Tuesday, October 23, 2012

ዳያስፖራው ጽንፈኛ ወይስ ተስፈኛ?

ከነበረበት ባሕል፣ ተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ፣ የኑሮ ዘዬ ወይም ባጭሩ ከነበረበት አገር (በማንኛውም መልኩ) ለቆ ወደ ሌላ አገር ለተወሰነም ሆነ ላልተወሰነ ጊዜ እየኖረ ያለ ሰው/ማኅበረሰብ ቀድሞ ለነበረበት አገር ሰዎች ‹ዳያስፖራ› ይባላል (dispersed; disaspora /የፈለሰ፤ ፈላሻ እንደማለት)፡፡ አገርኛ ስናደርገው ደግሞ ከኢትዮጵያ ወጥቶ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ የዓለም ክፍል ተበትነው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዳያስፖራ እንላቸዋለን፡፡ ‹‹የዳያስፖራ ፖለቲካ›› ስንል ደግሞ ዳያስፖራ በሆነው ማኅበረሰባችን የሚንፀባረቀውን ፖለቲካዊ አቋም፣ አመለካከት እና እንቅስቃሴን ማለታችን ነው፡፡ በተለይ አሁን አሁን ስለአገራችን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ‹ዳያስፖራው ምን አለ?› የሚለው ጥያቄ የማይሻር ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ ሆኖም ደግሞ በጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አይቶ ከኢትዮጵያ ውጪ በሚኖር ሰው የተሰጠ መሆኑን እና አለመሆኑን ለማወቅ ቀላል እየሆነ እንደመጣ የሚከራከሩም አሉ፡፡ እነዚህም፡-


  •  በተለምዶም የአስተያየቱን ጽንፉን ተመልክቶ ‹የዲያስፖራ ፖለቲካ›› የሚባል ስያሜ እየተሰጠው ይገኛል፡፡ የ‹የዳያስፖራ ፖለቲካ› ውስጥ በብዛት ጽንፉ ወዲህ ወይም ወዲያ ይሆን ይሆናል እንጂ ፅንፍ መያዙ አይቀርም የሚለው እምነት የብዙዎች እየሆነ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሁለቱንም ጽንፎች አዳርሰዋል በሚል ሰለሞን ተካልኝ በማስረጃነት ያነሳሉ፡፡
  •  ዳያስፖራው እኛ (በአገር ውስጥ ነዋሪዎች) የማናውቀውን የዴሞክራሲ ጣዕም የሚያውቅ፣ እኛ የሌለን የፖለቲካ ምኅዳር ያለው፣ ገሚሱ ኑሮው ሞልቶለት የወገኑ ጉዳይ ከሩቅ የሚቆረቁረው የለውጥ ተስፈኛ እንጂ ጽንፈኛ ሊባል አይገባውም የሚሉት ደግሞ በሌላ ወገን ይገኛሉ፡፡

በርግጥም ጽንፍ የያዙ እና ማንኛውንም ዓይነት በአገራችን ውስጥ የሚታዩ እንቅስቃዎችን ጥቃቅን ጉድለቶችን እየነቀሱ በማውጣት፣ በማጉላት እና ጠንካራ ትችት ማቅረብ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች መለያ እየሆነ ነው እንዲያውም ዋነኛ ዓላማቸው መቃወም እንጂ ለለውጥ መትጋት አይደለም ቢባልም፣ የእውነተኛ ለውጥ መንገድን ለማምጣት ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን እየፈሰሱ ያሉትም ‹‹ከኑግ የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ›› በሚል ሰበብ አብረው እየተጨፈለቁ ነው፡፡ ጉዳዩን በኮንትሮባንድ ውስጥ ለውስጥ ከማስኬድ ይልቅ በመወያየት የሚበጀውን አካሔድ በጽንፍ/ተስፋ ቅጥያ ሳንከፋፈል እንድንሄድበት ማድረግ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡  

ምንም እንኳን እነርሱ ከሌሉበት (አስተያየታቸውን ካልሰጡበት) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነፍስ የሌለው በድን ይሆናል የምንላቸው ዳያስፖራዎች ቢኖሩም፣ ይህ ጽሑፍ ግን ባመዛኙ ‹‹ስንዴውን ከገለባ ለመለየት›› ሲባል ሊወቀሱ የሚገባቸውን መውቀስ ላይ ያተኩራል፡፡ ሊወቀሱ የሚገባቸው የምንላቸው እነዚህን ያካትታል፡-
·         ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ የግል መጠቀሚያ (መተዳደሪያ) ከማድረግ ውጪ ፖለቲካ ያለ ለማይመስላቸው፣
·         በተለያዩ አደጋዎች የደረሰባቸውን አደጋ መንግስት እንዳደረሰባቸው በማስመሰል የሐሰት ትዝብት በመፍጠር ላይ ላሉ፣
·         ለምክንያት (causes) ሳይሆን ለጥገኝነት መጠየቂያ ሲባል ብቻ የመሪዎችን መምጣት ተከትሎ የሚደረጉ ሰልፎች መብዛት፣
·         ይህንና ይህን መሰሎች ችግሮች እያሉባቸው ጉዳዩን እንዳይወራ ለማነወር እየጣሩ ያሉ ቀጥተኛ ተጠያቂ ዳያስፖራዎችን ነውሩን ለመጠየቅ ነው፡፡

የአንድ “ተራ” ዳያስፖራ አመለካከት እዚህ አገር ካለ ፖለቲከኛ ይልቅ (ዕድሜ ለቴክኖሎጂ እና ሐሳብን ለመግለጽ ነጻነት) ሕዝቡ ጓዳ የመግባት ዕድል ያለው እየሆነ ነው፤ ስለሆነም የጎበጠ የሚመስለንን ለማቅናት እና የተቃናውን ደግሞ ለመጠናከር መወያያ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለውይይት እንዲያመቸንም አንድ በሚያደርጓቸው ባሕርያት እየከፋፈልን እንመለከታቸዋለን፡-

ጫና ያሳደዳቸው

የአገራችን ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሚጽፉ እና የተበደሉ ሕዝቦችን ድምፅ ባገኙት አጋጣሚ ሲያሰሙ የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ጸሐፊዎች እና የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾች እዚህ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አገር ውስጥ እያሉ በሠሯቸው ሥራዎች ዕውቅናን ያተረፉና የሕዝብን ጆሮ አግኝተው የነበሩ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሕዝቦቻቸው ልሳን በመሆናቸው ብቻ በስልክ ከሚደርሳቸው ማስፈራሪያ እና ዛቻ አንስቶ ለአካላዊ ጉዳት የመዳረግ፣ የመንገላታት እና የመታሰር ዕጣ ሊደርስባቸው እንደሚችሉ ጥቁምታዎች ወይም ምልክቶች በሚያገኙበት ጊዜ በተለያየ ምክንያት አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ይወስናሉ፡፡

እነዚህኞቹን በተመለከተ አገር ውስጥም ባሉ ሆነ ቀድሞውንም በተሰደዱ ሰዎች ‹‹መሰደዳቸው አግባብ አይደለም፤ እዚሁ ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ የሚደርስባቸውን ሁሉ ማለትም እስሩንም፣ እንግልቱንም፣ፍትሕ ማጣቱንም ከሕዝባቸው ጋር እንደጀመሩት መጨረስ ነበረባቸው›› የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ያሉትን ያክል ‹‹የለም፤ እነዚህ ሰዎች እስር ቤት ገብተው ለራሳቸውም ከሚንገላቱ፣ ወጥተው የቻሉትን ያህል ሕዝባቸውን በአቋራጭ ቢታገሉለት፤ በዚያውም ለዓለም አገር ውስጥ ያለውን ችግር ቢያስረዱ ይሻላል›› የሚሉትም ብዙ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ከሩቅ ሆነው በላፕቶፕ የሚታገሉት ሰዎች የመጀመሪያውን ሲናገሩ አገር ውስጥ ካሉት ይልቅ የበለጠ ያስከፋል፡፡ ለዚያም ነው ‹‹እነርሱ ሊኖሩት ያልፈቀዱትን ሌሎች እንዲኖሩ ግፊት ያደርጋሉ›› በሚል በጽንፈኝነት የሚከሰሱት፡፡

በተረፈ ግን ብዙዎቹ በዚህ መንገድ ተሰደው የወጡ ጋዜጠኞችን እንደምሳሌ ብንወስዳቸው ባመዛኙ ከጽንፈኝነ የፀዱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች፣ የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ፣ የፍትሑ አበበ ቶላ፣ እና እንደ አርጋው አሽኔ ያሉ ነጠላ ስደተኞች፣ ከተሰደዱ ወዲህ በተለያዩ አምባዎች እና ማኅበራዊ አውታሮች ከሚያሰፍሯቸው ጽሑፎች ውስጥ መረዳት እንደምንችለው፣ አንደኛ በስደት ሆነውም ብዙዎቹ አገር ውስጥ ሆነው የነበራቸውን አቋም ቀጥለውበታል፤ ሁለተኛ ከተሰደዱ ወዲህ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን በመከታተል ራሳቸውን ከአገር ውስጥ መረጃዎች አላራቁም፣ ሦስተኛ የአገር ውስጥ እውነታዎችን በተዛባ ሁኔታ አይረዱም፣ ወይም ለግል ጥቅማቸው መጠቀሚያነት ሲረባረቡበት አልታዩም፣ አራተኛ እነዚሁ ሰዎች የስርዓት ለውጥ ከመጣ ተመልሰው መጥተው እኛኑ ነውና ‹‹ጽንፈኛ›› በሚለው አብረን ልንፈርጃቸው አይገባም፡፡

የዳያስፖራ ተቃዋሚ ፓርቲ/ቡድን አመራሮችና እና አባላት

በርካታ የቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ተሰድደዋል፡፡ በተለይም የፈረሰው የቅንጅት አባላት ከነበሩት ውስጥ ጥቂት የማይባሉት በስደት የየራሳቸውን ቡድን እና ፓርቲ መስርተዋል፤ ከነዚህ ውስጥ እንደምሳሌ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት ሰባት አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኦባንግ ሜቶ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ፣ የዶ/ር ፍስሐ እሸቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤትም ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው፡፡ እዚያው ለረዥም ዓመታት ነዋሪ የነበሩ፣ በተለይም በደርግ ዘመን የተሰደዱ በርካታ የኢሕአፓ ሰዎችም ፖለቲካው ውስጥ በግልም በቡድንም አይጠፉም፡፡

እነዚህንም በተመለከተ ሁለት አመለካከቶች አሉ፤ ምንም አልሠሩም/አይሠሩም እና ያቅማቸውን እየሠሩ ነው የሚሉ፡፡ ነገሮችን በምሳሌ መመልከቱ እየሠሩ ያሉትን እና ያላግባብ ስም እየፈሱ ያሉትን ለመለየት እና ወደፊትም እየጠየቅን ምስጋናችንን/ድጋፋችንን እንድንችር ያደርገናል፡፡ እነሆ ምሳሌዎቹ፡-


  • በገዢው ፓርቲ በአሸባሪነት የተፈረጀው እና ግዝፈቱ እና አስፈሪነቱ በቴሌቪዥን የሚደሰኮርለት ግንቦት ሰባት እስከአሁን ድረስ የሠራው ሥራም ሆነ ያሸበረው ሽብር ምን እንደሆነ ቢጠየቅ፣ ተቃውሟቸውን በይፋ ለሚገልፁ ሰዎች ‹‹ባጅ›› በመሆን ለመንግስት ከማገልገል ውጪ ይሄ ነው የሚል መልስ  ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት መነሻዬ ያለውን ለኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ የተዘጋጀ የሽግግር መንግስት የማዋቀር ሥራውን ትቶ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሞት ቀን ላይ (እንደ መረጃ ሰጪ ሚዲያ) የጦፈ ክርክር በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን ስቶ ታይቷል፡፡ ሲመሠረት በሁለት ወራት ውስጥ፣ የአቶ መለስ ኅልፈት ከተሰማ ወዲህ ደግሞ በሁለት ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ ብሎ ቃል የገባው ይሄው የሽግግር መንግስት ቃሉ ከተግባሩ የፈጠነ መሆኑ ሌሎች የዳያስፖራ ቡድኖችንም ሆነ እራሱን ከተኣማኒነት ዝርዝር ውስጥ በዚህ መንገድ እንዳያወጣ ያሰጋል፡፡
  • EAC (Ethiopian Americans Council) በመባል የሚታወቀው ቡድን በተቃራኒው፣ በተቃራኒው ለኦባማ ደብዳቤ ከመጻፍ አንስቶ፣ በልማት ሰበብ የሚገኙ የእርዳታ ገንዘቦች ነጻነትን ማፈኛ እንዳይወሉ የማንቂያ ደውል ለአሜሪካ መንግስት በመደወል እየሰሩ ያሉት የሚበረታታ ነው፡፡ የጋራ ንቅናቄ የተባለውም ቡድን በተለይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ጽሑፎችን በማውጣት ይታወቃል፤ አሁንም እንኳን በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለውጥን የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ አሰራጭቷል፡፡ የHR2003 (የሰብኣዊ መብት ጉዳይን ያስቀደመ መመሪያ) የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ እንዲጥል አሊያም እርዳታ እንዲያግድ የሚያደርገውን ዶሴ በማርቀቅ እና እንዲፀድቅ እና አገር ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ጫፍ ደርሶ የነበረ ትግል የታገሉትም የዳያስፖራ ቡድኖች ናቸው፡፡ ይህንን በምክንያት ከመሟገት እና ለውጥን ከመወትወት ወይም የ‹‹አራማጅነት›› ሚና የተሻለ የሚሠሩ እና ሊበረታቱ የሚገባቸው አሉ፡፡


በተለያየ የፓለቲካ ግብ ውስጥ የሚንቃቀሱ የፓለቲካ ቡድኖች ምንም እንኳን የፓለቲካ አቋማቸውን በሚደግፍ መልኩ መረጃዎችን መተንተናቸው የሚያስቀወቅሳቸው ባይሆንም፣ ቡድኖቹ ግልጽ ባልሆነ የፖለቲካ ዓላማ እና የሕዝቡን ነባራዊ ፍላጎት እና ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባላስገባ እንቅስቃሴ የሚሰጡት ትንታኔ አቅጣጫ ወይም መረጃ አምታች እና አወናባጅ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር አገር ውስጥ ያሉትም የፖለቲካ ቡድኖች ቢሆንም በዳያስፖራዎቹ ይጋነናል የሚል እምነት አለን፡፡ ውሸት ይነግሩናል ባንልም ከነርሱ ጋር የሚያሟግተንን እውነት ሊደብቁን፣ ወይም ለነሱ ፍላጎት የሚያመዝነውን ብቻ ሊያስተጋቡልን ይችላሉ የሚለው ስጋት አገር ውስጥ ባለው ወገን ዘንድ የሚፈጠረውም ይሄን ጊዜ ነው፡፡

ለመኖሪያ ፈቃድ ሲባል…?

ለትምህርት፣ ለስልጠና፣ ለወርክሾፕ፣ ለስብሰባ፣ ለጉብኝት እና በመሳሰሉ ምክንያቶች ከአገር ወጥተው በዚያው ቀልጠው የሚቀሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች አሁን አሁን እንደፋሽን የሚጠቀሙበት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቅን ነው፡፡ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎቹን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ፤ በሚሄዱበት አገር የፖለቲካ ጥገኝነት ሊያሰጣቸው የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት አገር ውስጥ በነበሩበት ወቅት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መታወቂያ ለማግኘት መጣር፣ መንግስትን በመተቸት ከሚታወቁ ሰዎች ጋር ፎቶ መነሳት እና መንግስትን የሚቃወሙ ጽሑፎችን በግል የሕትመት ሚዲያዎች በስማቸው ማውጣትን በምሳሌ ማንሳት እንችላለን፡፡ አጋጣሚውን አግኝተው ከዚህ አገር በሚወጡበት ወቅት ቀድመው ያዘጋጇቸውን ምክንያቶች እንደማስረጃ በማቅረብ የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በሁለተኛው ክፍል የምናገኛቸው ደግሞ ከላይ በጠቀስናቸው ባንዱ ምክንያት ከአገር የመውጣቱን አጋጣሚ ድንገት ያገኙና  ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ የሚወጡ ናቸው፡፡ ካገር ሲወጡ እዛው የመቅረትን ጉዳይ በአዕምሮአቸው የነበራቸው ቢኖሩም የመመለስ ዕቅድ የነበራቸው እና እዛው ባሉበት ሐሳባቸውን ቀይረው ለመቅረት የወሰኑም ይገኙበታል፡፡ 

ሁለቱንም ቡድኖች የሚያመሳስላቸው በሄዱበት ለመቅረት ያላቸው ፍላጎት፣ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውና የሐሰት መረጃዎችን ለሚመለከተው ክፍል ማቅረባቸው ነው፡፡ በመጀመሪያው ቡድን ያሉት ቀደም ብለው በጉዳዩ ላይ ተዘጋጅተውበት በመውጣታቸው እንደሄዱ ማመልከቻቸውን በማስገባት  ባጭር ጊዜ ውስጥም ሊሳካላቸው የሚችል ሲሆን በሁለተኛው ቡድን ያሉት ግን የሐሰት መረጃዎችን ማሰባሰብ የሚጀምሩትና የሚያገኙት ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንዳንድ ጊዜም የቪዛቸው ጊዜ ወደማለቁ አካባቢ ወይም ካለቀ በኋላ ስለሚሆን ለብዙ መጨናነቅ፣ ወጪና እንግልት ይዳረጋሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ መኖሪያ ፈቃድ የማግኘታቸውና ያለማግኘታቸው ጉዳይ እኩል፣ እኩል ነው፡፡

እንደነዚህ ዓይነት “ዳያስፖራዎች” (በትዕምርተ ጥቅስ) ብዙዎቹ ስለአገራቸው የፖለቲካ ታሪክ እና ወቅታዊ ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ መረጃ ባይኖራቸውም፣ መንግስትን የሚቃወም የማንኛውንም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ሐሳብ ያስተጋባሉ፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ፌስቡክ እና ትዊተርን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ አውታሮች፣ ጦማሮችን እና ድረገጾችን እንደመሳሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ባለስልጣናት ለሥራም ሆነ ለስብሰባ እነሱ ወዳሉበት ቦታ በሚመጡበት ጊዜም - ነባር፣ በእውነተኛ ተቃውሞ ጦስ ተሰድደው የወጡ የዳያስፖራ አራማጆች በሚያስባብሯቸው - ተቃውሞዎች ላይ መታደም እና በቦታው መገኘታቸውን የሚያሳይ መረጃ መያዝ ተቀዳሚ ሥራቸው ነው፡፡

በተጨማሪም በአገራችን የሚካሄዱ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶችን በመቃወም የሚደረጉ ሰልፎችና አላግባብ የታሰሩ ዜጎችን ለማስታወስ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይም ቁጥር አንድ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ምናልባትም ከፕሮግራሙ ርዕስ በዘለለ የተዘጋጀበትን ምክንያት እና ዓላማ ላያውቁ ይችላሉ፡፡ ባጭሩ በዚህ ምድብ የሚገኙ “ዳያስፖራዎች” አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል የኔ የሚሉት ፖለቲካዊ አቋምም ሆነ አመለካከት የሌላቸው ሲሆን ዋነኛ ሥራቸው በመንግስት ላይ የሚሰነዘርን ማንኛውም ዓይነት ተቃውሞ ባገኙት አጋጣሚ ሲያስተጋቡ መታየት ወይም መሰማት ነው፡፡ እነዚህ ጠቅላላውን የ‹ዳያስፖራ ፖለቲካ› ውጤታማነት እንዴት እንደሚያውኩት በሚከተሉት ምሳሌዎች መረዳት ይቻላል፡-


  • የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች ላይ የሚሳተፉ እነዚህ ለፖለቲካው ጤንኝነት ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች ‹‹ጥገኝነት›› ፈላጊዎች ግንባር ቀደም እና አርማ ተሸካሚ ሆነው በፎቶ እና ቪዲዮ ማኅበራዊ አውታሮች ላይ በአጋጣሚ የሚመለከቱ እና ግለሰቦቹን የሚያውቋቸው የአገር ቤት ሰዎች ጠቅላላ የዳያስፖራውን እንቅስቃሴ በግለሰቦቹ ዓይን የመዳኘት እና በኢቴቪ ፕሮፓጋንዳ ‹‹ጥገኝነት ለመጠየቅ ሲሉ›› የሚለውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ስለሚሆን፣
  • ግለሰቦቹ የጥገኝነት ወረቀታቸውን ካገኙ በኋላ ተመልሰው ትግሉን ስለማይቀጥሉበት፣ መጣ ቅርት የሚሉ አራማጆችን መመልከቱ/መከታተሉ ተስፋ ስለሚያስቆርጥ፣
  • ግለሰቦቹ ወረቀቱን እስከሚያገኙ ድረስ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማጉላት እና ተቃዋሚነታቸውን ለማሳመን ጽንፍ ድረስ ስለሚጓዙ የጠቅላላውን ዳያስፖራ መልክ በአንድ ላይ የማጉደፍ ኃይል አላቸው፡፡

እነዚህን ግለሰቦች በጥንቃቄ መጠቀም ያልቻለ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ወይም ዝግጅት አስተባባሪ፣ ወይም በጥንቃቄ መከታተል ያልቻለ የአገር ውስጥ ነዋሪ መስመሩን የሳተ ግንዛቤ ስለዳያስፖራዎቻችንም ሆነ ስለአጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ያኖራል፡፡

የዳያስፖራ ሚዲያዎች

በተለይም በፖለቲካው ዙሪያ መረጃ እና ትንታኔዎችን የሚያቀርቡ በርካታ፣ ባብዛኛው ኢንተርኔት ላይ ጥገኛ የሆኑ መገናኛ ብዙሐን አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ በድረገጽ የሚሰሩት እነኢትዮሚዲያ፣ ዘሐበሻ፣ ኢትዮጵያንሪቪው፣… እና አሁን እየጎሉ ከመጡት ውስጥ ደግሞ ጎልጉል ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙሐን በተለይ ገዢው ፓርቲን በሚቃወሙ መጣጥፎች ላይ ምንም መመዘኛ የሌላቸው እስኪመስል ድረስ፣በአገራዊ ስነምግባራዊ እሴቶች የሚያስገምቱ ስድቦችን በማስተናገድ ጭምር ይታወቃሉ፡፡ ከነርሱ በተቃራኒው የቆሙት እና የገዢው ፓርቲን በማንቆለጳጰስ ሥራ ተጠምደው፣ ዓላማቸው ‹‹አማራጭ ሚዲያ›› መሆን ይሁን ወይም ካድሬነት የማይለዩት እነአይጋፎረም፣ ኢትዮጵያፈርስት እና ትግራይኦንላይን የመሳሰሉት ድረገጾች ደግሞ ተቃዋሚውን እስካዋረደላቸው ድረስ የሚያሰራጩት መረጃ እውነት ይሁን ሐሰት እንኳን ለማጣራት አይጨነቁም፡፡

በዚህ መሐል የሚዲያዎቹን ማንነት እና እሴት የማያውቀው አንባቢ በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል፡፡ አሁን በተቃዋሚ ወገን የምንመድባቸው በሙሉ በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ በመታገዳቸው በፊት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጎብኚ የነበራቸው እነናዝሬት እና ኢትዮጵያንሪቪው ከዝርዝሩ ወጥተው፣ ከፍተኛ ተነባቢነት ያላቸው እነትግራይኦንላይን መሆናቸውን የአሌክሳ ዌብ ትራፊኪንግ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ የታገዱትን ገጾች ዜናዎች በዚህም ሆነ በዚያ እያሉ (በተለይ በማኅበራዊ አውታሮች) በኩል የሚያገኙት ብዙሐን ናቸው፡፡

ከዚህ በፊት የአገር ውስጥ ጋዜጦች መለስ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው ብለው በማለታቸው ይቅርታ እንዲጠይቁን ወትውተን እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዳያስፖራ መገናኛ ብዙሐን መካከልም፣ በተለይ ኢትዮጵያንሪቪው ብዙ ባለስልጣናትን እና ባለሀብቶች ሳይቀር ሞተዋል፣ ተሰደዋል የሚሉ ዜናዎችን ጽፎ አንብበን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስህተት መሆኑን ሰምተናል፡፡ በተመሳሳይ እነርሱም ይቅርታቸው ይገባን ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጽሑፍ ይህንን ርእስ ለማንሳት ባያስብም የተአማኒታቸውን ነገር ግን ችላ ማለት አይገባም፡፡፡ 
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንም እዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታል፡፡ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዳያስፖራ እኩያው ነው መባል ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ በፅንፈኛነት ስሙ መነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሱት፣ ሙያዊ ስነምግባር (professional ethics) ላይ እምብዛም አለመጠንቀቃቸው፣ ከዜና እና ዜና ነክ ትንታኔዎች በላይ አንጀት አርስ ፕሮግራሞችን አለመሥራታቸው፣ ከአገር ቤት ጋር የሚገናኙ ጥቃቅን የሁከት ዜናዎችን ማጋነናቸው ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ድክመቶች ናቸው፡፡ አማራጭ መገናኛ ብዙሐን በሌለበት ኢሳትን አለማመን ቢከብድም፣ ኢሳት ይህንን ግዳጁን በሙሉ ኃላፊነት እንዲወጣ እና በሙሉ ልብ እንዲታመን ገና ብዙ ይጠበቅበታል፡፡

እርግጥ ነው፣ እነዚህ መገናኛ ብዙሐን እዚህ አገር የታፈኑ (የተነወሩ) በርካታ እውነታዎችን ለሕዝቡ በቻሉት መንገድ ሁሉ ለማድረስ በስደት ሕይወታቸው መፍጨርጨራቸው ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ቢሆንም ጥረታቸው ዋጋ እንዲኖረው ተአማኒነት ያላቸውን መረጃዎች ለማቅረብ መድከም አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ስናነባቸው በጥርጣሬ እንዲሆን ልንገደድ እንችላለን፡፡

የዳያስፖራ ምሁራን እና አራማጆች

በኢትዮጵያ ያሉ ምሁራን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚያስደፍር ሁኔታ ዝምታን በመረጡበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ምሁራዊ እይታ እንዳያጣ ትንሽ የረዱት የዳያስፖራ ምሁራን እና ሌሎችም ለነፃነት ተቆርቋሪ ስደተኛ አራማጆች ናቸው፡፡ እነአለማየሁ ኃይለማርያም፣ እነመሳይ ከበደ፣ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎችም ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡

የዳያስፖራ ምሁራን በተለያዩ ከላይ በጠቀስናቸው እና ሌሎችም መገናኛ ብዙሐን የሚያቀርቧቸው ትንታኔዎች ምንም እንኳን በአብዛኛው ወደሚደግፉት ቡድን ርዕዮት ያመዝናሉ የሚል ሐሜት ቢያጋጥማቸውም በዳያስፖራው ማኅበረሰብ ተአማኒነት ያለው መረጃ በመስጠት የተሻሉ ናቸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ ብዙ ጊዜ መከራከሪያ ነጥቦቻቸው እውነታዎች እና ሳይንሳዊ ርዕዮተ ዓለሞች መሆናቸው ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ምሁራን የሚያቀርቧቸው ጽሑፎች እንደሌሎቹ አጫጭር መጣጥፎች ከስድብ ይልቅ አመክንዮ ይበዛባቸዋል፡፡ ስለዚህ የምሁራኑን ትንታኔ እያነበቡ የራስን ውሳኔ መውሰዱ ጠቃሚ እንደሚሆን መደምደም ይቻላል፡፡

በጥቅሉ፣ ፖለቲካ ቀመስ የሆኑ ጽሑፎችን የምናነበው ወይም የምንጽፈው መረጃ ለመለዋወጥ ያክል ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ለውጥ ጉጉት ስላለን ነው፡፡ ቢሆንም ግን በአገር ውስጥም ሆነ በዳያስፖራው ውስጥ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ግለሰባዊ አጀንዳ ያላቸውም ሰዎች አሉ፡፡ ይህ በተለይ በኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ላይ ያተኮረው ጽሑፋችን ዓላማም፣ የዳያስፖራ ፖለቲካ ውስጥ ‹‹ማን፣ ምን እና ለምን›› የሚለውን በማገናዘብ ሁሉንም በጽንፈኝነት ወይም በተቃራኒው የዋሕነት ብቻ ሳይቀበል እንዲመረምር በማድረግ ማኅበራዊ ተዋስኦን ማበረታት ነው፡፡

በተለይ በጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት በተነሱ አስተያየቶች ዳያስፖራው ለሚታማበት ጽንፈኝነት የራሳቸውን ምክንያት የሚዘረዝሩ አሉ፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥ እኛ (በአገር ውስጥ ነዋሪዎች) በባሕላዊ አስተሳሰቦች እና በዴሞክራሲ መብት እጦት የታፈነ ማኅበረሰብ ውስጥ የነጻነትን ትክክለኛ ትርጉም እና ጣዕም በአግባቡ ማጣጣም ባለመቻላችን የመጣ ክፍተት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ በተጨማሪም፣ አንዳንዴ የነጻነትን ትክክለኛ ጣዕም ያጣጣሙ ስደተኞች ያን ዓይነቱ ለውጥ ወደአገር ቤት በተቻለ ፍጥነት እንዲመጣ ማሰባቸውም ለአንዳንድ ስህተቶች እንደሚዳርጋቸው ይታመናል፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ እዚህም ያለነው ወይም እዚያ ያሉት የምንታገለው ለጋራ ለውጥ ስለሆነ እነርሱም እኛን፣ እኛም እነርሱን የምናደምጥበት መድረክ እና ቋንቋ ያስፈልገናል፡፡

No comments:

Post a Comment