Sunday, October 7, 2012

ሁለት ዓይን፣ ሁለት ዕይታ




ጊዜው ለውጡ ከተካሄደ አምስት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው መንግስት ባጎናፀፈው የመወዳጀትና የመተባባር ባህል መሠረት ሃይማኖቶች ሕብረ ዝማሬ ያስተጋባሉ፡፡ የዱቤዎች ፈጣን ምቶችና የከበሮዎች ቀሰስተኛ ድለቃዎች ተደማምረው የራሳቸው የሆነ ሜሎዲ ፈጥረዋል፡፡ ዘማርያን በአንድ በኩል በሚያስረቀርቀው ድምፃቸው ዓለማቸውን ይቀጫሉ፡፡ መንዙማዎች በሌላ በኩል ያስተጋባሉ፡፡ ትላልቅ እንጨቶች የተጣለባቸው እሳቶች ይርመሰመሳሉ፡፡ ግቢው ጭስ በጭስ ሆኗል፡፡ ቄስና ሼህ አራጆች ሰንጋዎቻቸው ጥለው በትልቁ ጎራዴ ይበርካሉ፡፡ ደሞች በየአቅጣጫው ቦይ ፈጥረው ግቢውን ደም በደም አድርገውታል፡፡ የስጋ ዘለላዎች በተዘረጉት ቀጫጭን አጠናዎች ላይ ተዘርግተዋል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የሀገሬውን የባህል ጭፈራና ዝማሬ በጋራ ሆነው ያቀልጡታል፡፡ ከግቢው ውጪ የፈረስ ውድድር እየተካሄደ ነው፡፡ ጎረምሶች የገና ዱላቸውን ይዘው የገና ኳሳን ይጠልዛሉ፡፡ ሰዎች በእያንዳንዱ ነገር የመሳተፍ ውዴታ ውስጥ ተጠምደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግርግር በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ተሰርቶ የተጠናቀቀው በደቡብ ሸዋ በሐይቆችና ቡታጀራ አውራጃ የሚገኘው መስጊድ ለማስመረቅ ነበር፡፡

አባቴ በዛን ወቅት በብሔራዊ ስሜት ነህሉሎ ነበር፡፡ ከፍተኛ የብሔራዊ ስሜት ጡዘት ውስጥ ገብቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ‹የአሞራ አገር ዋርካ፣ የእስላም አገር መካ› እንዳልተባለ አሁን ደግሞ ሙስሊሞች እንደክርስቲያን ወንድሞቻቸው እንደአንድ ዜጋ ተቆጥረዋል፡፡ እንደሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የመታየቱ፣ የማሽሟጠጡና በጎሪጥ የመመልከቱ ብሎም የመፀየፉ ስርዓት ካከተመ አምስት ዓመት ደፍኗል፡፡ አባቴ ለውጡ ባስከተለው የማኅበረሰብ ግንኙነት ምክንያት ተደስቶ ሴት ልጁን ‹ኢትዮጵያ› አላት፡፡ ባያውቀው ነው እንጂ ለልጁ ትልቅ የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ ነበር የሰጣት - ነፍሱን ይማረውና፡፡ የሙስሊሞች እንደኢትዮጵያዊ በእኩል ዓይን የመታየት የቤት ሥራ፡፡ ይሄው የቤት ሥራው ሳይሠራ ፈተና ሆኖብን ምንም ለውጥ ሳይካሄድ እንዳለን አለን፡፡ በሁለት አቅጣጫ የተወጠረ ስስ ገመድ ይዘን አንዳች የአንዳችንን ከኢትዮጵያዊነት መዝገብ ለመፋቅ ጥረት አያደረግን፡፡ ይገርማል አባቴ በአፄዎቹ ጊዜ የነበረው ስርዓት ዳግመኛ ይከሰታል ብሎ ቢያምን ኖሮ ይህንን የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ ከልጁ ዘንድ ባላስቀመጠ ነበር፡፡

ሙስሊሞች በኢትዮጵያውነታቸው ላይ የመለየት ሥራ የሚሰሩት መንግስታት ብቻ አይደሉም፡፡ የባለፉት መንግስታት ሰበካ ያጀሉ አንዳንድ የአፄው ዘመን አመለካከት ያላቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰግስገው የጥላቻ አመለካከታቸውን በማኅበረሰቡ ላይ ያሰራጫሉ፡፡ እስቲ አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ ለታሪክ ሁሉ ነገር ታሪክ ነው፤ እዚህ አገር ከመወለዳችን በፊት ታሪክ፣ ከተወለድን በኋላ ታሪክ፣ አፈርም ስንለብስም ታሪክ፣ ሌላ የለንም ታሪክ፣ ታሪክ…፡፡ እዚህ ላይ ግን ኢትዮጵያ በድሮ ማንነቷ አንቱ ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ አንዷ መሆኗን አልክድም ችግሩ ግን የድሮ ማንነት አሁን ባለንበት ሁኔታ ላይ ለመመንዘር ስንሞክር ነው፡፡

ወደ ታሪኬ ልግባ… በአንድ ወቅት እህቴ ‹ኢትዮጵያ› ትምህርቷን ለመማር አንድ ስሙን በማልጠቅሰው የትምህርት ተቋም ውስጥ የመመዝገብ ሂደት እያከናወነች ነበር፡፡ መዝጋቢው ዕድሜያቸው ጠና ያሉ ባጠቃላይ እምቢ አላረጅም ብለው እዛ ተቋም ውስጥ የቀሩ አዛውንት ናቸው፡፡ ለምዝገባ ስሟን ጠየቋት፡፡ መለሰችላቸው ‹‹ኢትዮጵያ አህመድ…›› ያደፈውን መነፅራቸውን ወደ ግንባራቸው ከፍ አድርገው የጥላቻ ንግግራቸውን አወረዱት ‹‹… ቆይ ቆይ አባትሽ ምን እየሰራ ነው?! ሁለት የማይቀላቀል ነገር ያቀላቅላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብሎ አሕመድ የማይሆን ነገር! ሰው እንዴት ዘይትና ውሃን ለማቀላቀል ይሞክራል?! ኤዲያ! ዛሬ ደግሞ ምንድነው የምታሰማኝ…›› ይህን ሁሉ ተብትበው ኢትዮጵያ ከአሕመድ ጋር ደብለው መመዝገቡን ግን አልተዉትም፡፡ ሥራቸው ነውና፡፡ ቆይ እስቲ ሰዎች ኢትዮጵያ ከአሕመድ ጋር ወዳጅነት መፍጠር አይችሉም እንዴ? መቼም ይህ ስያሜ የሚያስገርመው ክርስቲያኑን ብቻ አይደለም ሙስሊሙንም ጭምር እንጂ! አንዳንዱ አገሩን ከዚህ ውጪ አድርጎ የሚስል ‹‹ይቺ በምኗም ተምሳሌት የማትሆን አገር¡… እንዴት አባትሽ ይህንን ማንንም የማይወክል ገዳይ ስያሜ ያወጣልሻል?›› የሚለውን ጨረር ይለቃል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አፉን እያጣመመ ‹‹ተሃድሶ ተካሂዷል ማለት ነው!›› ይላል፡፡ አንድ ሰው ተወልዶ እትብቱ የተቀበረበት ያደገበትና ስንት ውጣ ወረድ ያሳለፈበት አካባቢ ብሎም አገር የመውደድ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሰው መቼም የተወለደበት አካባቢ ነውና የሚመስለው፡፡



የኢትዮጵያዊነት ስፌት

ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ውስጥ በሌላ ዓይን መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በትንሹ አበበና አሕመድ ትምህርት ቤት ውስጥ ያላቸውን ቦታ ብንመለከት ለየቅል ነው፡፡ ያው አበበ በየመጽሐፍቱ ‹‹በሶ በላ!›› እንደተባለ ይዘከራል፡፡ አሕመድ ደግሞ በመማሪያ መጽሐፍት ውስጥ ምሳሌያዊ ቦታም የለውም፡፡ ስለዚህ አበበና አሕመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው እንድምታ የተለያየ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊና አረባዊ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የተለያዩ ዜጎች አንዱ የእናት ልጅ ሌላው የእንጀራ እናት ልጅ ሆነው የሚታዩ መምሰል ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡

በዚች እኛን ዜጎችዋን በምታስደምም አገር ሙስሊሞችን እንደመጤ የማየቱ እንድምታ ታውቆም ይሆን ሳይታወቅም በቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሲገለፅ ይስተዋላል፡፡ ቴዎድሮስ እንደአገር ገንቢ፣ አሕመድ ግራኝ እንደአገር አፍራሽ፡፡ ቴዎድሮስ ከቱባው የኢትዮጵያ አንድነት ጋር ሲገኛኝ በአንፃሩ ደግሞ አህመድ ግራኝ ወራሪና በታኝ የሚለውን የታሪክ ስያሜ ይለጠፍበታል፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን እንድምታዎች ከቅርብ ክርስቲያን ዘመዶቻችን ሳይቀር ሲገለፅ ይታያል፡፡ እስቲ በአንድ ወቅት ከአንድ ወዳጄጋ ስለኢትዮጵያዊነት ስንጨዋወት የነገረኝን ላውሳላችሁ፡፡ በክርክራችን መሃል ወዳጄ ምርር ብሎ ማውራቱን ቀጠለ፡፡ ‹‹እኛ (ክርስቲያኖች) ከሳውዲ ስትሰደዱ ተቀብለን ስላስጠለልን ነው እንዲህ የምትሆኑት፤ የዛን ጊዜ በእንግድነት ባንቀበላችሁ እና ባናስተናግዳችሁ ኖሮ ኢትዮጵያዊ አትሆኑም ነበር›› አለኝ፤ በጣም ተናደድኩ ኢትዮጵያዊ ደም እያለኝ እንደ መጤ በመቁጠሬ በጣም ስሜታዊ ሆንኩ፡፡ ‹‹ቆይ ቆይ ወዳጄ! አንተ እያልከኝ ያለኸው መጤ ነህ ነው፡፡ በዛን ጊዜ ከአሁኗ ሳውዲ የመጡትን እንግዶች ተቀብለው በእንግድነት ያስተናገዱትኮ ያንተውም የእኔም አያቶች ነበሩ፡፡ ክርስትናም እስልምናም የመጡት ከውጭ ነው፤ ያንተም የእኔም አያቶች እዚህ ነው እትብታቸውን የቀበሩት! ማንም አረባዊ ማንም እስራኤላዊ አይደለም፡፡ እምነቱ ይለያይ እንጂ…›› አልኩት፡፡ ዕድሜ ለETV! በእኛ የኢድ በዓል እቺን የማትቀየር ኢትዮጵያዊና እስላማዊ ግኑኙነት ሁሌ እንደደሰኮረ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት እንደዲሪቶ እየቀጣጠሉ አንዲት ሃባ የማይለወጥ የጃጀ ድስኮራ!! ይህ ድስኮራ በደንብ ስርዓት ባለው መልኩ በትክክለኛ መልዕክት ተላልፎ ሁሉንም ባኮራ ነበር፡፡ ነገር ግን የእያንዳንዱ ነገር ላይ ላዩ የሚያውቁት የETV ጋዜጠኞች በግልብ እያሉት እንደተለመደው ያልሆነ እንድምታ በማኅበረሰቡ ላይ ይፈጥራሉ፡፡

ኢትዮጵያዊነት በአፄዎቹ ጊዜ ሲሰፋ ሁሉን የኢትዮጵያ ቀለማት እንዳያካትት ተደርጎ ነው፡፡ ሕብረ-ቀለማዊነትን በማያስተናግድ በአንዲት ትንሽ ማንገቻ የታሰረ ትንሽዬ የሕፃን ቁምጣ፡፡ በአሁን ጊዜ ሁሉም ዜጎች እዛ ቁምጣ ውስጥ እራሳቸውን ሲከቱ ማንነታቸው በዜሮ የሚባዛበት የተንሸዋረረ ዜግነት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ይህን ትንሽዬ ኢትዮጵያዊነት እንደማያካትታቸው ሲያውቁ ሌላ ተቃራኒ ፅንፍ በመፍጠር ማንነታቸውን ያስከብራሉ፡፡ የተለያዩ የማንነት ፅንፎች መፈጠራቸው ለሀገሪቷ ዕድገት ማነቆ ነው የሚሆነው፡፡ “የተከበሩ ሟች  አባታችን” ‹‹የአክሱም ሃውልት ለወላይታ ምኑ ነው?!›› ነበር ያሉት፡፡ ይገርማል! ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰሜን እስከ ደቡብ ባለው የማንነት መገለጫ እንዲኮራ አባታዊ ምክር መስጠት ነበር ከመሪ የሚጠበቀው ፡፡ የአክሱም ሃውልት ለወላይታው የማንነት መገለጫ ካልሆነ፣ የላሊበላ አብያተ ክርስታኒያት ለሙስሊሞች እንደራስ ቅርስነት ካልታየ፣ የገዳ ስርዓት ለአማራው መኩሪያ ካልሆነ፣ የሐረር ግንቦችና  የነጃሺ መስጊዶች ለክርስቲያኑ እንደራሱ ቅርስ ካልተቆጠረ ኢትዮጵያ ምኗን አገር ሆነች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ሁሉኑም የሚያካትትና ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሆደ ሰፊ ሊሆኑ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ወቅቱ በጃንሆይ ገዜ ነበር፡፡ ከጉራጌ ቀቤና የተገኙት የቃጥባሬ ሼህ ጥልቅ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነበራቸው፡፡ ይህንን ብሔራዊ ስሜት እምነቱ ውስጥ የተለያዩ እስላማዊ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ የሆነ ማንነትና ባህል እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ የቃጥባሬ ሼህ ኮፍያ ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? ኮፍያው ላይ ከሦስት የተለያዩ ቀለሞች ማለትም አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የተዋቀሩ ሲሆን አምስት ክቦች ይታያሉ፡፡ አምስቱ ክቦች አምስቱን የእስምልና ማዕዘናት ሲያመለክቱ ሶስቱ ቀለማት ደግሞ ኢትዮጵያነት ያመለክታሉ፡፡ ይሄ ነው ኢትዮጵያዊነት በእምነት ውስጥ! ሁሉንም የሚያካትት! አሁንማ ሁሉም ጥግጥጉን ይዞ ሌላውን የማያካትትና ሌላውን ከአገራዊ አንድነት የሚፍቅ ተግባራት እያከናወነ በቃ የሚለው ጠፍቷል፡፡ አርቆ አሳቢ ድሮ ቀረ፡፡ ሁሉን ነገር ማጦዝ ነው በተንሸዋረረና ሁሉን በማያካትት እይታ….

ጊዜው ቴዎድሮስ ‹‹እምቢ ለአገሬ!›› ብሎ ራሱን የሰዋበትና አጤ ዮሐንስ በተገኘው አጋጣሚ ስልጣኑን ተረክቦ ሙስሊሞች ሃይማኖታቸውን በሀይል እንዲቀይሩ ከፍ ሲልም ያለ ርህራሄ የሚቀላበት ወቅት ነበር፡፡ በዛን ወቅት በጎጃም ሀገረ ገዢ የነበረው ይህንን አስገድዶ ክርስቲያን የማድረግ ዘመቻ በሚገርም ጥበብ ተወጣው፡፡ የሃይማኖት ቅየራው ሂደት የሚካሄደው በዋነኝነት ስጋ በማብላት ነበር፡፡ ሕዝበ ሙስሊም በተሰበሰበበት ቄሱ ከመጋረጃ ፊት ሼኩ ከመጋረጃ በስተኋላ ሆነው ሰንጋውን አጋደሙት፡፡ ከዛማ ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚገኙት የሃይማኖት አባት በሬውን ሸልተው ከበጋረጃው ፊትለፊት ለሚገኙት የሃይማኖት አባት ማረጃውን አቀበሉት፡፡ ቄሱ ማረጃውን ወደ ላይ ከፍ አደርገውት ‹‹ይሄው በስመ አብ ብለን ባርከነዋል›› አሉ፡፡ ይህንን ሚስጥር የሚያውቁት ጥቂት የሃይማኖት አባቶችና ባለስለጣናት እንዲሁም የዛ አካባቢ የሙስሊም ማኅበረሰብ ነበር፡፡ ይሄ ነው ጥበብ፣ መተባበሩ በአካባቢው ማኅበረሰብ ለዘላለም ሲወሳ ይኖራል፡፡ ምንም አንኳን ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ሙስሊሞችን ሃይማኖት የማስቀየር ስርዓት በቀጥተኛ መንገድ ቢገባደድም አሁንም ሙስሊሙን ሽባ የማድረግ፣ ሽባ አድርጎም ከሃይማኖቱም የማራቅ ሂደት እንደቀጠለ ነው፡፡ ቀጥሎ አንመልከተው፡-

ጭንቅላቱን በለው

እንደሚታወቀው እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አባት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለቤተሰቡ የመሪነት ሚና ይጫወታል፣ የገቢ ምንጭም ነው፣ ቤተሰቡን ከአደጋ ይከላከላል፣ ባጠቃላይ የቤተሰቡ ራስና ምሰሶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁን ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ሙስሊሙ የራሴ የሚለውን መሪ እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ መሪ ለመሆን ከፍ ከፍ የሚሉት ታዳጊ መሪዎች ጭንቅላቻቸው እየተመቱ ቤታቸው ይቀመጣሉ፡፡ ሌላው ደግሞ እንኳን አንድ ማኅበረሰብ ለመምራት ይቅርና አህያዎችን በሰልፍ መምራት የሚያቅተው ሰው የሸህና ሐጂ ካባ ይከናነብና የዚህ ከአፍሪካ በብዛቱ ሦስተኛ የሆነ ሕዝብ ባልፈለገው መልኩ ‹‹መሪ›› ተብሎ ይቀመጣል፡፡ በሌላ ወገን ከሃይማኖቱ አልፎ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ የሁሉም አገር የሆነችን ኢትዮጵያ ወክሎ አገራዊ ሚና ይጫወታል፡፡ ይሄ ነው ሁለት የተለያየ ዕይታ… በሙስሊሞች በኩል የመሪነት ሚና እንዳይጫወቱ ተቋማቸው ሽባ ሆኗል፡፡ ይህ ተቋም ሕጋዊ ዕይታው ከአንድ ኩባንያ የማይተናነስ በየዓመቱ ፍቃዱን የሚያድስ ተቋም ነው፡፡ ከግዴታዎቹ ውስጥ በዋነኝነት በዓመት ሦስቴ ለበዓላት ራሱን ማሳየትና የማያውቁትን ፖለቲካ መዶስከር ነው፡፡ በሙስሊሞች ዘንድ አንድ ነገር ጠብ ማድረግ የተሳነው ተቋም፡፡ ከባለሙያዎች ይልቅ ባህላውያን የሚበዙበት ተቋም፡፡ ካለመሪ አንድን የአገሪቷ እኩሌታ የሚሆን ማኅበረሰብ ለመምራት ይቅርና አንድን ቤተሰብ መምራት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ሙስሊሙ አውራው እንደተመታበት የንብ ቀፎ ተበታትኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ያለመሪ እንዳይቀሳቀሱ ተብትቦ የያዛቸው ገመድ ሊፈታ ይገባል፡፡

ወደ አንድ ጎን ያዘመሙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት

እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ ሃይማኖትና መንግስትን መለያየት እንደመፍትሄ ተመለክታ ትግበራውን ከጀመረች እነሆ ግማሽ ምዕተ አመት ሊሞላን ጥቂት ነው የሚቀረን ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት አንድ የመንግስት ተቋም ተሂዶ ስለአንድ ሃይማኖት የሚያመለክቱ ጥቅሶችንና ፎቶዎችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዴ የሰቀላ ፉክክር በግልፅ የሚካሄድ ከፍ ሲልም የሰቀሉት የሃይማኖት ጎራ ለማገልገል የተቆረጠ ነው የሚመስለው፡፡ አገሪቷ የምትመራው በዓለማዊ ሕግ ሆኖ ተቋማቱ ግን ሲወርድ ሲዋረግ የመጣውን ሃይማዎታዊ ማንነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ባጠቃላይ መለስተኛ የሃይማኖት ተወካዮች ይመስላሉ፡፡ ይህ ነው እንግዲ መገለጫው ወደ አንድ ጎን ያዘመሙ ነገር ግን ሁሉንም እናስተናግዳለን የሚሉ የመንግስት ዓለማዊ ተቋሞች፡፡ አንዳንዴ እንዲሁም የራሳቸውን የሚያቀነቅን ሲመጣ ነገሮች በሚያስገርም ፍጥነት ይጠናቀቃሉ፡፡ አመለካከታቸውን የማይደግፍ ሲመጣ ግን ጉዳዩን መጎተት፣ ማመናጨቅ ሲበዛም መሳደብ የራሳቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ባብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፈሪሃ አምላክ መሆኑን ባልክድም አለማዊነት ሁላችንም የሚያግባባ መስሎ ይታየኛል፡፡

ተቋም የለሽ ማድረግ

ሙስሊሞች ተቋም የለሽ ማድረግ ከትልቁ መጅሊስ እስከ ትናንሽ መድረሳዎች ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ እስላማዊ የሆኑ ተቋማት ሲቋቋሙ በጥርጣሬ ዓይን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለሙስሊሙ ስለየማይገሰሰው ሕገመንግስት ይሰበካል በሌላው ወገን ደግሞ የራሱን የሃይማኖት አጀንዳ እንዲያከናውን ባለሙሉ መብት ይሆናል፡፡ በቅርቡ በመቋቋም ሂደት ላይ እያለ ባልታወቀ ምክንያት የተቋረጠው የዘምዘም ባንክ በዐብይነት የሚጠቀስ ነው፡፡

መሠረተ ልማት ማሳጣት

ይህ ጉዳይ ለአንዳንዶቹ ላይዋጥ ይችላል ነገር ግን ሕዝበ ሙስሊሙን ከአፄዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከመሠረተ ልማት ማራቅ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ እስላማዊ ግብረሰናይ ድርጅቶች እንዳይገቡ በሩን መከርቸም የሌላው ዓለምአቀፍ የሚሽነሪዎች ተቋም እንዲገቡ የጥሪ ደውሉን በተደጋጋሚ መምታት የተለመደ ሆኗል፡፡ ባጠቃላይ ሙስሊሞች በመሠረተ ልማት አመካኝቶ የሚሽነሪዎች ሰለባ ማድረግ በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ በንፁህ መጠጥ ውሃ እየተመጣ!

በሩን መከርቸም

እንደሚታወቀው እስልምና ዓለም አቀፋዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በየትኛው የዓለም ቦታዎች እስልምና አይገኝም ማለት ይከብዳል፡፡ ሙስሊሞች ደግሞ የጋራ የሆነውን ችግሮቻቸውን በዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና አጀንዳዎች ላይ ይፈታሉ፡፡ ይህ ዓለም አቀፋ እስላማዊ ግኑኙነት ከትንሽዋ ጅቡቲ እስከ ብዙ ሙስሊም ሕዝብ የሚገኝባት ኢንዶኔዥያ ያካትታል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በብዛቱ ከአፍሪካ ሦስተኛ የሆነ የሙስሊም ሕዝብ እያላት በዓለም አቀፋዊ መገናኛ ብዙሐን ‹‹የክርስቲያን ደሴት ነኝ!›› ብላ በሩን ከዘጋች ሰነባብታለች፡፡ ሌላው ደግሞ ከግኑኙነቱ አልፎ የዓለም አቀፍ የግኑኙነቱ ኃላፊ ሲሆኑ ሙስሊሙ ግን ምንም ዓይነት ምልከታ እንዳያሳይ በማዕቀብ ታጭቋል፡፡ ማዕቀቡ መቼ ያበቃል? ዋናው ነገር ሠላም፣ ዋናው ነገር ጤና፣ ዕድሜ መስታወት ነው እናያለን ገና! ተብሎ የለ…

በመጨረሻም

እምነቶች ጌታቸውን የሚጠሩበት ስያሜ ወይም ቋንቋ ቢለያይም መሠረታቸው ግን አንድ ነው፤ እሱም በመልካም ፀባይ ያዛሉ፣ ከክፉ ምግባር ይከለክላሉ እንዲሁም ለራስህ የምትወደን ለወንድምህ እንድትወድ ያዛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የሦስቱ አብርሃማዊ ሃይማኖች ቤት ናት ብዬ ብገልፀው ማጋነን አይሆንም፡፡ ሦስቱም በሰላማዊ መንገድ የራሳቸውን አሻራ የጣሉባት አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

የኢትዮጵያና የኢስላም ግንኙነት ከሌላው ሀገር በተለየ መልኩ የቆየ ነው፡፡ ኢስላም ለዓለም ከመሰበኩ በፊት ኢትዮጵያ ነው የከተመው፡፡ የሰላት ጥሪ አዛን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስረቀረቀው የሐበሻ ልጅ የሆነው ቢላል ነው፡፡ እናትና አባታቸውን ያጡት ነቢዩ መሀመድ በኢትዮጵያዊው እናት እንደ እናት ክብካቤ ተደርጎላቸው አድገዋል፡፡ ነቢዩ መሐመድ መካና መዲና አልመች ሲላቸው ሙሉ እምነታቸው ኢትዮጵያ ላይ ጥለው ባልደረቦቻቸውንና ልጆቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሰደዋል፡፡ እንግዳ ተቀባይ የሆነው የሀገራችን ሕዝብ ብቸኝነት እንዳይሰማቸው መልካም እንክብካቤና እምነታቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ ፈቅደዋል፡፡

እንደሚታወቀው ውጭ ያሉ አካላት የራሳቸውን ኢ-ኢትዮጵያዊ አመለካከት ለማስረፅ እስከ አሁን ያልተቀረፈው ድህነትና ድንቁርና መፍትሄ ዘየድን በማለት እየሰረጉ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አንድነት ከሀይልም በላይ መሆኑንና ድህነትና ድንቁርናን ደግሞ በራሳችን ቀናኢ መፍትሄ አሻሽለን ልናሳያቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከውጭ የሚመጣ ‹‹መፍትሄ›› የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለውና፡፡ በአንድነት ስንሠራ ነው ለውጥና ልማት የሚያመጣው ነገርግን ሁሉንም ያላማከለ ወደ አንድ ጎን የተንጋደደ ተግባር እንደ ግመሏ ጀርባ በአንድ ጎን ያበጠ ይሆናል፡፡ አንዱ አድጎ ሌላው ቢተኮስ ምንም ለውጥ ባያስከትልም እንኳን ያደገው ዕድገት ይገታል፡፡

በጽሑፌ ማገባደጃ ላይ በወሎ ክፍለ ጠቅላይ ግዛት ጎጃም በሚባለው አካባቢ በ1897 እ.ኤ.አ የተወለዱተ የታላቁን አሊም ሸህ ሰዒድ መሐመድ ሳዲቅ ድንቅ ንግግር ልጥቀስና ልሰናበት፡፡

‹‹ … እኛም የአንድ አገር ሕዝብ የሆነው ኢትዮጵያኖች፣ ያንድ ቤት ሰው ስለሆነ ደካሞች በኃይለኞች እንዳይደመሰሱ፡፡ ….የሰው ልጆች በአዕምሮ ተመስርተው እንዲኖሩ የተመሰረተውን ሀይማኖት ለመለያያ መሳሪያ ማድረጋችን ቀርቶ እንዲሁ እንደተጀመረው መተሳሰራችን እየበረታ እንዲሄድና ለራስህ የምትወደውን ለወንድምህ አድርግ በተባለው መሠረት እርስ በርሳችን ተፋቅረን ያለው ለሌለው አካፍሎ... ያልተማረው ተምሮ ሕግን አክባሪ እንድንሆን እንመኛለን…›› ~ (ደሴ ከኢድ አልፈጥር ሰላት በኋላ በ3/6/1954)
-----
ጸሐፊውን ለማግኘት የኢሜይል አድራሻቸው የሆነውን ezunaa@facebook.com ይጠቀሙ::

No comments:

Post a Comment