Wednesday, October 17, 2012

የዓለም ሃይማኖቶች እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት

አቤል ዋበላ

መግቢያ

አንቀጽ ፲፰

እያንዳንዱ ሰው የሐሳብ የህሊናና የሃይማኖት ነጻነት መብት አለው፤ ይህም መብት ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመለወጥ ነጻነትንና ብቻውን ወይንም ከሌሎች ጋር በኀብረት በይፋ ወይም በግል ሁኖ ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የማስተማተር በተግባር የመግለጽ የማምለክና የማክበር ነጻነትን ይጨምራል፡፡

አንቀጽ ፲፱

እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው፤  ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት በሐሳብ የመጽናትንና ዜናን ወይም ሐሳቦችን ያላንዳች የድንበር ገደብ የማግኘትን፣ የመቀበልን ወይም የማካፈልን ነጻነትን ይጨምራል፡፡

እንዲህ ጎን ለጎን አጠጋግቶ ያሰፈራቸው ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR) ነው፡፡ ይሁንና በድንጋጌው በቅደም ተከተል እንደመስፈራቸው ሲስማሙ አይሰተዋልም፡፡ በአንድ ያለማችን ክፍል ያለ የማመን መብቴ ተደፈረ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድን በሌላው የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሰዎችን የመናገር ነጻነት ሲደፈጥጥ ይሰተዋላል፡፡ ሌላው የመናገር መብቴ ገደብ የለውም የሚል ደግሞ የሌላውን ሰው የማመን መብት ሲጥስ እና በአማኒው እሴቶች ሲያፌዝ ተመልክተናል፡፡ ይህ እሰጥ አገባ በተለያዩ እምነቶች፣ በአማኞች እና እምነት የለሾች፣ ባስ ሲል ደግሞ አንድ እምነት አለን ብለው በሚናገሩ ቡድኖች መካከልም ይስተዋላል፡፡ በቅርቡ በሀገረ አሜሪካ በ‹ዩቲዩብ› የተለቀቀ አንድ ቪድዮን ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ ምክንያት ይህ ርዕሰ ጉዳይ  በዓለም ዙርያ መነጋገገሪያ ሆኗል፡፡ ዐሳብን በነጻነት መግለጽ እስከምን ድረስ ነው? እስከመቼ እምነቶች የነውጥ እና ሁከት መነሾ ምክንያት ሆነው ይቀጥላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች በብዙዎች በሕሊናቸው እንዲያመላለሱ አድርጓል፡፡

በሀገራችን ዓለም አቀፉን ወጀብ የተከተለ ትርምስ ባይፈጠርም አንዳንድ ብልጭታዎች መታየታቸው አልቀረም፡፡ በተለይ ሁለቱ የየሀገራችን ሰፊ ተከታይ ያላቸው እምነቶች (እስልምናና ክርስትና) ‹‹ያለመሪ›› የሃይማኖት አባት በተቀመጡበት በዚህ ወቅት ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢና የሰከነ ውይይትን የሚጠይቅ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግስት በተለመደ ስልቱ እኔ ብቻ ላውራ ስለሚል ቄሱም ሼኩም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ካህናት እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡በዚህም ምክንያት እንኳን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ያላቸው እምነቶች ይቅርና ሌላው ግለሰብም ይናገር፣ የተለየ አስተሳስብ ይኑረው፣ ያን ይገልጽ፣ ያንፀባርቅ ዘንድ አልተፈቀደለትም፡፡ ለዚህ ማሳያ እሩቅ ሳንሄድ ይህች ጦማር በኢትዮጵያ እንዳትነበብ የደረሰባት ተደጋጋሚ እገዳ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ከሰው ልጅ መሠረታዊ እሱነቱ ጋር የተያያዙት እምነት እንዲሁም ዐሳብ መግለጽን እንዴት ማየት አለብን የሚለውን በመዳሰስ ለውይይት መነሻ የሚሆን ዐሳብን ለማቅረብ ይሞክራል፣ ለማብራራት የሚሞክረው ‘ይህ እምነት ልክ ነው፣ ያኛው ጸብ አጫሪ  ነው ወይም እምነቶች ሁሉ ልክ ናቸው የሚለውን ሳይሆን የተለያየ እምነቶች ያሉበት ሀገር (በተለይ ኢትዮጵያ) እንዴት ትኑር የሚለውን ይሆናል፡፡የውይይታችን ማጠንጠኛም ከዚህ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

መቻቻል እና የተዛባ ትርጉሙ

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካመጣብን ቃላትና የተዛቡ ዐሳቦች አንዱ  ‘መቻቻል’ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የእምነት ጉዳዮች ሲነሱ የመንግስት ሚዲያዎች ይህንን ቃል ደጋግመው በመጥራት ግጭቱን የሚያበርዱ ይመስላቸዋል፡፡ መቻቻል መቻቻል፣ መቻቻል፣. . . . ይህ ግን ከእምነቶቹ ዶግማ አንጻር ከተመለከትነው እጅጉን የተንሸዋረረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሠረቱ ሁለት የተለያዩ የእምነት አስተምህሮዎች ሊቻቻሉ አይችሉም፤ ተቻቻሉ ከተባለም አንዱ አንዱን ካልጨቆነ በስተቀር ሌላ ሁለቱንም ያልሆነ ሦስተኛ አዲስ እምነት ነው የሚሆኑት፡፡ ይህ ለሌሎች ጉዳዮች ሊሠራ እንደሚችል የተለያዩ ንደፈ-ሐሳቦች ሰፊ ማብራሪያን ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ አዝማናትን ለተሻገሩት በብዙ ክርክር ላለፉት እንደ ክርስትና እና እስልምና ካሉ እምነቶች ጋር ግን አይገጥምም፡፡ አንድ በሀልዎተ እግዚአብሔር በሚያምን እና ይህች ዓለም አስገኝ፣ ፈጣሪ የላትም ብሎ በሚያምን መካከል የተቀመጠ ዐሳብ ካለ ሌላ አዲስ አስተሳሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ ፈጣሪ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል ብሎ እንደ መጠርጠር ያለ፡፡ በክርስትና “እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታል” ሲል በእስልምና ደግሞ  በግልጥ “አላህ አይወልድም፣ አይወለድም” ይላል፡፡ ታዲያ የመንግስት ባለስልጣናት እንዴት ነው መውለድ እና አለመወለድን ለማቻቻል ጥረት የሚያደርጉት???

ይህንን እንደ ጥቁር ከሰልና እንደ ነጭ ወተት ያለ ልዩነት በማድበስበስ፣ ለእምነት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነታቸውን በመስጠት በቡድን አሊያም በግል የፈለጉት እምነት እንዲከተሉ ከመፍቀድ ይልቅ የቄሳራዊ ጳጳስነት (Caesario papal) መንገድን መከተል ይዟል፡፡ ይህም እምነት ተቋማቱን በቀሚስ ለባሽ ካድሬዎች በእጅ አዙር ለመምራት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ በአደባባይ ለሚዲያ ቀለብ ይሆን ዘንድ የካህናትቱን መስቀል ሲሳለሙ እና በየመስኪዱ ሲሰግዱ በማሳየት እኛም በእምነት ጥላ ስር ነን (ምእመን ነን)  ለማለት ይሞከራል፡፡ ይህም በየእምነቱ፣ በአማንያን አለመመራት፣ ተቋማቱን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር ባለመቻላቸው  ምክንያት ብሶት፣ ቁጭትና ጥያቄዎች እንደፈጠሩ አድርጓል፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡

መንግስት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የምከተለው (አብዮታዊ ዴሞክራሲ በራሱ ከእምነቶች ጋር ብዙ የሚያላትም ገጾች ቢኖሩትም ዛሬ ከተነሳንበት ዐሳብ ጋር የሚሄደውን ብቻ ይዘን እንሄዳለን፡፡) ቢልም እምነቶችን በተመለከተ በሕገ መንግስቱ ላይ እንደሰፈረው “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖት በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” ማለቱ በእምነቶች ላይ ያለው አመለካከት ኢ-ሃይማኖታዊ ሴኩላሪዝም (irreligion or secularism) መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሃይማኖቶች ከብዙ መንግስታዊ አካላት (መንግስት ከሕዝብ ተነጥሎ እንደተለየ አካል ተቆጥሮ) ከአገልግሎት ሰጪ፣  ከትምህርት ተቋማት፣ ከመንግስት ሚዲያ ከመሳሰሉት. . .  ሲገለሉ በተግባር አይተናል፡፡ ብዙዎቻችንም የሁከት፣ የብጥብጥ ስጋት ስላለብን ጉዳዩን በዝምታ ይሁንታን አጎናጽፈነዋል፡፡ ይህም ለችግሮች መፍትሔ የመሆን አቅም ያላቸው የእምነት በጎ እሴቶች እንደአማራጭነት እንኳን እንዳይታዩ አስገድዷቸዋል፡፡

በመሠረቱ ሴኩላሪዝም እንደመድህን መቀበል ተገቢ አይደለም፡፡ በየትኛውም መስፈርት የኢ-ሃይማኖታዊነት (ሴኩላሪዝም) ሕይወት መርህ ሳይንሳዊ አይደለም፤ ሃይማኖታዊ የሕይወት ዘዬም እንዲሁ ሳይንሳዊ አይደለም፡፡ ሳይንስ;- ሴኩላሪዝም ከአማኒነት እንደሚሻል ማሳየት አይችልም ምክንያቱም ጉዳዩ ከሳይንስ በላይ (beyond science ) ነውና፡፡ የሃይማኖት ኀልዮት በአመክንዮ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል የታመነ ነው፡፡ ይህንንም ማድረግ፣ መጠየቅ የቅኖች መንገድ ነው፡፡   በሴኩላሪዝም እውነት እና በሃይማኖት እውነት መካከል ያለው ውዝግብ ግን በመደበኛ ሎጂክ ሊፈታ አይችልም፡፡ ይህ እውነታ በሁለት እምነቶች መካከልም ለሚካሄድ ክርክርም አይሰራም፡፡ የእስልምናን ስህተት ለማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ (Christian scriptures) መጥቀስ እንደማለት ነው፡፡ለክርስቲያን መጽሐፍት ከቅዱስ ቁራን እና ሌሎች የበለጠ ስልጣን መስጠት ኢ-ምክንያታዊነት ነው፤ ከመጽሐፈ ሞርሞንም ቢሆንም የበለጠ የስልጣን የበላይነት የለውም፡፡

ይህ ሴኩላሪዝምን እንደገለልተኛ የማየት አካሄድ የተዛባ ነው፡፡ ምክንያም ሴኩላሪዝም ይህ ዓለም ከየት እንደመጣ እና ወዴት እንደሚሄድ የራሱ ትንታኔ አለው፡፡ ይህንን ካደረገ ከሌሎች ሃይማኖቶች ምን ለየው? ከጸበኞች መሀል አንዱን መርጦ ዳኛ አደርጎ መሾም ሲከፋ ደግሞ “እነዚህን አመጸኞች ግረፋቸው” ብሎ ልምጭ እንደመስጠት ያለ ነው፡፡ ሴኩላሪዝም የተውኔቱ አካል (entity) ነው እንጂ አዘጋጅ፣ አጋፋሪ ወይም ጸሐፌ ተውኔት ሊሆን አይገባውም፡፡ መንግስት ሴኩላሪዝምን እንደ ኀልዮት የማበረታታት መብት የለውም፤ በጉልበት ታንክ  ተደግፎ  ግን ተችሏል፡፡ ይህ ግን አላዋጣንም፡፡ ታሪካችንም ይህንን አያስተምረንም፡፡ ሀገሪቷ ጠንካራ ማኅበራዊ ጅማት ስላላት እንደሀገር መቀጠል ችላለች፤ ነገን ግን መተንበይ አንችልም፡፡

ከሴኩላሪዝም ባሻገር

ታዲያ ሴኩላሪዝም መፍትሔ ካልሆነ መፍትሔው ምንድን ነው የሚለውን ማጥናት ይገባል፡፡ በመሰረቱ ወደድንም ጠላንም አምልኮ ከሰው ልጅ ጋር የተሳሰረ፣ ከስሜት በላይ የሆነ አቅም ያለው ኃያል እንደሆነም ተረድተናል፡፡ብዙዎች ፍልስፍናን እና ሐሰሳን ለሕሊና ሰጥተው ለሃይማኖት ደግሞ ተረትን ይሰጣሉ፤ ከቀደሙት እጅግ የበዙት ደግሞ ሃይማኖት ፀረ-ሕሊና ወይም ህየንተ ሕሊና ሆኖ የሚቆም ነገር አይደለም፤ መልዕልተ ሕሊና ነው እንጂ ነው ይላሉ፡፡ ከሕሊና በላይ ነው እንደማለት፡፡ በዚህም ምክንያት ሃይማኖት እንደ ተበላ ዕቁብ የምንዘነጋው እንደ አረጀ አፈጀ ልማድ አሽቀንጥረን የምንጥለው ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእምነትን መሠረታዊ ባሕርያት በማጥናት መፍትሔ መፈለግ ይበጃል፡፡

የትኛውም እምነት ሁለት መልኮች አሉት፤ የመጀመሪያው ይህች ዓለም ከየት እንደመጣች፣ ሰዎች በምድር ላይ እንዴት መኖር እንዳለባውቸውና ከሞት በኋላ ደግሞ ተስፋቸው ምን እንሆነ የሚያትት ነው፡፡ ይህም በየእምነቱ ሊቃውንት የሚተነተን ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተለየ መብት (privilege) የሚሰጥ ሌሎችን የሚያገልል (exclusivist) የተንኳሽነት ባህርይ ያለው ነው፡፡ ይህም ሕዝብ  አሕዛብ፣ አማኒ ኢ-አማኒ፣ የተጠመቀ ያልተጠመቀ ብሎ የአዳምን ዘር የሚከፋፍል ነው፡፡ ይህ ልዩነት በመቀጠሉ በማኀበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የሚያገኙ እና የገንዘብ ጥቅም የሚያገኙ የእንጀራ ገመዳቸው ከእነዚህ የእምነት ተቋማት ጋር የተሳሰረ ሰዎች ደግሞ ልዩነቱን የበለጠ እንዲሰፋ ተግተው ይሰራሉ፡፡እውቁ  ጸሐፊ ሰልማን ሩሽዲ  የቁጣ መፈልፈያ (outrage industry) የሚላቸው ዓይነት ነገር ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይላት እምነትን የወግ አጥባቂዎች ማጎሪያ፣ የቁጡዎች መነሐሪያ፣  ኋላቀር፣  ማኅበረሰባዊነትን የሚንድ፣ ከሕሊና ውጪ ያለ (anti-rationale) ያደርጉታል፡፡

ሁለተኛው የእምነት ገጽ ደግሞ በተቃራኒው ሁሉን ሰብስቦ የሚያቅፍ፣ ስለሰብዓዊነት የሚሰብክ፣ የሰው ልጆችን የሚያስተሳስር ነው፡፡ ለበጎ ምግባር ሰውን የሚቆሰቁስ፣ ያጣው እንዲያገኝ፣ ያለው የበለጠ እንዲኖረው፣ የወደቀ እንዲነሳ፣ የታመመ እንዲድን፣ ለፍጹምነት ናፍቆት ያለው (nostalgic) ነው፡፡ በአጠቃላይ በነገረ መለኮት ዕውቀት ከመራቀቅ ይልቅ ስለፍቅር አብዝቶ የሚጨነቅ ነው፡፡  በእኛ ማኅበረሰብ ይህ መልክ የመጉላት አዝማማሚያ አለው፡፡ አቡነ ዘበሰማያት አንዴ መዝለቅ የማይችሉ ወይም “ያላህ ያረቢ አትበለን እምቢ” ብለው በእምነት ከማይመስላቸው ጋር ሳይቀር በፍቅር የሚኖሩ፤  ከአሕዛብ ጋር አትብላ! ከካፊር ጋር አትወዳጅ! የሚለውን ስብከት አልፈው (transcendence) ተካፍለው የሚበሉ ኢትዮጵያውያን ተቆጥረው አያልቁም፡፡ ሐዘኔታን የተላበሰ፣ ለድሆች የሚራራ፣ በደልን የሚጠየፍ ድሀ ሲበድል፣ ፍርድ ሲጓደል የሚቆጠቁጠው ነው፡፡ እንደማሕተመ ጋንዲ እና እማሆይ ትሬዛ ያሉ ታላላቆች ካልሆነ ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ያልኖሩበት ነው፡፡

የእምነት ሰው ሁለቱንም መልኮቹን ይዞ የሚዞር ነው፡፡ አንደኛ ሲጎላ አንደኛው ደግሞ ሲደበዝዝ የሚኖር፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለማችን ታንክና መድፍ በመስቀል የሚባርኩ ጳጳሳት፣ የጀሐድ ጦርነት የሚያውጁ ዑላማዎችን አስተናግዳለች፤ ብዙ ደም ፈሷል ብዙ ንብረትም ጠፍቷል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሙሉ ሕይወታቸውን ለድሆች የሰጡ፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት የቆሙ፣ ድምፅ ለሌላቸው ምፃቸውን የሰጡ ደጋጎችንም አይተናል፡፡

ይህ መልክ እንዲለዋወጥ ምክንያት የሆኑ ብዙ የእምነቶቹ የውስጥ ጉዳዮችና ከሌላው ጋር (በሌላ የእምነት ጥላ ስር ካለው፣ ከኢ-አማኒው እንዲሁም ግራ ከገባው) የሚጋሯቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ዐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ነው፡፡

ዐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ግንባር ቀደሙ እና የእምነቶቹን ሰላማዊነትን የሚቃኝ መልክ የሚያሲዝ ነው፡፡የመጀመሪያው እምነቶቹ በሕዝቡ ዘንድ በግልጽ እንዲነገሩ ዕድል ስለሚሰጥ የስማ በለው ደጋፊ አይኖራቸውም፡፡ሁሉም አውቆ እና ጠይቆ ስለሚረዳ እንደከብት የሚነዳውን ቁጥር ባያጠፋውም ይቀንሰዋል፡፡ ሁለተኛው ተገፋን እንዳናስተምር፣ እምነታችንን እንዳንመሰክር ተለከለን የሚል የእምነት ክፍል አይኖርም፡፡ ሐሳቡን በነጻነት የሚገልጽ እምነት፣ ነጻ የሆነ ህዝባዊ ምህዳሩን(public space) አቅሙ እንደፈቀደ ያለ አድሎ የሚጠቀም እምነት፣ ተቋማዊ ነጻነቱ የተጠበቀለት እምነት ለእኩይ ምግባራት ቦታ አይኖረውም፡፡ በዚህ ሂደት የእምነቶች መልካም ገጽ እያበበ ጸብ አጫሪነት እየከሰመ ይሄዳል፤ ፉክክር ካለም ለጽድቅ(ለእውነት) ይሆንና ማኀበረሰቡን የከበበው የቁስም ሆነ የመንፈስ  ድህነት ይወገዳል፡፡

ከሴኩላሪዝም ጋር ያለው ትልቁ ግጭት እዚህ ጋር ያለ ይመስለኛል፡፡ ሴኩላሪዝምን የአውሮጳ ስልጣኔ ምንጭ እምነትን ደግሞ የኋላቀርነት ምልክት የማደረግ አባዜ በመኖሩ ከላይ እንዳየነው ካለምንም ፍልስፍናዊ ዳራ (philosophical background) ሴኩላሪዝም ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ የአውሮጳ ስልጣኔ በመሠረቱ ከሴኩላሪዝም ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ የአውሮጳ የስልጣኔ መንፈስ ምን እንደ ሆነ ለማሰረዳት ዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ በፍልስፍና ካነሆለላቸው ሀይድልበርግ (Martin Heidegger) የኒቨርሲቲ እንደተመለሱ የጻፉትን መግለጹ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

“በስነ ምግባር ረገድ የሰውን ጠባይና ችሎታ በመመርመር ከከፍተኛ የሞራል ሐሳብ ጽርየት ደርሰዋል፡፡ በማኀበራዊ ኑሮ ረገድ የእያንዳንዱ መብት እና ተግባር ተጠብቆ ሰው በንጹሕ ተምኔቱ መሠረት በሰላም ተደስቶ የሚኖርበትን የሕግ ውሳኔ አስገኝተዋል፡፡ በሀብት በንብረት በኩል ባነሰ ድካም ብዙ የሥራ ፍሬ በማስገኘታቸው ከራሳቸው አልፈው ለመላው ዓለም የሚተርፉ ሆነዋል፡፡ በሥነ ፍጥረት ዕውቀትና የእርሱ ዘርፍ በሆነው በቴክኖሎጂ ረገድ ከላይ እንደጠቀስነው የሰውን ሕሊና በጣም በማበልጸጋቸው ሰው ከሰውነት ድንበር ለማለፍ ምንም አልቀረው፡፡ በውበት ጥበባት ረገድ እነ ራፉኤልን ዳቢንቺን ሞዛርትን ቤቶሆቨንን ስመ ስማቸው ብቻ ብዙ ይናገራል፡፡ የአውሮጳ ስልጣኔ በአጭሩ ይሄ ነው፡፡ ባጭር ለመናገር ስንል ሳንበድለው አልቀረንም፡፡ ግን በሌላ ዕድል እንክሰዋለን፡፡
. . . .እሊህን የሕሊና ሕግጋት ወይም የስልጣኔ ፍሬዎች ያስገኙት አውሮጳውያን ናቸው፡፡ ግን እስያውያንም አፍሪካውያንም የራሳቸው ለማድረግ ይችላሉ፡፡ ዕውቀት ሲባል በጠቅላላ በማናቸውም ሰው ዘንድ በአምሳለ ዘርዕ ያለ ነገር ነው፡፡ ያንተም የኔም አይደለም፡፡ የሁላችንም ነው፡፡”

እውነታው ይሀ ሆኖ ሳለ የምዕራብ ክርስትና መምህራን ሴኩላሪዝም የእነርሱን ብዙ እሴቶች ገንዘብ በማድረጉ በቀጥታ እምነታችነን ተቀበል ከማለት ይልቅ ወደ ሴኩላሪዝም በማስጠጋት ቀስ በቀስ ወደራሳቸው የእምነት ጎራ ለማስገባት (በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም እንዲሉ ወዳጅ ያደረጉት ሴኩላሪዝም እነርሱ ካበጁለት መስመር በማፈንገጥ ብዙ የምግባር እሴቶቻቸውን እንዲያጡ ሆኗል) ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ይህም ሌሎች እምነቶች የከሸፈውን ሚሺነሪ በዘዴ ቀይረው መጡ እንዴ ብለው እንዲጠይቁም አስገድዷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመጠቃት ስሜት ሳለለ ከምዕራብ የመጣን ነገር ሁሉ እንደ ርኩስ የማየት ዘይቤ አለ፡፡ ይህ በልማት እና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ አሻራው ጥሏል፡፡ ይህንን የመጠቃት ሰሜት በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች እና ምስራቃውያን ክርስቲያኖች (ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስያናትም ከዚህ ይመደባሉ) ይጋሩታል፡፡ ይህም እምነቶቹን ለመጠቀሚያነት ለሚያውሉ ሰዎች ምእመናንን ለእኩይ ዓላማ ለማሰለፍ እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኝ የትኛውም ሙስሊም አሜሪካ እና ምራባውያንን እንዲጠላ ተቀርጿል፡፡ ይህ አል ቃይዳን እና መሰል አሸባሪ (ይቅርታ አሸባሪ በኢትዮጵያ ሳይሆን በምዕራባውን ትርጉሙ ነው የተጠቀምኩበት) አባላትን ለም መሬት እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡

የመላው ዓለምን ችግር የመፍታት አቅም ላይኖረን ይችላል፡፡ ሀገሪቱን ሴኩላር ማድረግ በእምነቶች መካከል ያለን ችግርንም ሆነ እምነቶች አመጡት የሚባለው ችግር ማስቀረት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሀገር በቀል የሆኑ መልካም እሴቶችን በመንከባከብ የብዙሐን ሀገር (pluralistic state) መገንባት እችላለን፡፡ በብዙሐን ሀገር የትኛውም እምነት ሆነ እምነት የለሽ በእኩል የሚታይበት ለጋራ እሴት ሰብኣዊነት በማስቀደም በኅብረት የሚሠራበት ነው፡፡ የተገፋ የእምነት ክፍል ስሌለ (ሁሉንም እምነት ከሚገፋው ሴኩላሪዝም በተቃርኖ) ለአክራሪነት ቦታ አይኖርም፡፡

የኢሕአዴግ መንግስት ግን በጀመረው የጥፋት ጎዳና መቀጠል  መምረጡን የምንረዳው እምነቶችን ከህዝባዊው ምህዳር ማግለሉ አንሶት ተቋማዊ ነጻነታቸውንም ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው፡፡ Jo¨ rg Hausteina* and Terje Østebø  EPRDF’s revolutionary democracy and religious plurality: Islam and Christianity in post-Derg Ethiopia” የሚል ርዕስ በሰጡት ጥናታቸው ኢሕአዴግ በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት ሕዝባዊውን ምሕዳር በማወኩ ምክንያት፣ በእምነቶች መካከል ሀገራዊ መግባባት በማራቁ ምክንያት እምነቶቹ የየራሳቸው የተለያየ የታሪክ ትርክት እንዲኖራቸው ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ለሃይማኖት ጽንፈኝነት መምህራን ለመጽሐፋቸው ርዕስ ለሁከታው መቀስቀሻ እንደ የተቀበረ ድማሚት ያገለግላቸዋል፡፡  

ሌላው ሕሊችንን  ከፍ ከፍ ማድረግ የሚጠበቅብን ጉዳይ የእምነቶችን እሴቶች በተለመለከተ ነው፡፡ ሃይማኖቶች በጊዜ ሒደት ያበለጸጓቸው የራሳቸው እሴቶች አሏቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች በዚያ በእነርሱ ወረዳ ለሌለ ሰው ትርጉም ባይሰጡም ለምእመናን ግን ትልቅ ዋጋ አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን እምነትን የሚያሄሱ ሰዎች ይህንን ግምት ውስጥ አያስገቡም፡፡ ለሌሎች ተነጻጻሪ እሴቶች የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ለእምነቶች እሴት ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሕዝብ በዳሌ መጨፈር፣ ትከሻን ማውረግረግ፣ የአንዳንድ ድምጾች መደጋገም፣ ከትናጋ ጋር የሚጋጩ ድምጾች መብዛት የመሳሰሉ ነገሮች ያን ጎጥ ያስከፋሉ ተብሎ ስለሚታሰብ በእርሱ ላይ ላለመቀለድ ይሞከራል፡፡ ይህ ግን እምነቶች ላይ ሲደረግ አይስተዋልም፡፡ የሀገሪቱ መንግስትም ሴኩላር በመሆኑ ለእነዚህ የሰላም እሴቶች ድጋፍ እና ጥበቃን አያደርግም ይህም ለምንጓጓለት ሐሳብን በመግለጽ የሚያምንም ማኀበረሰብ ግንባታ እንቅፋት ሆኗል፡፡

ይህን ስናደርግ በእኔ እምነት “የክርስቲያን ደሴት” ወይም “ኢስላማዊት በሸሪአ የምትመራ ኢትየጵያን” ከመስበክ ይልቅ የጋራ ቅኝቶችን የሚደግፉና ለአዳዲስ አስተሳሰቦች በር የሚከፍቱ ቤተ እምነቶች ይኖሩናል፡፡ ነገር ግን እኛን የሚወክል ሀገራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ስርዓትን ተባብረን በሰላማዊ መንገድ ካልጠየቅን ምን አልባት በፈጣሪ ለማመን ፍቃድ መጠየቅ ሊኖርብንም ይችላል፡፡ በፈጣሪ መኖር አላምንም ብንል ደግሞ በፓርቲችን ማመን ግዴታህ ነው የሚባልበት ዘመን ሩቅ አይሆንም፡፡ጽሑፌን ሁሉን በሚያስማማው እና ‹‹በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በሌላው አታደርግ›› በሚለው ድንቅ ዓረፍተ ነገር ስዘጋ ልቤን ደስ እያለው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment