶብኛል ፡፡

- በካቴና ታስሬ እየተመረመርኩ ቢሆንም አንተ ጭራሽ ተመርማሪ አትመልስልም በሚል ተራ ምክንያት ማሰቃየት እና ጥፊ የተለመደ ነበር ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው  

ስቃይና መብት ጥሰት - ማህሌት ፋንታሁን

ማህሌት ፋንታሁን 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት አባላት መርማሪ ደስታ በዋናነት
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - በተያዝኩባቸው ቀናት በሙሉ (በተለይ ሚያዝያ 18 በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በሰፊው) 

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ቢሮ ላይ
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት

- በጠበቃ እና በቤተሰብ የመጎብኘት መብቴ ተጥሷል፡፡ ከተጎበኘሁም 10ደቂቃ ለማይሞላ ጊዜ በፓሊስ ተከብቤ ነበር፡፡

- በተደጋጋሚ በምርመራ ወቅት አመጽ ለማነሳሳት እነደጸፍሽ እመኚ እየተባልኩ በጥፊ እና በካልቶ ተደብድቤያለሁ፡፡

- በምርመራ ወቅት ልብሴን አስወልቀው አንድቀመጥ በማድረግ አይኔ ተሸፍኖ በምሽት ምርመራ ተደርጎብኛል፡፡

- ሙሉ ልብሴን እንዳወልቅ ተገድጄ ራቄቴን በወንድ መርማሪዎች ፊት ስፓርት አንድሰራ እገደድ ነበር ፡፡ “ሴትነትሽ አንዲህ ከሚዋረድ አመጽ እንዳነሳሳሽ እመኚ ተብያሁ”

- በሌሊት ግርፋት የሚፈጸምበት ክፍል ውስጥ ገብቼ ጫማሽን አውልቂ ተብዬ ጫማዬን አውልቄ ከቆምኩ በኋላ ውስጥ እግርሽን ከምትገረፊ አመጽ ማነሳሳትሽን አምነሽ ፈርሚ ተብያለሁ፡፡

- ሰጠሁት የተባለው ቃል ሰዎች በሚቀጥለው ክፍል እየተደበደቡ የጩኀት ድምጻቸው እየተሰማ ፈርሚ ተብዬ የተባልኩት ቦታ ላይ ሳላነብ በፍርሃት ፈርሜያለሁ።

- በተለያዬ ምርመራ ወቅቶች "ለነጭ አገሪትዋን የሸጥሽ ሸርሙጣ ውሻ ባንዳ..." አንዲሁም ለመጸፍ የሚከብዱ አፀያፈ ስድቦች በየቀኑ እሰደብ ነበር ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

ስቃይና መብት ጥሰት - ኤዶም ካሳዬ

ኤዶም ካሳዬ
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት አባላት መርማሪ ደስታ በዋናነት

ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - በተያዝኩባቸው ቀናት በሙሉ በተለይ ሚያዝያ 18 ,20, 21, 22, 23
የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ቢሮ ላይ
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት

-መርማሪዬ ደስታ በተደጋጋሚ በጥፊ ይመታኝ ነበረ ሲሆነ ከዚህ ቤት የፈለግነውን ልናደርግሽ እንችላለን በአካል አትወጪም እያለ አስፈራርቶኛል

-የዞን 9 አባል አይደለሁም በማለቴ ፌቴን አዙሬ ከባድ የአካል አንቅስቃሴ የሰራሁ ሲሆን በተጨማሪም አላማቸውን ተናገሪ ሲለኝ የተለየ አላማ እንዳላቸው አላውቅም በማለቴ ሳታውቂ አንዴት አብረሻቸው ትውያለሽ ሸርሙጣ ብሎ በተደጋጋሚ ሰድቦኛል፡። ሌሎቹ መርማሪዎች አብረው ተቀምጠው በስድቦቹ ይስቁ ነበር

-ሌላኛው ተከሳሽ አጥናፍ መደብደቡን ፍርድ ቤት በመናገሩ አንቺ ትሞክሪውና ዋጋሽን ታገኛለሽ እኛ ፍርድ ቤት አያዘንም የግለሰብ መብትም አያሳስበንም ብሎኛል

-ጥጋቡ የሚባለው መርማሪ ምርመራ መሃል ደንገት በሩን ከፍቶ ገብቶ በጥፊ መቶኝ ይወጣ ነበር ( ስለምናወራው ጉዳይም ሆነ ስለምርመራው ሳይሰማ) እምቢ ካለችህ ልብሷን አስወለወቀህ ግረፋት ብሎ እኔን የተለመደውን ስድብ ሰድቦኝ ሄዷል

-በምርመራ ወቅት የዞን አባል ነኝ ብለሽ እመኚ ተብዬ ልብሴን አውልቄ ሙሉ እርቃኔን አንድመረመር ተገድጃለሁ ፡። በጥፊ እመታ የነበረ ሲሆን በዚህ ቀን ምርመራው ምሽት ላይ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰአት ቆይቷል

-በተለምዶው ከምመረመርበት ቢሮ ውጩ አንደኛ ፎቅ አዳራሽ ውስጥ ለምርመራ ተወስጄ ልብሴን እንዳወልቅ እና የተለያዬ ለመናገር የሚከብዱ ስፓርታዊ አንቅስቃሴዎችን እንድሰራ ተገድጃለሁ፡፡ እንዲህ ከምትዋረጂ አመጽ ልናስነሳ ነበር ብለሽ ለምን አታምኚም እያለ ይመታኝ ነበር ፡፡ በጥፊው ተደጋጋሚነት የተነሳ ታምሜ ክሊኒክ ተመላልሻለሁ::

-በጋዜጠኝነት ሞያየ የተሳተፍኩበትን ስልጠናዎች ስናገር አንቺ ለምን ተመረጥሽ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ለምን አይሄዱም አንቺ ለፈረንጅ ስለምትሰልዬ ነው ብሎኛል፡፡ በተጨማሪም ዞን9 ላይ የሚወጡት ጽሁፎች አንድ ገጠር ያለ ሰው ቢያነበው ለአመጽ የሚያነሳሳው ልማቱን የሚያጣጥል ነው ብሎ በተደጋጋሚ በጥፊና በካልቾ ተመትቻለሁ፡፡

-በተጨማሪም በተፈቺ እስረኛ ወደውጪ መልእክት ልከሻል በሚል ሰበብ ሌሊት ተጠርጬ በዱላ ሲዛትብኝ አርፍዷል

-በእስሩ ወቅት ከማህሌት ፋንታሁን ጋር ለብቻችን ከሰው አንዳንገናኝ ተደርገን ቆይተናል፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

ስቃይና መብት ጥሰት - ዘላለም ክብረት

ዘላለም ክብረት
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት አባላት መርማሪ ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( ስሙ በትክክል የማላውቀው) በተለይ መርማሪ ምን ላድርግልህ መርማሪ ጽጌ መርማሪ አብዱልመጂድ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - በተያዝኩባቸው ቀናት በሙሉ በተለይ ሚያዝያ 17፣ ሚያዝያ 22 ሚያዝያ 25 እና ግንቦት 9
የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ቢሮ ላይ
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- በታሰርኩነት ወቅት ህጋዊ የእስር እና የብርበራ ትእዛዝ አልነበረም፡፡ ህጋዊ ያልሆነ ፍተሻ ከ12 ሰአት በኋላ አታድርጉ ብልም የሚሰማኝ አላገኘሁም ፡። ፍተሻው በከፍተኛ ማስፈራሪያ የታጀበ ነበር፡፡ ፓሊስ ጣብያ እሄዳለሁ ብለህ እንዳታስብ ራስህን ለምትሄድበት ቦታ አዘጋጅ እያሉ ከፍተኛ ስነልቦና ጫና አድርሰውብኛል
- በመጀመሪያው ቀን ፍርድ ቤት ስንቀርብ ትምህርቴን አጠናቅቄ ላስረክበው ያዘጋጀሁትን የመመረቂያ ጽሁፍ ፓሊስ መያዙን እና ኮፒ አድርጌ እንዳስረክብ ይፈቀድልኝ ብዬ ስጠይቅ ፍርድ ቤቱም መብቱ ነው ብሎ ትእዛዝ ቢሰጥም ፓሊስ ትእዛዙን ተግባራዊ አንዲያደርግ ብጠይቅ የማዕላዊ ወንጀል ምርመራ ሃላፊ ኢንስፔክተር “ፍርድ ቤት እኛን አያዘንም“ ” የት ያለህ መሰለህ” ዳኛዋ ታስረክብልህ” አንዲሁም “አንዲህ አይነት ጥያቄ ካነሳህ እርምጃ ይወሰድብሃል” የሚሉ ንግግሮችን ተናገረውኝ አንጓጠውኛል በዚህም ምክንያት መመረቂያ ጽሁፌን ማስረከቤ ተሰናክሏል፡፡
- በምርመራ ወቅት በዙ አጻያፌ ስድቦችን እየተሰደብኩ የምመረመር ሲሆን ከነሱም መካከል “የነጭ ተላላኪ የነጭ አምላኪ አገር ሻጭ ከሃዲ “ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
- የዞን 9 አላማ ተናገር ካልሆነ ያሉንን የምርመራ መንገዶች ተጠቅመን እንድታወጣ እናደርጋለን የሚለው ማስፈራሪያ በተደጋጋሚ በምርመራ ወቅት የደረሰብኝ ነው
- የሰጠሁት ቃል ላይ እኔ ያላልኩትን ጨምረው በፍርሃት ጥፋተኛ ነኝ ብዬ አንድፈርም ከመገደዴም በላይ የበላይ አካል ተቀባይ አንዲሆን በሚል እየቀያየሩ በተደጋጋሚ አስፈርመውኛል፡፡
*ይህ ጽሁፍ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

መብት ጥሰትና ስቃይ - ተስፋለም ወልደየስ

ተስፋለም ወልደየስ

ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) መርማሪ የህይስ መርማሪ ጽጌ መርማሪ ታደሰ ( ስሙን እርግጠኛ ያልሆንኩት) 

ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት ማእከላዊ ምርመራ በቆየሁበት ጊዜ ሁሉ 
የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
-በውል በማላስታውሳቸው ቀናት እስከእኩለ ሌሊት ድረስ የቆየ ምርመራ ተደርጎብኛል
-ለ75 ቀናት በተለምዶው ሳይቤሪያ የሚባለው ቦታ በቀን 15 ደቂቃ ብቻ የጸሃይ ብርሃን ለማየት ተፈቅዶልኝ ከዚያ ውጪ ያለውን ጊዜ 24 ሰአት አንድ በር ተዘግቶብኝ ቆይቻለሁ፡፡
-አራት በአራት በሆነ በዚህ ክፍል ውስጥ ቁጥራቸው አስር ከሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ጋር ጤናዬን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ
-በእስር በቆየሁባቸው ቀናት በቀዝቃዛው ሳይቤርያ ውስጥ በማሳለፌ በከፍተኛ ቅዝቃዜው የተነሳ ለጤና ጉዳት እና ለበሽታ ተዳርጌያለሁ
-ከፍተኛ እና ከአቅሜ በላይ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ ያደረኩ ሲሆን በምርመራ ወቅት በተደጋጋሚ እመታ ነበር
-በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የስነልቦና ጉዳት ደረሰብኝ ሲሆን በስተመጨረሻም ያላልኩትን አለ ተብዬ ፣ የማላምንበት እና ያልፈጸምኩትን ጥፋተኛ ነኝ ብለህ ፈርም በመባሌ ለመፈረም ተገድጃለሁ

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው 

ስቃይና መብት ጥሰት - ናትናኤል ፈለቀ

ናትናኤል ፈለቀ 

ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ ሳጅን ምን ላድርግልህ ፣ ም/ሳጅን አብተው 

ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 22 ( ከምሽቱ 2 ሰአት ገደማ)፣ ሚያዝያ 23 ከጠዋቱ 4 ሰአት፣ ግንቦት 6( ከምሽቱ 3 ሰአት ገደማ)፣ ሚያዝያ 24 ከጠዋቱ 4 ሰአት እና ከሚያዝያ 22 እስከ ግንቦት 6/2006 ድረስ ባሉት ቀናት ከእሁድ በስተቀር 

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ላይ ቢሮ ቁጥር 30፣ 32 በ1981 አም በተሰራው ህንጻ ላይ 2ተኛ ፎቅ በስተግራ ጥግ በኩል ያለ ቢሮ

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- በምርመራ ወቅት ዛቻ እና ማስፈራሪያ የደረሰብኝ ሲሆን በተጠራሁባቸው ቢሮ ውስጥ ሁሉ በጥፌ ተደብድቤያለሁ ፡፡ በጥፌ መመታት የተለመደ ነበር ፡። በተደጋጋሚ ክፍተኛ ስፓርት የሰራሁ ሲሆን በቀን 10 ደቂቃ ብቻ የፀሃይ ብርሃን እያየሁ በጠባብ ክፍል ውስጥ ያለምንም ተፈጥሮ ብርሃንና መጸዳጃ ለ 76 ቀናት ቆይቻለሁ፡፡

- ጫማዬን አውልቄ በባዶ እግሬ አንድቆም ከተደረኩ በኋላ እግሮቼ ጣቶች ላይ መርማሪዎቹ በጫማቸው በሃይል በመርገጥ እግሬ ላይ ከባድ ድብደባ አድርሰውብኛል፡፡ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስም እጄ እንደታሰረ አናቴ ላይ አድርጌ እንድመረመር ተገድጄ ነበር፡፡

- የምሽት ምርመራዎች ወቅት በአብዛኛው ጊዜ እጄን ወደላይ አድርጌ እንድመረመር እገደድ ነበር ፡። ምርመራው ቀኑን ሙሉ የሚቆይ ሲሆን ምሽት እስከ ሌሊቱ ስድስተ ሰአት ድረስ ስፓርት በመስራት እና ፌቴን በማዞር እንድመረመር እገደድ ነበር፡፡

- ሰብአዊነቴን የሚነኩ ስድቦች ልክስክስ ፣ ውሻ መሳሰሉትን ስድብ በምርመራ ወቅት እሰደብ የነበረ ሲሆን አካለ ጎዶሎ ሆነህ ነው ከዚህ ቤት የምትወጣው ፣ ለግለሰብ መብት አንጨነቅም አንተን አንደፈለግን እነድናደርግ አሰራራችን ይፈቅድልናል የሚሉ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎች ነበሩብኝ ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነውስቃይና መብት ጥሰት - በፍቃዱ ሃይሉ

በፍቃዱ ሃይሉ

ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎች ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ 
-መርማሪ ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( የሽፋን ስም ) 
- መርማሪ ጽጌ 
-መርማሪ ብቂላ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 22 ( ከምሽቱ 2 ሰአት ገደማ)፣ ሚያዝያ 23 ከጠዋቱ 4 ሰአት፣ ግንቦት 6( ከምሽቱ 3 ሰአት ገደማ)፣ ሚያዝያ 24 ከጠዋቱ 4 ሰአት እና ከሚያዝያ 22 እስከ ግንቦት 6/2006 ድረስ ባሉት ቀናት ከእሁድ በስተቀር

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ላይ ቢሮ ቁጥር 35 ፣ 27 እና ቁጥሩን በማላስታውሰው የቃለ መጠይቅ ቦታ

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- ማአከላዊ ምርመራ በቆየሁባቸው ቀናት ከእሁድ በስተቀር ጠዋት ከሰአት ማታ እየተጠራሁ በዛቻ በአጸያፌ ስድብ ጭካኔ የተሞላበት ግርፌያ ጥፌና እርግጫ አንዲሁም ከአቅሜ በላይ የሆነ ስፓርት እየሰራሁ ቃሌን እንድሰጥ ተገድጃለሁ፡፡የተያዝክበትን ድብቅ አጀንዳ ንገረን በማለት ራሴን እንድወነጅል ተገድጃለሁ፡፡

- መርማሪው በመጀመሪያ ቀን ምርመራ በጥፌ መምታት የጀመረ ሲሆን እያንዳንዱን ጥያቄ ከጠየቀኝ በኋላ በጥፌ ይመታኝ ነበር፡፡ የዞን9 አላማ ጠይቆኝ ስነግረው ድብቁን አውጣ በማለት መሬት ላይ አንድቀመጥ እና ያደረኩትን ነጠላ ጫማ እነዳወልቅ አዞኝ በኮምፒውተር ገመድ እግሬን መግረፍ ጀመረ፡፡ በተጨማሪም በሆዴ አንድተኛ በማዘዝ እና እግሬን አጥፌ ከፍ አንዳደርገው በማድረግ ውስጥ እግሬን ገርፎኛል፡፡ ድብቄ አጀንዳህን ካልተናገርክ ነገ እዘለዝልሃለሁ በሚል አስፈራርቶኛል፡፡ ግርፌያው ውስጥ እግሬን ሲለበልበኝ ነበር ፡፡

- ድምጽ እንዲያፍን ሆኖ ወደተሰራው የስብሰባ አዳራሽ ተወስጄ በጥፌ እየደበደቡኝ የዞን አላማ ተናገር ተብዬ ተደብድቤያለሁ፡፡ ስቃዬ ሲበዛብኝም የፈጠራ ታሪክ አንዳወራ ተገድጃለሁ፡፡ እኔ የምጽፈው ኢትዬጲያ ውስጥ አብዬት ለማስነሳት ነው ብዬ እንድፈርምም አስገድደውኛል

- በምርመራ ወቅት እጄ በካቴና እነደታሰረ ለሰአታት ቁጭ ብድግ አንድል ተገድጃለሁ፡፡

- መርማሪው በአንድ ወቅት አራት የዞን9 አባላት ሆናችሁ ስለአላማው የተወያያችሁትን በቃል መስጫው ክስ ላይ ልጽፍ ነው ሲለኝ አንደዛ አይነት ውይይት ማድረጋችንን አላስታውስም ስለው እንዴት አታስታውስም ብሎ በጥፌ መማታት ጀመረ፡። በተደጋጋሚ ከመደብደብም በላይ እስክስታስታውስ እዚሁ ታድራታለህ በማለት ድብደባው በመቀጠሉ አስታውሳለሁ ብዬ ተገላገልኩ ፡፡ የሰጠሁት ቃል ላይም እንደፈለገው አድርጎ ጻፈው፡፡ እኔም በድብደባ ብዛት ፈርሜያለሁ፡፡

- ዞን9 ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሌለው ከሆነ ይህንን ህዝብ አንዴት ነው ነጻ የምታወጡት በሚል ሲጠይቁኝ የነጻ አውጪነት ሚና የለንም ስላቸው ከወንበሬ አንድነሳ አዘዙኝ፡። ከዚያም በቆምኩበት ግራ ብብቴን እና እጄን በአንድ እጁ አንዳልወድቅ ወጥሮ ይዞ በእግሩ ጭኔን በሃይል ደበደበኝ ፡፡ ከድብደባው በማስከተል ደግሞ እግሬ መሃል እግሩን በማስገባት ወደግራ እና ወደቀኝ በመምታት ተዘርጥጬ እንድቆይ በማድረግ እጄን ወደላይ አድርጌ እግሬ ግራና ቀኝ ተዘርጥጦ ( በተለምዶ ስፕሊት በሚባለው) በግራ እና ከቀኝ በመደብደብ እጄን ወደላይ አድርጌ እነድመረመር ተደርጌያለሁ፡፡ከዚህ ምርመራ በኋላ ለሁለት ቀን እያነከሰኩ ነበር፡፡

- በጥቅሉ ምርመራው በተከናወነባቸው ቀናት ከእሁድ በስተቀር ሳልደበደብ ቢያንስ በጥፌ ሳልመታ የቀረሁበት ቀን የለም፡፡ ድበደባዎቹ አብዛኛው ድብቅ አጀንዳችሁን ተናገር የሚሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በጣም ጥቃቅን በመሆኑ ምክንያቶች ነው ፡፡ መልስህ ንቀት አለበት ለምን አላስታወስክም በሚሉ ምክንያቶች ስደበደብ ነበር ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

ስቃይና መብት ጥሰት - አቤል ዋበላ

አቤል ዋበላ 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ
- ምን ላድረግልህ 
- ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( የሽፋን ስም )
- ደስታ ወይም ሃሰን ( የሽፋን ስም)
- ዬሃንስ
- ፈይሳ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 18(ከሰአት ከ8-10) ፣ ግንቦት 11 ( ከምሽቱ 2 ሰአት- ሌሊቱ 6 ሰአት) እና ሰኔ 26 ( ከምሽቱ 4 ሰአት -ሌሊቱ 7 ሰአት) እና በማእከላዊ ምርመራ በልዬ ሁኔታ በቆየሁባቸው 76 ቀናት
የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ላይ ቢሮ ቁጥር 5.፣ 32፣30 ፣ የስብሰባው አዳራሽ እና ከዋናው ህንጻ ተነቅሎ በሚገኝ ህንጻ ውስጥ በሚገኝ ጨለማ ክፍል
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- የተያዝኩበት ማግስት አቶ ምን ላድርግልህ የተባለ የምርመራ ክፍሉ አባል ብሄሬን ጠይቆኝ ኢትዬጲያዊ መሆኔን እና በተለያዬ ብሄሮች ስር ራሴን አንደማልገልጽ እና በጥቅል ኢትዬጲያዊ መባል አንደምመርጥ ነገርኩት ተነስቶ ድብደባ ጀመረ ፡፡ በጥፌና በእርግጫ በተደጋጋሚ መታኝ፡፡ ሌላው መርማሪ ንግግራችንን ያልሰማ ከውጪ መጥቶ ያለምንም ጥያቄ ድብዳባውን ተቀላቀለ ፡፡ ከዱላው በተጨማሪ በጣም አጸያፌ ስድቦችን ሰደቡኝ፡፡ ብሄርህን የካድክ በብሄርህ የምታፍር ይሉኝም ነበር፡፡
- ከሚያዝያ 19-ሰኔ 26 2006 ባሉት ቀናት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ አያድንህም በማለት አጸያፌ ቃላት በመሰንዘር ሰውነቴ ሊቋቋመው የማይችለው የአካል እንቅስቃሴ እንዳደርግ ተገድጃለሁ ፡፡
- በተለይ ግንቦት 11 ላይ የዞን9 አላማ ጠይቀውኝ ስናገር እውነቱን አውጣ በሚል በተደጋጋሚ ድብደባ የደረሰብኝ ሲሆን ደስታ እና ሃሰን የተባሉ ሽፋን ስሞች የሚጠቀመው መርማሪ በተደጋጋሚ ባደረሰብኝ ጥፌ ድብዳባ ጆሮዬ ተጎድቶ በህመም ላይ እገኛለሁ፡፡
- ቤቴ የተገኘው ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያሉትን ቃላት ነጣጥለው የሰጠሁት ቃል ውስጥ ያስገቡትን፣ ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያለው ሙሉው ነው አንጂ ተነጣጥሎ ቃሌ ውስጥ ተካቶ አልፈርምም በማለቴ አቶ ፈይሳ፣ አቶ ዬሃንስ ( ስማቸው የሽፋን አንደሆነ የምጠረጥረው) ታደሰ( ጥጋቡ በሚልም ይጠራል) ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውብኛል፡፡
- ድብደባውም ጨለማ ክፍል ውስጥ በማስገባት አፌ ውስጥ ካልሲ በመወተፍ እግሮቼን ከላይ፣ ውስጥ እግሬን እና ከውስጥ ባቴን ታፋዬን እንዲሁም ጀርባዬን በእንጨትና በኮምፒውተር ገመድ ገርፈውኛል ፡፡
- የምርመራ ክፍሉ ወለል ላይ በደረቴ አንዲሁም በጀርባዬ እያገላበጡ በማስተኛት መላ ሰውነቴን ረግጠው ተራምደውብኛል፡። አፌን ሳይቀር ረግጠውታል፡። ይህንን በሚያደርጉበት ሰአት ሞራል የሚነካ ስድብ ይሳደቡ ነበር፡፡ ሁሉም የአካል ሆነ የስነልቦና ጥቃት ሲደርስብኝ እጄ በካቴና ታስሮ ሲሆን በቀን 15 ደቂቃ በላይ የጸሃይ ብርሃን የማላይበት ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ለ76 ቀናት ቆይቻለሁ፡፡
*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

Monday, April 27, 2015

የተሰደድኩ 'ለታ - በጆማኔክስ ካሳዬ

1.    ቶሎ እርምጃ ወስደን ነገሮች በፍጥነት ባይከናውኑ ኖሮ ይህንን መልአክት አሁን ከቅሊንጦ ሆኜ የምጽፈው ይሆን ነበር፡፡

ዓርብ የአዳማ ከሰዓቱ ሙቀት ያየለ ነበር ለሥራ ነጠል እንድታደርገኝ መርጬያት የነበረችው ጥግ ሙቀት ሲያይልባት ወጣ ገባ ማለት ጀምሬያሁ ቅዳሜ ማታ ቴዲ አፍሮ በሚያዘጋጀው ኮንሰርት አንድንገባ አዲስ አበባ እየደዋወልኩ ስጠይቅ  ኤዲ (ኤዶም ካሳዬ)  እንደማትገኝ ስትነግረኝ ትንሽ ቅር ብሎኝ ነበር ቢሆንም ቀን ቴስት-ኦቭ አዲስ የምግብ ፌስቲቫል ላይ ሳልናገር ተከስቼ የዞን ዘጠኝ ጓደኞቼን እና ሌሎች ጓደኞቻችንን ሰርፕራይ ለማድረግ ዱለታ ላይ ነኝ፡፡

የቀኑ መገባደጃ ላይ አንድ አጭር የስልክ መልእክት ወደ ስልኬ ገባ ፡፡ዞላ(ዘላለም ክብረት) ነበር ፡፡
ስልክ መልእክቷ  እጥር ምጥን ያለች ብትሆንም አንዳንድ ጊዜ የዞን9 አባላት ኦንላየን ያለው የግል ቡድናችን ውስጥ ውይይቶቻችን በድምጽ ብልጫ መወሰን ሲኖርብን  ወይም ደግሞ የሞቀ ክርክር እየተደረገ አንድ ሰው ኦፍላየን ሲሆን “ኀረ ወደኢንተርኔት ና እና ሃሳብ ስጥ” አይነት ነገር መልእክት ስልካችን ላይ እንላላካለን፡፡ ከዞላ የመጣውም አጭር መልክት ተመሳሳይነት ነበረው፡፡  ግን ይሄኛው በጣም ያጠረ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከዞላ ድጋሚ ሌላ ቴክሰት ተደገመ ፡፡  “they may arrest me” ይላል መልእክቱ ፡፡በድንጋጤ ወደ ኢንተኔት ስመጣ ሶሊ በሁሉም በኩም መልእክት ስትልክ ደረስኩ ፡፡ አብረው የነበሩት አጥኔክስ እና የበፍቄ ስልካቸው አይመልስም፣ ማሂ ከቢሮ ተወሰደች፣ አቤልም እንደዛው፡፡ የሆነ የከፋ ነገር እየተከናወነ ነው ዘግይተው ነው አንጂ እኔ መድረሳቸው እንደማይቀር ተስማማን፡፡


የዚያን ሰሞን ወከባችን ሲበዛና ምን ይሻላል የሚለው ውይይት ሲደጋገም ዞላ ‹‹ምንም በሌለበት ኢሕአዴግ እኛን ካሰረ አብዷል ማለት ነው›› ብሎ ይከራከር ነበር፡፡አሁን በአይኔ የማየው የመታሰር ስጋት መልእክት የመጣው ከዞላ ነው፡፡ የማህበራዊ ሚዲያን ፈጽሞ የማያውቀው ደህንነት ናቱን ሲያዋክበው “ናቲ ለደህንነት የትውውቅ ኮርስ እየሰጠ ነው” ብለን አንቀልድበትም ነበር ፡።  ናቲን አብረኽን ስራ የሚል ማስፈራራትም ጉትጎታም ሳይቀር ሲያዋክበው ነበር ፡፡ ጓደኞቹን አሳፎ ከሰጠ እሱ ምንም እንደማይሆን ሊወተውተውም ሞክሯል፡፡  አሁን የዞላን ንግግር እና እርግጠኝነት ሳስበው በእኛ እስኪደርስ ጠበቅን እንጂ ካበዱስ ቆይተው ነበር እላለሁ፡፡ 

የዛው ሰሞን  የዞን 9 አባላት የተጠናከረውን የደህንነቶች ክትትል ተንተርሶ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የመታሰር እድል ያላቸው በሚል ከፋፍለን  ለማስቀመጥ ሞክረን ነበር ፡፡ አገር ቤት ካለነው የመጀመሪያውን ደረጃ አጥናፍ እና በፍቄ ሲይዙ ማሂ እና እኔ መታሰር ስጋታቸው  የመጨረሻው ላይ ነው ብለን ታስበን የነበርነው ነን ፡፡ ማሂ መያዝ ዜና ይሄንን ግምታችን አፈር ድሜ ያበላ ነበር፡፡ ከዚህ ዜና በኋላ ኦን ላየን ካሉ ጓደኞቼ ነገሩን በማጣራት  ፈላጊዎቼ እስኪመጡ ሳልጠብቅ  ከስራ ቦታ ላፕቶፔን ብቻ ይዥ ተነስቼ ወጣሁ ፡፡ ስራ ቦታ ሰው ድንገት ከፈለገኝ ለስራ ወደ አዋሳ መሄዴን እና ቶሎ አንደምመለስ ተናግሬ ነበር ፡፡ ወደቤት መሄድ የማይቻል ሃሳብ ሆነ ቀኑም እየተገባደደ በመሆኑ ከስራ ቦታዬ ዞር ያደርገኛል ወዳልኩት አካባቢ ላፕቶፔን ይዥ በፍጥነት አቀናሁ ፡፡ ሥልክ ማጥፋት እና መቀየር፣ በሌላ ሥም አልጋ መከራየት፣ እንቅልፍ አልባ እጅግ በጣም ረጅም ሌሊት በአምባገነኖች በትር በሃዘን ልባችን የተሰበረበት ምሽት ነበር፡፡ የእኔ ነገር ያንን ምሽት ገና ስላለየለትም የኤዶም ስልክም ዝግ በመሆኑ ግራ እየተጋባንም( እስሩ ለዞን9 ብቻ ነው የመጣው የሚል የዋህ ሃሳብም ነበረን)  አንቅልፍ በአይናችን ሳይዞር ነጋ፡፡ ይህ ሌሊት ባለፈ በማግስቱ በእለተ ቅዳሜ አንዲት ነጭ ሸሚዝ እንደለበስኩ ላፕቶፔን ብቻ አንጠልጥዬ የጎረቤት አገር ኤርፓርት ላይ ሶል ተቀበለችኝ ምንም አይነት ኮምንኬሽን ስላልነበረኝ የኤዶምን መታሰር እርግጥ ዜና እና  የአስማማውን መታሰርም እዛው ሰማሁ፡፡  ቶሎ እርምጃ ወስደን ነገሮች በፍጥነት ባይከናውኑ ኖሮ ይህንን መልአክት አሁን ከቅሊንጦ ሆኜ የምጽፈው ይሆን ነበር፡፡  (በመትረፌ ብዙ ባለማድረጌ ከእነሱ ጋር መሆንን ብናፍቅም)፡፡  የታሰርኩ ለታ - ኤዶም ካሳዬ

 "   ከጥቂት ሰአታት በኋላ የእግር ኮቴ ስንሰማ ተሽቀዳድመን በቀዳዳ ስናይ ማህሌትን ወደ ሌላ ክፍል ሲያስገቧት አየሁ ፡፡ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ አለቀስኩ "

አርብ እለት መስሪያ ቤቴ ጎተራ ስደርስ 1.30 አካባቢ ነው በዚያ ጠዋት ቢሮ መግባት ስላልፈለኩ ለአንድ ሰአት ያህል ትዊተር ላይ ወሬ ስለቃቅም ቆየሁና 2.30 ላይ ቢሮ ገባሁ ፡፡ ጠዋቱ የተለየ ስራ የለውም ነበር የእቅድ ዶክመንቶች ማገላበጥ የስልጠና ዝግጅት እና የመሳሰሉትን ስሰራ ቆየሁ ፡፡ አዲስ ሰራተኛ ስለሆንኩ ብዙውን ጊዜዬን የስራውን ባህሪይ ለማወቅ ነው የማጠፋው ፡፡ ምሳዬን ከበላሁ በኋላ የምሳ እረፍት እስኪያልቅ ከሶሊ ጋር ስካይፕ አወራን፡፡  ከሰአት በኋላ አንዲት የስራ ባልደረባዬ መጥታ ደሞዝ መውጣቱን እና አዲስ ጭማሪ መኖሩን ነገረችኝ ፡፡ አዲስ ደሞዝ ጭማሪ ላይ መጣሽ እድለኛ ነሽ እያሉኝ በደስታ የተሞላ የቢሮ ካባቢ ላይ ስንሳሳቅ ቆየን፡፡  10 ሰአት አካባቢ አንድ ከአመታት በፌት ትምህርት ቤት የማውቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የደህንነት ሰራተኛ ነኝ እያለ የሚያዋራኝ ወዳጄ ደወለልኝ፡፡ በዚያን ሰሞን በዞን9 አባላት ጓደኞቼ ላይ አንድመሰክር አንደ ጓደኛ አንደመምከር አንደደህንነት በማስጠንቀቅ ሲያባብለኝ ከርሟል፡፡  አንገናኝ ሲለኝ መልሼ እደውልልሃለሁ ብዬው ዘጋሁት ፡፡ ከዚያ አንዲት ሴት ጓደኛዬን ከቢሮ ከመውጣቴ በፌት የት አንደሆነች ጠይቄያት ብሄራዊ አካባቢ መሆኗን ስትነግረኝ ሃሮ ካፌ አንገናኝ ብያት ዘጋሁት ፡፡ ስካይ ላይ ከሶሊ ጋር ስለደሞዝ ጭማሪ እና የመሳሰሉት አውርተን ማታ እቤት ስገባ ትዊተር ላይ እናወራለን ብያት ተሰነባብተን ከቢሮ ለመውጣት ተዘጋሁ፡፡ ከመውጣቴ በፌት የእስክንድር ጽሁፎች ስብስብ ከሆነው ፒዲኤፍ ላይ ቀንጭቤ ትዊተር ላይ ለጥፌ መውጣቴ ትዝ ይለኛል፡ እየወጣሁ እያለ ደህንነቱ ጓደኛዬ ድጋሚ ደውሎ አንገናኝ አለኝ ፣ ብሄራዊ እየሄድኩ አንደሆነ እና ሰው አንደቀጠርኩ እዛ ከመጣ አንደማገኘው ነግሬው ዘጋሁት፣ ሃሮን አላውቀውም ብሎ ጣፋጭ ካፌ ልንገናኝ ተስማማሁ፡፡

ብሄራዊ ስደርስ ጓደኛዬ ስላልደረሰች ጣፋጭ ካፌ  እሱን አንደማገኘው እና ስትደርስ አንድትነግረኝ ነግሬያት ወደጣፋጭ ካፌ ገባሁ ፡፡ ቤቱ በጣም ሙሉ ነው ስደውልለት ትራፌክ ይዞኝ ነው መጣሁ አለኝ፡፡ ከአንድ ከ30 ደቂቃ በኋላ መጣ፡፡ ፌቱ ላብ በላብ ሆኗል፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ የትምርህት ቤት ወዳጄ አብሮኝ የበላ አብሮኝ የጠጣ አብረን የሳቅን ብዙ ነገር ያወራን ነው ፣ ለደህንነት እሰራለሁ ከማለቱ ከ2 አመት በፌት ጀምሮ በደምብ ነው የማውቀው) ስለነፍሰጡር ባለቤቱ ደህንነት ጠየኩት ደህና ናት አለኝ፡፡ ፌቱ ግን መረበሽ ይታይበታል፡፡ ያዘዘውንም ማኪያቶ ሳይጠጣ ሂሳብ ከፍሎ ለመሄድ መዘገጃጀት ጀመረ ፣ ለምን እንደፈለገኝና ምን እነዳጣደፈው ስጠይቀው ክላስ አለብኝ መሄድ አለብኝ አለ፡፡ቀና ስል በመስኮቱ ማዶ አንድ ሰሞን ሲያናግረኝ የነበረ አንድ ሌላ የደህንነት አባል አየሁ ያን ጊዜ የሆነ ነገር አንዳለ ጠረጠርኩኝ |፡፡ ወዲያው ስልኬ ጮኽ።  ሶሊ ነበረች ( ያኔ ስለእስሩ ሰምታ ቼክ ልታደርገኝ አንደነበር አላወኩም) ስልኬን ይዜ ስነሳ ተከትሎኝ ስልክ የሚያወራ መስሎ አጠገቤ መጣ፡፡ ደህና ነኝ መልሼ እደውልልሻለሁ ብያት ዘጋሁት ፡፡

ወዲያው ልሂድ ብሎ ወጣ ጣፋጭ በር ላይ ተሰነባበትን ፡፡ ወዲያው አስፓልቱን ስሻገር አንድ መኪና መንገድ ዘጋብኝና ሁለት ተራ ወንበዴዎች የመሰሉ ሰዎች አንድገባ አዘዙኝ፡፡ አልገባም አልኩኝ ፡፡አንደኛው እጄን ጠምዝዞ አስገድዶ ወደመኪናው መራኝ ያኔ መከራከሩ እንደማያወጣ ገባኝ፡፡ ከኋላ አስገብተውኝ ግራና ቀኝ ተቀመጡ፡፡ መኪናዋን ይኸው የትምህርት ቤት ወዳጄ ይዟት እንዳየሁ አስታወስኩ፡። ቆሻሻና ዳሽ ቦርድ የሌላት  መኪና ናት፡። ከነሹፌሩ የቀን ስራ ሲሰሩ ውለው ያላባቸው የሚመስሉ ሶስት ወጣቶች አሉ፡፡ ጋቢና ያለው ወጣት “ኤዲ አንዴት ነሽ ?” አለኝ ጸጥ አልኩኝ፡፡ ፓሊስ ጣቢያ ለጉዳይ አንደፈለጉኝ እና ቶሎ አንደምለቀቅ ተናግሮ ሊያረጋጋኝ ሞከረ፡፡  ሹፌሩ ያለምንም ማቅማማት ጥቁር አንበሳ እና ባንኮዲሮማ ህንጻ ጋር ያሉትን መብራቶች እየጣሰ ጉዞ ወደፒያሳ ሆነ፣ ምን እነዳጣደፈው እንጃ ።። ቤተሰቦቼ ጋር አንድደውል ይፈቀድልኝ ብልም ስልኬን ወስደው ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ ፡፡ ማአከላዊ ስንደርስ 12.50 አካባቢ ሆኗል፡፡ መደበኛ ምዝገባ ተደርጎልኝ ንብረቶቼን አስረከብኩ ፣ እርቃኔን ከሆንኩ በኋላ ቁጭ ብድግ እያልኩ ሰውነቴ ሁሉ ተፈትሿል፡፡ ከታሰሩ ሴቶች ጋር ስቀላቀል እራትና የሌሊት ልብስ ሰጡኝ፡። ከጥቂት ሰአታት በኋላ የእግር ኮቴ ስንሰማ ተሽቀዳድመን በቀዳዳ ስናይ ማህሌትን ወደ ሌላ ክፍል ሲያስገቧት አየሁ ፡፡ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ አለቀስኩ ፡፡ ቤተሰቦቼ ልጃችን ምን ዋጣት ብለው አንዴት አንደሚነጋላቸው እየተጨነኩ ነጋ፡፡

“I saw Mahlet being taken to another room, I cried for the first time” – Edom Kassaye

That Friday morning I spent an hour on updating myself on Twitter and entered office at 8:30 AM. Since I was a new employee, I spend much of my time in understanding my job's description. After I ate my lunch, I skyped with Soli.  In the afternoon, a colleague came and informed me that the salary is released and there is also a new incremental change in our salary. My colleagues shared their happiness with me and congratulated me for being a staff at this time. Around 4 PM a friend of mine, who is my school friend years ago and who now said he is working as security agent for the government, called and asked me to meet him. I hang up the call by letting him  know that I will call him back. Before I get off from work, I called to my friend and agreed to meet around National Theater at Haron Cafe. I had a brief skyping with Soli and informed her about the incremental change in our salary and had an appointment with her to talk through twitter when I get home. Lastly, I twitted a quote from Eskinder's writing, and then, I got off from work. While I was in my way to meet my friend, my friend- the security agent-called me. I informed him about my appointment because he insisted I agreed to meet at Tafac’h Cafe.  
     
When I arrived at the Café, he was not around.  He came after 30 minutes. he was sweating. (Btw this person was a good friend of mine with whom I had good times for the last two years, I had always considered him as a friend)  I asked him about his pregnant wife and he answered that she is doing good. Yet, from his face I learned that he was disturbed.  Before he finished his Macchiato, he wanted to pay the bill and go. When I scanned the surrounding, I saw another security agent, who had been contacting me and suspected that there is something going on. In meantime, Soli called me and when I try to talk with her a bit away from him, he followed me as if he is also speaking through phone.  So, I informed Soli that I will call her back and hang up the phone.( At that time, I did not know that Soli was aware of the crackdown and she called me to check the situation I am in.)


 When I crossed the main traffic road, after finished talking to him, a car closed my way and two security agents-who look liked like gang of robbers- asked me to enter into the car. But I denied. One of them wringed my hand and forced me in the direction of the car. They forced me to enter the car in the backseat in the middle of two of them. I remembered that my school friend used to drive this car.

The car was very dirty, so us my detainers. There were three security agents in the car, who sweated as if they spent the whole day as daily laborers. The guy, who sat nearby the driver, asked me "Edi, how are you doing?". I remained silent. He tried to cool me down by saying that they want to talk to me at the police station and I will be released sooner.I asked them to call to my family but they denied me and confiscated my phone. It was around 6:50 PM when we arrived at Me'akelawi. I went through regular registration, submitted all my belonging materials, and investigated while I was naked. When I joined the women inmates, they gave me night close and a dinner. After few hours, we heard footsteps and when I saw through a hole, I saw mahlet being taken to another room. Then, for the first time since I get detained I cried. I was stressed by thinking of what my family would think of my disappearance and did not able to sleep the whole night. 


የታሰርኩ ለታ - ማህሌት ፋንታሁን

1.    እናቴ ስትገባ ቤቱ በፓሊስና በደህንነት ተከቦ እኔም ፓሊሶች ይዘውኝ ስታይ በጣም ደንግጣ ራሷን ስታ ወደቀች  

አርብ እንደማንኛውም የስራ ቀን ታናሽ እህቴን ስሜ ከቤት ወጣሁ፡፡ የዚያን እለት ያለወትሮው የወረዳችን ሰራተኛ ቤት መጥቶ መጽሃፍ አንድገዛለትና ከስራ ስወጣ ይዥለት አንድመጣ ከስራ የምወጣበትን ሰአት ጠይቆኝ ነበር፡፡ ተስማምቼ የመጸሃፉን ርእስ ነግሮኝ ገዝቼልህ እመጣለሁ አልኩት ፡፡ የምመለስበትን ሰአት ሰምቶ ሄደ፡፡ በጣም ያልተለመደ ነገር አንደሆነ ተሰምቶኝ አንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ (ያንን ሰው ከዚያ በኋላ አላየሁትም መልእክትም አልደረሰኝም) ፡፡ በእለቱ  አሁን በእስር ላይ የምትገኘው የርእዮት አለሙ እህት  ቹቹ ጋር ተደዋውለን በማግስቱ የፕሮፌሰር መስፍን ልደት ስለነበር ልደት ለማክበር አንደምንሄድ ተስማማን ፡፡ ስጦታውንም አብረን ለመግዛት ተቀጣጠርን፡፡

አርብ የምሳ መውጫ ሰአት በጊዜ ስለሆነ በጊዜ ወጥቼ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል ሄደን የመጨረሻውን ምሳዬን ጣይቱ ታደምኩኝ፡፡ ከሰአቱ ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም ፣የተለመደውን ቢሮ ስራ ስሰራ ቆየሁ ለአንድ ጓደኛዬ ስልክ ቴክስት መላኬ ትዝ ይለኛል አሁን  የላኩትን መልእክት ይዘት ሳስበው  ለተወሰነ ግዜ አንደማንገናኝ ታውቆኝ ነበር ማለት ነው እላለሁ፡፡  በግምት ከቀኑ 10-10.30 አካባቢ ሁለት ሲቪል የለበሱ ወንዶች ቢሮዬ ገብተው እንደሚፈልጉኝ ነገሩኝ፡፡ ከቢሮ ይዘውኝ ወጡና በወንጀል አንደምፈለግ የሚገልጽ የፍተሻ ማዘዣ አሳዩኝ፡፡ ወረቀቱ ላይ የአቤሎ የበፍቄን የአጥናፍ እና የናቲን ስሞች አየሁ ፡፡ ውጪ ሰንወጣ ደግሞ በተጨማሪ ሎሎች አራት ሲቪል የለበሱ ሰዎች ውጪ ቆመው ነበር፡፡  ከዚያ የቆመው የፖሊስ ፒክ አፕ መኪና ውስጥ አስገቡኝ ውስጡ አራት የታጠቁ ፓሊሶች እና እኔ ሆነን መኖሪያ ቤቴን ለማስፈተሽ ጉዞ ወደ ቤተሰቦቼ ቤት ሆነ፡፡  ወደኋላ ሳይ በቤት መኪና ሆነው የሚከተሉን ሲቪል ለባሾችም ነበሩ ፡፡

ስነደርስ ተቆልፈው የነበሩትን የጊቢና የቤት በሮች ከፍተን ገባን እነሱም ፎቶ ማንሳት ጀመሩ ፡፡ በሰአቱ ከስራ ወደቤት የገባ ማንም የቤተሰብ አባል አልነበረም ፡፡  በግምት ከአንድ ከ30 ደቂቃ በኋላ እናቴና አባቴ መጡ ፡፡ እናቴ ስትገባ ቤቱ በፓሊስና በደህንነት ተከቦ እኔም ፓሊሶች ይዘውኝ ስታይ በጣም ደንግጣ ራሷን ስታ ወደቀች፡፡ ከዚያ በኋላ ጊቢው ረብሻ በረብሻ ሆነ ፡፡ የሰፈር ሰዎች በሙሉ ነበሩ ፡፡ ፈተሻው ሲያልቅ ልብሷን አዘጋጁላት ብለው ለቤተሰቦቼ ነገሯቸው፡። ልብሴ ተዘጋጅቶልኝ ሰፈር ሰውና ቤተሰብ ለቅሶ ታጅቤ ከወላጆቼ ቤት በፓሊስ መኪና ወጣሁ ፡። ጉዞ ወደ ማእከላዊ ሆነ ።

ፒያሳ አካባቢ ስንደርስ አንግዳ የሆነ የመረበሽ ስሜት ተሰማኝ ምናልባትም ማእከላዊ እየቀረበ መምጣቱም እስሩም እውነት መሆኑም ሊሆን ይችላል፡፡ ማእከላዊ ስንደርስ መሽቷል፡። ተፈትሼ ስገባ ማእከላዊ ውስጥ ለስምንት ወራት የቆዬ ሁለት የሶማሌ ክልል ተወላጅ ተቀበሉኝ ፡፡ እነዚህ ልጆች በማእከላዊ ቆይታዬ አላማጅና አጽናኜ ሆኑ ፡፡

As any working day, on Friday I kissed my younger sister and left  home for work. In that day, one of the employee of our Worda administration office came and unusually asked me to buy a book for him.and healso asked me when I will get off from work. I agreed with his request and collected the title of the book and informed him my returning time after work. I now remember that I felt that it was very strange request (I did not see this person again nor received any message from him).  Later on, I called to Chuchu, a younger sister of the imprisoned Journalist Reeyot Alemu, to buy a gift for Prof. Mesfin since the next day was his birthday. We have agreed to go together to celebrate his birthday.

I had my last lunch with a friend of mine at Taitu Hotel in Piassa. I spent my afternoon while working my usual task. I remembered that I sent a text message for one of my friend. When I thought about the content of my message now, I feel  that I was unconsciously knew that we might not meet again. When it was around 4:30 Pm, two security agents, who wore civilian dress, came and told me that they want to talk to me. While I was in my way to get out off from my office, they gave me a searching warrant. On the warrant, I was able to see my friends name particularly Abelo, Befeqe, Atnaf and Nati. When we went out of my office, I saw additional four security agents, who were in civil dresses. They let me to enter a police pick up car and there were four militant police and went to home for searching. When I try to see the surroundings, I learned that there are security agents who followed us in private vehicles too.

When we arrived home, I opened the doors and they started taking pictures. At that moment, my families are not yet back from work. After half an hour, my mother and father came. When my mama entered home and realized that there were police officers and I was encircled by security agents she was stroked and failed down. After that there was a huge disruption. All our neighbors came to our home. After the search was completed, the police officers ordered my family to prepare my cloths. After my family prepared my cloths, I entered into the police vehicle while my neighbors and family members were crying.


When we were around Pissa, I felt some distribution feeling. May be it is because that I was near to Me'akelawi and I realized that my detention became true. It was too late when we arrived at Me'akelawi. After I went to through the procedural searching and regulation, I meet two women, who are from Somali region, these women became my helper and source of comfort in my stay there.


                         
        

የታሰርኩ ለታ - ዘላለም ክብረት

1.    ‹‹በእውነት ማዕከላዊ ስገባ እረፍት ነው የተሰማኝ››

አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ቢሮዬ ውስጥ ከአንዲት ህንዳዊት መምህርት ጋር እያወራሁ፣ ስለ ህንድ ባህል እየነገረችኝ ነበር፡፡ የፌስቡክ እና የትዊተር ገጾቼ እንደተከፈቱ ናቸው፡፡ ያን ዕለት ክላስ አልነበረኝም፤ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው በነበረው የተቃውሞ ሁኔታ ምክንያት አልገቡም ነበር፡፡ የአመቱ ክላስ እየተገባደደ ስለነበር በቀጣይ ክላስ ላይ ለተማሪዎቼ የምሰጣቸውን አሳይመንት አዘጋጅቻለሁ፡፡

ከህንዳዊቷ መምህርት ጋር እያለሁ አንድ የግቢ ጥበቃ ባልደረባ (የእኔ ተማሪ ነው፤ ህግ ይማራል) ቢሮየ መጥቶ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እንደሚፈልጉኝ ነገረኝ፡፡ እኔም እሺ ብዬ ለመሄድ ስዘጋጅ አንድ ወዳጄ  ማሂ መያዝዋን ሰምቶ ኖሮ  ማሂን ፖሊሶች ከቢሮዋ  ያዟት ብሎ ደወለልኝ፡፡ አንድ ነገር እንዳለ ጠረጠርኩኝ፡፡ በዚህ ጥርጣሬዬ ላይ እንዳለሁ አንድ የግቢ ደህንነት መጥቶ ለሁለተኛ ጊዜ ዶ/ር ቢሯቸው ይፈልጉሃል አለኝ፡፡ ሁኔታው ገባኝ፡፡ በፍቄ እና አጥኔክስ ጋር ስልክ ስሞክር የሁለቱም ስልኮች አይሰሩም፡፡ በዚህ ጊዜ ለሶሊ ሁኔታውን ገልጬ ጂሜል ቻት ላይ መልዕክት አስቀመጥኩላት፡፡ የቤተሰብን አድራሻም ሰጠኋት፡፡ዋት ዋት ዋት ?? የሚለውን የቻት መልእክቷን እያየሁ ነው የወጣሁት፡፡   ወዲያው ደግሞ ለጆማኔክስ ስልክ ደወልኩለት፤ ጆማ ትንሹዋን ገጽ እያት ብዬው ስልኩን ዘጋሁ፡፡ ይህቺ የስልክ ግንኙነቴም የመጨረሻየ ሆነች፡፡

ከቢሮዬ ወጥቼ የተፈለግሁበት የዶ/ር ቢሮ ስገባ ሁለት ሰዎች ቢሮ ውስጥ አሉ፡፡ አላውቃቸውም፡፡ ዶ/ሩ ስለሁኔታው የሚያውቁ ይመስለኛል፡፡ ( በነገራችን ላይ ከቢሯቸው ታሰርኩት የዬኒርሲቲው ምክትል ፕሬዘዳንት በፌርማቸው ስራ ገበታህ ላይ ባለመገኘት ብለው አንዳባረሩኝ እዚህ ቅሊንጦ ከገባሁ ሰማሁ ፡፡ ) በር ላይ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ፡፡ ሁለቱ ብቻ የፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሱ ሲሆኑ ሌሎች ሲቪሎች ናቸው፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስጠይቃቸው የብርበራ ትዕዛዝን የሚገልጽ ወረቀት አሳዩኝ፡፡ የእኔ እና የእነበፍቃዱን ስም ወረቀቱ ላይ አየሁት፡፡

ከቢሮ ወጥተን በሁለት መኪኖች ወደእኔ ቤት ተወሰድኩኝ፡፡ ሰዓቱ 12፡00 ሊሆን ተቃርቦ ስለነበር ከ12፡00 በኋላ ብርበራ ማድረግ ክልክል መሆኑን ነገርኳቸው፡፡ በአጭር ጊዜ እንደሚጨርሱ ነግረውኝ ወደቤት ሄድን፡፡ ቤት እንደደረስን በር ስከፍት ጀምሮ በቪዲዮ ካሜራ ቀረጻ ጀመሩ፡፡ ቤቴ ውስጥ ብዙ እቃ አልነበረም፡፡ መጽሐፎችን እያገላበጡ የፈለጉትን ያዙ፡፡ ብርበራውን እያደረጉ እያለ 12፡00 ሞልቶ ስለነበር ከዚህ በኋላ መበርበር ህገ-ወጥ ነው ስላቸው አንዴ ጀምረነዋል፣ ስለዚህ እንቀጥላለን አሉኝ፡፡ ፍተሻውን አከናውነው ከቤት ወጣን፡፡

ከቤት እንደገና ኮምፒውተርህን እንፈልገዋለን ስላሉ ወደ ቢሮ ተመለስን፡፡ ቢሮ ስንገባ መሽቶ ስለነበር ጨልሟል፡፡ ቢሮ ላፕቶፔን ይዘው ወጡ፡፡ ከዚያም በሁለት መኪኖች ታጅቤ ጉዞ ወደአዲስ አበባ ሆነ፡፡ ጉዞ ላይ አንድ ደህንነት ሊያነጋግረኝ ሞክሮ ነበር፡፡ ስንት ዶላር በላሽ እያለ ሊያሽሟጥጥ ሲሞክር ከፊት ወንበር ላይ የተቀመጠው አለቃው ማውራት እንዲያቆም ነገረው፡፡ ከዚያም በዝምታ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ሆነ፡፡ አዲስ አበባ ስንደርስ መሽቶ ነበር፤ መኪናው ላይ ሰዓቱን እንዳየሁት ከሆነ ሰዓቱ 3፡00 ሊሞላ ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ስደርስ ሌሎች ሰዎች ተቀብለው ወደውስጥ አስገቡኝ፡፡ በቃ አሁን ማዕከላዊ ነኝ አልሁኝ፡፡ በእውነት ማዕከላዊ ስገባ እረፍት ነው የተሰማኝ፡፡    

“Truly speaking, I feel relieved when I entered Maekelawi.” Zelalem Kibret

It was around 5pm and I was having a chat in my office with one Indian lecturer and she was telling me about Indian culture. My Facebook and Twitter pages were open. I didn’t have class that day. The students’ boycotted class because of a protest unrest in the university. Because the academic year was almost over, I prepared the assignment that I’m giving to my students next year.

While I was with the Indian Lecturer one of the campus police member (who is also my student) came to my office and told me that the vice president of the university is waiting for me in his office. One of my friends called me and told me that the police have taken Mahi from her office while I was preparing to go to the vice president. I suspected something. For the second time, one of the campus securities came and told me that the Dr. is waiting for me. Now I got it. When I tried to call Befqe and Atnex their phones are not working. At this time, I informed Soli about the situation and left her a message on Gmail chat. I also gave her my family’s address. I saw her last reply “What? What? What?”, while leaving the office. Immediately I called to Jomanex. I hanged up telling him to see the little page.( the page that we use to exchange information online) This was my last telephone conversation.

When I get to the Dr.’s office, there were two people. I don’t know them. I think the Dr. knows about the situation. (By the way, I heard while I’m here at Kilinto that even though I was arrested from his office,  this university vice president Dr dismissed me from my job with his signature because I’m absent from work.) There were also other people on the gate. Only two of them wear police uniform. When I asked them for court warrant they showed me the warrant for searching. I saw Befeqadu et.al’s and my name on the paper.

We left the office and I was taken to my house in two cars. Since it was passed 6pm I told them that it is not allowed doing the searching after 6pm. They told me that it won’t take much time. They started video recording form the moment I opened my door. There was not much stuff in my room. They took some of the books. I told them it is illegal to do searching after 6pm but they said they won’t stop before finishing. We left my house after the searching is complete.


We returned back to my office because they wanted to take my laptop. It was dark by the time they get to the office to take my laptop. Then we started our journey to Addis Ababa being escorted by two cars. One of the security guys wanted to talk to me while we were on the road. He tried to mock at me saying how much dollar I get but his boss siting on the front seat told him to stop. Then we continued our journey to Addis with silence. It was late when we reached Addis. As I looked at the clock in the car it was few minutes to 9pm. Other people guided me into Maekelawi. I said, “now I’m at Maekelawi”. Truly speaking, I was feeling relieved. 


               

የታሰርኩ ለታ - በተስፋለም ወልደየስ

1.    ‹ያዘዝኩትን ማክያቶ ሳልጠጣው ነው የወሰዱኝ››

ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የቢግ ባንድ ሙዚቃ ስለነበር እሱን ለማየት ፕሮግራም ይዤ ነበር፡፡ ላፕቶፔን ይዤዋለሁ፤ ብዙ ጊዜ ላፕቶፔ አይለየኝም፡፡ በዚህ ምክንያት ተስፍሽ እኮ ቢሮውን ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው ይሉኛል ጓደኞቼ፡፡ ብሄራዊ ስደርስ ከታክሲ ወርጄ ታይም መጽሔትን ገዛሁና በአምባሳደር በኩል ወደ አራት ኪሎ የሚያደርሰኝን ታክሲ ያዝኩ፡፡ አራት ኪሎ ስደርስ ሰዓቴን ተመልክቼ የሆነ ካፌ ማክያቶ የምጠጣበት ጊዜ እንዳለኝ አሰብኩ፡፡ ከዛም ምርፋቅ ካፌ ገብቼ ማክያቶ አዝዤ ተቀመጥኩ፡፡

ወዲያው ብሄራዊ የገዛሁትን ታይም መጽሔት አውጥቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ አንድ አንቀጽ እንዳነበብኩ ሦስት ሲቪል የለበሱ ሰዎች አጠገቤ ቆመው ተስፋለም ብለው ጠሩኝ፡፡ ቀና ብዬ ሳያቸው አላውቃቸውም፡፡ ምን ፈልጋችሁ ነው አልኳቸው፡፡ ለጥያቄ እንፈልግሃለን አሉኝ፡፡ እኔም እናንተ እነማን ናችሁ፣ መታወቂያ አሳዩኝ እስኪ ብዬ ጠየኳቸው፡፡ ምንም አይነት ድንጋጤ አልነበረኝም፤ እስር አንድ ቀን ሊመጣ እንደሚችል አስብ ነበር፡፡ መታወቂያ ስጠይቃቸው ከካፌው በር ውጭ የነበረን አንድ የደንብ ልብስ የለበሰ የፌደራል ፖሊስ አባል ይዘው መጡ፤ መታወቂያ አሳየኝ፣ የደንብ ልብሱንም ተመልክቼ ሁኔታው ገባኝ፡፡

ከካፌው እንድንወጣ ሲያደርጉኝ ያዘዝኩትን ማክያቶ አልጠጣሁትም ነበር፡፡ ሳነበው የነበረውን መጽሔትና ላፕቶፔን ነጥቀው ወደበር ይዘውኝ ወጡ፡፡ በር ላይ ሌሎች ሰዎችም አሉ፡፡ ጥግ ላይ አቁመውኝ ስልክ ይደዋወላሉ፡፡ ደሞ በምን ይሆን የያዙኝ እያልኩ አሰብኩ፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲያሳዩኝ በእነ በፍቃዱ ኃይሉ የሚል ነገር አይቼ በዞን ዘጠኞች ጉዳይ ነው አልኩና የበለጠ ተረጋጋሁ፡፡ ትንሽ እንደቆምን መኪና መጥቶ ወደቤቴ እንድንሄድ አዘዙኝ፡፡ መኪናዋ ሳይረን እያሰማች ወደቤት ሄድን፡፡ መንግስት በዚህ ደረጃ በጠላትነት ይመለከተናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ከካፌው እንድወጣ ስደረግም ሆነ ከካፌው በር ላይ ቆመን ሳለ፣ እንዲሁም ወደቤት ሲወስዱኝ ማንም ቀና ብሎ የሚያይ የለም፡፡ ገረመኝ! ወይ ህይወት አልኩኝ ለራሴ፡፡

ቤት እንደደረስን ቶሎ ወደ ቤት አልገባንም፡፡ ቤቱ ሲፈተሽ ታዛቢ ያስፈልጋል ስለተባለ ታዛቢ ፍለጋ ሰው እያስቆሙ ይጠይቃሉ፡፡ ብዙ ሰው እምቢ ሲላቸው አየሁኝ፡፡ ከ30 ደቂቃዎች በላይ በር ላይ ቆመናል፡፡ ሰው በግርታ ይመለከተናል፡፡ ታዛቢ የተባሉ ሰዎች ተገኙና ወደቤት ገባን፡፡ በር ስከፍት ጀምሮ ቪዲዮ ቀረጻ ያደርጋሉ፡፡ ቤት ብቻየን ስለምኖር ብዙም ያስጨነቀኝ ጉዳይ አልነበረም፡፡ የሚደነግጥ ሰው አልነበረም፡፡ ቤት ውስጥ ያልፈተሹት ነገር የለም፤ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ምኝታ ቤት፣ ሽንት ቤት አልቀራቸውም፡፡

ቤቴ ሲፈተሽ ሰዓቱ እየመሸ ነበር፤ 3፡00 አካባቢ ሆኗል፡፡ ፍተሻው እየተገባደደ እያለ አንዱ ደህንነት ‹ራት በልተሃል› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ማክያቶየን ሳልጠጣ እንዳመጣችሁኝ ታውቅ የለ ስል መልሼ ጠየቅሁት፡፡ ከዚያ ራት ብላ፣ ከጎረቤት ይምጣልህ ማንን ነው የምትግባባው አለኝ፡፡ በመሐል ሌላኛው ደህንነት እኛም እርቦናል ከውጭ ይታዘዝ ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ አይ ከጎረቤት ይምጣለት ተባለና አንዲት ህጻን ልጅ ያላት ጎረቤቴ በሳህን አመጣችልኝ፡፡ እኔም ጎረቤቴን አይዞሽ ሰላም ነው፣ ጋዜጠኛ ስለሆንኩ ነው የያዙኝ አልኳት፡፡ ከዚያ በፊት ጋዜጠኛ መሆኔን አታውቅም ነበር፡፡ ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው ስል ደህንነቶች ‹ምን አስር ጊዜ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ ትላልህ› እያሉ አንባረቁብኝ፡፡ እኔም አዎ ጋዜጠኛ ነኝ መብትና ግዴታየን አውቃለሁ፣ የያዛችሁኝም ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው አልኳቸው፡፡

ፍተሻው ተጠናቅቆ ከቤት ልንወጣ ስንል የቤቱ በሮችና መስኮቶች መዘጋታቸውን ማረጋገጥ አለብኝ አልኳቸው፡፡ ከዚያም ‹የቤቱ ቁልፍ…› ብዬ ስናገር፣ ከአፌ ተቀብለው ቁልፉ ከማን ከማን እጅ ነው የሚገኘው አሉኝ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ቢያንስ መታሰሬን የሚሰማ ሰው ላገኝ ነው አልኩኝ፡፡ ከዚያም አንድ ቁልፍ ከጓደኛዬ ጽዮን (ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ) ጋር መኖሩን ስናገር የሚያውቋት ደህንነቶች ሰው ልከው ነገሯት፡፡ ቤታችን ቅርብ ለቅርብ ነው፡፡ ጺዮን ሁኔታውን ስታውቅ በድንጋጤ ደረጃውን በፍጥነት እየወረደች ስትመጣ ተመለከትኩኝ፡፡ ምን ልታደርጉት ነው፣ እነማን ናችሁ…እያለች አካባቢውን ቀወጠችው፡፡ ሰው ተሰባሰበ፡፡ እኔም አይዟችሁ ጋዜጠኛ ስለሆንኩ ነው የያዙኝ እያልኩ ለማረጋጋት ሞከርኩኝ፡፡

የሰውን መሰብሰብ ያልወደዱት ደህንነቶች በመኪና ወዲያውኑ ግቢውን አስለቅቀው ይዘውኝ ነጎዱ፡፡ ጉዞው ወደ ማዕከላዊ ነበር፡፡ ማዕከላዊ እንደደረስን ብዙ ሰው (ደህንነቶችና ፖሊሶች) ግቢውን ወረውታል፡፡ ሌሎች የታሰሩ ሰዎችም መኖራቸውን ጠረጠርኩ፡፡ ምክንያቱም እኔን ለመያዝ ስምንት ሰው ተመድቧል፡፡ ያ ሁሉ ሰው ደግሞ ሌሎች ሰዎችን ይዞ መጥቷል ማለት ነው፡፡ እኔ ማዕከላዊ ስደርስ በዕለቱ ከታሰሩት ሰዎች ሁሉ ዘግይቼ ማዕከላዊ የደረስኩ እኔ መሆኔ ገባኝ፡፡ ውስጥ ገብቼ ስሜ ሲመዘገብ መዝገቡ ላይ የበፍቃዱን ስም አየሁት፡፡ አሁን ጉዳዩ የበለጠ ገባኝ፣ በዞን ዘጠኞች ነው ማለት ነው አልኩኝ፡፡ የበለጠ ተረጋጋሁ፡፡ ከምዝገባ በኋላ አንድ ሰው ብቻ ወደሚገኝበት ክፍል አስገብተው ቆለፉብኝ፡፡


“They took me before I drink the macchiato I ordered.” Tesfalem Woldeyes
I had a plan to attend the Big Band music show at Yared Music School. As usual I have my laptop with me. My friends always make fun of me saying “Tesfish moves carrying his office.” I bought Time magazine around the National Theatre and went to Ambassador Cinema to catch a taxi to Arat Kilo. By the time I got to Arat Kilo I thought that I have a time for a macchiato. Then I went to a café called Mirfaq and ordered one.

I started to read the Time magazine I bought. I read only just a paragraph when I heard my name being called by three civil wearing guys. I couldn’t recognize any one of them. I asked “What do you need?” “We need you for a question?”, they answered. “Who are you? Show me your ID.”, I continued asking. I was not frightened at all. I had the feeling that imprisonment will come one day. They brought a uniformed federal police member when I asked for their id. I understood the situation when I saw his uniform.

By the time we leave the café, I didn’t drink the macchiato I ordered. They snatched the magazine I was reading, my laptop and took me out. There were other people on the gate. They took me to one corner and started making calls. “Why do they arrest me?”, I keep on thinking. When they showed me the court warrant I saw Befeqadu Hailu et.al so I feel more relieved knowing that it is a case related to Zone Niners. After a while, they ordered me to go to my house. We went to my house while the siren of the car was on.  I never thought that the government had this much enmity against us. I noticed that nobody gave attention when I was taken out of the café, when we were waiting at the gate as well as when they took me to me house. I was stunned! “Oh! Life!”, I said.

We did not get in immediately when we get to my house. They were asking people to witness the searching. I saw many people refusing to be a witness. We stayed for more than 30 minutes. People were looking at us with some confusion.  They found the so called witnesses and we get into my house. They started video recording starting from the moment I opened my door. Since I’m living by myself, I was not worried at all cause there is no one to be disturbed. They searched everything in my house; newspapers, magazines, bedroom even the toilet.

It was getting late; around 9pm, when they searched my house. When they were about to finish one of the security guys asked “have you eaten your dinner?” “Don’t you know that you brought me here before I drink my macchiato?” I replied with a question. Then he said, “Have your dinner. Let’s ask your neighbours. Who do you know more?” One of the other security guys proposed in the middle for a meal to be ordered because they are also hungry. It was finally decided to get food from my neighbours and a woman who has a little kid brought me food. I comforted my neighbour saying “come down it’s ok. They arrested me because I’m a journalist.” She didn’t know that I am a journalist. When I said because I’m a journalist; “Why are you saying I’m a journalist again and again?” the security guys shouted on me. “Yes, I’m a journalist. I know my rights and responsibilities. You arrested me because I’m a journalist”, I told them.

When we were about to leave, I told them that I have to make sure the doors and windows are closed. Then when I said “the key …”, they quickly followed who else has the key. I feel happy. At least I will get someone who knows I’m arrested. When I told them I have extra key with my friend, Journalist Tsion Girma, the security guys who know her send someone to call her. Our houses are close to each other. I saw Tsion rushing down the stairs and coming to me in shock. “Who are you? What are going to do with him?” she controlled the scene. People gathered. I tried to calm down the people saying that they arrested me because I’m a journalist.


The security guys were not comfortable with the gathering so they rushed me out of the compound. We were heading to Maekelawi. I saw lots of security guys and police at Maekelawi. I suspected that there might be more people arrested today. Given that there were eight people assigned for me I can easily guess that these people might have brought more. I realized that I was a late comer from those who were arrested that day. I saw Befeqadu’s name when my name was being registered. This was confirmation that I’m arrested with a case related to Zone Niners. I was calmer than ever. After the registration, they took me to a cell with only one person and they locked the rood at me.