Monday, December 31, 2012

ያጣናቸው ሰዎች ናፍቆት

በፍቃዱ ኃይሉ

ያጣናቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ግን ቀስ በቀስ ስላጣናቸው አጠፋፋቸው እየቆየ ብቻ ነው የሚገባን፡፡ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ኢሕአዴግ የመሪነቱን ሥልጣን ሲረከብ ብዙ ደርግ ያሰደዳቸው ምሁራንና ባለሀብቶች በሙሉ ተስፋ ወደአገራቸው ተመልሰው ነበር፡፡ ከነዚያ ባለሀብቶች ውስጥ የቀድሞ አለቃዬ ይገኝበታል፤ የሶፍትዌር ኢንጂነሩ፣ የቀድሞ አለቃዬ በዐሥራ ምናምን ዓመት የካናዳ ቆይታው ያጠራቀማትን 4 ሚሊዮን ብር ጨብጦ መጥቶ የሶፍትዌር ኩባንያ መሠረተ… አሁን ኩባንያው ከስሮ በመሟሟት ላይ ሲሆን፤ አለቃዬም በመዓት ዕዳ ተይዟል፤ በሶፍትዌር አምራች ኩባንያነት የተሳካለትን ኢትዮጵያዊ ኩባንያ እና የማንነት ጥናት ብታካሂዱ ጥየቄውም መልሱም ይገባችኋል - የኢሕአዴግ ሰዎች ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ አንድዬነት (economic monopoly) ራዕይ እዚህ ይጀምራል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደጉድ ሲወራለት የነበረው እና በአገራችን የመጀመሪያው የቤት መኪና መገጣጠሚያ የሆነው ሆላንድ ካር ኩባንያ ባለቤት ቤተሰቡን ይዞ ወደቀድሞ የስደት አገሩ ሆላንድ ኮበለለ፡፡ (በነገራችን ላይ መስፍን ኢንዱስትረያል ኢንጂነሪንግ የሚያመርታቸውን ‹‹አዲስ›› በሚል ስም የሚጠሩ አውቶሞቢሎች የትግራይ ክልል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዲሸምቱ መደረጉን ሰምታችኋል?) ዶ/ር ፍስሐ እሸቴንም ከእነዚህ ተርታ አታጡትም፤ የመጀመሪያውን የግል ከፍተኛ ተቋም (እርሳቸው ‹‹ልጄ›› ነው የሚሉት) ለወግ ማዕረግ ካበቁ በኋላ፣ በአንድ ወቅት ‹‹ኢሕአዴግዎችን ‹ለምን እንደሆነ እንጃ› ግን እወዳቸዋለሁ፤›› ብለው በይፋ ለተናገሩት ባለሃብት ሸጠው፣ ኮበለሉ - ምክንያቴ ፖለቲካዊ ጫና ነው ብለዋል፡፡ በርካታ ምሁራን በቃኝ ብለው ወደመጡበት አገር ተመልሰው ሄዱ፡፡ (እዚህች’ጋ ነገሩን በዋዛ ለማፍታታት ያክል ‹‹ሊዮኔል ሜሲ ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ወይ ለደደቢት ተጫወት አሊያም አገርክን ለቀህ ተሰደድ ይባል ነበር›› የሚለውን የከተማ ቀልድ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ቀልዱ ስደተኞቹን ፍስሐ ተገኝን እና ኤርሚያስ አማረን ሊያስናፍቃችሁ እንደሚችል አይጠፋኝም ሆኖም ቀልዱን አቁሜ ጽሑፉን መቀጠል አለብኝ፡፡)

ከተሰደዱበት የተመለሱት ብቻ አይደሉም መልሰው የሚወጡት፤ እዚሁ በዚሁ ተስፋ ቆርጠው የኮበለሉም ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ስላጣናቸው ሰዎች ናፍቆት ቁጭ ብዬ በዓይን እርግብግቢት አፍታ ያሰብኳቸው ሰዎች እንኳን ወደውስጥ የሚፈስ እንባ ዓይነት ቅሬታ ፈጥረውብኛል፡፡ ለፖለቲካውም፣ ለኢኮኖሚውም… ለሁሉም ስደት መንስኤው የፖለቲካው ሥርዓት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መናፈቃችን ካልቀረ ፖለቲካው ውስጥ ተስፋ አስጥለውን የነበሩትን ሰዎች እስኪ እናስታውሳቸው፡፡

Friday, December 28, 2012

ከተሜውን ናፍቆት


መንገድ ላይ ነዎት፤ አንድ ከተማን ለቀው ወደ ሌላ ከተማ እየተጓዙ ነው፤ ቢጓዙ ቢጓዙ ቀጥለው የሚጠባበቁት ከተማ አልደረሱም፤ ገጠሩ ረዝሞብዎታል፤ ‹እንዴ ይህ ሀገር ገጠር ብቻ ነው እንዴ?› ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ እባኮትን ዝም ብለው ይጓዙ ገና ብዙ የገጠር መንገድ ይቀርዎታል፡፡ ትንሽ ከተማ ነገር ያገኙ መስሎዎ ፈገግ ሊሉ ይችላሉ፤ አይሞኙ ፈገግታዎት ከከንፈርዎት ዘሎ፤ ፊትዎትን ከማዳረሱ በፊት ያች እያለፉትት ያለችው ከተማ ከመቅፅበት ከእይታዎት ተሰውራ በድጋሚ ከማያልቀው ገጠር ተቀላቅለዋል፡ እንግዲህ መበርታት ነው፡፡

ፍጡራን በዓለም ሲኖሩ መሰላቸውን ፈልገው እና ተፈቃቅደው አንድ ላይ መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ ሰው ልጅ ባህሪም ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች ይሄን ቁርኝት እና አብሮ መኖር አጠናክረው እና የበለጠ አጥብቀው በአንድ አብረው ይኖሩበታል፡፡ ከተሞችም የዚህ ግንኑነት ቀጥተኛ ውጤቶች ናቸው፡፡ በግንኙነቱ የሚፈጠሩት ከተሞች ሲመሰረቱ እና ሲወድሙ እንደገና ሲመሰረቱ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጠው በከተማ እንደሚኖር አወጀ፡፡ ከተሜው ዓለምን ከገጠሬው ተረከበ፡፡

ከተሜ (Urbanism)

የዓለም እድገት እየጨመረ በመጣ ቁጥር በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥርም እየጨመረ እንደሚመጣ፤ መረጃዎቹን ተመልክቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሄም ከተሜነትን ከእድገት ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ማስረጃ ነው፡፡ ብዙ የከተማ ነዋሪ በተፈጠረ ቁጥር የዛች ሀገር እድገት በተሻለ መስመር ላይ ነው እንደማለት፡፡  Bert  Hoselitz, የተባሉ ምሁር 'The Role of Cities in the Economic Growth of Underdeveloped Countries' ባሉት መፅሃፋቸው:

“Cities are sources of innovation, loci of and providers of motivation for change, and centers where a peasant may go to remove himself from the constricting political organization and static economy of the countryside.”
 
ይላሉ፡፡ ከተሞች የሀሳብ መፍለቂያ፣ የፈጠራ መመንጫ እንደሆኑ እና ለገጠሬውም ገጠር ከተሰኝው ‹እስር ቤ›ት ወጥቶ ወደ ‹ነፃነት ምድር› የሚገባበት በር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይሄም ስልጣኔ ከከተማ እንጅ ከገጠር አትቀዳም የሚለውን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ከተሜ ሰፊውን ዓለም በማወቁ ተጠቃሚነቱ ይጎላል፤ ዓለምንም ለመከተል ያተጋዋል፡፡

ገጠሬ

በሌላ በኩል ዓለምን ለረጅም ዘመናት ነግሶባት የኖረው የገጠሬነት ይትበሃል ነበር፡፡ በገጠሬ ባህል ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የተበተነ አኗኗር፣ ለለውጥ ድንጉጥ መሆን (Change Resistant)፣ የንፅረተ አለም (World Outlook) መጥበብ ዋነኛዎቹ እንደሆኑ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የኑው መበተንም ሀሳብ በጋራ እንዳይብላላ እና የሀሳብ ፍጭቶች (Thesis Vs. Antithesis) አዲስ ሀሳብ (Synthesis) እንዳይፈጥሩ ያግዳቸዋል፡፡ ለውጥን መፍራቱ ደግሞ በትናንት በሬ ለማረስ መሻትን፣ ዛሬን መርሳትን እንዲሁም ለነገ ባዕድ መሆንን ይፈጥርበታል ለገጠሬው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገጠሬው ዓለም ከአራቱ ጋራዎች አለመዝለሉ የታፈነ እና ሌላውን ዓለም የማያውቅ፤ ራሱንም ከሌላው ዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማያዋህድ ‹ደሴት› ያደርገዋል፡፡ አዎ ሕይወት በገጠር በባህር ተከበበች ደሴት ላይ ያለች ሚጢጢ ነገር ነች፡፡ ይህ ማለት ግን ገጠሬ ሁለ-ጭፍን እና በግምት የሚኖር ነው ለማለት አይደለም፡፡

ገጠሬው ከተማን ሲሻ

በተለያዩ መንገዶች ገጠሬው ወደ ከተማ መግባቱ አይቀርም፡፡ የስበት ሀይሉ (Center of Gravity) ከተማ ነውና ገጠሬው በከተማ ሀሳብ ይሳባል፤ ከተማም ይገባል፤ ራሱንም በከተሜ ሀሳብ ለመቅረፅ ይጥራል ከተሜም ይሆናል፡፡ ገጠሬው ከተሜ ሲሆን ምን ይፈጠራል? ስንል May Diaz and Jack Potter የተባሉ ፀሃፍት 'Introduction: The Social Life of Peasants', in Peasant Society ባሉት መፅሃፋቸው ላይ ‹‹የመንግስት ቁጥጥር ይበጣጠስል፤ መንደሩ ግን ይኖራል›› - “The state apparatus could disappear overnight and an individual village could still manage to survive” ይሉናል፡፡ ይህም ማለት ገጠሬው በከተማ መሻቱ ‹ግለሰቡን ሰው› ከትቢያ ፈልጎ የማውጣትን መላ ይማራል፤ ዓለምን ያውቃል፤ እንደገናም ዓለምን ያሰፋል፡፡

ገጠር እና ከተማ በኢትዮጵያ

የከተማ አመሰራረት እና እድገት በቀዳሚዎቹ ዘመናት በኢትዮጵያም የተለየ ታሪክ አልነበረውም፡፡ ከአክሱም ስልጣኔ መክሰም በኋላ በሀገሪቱ ከተማ የሚባለው ፅንሰ ሀሳብ ጨርሶ ጠፍቶ ነበር፤ የነገስታቱ ግዛትም እጅግ የጠበበ እና ከመንደር ያልዘለለ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በጦርነትም የነገስታቱ መቀመጫ የሆኑትን ‹ዓምባዎች› ሰብሮ የገባ ሀይል ስልጣኑን ለመያዝ ይቀልለት ነበር፤ ድሉንም ዓምባዎቹን ሙሉ ለሙሉ በማውደም ይገልፅ ነበር፡፡ ይሄም ዓምባዎቹ ጎልብተው ወደከተማነት የሚሸጋገሩበትን እድል በእጅጉ አቀጭጮታል፡፡ በነገስታቱ ወንዝን እና ተራራን መሰረት በማድረግ የሚመሰረቱት የመናገሻ ‹ከተማዎችም› ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ እና እዚህ ግባ ሊባሉ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ በዚህም ምክንያት ከተማና ከተሜነት ያልነበረ፤ ብቅ ሲልም በነገስታቱ ግብግብ ‹‹ጨርሶ አጠፋ› በሚባል ሁኔታ አመድ ሲሆኑ ነበር፡፡ ለዚህም ነው “During the past millennium in Ethiopia, the state and not the city has been 'the decisive criterion of civilization” ሲሉ Eric  Wolf የሚናገሩት፡፡

ይሄም ማለት ኢትዮጵያዊያን በገጠር መኖራቸው፤ በከተማ የሚገኝውን ጥቅም ከማጣታቸውም በተጨማሪ የመንግስት ‹ሎሌ› ሁነው ኖረዋል እንደማለት ነው፡፡ መንግስት ‹ነጭ-ኑግ፤ጥቁር ወተት; ውለድ እያለ ‹እርፍ አሸክሞ-ጅራፍ አንግቶ› ኢትዮጵያን ሲሰራና ሲያፈርስ ነበር እንደማለት፡፡

ከፊውዳሉ ወደ ላብ አደሩ ወደ አርሶ አደሩ

በፊውዳላዊ ስርዓቱ ወቅት ገጠሬው እንደ ገባር ለመኳንንቱ ተደልድሎ በጉልበቱ እና በላቡ የመሳፍንቱ ሎሌ ሆኖ ኖረ፡፡ ለምን እረገጣለሁ? ከማለት ይልቅ ‹ግብር በዛብኝ› የሚሉ ትንሽ አመፆችን በየቦታው አስነስቶ ከሸፈ፡፡ ሙሉ የመብት ጥበቃ ይደረግልኝ ሊል አልቻለም፤ ገጠሬ ነውና፡፡ ይልቁንስ  ተማሪዎች ‹መሬት ለአራሹ፣ ለላብ አፍሳሹ› ብለው የገጠሬው መብት ይጠበቅ ዘንድ ተነሱ እናም ፊውዳላዊውን ስርዓት ገረሰሱት፤ በላባደሩ የሚመራ ከተማ-ተከል አብዮትም ታወጀ፤ ወታደሩ በመሃል ገብቶ ነገሩን ሁሉ አፈረሰው፤ ህልሙን አደፈረሰው፤ ለስሙ ግን እኔም ለላባደሩ ነኝ ብሎ ገጠሬውን ገሸሽ ያደረገ ስርዓትም ዘረጋ፡፡ገጠሬውን ለማዘመን ወታደራዊው መንግስት በሰፈራ ፕሮግራሙ አማካኝነት ትናንሽ አዳጊ መንደሮችን ለመፍጠር ሙከራ አደረገ - አልተሳካም፡፡ ነገር ግን የገጠሬው ቁጥር በፊውዳሉ ስርዓት ጊዜ ከነበረው በትንሹ ሊቀነስ ችሎ ነበር፡፡

በወታደራዊው መንግስት የተተካው በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢሕአዴግ) አርሶ/አርብቶ-አደሩን በሌላ ቋንቋ ገጠሬውን መሰረት ያደረገ ዲሞክራሲያዊት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን እፈጥራለሁ በማለት ግብርና መር የኢንደስትሪ ስትራቴጂን ነደፈ፤ ስንቶች የከተማ ትግል ብለው እንደወጡ ሲቀሩ እኔ አርሶ አደሩ ዛፍ ፍሬ አፈራሁ አለ፡፡ ገጠሬውም ሀገሪቱን በአጠቃላይ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን በተለይ ለመምራት በትረ - ሙሴውን ጨበጠ፡፡

ገጠሬው ይመራልን?

ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ገደማ (በ1959 ዓ.ም) በማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን በወጣው መረጃ መሰረት የዛሬዋን ኤርትራ ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ 248 ከተሞች የነበሩ ሲሆን የከተማው ሕዝብ ብዛትም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ 8 በመቶውን ብቻ ይይዝ ነበር፡፡  በ2004 ዓ.ም በወጣው የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ መሰረት ደግሞ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ 973 ከተሞች ያሉ ሲሆን ከአጠቃላይ ሕዝቡም 17 በመቶ የሚሆነው በነዚህ ከተሞች ውስጥ ይኖራል፡፡ ይህም ማለት ቀሪው 83 በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ገጠሬ ነው ማለት ነው፡፡
 
ኢሕአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ከነበረው 86 በመቶ የገጠር ነዋሪ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በ3 በመቶ ብቻ ነው የተቀነሰው፡፡ በአብዛኛው የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ገጠሬዎች በአሁኑ ወቅት ድህረ-ገጠሬ (Post-Peasant)፤ ማለትም ከከተማ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት የሚፈጥሩ ነዋሪዎች ደረጃ ላይ እንደ ደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሄም ማለት በቀጣይ ወደ ከተሜነት ራሳቸውን ለመቀየር አንድ እርምጃ ወደፊት ሂደዋል ማለት ነው፡፡ መንግስት የኢትዮጵያ ገጠሬ ይሄን ደረጃ መውጣት ጀምሯል ቢልም፤ በ20 ዓመታት ከታየው የከተሜነት ጉዞ አንፃር ተመልክተው ‹አይ አይመስለንም› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
Frederick  Gamst  ስለ ኢትዮጵያ የከተማ-ገጠር ተወስኦ ሲያወሱ:
 
“Lack of urbanism is found to be hindering the rate of modernization in Ethiopia where nonliterate [sic] people are still gradually making the transition into peasants.” በማለት ነው፡፡ የከተሜነት አለማደግ ኢትዮጵያን ከዘመናዊነት ጉዞዋ አቅቧታል፤ ያልተማረው ሕብረተሰብም ገጠሬ እየሆነ ነው እያሉ ነው፡፡
 
መንግስት በበኩሉ በተደጋጋሚ እንደሚገልፀው ‹መሰረቴ፤ ሰፊው አርሶ አደር ነው› ይላል፡፡ ‹የዲሞክራሲ ተቋማትን እና የልማት አውታሮችን የምዘረጋው ይሄን አርሶአደር መሰረት አድርጌ ነውም› ይላል፡፡ በአወዛጋቢ የምርጫ ወቅት እንኳን ‹አመኔታ በገጠሬው ላይ ነው› ይላል፡፡ ነገር ግን ገጠሬነት ለሀገር እድገት ‹እዳ› ነው ይሉታል ምሁራን በበኩላቸው፡፡ ‹‹የተበተነ፣ ለውጥ-ጠል እና ዓለመ-ጠባቡን ገጠሬ እንደ መከታ መያዝ አይገባም፤ ይልቁንም ገጠሬውን አዘምኖ ከተሜ ማድረግ ነው ድሉ›› ይላሉ እነዚህ አካላት፡፡
 
ከላይ የጠቀስናቸው  Frederick  Gamst  ‘Peasantries and Elites without Urbanism: The Civilization of Ethiopia’  ባሉት ፅሁፋቸው ላይ የከተሜነት አለማደግን ጠቅሰው የሚያቀርቡትን ሂስ እንደገና እንጥቀስ፡
 
“Lack of urbanism prevents in Ethiopia the beginnings of a concentration of a pool of laborers who are without bonds to the land. Such a labor pool is necessary for industrialization, and thus for the ensuing general modernization of all of the ways of life in Ethiopia. Lack of urbanism will […] insulate Ethiopia and its peasants from fundamental changes in traditional ways of life.”
መንግስት እንደሚለው ጉዟችን ወደ ኢንደስትሪ ከሆነ መግስት በፍቅር የወደቀለት ገጠሬው ትልቅ መሰናክል ነው ማለት ነው፡፡ መንግስት በአንድ በኩል የኢንደስትሪ ልማትን (Industrialization) አመጣለሁ ብሎ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹ገጠሬውን አትንኩብኝ› እያለ መንታ መንገድ ላይ ቆሞል፤ አንድ እግሩን በግራ፣ አንድ እግሩን በቀኝ በኩልም እየለጠጠ ይገኛል፡፡ መጨረሻውስ? የለውጥ ፈር ቀዳጁን ከተሜስ መች ይቀርበዋል? መቸስ ገጠሬውን ከተሜ ያደርገዋል? ነው ጥያቄው፡፡

Wednesday, December 26, 2012

አክሱምን ወላይታ አገኘሁት!!! (የአርባ ምንጭ ጉዞ ማስታወሻዬ)


በናትናኤል ፈለቀ

ኅዳር 12 ቀን 2005 ዓ.ም በሥራ ጉዳይ ወደ ጋሞ ጎፋ ዞን ዋና ከተማ አርባ ምንጭ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ለሁለት ቀን ተኩል የሚበቃኝን  ሸክፌ ከመሥሪያ ቤቴ በተመደበልኝ መኪና ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ለሚነሳው በረራ ለመድረስ ወደቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ በቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን በኩል ወደ ቦሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘን ስንጓዝ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ ላይ የተደረደሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት አቀባበል ወይንም ሽኝት የሚደረግለት ባለሥልጣን/እንግዳ እንዳለ ስለጠቆመኝ መንገዱ ሳይዘጋ ቦሌ ለመድረስ ጥረት እንዲያደርግ ለሹፌሩ ጠቆምኩት፡፡ ብዙም ሳንጓዝ አትላስ ሆቴል የትራፊክ መብራት ላይ ስንደርስ በስፍራው የነበሩት የትራፊክ ፖሊሶች ወደ ቺቺንያ ወይንም ወደ ቦሌ ሩዋንዳ የሚወስደውን መንገድ እንድንጠቀም አስገደዱን፡፡ ወዲያውኑ ሰዓቴን ተመለከትኩ፤ ለሰባት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ይላል፤ ብዙም አልተረበሽኩም፡፡ በስተቀኝ በኩል ታጥፈን በውስጥ ለውስጥ አቋራጭ መንገድ ጥቂት ከሄድን በኋላ መልሶ ዋናውን መንገድ ስላገናኘን መኪናውን አቁመን እንግዳውን እስኪያልፍ መጠባበቅ ጀመርን፡፡

በዚያው ሰሞን ወደ ሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ሄዶ የነበረ አንድ የሥራ ባልደረባችን በአምስት ቀን ቆይታው ሁለት ጊዜ በመንገድ ያለፋቸው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በከተማው መንገድ ላይ ሲጓዙ እሳቸው ከሚጓዙበት አቅጣጫ በተቃራኒው የሚወስደው የመንገዱ ጎን ክፍት እንደሚሆን የነገረኝን ለሹፌሩ እያጫወትኩት ሳይረን እያሰማ የሚከንፈውን ሞተረኛ ተከትለው ካልተሳሳትኩ አምስት መኪኖች በፍጥነት ወደ ቦሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሲያልፉ አየን፡፡ ካለፉት መኪናዎች ሦስቱ ባለግርማ ሞገሶቹ ጥቋቁር ሼቭሮሌቶች ነበሩ፡፡ ያለፉት ባለሥልጣን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆን አለባቸው (በእርግጥም ነበሩ፤ ለሥራ ጉብኝት ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ እያቀኑ)፡፡ እንደ ሥራ ባልደረባችን ከሆነ ፕሬዝዳንት ካጋሜን የሚያጅቡት አንድ ሞተረኛ ፖሊስ ከፊት እና አንድ መኪና ከኋላ ሆነው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ይህን ሁሉ ጥበቃ የሚደረግላቸው ከፕሬዝዳንት ካጋሜ ይልቅ ለደኅንነታቸው የሚሰጉ መሪ ስለሆኑ ነው? ወይስ ኢትዮጵያዊያን ከሩዋንዳዊያን ይልቅ አስፈሪ ሕዝብ ስለሆንን? ይህንን እቆቅልሽ እያሰላሰልኩ መንገዱ ተከፍቶ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአገር ውስጥ በረራ የሚደረግበት ጣቢያ ቁጥር 1 ደረስኩኝ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቀልቤ አይወደውም፡፡ ምናልባት የመጀመርያ በረራ ባደረኩበት ወቅት በድርጅቱ እንዝላልነት ምክንያት ያጋጠመኝ በሕይወቴ ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ አጋጥሞኝ የማያውቅ እንግልት ተፅዕኖ አድርጎብኝ ይሆናል፡፡ ጥሎብኝ ደግሞ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸው የቤተሰብ አባላት እና የቅርብ ጓደኞቼ ለአየር መንገዱ ተቀጥረው ሠርተዋል/እየሠሩ ነው፡፡ አየር መንገዱ ላይ ያለኝ አቋም ከነዚህ ወዳጆቼ ጋር አልፎ አልፎ ቅራኔ ውስጥ ይከተኛል፡፡

ተርሚናሉ ውስጥ ገብቼ በመፈተሻ መሳሪያው ካለፍኩ በኋል የያዝኩት ሻንጣ ማሽኑን አልፎ እስኪመጣ ቀበቶዬን እያጠለኩ ስጠባበቅ ‹‹ወደ አርባ ምንጭ ስለሆነ እንጂ ሌላ ቦታ ቢሆን አይፈቀድም›› የሚለው ከማሽኑ ጀርባ ተቀምጣ ሻንጣዎች ውስጥ ያለውን እቃ በምስል የምትከታተለው የጥበቃ ባለሙያ ንግግር ቀና አደረገኝ፡፡ ‹‹አቤት›› አልኳት በተገረመ ድምፅ፡፡ ‹‹አይ አንተን አይደለም›› አለችን በአገጯ ከአጠገቤ የቆመውን ሰው እየጠቆመችኝ፡፡ ሰውየው ስሙ ያልተጠራው እሱ ሻንጣ ውስጥ ያለው እቃ ምን እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ተረጋጋሁ፡፡ ወዲያው ደግሞ ሌላ ሐሳብ ገባኝ፤ ሌላ በረራ ላይ የማይፈቀድ ነገር ግን አርባምንጭ ስለሆነ የሚፈቀድ እቃ ምንድን ነው?

የአየር መንገዱ ሠራተኞች የ‹ቼክ-ኢን› ሰዓታቸው የደረሱትን በረራ ተሳፋሪዎችን በሁለት መስኮቶች እያስተናገዱ ነበር፡፡ ከሚያስተናግዱት የአየር መንገዱ ሠራተኞች መካከል አንደኛዋ ፀጉሯን መሸፈኛ (በእስልምና እምነት ሥርዓት) ‹ሂጃብ› አድርጋለች፡፡ ‹ሂጃቡ› ከለበሰችው የአየር መንገዱ ሰራተኞች የደንብ ልብስ ጋር አብሮ እንዲሄድ መደቡ ነጭ ሆኖ አረንጓዴ መስመሮች ያሉበት ሲሆን በቀጭኑ ‹የኢትዮጵያ/Ethiopian› የሚል ጽሑፍ አርፎበታል፡፡ ብዙ ድርጅቶች እንኳን ለሠራተኞቻቸው ይቅርና ለሚያገለግሏቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ምቾት እምብዛም እንደማይጨነቁ ስለማውቅ በአየር መንገዱ እርምጃ ተደሰትኩኝ፡፡ ወድያውኑ ስልኬን አውጥቼ ብዙ ግዜ በአየር መንገዱ ላይ የማማርርባት ጓደኛዬን ቁጥር መታሁ፡፡ ስልኩ ሲነሳም በአየር መንገዱ ውስጥ እንዳለሁ ጠቅሼ የደወልኩት እንደበፊቱ ለማማረር ሳይሆን ባየሁት ነገር ደስ ስላለኝ እንደሆነ፤ ጥፋት ሲሆን እንደማማርረው ሁሉ በቀጣሪዋ ሥራ ስደሰትም ማመስገን እንዳለብኝ ጉራ ቢጤ ቸበቸብኩ፡፡

ከፊቴ ከነበሩት ሰዎች ቁጥር አንፃር ሰልፍ ላይ ረጅም ሰዓት ያሳለፍኩ ስለመሰለኝ ‹ቼክ-ኢን› አገልግሎት የሚሰጠት ሠራተኞችን መከታተል ጀመርኩ፡፡ ጥርጣሬዬ ልክ ነበር፡፡ እኔ ስደርስ ቀድመውኝ ከፊቴ ከነበሩት መንገደኞች መካከል ከሦስት በላይ ተሳፋሪዎች ‹ቼክ-ኢን› ጨርሰው ወደ እንግዳ መቆያ ስፍራ አልተመሩም፡፡ ችግሩን ለማጣራት ሞክሬ ጥፋቱ የደንበኞች አገልግሎት የሚሰጡት ሠራተኞች እንዳልሆነ ተረዳሁኝ፡፡ ችግሩ ሠራተኞቹን የሚረዳቸው ‹ሲስተም› እክል ስለገጠመው ነበር፡፡ የመንገድ መዘጋቱን ተከትሎ አብዛኛው ተሳፋሪ ዘግየት ብሎ በመድረሱ ምክንያት ሰልፉ በርከት ብሏል፡፡ የደንበኞች አገልግሎት ሰራተኞቹ ደንበኞቻቸውን በቶሎ ማስተናገድ ስላልቻሉ ኮምፒውተር እየቀያየሩ ይሞክራሉ፣ ስልኮቻቸውን እያነሱ ችግሩን ለበላይ ሰዎች ለማስረዳት ይሞክራሉ፣ ፊታቸው ላይ መጨነቃቸው ያስታውቃል፡፡ እዛው ሰልፍ ላይ ሆኜ ለስምንት ሰዓት አስራ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ቀሩት፡፡ አርባ ምንጭ ስራዬን የምጀምረው በማግስቱ ስለነበር ማርፈድ አላስጨነቀኝም፡፡ ነገር ግን ከአየር መንገዱ የተሰጣቸውን ሰዓት ተንተርሰው የሥራ ወይንም ሌላ ቀጠሮ የያዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገመትኩኝ፡፡ ‹‹ቀድሞ ማመስገን ኋላ ለሐሜት ይቸግራል›› የሚለውን የሀገሬን አባባል አስታወስኩኝ፡፡

ስምንት ሰዓት ሊሆን ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አንድ በአካባቢው ከዛ ቀደም ያላየሁት በእጁ መገናኛ ሬድዮ (ዎኪ-ቶኪ) የያዘ የአየር መንገዱ ሠራተኛ (የቅርብ አለቃ ይመስለኛል) ወደ ጅማ እና አርባ ምንጭ የምንሄድ ተሳፋሪዎችን ጠይቆ ከሰልፉ ውስጥ ለይቶ ‹ቼክ-ኢን› በ‹ማንዋል› እንዲሰራልን አዝዞ ወደ አውሮፕላኑ በቀጥታ እንድንሳፈር አደረገ፡፡

Monday, December 24, 2012

የደሞዝ Vs. የጠብሽ* ሰሞን
አነጋገራችንን፣ አካሄዳችንን፣ አበላላችንን፣ አስተያየታችንን ባጠቃላይ የምናደርገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ቀጥጠኛ አስተዋፅኦ ካላቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው በኪሳችን ያለው ገንዘብ ዋነኛው ነው፡፡ ገንዘብ ከምናገኝባቸው አንዱ መንገድ ደግሞ ተቀጥሮ መሥራትና ወር ሲያልቅ የሠራንበትን ክፍያ/ደሞዝ ማግኘት ይገኝበታል፡፡ አብዛኛው በከተማ አካባቢ የምንኖር በዚህ መስመር ውስጥ እንገኛለን፡፡

ደሞዝ ተቀብሎ ቀጣዩን የደሞዝ ቀን እንደ ምፅአት ቀን በጉጉት የማይጠብቅ ካለ ይህ ሰው ከደሞዙ ውጪ ሌላ ተጨማሪ ገቢ አለው ወይም አንድ ቀልድ ላይ እንደሰማሁት በአስማት ነው የሚኖረው ማለት ነው፡፡ ደሞዛችን እዛው እንዳለ ወይም በተወሰነ ጭማሪ… ብቻ ኑሮ ግን በብዙ እጥፍ ጨምሮ መኖር መቻላችን እውነትም አስማተኛ ያስብላል፡፡ እንደየደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ አብዛኛው ደሞዝተኛ ደሞዝ ከተቀበለ በኋላ ካሉት የተወሰኑ ቀናት ውጪ ለመጪው የደሞዝ ቀን ስንት ቀን እንደቀረው በመቁጠር፤ ቀሪውን ጊዜ በብድር እንዴት እንደሚያሳልፍ በማውጠንጠን፤ የሰቀቀን ኑሮ መኖሩን የተለማመድነው ይመስላል፡፡

የደሞዝ ሰሞንና የጠብሽ ሰሞን እንደየሰው ይለያያል፡፡ በአብዛኛው ደሞዝ ከተቀበሉ ከ10-15ኛው ቀን በኋላ ሰሞነ ጠብሽ ይገባል፡፡ ደሞዝ የተቀበሉ እለትም ደሞዟ ብድር ብቻ ከፍላ የዕለቱለት ጠብሽ የሚጀምርበት አጋጣሚም አለ፡፡ የበዓል ወቅቶች እና ጳጉሜ ወር “የጠብሽ” ወቅትን ከሚፋጥኑ/ከሚያረዝሙ ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጳጉሜ ወር ግን ለምን ደሞዝ እንደሌላት ሁሌም ይገርመኛል፡፡ በዛ ላይ የአዲስ ዓመት ወጪ ተጨምሮበት አስቡት፡፡

Monday, December 17, 2012

ስለለውጥ፤ ለውጥን መቋቋም እና መፍራትለውጥን በምናብ ይወዱታል እንጂ በተግባር አይዳፈሩትም - ሰዎች፡፡ የሥርዓት ለውጥ ሲሆን ደግሞ ፍርሐቱ ያይላል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ሲሆን ደግሞ ከማንኛውም ሥርዓት ለውጥ በላይ ያስፈራል፡፡ የፍርሐት ፖለቲካዊ አንድምታ ከታሪክ አንጻር እየተመለከትን ስለራሳችን ለውጥ እንድናወራ ነው ይህ ጽሑፍ የተጻፈው፡፡

የፍርሐት ዘመን (Reign of Terror፡ 1793-1794)

የመጀመሪያው የፈረንሳይ አብዮት መባቻ ላይ ከፍተኛ ፍርሐት ሰፍኖ ነበር፡፡ አምባገነኑ ሉዊስ 16ኛን ገርስሰው ሰብኣዊ መብት እና ሕገ-መንግስታዊ አስተዳደርን ከአሜሪካ ለመኮረጅ የሞከሩት ፈረንሳውያን እርስ በእርሳቸው ተቀናቃኝነት ባፈሩት የለውጡ መሪዎች ጊሮንዲኖች እና ያቆቢኖች (Girondins and the Jacobins) አንደኛው ሌላኛውን ‹‹የአብዮቱ ጠላት›› በሚል በደም የታጠበ አብዮት በማድረጋቸው 25 ሺሕ ለሚደርሱ ሰዎች እልቂት መንስኤ ሆኗል፡፡ ያንን ጊዜ የፍርሐት ዘመን (The Reign of Terror) በሚል ታሪክ ጸሐፊያን ያስታውሱታል፡፡

እኔ የፈረንሳዩ አቻ ትርጉም ነው ልለው የምለውን ማሕሌት ፋንታሁን የፍርሐት ዘመን በሚል ርዕስ ዞን ዘጠኝ ላይ ከዚህ ቀደም ጽፋዋለች፡፡ ጽሑፏ ያለንበትን የፍርሐት ወቅት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ፍርሐታችን የፈረንሳይ አብዮት የወለደው የ‹‹ፍርሐት ዘመን›› ጋር የሚያመሳስለው ነገር ይኖር ይሆን በሚል የሚከተለትን ሁለት ክስተቶች ለማስታወስ እንገደዳለን፡፡

ሀ). ቀይ ሽብር

ምናልባትም ለአሁኑ ትውልድ አባት የሚባሉት የ‹‹ያ ትውልድ›› አባላት፣ የሚፈልጉት ለውጥ አቅጣጫውን እንዳይስት እና በየግላቸው መቆጣጠር እንዲመቻቸው ሲባል የሄዱበት መንገድ ሽብር ነበር - ቀይ እና ነጭ ብለው የሰየሙትን ሽብር፡፡

በዚህ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆነ የሽብር ድርጊት ሳቢያ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች አልቀዋል፡፡ ሌኒን ‹‹ያለ ቀይ ሽብር ማኅበረሰባዊነት አይገነባም›› ብሏል በሚል በአንድ ርዕዮተ ዓለም እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ በሚል እና ደርግ ጊዜያዊ መንግሥት አቋቁሞ ወደካምፑ ይመለስ የሚሉና ሌሎችም አብዮቱን ያቀጣጠሉ ጥያቄዎችን መልስ በመሻት እና በመነፈግ መካከል ለመገዳደል ሳይቀር የሶቪየት ኅብረትን ቀይ ሽብር የሚል ስም የተዋሱት ኢሠፓዎች እና ነጭ ሽብር የሚባል ምላሽ የሰጡት ኢሕአፓዎች ልክ የፈረንሳይ አብዮት ልጆች እንደሆኑት ጊሮንዲኖች እና ያቆቢኖች ‹‹አብዮት ልጆቿን በላች›› ተብሎላቸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የቻለው ሲሰደድ የቀረው መፍራት የሚችለውን ያክል የሚፈራበት ታሪክ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ፍርሐት  በከፊል የተቀረፈው በኢሕአዴግ አፍላ የሥልጣን ዘመን ነበር፡፡

Wednesday, December 12, 2012

ዘመቻ ገለአድበታምራት ተስፋዬ

ሰከንዶች ደቂቃን፣ ደቂቃ ሰዓትን፣ ሰዓት ቀናትን እየፈጠሩ ይኸው ዛሬ ላይ ደረስን፡፡ 

ዛሬ ትላንት አይደለም፤ ትላንት የዓለምን ሁኔታ  ለመተንበይ የነቢይነትን  ሚና  መጫወት አይጠበቅብንም ነበር፡፡  ትላንት የዓለም  ሁኔታ  በአዝጋሚ   ለውጥ ውስጥ   ከመሆኑም በላይ  ዓለም ለስር ነቀል ለውጥ የተጋለጠች  አልነበረም፡፡ ዛሬ  ሁሉ  ነገር ከመለወጡ የተነሳ ነገን  ለመተንበይ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ   ተደርሷል፡፡ የማትጨበጠውን ዓለም ለመረዳት ሀገራችን ባለፉት  ሦስት  ወራት ያሳለፈውን ሁኔታ  ማሰብ ብቻ   በቂ ነው፡፡  ለዛሬም የሰሞኑ  ዓቢይ  ክስተት  የሆነውን ፖለቲካዊ ለውጥ  እስኪ ትንሽ    አብረን እንየው፡፡

በነገራችን  ላይ  ገለአድ ማለት በመጽሐፍ  ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ  የተራራ ስም ሲሆን  ጌዴዮን ደፋር እና ፈሪ  ወታደሩን የለየበት ቦታ ነው፡፡  እንደሚታወቀው  ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለማርያም  ከሰሞኑ  ኳታር ደሃ ላይ  ሰንብተው  ተመልሰዋል፡፡  ከዓመታቶች  በፊት ኳታር  ከኤርትራ ጋር  ባላት ቅጥ ያጣ ግንኙነትና  ተዛማጅ  ጉዳዮች ጋር  ተያይዞ   ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ   ግንኙነቷን   ከማቋረጧም በላይ የጐሪጥ መተያየት  ደረጃ  ላይ  ደርሰው እንደነበር የቅርብ ጊዜ  ትዝታ  ነው፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትራችን   ከሦስት  ወር በፊት  ራዕይ ስለማስቀጠል   እና   ራዕይ   ስላለመበረዝ   አበክረው ሲገልጹልን  የነበረ ቢሆንም  ቃላቸውን   ጠብቀው  ለመዝለቅ   ሦስት ወር  እንኳ   ሳይሞላ  መንታ መንገድ ላይ የቆሙ   ይመስላል፡፡   የኳታሩ  ጉዞ  ምን ዓይነት ፖለቲካዉ ተግዳሮት አለው?  እውን  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የገለአድን ተራራ መውጣት  ጀምረው ይሆን? ከጉዞው  በስተጀርባ ሀገራችን ምን ትጠ ብቃለች? እስኪ  ትንሽ   እንየው፡-

የሰሞኑ የጦማሮች እፍታ


  በማሕሌት ፋንታሁን

የፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ኦፕን ሳሎን ጦማር ‹ሱዛን ራይዝና ሶስቱ የአፍሪካ እርኩሶች[ Susan Rice and Africa’s Unholy Trinity]› በሚል ፅሁፋቸው በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሱዛን ራይዝ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጋር ለሁለት አስርት አመታት ስታሽቃብጥ እንደነበረ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ሶስቱ እርኩስ መሪዎች የተባሉትም የአምባሳደር ሱዛን ምርጫ የሆኑት--የሩዋዳው ፖልካ ጋሜ፣የኡጋዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ በሶስቱ ሃገራት በለፉት ሃያ አመታት የነበራትን ታሪካዊ ግንኙነት በዝርዝር አሰቀምጠውታል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ 

 

‹ኢህአዴግ ህገመንግስቱን መቼ መቼ ነው የሚጠቀምበት… ለአመትባሉ ይሆንን!?› የሚለን ደግሞ የአቤቶኪቾው ጦማር ነው፡፡ በዚሁ ጦማሩ በዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማሪያን ቡድን ስለተዘጋጀውና “ህገ መንግስቱ ይከበር” በሚል መፈክር ስላነገበው ዘመቻ፣ መድረክ ኢህአዴግ ሕገመንግስቱን በመጣሱ ሊከሰው መሆኑን እና ሌሎች ከህገመንግስቱ ጋር ተያያዥ ሆኑ ጉዳዮችን አስነብቦናል፡፡ ሲያሽሟጥጥም እንዲህ ብሏል፡፡ “መድረክ፤ ‹ኢህአዴግ ህገመንግስቱን ጥሷል› ብሎ ፍርድ ቤት ሊገትረው እንደሆነ ሰምተናል። ጥሩ ሀሳብ ነው። እስቲ ‹ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ› የሚለው ብሂል መቅረት እና አለመቅረቱንም በዛው “ቼክ” እናድርገው።” ሙሉውን ለማበብ እዚህ ይጫኑ፡፡ 

ዘ ሊትል ቴስ የተሰኘ ጦማር ‹ ትናንሽ መንግስታት ብሶቴ….› በሚለው ፅሁፉ ፀሃፊው የቀበሌ መታወቂያ ለማግኝት ወደ ቀበሌ ጎራ ባለበት ወቅት የታዘበውን ያካፈለን ሲሆን ብሔርን በተመለከተ ቀበሌዎች ያላቸውን አሰራር ተችቷል፡፡ ብሔርን በተመለከተም ጓደኛው ያጫተውንም ሲነግረንም እንዲህ ብሏል፡፡ “ከአመት በፊት ጓደኛዬ ስራ ለማግኘት ሲል ፎርም ያስሞሉት የነበሩ ሰዎች ብሔሩን እንዳስቀየሩት አጫውቶኛል፡፡ እሱ ምክንያቱ ደግሞ በጣም አስቂኝ ነበር፡፡ ወጥሮም ተከራክሮ ነበር ሁኔታው ግን የእንጀራ ጉዳይ ነበር እና ተቀብሎ ወጣ፡፡ ስራውንም አገኘ፡፡  ብሔር የቀየረበት ምክንያት ደግሞ ለእናንተ ብሔር የተመደበው ኮታ ስለሞላ  ስራውን ከፈለክ እንደዚህ ተብለህ መፃፍህ ግድ ነው፡፡ ተብሎ ነው፡፡” ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡     

ካፋ ፎር ፍሪደም የሚባለው ጦማር ደግሞ ‹በ2012 ዓለም አቀፍ የአገሮች የሙስና ሰንጠረዥ፤ የኢትዮጵያ ገጽታ በጨረፍታ› በሚል ርዕስ ዓለም አቀፉ የጸረ-ሙስና የአገራትን የመልካም አስተዳደር ይዞታ የሚከታተለው ተቋም Transparency International ዓመታዊውን የዓለም አገሮች የሙስና ደረጃ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን ኢትዬጵያ ከ 177 ሃገራት 113ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኗን እና 2012ቱን ዓመታዊ የአሮች ገጽታ በመግቢያቸው የቃኙት  ካናዳዊቷ  የድርጅቱ ሊቀመንበር Labelle «ሙስና በከፋባቸው አገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝም ያንኑ ያህል የከፋውን መስመር ይይዛል፤» ማለታቸውን በፅሁፉ ገልጧል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ

ከበደ ካሳ የተሰኘው ጦማር  ‹አዲስ ራዕይ › በሚል ርዕስ ስለ አዲስ ራዕይ መፅሄት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዞአል፡፡ “እዉነቱን  ለመናገር  የኢሕአዴግ  የንድፈ  ሃሳብ  መፅሄት  የሆነችዉ  አዲስ ራዕይ  መፅሄት  ዋና አዘጋጅ  ታላቁ  መሪ  መለስ  ዜናዊ  እንደነበር አላዉቅም ነበር፡፡ በርግጥ መለስ  ዜናዊ  በተለያዩ  መድረኮች ከሚያራምዳቸዉ  አቋሞች  ጋር  የሚመሳሰሉ  ፅሁፎችን በመፅሄቷ  ስመለከትና  በይዘቷና  በአቀራረቧ  ካላት  ብስለት  አንጻር  በመመዘን  ‘ሰዉየዉ’ ፅፏት ይሆንን  ብዬ  መጠርጠሬ  አልቀረም፡፡ ዋና  አዘጋጇ  መለስ መሆኑን  ርግጠኛ  መሆን የጀመርኩት  ግን  የዚህ  አመት  የመጀመሪያዋ  ልዩ  እትም  የገበያ ማስታወቂያ/commercial ad/ በኢትዮጵያ  ቴሌቪዥን  ሲነገር  ነዉ፡፡” ፅሁፉ ስለ አዲስ ራዕይ መፅሄት የፃፈውን ሙሉውን ለማግኘት እዚህ ላይ ተጫኑ፡፡


ይሔው ጦማር ‹እዉቅና እና እዉቀት፤ ዱባ እና ቅል› በሚል አርዕስት ሰሞኑን በኢቲቪ ተላልፎ በነበረውና ሴቶች በማስታወቂያ ላይ የሚጫወቱትን ሚና በሚል የመወያያ ርዕስ  ፕሮግራም ላይ የተሰማውን ሃሳብ በፅሁፉ አስፍሯል፡፡ “የሴቶችን ገላ ለምርት/አገልግሎት ማሻሻጫ መጠቀምም የማስታወቂያዎቻችን ችግር ሆኖ ቀርቧል፡፡ በአስተዋዋቂዋ አማላይ ዉበት ተማርከን ምርቱን/አገልግሎቱን እንድንገዛ የሚፈልጉ ነገር ግን ስለሸቀጡ የማይነግሩን አሉ ነዉ ያለዉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ፡፡ እነዚህ ቅሬታ ያዘሉ አስተያየቶች የተሰነዘሩባቸዉ የማስታወቂያ ባለሙያወችና አስተዋዋቂዎች ታዲያ የየራሳቸዉን ምላሽ ይዘዉ ቀርበዋል፡፡ እኔን የሳቡኝና ቅሬታዬን እንዳቀርብ የገፋፉኝ ታዲያ የተሰጡት መልሶች ናቸዉ፡፡” ብሎ ቅሬታዎቹንና የራሱን ሃሳብ የገለፀበትን ሙሉ ፅሁፍ እዚህ ላይ ተገኙታላችሁ፡፡

‹የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች መጨመር ሕገ መንግሥታዊነት?????›  የሚል  ፅሁፍ ያስነበበን የሚኒሊክ ሳልሳ ጦማር ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ስለ ሦስት ም/ጠ/ሚኒስቴር ሹመትና ሕገመንግስታዊነት፤ ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚናገረው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አንቀጽ 75 በመጥስ ስለ ወቅታዊውን ጉዳይ ዳሷል፡፡ ሙሉውን ለማግኘት እዚህ ላይ ተጫኑ፡

 

ይሄው ጦማር  በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የኦነግ አባል  ሆነዋል  በሚል  በተከሰሱት  በቀለ  ገርባ፣ ኦልባና ለሊሳ፣ ወልቤካ ለሚን  ላይ  እና ሌሎች በአሸባሪነት ክስ በተመሰረተባቸው ሰዎች ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን ፅፏል፡፡  “1ኛ. አቶ በቀለ ገርባ – በ8 ዓመት እሥር 2ኛ. ኦልባና ለሊሳ – በ13 ዓመት እስር 3ኛ. ወልቤካ ለሚ – በ7 ዓመት እስር 4ኛ. አደም ቡሳ – በ3 ዓመት እስር፣ 5ኛ. ሀዋ ዋቆ – በ8 ዓመት፣ 6ኛ. መሀመድ ሙሉ- በ 10 ዓመት እስር 7ኛ. ደረጀ ከተማ – በ8 ዓመት እስር፣ 8ኛ. አዲሱ ሞክሬ – በ10 ዓመት እስር 9ኛ ገልገሎ ጉፋ – በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከሁለት እስከ አራት ዓመት ለሚደርስ  ጊዜም ህዝባዊ መብታቸው ፍርድ ቤቱ መሻሩም ታውቋል።” ሙሉውን እዚህ ላይ በመጫን ታገኙታላችሁ፡፡ 

 

በዚሁ በዞን ዘጠኝ ጦማር ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት አራት ጦማሮች የተፃፉ ሲሆን ከነዚ ውስጥ ሶስቱ ‹ሕገ መንግስቱ ይበር› በሚል ለሶስት ቀን የቆየው የበይነመረብ ዘመቻ ቀናት በተከታታይ ለንባብ የበቁ ናቸው፡፡

 

በዘመቻው የመጀመሪያ ቀን የወጣው  የበፍቃዱ ኃይሉ “ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ” የተሰኘው ፅሁፍ ሲሆን በሕገ መንግሥቱ የጠቅላይ ሚኒስትርን ተግባር የተጠቀሰባቸውን ቦታዎችና ተግባር ደብዳቤውን ለመፃፍ የተገደደበትን ምክንያት እንዲህ ያስረዳል፡፡ “አንቀጽ 74 ፥ ቁጥር 13 ላይ “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል” ይላል፡፡ ትንሽ ከፍ ብሎ ደግሞ በቁጥር 8 ላይ “የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብቃት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል” ይላል፡ እናም እርስዎ በቅርቡ አመራሩን የተረከቡት መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ሕገ መንግሥቱን በመጣስ የመቃወም፣ የመደራጀትና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንደወንጀለኝነት እንዲፈሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እያደረገ በመሆኑ እና በውጤቱም ብዙ ንጹሐን ዜጎች በሠላማዊ ትግል ተስፋ እየቆረጡ እንዲሳደዱ፣ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርጉ፣ “አሸባሪ” ድርጅቶችን እንዲቀላቀሉ እያስገደደ መሆኑን በመታዘቤ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ልጽፍልዎ ተገድጃለሁ፡፡” በማለት ተጣሱ የሚላቸውን አንቀፆች እና ነባራዊውን ሁኔታ በዝርዝር አከቷል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

በዘመቻው ሁለተኛ ቀን የተፃፈው ደግሞ የዘላለም ክብረት ‹ሕገ መንግስታዊነት› የተሰኘው ፅሁፍ ነው፡፡ የሕገመንግስት አስፈላጊነት እና ፅንሰሃሳብ፣ የሕገመንግስት ዓለማና ተግባር፣ ሕገመንግስት ያለሕገመንግስታዊነት የነበረበትን የንጉሡን ዘመንን እንዲሁም አሁንም ተመሳሳይ ችግር የሚታይበት ኢህአዴግ መንግስት እንዴት ሕገመንግስት እንደማይከበር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም አካቷል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ 

በሶስተኛው እና በመጨረሻው የዘመቻ ቀን ‹ሰብኣዊ መብቶች፣ ሕገ-መንግሥቱ እና መንግሥት› የሚለው ፅሁፏን የስነበበችን ሶሊያና ሽመልስ ናት፡፡ ሶሊያና በዚህ ፅሁፏ ሰብዓዊ መብትን የሚመለከቱ አንቀፆች በሕገመንግስቱ መካተታቸውን ነገር ግን ተግባር ላይ የመዋል ችግር እንዳለባቸው፣ የተናቁ አንቀፆችን ዝርዝር እና የተጣሱበትን ሁኔታዎች እንዲሁም መፍትሔ ያለችውን ያስቀመጠችበት ሲሆን ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

ሌላው በዚሁ የዞን ዘጠኝ ጦማር ትላንት የወጣው በፍቃዱ ‹ስለለውጥ› በሚል በተከታታይ እያቀረበ ያለውን ፅሁፍ ሲሆን በዚህኛው ክፍል ደግሞ “ስለለውጥ፤ አብዮት ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?” ይለናል፡፡ በፍቃዱ በዚህ ፅሁፉ ስለ አብዮትና አዝጋሚ ለውጥ ምንነት፣ ለውጥ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በማሕበራዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶችም ላይ እንደሚያስፈልግ፣ የፈረንሳይ አብዬቶች እና በኢትዬጵያ ስለታዩ አብዮቶች እንዲሁም የአብዮትና የአዝጋሚ ለውጥ ባህሪያትን በዝርዝር የፃፈበት ሲሆን ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

 

መልካም ንባብ! 

  

 

 

 


ዘ ሊትል

ብሶቴ

ዘ ሊትል

 

 

 

 

 

Monday, December 10, 2012

ስለለውጥ፤ አብዮት ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?
‹‹ለውጥ የማይለወጥ ሕግ ነው፤›› አሮጌውን በአዲስ መተካት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ የቡድን ሥርዓት ለውጥን ማምጣት ነጠላ ለውጥ እንደማምጣት ቀላል እና ተቆጣጥረው በተፈለገው አቅጣጫ በቀላሉ ማስኬድ የማይችሉት መሆኑ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ የጊዜ ጉዳይ አለ፤ ለውጡ በቶሎ ነው የሚፈለገው ወይስ ቀስ ብሎ ይደርሳል? በአንድ ዘርፍ ነው ወይስ በብዙ ጎኖች?

በአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግ የሚስማሙ ሰዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፤ የሥርዓት ለውጥ የማይፈልጉት እንኳን ሥርዓቱ በስም ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይበት ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ብቻውን ለውጡን እውነተኛ ያሰኘዋል? በሁሉም ረገድ ለውጥ ለማምጣት የትኛው መንገድ ያዋጣል? አብዮታዊ ወይስ ዘመን አመጣሽ (አዝጋሚ ለውጥ)?

‹‹ለእያንዳንዱ ትውልድ አንድ አብዮት›› ያስፈልገዋል ይባላል፡፡ በተለይ የሰሜን አፍሪካ ሕዝቦች ረዥም ዓመት የቆዩ መሪዎቻቸውን በአብዮት ከገረሰሱ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ሌሎች ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሌሎች አገራትም በአብዮት ምጥ ተይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከ1960ዎቹ ወዲህ ልታይ የነበረው ለውጥ ምናልባትም የ1997ቱ የምርጫ ለውጥ ነበር፤ አልተሳካም እንጂ ቢሳካ ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ያህ ነበር፣ ሕዝቡም የሥልጣን ባለቤት ይሆን ነበር፡፡

የምርጫው መክሸፍ የተዳፈነ የአብዮት ስሜት ቀስቅሷል ባይ ነኝ፡፡ ያ የተዳፈነ የአብዮት ስሜት በሰሜን አፍሪካውያውኑ አብዮት ተነቃቅቶ አብዮት ይመጣል በሚል ተስፋ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆን፣ አብዮቱን እንመራለን የሚሉም እንቅስቃሴ ጀማምረዋል - ጥቂቶቹ በማኅበራዊ አውታሮች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከባሕር ማዶ፡፡ እኔ ግን አሁን ልጽፍ  የምፈልገው ስለእነዚህ እንቅስቃሴዎች አይደለም፤ ‹‹ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አብዮት ነው ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?›› የሚል ጥያቄ ጠይቄ መልስ አፈላልጋለሁ፤ አብረን እናፈላልግ፡፡

አብዮትም ሆነ አዝጋሚ-ለውጥ ሁለቱም የሽግግር መንገዶች ናቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከራሷም ሆነ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመነሳት የሚያስፈልጋት አብዮታዊ ለውጥ ነው ወይስ አዝጋሚ /ሒደት የወለደው/ ለውጥ የሚለውን በአፅንኦት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የአብዮት እና የአዝጋሚ-ለውጥ ለውጦች (‘Revolutionary and Evolutionary changes’) ብዙ ተፈጥሯዊና የማይነጣጠሉ (አብረው የሚጓዙ) ባሕርያት አሏቸው ሆኖም ሁለቱም የየራሳቸው መለያም አያጡም፡፡ የአብዮት ለውጥ ትልቅ እርምጃ ባንዴ የሚራመዱበት፣ ከተሣካ የሚፀና ነገር ግን አስፈሪ እና በተግባር ለመተርጎም የሰው ሕይወት የመክፈል ያክል የሚከብድ፣ ብዙ ጊዜ በአንድ የፖለቲካ ወይም ሌላ ስርዓት ላይ በማመጽ የሚመጣ ነው፡፡ የአዝጋሚ-ለውጥ ለውጥ ግን በአንዴ ጥቂት /የማይስተዋል/ እርምጃ የሚሄዱበት፣ አተገባበሩ አደጋ የሌለው ነገር ግን ለውጡን ለማፅናት የሚከብድ እና ረዥም ጊዜ የሚፈጅም ነው፡፡

የቱ ነው እውነተኛ ለውጥ የሚያመጣው? የቱን ለውጥ ነው ሕዝብ የሚፈልገው? የትኛው ለውጥ ነው ለሕዝብስ የሚያስፈልገው?