በታምራት
ሐዘን አጥንት ሲደርስ ደግ አይደለም:: ሰውም እግዜሩም አይወዱትም:: ለአገርም አይጠቅምም ለጠላትም ደስ አይበለው:: እንዲህ አገር ነቅሎ ሙሾውን ሲያስነካው ተዉ እሚል ይጥፋ? ያ ምስኪን ትዝ አለኝ... ጃንሜዳ ጋር ሞቶ እሚቀብረው ሲያጣ አዝኖ ወደቤቱ የተመለሰው ሃሃሃሃ…:: ለማንኛውም ሕገ መንግስቱ እንደሚለው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያርፍ ወይም በሞት ሲለይ አንድ ቀን ብሔራዊ ሃዘን ይታወጃል:: እንደ በረከት ስምኦን ቢሮ አሥራ አራት ቀን መሆኑ ነው:: [በየቀኑ የሚጣስን ሕገመንግስት አንስቶ መከራከሩ ፅንፈኛ ያስብለኛል ስለዚህ ይለፈኝ] በዛ ላይ ዋሽንት አለ [ለአንዳንዶች vuvusela ሆኖባቸዋል]:: ስለዚህም እንደ አንድ ሐዘናችንን ለማስረሳት እንደሚጥር ልማታዊ አፅናኝ በለቅሶው አካባቢ ከተሰሙት ንግግሮች ጀምሮ ወሬው እንዳመራን ውል አልባ ጨዋታ ብንጨዋወትስ...
ሰሞኑን እንደ ጆሮ ስቃዩን ያየ (ሰደቃውን የበላ) የለም... ጆሮ ሆይ አድናቂህ ነኝ!
የልማታዊው በረንዳ አዳሪ አስተያየት፣ "አባታችንን ተማምነን ነው በረንዳ የምናድረው" የሚለው አስገራሚ ለቅሶ የልማታዊውን እስረኛ ሰሜ ባላገሩን ቃለ ምልልስ ያስታውሰናል፤ "በመታሰሬ በጣም ደስተኛ ነኝ መንግስቴንም አመሰግነዋለው" ነበር ያለው ሰሜ ከእስር ቤት እንደወጣ [ሰሜ ሮሚዎን ሆኖ ትያትር እንደተጫወተ ላስታውስ]፡፡ ሰሜን ተንጠላጥለን ወደ ሁዋላ ስንሄድ "ታንክ ተደግፎ መጽሐፍ ያነብ ነበር" ያለው የኢትዮፈርስት ዌብሳይት አዘጋጅ ቤን፣ "HR 2003ን ከማፅደቃቸው በፊት የአሜሪካን ሴናተሮች ጉዳዩን መላልሰው እንዲያዩት የመከሩት የብቸና ገበሬዎች፣ የአሜሪካንን ኢምፔርያሊዝም ከተሳሳተ ርዕዮተ-ዓለሙ እንዲታረም ያስጠነቀቁት የቦረና አርብቶ አደሮች" ...