Saturday, May 30, 2015

ሥነ-ስርዓት! የአቤል ማስታወሻ ከቅሊንጦ

“they say that time heals all things,they say you can always forget;
but the smiles and the tears across the years
they twist my heart strings yet!”
― George Orwell1984
የመታሰሬ ምክንያት መናገሬ ነው ፡፡ መንግሰት በሬ ወለደ “ሽብር” የሚል ክስ ሳይመስርትብኝ በፊት ይጠይቀኝ የነበረው በማህበረሰብ ሚዲያ የምጽፍበትን የምናገርበት አላማ ነበር፡፡ አላማዬ ተፈጥሮአዊ የመናገር መብቴን ማከናወን አንደሆነ ስናገር ከዚህ ተጨማሪ ሌላ ምክንያት ያለኝ ይመስል የተረፈኝ ድብደባ ነበር ፡፡ በዚህ ሂደት ወትሮም ገመምተኛ የነበረውን ግራ ጆሮዬን አጥቻለሁ፡፡ የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ የሚያስቆጭ ነገር ካለም መቆጨት ያለብኝ የመናገር ነጻነት ያለውና ያን ነጻነቱን የሚጠቀም ሰው ሆኜ በመፈጠሬ ነው ፡፡

አላማዬ መናገር ነው ፡፡ አላማዬ መማር መማማር፣ ግድየለሽነትን በእውቀት ማስወገድ ነው ፡፡ ይህ አላማዬ ከማንም ያልተቀበልኩት ሰው በመሆኔ ብቻ ያገኘሁት ነው፡፡ ይህንን መሰረታዊ የሰውነት መብቴን ማንም አንዲነፍገው አልፈቅድለትም ፡፡ የመንግሰት ሹመኛ ይሁን ተራ ግለሰብ ፣ ተቋም ይሁን ማህበረሰብ የመናገር መብቴን ልሰጠው አልደራደርም ፡፡
የምናገረው በአደባባይ ፣ በገዛ ቤቴ ፣ በማህበራዊ ሚዲያ በእስር ቤት በፍርድ ቤት በፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል በአጠቃላይ በአካባቢዬ ያለውን ግለሰብና ቡድን ሳላውክ በሃላፊነት ነገር ግን በማንኛውም ቦታ ነው ፡፡ ይህንን እነዳላደርግ ቁጣ ፣ ማስፈራሪያ፣ የማሰቃየት ተግባር እስርና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች መከልከል አላገደኝም ለወደፊትም እንዲያግደኝ አይሆንም ፡፡
ጓደኞቼም ሆነ እኔ አሁን ያለንበትን እስር ማስወገድ እንድንችል ስደትና ሌሎች መንገዶች አንድንመለከት ሥርዓቱ በደህንነት ሰራተኞቹ ጥቆማ ሰጥቶን ነበር፡፡ የመጨረሻዋ ሰአት ስትቃረብ ከልብ የሆነ አእምሮን የሚፈታተን ውይይት አድርገን ነበር፡፡ ከመታሰራችን ቀናት ቀድሞ ሚያዝያ 15/2006 በገጻችን ዞን9 አንዳስነበብነው“ ተፈጥሮአዊና ህገ መንግሰታዊ መብታችንን ማስረከብ “ እጅግ ስለበዛብን የምንከፍለውን ዋጋ እና የስርአቱን ቂመኝነት እያወቅን መናገራችንን አንደምንቀጥል አውስተን ነበር፡፡

የተራዘመው የእስር ጊዜም ይሄንን አቋም አልለወጠውም፡፡ አሁንም መናገር አሁንም ሃሳቤን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ሰው ሆኖ የመወለድ መብት በምንም አይነት ላባክነው አልፈልግም፡፡ግንቦት 19/2007  በዋለው ችሎትም የተፈጸመውም ይሄ ነው፡፡ 

ይህንን ክስ የሚከታተል ሰው ሁሉ አንደሚያውቀው19ኛ ወንጀል ችሎት በቀረብንባቸው ጊዜያት ዳኞቹ ንጽህናችንን የምናረጋግጥበትን እድል የሚያጣብቡ ውሳኔዎቸን መወሰናቸው ፣ የራሳቸውን ውሳኔ መልሰው መካዳቸው ፣ አቃቤ ህግ በቸልተኝነት የፍትህ ሂደቱን አንዲያዘገይ መፍቀዳቸው ፣ ማረሚያ ቤት የሚደርሱብንን የመብት ረገጣዎች ሰምተው አጥጋቢ እርምጃ አለመውሰዳቸው ሳያንስ ከሁሉም የከፋው ደሞ ችሎት ውስጥ እነዳንናገርና ሃሳባችንን እንዳንገልጽ ማፈናቸው ነው ፡፡

ይህንን ተከትሎ መፍትሄ ይሆናል በማለት ሃሳባችንን በችሎት እንዳንገልጽ መታፈናችንን በመግለጽ የመሃል ዳኛው አንዲቀየሩ አቤቱታም አቅርበን ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችንን ውድቅ ቢያደርገውም መሃል ዳኛው በራሳቸው ፍቃድ ከእኛ ( ከነሶልያና ሽመልስ) የክስ መዝገብ ራሳቸው አግልያለው ብለው የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ የሚሰየሙት ራሳቸው ናቸው :: ችሎቱም አንደተለመደው ለአቃቤ ህግ እንደፈቀደ ለእኛም ሆነ ለዳኞቹ ለራሳቸው የማይገቡ ነገሮች የሚናገርበት እኛም አንዳንዴ ካልሆነ በስተቀር እንዳንናገር የምንታፈንበት ሆኖ በኤሊ ፍጥነት እያዘገመ ነው ፡፡

ይህ መዘግየት አንደሚያሳስበን ዳኞቹ የተረዱ አይመስለኝም፡፡ በነጻነት ልናደርጋቸው የምንፈልጋቸው ነገሮች አንዳሉን ከሚወዱንና ከምንወዳቸው ሰዎች እስር ቤቱ አንደነጠለን ዘንግተውታል፡፡
የአገሪትዋን የማረሚያ ቤቶች ሁኔታ እና የማረሚያቤቶቹን የእስረኞች አያያዝ አያውቁት ይመስል፣ እኛ የተፈጠርንበትን የጉድ ዘመንና የምንተውንበት ወለፈንድ ድራማ አስገርሞን ፈገግ ማለታችንን አይተው እስሩ የተመቸን እየመሰላቸው በቀጠሮ ላይ ቀጠሮ መደራረባቸው አግባብ አለመሆኑን መናገር ነበረብኝ ፡፡ መታሰራችን ጤናማ መንፈሳችንን እያደከመ መሆኑን አቃቤ ህግ እስከዛሬ አለኝ ሲል ያልተደመጠውን በድንገት ያመጣውን አንድ ዶክመንተሪ ሲዲ (አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የቀረበ) ለማየት ሃያ ቀናት መውሰዱ ፣ በአጭር ቀናት ውስጥ አይተው በፍጥነት ወደቀጣዩ የፍርድሂደት እንድንሄድ አንዲደርጉ ለመግለጽ በፍርድ ቤቱ ሥርአት መሰረት እጄን አውጥቼ አውጥቼ አሳየሁ። አንደተለመደው እነዳንናገር ዳኞቹ እቀባ በማድረግ የመሰማት እድላችንን ነፈጉን ፡፡ ለመናገር ፍቃድ ስንከለከል ሳይፈቀድልን መናገር ጀመርን ፡፡ “ የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ” አንዲል ያገሬ ሰው ተበድለን በተናገርን “ስነስርአት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ከዳኞቹ መጣ፡፡ በዚህ ሰአት “እናንተ ራሳችሁ ሥነ-ስርዓት አድረጉ” በማለት ስርአት አልበኛ የሆነው የንጹሃን ዜጎችን መብት ለማፈን የተዘጋጁት እነሱ መሆናቸውን ተናግሬያለሁ፡፡ ይህንን ስናገር ስሜት ተጭኖኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚያ ችሎት የሚፈጸመውን በደል ትውልድ እንዲረዳው ታሪክም መዝግቦ አንዲያቆየው መዘከር ነበረብኝ፡፡
ጦማሪ አቤል ዋበላ

ሥነስርዓት ምን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ወላጆቼ በገባቸው መጠን ጥብቅ በሆነ ስነስርዓት አሳድገውኛል፡፡ ይህ ታላቅን ብቻ ሳይሆን ታናሽንም ማክበር አንደሚገባ ሥነ-ስርዓትና ደንቦችን መጣስ አንደማይገባ ይጨምራል፡፡ ( በሁለት አመት የዞን9ሥራቸንም ለማንኛውም የአገሪቷንህግ ሳንጥስ ህጋዊ ሆነን የቆየነው ለዚያምጭምር ነው ) ነገር ግን መታፈንን በጻጋ መቀበልና በደልን መሸከምን አይጨምርም፡፡ የማንም ሰብአዊ መብት ተሟጋች ወይም ነጸ አውጪአይደለሁም ፡፡ የግለሰብ መብቴ ሲነካ ግን ዝም ማለት አልወድም ፡፡ በተለይም ደግሞ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴ አንዲከለከልአልፈልግም ፡፡ ስለዚህም ይህንነ ከዚህ በፌት ላደረገ ፣ ከአሁን በማድረግ ላይ ያለ ፣ ወደፌትም ለማድረግ የሚያስብን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ………….ሥነ-ስርዓት !!

Thursday, May 28, 2015

የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞቹ የሃያ ዘጠነኛ የፍርድ ቤት ውሎ

ከትላንትና ወዲያ በምሰክሮች እና ሲዲ ውዝግብ በይደር ተቀጥሮ የነበረው የነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝግብ የፍርድ ቤት ውሎ ትላንትናም በተለያዬ ድራማዎች ታጅቦ ለግንቦት 25 እና ለሰኔ 8 ተቀጥሯል፡፡
የፍርድ ቤቱ ብይን
ፍርድ ቤቱ በ29ኛ ቀጠሮው ተጨማሪ ምስክሮችን ለመስማት እና ሲዲ ማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስጠት የነበረ ሲሆን በዚህም መሰረት
1. የሲዲ ማስረጃ ተብለው አቃቤ ህግ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው ነገር ግን በስተመጨረሻ ከኮምፒውተር ላይ የሰነድ ማስረጃዎቸን ለመገልበጥ ብቻ የተጠቀምኩባቸው ናቸው ያላቸውን ሲዲዎች የኤግዚቢትም የሰነድም ማስረጃ ስላልሆኑ ሙሉ ለሙሉ አንዲሰረዙ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ አቃቤ ህግ ከመጀመሪያው የማስረጃ መስማት ሂደት አንስቶ እስከ 28ተኛው ቀጠሮ ድረስ አንዴ ባለሞያዎች የሉም ሌላ ጊዜ የወንጀሉ ኤግዚቢት ናቸው ሲላቸው የከረሙትን ሲዲዎች በስተመጨረሻ ምንም አይነት የተለየ ይዘት ያላቸው ሲዲዎች የሉኝም ሲል አምኗል፡፡ እነዚህ ሲዲዎችን አስመልክቶ ብቻ ትንሽ የማይባሉ ቀጠሮዎች መሰጠታቸው ከዚያም በተጨማሪ የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞቹ እነዲሁም የጠበቆች እና የፍርድ ቤቱ ጊዜ እና ጉልበት መባከኑ ይታወቃል፡፡
2. አቃቤ ህግ የጠየቀውን ተጨማሪ ምስክሮች ተፈልገው አንዲመጡ ጊዜ ይሰጠኝ ያለውን ጥያቄ አስመልክቶ ምስክሮቹ አሁንም የደረጃ ምስክሮች በመሆናቸው እቃ ሲፈተሽ አይተናል ከማለት ውጪ ስለማይመሰክሩ አቃቤ ህግም በተደጋጋሚ በፍርድ ቤቱ እድል ተሰጥቶት ምንም የተለየ ምስክር ሊያቀርብ ባለመቻሉ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማቅረብ ተጨማሪ ቀጠሮ አይሰጠውም በማለት የምስክሮቹን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ዘግቶታል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስን የተመለከተ ማስረጃ
አቃቤ ህግ እስካሁን ምንም ሳይል የቆየባት አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስን በተመለከተ በትናንትናው የፍርድ ቤት ውሎ ማጠቃለያ ላይ አንድ ዶክሜንተሪ የያዘ ሲ.ዲ በማስረጃነት ማቅረቡን ገልጾ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከተው ማመልከቱ ይታወሳል፡፡ ይህን የሲ.ዲ ማስረጃ በተመለከተ በ29ኛው ችሎት ቀጠሮ ብይን የተሰጠ ሲሆን፣ በብይኑ መሰረትም ትላንትና ከሰዓት በኋላ አቃቤ ህግ ሲ.ዲውን በጽ/ቤት በኩል እንዲያስገባ ታዝዟል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጨምሮ እንደገለጸው በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን ዶክሜንተሪ በቢሮ ዳኞቹ እንዲመለከቱት ከተደረገ በኋላ ሲ.ዲው ሌሎችን ተከሳሾች ይመለከታል ወይስ አይመለከትም የሚለውን አይቶ ብይን የሚሰጥ ይሆናል፤ ብይኑን ለመስጠትም ለሰኔ 8/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ሲ.ዲው የያዘው ዶክሜንተሪ በግልጽ ቢታይ የሚያስከትለው ጉዳት አለ ወይስ የለም የሚለውንም ፍርድ ቤቱ ብይን እንደሚሰጥበት ይጠበቃል፡፡ አቃቤ ህግ በቀደመው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አመጽ ስታነሳሳ የሚያሳይ ዶክመንተሪ ሲዲ አለኝ ማለቱ ይታወሳል፡፡
አቃቤ ሀግ ጠበቆች ላይ ያቀረበው አቤቱታ
አቃቤ ህግ በዚሁ ችሎት ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ውሎ አስመልክቶ የሚሰጡትን አስተያየት የአንድ ወገን አስተያት ከመሆኑም በላይ የፍርድ ሂደቱን ተጽእኖ ሊያመጣ ይችላል የሚል በቤቱታ አቅርቧል፡፡
ጠበቃ አምሃ መኮንን በበኩላቸው አቃቤ ሀግ እዚህ አንድ ተከራካሪ ወገን አንጂ የሂደቱ አዛዥ አለመሆኑን በተጨማሪም ግድፈት ካለ የተጣሰውን ህግ ግድፈት በጽሁፍ አቤቱታ ማቅረብ አንደሚችል ከዚያ ውጪ ግን በግልጽ የተሰየመውን ችሎት ከአገር ቤት እስከአለም አቀፍ ሚዲያዎች በዝርዝር አንደሚዘግቡትና የጠበቃው አስተያየትም ከዚህ የተለየ አንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ‹‹የተሰጠው አስተያየት አቃቤ ህግ በሰጠው ቃል መሰረት ተፈጽሞ ከሆነ ስህተት ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል›› በሚል ማሳሰቢያ ብቻ አልፎታል፡፡
በፍርድ ቤትም ውስጥ የታፈነው የተከሳሾቹ ድምጽ
ብይኑ መሰማት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ጥያቄ ለመጠየቅ ሲጠይቁ የነበሩት ተከሳሾች በፍርድ ቤቱ እድል አልተጣቸውም ፡፡ በተለይም የአቶ አመሃን የሚዲያ አስተያት ተከትሎ
ጦማሪ ናትናኤል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በተከሳሾች ላይ የወንጀለኛነት ንግግር ሲያደርጉ መደመጣቸውን በማስታወስ የፍርድ ቤቱ ማሳሰቢያ ለእሳቸውም ይሁን በማለት ንግግሩን ለማብራራት ሲሞክር ፍርድ ቤቱ ‹‹ይሄ የአቶ አምሃ ጉዳይ እንጂ እናንተን አያገባችሁም›› በሚል አቋርጦታል፡፡ ጦማሪ ዘላለም ክብረትም አንዲሁም ጋዜጠኛ አስማመው ሃይለጊዬርጊስ በተመሳሳይ ሀሳቡን ለመግለጽ ጠይቀው ተከልክለዋል፡፡ ጦማሪ ናትናኤል ፍርድ ቤቱ ሳይፈቅድለት ተናግሯል ወደጎንም ዞሮ አውርቷል በማለት ፍርድ ቤቱ ለጥያቄ አንዲነሳ ሲታዘዝ የናትናኤል ጥያቄ የሁላችንም ጥያቄ ነው በማለት ሁሉም ተከሰሶች አብረውት ተነስተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሎሎቹ ተከሳሾ አንዲቀመጡ ቢያሳስብም አንቀመጥም በማለት አብረውት ቆመዋል፡፡
ናትናኤል መናገር ሲከለከል ‹‹ከአሁን በፊትም ሀሳባችን እንዳንገልጽ ገደብ ባደረጉብን ዳኛ ላይ አቤቱታ ማሰማታችን ይታወሳል፡፡ ህገ መንገስታዊ መብታችንን አክብሩ...ሀሳባችንን እንግለጽ›› ሲል ተናግሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ንግግሩን አስቁሞ በመሐል ዳኛው አማካኝነት ‹‹ወዳልሆነ ነገር አታስገቡን›› ሲል ዛቻ መሰል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በዚህ ያላበቃው የተከሳሾችና የፍርድ ቤቱ ውዝግብ ጦማሪ አቤል አሁንም ለመናገር አድሉ አንዲሰየው ሲጠይቅ " ስነስርአት ያዙ " በማለት ፍርድ ቤቱ በመከልከሉ ጦማሪ አቤል " እኛ ብቻ ሳንሆን ራሳችሁም ስነስርአት አድርጉ ጥያቄ አለን ሰምታችሁ ምላሽ ስጡን" በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ምላሹን ፍርድ ቤቱ ችሎት መድፈር ነው ብሎታል፡፡ ይህንን ተከትሎ ጠበቆች ጣልቃ በመግባት ደንበኞቻቸው አንዲደመጡ ፍርድ ቤቱን በማሳሰብ አቤልም ይህን እድል በመነፈጉ በስሜታዊነት የተናገረው በመሆኑ በተግሳጽ አንዲታለፍ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤልን በዚህ የጠበቃው ሃሳብ ይስማማ እነደሆነ ሲጠየቅ የጠየቁት መብቴን ነው የምጠይቀው ይቅርታ የለም በማለቱ የችሎት መድፈሩን አስመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ይህንን ተከትሎ የአቤል ሀሳብ የሁላችንም ሃሳብ ስለሆነ ሁላችነም በዚያ ቀን ልንቀርብ ይገባል የሚል አቤቱታ ሁሉም ተከሳሾች ቢያሰሙም ፍርድ ቤቱ ፓሊስን አንዲያስወጣቸው በመታዘዙ ችሎቱ ወጥተዋል፡፡ በኋላ ከተከሳሾች ጠበቆች አንደገለጹት የጦማሪ አቤል ጥያቄ አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የሚቀርበው የተባለውን የዶክመንተሪ ማስረጃ ሎሎች ተከሳሾችም አንዲያዩት ለመጠየቅ ነበር ፡፡
የዞን 9 ማስታወሻ
1. ዘግይቶም ቢሆን የተወሰደውን የፍርድ ቤቱን የሲዲ ማስረጃዎቸን መሰረዝ አንዲሁም ለአቃቤ ህግ ተጨማሪ ጊዜ አለመስጠት ውሳኔ እናበረታታለን ፡፡ ይህ ውሳኔ ከሶስት ቀጠሮ አስቀድሞ መወሰድና የጓደኞቻችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ሊከበር ቢገባውም አሁንም ቢሆን ከመቅረት ይሻላል ፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንን መሳይ ፈጣን ምላሾችን በመስጠት ጓደኞቻችን ጦማርያን እና ጋዜጠኞች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ማሰናበት የሚቀጥለው ብይን ሊሆን ይገባል፡፡ ያልተሰራ ወንጀል ምስክርም ሆነ ማስረጃ ለአመታት ቢፈለግም አይገኝለትም ፡፡
2. ፍርድ ቤት ውስጥ ያለውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አሁንም አሳሳቢ ነው ፡፡ ተከሳሾች ሃሳባቸውን አንዲሰጡ መፍቀድ አንድ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለተከሳሾች ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ መብት ሆኖ ሳለ ተከሳሾች ይህንን መብት በተደጋጋሚ መነፈጋቸው ከዚም አልፎ ይህንን መብት በመጠየቃቸው ችሎትን አንደደፈሩ መቆጠሩ በጣም አሳዛኝ ነው፡። የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች እንኳን አሁን ታስረንና ተሰደን መስዋእትነት እየከፈልንበት እያሉ ቀርቶ ቀድሞም ሃሳብን የነጻነት የመግለጽ መብት የማይቀየር ቋሚ እሴታችን አንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህንን ቀላል መብት መንፈጋቸው ደግሞ የተለመደውን የስራ አስፈጻሚው አካልነታቸው ሃሜት የሚያጠናክር ከመሆን ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም ፡፡
አሁንም ስለሚያገባን እንጦምራለን!
ዞን9
ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ እና ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን

Tuesday, May 26, 2015

የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ከሚገኙት ሰባት የዞን 9 ጦማርያን እና ሶስት ወዳጅ ጋዜጠኞች ስድስቱ ጦማርን እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ዛሬ ግንቦት 18/2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍ/ቤት ቀርበዋል፡፡ መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ሁለት ጉዳዮችን ለማየት ሲሆን፣ አንደኛው አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት አሉኝ ያላቸውን ኤግዚቢቶችና 12 ሲ.ዲዎች መዝገብ ቁጥራቸውን በመጥቀስ አሟልቶ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሰረት ማቅረቡን ለመመልከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአቃቤ ህግ ቀሪ የደረጃ ምስክሮችን ለመስማት ነበር፡፡
በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት የያዛቸውን ላፕቶፕ፣ ሞባይል፣ ሲምካርድ፣ ሃርድ ዲስክ ይዞ ቀርቧል፡፡ ሆኖም ግን ሲ.ዲዎችን በተመለከተ ሲጠየቅ ‹‹ሲ.ዲዎቹ እየመጡ ነው››የሚል ምላሽ በመስጠቱ እና የተከሳሾች ጠበቆች ሲዲዎቹ ሳይመጡ ምስክሮች መሰማት የለባቸውም ብለው በመቃወማቸው ሲዲው ከማእከላዊ ምርመራ እስኪመጣ ምስክሮች አያሰሙም ተብሎ ለከሰአት ተቀጥሮ ነበር ፡፡
ከሰአት በኋላ አቃቤ ህግ ቀሪ ናቸው ካላቸው 16 ምስክሮች መካክል 3ቱን ብቻ ይዞ የቀረበ ሲሆን 13ቱን ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል፡፡ የቀረቡት ሶስቱንም ፍተሻ ሲከናወን ያዩ የደረጃ ምስክሮች ሲሆኑ ፍተሻ ሲከናወን ከማየታቸው በስተቀር ተጨማሪ ነገር መመስከር አልቻሉም ፡፡
የምስክሮች ቃል
19ኛ ምስክር፡- ቸርነት ተፈራ ይባላል፤ 23 አመቱ ነው፡፡ ደንብ በማስከበር ስራ ላይ እንደተሰማራ የገለጸው ይኸው ምስክር አድራሻው አ.አ ጉለሌ ክ/ከተማ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ላይ ነው ምስክርነቱን አሰምቷል፡፡ "ቤት ሲፈተሽ አይቻለሁ፣ ሲ.ዲ፣ ላፕቶፕ፣ አሮጌ ካሜራ፣ ሚዲያ ኤንድ ኢሌክሽን የሚል ጽሑፍ፣ መጽሐፍ፣ ወረቀቶች፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተገኝተዋል፡፡ የላፕቶፑን አይነት አላስታውስም፡፡ ሲ.ዲዎች ሁለት ናቸው፣ ይዘታቸውን ግን አላውቅም፡፡ እሷ የፈረመችበትን አንዳለ ፈርመናል ብሏል፡፡
ለምስክሩ ‹‹ሲ.ዲው ባዶ ይሁን የተጻፈበት ይሁን ያየኸው ነገር ነበር›› የሚል መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብለት ‹‹አላየሁም›› ሲል መልሷል፡፡ ሲ.ዲው ላይ ፈርመሃል ሲባልም መፈረሙን አስረድቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የፈረመበትን ሲ.ዲ እንዲያሳይ ተጠይቆ አቃቤ ህግ ጣልቃ በመግባት ‹‹ኤዶም ላይ ሲ.ዲ በማስረጃነት አልያዝንም›› የሚል አስገራሚ መልስ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ምስክሩ 30 ገጽ የእንግሊዝኛ ጽሁፍ የተጻፈበት ወረቀት ላይ መፈረሙን ስለገለጸ ፊርማውን እንዲለይ ሰነዱ ይቅረብላቸው ሲባልም አቃቤ ህግ ‹‹በማስረጃነት አላያያዝንም›› ብሏል፡፡ ምስክሩ ሁለት በማስረጃነት ባልተያዙ ሰነዶች ላይ ነበር ምስክርነቱን የሰጠው ፡፡ በተጨማሪም በፍተሻ ወቅት የተገኘውን ላፕቶፕ እነዲያሳይ የተጠየቀው ምስከሩ የጦማሪ አቤል ዋበላን ላፕቶፕ አሳይተዋል፡፡
20ኛ ምስክር፡- እኒህ ምስክር ደግሞ ቢላል ሙሄ የሱፍ የሚባሉ ሲሆን 38 አመታቸው ነው፡፡ ‹‹ሚያዝያ 2006 ፌደራል ፖሊስ የተስፋለምን ቤት ሲፈትሽ በታዛቢነት አይቻለሁ፡፡ ቤቱን የከፈተው ተስፋለም ነው፡፡ ቤቱ ውስጥ ብዙ መጽሔትና ጋዜጦች፣ መጽሐፎች፣ ወረቀቶች፣ መቅረጸ ድምጽ፣ ላፕቶፕ ተገኝተዋል፡፡›› ተስፋለም ቤት 28 ሲዲዎች ተገኝተዋል ያሉት ምስክሩ ምን አይነት ይዘት አንደነበራቸው ባዶ ይሁኑ ጽሁፍ ያላቸው አላውቅም እነዲሁም ሲዲዎቹ ወጥቶ የታተመ ነገር አላስታውስም ብለዋል፡፡
21ኛ ምስክር፡- ሚሊዮን አሸብር ደግሞ የ31 አመት በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ የአ.አ ነዋሪ ነው፡፡ ለምስክርነት መምጣቱን የገለጸው ሚሊዮን በማን ላይ ልትመሰክር ነው የመጣኸው ሲባል በአማኑኤል ፈለቀ ላይ ሲል መልሷል፡፡ ሆኖም ግን ዳኞች ደጋግመው ሲጠይቁት ስሙን አስተካክሎ በናትናኤል ፈለቀ ላይ ሊመሰክር መሆኑን ገልጹዋል፡፡
‹‹ሚያዝያ 17/2006 ቂርቆስ ክ/ከተማ ኮንስትራክሽን ባንክ ፌደራል ፖሊስ የፍርድ ቤት ወረቀት አሳይቶ ፍተሻ ሊያደርግ ስለሆነ እንድታዘብለት ጠይቆኝ ታዝቤያለሁ፡፡ ናትናኤል ፍተሻው እንዲካሄድ ፈቃደኛ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ተፈትሹዋል፤ ፍተሻውንም አይቻለሁ፡፡ ላፕቶፕ፣ ሲ.ዲዎች (በቁጥር ወደ 16 የሚሆኑ) እና ሰነዶች ተገኝተዋል፡፡ የተገኙት ነገሮች ላይ ፈርሜያለሁ ፡፡ ሲዲም ሆነ ላፕቶፑ ውስጥ ያለውን ነገር ይዘት አላየሁም አላውቅምም ብሏል ፡፡ ላፕቶፑንም ቀርቦ አሳይቷል ፡፡
ሲዲዎቹ
አወዛጋቢዎቹ ሲዲዎች ዛሬም ቀርበዋል ተባለ እነጂ በአቃቤ ህግና በጠበቆች መካከል ያለው ክርክር አልተቋጨም ፡፡ ሲዲዎቹ ኤግዚቢት ስለሆኑ ለተከሳሾች ለማድረስ አልገደድም ሲል የነበረው የአቃቤ ህግ ክርክር ዛሬ ሲዲዎቹ የሰነድ ማስረጃው ላይ የተያያዙትን ሰነዶች ከላፕቶፕ የገለበጥንባቸው ናቸው ብሎ የሰነድ ማስረጃ አካል አድርጓቸዋል ፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች ሲዲዎቹ ማስረጃ ከሆኑ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ሲዲዎቹ አንድ ወይም ሁለቱ ናቸው የቪዲዮ ማስረጃ ያላቸው ሌላው ከክሱ ጋር የተያያዘውን ሰነድ የገለበጥንበት ነው፣ ሁሉም በሰነድ የተያየዙ ናቸው ሲል አቃቤ ህግ አዲስ የህግ ፍሬ ነገር አቅርቧል፡፡
የአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበ ማስረጃ
አቃቤ ህግ በዛሬው ውሎው አዲስ ግኝት ይዞ መጥቷል፡፡ የሲዲ ውዝግቡ መሃል ላይ "አንድ ዶክምንተሪ አንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበና ቡድኑ ለቅስቀሳ ይጠቀምበት የነበረ አለንና ፍርድ ቤቱ ሌሎች ማስረጃዎችን አቅርበን ሰንጨርስ ይሄንን ሲዲ እንዲያይልን" ብሏል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ በማስረጃነት አለኝ ያለው ሲዲ መቼ የተገኘ አንደሆነ ምን ይዘት እንዳለው የተጠቀሰ ነገር የለም ፡፡
በመጨረሻም አቃቤ ህግ ቀሪ 13 የደረጃ ምስክሮቹን ፈልጎ ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችም ሲዲዎቹ የሰነድ ማስረጃዎች ከሆኑ እንዲሰጣቸው ካልሆነም ኢግዚቢትነታቸው ምዝገባ እንዲለይ ጠይቀዋል፡፡ በሁለቱ ጉዳዬች ላይ ለመወሰን ለነገ ጠዋት ግንቦት19 ከጠዋቱ 3 ሰአት ተቀጥሯል፡፡
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች በከፍተኛ የአካልና የመንፈስ ደህንነት ሆነው የታዬ ሲሆን ቀኑን ሙሉ ፍርድ ቤት ጊቢ ውስጥ አብረው ለመዋል እድል አግኝተዋል፡፡
የዞን ማስታወሻ
ከዚህ በፌት በተደጋጋሚ አንደጠቀስነው ያልተሰራ ወንጀል ማስረጃና ምስክር አይገኝለትምና ተከሰሾችን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ በማሰናበት ፍርድ ቤቱ ሃላፌነቱን በመወጣት ከህግ የበላይነት ጎን መሆኑን አንዲያሳይ በድጋሚ አንጠይቃለን፡፡
 

 

 

Wednesday, May 20, 2015

ግልጽ ደብዳቤ ለፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ከየሸዋስ አሰፋ ቅሊንጦ

ክቡር ፕሬዘዳንት ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ያየሁዎትበፕሬዘዳንትነት ለመመረጥ በተወዳደሩባቸው ጊዜያት ሲሆን በወቅቱ ከእርስዎ ምርጫ ጋር በተገናኘ ድምጽ መስጠት ባልችልም ምርጫውንለመከታተል ብዙ ጊዜዬን እነዳሳለፍኩ አስታውሳለሁ፡፡ በወቅቱ ይህንንያደረኩት የተመረጡት ለአሜሪካን መሆኑን አጥቼው ሳይሆን የታላቅዋ አገር መሆንዎ በወቅቱ ከነበረው ተስፋ ጋር ተደምሮ ለአለም ሰላምሊያበረክቱ የሚችሉትን በጎ ምግባር ተስፋ በማድረግ ነበር ፡፡
አሁን ይህንን ደብዳቤ እንድጽፍልዎት ያነሳሳኝግን ዛሬ መንግሰትዎ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኛ እና የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ምክትክ ሚኒስትሯ ዌንዲ ሸርማንአዲስ አበባ መጥተው የተናገሩት ንግግር ነው ፡፡ መቼም አንደሚገምቱትአንደማንኛውም ኢትዮጲያዊ ንግግራቸው ስሜቴን መርዞታል፡፡
ምክትል ሚኒስትሯ የተናገሩት ብዙ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ስለሽብርተኛነት ፣ ስለምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ ስለግንቦት 7 ስለ ኢትዬጵያ እድገት ሰላም ዴሞክራሲ ወዘተ፡፡ ዋና ጉዳይ ብለውየገለጹት የቀጣዩ የ2007 ምርጫ ላይ የሰጡት አስተያየት ግን እጅጉንአሳዝኖኛል፡፡ ምርጫው ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ነው መጪው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው እንደሚሆን አንጠብቃለን ነበር ያሉት፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ የልእለ ሃያልዋ አሜሪካ አቋምመሆኑን መግለጻቸው ነው ፡፡ መቼም በፍቃደኝነት ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት አጭበርባሪ አምባገነን በዚህ ደረጃ ያጃጅላቸዋልብሎ ማመን ይከብዳል፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችበመዘርዘር ውድ ጊዜዎን አላጠፋም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በየአምስት አመቱ ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚሰሩና እየተሰሩ ያሉ ምርጫ አደናቃፌዎችንልገልጽልዎት እፈልጋለሁ፡፡ ከእነዚህ አደናቃፌዎች መካከል መጨውን ምርጫ 2007 ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ የሚያደርጉት
1. ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከመዋቅሩ ውጪ ባሉ ግለሰቦች የሚሽከረከር አቅመቢስ ተቋም ከመሆኑም ባሻገርዛሬ ገዥው ቡድን አንደራሱ የፓርቲ አካል የሚያሽከረከረው መሆኑ
2. ገዥው ቡድንም ምንም አይነትየፓርቲ ቅርጽ የሌለውና ከ20 አመታት በፌት ጀምሮ በአሜሪካን መንግሰት በአሸባሪነት ተፈርጆ የነበረው ህወሃት በጠርናፌነት ጠቅልሎየያዘውና ምርጫውንም የስልጣን ጊዜውን ለማራዘም ብቻ የሚጠቀምበትመሆኑ
3. ምርጫ በመጣ ቁጥር 1987ኦነግን ፣ በ1992 መአህድን፣ በ1997 ቅንጅትን ፣ በ2002 አንድነትን በ2007 ሰማያዊን ኢላማ በማድረግ የተሻሉ ተፎካካሪፓርቲዎቸን በማጥፋት አመራርና አባላቶቸን በማሰር ብቻውን የሚወዳደር መሆኑ
4. በፓርቲና በመንግሰት መካከልያለው ልዬነት ጭራሽ ጠፍቶ የፍትህ አካላትና ፍርድ ቤቶቸን ሳይቀር በቀጥታ የፓርቲ አገልጋዮች ያደረገ መሆኑ
5. ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም የግል ሚዲያ የሌለ መሆኑና 90 ሚሊዬን ህዝብ በሚኖርበት አገር 2000 ኮፒ የሚያሳትሙ ህትመቶችን ሳይቀርበመዝጋት ጋዜጠኞችና ጦማርያንን ወህኒ የከተተ መሆኑ
6. ከምርጫ 97 በኋላ በወጣውአፋኝ አዋጅ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምንም አንዳይሰሩ ተደርገው ትውልዱ መሪ እና አስተማሪ ያጣ መሆኑ
7. ህገ መንግስቱ ን በጸረ ሽብርአዋጅ በመጣስ የተለያዬ የአገሪቱን ዜጎች በተለይ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ኢትዮጲያውያንን በጅምላ ማሰር ፣ በሃይማኖት ጣልቃ መግባት በተለይየእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ በማሰር እስርቤቶችን በፓለቲካ እስረኛ የሞላቸው በመሆኑ
8. በአገዛዙ በተለያዬ የስልጣንእርከን ያሉ ግለሰቦች ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ከልክ ያለፈ ገንዘብ እየመነዘሩና ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ በመሆኑ እና ዛሬም በአልጠግብባይነት በዚሁ መቀጠል የሚፈልጉ መሆኑ
9. ምርጫ 2007 የአውሮፓ ህብረትንጨምሮ ሌሎች ተአማኒነት ያላቸውና አምባገነኖችን የማጋለትጥ ልምድ ያላቸው ድርጅቶች የማይታዘቡት መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ፕሬዘዳንት ኦባማ-በዛሬዋ ኢትዮጵያ እነዚህ ችግሮች አይኑን ለጨፈነ አንኳን የሚዳሰሱ ሃቆች ሆነው ሳለ የመረጃ ሰዎችዎ ይስቷቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ የገዥዎችፕሮፓጋንዳ ስክሪን ሴቨር ኑሮ የሚገለጸውን እውነታም የሚሸፍንባችሁ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ከላይ የተገለጹት መባባሶች መሻሻል ተብለውሲገለጹ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምን የሚሰማው ይመስልዎታል? ይህ የተገለጸው ደግሞ በዴሞክራሲ በተመረጠ መንግስትና መሪ ካለበት አገርሲሆንና ገዥው ቡድን ለሚደርገው ግፍና ጭቆና አሜሪካ እውቅና ስትሰጥስ ?
እነደሃያል አገር ሲሆንሲሆን የነጻነት ትግል ላይ ያሉ ህዝቦችን ማገዝ ሲገባ ፣ ማገዝ ካልተቻለም ደሞ ቁስላቸው ላይ ሚጥሚጣ ባለመጨመር ዝም ማለት አይቻልም?የአለምን ሰላም ካለነጻነት ማሰብ አንደማይቻል የተቀመጡበት የአባቶችዎም ዙፋን አንደሚያሳይዎት አውቃለሁ ታዲያ የህዝቦችን የነጻነት ትግል ማጣጣል ለምን ??
እርስዎም ሆኑ ሸርማንየአሜሪካንን ጥቅም አንደምታስቀድሙ እናውቃለን፡፡ መረሳት የሌለበት ቁም ነገር ግን ህዝባዊ ወዳጅነትን አንጂ አምባገነን አገዛዙንበመተማመን የሚገኘው ጥቅም ዘላቂ አለመሆኑ ነው፡። ከአገዛዞች ጋር የሚደረገው ቁማር አሜሪካን ቆምኩለት የምትለውን የሞራል ልእልናእና እሴት የሚመጥን አይመስለኝም፡፡ ቢያንስ በአገር ደረጃ ጥቅም ህሊናን ገርስሶ የፓለቲካ ትርፍ ሰው መሆንን ጨርሶ መደምሰስ የለበትም፡፡ትልቅነት የአለምን ሰላም መጠበቅ ከሚወሰድ ሃላፌነት ቀርቶ ሌላውን ለመዋጥ ለሚከፈት አፍ ከተለካ ህገ አራዊት የአለም ትልቁመተዳደሪያ ይሆናል፡፡
ፕሬዘዳንት ኦባማ-ለዴሞክራሲያዊ ስርአት አንጂ ለአምባገነንነት ጥሩ ፊት አንደማይኖርዎት እረዳለሁ፡፡ በአሁኑ መልእክት ግራ የተጋባሁትም ከዚህ የተነሳነው፡፡ አምባገነን የሚያስበው በአይኑ ነው እንደሚባለው የኢትዮጵያ አገዛዝ በአሁኑ ሰአት እውነት ቢነገረውም እንደማይሰማ ይታወቃል፡፡የወይዘሮዌንዲ ሸርማን መግለጫ ሊወድቅ ሳምንታት ሲቀሩት የግብጽ አገዛዝ “strong and stable government” ….. “ጠንካራ እና የተረጋጋ መንግስት” ከሚለው በወቅቱ የአሜሪካንየውጪ ጉዳይ ሚኒስተር ከነበሩት ወ/ሮ ሂላሪ ክሊንተን መግለጫ ጋር ተመሳሳይ ሆኖብኛል፡፡ ይህ አይነት ከእውነታው ያፈነገጠ አገላለጽለሁለቱም አገሮች አንደማይጠቅም ይገባዎታልም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ፕሬዘዳንት ኦባማ- የኢትዬጵያ ታላቅነት ይመለሳል፡፡ በእርግጥም በነጻነትና በዴሞክራሲ ምርጫ ወደስልጣን የሚወጣ ተርሙን ሲጨርስ ለቀጣዬ በሰላምየሚያስረክብ መሪ ይኖራታል፡፡ ህዝቦቿ በእርቅ ይተቃቀፋሉ፡፡ ጨቋኝም ተጨቋኝም ነጻ ይወጣሉ ፡፡ ኢትዬጵያ ጦር በመስበቅ ሳይሆንፍቅርን በተግባር በመስበክ ለአካባቢዋም ለአለምም አስተዋእጾ የምታበረክትበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ፡፡ ለዚህ ታላቅ ሽግግር እርሶምአንደመሪ አገርዎም እነደሃያል አገር ከኢትዮጲያ ጎን ብትቆሙ የሁለቱ አገሮች ጥቅም በአለት ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡
ቀሪው የስራ ዘመንዎምይህን የአሜሪካን የሞራል ልእልና በተግባር የሚያሳዩበት አንዲሆን እመኝልዎታለሁ፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንም አሜሪካንንም ይባርክ፡፡
የሸዋስ አሰፋ! ከቅሊንጦኢትዮጵያ

Wednesday, May 13, 2015

ሶስተኛ አመት

‪#‎Ethiopia‬ #FreeZone9Bloggers 
ለተሻለች ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ ያገባናል ያሉ ወጣቶች ከተሰባሰብን ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ጦማራችንን በይፋ ካወጅን ዛሬ ድፍን ሶስተኛ አመታችን ሆነ፡፡
እንደ ዜጋም፣ እንደ አገርም ያለመታደል ሆኖ ብዙ ብለን ተባብለን፣ የምንማማርበት ጊዜ እንዲኖረን አምባገነኖች አልፈቀዱምና ፣ የጠበበው ነጻነት ተዳፍኖብን ሥራችንን ሳይሆን እስራችንን መቁጠር ከጀመርን ደሞ አንድ ዓመት ሞላን፡፡ ራሳችንን እና የተቋቋምንበትን ስራችንን ረስተን እስራችንን ብቻ በምናስብበት ሰዓት ጎግል ልደታችንን ስላስታወሰን እናመሰግናለን፡፡
ይህ ሶስተኛ አመት በእስርና በስደት ያለን ዞን9ኛውያን ሳንነጋገር የምናስታውሰውና ወደኋላ ተመልሰን ሃሳባችንን የምናንጸባርቅበት አንደሆነ እናምናለን፡፡
ሶስቱን አመታት በሙከራችን በጥረታችን እንዲሁም በክፉ ጊዜያት አብራችን ስለቆያችሁ እናመሰግናለን፡፡
አጋርነታችሁ አይለየን ፣ ስለሚያገባን እንጦምራለን፡፡