ሴቶች በዝግመተ ለውጥ ካለመቆጠር ወደ መቆጠር ከመቆጠርም አልፈን ‹ከስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት
ጠንካራ ሴት አለች› የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ተፈጥሮና ባህላችን ተደማምረው አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የሴትና የወንድ
የሆኑ ነገሮች እንዲለዩ ሆነዋል፡፡ የሥራ ዘርፍ፣ የትምህርት ዘርፍ፣ አለባበስ፣ አነጋገር፣ አካሄድ፣ አጻጻፍ፣ ባሕሪ፣ አመለካከት…
ሁሉም የሴት እና የወንድ የሚባሉ አሏቸው፡፡ ጥልቅ የመመራመር ክህሎትን በሚጠይቁ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ ሴቶች የተቀረነውን
ወክለው የተቀመጡ እንጂ እንደወንዶቹ እራሳቸውን ብቻ ወክለው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹የመጀመሪያው የወንድ ጄኔራል› የሚባል ነገር
ሰምተን አናውቅም፡፡ ‹በመጀመሪያ ወደጠፈር የተጓዘው ወንድ› ሲባል ልንሰማም አንችልም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያውኑ ወደ ጠፈር የመጓዝ
ተግባር እና የጦር አዛዥነት ሥራ የወንድ ብቻ ተደርጎ ስለሚቆጠር እና በዘርፉም የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶቹ ጋር ሊነፃፀር የሚችል
ስላልሆነ ነው፡፡
በአገራችን ከተለመዱና የወንዱ ተግባር ተደርገው ከሚቆጠሩ ነገሮች አንዱ ወጪዎችን የመሸፈን
ኃላፊነት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ‹ሴትማ አትከፍልም› እየተባለ የከፋይነት ሥራ የወንድ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ማኅበረሰባችን ለወንድ
የወጪ ሸፋኝነት ኃላፊነት ሲሰጥ በውስጥ ታዋቂነት ጥሮ ግሮ በሚያፈራው ኃብት የሚመሰርተውን ቤተሰብ የማስተዳደር ሥራ ከሱ እንደሚጠበቅ
ይረዳዋል፡፡ ስለዚህም በተሰማራበት ዘርፍ ጠንክሮ በመሥራት ገቢውን ማሻሻል የሕይወት ዘመኑ መመሪያው ይሆናል፡፡ ከሴት የሚጠበቀው
ጥሩ ሚስት እና እናት እንድትሆን ነው፡፡ የራሷ ገቢ የምታገኝበት መተዳደሪያ ወይም ሥራ ያላት ብትሆንም እሰየው ነው፤ ባይኖራትም
ግን ችግር የለውም፡፡ እንዲኖራት አትገደድም፡፡
ወንድየው ወደፊት ለሚያገባት ሚስቱና በጋራ ለሚያፈሯቸው ልጆች ማስተዳደር እንዲችል ገቢውን
ለማሳደግ እና ኃብት ለማፍራት ተግቶ ይሠራል፡፡ ‹ቤት ሳይኖረኝ› ‹ቋሚ ሥራ ሳልይዝ› ‹ጥሩ ደሞዝ ሳይኖረኝ› የሚሉ ወንዶች እንጂ
ሴቶች እምብዛም አይደሉም፡፡ ባጭሩ ማኅበረሰባችን ለሴቶችና ለወንዶች ብሎ ሁለት የተለያየ የተግባር መንገድ አስቀምጦልናል፡፡ በሴቷ
መንገድ የሚገኙ ወንዶች እንዲሁም በወንዱ መንገድ የሚገኙ ሴቶች ቢኖሩም
በአብዛኛው ሴቱም ወንዱም በተመደበለት መንገድ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ይህ አመዳደብ ወንዶችን የሴቶች የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር
ሆነው በበላይነት እንዲመሩን ያደርጋቸዋል፡፡ እኛ ሴቶችም በአብላጫ ድምፅ ያፀደቅንላቸው ይመስላል፡፡