በበፍቃዱ ኃይሉ
ጥንት፣ ዐሥር
ዓመት ከዘለቀ የግሪክ እና ትሮይ ጦርነት በኋላ ግሪኮች ሰለቻቸው እና መላ ዘየዱ። ግዙፍ የጣውላ ፈረስ ገንብተው ውስጡ የተመረጡ
ወታደሮችን አስቀምጠው ሸሹ። ይህንን እንደ ድል የቆጠሩት ትሮዮች ለድላቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ፈረሱን ጎትተው ከተማቸው መሐል
አቆሙት፡፡ በውድቅት ለሊት፣ ፈረሱ ውስጥ የተደበቁት ግሪኮች ወጥተው የትሮይ ከተማን በማውደም በጦርነቱ አሸናፊነት ተቀዳጁ እስከወዲያኛው
ይባላል። ዛሬ-ዛሬ በመላው ዓለም “የትሮይ ፈረስ” (Trojan Horse) የሚለው ሐረግ ‹ለእኩይ ዒላማ መሸሸጊያነት የሚሰጥ መልካም
መሳይ ምክንያት› የሚለውን ለመግለጽ ይጠቅማል።
![]() |
ኢትዮጵያ ውስጥ
ባለው የገዢው ፓርቲ ብያኔ መሠረት የኢትዮጵያ ችግር የሠላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ (እንደ ቅደም ተከተላቸው) ነው። ሦስተኛው
ለሁለተኛው፣ ወይም ሁለተኛው ለአንደኛው ሲባል ሊጨፈለቁ ይችላሉ። ሦስቱ አብረው እንደሚገኙ ሳይሆን፣ በተራ በተራ እንደሚረጋገጡ
ይደሰኮራል፡፡ ሠላም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መኖር አለበት የሚለው የኢሕአዴግ መደምደሚያ የኦጋዴንን፣ የጋምቤላን እና በቅርቡ ደግሞ
(በማስተር ፕላኑ ሳቢያ) የኦሮሚያን ሕዝባዊ ጭፍጨፋዎች ለማስተባበል (to justify) ከመዋሉም በላይ ብዙ የተሞተለትን የባድመን
መሬት አሳልፎ መልሶ አስከመስጠት አስደርሷል። “ለሠላም” ሲባል! አንፃራዊ ሠላም ባለበት ጊዜ ደግሞ ዴሞክራሲ ለልማት በሚል ሰበብ
እየደማ ነው። በሌላ በኩል የዚሁ ብያኔ ባለቤት ኢሕአዴግ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ አይደለም፣ ግዴታ ነው” ይላል። ስለዚህ
‹ልማትና ዴሞክራሲን አብረን እያስኬድን ነው› የሚል ነቢብ እየደሰኮረ በሌላ አጀንዳ ደግሞ መልሶ ‹ለልማት ሲባል ዴሞክራሲ ይ ቆይ፤
የድኃ ሕዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ዳቦ ነው› በሚል ዴሞክራሲን ጥያቄ እንደቅንጦት እቃ ጥያቄ ቸል ይለዋል። የሁሉም ነገር ታዛቢዎች ‹አለ
የሚባለው ልማትስ የታለ?› ብለው መጠየቃቸው አልቀረም።
እውን ልማትና ዴሞክራሲ ይጋጫሉ?
ቻይናና ሕንድ፣
ሁለቱም፣ ልማታዊ አገረ-መንግሥት (developmental state) የሚል ማዕረግ አግኝተዋል። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ሕንድ
ዴሞክራሲያዊ መሆኗ ላይ ነው። ፋሪድ ዘካርያ “The Post-American
World” ባሰኘው መጽሐፍ ሕንዶችን “በየዓመቱ በአማካይ 9 በመቶ
የሚያድግ ኢኮኖሚ ይዘው በመሪዎቻቸው የማይደሰቱ ሕዝቦች ናቸው” ይላቸዋል። በየምርጫው መሪ ይቀያይራሉ። ቻይኖች ግን ለዚህ
አልታደሉም። ነገር ግን እነሱ በፈንታው ‹ታድለናል› የሚሉለት ነገር አለ።
ፋሪድን አንድ
የሕንድ ባለሥልጣን እንዲህ ብለውታል፡- “በፖለቲካው ረገድ ሕዝባዊነትን
የሚያስገኙ ብዙ ቂላቂል ተግባሮችን መፈፀም አለብን።… እነዚህ ነገሮች የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕቅዶቻችንን ያደናቅፋሉ። ነገር ግን
ደግሞ ፖለቲከኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ድምፅ ያስፈልጋቸዋል።…” አርክቴክት ኖርማን ፎስተር የተባለ ሰውም ይህንኑ የሚያጠናክር
የሚመስል ነገር ለፋሪድ ነግሮታል። “በሕንድ፣ የኸርትሮው 5ተኛ ተርሚናልን
ለመገንባት፣ የአካባቢ ተስማሚነት ቅኝት (environmental review) ለማድረግ የወሰደበት ግዜ፣ በቻይና ቢሆን የቤጂንግ
አየር ማረፊያን (የኽርትሮው 5ቱንም ተርሚናሎች ቢደመሩ የሚበልጠውን) ጨምሮ ለመፈፀም የሚበቃ ጊዜ ነው።” ቻይናዎች የዴሞክራሲ
“ጣጣ” የለባቸውም፤ ኮሚኒስቶቹ ይህንን እንደመታደል ይቆጥሩታል።
የሁለቱን ልዩነት
ፋሪድ ዘካሪያ ሲደመድም “ዴሞክራሲ ለረዥም ጊዜ ልማት የራሱ የሆነ
ተመራጭነት ሊኖረው ይችላል፤” ይላል። ሆኖም አውቶክራሲያዊ (ሕዝባዊ ተጠያቂነት የሌለባቸው) መንግሥታት “ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማይቀናቀኑት አቅም ዐቅደው፣ ማስፈፀም ይችልሉ፤” ይላል። ፋሪድ በመደምደሚያው ያልገለፀው
አውቶክራሲያዊ መንግሥታት የሚሠሯቸው ፕሮጀክቶች ያለበቂ ‹ሴክተር ሪቪው› በመሆኑ ለዘለቄታው የሚያስከትሉት ችግር መኖር አለመኖሩን
ቀድሞ መገመት የማይቻል መሆኑን ነው። እንዲያም ሆኖ የቻይናን ልማት “ተአምራዊ” የሚሉት ኢኮኖሚስቶች የሕንድን የዛን ያክል አያዳንቁትም።
ሕንድ የቻይናን ያክል መገስገስ ያልቻለችው በከፊል የሕዝብ ብዛት ዕድገቷን (Population growth rate) እንደ ቻይና መቆጣጠር ስላልቻለች ነው። ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት
የሌለባት ቻይና የሕዝብ ብዛት ዕድገቷን ፍጥነት በጉልበት መቆጣጠር ችላለች። ይህንን ለማድረግ የነደፈችው ስትራቴጂ ብዙ ማኅበራዊ
ቀውስ እና ሰብኣዊ እልቂት ያስከተለ ቢሆንም መንግሥቷ አውቶክራሲያዊ ተጠያቂነት አላስከተለም። ያለቀው አልቆ የቀረው በቁሳዊ ጥቅም
አንፃር ይለፍለት የሚል አቋም ይመስላል። ሕንድ ዴሞክራሲያዊ በመሆኗ ይህንን ዓይነት ነገር ማድረግ አትችልም፤ “ቻይኖች በሁሉም ነገር ይበልጡናል፤ ከሕዝብ ብዛት ዕድገት ፍጥነት በቀር”
የሚሉትን ዝነኛ አባባላቸውንም ያፈሩት ለዚያ ይመስላል።
