Thursday, January 29, 2015

አዲስ ዜና

አዲስ ዜና 
ሶስት ዞኖች እነዳሉት የሚታወቀው የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በአስቸኳይ አራተኛ ዞን እየተገነባ እንደሆነ ታወቀ፡፡ በሶስቱ ዞኖች ውስጥ በአማካይ ከ100 በላይ ያልተፈረደባቸው የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን የሚከታተሉ እስረኞች ሚገኙበት ሲሆን አሁን አራተኛው ዞን ግንባታ በፍጥነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ 

News update - Ethiopian government prison administration is expanding kilinto prison. according to the sources the prison is establishing new 4th Zone in addition to those three zones existing now. Currently, more than 100 male cell mates are under custody in each existing Zone.

ክሱ ተሻሻሏል ሲል "ፍርድ ቤቱ" ወሰነ

‪#‎FreeZone9bloggers‬ ‪#‎FreeEdom‬ ‪#‎FreeTesfalem‬ ‪#‎FreeAsemamaw‬ ‪#‎Ethiopia‬
ሰበር ዜና -----ክሱ ተሻሻሏል ሲል "ፍርድ ቤቱ" ወሰነ smile emotለስድስት ወራት የክሱን ፎርማት ይዘትና ህጋዊ መሰረት ሲያጠና የከረመው "ፍርድ ቤት" ክሱ ተሻሽሏል የሚል ብያኔውን ዛሬ በተደረገው 16ተኛ የዞን9 የጦማርያን እና ጋዜጠኞች ችሎት ላይ በንባብ አሰምቷል ፡አንዲሻሻሉ ከታዘዙት አራት ነጥቦች መካከል ሶስቱ መሻሻላቸውን አይቻለሁ ያለው "ፍርድ ቤቱ "
1. ቡድን በሚል የተጠቀሰው ተከሳሾቹ ያቋቋሙት የህቡህ ቡድን አንደሆነ ፍርድ ቤቱ ተረድቷል ቡድኑ ዝርዝር ሁኔታ በማስረጃ መስማት ወቅት ተቀባይነት ሊኖረው ወይም ደግሞ ውድቅ ሊሆን የሚችል ስለሆነ ክሱ ውስጥ መካተት አለበት ሲል ወስኗል ፡፡
2. ስልጠናን አስመልክቶ ‹‹ተከሳሾች ከ2004 ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በግንቦት 7 አመቻችነት ስልጠና መውሰዳቸውን የተሻሻለው ክስ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም ጊዜውና በማን የሚለው ስለተጠቀሰ ክሱ መሻሻሉን ፍርድ ቤቱ ተቀብያለው ብሏል፡፡
3. ለሽብር ተግባር ዋለ የተባለውን 48.000 ብር አስመልክቶ ክሱ ውጨ አገር የሚገኙ የቡድኑ አባላት ናቸው በሚል ስለሚያብራራው ተቀባይነት አግኝቷል ያለ ሲሆን ስራ ክፍፍልን አስመልክቶ በቂ ዝርዝር ባለመቀረቡ ከስራ ክፍፍል ፍሬ ነገር ውጪ ያሉት የክሱ ፍሬ ነገሮች ተካተው ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆን አለመሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ጠይቋል፡፡
በተከሳሾች ጠበቃ የፍርድ ቤቱ የሶስቱን ፍሬ ነገሮችን መቀበል ያልተጠበቀ መሆኑን ገልጸው ከደንበኞቻቸው ጋር ለመመካከር ጊዜ ጠይቀዋል ፡፡ በዚህም መሰረት ችሎቱ ለከሰአት 8.00 በድጋሚ ተቀጥሮ የጠዋቱ ችሎት ተጠናቋል፡፡
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ብዙም ያልተገረሙት ተከሳሾች ወንዶቹ የምሳ እረፍታቸውን በልደታ ፍርድ ቤት ውስጥ ሲያሳልፉ፣ ሴቶቹ ወደ ቃሊቲ ተመስደው ተመልሰዋል፡። በጠንካራ መንፈስ ላይ የነበሩት እስረኞች ብይኑ በችሎት ሲሰማ ከፈገግታ እና ሳቅ ባለፈ ምንም አይነት መደናገጥ አልታየባቸውም ፡። በቆይታቸውም እርስ በርሳቸው ሲያወሩ ሲወያዬ እና ወዳጅ ዘመዶችን ሰላም ሲሉ ተስተውለዋል፡፡
በከሰአቱ ችሎት በቂ የመወያያ ግዜ ለማግኘት ስላልተቻለ ጠበቃ አምሃ አጭር ቀጠሮ በመጠየቃቸው ችሎቱ ለሚቀጥለው ማክሰኞ ለጥር 28 ተቀጥሮ ተጠናቋል፡፡
ማስታወሻ
የዞን9 ጦማርያን ፍርድ ቤቱ እድሉን ተጠቅሞ የፍትህ ስርአቱን ነጻነት የሚያረጋግጥበትን ወርቃማ እድል አንዲጠቀም ደጋግመን መጠየቃችን ይታወሳል፡፡ ከማስረጃው 90 በመቶው ጦማራችን ላይ የወጡ ጽሁፎች በመሆናቸው ክሱ ሃሳባቸንን በነጻነት በመግለጻችን ብቻ የተቀናበረ ፓለቲካዊ ክስ መሆኑን ግልጽ ያደርገዋል ፡፡ አሁንም አልረፈደምና ዞን9 ጦማርያንን እና ጋዜጠኞችን በነጻ በማሰናበት የፍትህ ስርአቱ ራሱን እንደቁምነገር የሚያስቆጥርበትን እድል አንዲጠቀም ደግመን እናሳስባለን፡፡ የፍትህ ስርአቱ መስተካከል ከጦማርያኑ እና ጋዜጠኛ ወዳጆቻችን ከታሰሩለት አገራዊ አጀንዳ አንዱ ነውና !

“ሽብርተኛውን“ ተዋወቁት

አብርሃም ሰለሞን ይባላል ፡፡ በነ ዘላለም ወርቃለማው የክስ መዝገብ ከአራቱ የፓለቲካ አመራሮች በተከሰሱበት መዝገብ ስድተኛ ተከሳሽ የሆነው አብርሃም ሰለሞን መምህር ነበር ፡፡ አብርሃም ከመታሰሩ በፊት ቤተል ትምህርት ቤት መምህር ነበር ፡፡ በሞያውም የፈጠራ ስራዎች ላይ ማተኮር ይወድ ስለነበር አገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሽልማት አሸናፊ በመሆን ከተመረጡ መምህራንም መካከል አንዱ ነው ፡፡ 
ነሃሴ ላይ ከታሰረ በኋላ ጥቅምት ላይ በተደረገው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ሽልማት ተሸላሚ በመሆኑ በጥቅምት ወር በተደረገው የሽልማት ስነስርአት እናቱ ወክለውት ሽልማቱን ተቀብለዋል ፡፡ ይህ በሽብር የተከሰሰ ወጣት አስተማሪ አይሲቲን በቀላሉ እና በሚገባ መልኩ ማስተማር የሚረዳ የፈጠራ ውጤት ባለቤት በመሆኑ ነው ሽልማት ያገኘው ፡፡ የሽልማቱ ቲሸርት እና ሜዳልያን ይዘው ሊጠይቁት የሄዱት እናቱ ሜዳልያውን ማስገባት ባይችሉም ቲሸርቱን አስገብተውለት ተመልሰዋል ፡፡ በማስተማር እና በፈጠራ ስራ የተሰማራው ይህ መምህር አንድም እውነተኛ ሽብተኛ ተከሶበት በማያውቀው ክስ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን2 ይገኛል፡፡ በእርሱ የመምህርነት ደሞዝ ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦቹም እሱን ቅሊንጦ ድረስ እየሄዱ በመጠየቅ እየተንከራቱ ይገኛሉ ፡፡ 

ቢያንስ ኢንተርኔት ላይ ሼር በማድረግ የማናውቃቸው ብዙዎች ለሚከፍሉት ዋጋ እውቅናን እንስጥ

Saturday, January 24, 2015

ተስፋለምን ሳስታውሰው . . . .

ማስረሻ ማሞ
እኤአ ጁላይ 10/2010 ጠዋት፤ ግማሽ ሰው ግማሽ ሰካራም ኾኜ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ጭንቅላቴ በምሳር እንደተፈለጠ እንጨት ውስጡ ብርግድ ብሎ ደርቋል። የኾነ ነገር ጠጥቼ ራስ-ካላደረግኹት፤ ከፍላጩ የሚወጣው ስንጣሪ ቀኑን ሙሉ ሲረብሸኝ እንደሚውል አስቤ እንደ መጋዣ እየተጎተትሁ ተነሳሁ። መገለጥ ያቃታቸውን ዐይኖቼን በአይበሉባዬ ጨምቄ ዞር ስል ተስፋለም ወልደየስ ጧ ብሎ ተኝቷል። የቀኝ እጁ ከአልጋው ጠርዝ ላይ ከርፈፍ ብሏል። ግማሽ ፊቱ በብርድ ልብስ ተሸፍኗል። አተኛኘቱ አስቀናኝ። ልክ እንደ ሕጻን ልጅ ያለበትን አያውቅም። አእምራቸው በክፋት ያልተሞላ ሰዎች ብቻ ይመስሉኛል እንዲዘህ የሕጻን ልጅ እንቅልፍ መተኛት የሚችሉት። ተስፋለም አልጋ ላይ ሳይኾን የኾነ ደመና ላይ የተንሳፈፈ ይመስላል።

ይኼን የመሰለ ሰላማዊ የኾነ እንቅልፍ የተኛ ሰላማዊ ልጅ፤ ከእንቅልፉ እንዳለቀሰቅሰው ብዬ በሩን በቀስታ ከፍቼ ወጣሁ። ለነገሩ በሩ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከማውቃቸው ሳይነኩ በቋቋታ ከሚያሳብቁ በሮች የተለየ ነው። ቋ የለ፤ ሲጥ የለ ማንንም ሳይረብሽ ተዘጋ። ሳሎኑን በረጅም እግሮቼ ሁለቴ አጠፍኩት። ራሴን ፍሪጅ ውስጥ አገኘሁት። ቀዝቃዛውን ውኃ ከእነ ጆጉ ጠመድሁት። ጉሮሮዬን ቸሰሰሰሰሰሰ እያደረገው ሲወርድ ኤርታሌ ላይ ዘላለማዊ በረዶ የወረደበት የሚመስል ዐይነት ድምፅ ጭንቅላቴ ውስጥ ተሰማኝ። ዐይኖቼ በትንሹ ተዘረጉ። ወዲያው የቡና ማሽኑን አውጥቼ ቡና ጣድኹ። ከሳሎኑ ፊት ለፊት በጓሮ በኩል አንዲት ሰታቴ የምታክል የዋና ገንዳ አለች። የጃኩዚ ታላቅ ወንድም፤ የዋና ገንዳ ታናሽ እህት ትመስላለች። ጠርዟ ላይ ቆሜ ሰታቴዋ ላይ አፈጠጥኹባት። ልግባ አልግባ ብዬ ከራሴ ጋራ ሙግት ገጠምኹ፤ ሐሳቤን ሰርዤ ከቤት ውጭ ካሉት ወንበሮች አንደኛውን ስቤ ተቀመጥኹ።

ቂጤ መቀመጫውን ሳይዝ የቡና ማሽኑ በፉጨት ጠራኝ። ቀድቼ ተመልስኹ፤ ሲጋራ ለኩሼ ቁጭ አልኹና እንዲህ ግማሽ ሰው ግማሽ ሰካራም ያደረገኝን ነገር ማሰብ ጀመርኩ። የቅዳሜ ምሽቱ አስረሽ ምቺው ነበር ለዚህ ያበቃኝ። ሦስት ሎንግ አይላንድ አይስ ቲ አከታትዬ ነበር የጠጣኹት፤ ቢራና ተኪላው ሳይቆጠር። ተስፋለም አጠጣጤን ተመልክቶ እንደታላቅ ወንድም ሲቆጣኝ ነበር ያመሸው። አንዳንዴ ቶሎ ስክር ብሎ፤ ቶሎ ጭፍር አድርጎ፤ ቶሎ ጥቅልል ብሎ መተኛት ያምረኛል። እንዲህ ነኝ። የትንሹ ተስፋለም ምክር ልክ እንደነበር የገባኝ ግን ሲነጋ ነው። ጭንቅላቴ ሙቀጫና ዘነዘና ፈጥሮ ሲወቅጠኝ ይሰማኛል።  

ከአንድ ሰዓት ቁዘማ በኋላ ሶፊ ከኋላዬ መጥቶ “ዛሬ ምን ተገኝቶ በጠዋት ተነሳህ እባክህ?” አለኝ። ሁሌ ቀድሞኝ ስለሚነሳ በነገር መጎሸሙ ነው። ሶፊ ሥራ ይኑርበትም አይኑርበት ማልዶ መነሳት ዋና መለያ ጠባዩ ነው። ከእንቅልፋችን ሳንነሳ ቁርስ ለማዘጋጀት ተፍ ተፍ ይላል። ከራሱ ደስታ ይልቅ የሌሎች መደሰት የሚያስደስተው ዐይነት ሰው ነው።  ኮቴውን እንኳ ሳልሰማ ስለመጣ ትንሽ ደንገጥ አልኹ። ቡናውን ቀድቶ ወሬ መሰለቅ ጀመርን። እኔና ሶፊ ለእግር ኳስ ብዙም ግድ የለንም፤ ነገር ግን የኔዘርላንድስና የስፔንን ጫዎታ እንዲያመልጠን አልፈለግንም። የት እንደምናይ መከርን። ‘ሐበሻ የሚባዛበት ሰፈር ጎራ ብንል ይሻላል’ በሚል ወደ ካባላጋላ ስለመሄድ እያወጋን እያለ ተስፋለም መጣ። ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ ልክ እንደ ሰባት ዓመት ልጅ ለንቦጩን መጣል ይወዳል። ሁለታችንም ዐይተነው ሳቅንበት።
 ለማናደድ ፈልገን “ዛሬ ቁርስ የመሥራቱ ተራ ያንተ ነው” ብለን አዘዝነው።

“እኔ እንደናንተ መሥራት ስለማልችል ራሳችሁ ሥሩ” ብሎ ወተት ይዞ ቁጭ አለ። ጣቶቹ ብዕር ለመጨበጥና ኪይቦርድ ለማንጣጣት ብቻ የተፈጠሩ ይመስል ቢላን ከሽንኩርት ጋራ ማገናኘት ይከብዳቸዋል። ተስፋለም የሚወደው፤ መጻፍ፣ መዘገብ፣ ኤዲት ማድረግ፣ ዲዛይን ላይ አፍጦ መዋል፣ ኹነት ማሳደድና አዲስ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ማየት ነው። ለጋዜጠኝነት ሞያ ያለውን ፍቅር ስመለከት ድንቅ ይለኛል። የጋዜጠኝነት መርሆዎችን የምሩን ይወስዳል። መርኾቹ ሲጣሱ ይጨቃጨቃል። ማንም ሰው ጽሑፍ አምጥቶ ሲያሳየው የመሰለውን አስተያየት ከመስጠት ወደኋላ አይልም። ዋና አዘጋጅ ኾንኽ ሪፖርተር ለእርሱ ጉዳዩ አይደለም። ካሳየኸው “ይኼን ቁረጠው፣ ይኼን አስቀድመው፣ ይኼን ከኋላ አድርገው፣ ያኛውን አውጣው፤ እንዲያውም ይኼኛው የአንተ እምነት እና አስተያየት እንጂ ከጽሑፉ ጋራ አይሄድም” ምናምን ይልኻል። መረጃ ላይ ያልተንተራሰ ጽሑፍ አያስደስተውም። ከምንም በላይ የሚያስገርመኝ ግን ዜና ለመስበር ያለው ጉጉትና ጥድፊያ ነው።

“አንደኛ ብሬክ ማድረግ አለብን” ይላል ሁሌ።     

“ኳስ ኢትዮጵያን ቪሌጅ እንይ ብለናል” አልኹት፤
“ይመቸኛል፤ ቹፒ አልተነሳችም እንዴ?” ብሎ ጠይቀኝ።
“ተነስታ ቢኾን ታያት አልነበር?”

“አንተ ደግሞ ቀጥ ያለ ጥያቄ ስትጠየቅ፣ ቀጥ ያለ መልስ ስጥ” ብሎ በስጨት አለብኝ። ለምን እንደኾነ አላውቅም በቀን ውስጥ ተስፋለምን አምስት ስድት ጊዜ ካላበሳጨኹት ደስ አይለኝም። ሲናደድልኝ ደስ ይለኛል።
ቹፒ ሳቃችንንና ወሬያችንን ሰምታ መጣች። ቹፒ ትክክለኛ ስሟ ሕሊና ዓለሙ ነው። ጋዜጠኛ ናት። ስለ ዩጋንዳ ኮሚዲቲ ኤክስቼንጅ አመሠራረት እና በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ የ15 ቀን ጥናት ልታደርግ ነው የመጣችው። ቁርስ ተበላ፣ ስለ አዋዋል ዕቅድ ወጣ። ሙኞኞ ወደ ተባለው የካምፓላ ሆቴል ለመሄድ ተወሰነ። ጊዜውን ዋና በመዋኘት ለማሳለፍና የኳስ ሰዓት ሲደርስ ወደ ካባላጋላ ለመመለስ።

ሙኞኞ ካምፓላ አሉኝ ከምትላቸው ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ አንዱ ነው። አንዱ ነው ማለት ግን በጥራቱ ከሌሎቹ ጋራ ይመሳሰላል ማለት አይደለም። የአዲስ አበባው ሻራተን ከሌሎች እንደሚለየው ሁሉ ይለያል። ባራዳ ቋንቋ ጉደኛ ነው። ከ2000 በላይ አልጋዎችን ታቅፎ ከቪክቶርያ ሐይቅ ስር ተንጣሏል። ወደ ውስጥ ዘልቀው ሲገቡ ሆቴል ውስጥ ሳይኾን የኾነ መንደር ውስጥ የገቡ ይመስላል። አራት አራት ፎቅ ያላቸው ብዙ አፓርትመንቶች ተሰባጥረው ተቀምጠዋል። ለፈረሶች የተከለለ ትልቅ ስፈራ አለው። የአፍሪካ መዲናዋን አዲስ አበባን 1/4ኛ የሚኾኑ መኝታዎች የታቀፈውን ሆቴል ሳስብ “ደሞ ሆቴል” ብዬ አሸሙሪያለሁ በአዲስ አበባ። ያየኹት ቀን። (አገሬው በሙሉ ሙሴቬኒ ከዚህ ሆቴል ጀርባ ኾኖ ሽልንግ ያትማል እያለ ያንሾካሹካል)።  

ቹፒ ስለ ሙኞኞ ሲወራ ጉጉቷ ናረ። ሆቴሉ ውስጥ የፈለጉበት ቦታ ተዘዋውሮ ማየት ይቻላል፤ ከመዋኛ ስፍራው በስተቀር። ለሚዋኙ 20ሺሕ፣ ለማይዋኙ 10ሺሕ ዱብ ዱብ አድርገን ገባን። ሺሕ ሲባል ያስደንግጣል፤ 8 ዶላርና 4 ዶላሩን እኮ ነው ቁልል አድርገው የሚጠሩት። ሺሕ ሽልንግ ገብቶ ሺሕ ሽልንግ ሲወጣ ግን ይደብራል። ያው ወፍ እንዳገሯ ነው ነገሩ፤ እኛም በሺሕ እንቆጥራለን።

ለማንኛውም ግን ዋና የማልችለው እኔ ነኝ። ዐሥር ሺሕ በባዶ ከፍዬ ገባሁ። አንድ አራቴ ነው መሰለኝ፤ በቁስቋምና በመቀጠያ ወንዞች ውስጥ በልጅነቴ ተንቦጫርቄያለሁ። እርም ብዬ የተውኩት ግን አብሮ አደግ ጓደኛችን ‘ሴጣን ባሕር’ ተብሎ ከሚጠራው ወንዝ ውስጥ ሲዋኝ ሞተ የሚባለውን ዜና ከሰማሁ ጀምሮ ነው። አጋነንኹት አይደል? እርም ብዬ የሚለው እንዴት ብሎ አራቴ ለዋኘ ሰው ይሠራል? ያው ወሬ ለማጣፈጥ ያህል ነው። ለነገሩ ሰይጣን እና ውኃ በአንድነት ወደ ሞት ከሚወስዱኝ ቢቀርብኝስ ብዬ ነው የተውኹት። ውኃ አልፈራም፤ ግን ደግሞ ዋና አልችልም።

ተስፋለም፣ ቹፒና ሶፊ ዋና ገንዳው ውስጥ ገብተው ውኃ ሲራጩ፤ እኔ መጽሐፍ እያነበብኹ በደፍንደቃቸው ደስ እያለኝ ቆየሁ። ተስፋለም ያደገው ጦር ኀይሎች አካባቢ ከሚገኘው ቶሎሳ ሰፈር ነው። እርሱም እንደኔ ዋና አይችልም። እየደፈቁ እያወጡ ያስተምሩታል። ይስቃል፣ ይቦርቃል።

ለተስፋለም አንድ ነገር የማትችል ከኾነ አልቻልክም ነው። መቻል የሚባለው ነገር ከመሞከር ይመጣል። ስለዚህ እየተሳሳተ ይዋኛል። እየዋኘ ይሳሳታል። ውኃው ሲያስጨንቀውና ትንፋቀሽ ሲያጥረው መሬት ላይ እንዳለ ሰው ቀና ብሎ ለመቆም ይታትራል። መጽሐፍ ማንበቤን ትቼ ውኃው ሲንገዳግደውና ፊቱን አስር ጊዜ ሲሞዥቅ እያየኹ እስቃለሁ። 

ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲኾን ሙኞኞን ጥለን ከመውጣችን በፊት በቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ጸሐይ ስትጠልቅ ለማየት ሄድን። ነፋሱ ከቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ሙዚቃ እያባዘተ ጆሯችንን ይዳብሳል። ጸሐይዋ ሐይቁን ሰንጥቃ እያጥበረበረች ውስጡ ገብታ ትዋኛለች። ውኃው ውስጥ ስትኾን ስብርብር ትላለች-እንደሚሽኮረመም ልጃገረድ። ድንገት ዞር ስል ሐበሻ ባልና ሚስት ትንሽ ትንቡክ ያለ የሦስት ዓመት ልጅ ይዘው መጡ። ማለፍ አልቻልኩም። ማጫወት ጀመርኩ። ጉንጩን ግምጥ አደረግኹት። ተስፋለምም ተከተለኝ። ከልጁ ጋራ ትንሽ ጊዜ ፈጨን። እናቱና አባቱ ኤርትራውያን ናቸው። ከልጃቸው ጋራ ጊዜ ስለሰጡን አመስግነናቸው ወጣን። ጥድፊያ ወደ ራትና ኳስ።

ከሙኞኞ ወደ ካባላጋለ መሄድ ፈተና ኾነ። ከሰላማ ሮድ የሚመጡ የሚኒባስ ታክሲዎች ሰው እንደ ጎመን አጭቀው እብስ ይላሉ። እጆቻችንን በተደጋጋሚ ከመዘርጋታችን የተነሳ ትከሻችን ሊረግፍ ምንም አልቀረውም። ስልችት አለን። “አማራጭ የሌለበት ውብ አገር” እያልን ማጉረምረም ጀመርን። ከሙኞኞ ግቢ ውስጥ አንዲት ራቫ ፎር እንደ ዓሊ እየተጎተተች ቀረበችን። ያ ትንቡክ ያለ ሕጻን ከኋላ ወንበር ላይ ተሰፍቶ ጥርሶቹን ብልጭ አደረጋቸው። መኪናዋ ቆመች። ለሊፍት መኾኑ ሲገባን ሮጥ ሮጥ ብለን ገባን። ሶፊ ከአንድ ሰዓት በፊት ጥሎን ሄዷል።

“እስከ ካንሳንጋ መንገድ እናቅልላችሁ” አለች ሚስትየዋ የትግርኛ ቅላጼ ግምድ ባደረገው አማርኛ። በግዕዝ የምታዋራን ነበር የምትመስለው። የኾነ የሚጣፍጥ ነገር አለው።
“ትልቅ ነገር ነው ለእኛ፤ በጣም ነው የምናመሰግነው፤” አለ ተስፋለም። ባልየው እስከ ካንሳንጋ ነዳን።

ካባላጋላ ከካንሳንጋ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። ቹፒ ርቧት ስለነበር ‘ታክሲ እንያዝ ወይም ቦዳ ቦዳ እንፈናጠጥ’ አለች። የለም እንደርሳለን በሚል ወገምናት። ሁለት ለአንድ መሸነፏ ሲገባት ዝም አለች። ደስ እያላት ግን አልነበረም። የምስራቅ አፍሪካ የሐበሻ ምግብ ወዳጆች ከሚያዘወትሩት የአብነት ምግብ ቤት ሄድን። መብላት የፈለግነው ክትፎ ነበር። አብነት በዘወትር ቀለስላሳ አንደበቱ ከወገቡ ስብር ብሎ “ክትፎ ጨርሰናል፤ ሌላ ምን ይኹንላችሁ?” አለን፤ የአብነት ምግቡ ብቻ ሳይኾን አጎነባበሱም ገበያ ስቦለታል።  

“ክትፎ ነበር የፈለግነው፤’ ብለን ወጣን። ክትፎ ቀን ከሌት ወደማይጠፋበት ቤት አመራን። ሆቴሉን ማቢራ ይሉታል፤ ከውስጡ ያለውን የክትፎ ፋብሪካ ደግሞ ሌዋውያን የሚል ስም አውጥተውለታል። የሌዊ ሰዎች ክትፎ ስለማወቃቸው እርግጠኛ ባልኾንም፤ ‘በስማቸው ታዋቂ የክትፎ ፋብሪካ እንደተከፈተላቸው አያውቁ’ እላለሁ ሁሌ ለራሴ። ክትፎው ከቀረበበት ሰዓት አንስቶ በላን ሳይኾን አጋበስን ነበር የሚባለው። ቹፒ የእግር ኳሱ ሰዓት አልፎ እንዳንደርስ የሚለው አስጨንቋታል። ተስፋለምም እንደዚያው። በተለይ ቦታ እናገኛለን የሚለው ጉዳይ በጣም አሳስቧቸው ነበር።

እኔ ደንበኝነቴን ተማምኜ አንዱን አስተናጋጅ ወደ ፊት ቦታ ፈልግ ብዬ አስሞስነዋለሁ እያልኹ ሳስብ ነበር። አልነገርኳቸውም። እየተጣደፍን በልተን ወጣን። ካንሳንጋ ሁሌ ባለፍኩበት ቁጥር ሁለት ቦታዎችን ያስታውሰኛል። ቺቺኒያንና ሰባተኛን። ሁለቱን ሰፈሮች አደባልቆ የያዘ ቦታ ነው። ዩጋንዳዊ ስልክ ደውሎልህ ‘ካባላጋላ ነኝ’ ብለህ ከመለስክ “አምሮሃል ማለት ነው ዛሬ” ይልኻል። “ምን?” ስትለው “ሄሄሄሄ” ብሎ ይመልስልኻል። ዩጋንዳውያን “የእንትንን” ስሙን አይጠሩትም፤ ግን እንደ ጉድ ይበነግጉታል። ከካባላጋላ ባሮች ውስጥ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወሲብ የሚሸጡ ሴቶች ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተው ይጠብቁኻል። ወጣ ስትል መንገድ ላይ የሚጠበስ ዶሮና ቻፓቲ (ቂጣ) በእንቁላል እየሞለሞሉ የሚሰጡ ባለ ትናንሽ ብረት ምጣዶች ትኩስ ትኩሱን ያቀርቡልኻል። በአቅምህ ገዝተህ እንድትበላ እነ እናት ጓዳዎች በስጋ ያበደ ሩዝ፣ በዓሳ የጣፈጠ ማቶኬ፣ ሜዳውን ከለል አድርገው ይሰጡኻል።

ቹፒ ግርግሩን ማቋረጥ ምጥ መስሎ ስለታያት አሁንም ቦዳ ቦዳ ካልያዝን አለች። አንሰማሽም አልን። ካምፓላ ላይ ከአንድ ኪሎ ሜትር በታች ለኾነ ርቀት ቦዳ መያዝ ጥጋብ ነው። እጇን ጠበቅ አድርገን ይዝን ወደ ኢትዮጵያን ቪሌጅ ሬስቶራንት አሻቀብናት። ስንደርስ ሬስቶራንቱ ጢም ብሎ ሞልቷል። የወቀሳ ዐይኖቿን ለመሸሽ ወደ ፊት ራመድ አልኩ። አንዱን አስተናጋጅ ጠርቼ ከስክሪኑ ፊት ለፊት ቦታ እንዲፈልግ በትዕዛዝም በልመናም ድምፅ ጆሮው ውስጥ ነገርኹት። ጥቂት ቆይቶ ተመለሰ። የማይታሰብ መኾኑን ነገሮኝ፤ ወንበሮች ይዞ መጣና “በግማሽ በኩል ስክሪኑን፤ በግማሽ በኩል ደግሞ ከጠባቧ ክፍል ውስጥ ያለውን ቲቪ እያያችሁ ተደሰቱ” አለን። ምርጫ የለም። የተገኘችውን ዕድል ፈጥነን ተጠቀምንባት።

ኳሱ ተጀመረ። በተጀመረ በዐሥር ደቂቃ ውስጥ ሶፊ መጣ። የያዝኹለትን ወንበር ሰጠኹት። ጫዎታው የጠበቅነውን ያህል አስደሳች አልነበረም። ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ ማየቱንም አልወደድነውም ነበር። ሁለተኛውን ግማሽ ጫዎታ ሌላ ቦታ ሄደን እናያለን ብለን ዶለትን። ተስፋለም ራቅ ብሎ ቁጭ ብሏል። ተስፋለም እያንዳንዷን ሰከንድ ይዘግባት ይመስል በትኩረት ይከታተላል። ቹፒ ከእኛ ጀርባ ኾና ታያለች። እኔና ሶፊ አጠቃላይ ኹኔታው ስላልተመችን ምን ጊዜ ፊሽካ በተነፋና በወጣን ብልን እየተቁነጠነጥን ነው። የኾነ ብረሩ ብረሩ የሚል ስሜት ወጥሮ ይዞናል። ሁለታችንም ጃኬታቾችን ደረብን።

የኳስ ሰዓቱ 44፡10 ላይ ያሳያል። ድንገት መሬትን የሚንጥ፣ ጆሮን የሚያናውጥ፣ ውስጥን ወደላይ የሚገለብጥና ሁለመናን የሚጎረብጥ ፍንዳታ ተሰማ። ሶፊ ከፊቴ ካለው ወንበር ላይ ሚዛኑን ስቶ ሲንሸራተት እንደ ሕልም የቀኝ እጁን አፈፍ አድርጌ ስይዘው ብቻ ይታወቀኛል። ባጋጣሚ ወደ ስክሪኑ ፊቴን አዙሬ ስለነበር ከስክሪኑ ጥቁር ጭስ ሲወጣ ብቻ ተመልክቻለሁ። ሰከንዶች የዓመታት ያህል ረጅም የኾኑ ይመስል ነበር። በእውንና በሕልም መካከል ያለሁ መስሎ ተሰማኝ።

እንደአጋጣሚ ኾኖ ፊቴን ወደ ትልቁ ስክሪን አዙሬ ነበር። ዐይኔ ያየው የስክሪኑ ጨርቅ ሲነድና ሲጨስ ነው። ወዲያው ግቢው በጭስ ታፈነ። ምን እየተከናወነ እንደኾነ ለማወቅ ግራ ተጋባን። አንዱ ጮክ ብሎ “ ስክሪኑ ነው የፈነዳው” እያለ ይጮኻል። ባዶ ጨርቅ ብቻውን ዝም ብሎ ሊፈነዳ እንዴት ይችላል? የሚለውን እያሰብኩ ዞር ስል ግማሽ ፊቱ የተቦጨቀ ሰው የአሳንሳ ተይዞ ሲያልፍ ተመለከትሁ። ቦምብ እንደኾነ የገባኝ ያኔ ነበር። ወዲያው ጭንቅላቴ ውስጥ የመጣው ሌላ ተጨማሪ የተጠመደ ቦምብ ሊኖር ይችላል የሚለው ነበር።

ሶፊን፣ ተስፋለምንና ቹፒን “ይኼን ግቢ በፍጥነት ለቀን መውጣት አለብን! ሌላ ቦምብ ሊኖር ይችላል!” ብዬ በትዕዛዝ ጮክኹባቸው። እንዲከተሉኝ ነግሬ ወደ ውጪ በር ልወጣ ስል የፕላስቲክ ወንበሮቹ መንገዱን ዘግተውታል። ወንበሮቹ እየጠለፏቸው ብዙዎች ይወድቃሉ፤ ይነሳሉ። ያገኘሁትን ቀዳዳ ተጠቅሜ የውጪው በር ላይ ደረስኹ። ዞር ስል ማንም አልተከተለኝም። ተበሳጨሁ። የምላቸውን ስላልሰሙኝ አረርኩ። ተመልሼ ወደ ውስጥ ስገባ ተስፋለምና ሶፊ የተጎዳ ሰው እየረዱ ነው። ቹፒ አንዲት ፈረንጅ ለማረጋጋት ጥረት ታደርጋለች። ለቅሶ፣ ዋይታና እሪታ ግቢውን ዋጠው። ጉዳት የደረሰባቸው ፈረንጆችና ሐበሾች በድንጋጤ ይጮኻሉ። አንዳንዶቹ ራሳቸውን ስተዋል። እኔም እነርሱን ወደማገዝ ተሻገርኹ።  

ተስፋለም ከጋዜጠኝነት ውጪ ሌላ ነገር ያን ያህል ይሳካለታል ብዬ አላስብም ነበር። በዚያች ቅጽበት የነፍስ አድን ጥሪ ላይ ተልእኮ ያለው ባለሞያ ይመስል ነበር። እያንዳንዱን ጉዳት የደረሰበትን ሰው በሙሉ በቻለው መጠን ለመርዳት ይራወጣል። ደንግጧል። በዚያ ድንጋጤው ግን የሚገርም ብርታት ይነበብት ነበር። እየተጋገዝን ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በወንበር ላይ እያመቻቸን ማስቀመጥ ጀመርን። የአንዳንዶቹን ቀሚስና ሱሪ እየቀደድን የሚደማውን የሰውነት ክፍላቸውን ማሰር ያዝን።

ያ ያልታሰበ ቦምብ የፈነዳው እኛ ተቀምጠን ከነበረበት ከአንድ ሜትር ተኩል ርቀት ላይ ነበር። ሞትን በዚህ ቅርበት እንደምናየው አንዳችም ግምት አልነበረንም። ባንድ በኩል ወደዚህ ቦታ ቀድመን አለመምጣታችንንና ሰዓቱን በዎክ ማሳለፋችንን እንደ መልካም አጋጣሚ ማሰብ ጀመርኩ። አስተናጋጁን በጠየቅኹት መሠረት ቦታ አግኝተን ቢኾን ኖሮ ሄደን የምንጣደው ቦምቡ ከተጠመደበት ቦታ ላይ ነበር። ስድስት ኤርትራውያንን እና አንድ ኢትዮጵያዊን በሞት ተነጠቅን። ዐሥራ ሦስት ሰዎች በከባድና ቀላል ጉዳት አደጋ ሰለባ ኾኑ። በፍጥነት ቦታውን ለቀን ራሳችንን ለማረጋጋት ወደ ሌላ ሆቴል ሄድን።

ተስፋለም ወደ ጋዜጠኝነቱ ከተመለሰ ቆየ። መንገድ ለመንገድ ለሚያውቃቸው የዓለምአቀፍ ጋዜጠኞችና ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች የነበረውን ሁኔታ መዘገቡን ቀጠለ። ከሞት ጋራ ፊት ለፊት መገናኘቱን ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም። ዜናው በፍጥነት ለዓለም መድረስ ስላለበት በስልኩ ከተለያዩ ሰዎች ጋራ ማውራት ቀጠለ። ከሞት ጠርዝ ላይም ቆሞ “ብሬክ” ስለማድረግ ያስባል፤ ለእርሱ ዋናውና ትልቁ የጋዜጠኝነት ግብ መረጃን ለሕዝብ በፍጥነት ማድረስ ነው። ሲጨርስ ወደ ድንጋጤው ተመለሰ። ያ ቅጽበት ስለ ሰው ልጅ ውስብስብ ባሕርይ የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር። አራታችንም ከአንድ ሆቴል ውስጥ ቆዝመን ተቀመጥን። ሁላችንም ማልቀስ ጀመርን። ሌላ ዜና ሰማን። ካምፓላ ውስጥ ታዋቂ ከኾነው የራግቢ ክለብ ውስጥ ሌላ ቦምብ ፈንድቶ ከአምሳ ሰዎች በላይ መሞታቸውን ሰማን። ሽብርንና ሽብርተኞችን መርገም ጀመርን። አልሻባብ የሚባለውን ቡድን እንደ ጭራቅ ጠላነው። አልሸባብን የፈጠሩብንን ፖለቲከኞች አምረን መውቀስ ጀመርን።

የተቀመጥንበትን ሆቴል ለቀን ቹፒ ይዛው ወደነበረው ሆቴል ተጓዝን። ሁሉም ነገር ሕልም እንጂ እውነት አይመስልም። የለበስነው ልብስ በሰዎች የተቆራጠ ስጋና ደም እንደተበከለ ያወቅነው ዘግይተን ነው። የተስፋለም መነጽሩ ሳይቀር በቁርጥራጭ ስጋ ተሞልቷል። ፊቱ ላይ ደም ተለጥፏል። ተስፋለም ራሱን በመስታዎት ማየት ሲጀምር እንባው ይወርድ ጀመር። ቁጭት፣ እልህና ንዴት ያንገበግበው ጀመር።
ተስፋለም በየዓመቱ ቀኑን እያስታወሰ “ሞትን ለጥቂት ያመለጥንበት” የሚል መልእክት በፌስ ቡክ ይልክልን ነበር። ዛሬ ተስፋለም የዓለም እግር ኳስ ጫዎታን ለማየት አልታደለም፤ ከሽብርተኛው አልሻባብ ቦንብ የተረፈበትን ቀን ለማሰብም ጊዜና ፋታ የሚሰጠው መንግሥት አላገኘም። እንዲህ ዐይነቱን ጠንቃቃና ለሞያው ከፍ ያለ ክብር የሚሰጥ፣ ሽብርና ሽብርተኞችን አምርሮ የሚጠላ ዜጋ የኢትዮጵያ መንግሥት ዐመጽ ለማነሳሳት በሚል ጠርጥሬዋለሁ ብሎ አስሮታል። ገና በምን እንደሚከሰውም አይታወቅም። ዜና ከመስበር ውጪ ዕቃ ለመስበር እንኳ ፍላጎት እና ምኞት የሌለውን ተስፋለምን በዐመፅ መጠርጠር ለመንግሥት የሞት ሞት ነው። ተስፋለምን ባሰብኩት ጊዜ . . . . .ተነግረው የማያልቁ ብዙ ትዝታዎች በውስጤ ይጎፈላሉ::

ይህ ጽኹፍ በቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ ከወራት በፊት ተጽፎ የነበረ ቢሆንም ለብዙ አንባቢያን ይደርስ ዘንድ በገጻችን አውጥተነዋል::