Monday, February 6, 2017

የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ከታሰሩ 1020 ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

ሚያዚያ 17፣ 2006 የታሰሩት አራት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ በፍቃዱ ኃይሉና አጥናፉ ብርሃኔ እንዲሁም በሌለችበት ክስ የቀረበባት ሶልያና ሽመልስ ለመጨረሻ ውሳኔ ዛሬ ጥር 30፣ 2009 ለሃምሳ አንደኛ ጊዜ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ይቀርባሉ::

ጥቅምት 05፣ 2008 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ችሎት አራቱን ጦማርያን ከቀረበባቸው ክስ በነፃ ያሰናበተ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ላይ የቀረበበት ክስም ወደ መደበኛው የወንጀል ሕግ ተቀይሮ በዋስትና ከእስር ተፈትቷል:: ነገር ግን ከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ "በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ" በማለት በታሕሳስ 04፣ 2008 ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል::
በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ሶልያና ሽመልስ ፣ አቤል ዋበላና አጥናፉ ብርሃኔ
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎ የሁለቱንም ወገን ክርክር ከሰማ በኋላ "የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት" በሚል የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ከዓመት በላይ የወሰደ ሲሆን ፤ ጥር 19፣ 2009 በዋለው ችሎትም አስፈላጊው ሰነዶች ሁሉ ተሟልተው መቅረባቸውን አረጋግጦ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ጥር 30፣ 2009 ቀጠሮ ይዟል::

በሌላ በኩል ጦማሪ አቤል ዋበላ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የነበረበትን ክስ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ችሎት "ከስራው የታገደበት አግባብ ተገቢ ነው" በሚል ምክንያት ወደ መደበኛ ስራው እንዳይመለስ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ፤ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉም በድጋሚ በተለያዩ ምክንያቶች በቅርቡ ታስረው የተፈቱ መሆናቸው የሚታወስ ነው::