Showing posts with label ቋንቋ. Show all posts
Showing posts with label ቋንቋ. Show all posts

Sunday, October 28, 2012

“ጠንቅቆ” የመጻፍና አለመጻፍ ጉዳይ


በእንግሊዝኛው spelling ወይንም orthography የሚባለውን ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ “ጠንቅቆ መጻፍ” ሲሉ ሠይመውታል፡፡ ጠንቅቆ መጻፍ በአማርኛ ቋንቋ ትክክለኛውን ሆሄ በትክክለኛው ቃል ላይ መጠቀምን ይመለከታል፡፡


ስንጽፍ ‘መጽሀፍ፣መጽሃፍ፣ መጽሐፍ፣ መጽሓፍ፣ መጽኀፍ፣ መጽኃፍ፣ መጽኻፍ፣ መፅሀፍ፣ መፅሃፍ፣ መፅሐፍ፣ መፅሓፍ፣ መፅኀፍ፣ መፅኃፍ፣ መፅኻፍ’ ከሚለው ውስጥ የትኛው ነው ትክክል ከሚለው ጥያቄ አንስቶ፥ ትክክለኛው ቃል ከታወቀ በኋላ ያንን ቃል በተጠቀሙ ቁጥር ለማስታወስ መቸገሩ፣ ያንኑ የሆሄ አጠቃቀም በርቢዎቹ ላይ (መጽሐፍ፣ ጸሐፊ፣ ጽሕፈት…) ላይ ለመተግበር እስከማስታወስ ድረስ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ የግድ ነው፡፡

ሰሞኑን ከኢቴቪ እስከ ፍትሕ/አዲስ ታይምስ… ከፍትሕ/አዲስ ታይምስ እስከ ፌስቡክ ቃላትን በትክክለኛ ሆሄያቸው የመጠቀም እና ያለመጠቀም፣ ተደጋጋሚ ደምፅ ያላቸውን ሆሄያት የማስወገድ እና ያለማስወገድ ጉዳይ በጣም እያወያየ ነው፡፡

ችግሩን መፍትሔ የሌለው ወይም ክርክሩ ማቧሪያ የሌለው የሚያስመስለው ደግሞ በተለይ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የሆሄያቱ መቀያየር የድምፅ እና የትርጉም ልዩነት የማያመጣ መሆኑ ነው፡፡ (ይህ ዓይነቱ ልዩነት ግን በግዕዙ ውስጥ የተለመደ ነው) ሌላኛው የአይቀነስ ባዮች መከራከሪያ ነጥብ ደግሞ “መቀነስ ምን ይጠቅማል?” የሚል እና “ከዚህ በፊት የተዘጋጁ እና የተከማቹ መዝገቦች እና ድርሳናት ማንበብ ይቸግራል” የሚል ነው፡፡

ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በርግጥ የሆሄያቱ መብዛት ለቋንቋው ቴክኖሎጂካል አገባብ (በተለይ ከኮምፒዩተር የቁልፍ ሰሌዳ አቀማመጥ አንጻር አስቸጋሪ እየሆነ ስለሆነ) ቢቀነስ ይጠቅማል  ማለትም ይቻላል፡፡ የሆነ ሆኖ የዚህ ዓይነቱ ክርክር ሰሞኑን የተፈጠረ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ መጽሐፍ እጃችን የገባው፥ ለዞን ዘጠኝ የቋንቋ ዘዬ እያዘጋጀን ሳለን ነበር፡፡