Sunday, October 28, 2012

“ጠንቅቆ” የመጻፍና አለመጻፍ ጉዳይ


በእንግሊዝኛው spelling ወይንም orthography የሚባለውን ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ “ጠንቅቆ መጻፍ” ሲሉ ሠይመውታል፡፡ ጠንቅቆ መጻፍ በአማርኛ ቋንቋ ትክክለኛውን ሆሄ በትክክለኛው ቃል ላይ መጠቀምን ይመለከታል፡፡


ስንጽፍ ‘መጽሀፍ፣መጽሃፍ፣ መጽሐፍ፣ መጽሓፍ፣ መጽኀፍ፣ መጽኃፍ፣ መጽኻፍ፣ መፅሀፍ፣ መፅሃፍ፣ መፅሐፍ፣ መፅሓፍ፣ መፅኀፍ፣ መፅኃፍ፣ መፅኻፍ’ ከሚለው ውስጥ የትኛው ነው ትክክል ከሚለው ጥያቄ አንስቶ፥ ትክክለኛው ቃል ከታወቀ በኋላ ያንን ቃል በተጠቀሙ ቁጥር ለማስታወስ መቸገሩ፣ ያንኑ የሆሄ አጠቃቀም በርቢዎቹ ላይ (መጽሐፍ፣ ጸሐፊ፣ ጽሕፈት…) ላይ ለመተግበር እስከማስታወስ ድረስ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ የግድ ነው፡፡

ሰሞኑን ከኢቴቪ እስከ ፍትሕ/አዲስ ታይምስ… ከፍትሕ/አዲስ ታይምስ እስከ ፌስቡክ ቃላትን በትክክለኛ ሆሄያቸው የመጠቀም እና ያለመጠቀም፣ ተደጋጋሚ ደምፅ ያላቸውን ሆሄያት የማስወገድ እና ያለማስወገድ ጉዳይ በጣም እያወያየ ነው፡፡

ችግሩን መፍትሔ የሌለው ወይም ክርክሩ ማቧሪያ የሌለው የሚያስመስለው ደግሞ በተለይ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የሆሄያቱ መቀያየር የድምፅ እና የትርጉም ልዩነት የማያመጣ መሆኑ ነው፡፡ (ይህ ዓይነቱ ልዩነት ግን በግዕዙ ውስጥ የተለመደ ነው) ሌላኛው የአይቀነስ ባዮች መከራከሪያ ነጥብ ደግሞ “መቀነስ ምን ይጠቅማል?” የሚል እና “ከዚህ በፊት የተዘጋጁ እና የተከማቹ መዝገቦች እና ድርሳናት ማንበብ ይቸግራል” የሚል ነው፡፡

ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በርግጥ የሆሄያቱ መብዛት ለቋንቋው ቴክኖሎጂካል አገባብ (በተለይ ከኮምፒዩተር የቁልፍ ሰሌዳ አቀማመጥ አንጻር አስቸጋሪ እየሆነ ስለሆነ) ቢቀነስ ይጠቅማል  ማለትም ይቻላል፡፡ የሆነ ሆኖ የዚህ ዓይነቱ ክርክር ሰሞኑን የተፈጠረ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ መጽሐፍ እጃችን የገባው፥ ለዞን ዘጠኝ የቋንቋ ዘዬ እያዘጋጀን ሳለን ነበር፡፡

መጽሐፉ የፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ “የአማርኛ ሞክሼ ሆሄያትን ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ” ይሠኛል፡፡ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች ላይ የሆሄያት አጠቃቀም ግድፈቶች ለመጽሐፉ መዘጋጀት ምክንያት እንደሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም የአማርኛ ቋንቋዎች መርሐ ልሳን (አካዴሚ) በ1973 ባወጣው የአጻጻፍ ሥርዓት ላይ “ለአንድ ድምፅ አንድ ምልክት” በሚል መርሕ ‘ሐ’፣ ‘ኀ’፣ ‘ሠ’፣ ‘ዐ’ እና ‘ጸ’ እንዲወገዱ ‘ሀ’ እና ‘አ’ እንደ ‘ኸ’ እና ‘ኧ’ እንዲተኩ ቢወሰንም የተጠቀመበት ባለመኖሩ መክሸፉን ይነግሩናል፡፡ ስለዚህ ሆሄያቱ እንዲጻፉ በማለት እነዚህን ሞክሼ ቃላት የያዘ፣ ጠንቅቆ መጻፍን የሚያግዝ ነው - መጽሐፋቸው፡፡


በዚህ እና በነዚህ ጠንቅቆ የመጻፍ ጉዳዮች ዙሪያ በግሌ በተደጋጋሚ በማሰብ እና በመሞከር በርካታ መሠረታዊ ቃላትን ከነሆሄያቱ እንዲለምዱብኝ በማድረጌ ባልተለመደው ሀሄ ተጽፈው ሳይ ቅሬታ ይሰማኝ ጀምሯል፡፡ ችግሩ ይህ ልምድ አጻጻፋቸውን በትክክለኛው በለመድኳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በተሳሳተ ልምድ የምጽፋቸው ቃላት ላይም እውነት ነው፡፡ ሌላው ችግር፣ በሞክሼ ሆሄያት ሊጻፉ የሚችሉ እጅግ በርካታ ቃላት አሉ፡፡ አንዳንዶቹን እጃችን በመራን ሆሄ መጻፍ ከመልመዳችን የተነሳ በየትኛውም ሆሄ ተጽፈው ብናይ ምቾትም ቅሬታም አይሰማንም፡፡ እንደ እንግሊዝኛው “የጠንቅቆ አጻጻፍ ማረሚያ (spelling correction)” ያስፈልገዋል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ሶፍትዌር እንደ መፍትሔ

የማይክሮሶፍት ኦፊስ ወርድ የተለመደ የእንግሊዝኛ ቃለት spelling ስህተት ሲሠራ በራሱ እንዲያርም ተደርጎ ተሠርቷል፡፡ ተመሳሳይ ነገር በአማርኛው ቋንቋ ላይ ለመተግበር ቢታሰብም በተለይ በቋንቋው ላይ ጠንቅቆ የመጻፍ ጉዳይ ትክለኛውን የሞክሼ ሆሄ የመምረጥ ችግር ከአንግሊዝኛው የspelling ችግር የቀለለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ በዚህ በሶፍትዌር ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች “ጠንቅቆ አጻጻፍ” አጋዥ የሆኑ ሶፍትዌር ቢያዘጋጁ እና… ለምሳሌ  ‘መጽሀፍ፣መጽሃፍ፣…’ ብለን ስንጽፍ በትክክለኛው ሆሄ  ‘መጽሐፍ’ ብሎ ቢያርመን ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ 

2 comments:

  1. Thank you Befekadu! But ... Yehone Asamange reason betagengelet, something that can force any anbabi or writer... To use the right fidels. I'm saying this because I found my self asking after reading ur Tomatre, so why not use the other fidels as long as it doesn't change the meaning? I hope u get my point!
    Bertalene!!! We need more Ethiopiayawi like u!!

    ReplyDelete