አምስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች፣
ሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት)፣ በፍቃዱ ኃይሉ (ከእስር ቤት)፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላና ናትናኤል ፈለቀ ነገ ማክሰኞ ሕዳር
27፣ 2009 ለመጨረሻ የይግባኝ ብይን ይቀርባሉ፡፡ ሰባት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ሶስት ጋዜጠኞች ከታሰሩበት ሚያዚያ 17፣
2006 ጀምሮ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ቆይተው አምስት ተከሳሾች ከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ አንስቻለሁ በማለቱ
ሐምሌ 01፣ 2007 የተፈቱ ሲሆን አራቱ ተከሳሾች ደግሞ ነፃ ናቸው ተብለው ጥቅምት 5፣ 2008 ከእስር ተለቀዋል፡፡ የዞን ዘጠኝ
ጦማሪ የሆነው በፍቃዱ ኃይሉም የቀረበበት ክስ ከፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ በመደበኛው የወንጀል ሕግ አንቀፅ
257/ሀ መሰረት በጽሁፍ አመፅ የመቀስቀስ መተላለፍን ፈፅሟል፣ ይሄንም ይከላከል ተብሎ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል
ችሎት በጥቅምት 10፣ 2008 በተሰጠው ውሳኔ መሰረት በሃያ ሽህ ብር ዋስትና ከእስር መለቀቁ ይታወቃል፡፡
በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ሶልያና ሽመልስ ፣ አቤል ዋበላና አጥናፉ ብርሃኔ |
ነገር ግን የፌደራል ማዕከል
ዓቃቤ ሕግ በታሕሳስ 04፣ 2008 በተፃፈ ይግባኝ ‹በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ፣ ተከሳሾቹ በነፃ መሰናበት የለባቸውም›
በማለት ባቀረበው ይግባኝ መሰረት ላለፍት አስራ ሁለት ወራት በስር ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠበት በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ
አምስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት በመቅረብ ክሳቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን በነገው
ዕለትም ለ50ኛ ጊዜ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔን ለማፅናት ወይም ለመሻር በሚሰየመው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጦማሪ በፍቃዱ
ኃይሉ ጥቅምት 18፣ 2009 አየር ላይ ለዋለው የአሜሪካን ድምፅ (Voice of America) ‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አጥላልተሃል›
በሚል አርብ ሕዳር 02፣ 2009 ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ የታሳረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ከመሆኑም
በላይ በአሁኑ ወቅትም ‘በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ’ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ጠበቃም ሆነ የቤተሰብ አባልም መጠየቅ
እንደማይችል የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በነገው የፍርድ ሒደትም የመቅረቡ ጉዳይም እንዲሁ አጠያያቂ ነው፡፡