Thursday, September 10, 2015

የዞን 9 የ2007 ዓ/ም የእስር መስመር

የዞን 9 ጦማርያን ከታሰሩ አንድ አመት ከአምስት ወራት የተቆጠረ ሲሆን ወዳጅ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከጠቅላላው ዘጠኝ እስረኞች መካከል አራት ጦማርያን አሁንም በእስር ላይ በመሆናቸው ሁለተኛ እንቁጣጣሻቸውን በቅሊንጦ እስር ቤት ያከብራሉ ፡፡ ባለፉት አንድ አመት ከአምስት ወራት 36 ግዜ ፍርድ ቤት የተመላለሱ ሲሆን እስራቸው እና የፍርድ ሂደቱ በ2007 ዓ/ም ምን ይመስል እንደነበረ በመጠኑ እናያለን፡፡

የዞን 9 የእስር መስመር

መስከረም 2007  -የዓመቱ መጀመሪያ ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ በጻፈው  የቀድሞው አብዮተኛ ኑዛዜ  ተጀመረ፡፡ ጽሁፉ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ የዞን9 ጦማር ላይ ታትሟል፡፡

ጥቅምት 2007 የህግ የበላይነት እና ጸረ ሽብርህጉ ሲገመገም የሚለው ‹‹የጸረ ሽብር ሕጉና›› የአሁኗ ኢትዮጲያ ያላቸውን ግንኙነት አንዲሁም ምን ተፅእኖ እንዳለው የሚያሳየው ልዬ ሪፓርተዥ ተዘጋጀ፡፡
ጥቅምት 11 2007 ዓ/ም በእስር ላይ ይገኙ የነበሩትን ጦማሪት ማህሌት ፋንታሁንን እና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬን የእስር ቤት አያያዝ አስመልክቶ የቀረበውን አቤቱታ ለማየት ችሎቱ ተሰየመ፡፡ በእለቱም እስር ቤቱ የተለየ አያያዝ መኖሩን ክዶ የተከራከረ ሲሆን ፍርድ ቤቱም አንደተለመደው እንዳይደገም በሚል የማረሚያ ቃል ችሎቱን አጠናቀቀው፡፡
ከጥቅምት 12 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ለዞን9 ጦማርያን 6 ወር የእስር ቆይታን አስመልክቶ ለቤተሰቦቻቸውን ድካም የማገዝ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ በዞን9 ጦማርያን ወዳጆች አማካኝነት በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ፡፡
ጥቅምት 25 - የዞን9 ጦማርያን ለአስረኛ ፍርድ ቤት ቀረቡ ፡፡

ህዳር 2007  -
ህዳር 1 ቀን የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይማርያም ደሳለኝ በተለያዬ ሚዲያዎች ላይ ሲቀርቡ የሚሰጡትን አስተያየት ሕገ-መንግስታዊነትን የጣሰ መሆኑን አስመልክተው ደብዳቤ ጻፉ፡፡ ደብዳቤው የተከሳሾችን በህግ ፊት ንጹህ ሆኖ የመቆጠር መብት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየጣሱ እንደሆነ እና እንዲታረም የሚጠይቅ ነበር፡፡
ሕዳር 3  ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ ለ11ኛ ፍርድ ቤት ቀረቡ ፡፡ በዚህ የፍርድ ቤት ውሎም አቃቤ ህግ በአምስት ጉዳዬች ላይ ክሱን አንዲያሻሽል ትእዛዝ ተሰጠው ፡፡ ( ሊፈጽሙ ነው የተባለውን የሽብር ወንጀል በግልጽ ማስቀመጥ፣ ቡድኑ እየተባለ የተቀመጠው ቡድን ማን እነደሆነ በግልጽ ማስቀመጥ፣ የሥራ ክፍፍልን አስመልክቶ የተጠቀሰውን በግልጽ መስቀመጥ ፣ ተላከ የተባለውን 48000 ብር አስልክቶ በግልጽ ከማን አንደተላከ ማስቀመጥ ፣ ስልጠና የተባሉት ምን እንደሆኑ በግልጽ ማስቀመጥ እና የሽብር ስልጠና ሰጪ ድርጅቱን በግልጽ ማስቀመጥ ይገኙበታል)
ሕዳር 17 - በጦማርያኑ የዋስትና መብትን አስመልክቶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደርጎ በእስር መቆየታቸው እርግጥ ሆነ ፡፡
ሕዳር 24 - ተሻሻለ የተባለው ክስ በድጋሚ ለፍርድ ቤት ቀረበ ፡፡ ጠበቆች የተሻሻለው ክስ ላይ አስተያየታቸውን አንዲሰጡ ተነገራቸው፡፡ ተሻሻለ የተባለው ክስ ቡድኑ ግንቦት 7 ነው ከማለት ውጪ ምንም አይነት መሻሻል ሳይደረግበት ነበር ለፍርድ ቤት የቀረበው ፡፡

ታህሳስ 2007
ታህሳስ 7 - ጦማሪ ዘላለም ክብረት በእንግሊዘኛ የጻፈው የናፍቆት ደብዳቤ  ታተመ
ታህሳስ 9 - ጦማሪ አቤል ዋበላ ‹‹ሕልም እንደሆነ አይታሰርም›› የሚለው ተወዳጅ ጽሁፉ በዞን9 ጦማር ላይ ታተመ ፡፡
ታህሳስ 27 ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱ አንዲሻሻል ታዞ ነገር ግን በተለያዩ አራት ጉዳዮች ላይ አሁንም ባለመሻሻሉ በድጋሚ አንዲሻሻል ሁለተኛ ትእዛዛ ሰጠ፡፡

ጥር 2007
ጥር 6 የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኛ ወዳጆች በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀረቡ ፡፡ በእለቱ አቃቤ ህግ በድጋሚ አሻሻልኩት ያለውን ክስ ይዞ ቀረበ፡፡
ጥር 20 - ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ያቀረበውን ያልተሻሻለ ክስ እንደተሻሻለ መቁጠሩን በመግለጽ ተከሳሾች የህብረተሰቡን ደህንነት ወይም ጤና በማወክ በጸረ ሽብር ህጉ አንቀጽ 4 መከሰሳቸውን አጸና፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ የተጠቀሰበትን አንቀጽ በቀደመው ብይን ውድቅ በማድረጉም የተከሳሾች ጉዳይ ‹‹በጸረ ሽብር›› ሕግ ብቻ እንዲዳኝ ተወሰነ፡፡ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተቀጠረ፡፡
ጥር 26 - የዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት መሃል ዳኛው አንዲነሱላቸው አቤቱታ አቀረቡ፡፡ ችሎቱም አቤቱታውን ሰምቶ ለመወሰን ሌላ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ጥር 27 - በዚህም ቀጠሮ የተገኙት ተከሳሾች ሁለቱ ዳኞች ተሟልተው የዳኛው ይቀየርልን አቤቱታን መስማት ስላልቻሉ  በማግስቱ ለጥር 28 ተቀጠሩ ፡፡
ጥር 28 - በዚሁ እለት መሃል ዳኛው ባልተገኙበት ሁለቱ ዳኞች ጉዳዩን አይተው መሃል ዳኛው በፍርድ ሂደቱ ወቅት ጣልቃ አልገቡም አንዲሁም አፋጣኝ ፍትህን አላጓደሉም በማለት ውሳኔ መስጠታቸው ተገለጸ፡፡ ይህንን ተከትሎ የመሃል ዳኛው ምንም አንኳን በጉዳዩ ላይ ዳኞች ችሎቱ ላይ አንድቀጥል ቢፈልጉም ለእኔ ግን አንዲህ እየተባል ክሱ ላይ መቆየት አግባብ ስለማይሆን ራሴን ከችሎቱ አግልያለሁ በማለት አስተያየታቸው ሰጡ ፡፡ ( ነገር ግን ችሎቱን አሁንም የሚያስችሉት እኚሁ ዳኛ ናቸው) ፡፡
በተመሳሳይ እለት ጦማሪ አቤል ዋበላ ከማረሚያ ቤት የደረሰበትን የመብት ጥሰት ( በውሻ ሰንሰለት ታስሮ መቀመጥ እና በማዕከላዊ ሳለ በደረሰበት ድብደባ እንዲጠቀም የተገደደውን የጆሮ ማዳመጫ መሳሪያውን መቀማት) አስመልክቶ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቀረበ ፡፡ ይህን አቤቱታውን በጽሁፍ አንዲያቀርብ ከፍርድ ቤት ቢነገረውም በእለቱ የነበረው ሂደት ብዙዎን በፍርድ ቤት ውስጥ እንባ አራጨ፡፡ በእለቱ የነበሩት የእስር ቤት ተጠሪ የማውቀው ጉዳይ የለም በማለት የመብት ጥሰቱን ክደዋል፡፡

የካቲት 2007
የካቲት 11 - የዳኛው መቀየር አቤቱታን ፍርድ ቤቱ ውድቅ ካደረገው በኋላ የዞን 9 ጦማርያ እና ጋዜጠኞች የካቲት 11 ቀን ለ20ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት በመገኘት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በእለቱን ጦማሪ በፍቃዱ ‹‹የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም ሽብር ተፈጽሞብኛል›› ሲል፣ ጦማሪ ናትናኤል በበኩሉ ‹‹እዚህ አገር ፍትህ ቢኖር ኖሮ እኔ የቆምኩበት ቦታ ላይ መቆም የሚገባቸው ከሳሾቼ ናቸው፤ ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም›› የሚል ቃሉን ሰጥታል፡፡ ጦማሪ አጥናፍ ‹‹ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም›› ያለ ሲሆን ጦማሪ አቤል በበኩሉ ‹‹የኅብረተሰቡን ደህንነት ለመጉዳት አላቀድኩም ለሽብር ተግባርም አላሴርኩም ብሏል፡፡››  የሴት እስረኞችን አያያዝ አስመልክቶ አጭር ቀጠሮ የሰጠን ሲሆን አጠቃላይ የማስረጃ ማሰማት ሂደቱን ግን ከአንድ ወር ከ10 ቀን በኋላ በተከታታይ ለሶስት ቀን ቀጥሮታል፡፡
የካቲት 18 - የሴት እስረኞችን አያያዝ አስመልክቶ ችሎቱ የተሰየመ  ጉዳዬን ለማየት በድጋሚ ቀጠሮ ሰጥታል፡፡  

መጋቢት 2007
መጋቢት 21 - የሰው ምስክር ናቸው ተብለው የቀረቡ ሰዎችን ምስክርነት መስማት ተጀመረ ፡፡ ሁሉም ምስክሮች እቃዎች ሲፈተሹ ያየን ነን በማለት የተያዙ እቃዎቸን ከማየታቸው በስተቀር ያቀረቡት የተለየ የወንጀል ምስክርነት አልነበረም ፡፡ ምስክሮቹ ተከሳሾን መለየት ሲያቅታቸው የተስተዋሉ ሲሆን በመጀመሪያው ቀን 6 ሰዎች ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች ባልተካደ ነገር ላይ የፍርድ ቤቱም የተከሳሾችም ጊዜ መባከን አይገባውም እቃውም የእኛ አይደለም የሚል ቃል አልሰጠንም ስለዚህ የደረጃ ምስክሮች መስማት ይቁም ቢሉም ፍርድ ቤቱ ታዛቢዎቹን መስማት መቀጠል አለበት በማለቱ የተገኙ እቃዎችን ሲዘረዝሩ ከርመዋል ( መጽኃፍት ፣ መጽሄቶች፣ አርቲክሎች ላፕ ቶፕ ስልኮች እና ሲምካርዶች የመሳሰሉት ከፍተሻ ዝርዝሩ ውስጥ የተገኙ ናቸው)
መጋቢት 22 - ተጨማሪ 8 ምስክሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ቃላቸውን ሲሰጡ ውለዋል፡፡ ከነዚህ በላይ ምስክሮችን ማቅረብ ያልቻለው አቃቤ ህግ ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቁ ለመጋቢት 30 ቀጠሮ ተሰጥታል፡፡
መጋቢት 30 - አቃቤ ህግ ምስክሮቼ ጠፍተውብኛል፡፡ የሲዲ ማስረጃዎችንም የያዘው ሰው በአገር ውስጥ ስለማይገኝ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ አቅርቦ በመፈቀዱ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ ችሎቱ ተበትናል ፡፡
መጋቢት 25 - ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ይድረስ ለኢቢሲ ጋዜጠኞች የጻፈው ጽሁፍ ታትሞ ወጥቷል፡፡

ሚያዝያ 2007
ሚያዝያ 16-19  የ6ቱ ጦማርያንን እና የ3ቱን ጋዜጠኞች እስር አንደኛ አመት አስመልክቶ ለነጻነታቸው ዋጋ የሚከፍሉትን እናወድስ የሚል የሁለት ቀናት ማስታወሻ ተዘጋጀ፡፡ በማስታወሻው ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት ዝርዝር እና የተያዙበትን እለት የነበረውን ድባብ ያሳየ ሲሆን ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች በሁነቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል ፡፡  በዚሁ የማስታወሻ ዝግጅት ላይ የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የላኩት የአንደኛ አመት ማስታወሻም ተስተናግዷል፡፡

ግንቦት 2007
ግንቦት 2
በዞን 9 ወዳጆች አማካኝነት የተዘጋጀው ሁለተኛው የቤተሰቦቻቸውን ሸክም መጋራት የሚለው የአንድ ሳምንት ዘመቻ ለሁለተኛ ጊዜ ተካሄዷል፡፡
ግንቦት19-21 በነዚህ ቀናት በዋለው ችሎት ላይ ከፍተኛ መወዛገብ ያሳየው አቃቤ ህግ ሲዲዎቹን እንደማስረጃ ማስመዝገብ ባለመቻሉ እና ምስክሮችንም ማቅረብ ስላልቻለ ሲዲዎቹ ከማስረጃ ላይ አንዲወገዱ እንዲሁም ተጨማሪ ምስክሮችን ለማቅረብም የተወሰነው ጊዜ በቂ ሆኖ አልተጠቀመበትም በሚል ምክንያት ተጨማሪ እድል እንዳይሰጠው ተወስኗል ፡፡
አቃቤ ህግ አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ አለኝ ያለውን የሲዲ ማስረጃ አስመልክቶ ሌሎች ተከሳሾች ማየት አለባቸው ወይስ ፍር ቤቱ በጽህፈት ቤት ማየት አለበት የሚለውን ለመወሰን ሰኔ 8 ተቀጥሯል፡፡
በተመሳሳይ ቀን ችሎት ውስጥ አቤል ዋበላ ከዳኞች ጋር በነበረው አለመስማማት የተነሳ የችሎት መድፈር ጥፋተኛ ተብሎ ለቅጣት ለግንቦት 25 ተቀጠረ፡፡
ግንቦት 23 - ሥነ-ስርዓት የሚለው የጦማሪ አቤል ዋበላ ጽሁፍ ታትሟል፡፡
ግንቦት 25 አቤል ዋበላ በችሎት መድፈር በገደብ 4 ወር ተፈርዶበታል ፡፡

ሰኔ 2007
ሰኔ 8 - ፍርድ ቤት የቀረቡት 9 ተከሳሾች  ከብይን ለሃምሌ 13 የተቀጠሩ ፡፡ በእለቱም አንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን የሲዲ ማስረጃ በጽህፈት ቤት አይተን እንደማስረጃ ቆጥረነዋል፡፡ ለሌሎች ተከሳሾም መድረስ አይገባውም በማለት ችሎቱ ወሰነ

ሃምሌ 2007
ሃምሌ 1 ቀን 2007 ዓ/ም ባተጠበቀ ሁኔታ ሶስቱ ጋዜጠኞች እና ሁለት የዞን9 ጦማርያን ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መፈታታቸው ዜና ተሰማ ፡፡ በእለቱ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ እና ጦማሪ ዘላለም ክብረት ሲፈቱ በማግስቱ ጠዋት ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ እና ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን ተፈቱ፡፡





በተመሳሳይ ቀን በቀሪዎቹ 5ቱ ተከሳሾች ላይ ክሱ አንደሚቀጥል የመንግስት ወዳጅ የሆነው ሬዲዬ ፋና በድረ ገጹ አሳወቀ ፡፡
ሃምሌ 9-11 ለሶስት ቀናት የሚቆይ እስቲ አንነጋገር የማስረጃን ነገር በሚል የተዘጋጀው ዘመቻ ተካሄደ ፡፡ ይህ ዘመቻ ሃሳቡ ተከሳሾች ላይ ማስረጃ ተብለው የቀረቡ ጉዳዬችን ለአደባባይ ማብቃትና ቀሪ አራት ታሳሪዎች የሚከላከሉት ምንም ነገር እንደሌለ ለማሳወቅ የታለመ ነበር ፡፡
ሃምሌ 10 - ጦማሪ በፍቃዱ ቁዘማ፣ ከአቃቤ ሕግ ማስረጃዎች በፊት እና ጦማሪ ናትናኤል የዕለት ተዕለት ጥያቄዎቻችን ብይናቸውን አስመልክቶ የጻፋቸው ጽሁፎች ታተሙ፡፡
ሃምሌ 13 - ፍርድ ቤቱ የአንድ ምስክር ቃል ተገልብጦ አልደረሰኝም በማለት ብይኑን መስራት አለመቻሉን ገልጾ ጽሁፉ መገልበጡን ለማረጋገጥ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ ፡፡
ሃምሌ 22 - የተከሳሾች ጽሁፍ ተገልብጦ ማለቁን አረጋግጫለሁ ያለው ፍርድ ቤቱ ከጽህፈት ቤት በማስቻል በድጋሚ ለጷጉሜ 2 ቀጠሮ ሰጠ
ሃምሌ 25 - ጥቂት ስለማእከላዊ የሚል ጽሁፍ ታተመ፡፡

ሜ 2007

በአመቱ የመጨረሻ ሳምንት የመጨረሻ የእስር ሳምንታቸው ይሆናል ተብሎ ተስፋ ቢደረግም ፍርድ ቤቱ ዳኞች አልተሟሉም በሚል ሌላ ሰበብ ሁለተኛ እንቁጣጣሻቸውን በእስር እንደሚያሳልፉ ያረጋገጠውን የ31 ቀን ቀጠሮ በመስጠት ለመስከረም 27 ለአራተኛ ጊዜ በአጠቃላይ ደሞ ለ37ተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጠ ፡፡ 

Saturday, September 5, 2015

ግብታዊ ጩኸት፣ ለቅስፈት....

Non-Violence for Dummies!
ግብታዊ ጩኸት፣ ለቅስፈት....


ሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነን መሆኑ ታውቋል፡፡ ምርጫ እንደሚያጭበረብር ታውቋል፡፡ የሲቪል ማኅበራት ፓርቲዎችን ገቢ በማሳጣት፣ መሪዎቻቸውን በማሰር፣ ውስጣቸው ክፍፍል በመፍጠር እንደሚያዳክማቸው ታውቋል፡፡ ነፃ ፕሬሶችን እንደሚያደናቅፍ ታውቋል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ከነዚህ በላይ ሆኖ የሚያሸንፍበትን መንገድ (Strategy) መንደፍ አለበት፡፡ ነገር ግን ያልታወቀም ነገር አለ፡፡ ኢሕአዴግ አስካሁን አልተፈተነም፡፡ ለቀላሏ ፈተና (ድኅረ ምርጫ 97 ለገጠመው ተግዳሮት) የሰጠው ምላሽ ያልተመጣጠነ ነበር፡፡ እርግጥ ያ አጋጣሚ ተቃዋሚው ሰላማዊነቱን ያጣበት ነበር፡፡ የመንግሥት እርምጃ ግን የቻይናውን (የታይናንሜን ስኩዌር) እርምጃ ያስታውሰናል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት አደባባይ ወጥተው አንገባም ያሉትን ሰልፈኞች የቻይና መንግሥት በታንክ ሳይቀር ነው የበተነው፡፡ ኢሕአዴግ የደርግን ያክል ቢፈተን ከደርግ አይብስም ወይ? እነዚህን ያወቅናቸውን እና ያሳወቅናቸውን የኢሕአዴግ ባሕርያት ማሰላሰል የሰላማዊ ትግሉን መሥመር ለመወጠን ወሳኝ ቁምነገር ነው፡፡ እስከአሁን የነበረው ዓይነት ሁሉም በየፊናው ያሰኘውን የሚያደርግበት፣ ያልታሰበበት መፍጨርጨር በአጭር በአጭሩ ከመሰበር በቀር ምንም አልፈየዱም፡፡ ብዙ ጊዜ አምባገነኖች የሰላማዊ ትግልን አከርካሪ ለመስበር የሚጠቀሙበት ዘዴ ሰላማዊ ያልሆነ ነገር እንዲሰሩ ማድረግን ነው፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ሁለቱን እርከኖች (ማንቃት እና ማደራጀት) አልፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምር ሰላማዊነቱ እና ደኅንነቱ እንዴት ይጠበቃል?
ሐዲስ አለማየሁ ‹‹የልምዣት›› ላይ ‹‹የጨለማው ንጉስ›› የተባለ በበሻህ ዘለሌ የሚመራ ቡድን ፈጥረዋል፡፡ ቡድኑ ሕዝብ የበደሉ ባለሥልጣናትን እየገደለ፣ ለምን እንደተገደሉ የሚገልጽ ማስታወሻ ጽፎባቸው ይሰወራል፡፡ ኋላ ግን ቡድኑ ከበሻህ ዘለሌ ቁጥጥር ውጭ ሆነ፡፡ የቡድኑ አባላት መነሻቸውን ረስተው ገንዘብ ለመዝረፍ ተሰማሩ፡፡ ይህንን ቁንፅል የመጽሐፉን ታሪክ እዚህ መጥቀሴ የግብታዊ ርምጃን የመጨረሻ ውጤት ከዚህ የተሻለ የሚያሳይልኝ ምሳሌ ስለሌለ ነው፡፡


መጀመሪያ የብብቷን.......!
በተቃዋሚው ጎራ የተለመደ ድክመት አለ፡፡ ተቃዋሚው የቱንም ያክል በትንሽ አቅም ቢንቀሳቀስ፣ የሚጠብቀው ውጤት ብዙ ነው፡፡ ይህ የስስት ባሕሪ የያዘውን ጭምር ያሳጣዋል፡፡ በምርጫ 97 ተቃዋሚው ከመቼውም የበለጠ (31.6% ያህል) የፓርላማ ወንበር እንዳገኘ ኢሕአዴግ አምኖለታል፡፡ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ ሆኖም ተቃዋሚው ‹ኢሕአዴግ ምርጫውን ቢያጭበረብርስ በማለት አማራጭ ውጥን  (Plan B) ያላዘጋጀ በመሆኑ የያዘውን ይዞ ማልቀስ ሲኖርበት የያዘውንም አጥቷል› በማለት አቶ ግርማ ሞገስ ‹ሰላማዊ ትግል 101 ላይ› ይከራከራሉ፡-
‹‹በትግሉ ሜዳ መቆየት ያለብህ ያገኘኸውን ድል ሳትነጠቅ ተጨማሪ ድሎችን ማግኘት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም እንዳለህ እርግጠኛ ስትሆን ብቻ ነው፡፡›› (ገጽ 199)
‹‹....ተቃዋሚው የነበረውን የተሻለ አማራጭ በምርጫ ያገኘውን ፓለቲካዊና ድርጅታዊ ድል ከነእንከኑ መቀበል ነበር፡፡ (ገጽ 205)
የውሸት ምርጫ አምባገነኖች ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኛ የሚጠቀሙበት ‹ዕውቅና› መግዣ ነው፡፡ የፈለገውን ያክል ተፎካካሪዎቻቸውን ቢደፈጥጡም፣ እነርሱን መጣል የሚችል ሰላማዊ ስትራቴጂ መንደፍ የሚቻለውን ምርጫን አስታኮ ነው፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች የያዙትን ይዘው፣ በምርጫዎች መሐል ራሳቸውን ወንበር መነቅነቅ በሚያስችላቸው መንገድ ማደራጀት እና ማዘጋጀት አለባቸው-ከነፈተናው፡፡


‹‹ምን ተይዞ ጉዞ?››
ተቃዋሚው ዘንድ በችኮላ የሚወሰኑ ግብታዊ ርምጃዎች ለዘላቂ ክሽፈት መንስኤ እንደሚሆኑ ተመልከተናል፡፡ የተደራጀ እና የነቃ ማኅበረሰብ በሌለበት ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት-አንድም በሚገኘው ሰው ማነስ (ትግሉ የሕዳጣን እየመሰለ)፣ አንድም ለአገዛዙ ምት እየተመቸ ከሚጠራው የሚያባርረው ሰው እንዲበዛ ያደርጋል፡፡ (ከምርጫ 97 ወዲህ እንኳ አንድም ሰው ያልወጣባቸው ሁለት የአብዮት ጥሪዎች ተደርገዋል፡፡) በሌላ በኩል የተለያዩ አድማዎችን ለመጥራት ብዙ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ አብዮት ባለታክሲዎች ያደረጉት አድማ ወደር የለውም፡፡ ጆን ያንግ ላይ ‹አዲስ አበባ ሽባ ሆና ዋለች› ብለው ጽፈዋል፡፡በአምስት ሣንቲም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አገር ተንቀጠቀጠ፡፡ ይህንን እያስታወሱ የታክሲ ሥራ ማቆም አድማዎች ተጠርተዋል፡፡ ችግሩ ግን እነሱን የሚመለከት መነሻ አልነበረውም፡፡ እንዲያውም በድኅረ ምርጫ 97 የተጠራው በራሳቸው ተነሳሽነት በመሆኑ በከፊል ተሳክቷል፡፡ ግን ያለምንም ትርፍ ከ5 ቀናት በኋላ ወደነበረበት ቀስ በቀስ ተመልሷል፡፡ ለምን?፡- ሾፌሮቹ፣ ባለቤቶቹ፣ ረዳቶቹ ምን ይብሉ? ኤርምያስ ለገሠ (‹‹የመለስ ትሩፋት›› ባለው መጽሐፉ ላይ ) ‹ሥራው እንዲቀጥል ከመንግሥት ጋር መሞዳሞድ የጀመሩት ሱስ ያናወዛቸው ተራ አስከባሪዎች ናቸው› ይላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ድል አድራጊነት አድማው ከሽፏል፡፡ ጥቁር አሜሪካውያን በሞንትጎምሪ ከተማ (አላባማ)የጥቁሮችን መገለል በመቃወም በከተማ አውቶቡስ ላለመሳፈር ሲያድሙ፣ ጥቁሮች የሚጓጓዙባቸውን አማራጮች አመቻችተው ነበር፡፡ በአገራችን ሕወሓት/ኢሕአዴግን የኢኮኖሚ ትብብር ለመንፈግ ሲባል ‹ከነእከሌ አትግዙ› የሚሉ የአድማ ምክሮች ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ግን አልተሳኩም፤ ምክንያቱም ሸማቹ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ አድማዎች የሚጠሩ ከሆነ፣ ጉዳታቸው (ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው) አድማ መቺው ላይ ሳይሆን አምባገነኑ አካል ላይ መሆኑን (ወይም መሆን የሚችልበት መንገድ) ማረጋገጥ የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡


መውጪያ
‹‹ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ እንደማንማር ነው›› የሚለው አባባል የመጣው ለሰዎች የሚቀለው የሚያውቁትን መደጋገም ስለሆነና ያንኑ ስለሚያደርጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ እንኳን በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል፣ ልጅ ከአባቱ ሥልጣን የሚወስደው በጦርነት ወይም በኃይል ነው፡፡ (ታላቁ ንጉሥ ቀዳማዊ እያሱ በ17ኛው ክ/ዘመን መስክ ጉብኝት ደርሶ ሲመለስ ጎንደር በብዙ መልኩ ተቃውሳ ጠበቀችው፡፡ በዚያ ላይ የሚወዳት እቁባቱ ሞታለች፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ንጉሱ ጣና ደሴት ካሉ ገዳሞች ገብቶ መነነ፡፡ ልጁ ተክለሃይማኖት  አጋጣሚውን ተጠቅሞ ንግሥናውን አወጀ፡፡ ሆኖም ግን አባቴ ተመልሶ ንግሥናዬን ይቀማኛል በሚል ስጋት እዚያው ጣና ደሴት ላይ አስገድሎታል፡፡)
ይህ የታሪክ ዥረት ፈሶ ፣ ፈሶ እኛ ጋር ደርሷል፡፡ የእኛ ትውልድም፣ እንደቀድሞው ሁሉ በትረ-ሥልጣኑን በኃይል ከጨበጠው ፋይል ጋር ተፋጧል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹‹ዴሞክራሲ ማለት ሕዝቦች ከጦር ሰራዊት (የበላይነት) ነጻ ሲወጡ ማለት ነው፡፡ ይላል እንደ ኮስታሪካ የጦር ሰራዊታችንን በትነን እስካሁን (67 ዓመት)በሰላም መኖር ባይሆንልን እንኳን ጦር ሠራዊቱን፣ ፖሊስ እና የደህንነት አካሉን የማንፈራ እና የማናፍርበት እንዲሆን ብዙ መታገል አለብን፡፡ በመታደል የሚገኝ የለምና፡፡ ጥያቄው ከትግል ሒደቱ ‹‹ጨዋ›› ወይስ ‹‹ባለጌ›› ይወጣን ይሆን› የሚለው ነው፡፡ የተለመደውን የጦርነት ታሪክ እናስቀጥላለን ወይስ አዲስ ታሪክ ለመሥራት   ተዘጋጅተናል›


ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ እና የመጨረሻው ክፍል ነው፡፡
የቀደሙትን ጽሁፎች ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? ‹‹ሠላማዊ ትግል ስንል?›› ‹‹ከሕወሓት መማር›› እና 
የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ ማስፈንጠሪያዎቻቸውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ፡፡

Friday, September 4, 2015

የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ

Understanding Dictators
የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ
ጂን ሻርፕ የአረቡ አለም አብዮት የሚባለውን እንዲቀጣጠል ነዳጅ ጨምሯል የተባለለትን ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ›› የተሰኘ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ መጽሐፍ ውስጥ አብዛኛዎቹ አስረጂ ምሳሌዎች አምባገነኖች መሰረታቸው ሕዝብ መሆኑን ነው የሚነግሩን፡፡ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በተደጋጋሚ ‹‹ጭቆና የሚሸከመው ትከሻ ይፈልጋል›› የሚሉን ይህንን ነው፡፡ አምባገነኖች ሕዝብ ጭቆና ለመሸከም ትከሻውን እንዲሰጣቸው ብዙ መንገዶቸን ይጠቀማሉ፡፡ የ‹ሠላማዊ ትግል 101› ጸሐፊ ግርማ ሞገስ ሶስት ነገሮችን የጠቅሳሉ፡- እነዚህም ፈቃደኝነት፣ ፍራቻ ወይም ግዴለሽነት ናቸው፡፡ የሚኪያቬሊ ፍልስፍናም (The Prince ላይ እንደተገለጠ) ‹‹ነገሥታት በመወደድ ብቻ ሳይሆን በመፈራትም ነው የሚኖሩት፡፡›› ከተቻለ ወዶ እና ፈቅዶ የሚተባበር፣ የሚታዘዝና ለምዶበት የሚታመንላቸውን፤ ይህ ሲከብድ ትልቅ ሠራዊት በመገንባት ወይም የደህንነት መረባቸው ትልቅ፣ ብልህ እና አስተማማኝ እንደሆነ በማስወራት ሕዝባቸውን እያስፈራሩ ትከሻው ላይ ይወጣሉ፡፡ ይህ ብቻውን ስላማያቆማቸው ያገኙትን ሞኝ ለማታለል ተቀባይነት የሚያስገኝላቸውን ዘዴም መዘየዳቸው አይቀርም፡፡
መንግሥታት ሥልጣን ላይ የሚቆዩት የተወሰነ ቅቡልነት (Legitimacy) እስካላቸው ድረስ ነው፡፡ የቀድሞ ነገሥታቶቻችን ራሳቸውን ‹‹ስዩመ እግዚአብሄር ›› በማለት ቅቡልነትን ለማግኘት ይጥሩ ነበር፡፡ ጳጳሳቱም (ሲሦ ቀላዳቸውን ለማግኘት) ይህንኑ ለሕዝቡ ይሰብኩ ነበር፡፡ ለአሁኖቹ መሪዎች ይህ አያዋጣም፡፡ ሕዋሓት የዘውግ ብሄርተኝነትን (ዕኩልነትን አስጠብቃለሁ በሚል ስም) ቅቡልነትን ሊገዛበት ሞክሮ ነበር፡፡ ብዙም አላስኬደውም፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ልማታዊነት›› የተባለውን ጨብጧል፡፡ ድሃ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች እንደሚያዘናጉት በመረዳት ‹‹መጀመሪያ ዳቦ›› እያለ እስከዚያው የመጨቆኛ ካርድ ለማግኘት ይጥራል፡፡ በዚህ አካሄድ ዊኒ ማንዴላ ተናግረውታል እንደሚባለው ‹‹ወፍራም ባሪያ›› መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡  

አባገነኖች፣ ልዩ ፍጡሮች?
አምባገነንነት የሚፈጠረው ሰዎች ያልተገደበ ስልጣን ሲገጥማቸው ራሳቸውን መግዛት ስለሚከብዳቸው ነው፡፡ ብዙዎች የዓለማችን አምባገነኖች መጀመሪያ ምስኪን ነፃ አውጪዎች ነበሩ፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን እንኳን ብንወስድ ዐፄነት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የድሀ አባት ነበሩ፤ ያውም ከበዝባዥ ፊውዳል ባለሀብቶች እየዘረፉ ለድሀ የሚያከፋፍሉ፡፡ ኋላ በትረ ሥልጣኑን ሲይዙ ግን በገዳይነት የሚወዳደራቸው አጡ፡፡  ‹‹የአገሬ ሕዝብ ስራት ያዝ ብለው እምቢ አለኝ›› እያሉ በስርዓት ማስያዝ ስም ሕዝቡን ፈጁት፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን ውስጣቸው የነበረው ቅንነት እየወቀሳቸው ‹‹አቤቱ አምላኬ፣ እባክህን ግደለኝ እና ሕዝብህን ነፃ አውጣ›› እስከማለት ደርሰው እንደነበር እንግሊዛዊ እስረኞቻቸው ጽፈዋል፡፡ሰዎች ሰላማዊነትን መምረጥ የሚኖርባቸው ከራሳቸው ድብቅ አውዳሚነት ራሳቸውን መጠበቅ ስለሚከብዳቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ- አምባገነንነት ባሕል ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምባገነኖቻችን በቁልምጫ ነው የሚታወሱት፡፡ ‹‹መንጌ››ን መጥቀስ ይቻላል! አባወራዎች በቤተሰቡ ላይ ፍፁማዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ መምህራን በክፍል ተማሪዎቻቸው ላይ ፍፁም የበላይ ተደርገው ይሾማሉ፡፡ አለቆችም በምንዝሮቻቸው ላይ እንዲያው ናቸው፡፡ ሁሉም አቅሙ በፈቀደው ላይ ፍፁማዊ ኃይልን እና የበላይነትን መጠቀምን ባሕላችን ያበረታታል፡፡ ዘበኛው በደጅ ጠኚው ላይ፣ አሠሪው በሠራተኛዋ ላይ ኃያል ነው፡፡ ዕድሩ ስብሳቢው አይለወጥም፤ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ እስኪሞት አይሻርም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው ሊቀመንበር አይቀየርም በዚህ ባሕል ውስጥ እየኖርን የአገር መሪ ብንቀያየርም ‹‹ተረኛ ጨቋኝ›› እንጂ ዴሞክራሲን አናመጣም፡፡
የአምባገነኖች አንድነት
አምባገነን አገር ወይም ብሔር የለውም፡፡ ቋንቋ የለውም፡፡ ሁሉም ያልሠለጠኑ ሕዝቦች ውስጥ ያለ ዕዳ ነው፡፡ አማር ቦንጎ ጋቦንን ለ42 ዓመታት ገዝቷል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎችን ለቤተዘመዱ አከፋፍሏል፡፡ ልጁ እሱ ሲሞት ሥልጣኑን ወርሷል፡፡ ሴት ልጁ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ነበረች፡፡ ባሏ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡ በስሙ ያልተሰየመ ነገር የለም፤ ቦንጎ ዩኒቨርስቲ፣ ቦንጎ አየር ማረፊያ፣ ቦንጎ ሆስፒታል.... ሌላው ቀርቶ የትውልድ ከተማው ቦንጎቪል ተብላለች፡፡ እኛም አገር ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እስከ መለስ ዜናዊ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡
የኮትዲቯሩ ሆፎኤት-ቦይኚ 6 ጊዜ የፕሬዚዳንት ምርጫን አሸንፏል፡፡ ያውም 99.7 በመቶ አማካኝ ድምፅ አግኝቶ! የአንዱን አምባገንነት ታሪክ መስማት፣ የሌላኛውን እንደመስማት ነው፡፡
አምባገነኖች ሥራቸውን ልባቸው ስለሚያውቀው ይፈራሉ፡፡ የደህንነት ሠራተኞችም ፍርሐታቸውን ለማረጋጋት የውሸት መረጃ ይሰጧቸዋል፡፡ የዩጋንዳው ኢዲ አሚን ዳዳ ለምሳሌ ‹‹ሕዝቡ በፕሬዚዳንቱ ፍቅር አብዷል›› የሚል የደኅንነት ሪፖርት ደርሶት እንደነበር ተነግሯል፡፡  አሁን፣ አሁን የአገራችን ባለሥልጣኖችም በጋዜጣ መግለጫዎቻቸው የሚያሳዩት ባሕሪ እንዲህ ዓይነት ሪፖርት የደረሳቸው በሚመስል መልኩ ነው፡፡
የራሺያው የቦልሼቪኮች ፓርቲ (እ.ኤ.አ በ1917 ጀምሮ እስከ 1940 ብቻ) በ23 ዓመታት ውስጥ ከ24 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ የቀረው አንድ ጆሴፍ ስታሊን ብቻ ነበር፡፡ 8ቱ ተገደሉ፣ 7ቱ ‹‹በተፈጥሮ አጋጣሚ ሞቱ›› ተባለ፣ 7ቱ ‹‹የደረሱበት ጠፋ›› ተባለ፣ አንዱ ታሰረ፡፡ ቀሪው አንድ አምባገነን ብዙ ሚሊዮኖችን ፈጀ፡፡ ይህንን ስታሊኒስታዊ አመራር (ተቀናቃኞችን ማጥፋት) ከልባቸው ያሳደሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንደስታሊን ማዕከላዊ ኮሚቴውን ባዶ ከማድረግ ይልቅ ፣ ታዛዥ አላዋቂዎች እንዲሰበሰቡበት አደረጉ፡፡ ልዩነቱ ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን ሞት ቀደማቸው፡፡ የቀሩት አባላት የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ ስለዚህ የሟቹን ሌጋሲ (‹‹ትሩፋት››) እናስቀጥላለን በማለት በመለስ የተሾሙለትን ዓላማ እያስፈፀሙ ነው፡፡

ምርጫ በአምባገነኖች አገር
በአምባገነኖች አገር ምርጫ ማለት አሸናፊውን (ገዢውን) አጅቦ ለድል ማብቃት ማለት ነው፡፡ ወይም አምባገነኖቹ የሚፈልጉት እንደዚያ እንዲሆን ነው፡፡ The Dictator የተሰኘው ፊልም ነገሩን ግልጽ አድርጎታል፡፡ ሳላዲን የተባለው የዋዲያ መሪ የራሱን ኦሎምፒክ አዘጋጅቶ፣ ራሱ ተወዳድሮ ያሽንፋል፡፡ ውድድሩን ተኩሶ የሚያስጀምረው ራሱ ነው፡፡ የሚቀድሙትን ተወዳዳሪዎች እየተኮሰ ይጥላቸዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ራሱ ያሸንፋል፡፡ ምርጫ ለአምባገነኖች እንዲህ ቀላል ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ አሸንፌ ድሌ ይከበርልኛል፡፡ ብለው ከሚያስቡ የሳላዲንን ሽጉጥ የጨበጠ እጅ ቢይዙ የተሻለ ያዋጣቸው ነበር፡፡ የአምባገነን መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአምባገነንነት መንግሥት እጅ መያዝ አለባቸው፡፡
አገዛዙ ወይም የአገዛዙ ልሒቃን በምን ጥገኛ እንደሆኑ መለየት እና ያንን መንፈግን እንደትግል መሣሪያ (መደራደሪያነት) መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አምባገነኖች ተፎካካሪዎቻቸውን የሚጥሉት በየትኛው እጃቸው ነው? የኃይል ምንጫቸው ምንድን ነው? ሠላማዊ ትግሉ ሊሠራው የሚጠብቀው የቤት ሥራ ነው፡፡ …ይቀጥላል፡፡

ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የቀደሙት ጽሁፎች ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? ‹‹ሠላማዊ ትግል ስንል?›› ‹‹ሓት መማር›› ማስፈንጠሪያዎቻቸውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ፡፡

Thursday, September 3, 2015

ከሕወሓት መማር

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ What to Learn From TPLF
እስከዚያው ከሓት መማር የሚቀናቀኑትን አካል በቅጡ መረዳት ግማሹን መንገድ መምጣት ነው፡፡ የሕሓትን ታሪክ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ወዘተርፈ መለየት ለሠላማዊ ትግላችን ሰፊ አስተዋፆ ይኖረዋል፡፡

ትምህርት አንድ
ሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት በአውራ ፓርቲ ሥም፣ አሀዳዊ ፓርቲ ስርዓት እየዘረጋ ነው፡፡ መላ አገሪቱ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ በአንድ አይነት አስተሳሰብ የተቃኙ፣ የአንድ ፓርቲ ሰዎች እንዲሞሉት አድርጓል፡፡ ይህ አመል ኢሕአዴግ የመንግስት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የመጣ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሕሓት ከቀድሞ ወዳጁ ሻዕቢያ የተማረው ‹‹በአንድ ሜዳ ሁለት ኃይል አይኖርም›› የሚል አባባል አለው፡፡ በዚህ ፍልስፍና ሻዕቢያ ጀብሃን አጠፋ፡፡ ሕወሓት ደግሞ ሕግሐኤ፣ ኢዴኃ (EDU)፣ ኢሕአሠን በኃይል ደምስሷል፡፡ ሕዋሓት ደርግን ከመደምሰሱ በፊት አምባገነኑን ደርግን እንወጋለን ብለው ግን ደግሞ ከሱ በጥቂቱ የተለየ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዘው ከጎኑ የተሰለፉ ኃይሎችን አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህ የጫካ አመሉ ያደገበት ሓት (ኢሕአዴግን ለብሶ) ከተማ ሲገባ የቱንም ያክል ‹‹ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው›› እያለ ቢፎክርም፣ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን መታገስ አልቻለም፡፡
ሓት/ኢሕአዴግ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን ቀርቶ በውስጡ የሚከሰቱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን እንኳን መታገስ አይችልም፡፡ ትግል ላይ በነበሩት ጊዜ የተነሳው የመጀመሪያው ሕንፍሽፍሽ (ቀውስ) ‹የአሽዓ (አክሱም፣ ሽረ እና አደዋ) ሰዎች የሥልጣን የበላይነት (ልክ አሁን የትግራይ ልሒቃን የሥልጣን የበላይነት በፌደራል መንግስቱ ውስጥ በዛ እንደምንለው) ፓርቲያችን ላይ እየታየ ነው› የሚል አቤቱታ ያቀረቡ አባላቱን በማስወገድ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በ1993 በተፈጠረው ቀውስ ደግሞ የሉአላዊነት ጥያቄ ያነገቡ አባላቱን የውስጥ ሕገ-ደንቡን (ሓትን በማዳን ስም) ሽሮ፣ ምርጫ ቦርድ ባለበት አገር በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ማሕተም የተፃፈ ደብዳቤ ነበር ያሰናበታቸው፡፡ ይሕ ባሕል ከጫካ ተከትሏቸው የመጣ ባሕል ነው፡፡ የውብማር አስፋው ‹ፊኒክሷ ሞታም ትነሳለች› ባለችው መጽሐፏ እንዲህ ትለናለች፡-
‹‹ሓት ደንብ መሠረት አንጃ መፍጠር እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ያስከትል ስለነበር፣ የሓት ፖሊት ቢሮ ይህንን ሲያስቀምጥ በማኅበሩ አመራር ውስጥ የማይፈልጋቸውና የሚጠላቸው የአመራር አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመለክት ነበር፡፡ . . . ›› (ገጽ 112፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ እንዳጣቀሰው)
እነዚህ ችግሮች ስር ሰደው ነው የአሁኑን አማራጭ ሐሳብ የማይቋቋም ኢሕአዴግ የፈጠሩት፡፡ ይህንን የ1993ቱ የሓት ቀውስ ወቅት ከፓርቲው ከወጡት ታጋዮች መካከል አረጋሽ አዳነ ለጥሕሎ መጽሔት በሰጠችው ቃለምልልስ ከስር ከስሩ ባለመታረሙ የመጣ ጣጣ ነው በማለት ከታሪክ እንድንማር ትመክረናለች፡-
‹‹እነዚህ ሁሉ [ጥያቄዎችን በኃይል የመጨፍለቅ] ችግሮች ገና ድሮ ከመፈጠራቸው፣ [ስ]ር ከመስደዳቸው በፊት ቀደም ብለን ለዚህ ሁሉ መሰረት የሆኑትን ችግሮች . . . አስተውለን ከስር ከስር ወይም ደረጃ በደረጃ እየታገልናቸው ያለመምጣታችን አሉታዊ ፍፃሜ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡››
(ገጽ 77፣ ዮናስ በላይ፣ የትግራይ ሕዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ)
የቀድሞ የሓት ታጋዮች ፀፀትም ሆነ የአሁን ታሪኩ የሚያስተምረን ዴሞክራሲ መንገድ እንጂ መዳረሻ አለመሆኑን ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያልመጣ ኃይል ዴሞክራሲን ሊያመጣ አይችልም፡፡

ትምህርት ሁለት
ሓት ደርግን ወግቶ ለድል እንዲበቃ በተለይ ሁለት ዘዴዎች ረድተውታል፡፡ ሠላማዊ ታጋዮች እነዚህን ዘዴዎች በራሳቸው መንገድ ተርጉመው ሊጠቀሙበት የችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ደርግን እራሱን መጠቀሚያ ማድረግ ነው፡፡  ሓት የደርግን ክፋት ለራሱ ተቀባይነት መግዣ በማድረግ ተጠቅሟል፡፡ ለምሳሌ በትግል ወቅት የማረካቸው ወታደሮች ‹ተሃድሶ› ካሰለጠናቸው በኋላ ሁለት አማራጭ ይሰጣቸው ነበር፡፡ አንድ ከጎን ተሰልፈው ደርግን እንዲወጉ አልያም ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፡፡ የትኛውንም ቢመርጡ ሕዋሓት ያተርፋል፡፡ ተመላሾቹ የገጠማቸውን ለቀሪው ወታደር ስለሚናገሩ ወታደሩ በወኔ ለመዋጋት ይለግማል እነርሱም ተመልሰው ሓትን አይወጉም፡፡ የደርግ አባል የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ደበላ ደንሳ ተመላሽ ‹‹ምርኮኞችን መልሶ ማዝመት›› ደርግን እንዲሸነፍ ያደረጉት ካሏቸው 13 ነጥቦች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ሠላማዊ ታጋዮች ተቀናቃኜ የሚሉትን አካል ከጎናቸው ማሰለፍ የሚችሉበትን ስልት መንደፍ አለባቸው፡፡ በሐሳብ በመብለጥ! የሓት ወገን የነበሩ በመሆናቸው ብቻ በለውጡ እንደማይቀጡ ዋስትና ይፈልጋሉ፣ ሁለተኛ በለውጡ ሐሳብ መማረክ አለባቸው፡፡
ሁለተኛው የሕዋሓት ብልሐት ደርግን የሚዋጋበትን መሣሪያ ከራሱ ከደርግ ማግኘት መቻሉ ነው፡፡ የአሁን ሰላማዊ ታጋዮች ሕዋሓት (ኢሕአዴግን ለማሸነፍ ወይም በዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ስርዓት ለመተካት የራሱን መሳሪያዎች መጠቀም መቻል አለባቸው፡፡) ሕገ-መንግሥቱን፣ የመንግሥት መዋቅሮችን፣ የመንግሠት ሠራተኞችን፣ ወዘተርፈ ለሠላማዊው ትግል የሚፈይዱበትን ዘዴ መቀየስ ይበጃል፡፡

ትምህርት ሦስት
ሓት ትግሉ ሕዝቡ ውስጥ ስር እንዲሰድ ከረዱት መንገዶች መካከል ሳይጠቀስ የማይታለፈው ኪነትን መጠቀም መቻሉ ነው፡፡ በተለይ በዘፈን ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በወኔ የሚቀሰቅሱ፣ ሕልም እንዲያልሙ የሚረዱ እና የራሳቸውን የዘመን ወግ (Folklore) መፍጠር የቻሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ‹ንገሪን እንደ ሐለፋይ . . . › የሚለው (በትርጉሙ ‹‹ንገሪኝ እስቲ እናቴ፣ ወዴት ነው የሄደው አባቴ?›› የሚል) የማሚት እና ብርሃነ (ሐለፋይ) የቅብብሎሽ (duet) ዘፈን፣ አሳዛኝ እና የተከፈለው መስዋዕትነት ለሚመጥነው ዋጋ መሆኑን የሚዘክር ዘፈን ነው፡፡ ይህንን ዘፈን ትግሪኛ ተናጋሪ ጓደኞቼን ‹‹ንገሪኝ እስኪ እናቴ፣ ለዚህ ነበር ወይ የሞተው አባቴ?› በሚል ምፀት እንዲቀይሩት ጠይቄያቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ . . . ጥበብ (ኪነ ጥበብ ይሁን ሥነ ጥበብ) በጥቅሉ ከአመፃዊ ይልቅ ለሠላማዊ ትግል መሣሪያ መሆን የችላል፡፡ በዚህ ረገድ በዓለማችን ብዙ ትምህርት የሚሆኑ ሥራዎችን አይተናል፡፡ የማርያ ማኬባ ፀረ-አፓርታይድ ዜማዎች፣ የቦብ ማርሌይ የነፃነት ሬጌምቶች፣ . . . እና በአገራችንም የቴዲ አፍሮ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ከነዚሁ ተርታ ይመደባል፡፡ የቀድሞዎቹን የጦር ሽለላዎችና ቀረርቶዎች በመጠቀም ያውም ለዚህ ትውልድ ጆሮ በሚስብ መልኩ በሂፕሆፕ (ራፕ) መልኩ፣ የለውጥ ሰባኪ ግጥሞች ተጽፈውለት መሥራት ይቻላል፡፡ ኬናን የተባለ ካናዳ-ሶማሊያዊ ራፐር ይህንን አሳይቷል፡፡
በጥበብ ረገድ የሚደረጉ ሠላማዊ ተጋድሎዎች በዘፈን ብቻ ሊገደቡ አይገባም፡፡ በሥዕል፣ በሥነፅሁፍ፣ በቲያትር፣ ፊልም፣ ካርቱኖች እና ሌሎችም አማራጮች ቀርበው ሁሉንም እንደየፍላጎቱ ሊደርሱት ይገባል፡፡

…ይቀጥላል፡፡

ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ 

Wednesday, September 2, 2015

ሠላማዊ ትግል ስንል?

ሠላማዊ ትግል ደርዘ ብዙ ትንቅንቅ ነው፡፡ አንዳንዶች ‹ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ መጠቀም ነው› ብለው የምናሉ፤ ነገር ግን በዚህ የማይወሰንበት ጊዜ አለ፡፡ ሠላማዊ ትግል ከነፍስ ማጥፋት፣ አካላዊ ጉዳት ከማድረስ እና ንብረት ከማውደም መቆጠብን ብቻ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ‹ሠላማዊ› የተባለው፡፡ ለምሳሌ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (Civil disobedience) አንድ የሠላማዊ ትግል ዘርፍ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) ‹‹ኢ- ፍትሐዊ ሕጎች፤ ሕጎች አይደሉም›› ይል ነበር፡፡ በዚህ ፍልስፍና ነው ለሕግ አለመታዘዝ የሚወለደው፡፡ ለምሳሌ በአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ ያሉትን አግላይ ሕጎች በሠላማዊ ትግል ለመቃወም የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ከነደፋቸው ስልቶች አንዱ ለአግላይ ሕጎች የማይታዘዙ (እና በዚያ ሳቢያ ለመታሰር ፈቃደኞች የሆኑ /እስር እንደትግል/ ) ሰዎችን መልምሎ ማሰማራት ይገኝበታል፡፡ ተግባሩ ሠላማዊ ነው ግን ሕጋዊ አይደለም፡፡ ሕጉ ኢ-ፍትሐዊ ነውና፡፡

በኢትዮጵያ፣ በአብዛኛው የሚስተዋሉ ከኢ-ፍትሓዊ ሕጎች ይልቅ የሕግ የበላይነት ማጣት ነው፡፡ የማበላለጥ ጉዳይ ሆኖ እንጂ ኢ-ፍትሓዊ ሕጎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብን ለማደንቆር (እንዳይነቃ) የወጣው የመያድ ሕግ እና ሁሉን ነገር ሽብር ያሰኘው የፀረ- ሽብርተኝነት ሕግጋት በዚህ ረገድ ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡ 
ሆኖም የሕግ የበላይነትን ባለማክበር የሚፈፀሙ ጥፋቶች ይህንን አምባገነን ስርዓት የበለጠ ይገልፁታል፡፡ ለምሳሌ መደራጀት ይፈቀዳል (በሕግ)፣ በተግባር ግን ይደናቀፋል፡፡ ይህንን በሠላማዊ መንገድ መታገል የሚቻለው ከስርዓቱ ጆሮ ጠቢዎች በላይ የሆነ (ነገር ግን በሕግ ያልታወቀ) ሠላማዊ ድርጅት በመፍጠር ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት በሕግ ተፈቅዷል፤በተግባር ግን አይቻልም፡፡ ከቴክኒካዊ ማደናቀፊያ እስከ ጋዜጠኛ ማሰር በሚደርሱ ሕገወጥ ተግባሮች ነው ይህ የሚሆነው፡፡ ዘመኑ ይህን ለማሸነፍ ምቹ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአፈናውም ከእስሩም በላይ የሆነ (በእነዚህ እርምጃዎች የማይደናቀፍ) የመረጃ ማቅረብ ወይም ሕዝባዊ ንቃት የመፍጠር ስራ መስራት ድርጅታዊ መረብ መፍጠር ይቻላል፡፡ የአገራችን የሰላማዊ ትግል ፈቀቅ አለማለት አማራጭ መንገድ ከማጣት ይልቅ ያለመፈለግ የፈጠረው ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ሠላማዊ ትግል አልፈልግም›› እያለ ቢሆንም እየሄዱ ፊት ለፊት መላተም ብቻ (አስፈላጊ ቢሆንም) በቂ አይደለም፡፡ አስፈላጊነቱ የስርዓቱን ሕገ-ወጥነት ለማሳየት ሲሆን በቂ የማይሆነው በዚህ የኢሕአዴግ ባሕሪ ፊት ለፊት መላተም ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ነው፡፡ ፊት ለፊት መላተም ሲበዛ፣ መጠቃት ስለሚበዛ ሰዎች ትግሉን ከመቀላቀል ይልቅ በፍርሓት እንዲርቁት ያደርጋል፡፡ ይህን ችግር፣ በትጥቅ ትግል ቋንቋም ቢሆን ሲያስረዱ አቶ ገብሩ አስራት (‹ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ › ላይ) እንዲህ ብለዋል፡፡
‹‹አንድ አባት ገበሬ ‹‹ልጆቼ እንታረዳለን፣ መሬት ቀውጢ ትሆናለች እያላችሁ አትቀስቅሱ፡፡ የዚህ ዓይነት ቅስቀሳ ሰው ወኔው እንዲሞት፣ ተስፋ እንዲቆርጥና አንገቱን እንዲደፋ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እናቸንፋለን፣ ተቃርበናል፣ አይዟችሁ፣ በርቱ፣ ብላችሁ ብትቀሰቅሱ ይሻላል›› ብለው መክረውን ነበር፡፡››
ቢያንስ በእኔ እምነት፣ ያውም ለቆረጠ እና ዓላማውን በቅጡ ለሚያውቅ ሰው ሠላማዊ ትግል ከአመፃዊ ይልቃል፡፡ እርግጥ የፍትሕ እጦት ትውልድ እየበላ የምንታገስበት አንጀት አይኖረን ይሆናል፡፡ ሆኖም አመፃዊ ትግል ፍትሕ የምናገኝበትን መንገድ ማሳጠር አይችልም፡፡ የካርል ማርክስ ‹‹There is no short cut to history›› (የታሪክ አቋራጭ መንገድ የለም ብሒል) እዚህ ይሰራል፡፡ ሚስተር ኪንግ በሠላማዊ ትግል ጎዳና ሦስት ደረጃዎች አሉ ይላል፡፡ መንቃት (Awareness) ፣ መደራጀት (Organize) እና መተግበር (Action) በቅደም ተከተል የሚመጡ የሠላማዊ ትግል ሒደቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡  የመጀመሪያዎቹ ሁለቱን (ምንጬ አጠገቤ ስለሌለ) አቀያይሬያቸው ይሆናል፡፡ አሁን ችግር የሆነብን ተግባር ተግባሩ እየቀደመ ነው፡፡ ጥቂት የነቁ እና የተደራጁ (ሁለቱንም ያሟሉ) አደባባይ ሲወጡ ወይም በሆነ የትግል ተግባር ሲጠመዱ ገዢው በቀላሉ ይጨፈልቃቸዋል፡፡ ለተመልካችም ሕዳጣን ያስመስላቸዋል፡፡ በሠላማዊ ትግል ሕዝብ ኃይል የጨበጠውን ገዢ የሚያሸንፈው በብዛት ነው፡፡ ብዙዎችን በኃይል መጨፍለቅ አይቻልም፡፡ እንግዲህ ስለመደራጀት ቀደም ሲል ለመጥቀስ ሞክሬያለሁ፤ አስፍቶ ማሰብ የእያንዳንዳችን ቀጣይ ድርሻ ይሆናል፡፡

መንቃት ለምንና ለማን?
‹ለውጥ› የሚፈልጉ ለውጥ አማጪዎች (Activists) ሕልማቸውን ብቻቸውን ይዘውት ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ ለሌሎች ማጋራት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ነው ተከታይ ማፍራትም ሆነ፣ ያፈሩት ተከታይ ሕልማቸውን ማስቀጠል የሚቻላቸው፡፡ ሕልማቸው ከራሳቸው አልፎ ሌሎች ላይ መጋባት ከቻለ ነው ከራስ ስዩምነት ወደ ሕዝበ ስዩምነት መሸጋገር የሚችሉት፡፡ ብዙኃን የሚመሩት/የሚሳተፉበት ትግል የመክሸፍ እድሉ አነስተኛ ነው፡፡ የ1953ቱን ሰዓረ መንግስት እንደምሳሌ እናስታውሰው፡፡ በወቅቱ የንጉሡ ደጋፊዎች እና የስዓረ መንግስቱ ደጋፊዎች ያደረጉትን ውጊያ ጣልያናዊው አንጄሎ ዴል ቦካ (la negus ባሰኘው መጽሐፋቸው) እንዲህ ተርከውታል፡-
‹‹ለሰዐታት የዘለቀ ውጊያ መንገዱ ላይ ተካሂዶ ነበር፤ ሕዝቡ ግን በወታደሮቹ መካከል የነበረውን ጦርነት ያለውገና (indifference) ይመለከተው ነበር፡፡›› (እንግሊዘኛው ትርጉም ገጽ 260)
በዚህ ታሪክ የምናስታውሰው ብዙኃኑ ለአመፃ የሚኖረውን ምላሽ ብቻ ሳይሆን ውጊያው ለምን እየተካሄደ እንደሆነ እንኳን ግንዛቤ እንዳልነበረው ነው፡፡ ደራሲው ሲቀጥል፡-
‹‹ . . . ግርማሜ ንዋይና ወርቅነህ ገበየሁ [የወቅቱ የደኅንነት ሹም]፣ ሁለቱም የአሮጌው መንግስት መውደቅ ብዙ ነገር ማግኘት እንደሚችል በቂ ግንዛቤ አለው ብለው የአዲስ አበባን ሕዝብ በመገመታቸው የምር ስህተት ፈፅመዋል፡፡››
ይሁን እንጂ የንጉሡ መንግሥት ከዚያ በኋላ የቆየው 13 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ያ በኢትዮጵያ ታሪክ በአግባቡ የተደራጀ እና ዘመናዊ ሠራዊት እና የደኅንነት ተቋም የመሰረተው የመጀመሪያው መንግሥት የወደቀው ያለመሣሪያ ጩኸት ነው፡፡ በሕዝቡ መንቃት እና በሐሳብ መበለጥ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹ሕዝቡ/ተማሪዎች ‹‹መሬት ላራሹ›› ሲሉ በወቅቱ መሬት የባላባቶች በመሆኑ መንግስት በሐሳብ ተበለጠ . . . ወደቀ› ይላል፡፡ አንጄሎ ዴል ቦካ ለዚህ ለውጥ የስዓረ መንግስቱ ሙከራ አስተዋፅዖ እንደነበረው አልሸሸገም፡፡ ከሙከራው በኋላ ሕዝቡ ነቃ ይላል፡-
‹‹ [ከዚያ በፊት የነበሩት] ሌሎች አማፂዎች፣ እነባልቻ፣ ጉግሳ ወሌ፣ እና ኃይሉ ተ/ሃይማኖት በማዕከላዊው ኃይል ላይ ያመፁት በጥላቻ፣ vendetta ወይም ምኞት ብቻ ተነድተው ነበር፡፡ ለአገሪቱ ያቀረቡት አማራጭ ራዕይ አልነበራቸውም፡፡›› (ገጽ 264)
የስዓረ መንግሥቱ ሞካሪዎች ግን ነበራቸው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ያንን ራዕይ ከአፈሙዝ ፉክክሩ ነጥለው መመልከት ችለዋል፡፡ በወቅቱ አመፁን የደገፉ 200 ተማሪዎች ሰልፍ ወጡ እና ከትምህርታቸው ታገዱ፡፡ ቆይተው ግን ይቅርታ ጠየቁና ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ፡፡ እኔ የቅድመ እና ድኅረ ምርጫ 97ን ጉዳይ እንደዚህኛው ሰዓረ መንግስት ሙከራ ነው የምመለከተው፡፡ ያኔ ተማሪዎቹ ይቅርታ ጠይቀው ትምህርት ቤት ሲመለሱ የተከሰተው ዝምታ የተቀረፈው የአብዮቱ ሰሞን ነው፡፡ ዝምታቸው የተገፈፈው ሕዝባዊ ንቃቱን ተከትሎ ነው፡፡ ሕዝብ የነቃ ለታ ምንም እንኳን ወታደራዊው ጁንታ (ደርግ) ቢነጥቃቸውም ለውጥ መጥቶ ነበር፡፡ አሁን ሕዝብ መንቃት ያለበትን ያህል ሲነቃ ለውጥ ይመጣል፡፡ እኛ ዘብ ሆነን መጠበቅ የሚኖርብን የደርግ ዓይነቱ የለውጥ ሌባ እንዳይዘርፈን ነው፡፡
…ይቀጥላል፡፡

ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

Tuesday, September 1, 2015

‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››?

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ
ሐምሌ 27/2007 ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ቀናኢ ፍትሕ ለሆኑ ሰዎች በሙሉ የመርዶ ቀን ነበር፡፡ ስለ ሠላማዊነታቸው የተመለከታቸው በሙሉ የፈረደላቸው፣ ባንድ ወቅት መንግስትም በወኪሉ በኩል ሲደራደራቸው የነበሩ፣ ለሦስት ዓመታት ያክል በሕግ የበላይነት አምነው ችሎት ፊት የሠላማዊነታቸውን ማስረጃ ሲደረድሩ የቆዩት የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ‹‹ኮሚቴዎች›› (በተለምዶ የሚጠሩበት ስማቸው) እስከ 22 ዓመት የሚድረስ የጽኑ እስራት ፍርድ ተጣለባቸው፡፡ ይህንን ዜና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ከ7፡30 የቀን ዜና እወጃ ጀምሮ ሲለፍፈው ነበር፡፡ ከዜናው ጋር በማነፃፀሪያነት የቀረበው ሌላ ዜና ግን ግቡን ስላልመታ ይመስላል ማታ አልተደገመም፡፡ ይህንኛው ዜና በተመሳሳይ አንቀፅ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለተፈረደባቸው ሰዎች ነው፡፡ እነዚህኞቹ መሣሪያ ታጥቀው የተወሰኑ ሰዎችን ገድለዋል፡፡ሆኖም እንደ ኢብኮ ዘገባ ‹‹የቅጣት ማቅለያ በማስገባታቸው›› 14 ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ዜናዎቹን ያዳመጡ ሰዎች ግን ማነፃፀር የቻሉት የሠላማዊነት ቅጣት መክበዱን ነው፡፡

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ"Military and militarism in Africa: the case of Ethiopia" ባሰኙት ጥናታቸው ላይእንዲህ ይላሉ፡-

‹‹በመካከለኛውዘመን እንዳየነው [ጨዋ] ማለት መሣሪያ ታጣቂ ማለት ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ትርጉሙ ተለውጦ መልካም ፀባይ ያለው ማለት ሆነ፡፡በተመሳሳይ፣ የቃሉ ተቃራኒ የሆነው ‹‹ባለጌ›› የሚለው ቃልም የሚወክለው ጭሰኛውን (ማለትም መሣሪያ የማይታጠቀውን) ነበር፡፡ አሁንየዚህም ቃል ትርጉም ተለውጦ መጥፎ ፀባይ ያለው ማለት ሆኗል፡፡›› (እራሴው እንደተረጎምኩት)

እንግዲህ ኢሕአዴግም የሚያስበው በቀደመው ዘመን የ‹ጨዋ› እና ‹ባለጌ› ትርጉም ነው ማለት ነው፤ ለእርሱ መሳሪያ ከታጠቀ ይልቅ ሠላማዊ ይባልግበታል፡፡ (‹ይባልግበታል› በአሁኑ ትርጉም!) ስለዚህ አቀጣጡም በዚያው መሠረት መሆኑን መግቢያ አንቀፁ ያመለክታል፡፡
የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ገዢዎች (‹አመራሮች› አላልኩም፤ አይመጥናቸውም) የመንግስትን ስልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን (ለሁለት ዐሥርት ዓመታት) ሠላማዊ ትግሎችን በፅኑ ተቃውመዋለል፡፡ እንዲያውም ‹‹የሚችለን ካለ በትጥቅ ትግል ይሞክረን››የሚል መፈክር በተደጋጋሚ አስደምጠዋል፡፡ ዓላማቸው ግልፅ ነው፡፡ ያዋጣናል፣ እናሸንፍበታለን የሚሉትን የትግል ሜዳ እየመረጡ ነው፡፡የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችስ? ገዢው በመረጠላቸው ሜዳ (battlefield) ቢገጠሙት ይሻላል ወይስ ሰላማዊነትን የሙጥኝ ቢሉ? የትኛው ያዋጣል? የትኛው ይቀላል? ከሕዋሐት ምን መማር ይቻላል? አምባገነኖች እንዴት ሥልጣን ላይ ይሰነብታሉ?
ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመፈለጌ በፊት ነገሩ ሁሉ ለለውጥ ነው እና በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ‹ለውጥ› የሚባለውን ነገርልበይን፡፡ ‹ለውጥ› ማለት በዚህ አገባቡ ‹ወደ ሕዝባዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚደረገው ሽግግር› ነው፡፡

Why Not Violence?

አመፃዊ የትግል ስልት ያዋጣል?
ሠላማዊ ያልሆነ ትግል በሙሉ የትጥቅ ትግል አይደለም፡፡ አመፃዊ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ከትጥቅ ትግል ወዲያ ሰላማዊ የማይባሉ ስልቶችንም እንዲያካትትልኝ ስለፈለኩ ነው፡፡ በዚህ መስፈርት አመፃዊ ትግል በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከአገሪቱ ታሪካዊ ሁነትም፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም በመነሳት ያዋጣል ወይ የሚልውን እንጠይቃለን፡፡ ለዚህ ጥያቄ በዚህ ጽሑፍ ሰጥቼ የማልፈው ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የሚመጡልኝን መልሶች ነው፡፡


     1ኛ- የዴሞክራሲ መንገድነት

 ዴሞክራሲ በየትኛውም መመዘኛ መንገድ እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ ይህም ማለት አንድ አገር የሆነ የጊዜ ነጥብ ላይ ‹ዴሞክራሲያዊ ሆነ፤ በቃ አበቃ! › የሚባልበት ፈሊጥ የለም፡፡ዴሞክራሲያዊነት ማለት ሁሉንም ሕዝባዊ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ (በብዙኃን አመራርና ሕዳጣን መብት ጥበቃ፣ በሕግ የበላይነት፣ በወቅታዊ እና ነፃ ምርጫ . . .) መፍታት መቻል ነው፡፡ ይህ የማይቆም፣ መድረሻ የሌለው ጉዞ ነው፡፡ የአመፃ ትግል ዴሞክራሲን ማምጣት አልሞ ሲደረግ ከመነሻው ዴሚክራሲን እንደመድረሻ ስለሚቆጥረው ስህተት ይሆናል፡፡ በአካሄድም ቢሆን አመፃዊ ዴሞክራሲያዊነት ስለማይኖር ምናልባት ነባሪውን ፍፁማዊ አምባገነን በለዘብተኛ አምባገነን (Benevolent dictatorship) መተካት ካልቻለ በቀር አመፃ ለዴሞክራሲ መንገዱን እንደሚከፍት ዋስትና አይሰጥም፡፡
    2ኛ- ‹‹ውሻ ወደትፋቱ ይመለሳል››
ምንም እንኳን ነፃ አውጪዎች በብረት ነጻነትን፣ በእኛ ጉዳይ ዴሞክራሲን እናመጣለን ብለው ቢሸፍቱም - የሚያውቁትም፣ የሚለምዱትም የብረት (አፈሙዝ) ሕግን ነውና - በዓለም እንደታየው መጀመሪያ ላይ ዴሞክራሲያዊነትን ለማስመሰል ቢሞክሩም ቆይተው ግን በብረት ስልጣናቸውን ማቆማቸው የተለመደ እውነት ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስነው የባሕሩ ዘውዴ ጥናት እንዲህ ይላል፡-
‹‹.. . ሥልጣን የራሱ የሆነ የማይሻር አመክንዮ አለው፤ ለአብዮታዊ ዲስኩር አያጎበድድም፡፡ ስለዚህ በሕዝባዊ ድጋፍ ተመርኩዞ በአፍሪካ ግዙፍ ከሆኑት ወታደራዊ ሠራዊቶች አንዱን የደመሰሰው እሕአዴግ የራሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ መልሶ ወታደራዊ ኃይል ላይ መንጠላጠሉ የሚያስገርም አይደለም፡፡ . . . ››    
በዚህ ረገድም ስናስበው አመፃዊ ትግል እኛ ‹ለውጥ› የምንለውን እንደሚያመጣልን ዋስትና መስጠት አይቻልም፡፡
   3ኛ- ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነርሱ›› እንሆናለን
አመፃዊ ትግል (በተለይ የትጥቅ ትግል) አንድን ሕዝብ ቢያንስ ለሁለት ይከፍለዋል፡፡ (እንደ ሶሪያ አይነቶቹ ከዚያም በላይ ከፋፍለውት አሳይተውናል፡፡) ስለዚህ በትግሉ ወቅት የወገን እና የጠላት እየተባሉ የሚፈረጁ የአንድ ሕዝብ ሁለት ክፍሎች፣ከትግሉ በኋላም በዚያው ዓይን መተያየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው አሁንም በገዢዎቹ የሕዋኃት ልሒቃንና ደጋፊዎቹመካከልና በሌሎች ኢትዮጵውያን መካከል ያለው ልዩነት (ያውም ከ 24 ዓመት በኋላ) የሁለትዮሽ ነው፡፡ ቂም የያዘ እና ያስያዘ ሁለት ወገን ካለ፣ ቂመኛው መልሶ ስለሚሸፍት እንደመጀመሪያው ሁሉ ‹ንጉስ ያለ ለውጥ› እንደጉልቻ እያቀያየረ ይሄዳል፡፡ ዴሞክራሲ መሠረታዊ ሕዝባዊ ስምምነት (consensus) ስለሚጠይቅ አመፃዊ ትግል ዴሞክራሲን እንደማያስገኝ ይህም አንድ ማሳያ ነው፡፡
   4ኛ- ለፍቶ መና
ሕዋኃት የዱር ትግሉን ጨርሶ ቤተመንግስት ሲገባ ከገጠሙት ፈተናዎች አንዱ ‹‹ታጋዮቹን ምን ላድርጋቸው?›› የሚለው ነው፡፡ 17 አመት ሙሉ በዱር በገደሉ ሲዋደቁ ከርመው የስልጣን በትሩን ሲጨብጡ፣ የተለያዩ የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎችን በሙያ ብቃት ብቻ ለመሾም (አላሰቡም እንጂ) ቢያስቡም ለትግሉ ስኬት የመማርና የሙያ ልምድ የማካበት እድላቸውን ያባከኑትን ሰዎች ‹‹አፍንጫችሁን ላሱ›› ሊሏቸው አይችሉም፡፡ ምንም እንኳን ታጋዮቹ የሚታገሉት ለዓላማ (cause) ነው ቢባልም፣ድል ሲቀናቸው የአላማው ፍሬ የመጀመሪያው ተቋዳሽ ለመሆን ከመጓጓት አይተርፉም፡፡ ሰው ናቸውና፡፡ ስለሆነም በወታደራዊ አስተዳደር(ማለትም ማዕከላዊነት እና ከላይ ወደታች የትዕዛዝ መሥመር በሚሠራ የአስተዳደር ዘዬ) የሰለጠኑ ሰዎች ከወረዳ እሰከ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሲገቡ ዴሞክራሲን (ከታች ወደላይ የሚወሰንበትን አሰራር) ያመጣሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ያውም ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የኃላፊነት ቦታዎችን እንዲይዙ ለምርጫ ቢቀርቡ በዕውቀትና ልምድ ማነስ ስለማይመረጡ ከታገሉለት ስርዓት ጋር ቅራኔ ውስጥ በመግባት እንደማያጨናግፉት ምንም ዋስትና የለም፡፡ ይህም አመፃዊ ትግልን ለዴሞክራሲ እንዳይመች ያደርገዋል፡፡
  5ኛ- ዴሞክራሲን ይኖሩለታል እንጂ አይሞቱለትም!
ሕውኃቶች ለ 17 ዓመት ሲታገሉ፣ 60ሺ ነፍስ መስዋዕት ሲያደርጉና ከዚያ በላይ ሲገድሉ፣ተስፋ ያደርጉ የነበሩት እንደ ሃይማኖት ያመልኩት የነበረውን ማርክሳዊ-ሌኒናዊ ርዕዮተ አለም ነበር፡፡ ትግሉ ድል ሲቀናው ግን የታገሉለትርዕዮተ ዓለም ‹‹አለፈበት››፡፡ በዓለም እንደ መንግስት ፀንቶ ለመኖር ‹‹ነጭ ካፒታሊዝም››ን መቀበል ነበረባቸው፡፡ እንደ ገብሩ አስራት ንግግር ‹አልባንያ፣ አልባንያ እየተባለች እንደ ሞዴል የተጠራችው አገር ትግሉ ሳይጠናቀቅ ብትንትኗ ወጣ›፡፡ ሕወኃትም የሞተለትን እና የገደለለትን ስርዐት ንቆ ‹‹የዘመኑን›› ያዘ፡፡ እንግዲህ የአመፃ ትግልን ከሚያስፈሩ ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ ምናልባት ለሚለወጥ ርዕዮተ ዓለም መልሶ የማይገኝ የሰው ልጅ ነፍስ መስዋዕት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ለሰዎች አንፃራዊ ሰላም እና ደህንነት ሲባልመሞት የውም በገፍ-ምክንያታዊ አይደለም፡፡
በለውጥ ትግል አለሞች ሁሌም ጠርዘኛ (radical) እና መሐከለኛ (moderate) አቋሞችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ፡፡አመፃዊም ሆነ ሠላማዊ ትግሎችን የሚከተሉት ሰዎች እንደ ጠርዘኛ የሚቆጥሯቸው አሉ፡፡ ራሳቸውን አማካይ ብለው ይጠራሉ፡፡ የሚሰጡትም ምክንያት ሠላማዊውም ሆነ አመፃዊው ትግል ለየብቻ መቆም አይችልም የሚል ነው፡፡ በኃይል ስልጣኑን የያዙ ሰዎች ከሠላማዊዎች ጋር መደራደር እና ለለውጥ ፈቃደኞች የሚሆኑት አማፂዎቹን በመፍራት ነው ይላሉ፡፡ ይህንን እንስማማበት ቢባል የአማፂዎችን ሚና ወስዶ የሚጫወተው ማን ነው? በግሌ እኔ የምኖርለት እንጂ የምሞትለት ግብ የለኝም፡፡ አመፃዊ ትግል ደግሞ ለመግደልም ብቻ ሳይሆን ለመሞትም መዘጋጀትን የጠይቃል፡፡ በበኩሌ እኔ የማልገባበትን የትግል መሥመር ሌሎች እንዲገቡበት የምመክርበት ሞራል የለኝም፡፡ እንዲያውም እስከ መሞት በሚደርስ ወኔ የሚታገሉ ሰዎች ካሉ ለሠላማዊ ሜዳ ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይችለላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
በሠላማዊ እና በአመፃዊ ትግሎች መካከል ያለው ልዩነት የሕይወትና የሞት ያክል ነው፡፡በሠላማዊ ትግል ትልቁ ፈተና እስር ነው፡፡ አልፎ፣አልፎ ሞት የሚከሰትባቸው ሠላማዊ ትግሎች ቢኖሩም የአመፃዊ ትግሎችን የክል እልቂት የሚያስከትሉ አይደሉም፡፡ ጌታቸው ማሩ ‹ደርግን ለአመፃ ትግል መጋበዙ ይብስ አረመኔ ያደርገዋል› የሚል ስጋት እንደነበረው ሕይወት ተፈራ ‹‹Tower in the sky›› ላይ ገልፃዋለች፡፡ ስጋቱ አልቀረም፤ ለኢሕአፓ የነጭ ሽብር ምላሽ ደርግ በቀይ ሽብር አገሩን አጠበው፡፡ ትግሉ በሁለት ገዳዮች መካከል ስለነበር ኃያሉ ገዳይ አሸንፎ ወጣ፡፡ በድኅረ ምርጫ 97ም የቅንጅት መሪዎች (በተለይ እነ ልደቱ) ስለ ጆርጂያና ዩክሬን የቀለም አብዮት የቀሰቀሱትን ሕዝብ እንዴት ሰላማዊ መሆን እንዳለበት ስላልነገሩት፣ በድንጋይ ውርወራ እና ጎማ በማቃጠል ብሶቱን ገለፀ፤ አጋጣሚው ግን ለኢሕአዴግ ሕዝባዊ ብሶቱን ለማፈን ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም እንዳይደገም እድሉን እንዲዘጋ መንገድ ጠረገለት፡፡ አሁንም የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴች አሉ፡፡ በተለይ በኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባት ስም የተጨፈለቁ ሰላማዊ ታጋዮችን ቁጥር ወሕኒ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንግዲህ መደራደሪያ ይሆናል የተባለው የአመፃ ትግልም ሠላማዊውን ለማደናቀፊያ እያዋሉ ነው ማለት ነው፡፡
አመፃዊው ትግል ውስጥ (በተለይ በትጥቅ ትግሉ) ሌላም ፈታኝ ጉዳይ አለ፡፡ ሕዋሓት ለድል የበቃው ‹‹የሻቢያ የትሮይ ፈረስ ሆኖ ነው›› የሚሉ አሉ፡፡ ሕዋሓት ጫካ እያለ የማይደራደርባቸው ከነበሩ አቋሞቹ ውስጥ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ነው፤ እና የሚፈታው በነፃነት [መገንጠል] ነው›› የሚለው አንዱ ነበር፡፡ ሻቢያ ያን ሕልሙን በሕዋሓት አሳክቷል፤አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ አማፂዎች ወዳጅ ሆኗል፡፡ ሻቢያን እንደ ኢትዮጵያ ወዳጅ መቁጠር የሚቻልበት መስፈርት አይታየኝም፡፡ አዲሶቹ አማፂዎችም እንደ ሕዋሓት የሻቢያ የሌላ አጀንዳ የትሮይ ፈረስ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ፡፡  
...ይቀጥላል፡፡