Thursday, October 4, 2012

‹‹ሕዝብ›› ምንድን ነው?በክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሙሴ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል፡፡ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፆች ቅኝ ተገዢነት ነፃ ያወጣ መሲህ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በሙሴ ላይ ያፈነግጥ እንደነበር ዘጸአት፣ ምዕራፍ 32 (ቁጥር 1 - 4) ይተርክልናል፡-

“ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። አሮንም፣ በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው።”

በ1997 ተቃዋሚዎችን የመረጠ ሕዝብ በ2002 ገዢውን ፓርቲ ይመርጣል፣ በ2008 ለኦባማ ራሱን የሳተ ሕዝብ በ2012 ለራምኒ ይዘምራል፡፡ ይህ ሕዝብ ምን ዓይነት ፍቺ ይገኝለታል? በዚያው በምርጫ 97 ሚያዝያ 29 ኢሕአዴግን በመደገፍ ‹‹ማዕበል›› ለመሰኘት የበቃ ሕዝብ መስቀል አደባባይ ወጣ፤ በማግስቱ ሚያዝያ 30 ከዋዜማው እጥፍ የበዛ (‹‹ሱናሚ›› የተሰኘ) ሕዝብ ወጣ፤ የቱ ነው ሕዝብን በትክክል የሚገልፀው?

ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ሕዝብ›› የሚለውን ቃል ሲፈታው ‹‹በአንድ አገር፣ ከተማ፣ ክልል፣ ገጠር ውስጥ የሚኖር ጠቅላላ የሰዎች ቁጥር፣ ብዛት›› ይለዋል፡፡ በርግጥ ይህ መዝገበ ቃላት እንደሚለው ‹‹ሕዝብ›› ቁጥር ብቻ ነው ወይስ ሌላ ትርጉም ይኖረው ይሆን? በየፈርጁ እንመለከተዋለን፡፡

ሕዝብ ሕገመንግስቱ ውስጥ

የኢፌዲሪ ሕገመንግስት (1987) በመግቢያው ላይ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡-›› ብሎ ይጀምራል፡፡ አካሔዱ ከላይ - ሁሉንም ብሐሮች ካቀፈው ስብስብ (set) ወደታች - ነጠላ ብሔር/ብሔረሰብ (subset) ስለሚወርድ ‹‹ሕዝቦች›› የሚለውን ‹‹የተለያየ የዘር ሐረግ ያላቸው ሰዎች ስብስብ›› ብለን ልንፈታው እንድንዳዳ ያደርገናል፡፡ ግን ደግሞ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ዕውቀታችንን ስናስታውስ ሕዝቦች የሚባሉት የብሔር ዕውቅና ያላገኙ፣ የአንድ ቋንቋ እና ባሕል ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይሄ ትርጉም የትም ስለማያደርሰን ሌላ የ‹‹ሕዝብ›› ትርጓሜ ፍለጋ እንጓዛለን፡፡

የሕገመንግስቱ ፈጣሪ ኢሕአዴግ ነውና፣ በግንባሩ ስያሜ ውስጥ ያለው ሕዝቦች ማንን እንደሚወክል እንጠይቅ፡፡ ግንባሩ የብሔር ፓርቲዎች ስብስብ ስለሆነ ብዙ ብሔሮችን በአንድነት ‹‹ሕዝቦች›› ብሏል ስንል ደግሞ እላይ ከደረስንበት ድምዳሜ የተለየ ትርጉም እናገኛለን፡፡

ሕዝብ በቁጥር

ነገሩን በምሳሌ እንጀምረው፤ ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን መረጠ›› ሲባል ምን ማለት ነው? በ2000ው የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ከ1.88 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፖለቲካዊ ምርጫ ለመምረጥ ዕድሜያቸው ይፈቅድላቸዋል፡፡ ነገር ግን ድምጻቸውን የሰጡት 1.04 ሚሊዮን ያክሉ ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 0.56 ሚሊዮኖቹ ብቻ ናቸው ለኢሕአዴግ ድምጻቸውን የሰጡት (ማለትም ዕድሜያቸው ከደረሱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አንፃር 30% ያክሉ ብቻ)፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን መረጠ ይባላል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት መሪር ሐዘን አዘነ፣ መተኪያ እንደሌላቸውም ተናገረ›› ሲባልስ የትኛውን ሕዝብ ነው? ስንት ያክሉን ሕዝብ ነው?

ሕዝብ በአስተያየት እና ፍርድ አሰጣጥ

‹‹ሕዝብ ይፈርዳል፤›› እርግጥ ነው ሕዝብ ብዙ ነገሮችን አንድ ላይ አመሳክሮ ይፈርዳል፣ የፍርድ ባለቤትም ስለሆነ ፍርዱ ቢወደድም ቢጠላም ይፀድቃል፡፡ ሕዝቦች ሶቅራጠስን፣ እየሱስን እና ሌሎችንም ያለዘመናቸው የተፈጠሩ ነብዮችን እንደተሳሳቱ ፈርዶ አይቀጡ ቅጣት አስቀጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ፍርድ ሁሌም ፍትሐዊ ነው ማለት ይቻል ይሆን?

ሀ). ሕዝብ for dummies

ሕዝብን እና ፍርድ አሰጣጡን፣ ወይም ውሳኔ አስተላለፉን በገደምዳሜው ከተቋረ ውሃ ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ አንድ የውሃ ኩሬ ቦይ ከተቀደደለት፣ መጨረሻው ገደልም ይሁን ግድብ፣ በየትም በኩል ይቀደድለት በየትም ዝም ብሎ ይፈሳል፡፡ አንድ ኩሬ ውስጥ የተቋረ ውሃ የኬሚካል ጠብታ ብናፈስበት፣ ኬሚካሉ መርዝም ይሁን መድሃኒት ወዲያው ይቀላቀላል፡፡ ቅልቅሉም እንደኬሚካሉ ብዛት በውሃው ውስጥ ሰርፆ ይቀራል፡፡

ሕዝብም እንዲሁ ነው፡፡ የመገቡትን ሐሳብ አዳኝም ይሁን አጥፊ ይቀበላል፡፡ የከፈቱለትን መንገድ መጨረሻው ይመርም አይመር ይከተላል፡፡

ግለሰቦች የተሰጣቸውን ሐሳብ መመርመር ሲጀምሩ፣ ወይም ‹‹ለምን?›› ብለው መጠየቅ ሲጀምሩ ከ‹‹ሕዝብ›› ተራ ይወጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጠያቂ ግለሰቦች በተቀደደላቸው በመፍሰስ ፈንታ ቦይ ቀዳጅ፣ ፈር ቀዳጅ ወይም መሪ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ከሕዝብ የጋርዮሽ ሐሳብ አራማጅነት ያፈነገጡትን ግለሰቦች እንበላቸው እና ስለሕዝብ ምንነት እናስረዳቸው፡፡

ለ) ሕዝብ ለግለሰቦች

ሕዝብ ባገኘው ሁሉ መንገድ የሚማር ከዘመን ዘመን እያደገ፣ እየተሻሻለ የሚሄድ በአንድ አካባቢ ወይም አገር ለረዥም ዘመናት አብረው የሚኖሩ ትውልዶች ስብስብ ነው፡፡ ሕዝብ ካገኘው ነገር ሁሉ ትምህርት እየቀሰመ፣ በቀሰመው ነገር ላይ ተመስርቶ ባሕሉን እና እሴቱን የሚገነባ፣ በገነባው እሴት ላይ ተመስርቶ ፍርድ የሚሰጥ፣ ግለሰቦችንም ሆነ ሁነቶችን ገዢ/ከሳች አካል ነው፡፡

በዘመናችን ሕዝባዊ አስተሳሰብን ከሚፈጥሩ ነገሮች ውስጥ
(1) ትምህርት፣
(2) መገናኛ ብዙሐን እና
(3) ስርዓተ አምልኮ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

እነዚህን ሦስት የሕዝባዊ አስተሳሰብ ምንጮች የሚገብሩት ዕውቀት የሕዝቡን ትውፊት፣ ባሕል፣ እሴት ይቀርጻሉ፡፡ ስርዓተ አምልኮን በተመለከተ ወደፊት አዳዲስ ሃይማኖቶች እና አማልክቶች የመፈጠር ዕድላቸው ጠባብ ነው፤ ቢፈጠሩም አማኝ/አምላኪ የማግኘት ዕድል የላቸውም፡፡ መገናኛ ብዙሐን እና ትምህርት ግን መቆሚያ የላቸውም፡፡

መንግስታት ስርዓተ ትምህርትን እና መገናኛ ብዙሐንን የሚቀርፁበት መንገድ ምን ዓይነት ሕዝብ ማፍራት እንደሚፈልጉ ያሳብቃል፡፡ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ለትምህርት በጣም ጉጉ ከመሆናቸው የተነሳ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ጥረት ትምህርትን ለማስፋፋት አድርገዋል፡፡ ሚኒስትሮቻቸውም ጥሩ የትምህርት ደረጃ የነበራቸው እንጂ እንደአሁኑ ዘመን በፓርቲ ታማኝነት ብቻ የሚሾሙ አልነበሩም፡፡ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሕዝብ እንዲያውቅ እና እንዲነቃ ያደረጉት ሙከራ በራሳቸው/በአስተዳደራቸው ላይ የሚያምፅ ትውልድ እንዲያፈራ ሆኗል፡፡

አሁን የእርሳቸውን ተቃራኒ እየተከተሉ ያሉት መሪዎች የፈጠሩት የትምህርት እና መገናኛ ብዙሐን ስርዓት ግን በአሁኑ ሰዓት ለሚስተዋሉት አምባገነን ገዢን የመቀበል (እና ‹‹መተኪያ አይገኝላቸውም›› ብሎ የመስጋት) እውነታዎች መንስኤ ነው፡፡

ሕዝብ የስርዓት ውጤት ነው፤ ጠያቂን ሕዝብ መፍጠር የመንግስት ግዴታ እንጂ መብት አይደለም፤ ጠያቂ መሆን ደግሞ የሕዝብ መብት ነው፡፡

3 comments:

 1. "ሕዝብ የስርዓት ውጤት ነው፤ ጠያቂን ሕዝብ መፍጠር የመንግስት ግዴታ እንጂ መብት አይደለም፤ ጠያቂ መሆን ደግሞ የሕዝብ መብት ነው፡፡" Mengest Gedetawen ende Gededat sayehon ende generosity eyayebete Yalebete huneta newe Yalewe!
  Thank you Feke

  ReplyDelete
 2. I say it is the other way round. It is the public responsible to force the government to act accordingly. The English had been forcing their governments(Kings, monarchs and parliaments) to be democratic. It was not the government who pushed the public to the good.

  ReplyDelete
 3. እጅህ ይባረክ የብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዘቦች ተብሎ የሚፃፍበትም ቦታ አለ። ለመሆኑ ስንት ዓይነት ሕዝብ የታጠበ,የተቀሸረ,ጀንፈል እያሉ ሊቀሽቡት ይሆን?

  ReplyDelete