በዘላለም ክብረት
አፍሪካ ከበደ ገና በአስራዎቹ የዕድሜ መጨረሻ ላይ ያለ ወጣት ነው፡፡ በጣም ተስፈኛ ነው፡፡ ሁሌም ለውጥ እንደሚመጣ መናገር ይወዳል፡፡ ለምን ስሙ ‹አፍሪካ› እንደተባለ ሲጠየቅ ደጋግሞ ወደ መምህር አባቱ ይጠቁማል፡፡ አባቱ ስድስት ልጆች እንዳላቸውና የመጀመሪያዋን ዓለም፣ ሁለተኛውን አፍሪካ፣ ሦስተኛውን ኢትዮጵያ፣ አራተኛዋን ኦሮሚያ፣ አምስተኛዋን ወለጋ እንዲሁም ስድስተኛዋን ደግሞ ሊሙ ብለው ስም እንዳወጡላቸው ለጠየቀው ሁሉ ፈገግ እያለ መናገር አይሰለቸውም፡፡ አፍሪካ በወጣትነት ዕድሜው የትውልድ ከተማው የምስራቅ ወለጋዋ ሊሙ ወረዳ፣ ገሊላ ከተማ ውስጥ የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መሆን ብዙ መዘዝ በሚያስከትልበት አገር አፍሪካ በተስፋ ጽሕፈት ቤቱን በራሱ ያቋቋመው ‹የአካባቢው ሰው አማራጭ እንዲኖረው› በሚል ሐሳብ እንደሆነና፤ ከፓርቲው የማረጋጋጫ ፈቃድ ተቀብሎ በጽሕፈት ቤቱ ጊቢ ውስጥ የኦፌኮን አርማ የያዘ ሰንደቅ ዓላማ ከክልሉና ከብሔራዊው ሰንደቅ ጎን የሰቀለ እለት በወረዳዋ የተፈጠረው ትርምስን እያስታወሰ ፈገግ ይላል፡፡ ‹‹አፍሪካ የመረራን ባንዲራ ሰቀለ›› በሚል የወረዳው አመራሮች ተሰብስበው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተወያይተው ለጥቂት ቀናት ከታሰረ በኋላ በፓርቲው ጥረት ተፈቶ ወደስራ እንደገና አንደተመለሰ ይናገራል፡፡ ‹‹የእኛ ጽሕፈት ቤት መክፈት በወረዳው አመራሮች ለሚበደሉ ሰዎች ትልቅ ተስፋ ሁኖ ነበር›› ይላል አፍሪካ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የመንግስት ሰራተኞች አለቆቻቸውን ‹‹አላሰራም የምትሉን ከሆነ አፍሪካ ጋር ሒደን እንሰራለን›› እያሉ ያስፋራሩ ነበር ይላል፡፡
ለአፍሪካ የፓርቲው መኖር ትልቁ ትርጉሙ ለዜጎች ተስፋ መስጠቱ ነበር፡፡ ከዚህ ተስፋ ጀርባ ደግሞ አንድ ስምን ደጋግሞ ያነሳል፤ መረራ ጉዲና፡፡ ‹‹ዶክተር ጋር ከደወልኩ የማንፈታው ችግር አልነበረም፡፡ የታሰሩ አባላቶቻችን በአንድ ስልክ ወዲያው ነበር የምናስፈታው›› ይላል መረራን እያወደሰ፡፡ በርግጥም አፍሪካ በወጣትነቱ ተስፋ ስለሰጡት ጎልማሳ መረራ ጉዲና አውርቶ አይጠግብም፡፡
የሦስት ጨቋኞች እስረኛ
መረራ ከ21 ዓመታት በፊት በሚያዚያ 1988 የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስን (ኦብኮ) ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር ሲመሰርቱ የሚጓዙት መንገድ ረጅም እና አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አልገመቱም ማለት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ከነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አንፃር እንዲሁም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የኢሕአዴግ አካሔድ ትዝብታቸው ነበር ለዚህ ድምዳሜያቸው መሰረቱ፡፡
የንጉሱን አምባገነናዊ ስርዓት እንደ ዕድሜ አቻዎቻቸው በማርክሳዊ መንፈስ ተለክፈው ተቃውመው በመነሳት ገና በአስራዎቹ የዕድሜያቸው መጨረሻ ነበር በትውልድ አካባቢያቸው አምቦ ለመጀመሪያ ጊዜ እስርን የቀመሱት፡፡እስራቸው አጭርና የማያስቆጭ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ እንደማንኛውም የዘመናቸው ወጣት የሶሻሊዝምን ጠበል የተረጩት በዛው ዘመን ነበር፡፡ ‹እኔ› ማለት ትተው ‹እኛ› ማለት የጀመሩበት ዘመን፡፡ መታሰራቸው የፖለቲካ ፍላጎታቸው ጨመረው እንጅ አልቀነሰውም፡፡
መረራ ለሁለተኛ ጊዜ ሲታሰሩ አዲስ መንግስት ተቋቁሞ የእራሳቸውም የፖለቲካ ተሳትፎ በእጅጉ ከፍ ያለበት ወቅት ነበር፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄን (መኢሶንን) በዩንቨርስቲ የትምህርት ጊዜያቸው የተቀላቀሉት መረራ፤ ፓርቲያቸው ጨካኙን የደርግ ስርዓት ‹ይስተካከል ይሆናል› በሚል ተስፋ እየገሰፀ ለመደገፍ በወሰነው መሰረት ሁለት ዓመታት ያክል በስጋት ከኖረ በኋላ ደርግ ፊቱን ሲያዞርበት እርሳቸውም እንደ ማምለጥም እንደ ሽፍትነትም አሰኝቷቸው ሲሸሹ ከትውልድ ቀያቸው ብዙም ሳይርቁ ተያዙ፡፡ አሁን አልፎ ሲያስታውሱት የፓርቲያቸው አመራሮች ከመዲናዎ ወጥተው ሱሉልታ ላይ መያዛቸውን አስመልክቶ ‹‹የመኢሶን ሽፍትነት ከሱሉልታ አላለፈም›› ለሚሉት መረራ የእራሳቸው ሽፍትነት በመጠኑም ቢሆን የተሻለ ርቀት ተጉዞ ነበር፡፡
የመረራ ሁለተኛ እስር ግን እንደመጀመሪያ ቀላል አልነበረም፡፡ ከሰባት ዓመታት በላይ ታስረዋል፡፡ የታሰሩበትን ምክንያት በውሉ አልተነገራቸውም፡፡ ጓደኛቸው ‹‹ ‹ቀንደኛው ወንበዴው መረራ ጉዲና ከነሙሉ ትጥቁ በቁጥጥር ስር ዋለ› የሚል ፅሁፍ በወቅቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተፅፎ አይቻለሁ›› እያለ ይቀልድብኝ ነበር ይላሉ ስለተያዙበት ሁኔታ ሲተርኩ፡፡ በርግጥም ይህን መሰል ዜናዎች በወቅቱ በርከት ብለው ይታዩ ነበር፡፡ ‹‹ቀንደኛው ወንበዴ አሊ ፋሪስ ከግብረ አበሮቹ ጋር ተያዘ››፤ ‹‹በጢቾ ማማ አብዱልቃድር የተባለ ቀንደኛ ወንበዴ ከነመሳሪያው ተያዘ››፤ ‹‹በጀልዱ ወረዳ በ19 ወንበዴዎች ላይ አብዮታዊ እርምጃ ተወሰደ›› … የሚሉ ዜናዎች የመንግስታዊው ጋዜጣ የፊት ገፅ አድማቂዎች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን እርሳቸው በታሰሩበት ወቅት የታተሙትን መንግስታዊ ሕትመቶች የፊት ገፆች አስሰን ‹‹ቀንደኛው ወንበዴው መረራ ጉዲና ከነሙሉ ትጥቁ በቁጥጥር ስር ዋለ›› የሚለውን ዜና ማግኝት ባንችልም ግመታው (the claim) ከእውነታው ብዙም የራቀ ነው ማለት አንችልም፡፡
በርግጥ የመረራ የደርግ እስር ቤት የሰባት ዓመታት ቆይታ መረራን እጅግ ቀይረዋቸው ነበር፡፡ እርሳቸው እንደሚሉትም፡
ከአምቦ የተማሪዎች ንቅናቄ ተጀምሮ እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም አልፌ፣ ሰባት ዓመት ታስሬ ስወጣ በጣም ካልተገፋሁ በስተቀር የጭንቀት ፖለቲካውን ትቼያለሁ፡፡ ትዝ ይለኛል ‹‹ወደድክም፤ ጠላህም መኢሶን ያሸንፋል!…›› እንዲህ ያለ ነገር በወጣትነታችን ጠንከር ባለ መንገድ ተከራክረናል፡፡ በዚያ ውስጥ የተለወጠ ህይወት ነው፡፡ አክርረህ የፈለከውን ያህል ብታቀርብ ዝም ብሎ ውሃ ልኩን አያልፍም፡፡ ስለዚህ፤ የማክረር ፖለቲካውን የተውኩት በተወሰነ ደረጃ በዚያ ሰባት ዓመት እስራት ነው፡፡ በእርግጥ፤ ብዙ ጊዜ ሞት አጋጥሞኛል፡፡ ከአምቦም፤ ደርግ ጽ/ቤትም፣ ቢያንስ ሶስት፣ አራት ግዜ ከሞት በዕድል አምልጬያለሁ፡፡ … ስለዚህ፤ በተለይ ላለፉት 40 ዓመታት የከረረ ፖለቲካችን የትም አላደረሰንም፡፡ ያ ያለፍንበት ሁለመናዬን ለውጦታል … አንዳንድ ግዜ ማክረሩን እየተውክ ስትመጣ ወደ ተፈጥሮ ትሄዳለህ፡፡
መረራ ሁሌ የሚሉት በአገራችን ፖለቲካ የጠፋውን የመሃል መንገድ ያገኙት በእስር ቤት ነበር፡፡ አክርሮ ጫፍ ላይ መቆሙ ለማንም አይጠቅምም ባዩ መረራ ከደርግ እስር የዛሬውን መረራ አገኙ፡፡ ‹‹እስር ቤት ሰውና እንስሳ ተቀራራቢ መሆናቸውን የተረዳውበት ቦታ ነው›› ለሚሉት መረራ የእስር ቤት መንፈስ ሰባሪነት ቢታያቸውም፤ ነገር ግን ስለእስራቸው ሁኔታ እየተቆጩ ሲናገሩ ብዙም አይሰሙም፡፡
ከደርግ የሰባት ዓመታት እስር ከተፈቱ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ መረራ በድጋሚ ደርግን በተካው ኢሕአዴግ ታስረዋል፡፡ ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ቀን ከሌት የሰሩ-የተናገሩት መረራ ‹‹ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በመሞከር›› በሚል ክስ ቀርቦባቸው በድጋሚ ወደ እስር ተልከዋል፡፡ ‹‹ፅንፍ ይዘን እርስ በርሳችን መበላላቱ የትም አያደርሰንም››፤ ‹‹የእኔ ትውልድ የተሳሳተውን ስህተት መድገም የለብንም›› እያሉ ጠዋት ማታ የሚዘምሩት መረራ፤ ‹‹በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት ለመውደሙ ተጠያቂ ነህ›› ተብለው በእስር ይገኛሉ፡፡ ከትናንት እስከዛሬ በመብት ረገድ በአገሪቱ ውስጥ በመሰረታዊነት የተቀየረ ነገር ላለመኖሩ ከመረራ በላይ ማሳያ የለም፡፡
ከዶናልድ ሌቭን አምስት አስቆጭ የ50 ዓመታት እድሎች (five missed chances) ጋር በተመሳሳይ መረራ የአሁኗን ኢትዮጵያ ለመረዳት በተለያዩ ጽሁፎቻቸው መቶ ሃምሳ ዓመታትን ወደኋላ ተጎዘው ማየት ይመርጣሉ፡፡ መረራ ያለፉት መቶ ሃምሳ ዓመታት አገሪቱን ከማጠናከርና ሁሉም ዜጎች እኩል ዜግነት ተሰምቷቸው እንዳይኖሩ ያደረጉ አምስቱ ታላቅ ኪሳራዎች (the five grand failures) ነበሩ ይላሉ፡፡ ከቴዎድሮስ እስከ ምኒልክ፣ ከምኒልክ እስከ ጣሊያን የማይጨው ሽንፈት፣ ከጣልያን ወረራ ማግስት እስከ የዘውዳዊው አገዛዝ ማብቃት፣ የወታደራዊው መንግስት ዘመን እንዲሁም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ያሉትን አምስት የዘመናት ክፋዮች በተለያዩ የራሳቸው ምክንያቶች ለአገሪቱ መዳከም እና ለዜጎች ተስፋ ማጣት መሰረት ናቸው፤ ሁሉንም የአገሪቱን ልጆች ከማቀፍ (inclusiveness) ይልቅ፤ አንዱን አቅፎ ሌላውን የሚገፉ ሁነው አልፈዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል ባይ ናቸው፡፡ ስርዓቶችን ለመተቸት የማይቸኩሉት መረራ ከነዚህ አምስት ውድቀቶች በሦስቱ በግል ደረጃ ታስረው ተሰቃይተዋል፡፡ አሁንም በእስር ቤት ከሺዎች የአምስተኛው ውድቀት ሰለባዎች ጋር የጎልማሳ እድሜያቸውን እየገፉ ነው፡፡
ሦስቱ መረራዎች: ምሁር፣ ፖለቲከኛ፣ አራማጅ
የምሑራን ፖለቲከኛነት (Intellectual Politician) ብዙ አወዛግቧል፤ እያወዛገበም ነው፡፡ ‹‹ምሁራን የፖለቲካ ተሳታፊዎች መሆን የለባቸውም›› የሚለውን ሃሳብ በዋናነት የሚያራግቡት አካላት ከስኬታማነታቸው ጋር በተያያዘ ትችታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ምሁራን ሃሳባቸው ውስብስብ (complex) አድርገው ስለሚያቀርቡት ፖለቲካ ከሚፈልገው ከብዝሃው (irrational actors) ጋር በሚያግባባ ቋንቋ መነጋገር አይችሉም፤ መልዕክታቸውንም በሚገባ ማስተላለፍ አይችሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ ስኬታማ የፖለቲካ ሕይወት አይኖራቸውም የሚለው የመጀመሪያው ነው፡፡ ትችቱ ብዙ እውነታ ቢኖረውም እንደ መረራ ያሉት ላይ ሲደርስ ውሃ የማያነሳ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹አካዳሚውንም ፖለቲካውንም በሚዛናዊነት ለማስኬድ ሞክሬያለሁ›› የሚሉት መራራ በግብራቸው ሲመዘኑ ይህ አባባላቸው እጅግ እውነት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እርሳቸው ‹መለስተኛ ጦርነት› በሚሉት የኢሕአዴግ የምርጫ ወቅት እንደ ሰለጠነው የዴሞክራሲ አገራት ምርጫ የምርጫ ክልላቸውን በአራት አቅጣጫ እየዞሩ ሕዝብ የሚቀሰቅሱ ፖለቲከኛ፤ በምርጫ ክርክር ወቅት እንደ ምሁር እነሮበርት ዳሃልን እየጠቀሱ - እንደ ፖለቲከኛ ሰፊው መራጭ ሕዝብ በሚገባው ለዘኛ ቋንቋ (witty) እየተናገሩ መራጭ የሚጠሩ ምሁር-ፖለቲከኛ፤ አባላት ታሰሩ በተባሉ ቁጥር እንደ አራማጅ (activist) ሰልፍና ዘመቻ የሚመሩ ሰው ናቸው መረራ፡፡
‹‹በአጼው ጊዜ ድንጋይ ከሚወረውሩ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ›› የሚሉት መረራ አሁን ጎልማሳ ምሁር እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ መሬት ላይ ስራ ከመስራት ውጭ መናገሩ ብቻ ለውጥ የለውም በማለት እስከታች ወርደው መቀስቀስ ማደራጀትን በዋና ግብነት ይዘው የኖሩት:: አምስቱ የኢሕአዴግ መዋቅሮች (the five-tiers of government) ማለትም፡ ፌደራል መንግስት፣ የክልል መንግስታት፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና እንዲሁም ቀበሌዎችን በቻሉት መጠን እንዴት ሰብሮ መግባት እንደሚቻል እንደፖለቲከኛ ሲወጥኑ እንደ አራማጅ መሬት ወርደው ሲለፉ፣ እንዲሁም እንደ ምሁር ሲጽፉ ሲናገሩ ኑረዋል–መረራ።
ዶክተር መረራ ጉዲና (2005) |
ኢሕአዴግ የመረራን አንድም ሶስትምነትን አልወደደውም፡፡ ለዚህም ይመስላል መረራ አንድ ነገር በተናገሩ ቁጥር ትችትና ስላቅ የሚያዘወትረው መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለያየ ጊዜ ምሁርነታቸው ላይ ‹‹የሻዕቢያው ባለሟል ዶክተር››፤ ‹‹ዘርጣጩ ዶክተር››፤ ‹‹ጥገኛው ዶክተር››፤ ‹‹ፊደላዊ ምሁር›› እና የመሳሰሉትን ስድብና ስላቅ ሲያወርድባቸው የሚታየው፡፡ ሌላው ቀርቶ በልፋታቸው ያገኙትን የዶክተርነት ማዕረግ እንኳን በሹማምንቱ የሚፃፉት ጽሁፎች ‹ዶክተር› የሚለውን ማዕረጋቸውን በተጠራጣሪነት በትምዕርተ-ጥቅስ ውስጥ ነው የሚጠቀሙት፡፡ በሳል (seasoned) ፖለቲከኝነታቸውን በማጣጣል ‹‹ፖለቲከኛው ኮሜዲያን››፣ ‹‹የዶክተሩን ዘፈን አንድና አንድ ብቻ ነው — ሥልጣን›› የመሳሰሉትን በማለትም የመንግስት አካላት ይዘባበቱባቸዋል፡፡
ፕሌቶ ምሁርና ፈላስፋን በለየበት መልኩ መረራ ምሁር ነው:: ምሁር እውቀቱን ለጥቅም የሚገለገል ነው ነበር የፕሌቶ የምሁር ትርጉም ከፈላስፋ አንፃር ሲቀመጥ፡፡ በሌላ አነጋገር መረራ ከምቹ የምሁር ዳተኞች (Ivory-tower Intellectuals) በተለየ መልኩ የተማሩትን እንደ ምሁር የሚያስተምሩ፣ ያወቁትን ‹ይህች መከረኛ አገራችን› የሚሏትን አገር ለማሻሻል የሚጠቀሙ እንዲሁም እንደ አራማጅ እውቀታቸውን መሬት ወርደው ለመተገበር የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የመረራ የግማሽ ምዕተ ኣመታት ሁሉን አቀፍ ተሞክሮን አይተን ‹ዓላማቸው ስልጣን ብቻ ነው›፣ ‹ምሁርነታቸው ፊደላዊ ነው› … እያለ የሚተችን ስርዓት ከመታዘብ ባለፈ ምን ማለት እንደሚቻል ግራ አጋቢ ነው፡፡
ሦስቱ የመረራ ትዝብቶች: የፌደራል ሥርዓት፣ የብዝሃ-ፓርቲ ዴሞክራሲ፣ የነፃ ገበያ ሥርዓት
ከአርባ ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካን በንቃት እንደተከታተሉት መረራ የአሁኑን አሳሪያቸውን ኢሕአዴግን በሚገባ የሚያውቀው ሌላ ሰው የለም ማለት ግነት አይሆንም፡፡ መረራ ኢሕአዴግን እንዲሁ በጭፍን አልጠሉትም፡፡ ቀርበው አይተው ምን ይዞ-ምን ያስፈፅማል የሚለውን ገምግመው ነው የኢሕአዴግ ተቃውሞ-ትዝብታቸውን በተለያዩ መንገዶች የሚያቀርቡት፡፡
ኢሕአዴግን መቃወም እንዴት እንደጀመሩ ሲጠየቁ ሰከን ብለው ‹‹ጫካ እያሉ እደግፋቸው ነበር›› የሚሉት መረራ ሐሳባቸውን ሲያብራሩም ‹‹[ኢሕአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት የገባው] ቃል ኪዳን ጥሩ ነበር። የብሔረሰቦችን እኩልነት እናመጣለን። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናመጣለን። የእዝ ኢኮኖሚን አስወግደን በተሻለ መንገድ የገበያ ስርዓት እንድንመራ እናደርጋለን ያሏቸው ቃል ኪዳኖች [ሁሉ] በጣም ጥሩ ነበሩ›› በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ተስፋቸው ለመጨለም ብዙም ጊዜ አልፈጀትም፡፡ በኢሕአዴግ ተከፍተው ተቃውሟቸውን ስለጀመሩበት ሁኔታ ሲናገሩ ‹‹ከኢሕአዴግ ጋር የተለያየነው ‹ከጁላዩ ኮንፈረንስ› በዃላ ነው›› ምክንያቱም ‹‹የጁላዩ ኮንፈረንስ የሚባለውም የኢሕአዴግ ሰርግ ነበር›› ይላሉ፡፡፡፡ ‹የጁላዩ ቲያትር› እያሉ በተደጋጋሚ የሚጠሩት የሽግግር መንግስቱ ጉባኤ ኢሕአዴግ ካለፉት አስከፊ ስርዓቶች የማይሻል መሆኑን ያመላከታቸው እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህም ተነስተው ‹‹ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ የትም አይደርስም የሚል መደምደሚያ ላይ የደረስኩት ለዚህ ነው›› ይላሉ፡፡
ኢሕአዴግ የሚመራውን ስርዓት ለመታገል ወስነው ከጓዶቻቸው ጋር የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስን (ኦብኮ) ሲመሰርቱ ኢሕአዴግ የአምስት ዓመታት ዕድሜ አስቆጥሮ የነበረ ሲሆን የፌደራል ስርዓትና በይዘቱ ክፉ የማይባል ሕገ-መንግስት አፅድቆ ነበር፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሕዝብ ልብ ውስጥ ገብቶ ነበር ብለው ያምናሉ?›› ተብለው ሲጠየቁ መረራ ገላጭ በሆነ መልኩ ‹‹ተንደርድሮ ነበር ባይ ነኝ›› ይላሉ፡፡ ተንደርድሮ ሕዝብ ልብ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ግን በሒደት እንደታዘብነው የሕዝብ ልብን የሚወጋ ስርዓት መሆኑ ነው የመረራ ተስፋን ያጨለመው፡፡
ያወጣውን ሕግ የማይኖረው ኢህአዴግ ከሕዝብ ጋር ለመጣላት ረጅም ጊዜ እንዳልወሰደበት የሚያትቱት መረራ በተለይም ግን በሦስት ጉዳዮች ላይ ኢሕአዴግ የተነሳበትን ዓላማ ስቶ እንደወደቀ ይገልፃሉ፡ የፌደራል ስርዓት ፣ የብዝሃ-ፓርቲ ስርዓት፣ የነፃ ገበያ ስርዓት፡፡ ለመረራ ኢሕአዴግ የፌደራል ስርዓትን በሞግዚት አስተዳደር፤ የብዝሃ-ፓርቲ ዴሞክራሲን በይስሙላ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሁም የነፃ ገበያ ስርዓትን በመንግስታዊ ካፒታሊዝም ተክቶ ከሦሰት ያጣ የምርጫ አምባገነን (electoral authoritarianism) ሥርዓት ሁኗል፡፡ ለዛም ነው መረራ ከ20 ዓመታት በፊት የኢሕአዴግን በሕግና በመርህ አልገዛም ባይነት ተመልክተው ‹‹የኢሕአዴግን ልብ እግዚአብሔርም አላወቀውም ሳይንስም አልደረሰበትም›› በማለት የሥርዓቱን መርህ አልባ አይገመቴነት (unpredictability) የገለፁት፡፡
ኢሕአዴግ በየዘመናቱ ተለዋዋጭ፤ ስልጣኑን እስከ አስጠበቀለት ድረስ ምንም ከማድረግ የማይመለስ ሥርዓት ነው ባይ ናቸው መረራ፡፡ ኢሕአዴግን ሦስት አስርት ሊደፍን ጫፍ ላይ በደረሰው የሥልጣን ዘመኑ መመዘን የሚመርጡት መረራ ‹‹ኢሕአዴግ …›› ይላሉ ‹‹ኢሕአዴግ እስከ ምርጫ 97 ድረስ ‹‹ፈሪሃ እግዚአብሔር›› እንኳን ባይኖረው ‹‹ፈሪሃ ፈረንጅ›› ነበረው፣ ነውር የሚባልም ነገር ትንሽ ነበረው፡፡ ከ[97] በኋላ ግን ነውር ተወ›› ባይ ናቸው፡፡ አክለውም ከምርጫ 97 በኋላ ያለው ኢሕአዴግ የተነሳባቸውን ቀልብ የሚስቡ መርሆች ብቻ የተወ ሳይሆን በዓለም ላይ ብዙም ያልተለመዱ አዳዲስ የአፈናን ዘዴዎችን ይዞ የመጣ ሥርዓት ነው ባይ ናቸው፡፡ መረራ በፃፏቸው የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ላይ ‹‹የኢሕአዴግ ፈጠራ›› (the EPRDF novelty) በማለት የሚጠሯቸው ዓለም ላይ ብዙም ያልተለመዱ የአገዛዝ ዘዴዎችን ይተነትናሉ፡፡
ከዚህም በመነሳት ኢሕአዴግ የፌደራል ሥርዓቱን ወደ የሞግዚት አገዛዝነት የቀየረው ባልተለመደ ሁኔታ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎችን (በእንግሊዝኛው People’s Democratic Organizations (PDOs) ከማዕከል ሆኖ በመፍጠር ክልሎችን በቁጥጥር ስር አድርጎ የተዘረጋው የፌደራል ሥርዓት የሞግዚት አስተዳደር እንዲሆን በማድረግ ነው ባይ ናቸው፡፡ የብዝሃ-ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ደግሞ የምዕራቡን ዓለም ሊበራል ዴሞክራሲ መርሆዎች ወረቀት ላይ ተቀብያለሁ በማለት ከምስራቁ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲ እየማለ የትም አገር ባልተለመደ ሁኔታ እሳትና ውሃን አዳቅሎ ለመራመድ ሲሞክር የአገሪቱን ዴሞክራሲ የይስሙላ አድርጎታል ባይ ናቸው መረራ፡፡ መረራ ሦስተኛው የኢሕአዴግ ፈጠራ የሚሉት የነፃ ገበያ ሥርዓትን ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን እንደፈለጉ ለሚጋልቡ የፓርቲ ስሪት ነጋዴዎች አስረክቦ ካፒታሊዝምን የሚዘመር፤ ግን የእዝ ኢኮኖሚ የሚተገብር ቢሮክራሲ መፍጠሩን ነው፡፡ ኢሕአዴግ እነዚህን ድቅል ባህሪያቱን መተውን የሚጠራጠሩት መረራ፤ እነዚህን ባህሪዎች የያዘ ስርዓት ደግሞ አገሪቱንና ሕዝቧን ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ ያመጣላታል ብለው አያምኑም፡፡
ሁሌም ቢሆን ‹‹ኢሕአዴግ ዳኛም ተጫዋችም ነው›› የሚሉት መረራ፤ ሥርዓቱ በቃሉ የማይውል መሆኑን ሲገልፁ ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ ለሕዝቡ ‹‹ኢሕአዴግን እመን›› ብሎ ቢናገር እንኳ ሕዝቡ የሚያምን አይመስለኝም›› የሚል ብይን ይሰጣሉ፡፡ ከመታሰራቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹በውጭ አገር ያሉ ፖለቲከኞች ይሄን ይሄን ብለዋል›› ምን ይላሉ በሚል ለትንኮሳ በጠየቃቸው ወቅት የሚታገሉትን አካል በሚገባ የሚያውቁት መረራ «አንድ ሰው […] ኢትዮጵያ ትበታተናለች ስላለ ኢትዮጵያ አትበታተንም። ኢትዮጵያ ከተበተነች ኃላፊነቱ በዋናነት ደግሞ የኢሕአዴግ ነው» በማለት ለገዥው ሥርዓት ተጠያቂነትን አዙረው መስጠትን ያውቁበታል መረራ፡፡ ‹‹ለቲያትር የሚሰለጥኑ›› የሚሏቸውን የኢሕአዴግ ካድሬዎችም ሆነ ራሱ ኢሕአዴግን ሲተቹ ዘልቆ በሚያቃጥል ቋንቋ ነው፡፡ ፓርቲያቸው በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ያለውን አቋም አስመልክቶ ‹‹መሬት በሕዝቡና በመንግሥት ይተዳደር ማለታችሁ ከኢህአዴግ ጋር ያመሳስላችኋል ማለት ነው?›› ተብለው ሲጠየቁ እድል የማያባክኑት መረራ በፍጥነት ‹‹ይህ ቢሆንም ኢህአዴግ ግን መሬትን ለካድሬዎች ነው ያደረገው›› ብለው ነገሮችን ቶሎ ወደ ኢሕአዴግ ሥርዓት ይገፉታል፡፡ ይህን የመረራን አይበገሬ የረጅም ዘመን ተቃውሞ ለማጣጣል በሚመስል መልኩ የገዥው ስርዓት የተለያዩ ድምፆች ‹ምላሳቸው ወጌሻ ያስፈልገዋል›፣ ‹ያገኙትን ቃላት በመመለጠፍ የሚታወቁትና ያልተገራ ምላስ ባለቤት›፣ ‹ዘርጣጩ ዶክተር› እና የመሳሰሉትን ተራ ስድቦች በመንግስታዊ ሚዲያዎች ሲያዘንቡባቸው ይታያል፡፡
ኢሕአዴግ ደርግን ማስወገዱን በመልካም የሚወስዱት መረራ ‹‹ቢያንስ ቢያንስ ግን ደርግን ስንታገል ለነበርነው ኃይሎች ደርግን ማስወገዳቸው በየትኛውም ሚዛን ትልቅ ድል ነው›› ይላሉ፡፡ ‹‹[ነገር] ግን ደርግ የሰራውን ስህተት በቪዲዮ እያየ እሱኑ መድገሙ ትልቅ ወንጀል ነው። ይህን ስህተት ካላረመ [ኢሕአዴግ] ከደርግ የተሻለ የታሪክ ስፍራ ይኖረዋል የሚል ግምት ለመስጠት ያስቸግራል›› በማለት ኢሕአዴግን ይበይኑታል፡፡ የኢትዮጵያን ያለፉት አርባ ዓመታት የፖለቲካ ታሪክ ለሚከታተል ሰው ከዚህ የመረራ ፍርድ የተሻለ ፍትሃዊ ፍርድ ለመፍረድ ያስቸግራል፡፡
መራራ የሚማፀኗቸው ሦስት አይነት ልኂቃን
በአንድ አገር ውስጥ ለሚፈጠረው በጎም ሆነ መጥፎ ነገር እንደ አገሪቱ ልኂቃን (elites) ወሳኝ ሚና የሚጫወት የሕብረተሰብ ክፍል እንደሌለ መረራ አበክረው የሚናገሩ-የሚፅፉበት ርዕሰ-ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ገዥውን ስርዓት ከመንቀፍ-መውቀሳቸው ባለፈ በአገሪቱ እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ/እየተጫወቱ ነው ብለው የሚያምኗቸውን የሦሰት ዘውግ ልኂቃንን አገሪቱ ለገባችበት ማጥ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡
‹‹እውነት እንነጋገር ከተባለ›› በማለት የሚጀምሩት መረራ በመጀመሪያ ‹‹የትግራይ ልኂቃን … የሚባሉት፤ ሰማይ ምድር ገብተው [አሁን የያዙትን ስልጣን] ለመጠበቅ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር ይወቀው እንጂ ለዛሬው እሱ ነው ዋናው ስራቸው›› የሚሉት መረራ የትግራይ ልኂቃን አሁን ያላቸውን የበላይነት ላለማሰነጠቅ ግብግብ ውስጥ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ አስከትለውም ‹‹የኦሮሞ ልኂቃን የሚባሉት አሁንም ቢሆን ብዙ ቦታ ኢትዮጵያ የምትባለውን መስማት አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለውን በሀገር ደረጃ ለውጦ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ አይታዩም›› በማለት ‹‹የኦሮሞ ልኂቃን በአገሪቱ ሁኔታ ላይ አኩርፈው እሰከመቼ ይዘልቃሉ;›› በሚል ይጠይቃሉ፡፡ መረራ በልኂቃኑ ላይ ያላቸውን ትችስ ሲያሰልሱም ‹‹የአማራ ልኂቃን የሚባሉት ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያን የፈጠርኩ እኔ ነኝ›› በሚል አይነት፤ ከዚያም፤ ከላይም፤ ከታችም፤ ከዚህም፤ ከሁሉም ቦታ ‹‹እኛ የፈጠርናት ኢትዮጵያ ልትጠፋብን ነው›› ወደሚል፤ አንዳንድ ጊዜም ‹‹የኢትዮጵያዊነት ሠርተፍኬት ሰጪና ከልካይ እኔ ነኝ›› ብሎ፤ ራሱን ሰይሞ ማዶ ቆሟል›› በማለት ‹‹የአማራ ልኂቃን ‹አገሪቱ የእኛ ናት ብለው› እስከመቼ ነው የሚቀጥሉት?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡
የአገሪቱን ውጣ ውረድ የበዛበት ታሪክ ከሰፊው ሕዝብ አኗኗር ይልቅ በየዘመኑ የሕዝብ ወኪል ነን ብለው በወጡ ልኂቃን መነጽር ለሚመለከቱት መረራ የነዚህ ሦስት ልኂቃን እሰጥ አገባ የሁሌም ጭንቀታቸው ነው፡፡ ‹‹በግልፅ ቋንቋ …›› ይላሉ መረራ ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩ፤ ‹‹በግልፅ ቋንቋ የትግራይ ልኂቃን ስልጣኑን የሙጥኝ ካሉ፣ የአማራ ልሂቃን ‹ትናንትን እመልሳለሁ› የሚሉ ከሆነ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ልኂቃን ‹ከኢትዮጵያ እገነጠላለሁ› እያሉ የሚቀጥሉ ከሆነ ለልጆቻችን ስቃይን ነው የምናወርሳቸው›› በማለት መጭው ዘመን የነዚህ ሦስት ዘውግ ልኂቃን ግንኙነት ላይ የሚመሰረት እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡ የአገሪቱ የቅርብ ዓመታት የታሪክ ዕዳም የነዚህ ልኂቃን ቁርሾ እንደሆነ ይናገራሉ መረራ፡ ‹‹[በእኔ እምነት] ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ችግር ውስጥ የገባችው […] ከሁሉም በላይ በእነዚህ ሦስቱ የትግራይ፣ የአማራና የኦሮሞ ሊኂቃን በሚፈጥሩት ፍጭትና ግጭት ነው፡፡ አገሪቷን ወደሌላ አቅጣጫ እንጂ የጋራ አቅጣጫን ወደምንገፋበት አላመጣንም፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት በእሱ ላይ ነው የኖርነው […] [በዚህም ምክንያት] ስለወደፊቷም ኢትዮጵያ የጋራ አመለካከት ለመያዝና መፍትሔውም ላይ አንድ መሆን አልቻለንም፡፡››
መረራ ያላቸውን ተስፋ ከነዚህ ተፎካካሪ (competing) ልኂቃን ውጭ ይመስላል፡፡ ለዛም ነው ‹‹በእውነት ለመናገር የደቡብ ሊኂቃን ላይ ብዙ ችግር አላይባቸውም›› የሚሉት፡፡ የኢትዮጵያ ልኂቃን የፖለቲካ አሰላለፍ በትግራይ ልኂቃን የበላይ ነን (hegemonic) ባይነት፣ በአማራ ልኂቃና ትናንት ናፋቂነት (nostalgic) እንዲሁም በኦሮሞ ልኂቃን እገነጠላለሁ (secessionist) ባይነት ምክንያት መታለፍ ያለበትን ወንዝ መሻገር ባለመቻሉ ወንዙ ከጊዜ ወደጊዜ እየሞላ መሻገር የማይቻል እንዳይሆን የመረራ ስጋት ነው፡፡
መረራ መፍትሔ ነው ብለው ለረጅም ጊዜያት የያዙት ‹የመሀል መንገድ ፖለቲካም› የሚቀዳው ከዚህ ለረጅም ጊዜ አብሯቸው ካለ ፍራቻ እና ስጋት ይመስላል፡፡ ለዛም ነው ሁሉም ወደ መሀል መጥቶ ‹‹ … አንዱ ሌላውን ለመግዛት ያለውን ሕልም ካላቆመ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ለመገንባት የሚደረገው ትግል ከሕልምነት የሚያልፍ አይመስለኝም›› የሚሉት፡፡ የሦስቱ ዘውጎች ልኂቃን ወደመሃል መጥተው በሚያኗኑሯቸው ጉዳዮች ላይ ተስማምተው ካልቀጠሉ ያገሪቱ ሕልውና ያሳስባቸዋል፡፡ እርሳቸው በሚወክሉት የኦሮሞ ሕዝብ መሃል ባሉ ተፎካካሪ ኃይላት መካከል ሳይቀር የመሃል መንገድ ጠፍቷል በማለት ፓርቲያቸውን እንደመሰረቱት ነው የሚገልጹት፡፡
ይሄን የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን የመሃል መንገድነት ሲያስረዱም ‹‹የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥም ሁለት ጫፎች አሉ፡፡ እኛ እዚህ መሐል ነን፡፡ መሐሉን እንዲሰፋ ደግሞ እየገፋን ነን›› በማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት ‹‹በአንድ በኩል የመንግስት የገዥው ፓርቲ አሽከር ነው የምንለው ወይም የኦሮሞ ህዝብ አብዛኛው የሚለው ‹‹ኦህዴድ›› አለ፡፡ ጠዋትና ማታ የሚያስበው ኢህአዴግን ማገልገልና ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ እንዴት ይቆይ እንጂ የኦሮሞ ጥያቄ የሚባለውን፤ መጀመሪያውንም ያንን ይዞ መፈጠሩን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አሁንም ቢሆን ያንን እየገፋ አይደለም›› በማለት ገዥውን ኦሕዴድ አምርረው የሚተቹት መረራ፤ ‹‹በሌላ በኩል ደግሞ …›› ይላሉ፤ ‹‹በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ብሔርተኞች ኦነግን ጨምሮ ሌሎች አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የሚባለውን የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ መያዝ አቅቷቸዋል፡፡ ያንን የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ለኦሮሞውም፣ ለተቀረውም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሻል የጋራ አጀንዳ መግፋትም አልተሳካላቸውም›› ብለው ይተቻሉ፡፡ ሐሳባቸውን የሚያሳርጉት ‹‹እኛ (ፓርቲያቸውን ማለታቸው ነው) እዚህ መሐል ነው ያለነው›› በማለት ነው፡፡
መረራ ‹‹አመቻማች የመሃል መንገድ መርጣችሁ በሰላማዊ ትግል ስም ለገዥው ሥርዓት ቅቡልነት ከመፍጠር ያለፈ ምንም እየሰራችሁ አይደለም›› ሲባሉ፤ ‹‹በርግጥ አንዳንዶች ሠላማዊ ትግል እያላችሁ፤ ሠላማዊ እንቅልፍ ላይ ናችሁ›› ይሉናል በማለት በራሳቸው ላይ እየቀለዱ፤ ነገር ግን ‹‹የፅንፍ ፖለቲካ የአገሪቱ ያለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት እዳ ሁኖ ቆይቷል ከዛ መውጣት መጀመር አለብን›› እያሉ ከመናገር አይቦዝኑም፡፡ የሚማፀኗቸው የሦስት ዘውግ የፖለቲካ ልኂቃን ተስማምተው ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው፡፡ እውን መሆኑ ግን እራሳቸውን ጨምሮ ለብዙዎች አስጨናቂ ጉዳይ ነው፡፡
የመረራ ሦስት መፍትሔዎች: ዴሞክራሲ፣ ‹ሃቅ›፣ ትብብር
ይሔን ጽሑፍ ስጽፍ መረራ በሕይወት ዘመናቸው የፃፏቸውን ከአስር በላይ ‹አካዳሚያዊ› ፅሁፎች፤ አራቱን መጽሐፎቻቸውን እንዲሁም ባለፉት ሐያ ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ሁኔታዎች የሰጧቸውን ከሐያ በላይ ቃለ-ምልልሶች ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ መረራ የፃፏው አካዳሚያዊ ፅሁፎችም ሆኑ በተለያዩ መድረኮች ያቀረቧቸው ጽሑፎች ከሶስቱ ውጭ (ሁለት የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን የተመለከቱ እንዲሁም አንድ የጉራጌ ባሕላዊ ተቋማትን የተመለከተ) ሁሉም ጽሑፎቻቸው ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያተኩሩት በዴሞክራሲ፣ ምርጫ እና የሽግግር ጉዳዩች ላይ ነው፡፡ በጽሑፎቻቸው እና በቃለ-ምልልሶቻቸው አንድ መረዳት የሚቻለው ነገር የመረራን እውናዊነት (Realist) ነው፡፡ በጽሑፎቻቸው የሚያዘወትሯት ‘modus operandi’ የተባለች የላቲን ሐረግ የሰውየውን የትኩረት አቅጣጫ አመላካች ነች፡፡ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከመብሰልሰል ይልቅ ለተግባራዊ መፍትሔ የሚተጉ ናቸው፡፡ ምሁሩ መረራ ፖለቲከኛው መረራን ለተግባራዊነት የሚረዱ ናቸው፡፡
የአገሪቱን የፖለቲካ ሒደት ስለማስተካከል በማሰብ መረራ በሐሳብ ደረጃ በሥራዎቻቸው ሁሉ የሚያተኩሩባቸው ሦስት መሠረታዊ ነጥቦችን ነው፡፡ ዴሞክራሲ፣ ሃቅ፣ እና ትብብር፡፡ ይህን ሐሳባቸውን በአንድ አንቀጽ ሲጠቀልሉት ‹‹ፖለቲካ በአጠቃላይና የአገራችን ፖለቲካ በተለይ እስከገባኝ ድረስ፣ የአገራችን ፖለቲካ ከገባበት ቅርቃር ውስጥ የሚወጣው ወይ እኛ ኢሕአዴግን ከገባበት ቅርቃር ለማስወጣት የሚያስችል የተባበረ ትግል ውስጥ በቁርጠኝነትና በሐቅ መግባት አለብን፣ ወይ የኢሕአዴግ መሪዎች ከንጉሡም፣ ከደርግም ተምረው ከሌሎች ኃይሎች ጋር ብሔራዊ መግባባት ፈጥረው አገሪቷንና ሕዝቦቿን ለመታደግ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በማሳየት እውነተኛ ዴሞክራሲን ሲያሰፍኑ ነው›› በማለት ነው፡፡
መረራ ዴሞክራሲ ሲሉ በዋናነት ኢሕአዴግ በወረቀት ቃል ገብቶ በተግባር የወደቀበትን በአገሪቱ የዴሞክራሲ መሠረት መዘርጋትን ነው፡፡ የቱንም ያክል የኢሕአዴግ መሪዎችና ሰነዶች ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ቢሉም በተግባር ግን ፈላጭ ቆራጭ እስከሆኑ ድረስ የራሳቸውን ወንበር አስጠብቀው ለራሳቸው ልጆች የተዳከመችና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገር አስረክበው ነው የሚያልፉት ባይ ናቸው መረራ፡፡ ሌላው መረራ ዴሞክራሲን በመፍትሔነት የሚያቀርቡለት አካል የተቃውሞ ኃይሉን ነው፡፡ የተቃውሞ ኃይሉ ሊለወጡ ከማይችሉ/ከሚያስቸግሩ የልዩነት ወንዞች ተሻግሮ ዴሞክራሲን በሐሳብ ደረጃ እንደ ግብ ቢይዝ ልዩነቶችን ማጥበብና ገዥውን ሥርዓት መግፋት አይሳነውም ይላሉ፡፡
ሌላው የመረራ የመፍትሄ ሐሳብ ደግሞ ፖለቲካ ከሚተገበርበት አግባብ አኳያ የሚያቀርቡት ሐሳብ ነው፡፡ መረራ በተለያዩ ሥራዎቻችውና ቃለምልልሶቻቸው ‹ሃቅ› የምትል ቃል ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ሐቀኛ ዴሞክራሲ፣ ሐቀኛ ፌደራሊዝም፣ ሐቀኛ ምርጫ፣ ሐቀኛ ተቃዋሚ … የመሳሰሉት፡፡ አንድ ሐሳብ ምን መልካም መስሎ ቢታይ ስለእውነት በእውነት የማይተገበር ከሆነና ሕዝብን ለማታለያነት የሚውል ከሆነ በረጅም ጊዜ ሂደት እጅግ አደገኛ መዘዝ ይዞ ይመጣል ባይ ናቸው መረራ፡፡ አዘውትረው ‹‹ዩጎስላቪያ የተበተነቸው እኮ በውሸት ፌደራሊዝም እና በውሽት ዴሞክራሲ ጦስ ነው›› ለሚሉት መረራ ፖለቲካ ያለሐቅ በጣም አደገኛ እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበው አያውቁም፡፡
በሦስተኝነት መረራ እንደመፍትሔ በተደጋጋሚ ሲጠቅሱ የሚታዩት የመተባበርን ጠቀሜታ ነው፡፡ ‹‹ለእኔ ርዕዮተዓለም ያን ያህል አያስጨንቀኝም›› ለሚሉት መረራ በሚያግባቡ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከማንም ጋር አብረው የመስራት አስፈላጊነት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆን ዘንድ ከተመሰረተ አስር ዓመት ገደማ ያስቆጠረውን የእርሳቸው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት አባል የሆነበትን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሚክራሲያዊ አንድነት መድረክን (መድረክ) እንደምሳሌ ያነሳሉ፡፡ ‹‹መድረክ ውስጥ….›› ይላሉ መረራ መድረክ ውስጥ […] ‹ሶሻል ዴሞክራት ነን› የሚሉ አሉ፤ ‹ሊበራል ዴሞክራት ነን› የሚሉ አሉ፡፡ ‹ሁሉንም አንቀበልም› የምንለው[ም] አለን››፡፡ በመሆኑም ለመተባበር በሁሉም ጉዳዮች ላይ የግድ ተመሳሳይ አስተሳሰቦች እንዲኖሩ አይጠበቅም ባይ ናቸው፡፡
ይሄን ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም ‹‹የሁላችንም የፖለቲካ መንግሥተ ሰማያት ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለነገ የምንለው መሆን የለበትም። የጋራ የታሪክ ፈተናችን ለማለፍና የጋራ ሕልማችን ዕውን ለማድረግ የሰከነ፣ በአቅም ላይ የተመሠረተ፣ የተደራጀ እና የተባበረ ትግል ውስጥ በሐቅ፣ በፍጥነትና በቁርጠኝነት መግባት አለብን›› ይላሉ፡፡ እንዴትና የት የሚለው ጥያቄ አብሮ በመሥራት የሚመለሱ ጉዳዩች እንደሆኑ ያስራዳሉ መረራ፡፡
መራራ ጉዲና ከአርባ ዓመታት ለላቀ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው እንደ ምሁር፣ ፖለቲከኛ እና አራማጅ እርሳቸው እንደሚሉት ‹በገባቸው መጠን› መጭው ዘመን ጥሩ እንዲሆን ለፍተዋል፡፡ መረራ ስለመታሰር በተደጋጋሚ ሲጠየቁ ‹‹ኢሕአዴግ እኔን አስሮ ምን ይጠቀማል›› እያሉ በቀልድ፤ ‹‹እኔ ብታሰር የታገልኩለት ሕዝብ ትግሉን ያስቀጥለዋል›› በማለት በቁም ነገር ይመልሳሉ፡፡ አሁን በሠላማዊ ትግል የቆረቡት መረራ ከብር 1.4 ቢሊዮን በላይ ንብረት መውደምና የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ነውጥ አስነስተዋል ተብለው ታስረው ከባድ ፍርድ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡ በርግጥም እርሳቸው አርአያ ሆነዋቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሰለጠነ የፖለቲካ ሒደትን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለመምራት ለተቀላቀሉት እንደ አፍሪካ ከበደ ላሉ የነገ የአገሪቱ ተስፋዎች የመረራ እስር ልብ የሚሰብር ነው፡፡ መረራ በአንድ ወቅት ከፖለቲካውስ ራስዎን የሚያገሉት መቼ ነው? ተብለው ሲጠየቁም የሰጡት ምላሽ እንደ አፍሪካ አይነት ወጣቶችን ለማን ትቼ? በሚል መልኩ ‹‹አሁንም ቢሆንም ከፖለቲካው ጡረታ ብወጣ አልጠላም፡፡ ነገር ግን እኔን አምነው እዚህ ትግል ውስጥ የገቡ ሰዎች በተለይ ወጣቶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹም እስር ቤት ነው ያሉት፡፡ እኔ ኑሮ አልተመቸኝም ብዬ ጥያቸው አልሄድም›› ነበር ያሉት፡፡ አሁን መረራ ‹‹ኑሮ አልተመቸኝም ብዬ ጥያቸው አልሄድም›› በማለት ቃል የገቡላቸውን ወጣቶች በእስር ቤት ተቀላቅለዋል፡፡ ነገር ግን በአይበገሬነት ሰላምንና ለውጥን ለሚሰብኩትና ለሚኖሩት መረራ እስራቸው የአካል ነው፡፡ ሐሳባቸውማ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም አገሪቱን የሚያክማት መድሃኒት ነው፡፡
***
ለዚህ ጽሑፍ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተጠቀምኳቸው መጽኃፍት፣ አካዳሚያዊ ጽሑፎች፣ እንዲሁም ቃለ-መጠይቆች እንደ ጊዜ ቅደም ተከተላቸው የሚከተሉት ናቸው:
መጽኃፍት
1. Ethiopia Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy (2003)
2. Ethiopia: from Autocracy to Revolutionary Democracy, 1960s-2011, (2011)
3. የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች: ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢሕአዴግ (2005)
4. የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጬ ሕልሞች (2008)
‹አካዳሚያዊ› የምርምር ስራዎች
1. The Ethiopian Revolution 1974-1987: A Transformation from an Aristocratic to a Totalitarian Autocracy, Book Review (1994)
2. The Elite and the Quest for Peace, Democracy, and Development in Ethiopia: Lessons to be learnt (2001)
3. Ethiopia: a Transition without Democratization (2003)
4. The Problematic of Democratizing a Multi-cultural Society: The Ethiopian Experience (2007)
5. Ethnicity, Democratisation, and Decentralization in Ethiopia: The Case of Oromia (2007)
6. The Ethiopian State and the Future of the Oromos: ‘Self-Rule vs. Shared-Rule’ (2008)
7. Civil Society and Transition Politics in Ethiopia (2009)
8. Party Politics, Political Polarization and the Future of Ethiopian Democracy (2010)
9. Traditional Institutions of the Gurage people (2010)
10. Elections and democratization in Ethiopia, 1991–2010 (2011)
11. የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች፤ አልታረቅ ያሉ ሕልሞችና የኢሕአዴግ ቆርጦ-ቀጥል ፖለቲካ (2016)
ቃለ-መጠይቆች
1. ‹‹ቃለ - መጠይቅ ከአቶ መረራ ጉዲና ጋር›› - ጦቢያ ፤ መስከረም 1991
2. ‹‹ብሄራዊ እርቅን መሸሽ እንደ መንግስቱ ኃይለማርያም ለመጥፋት ካልሆነ በቀር ...›› - ኢትኦጵ፤ ጥር 1992
3. “Hiber Radio Exclusive Interview with Dr. Merera Gudina” - Hiber Radio, September 2013
4. ‹‹Dr. Merera Gudina talks about his new book "Ethiopia's chaotic political journey and my memoirs: from the Ethiopian students' movement up to EPRDF›› - SBS Amharic, November 2013
5. ‹‹ከፕ/ር መረራ ጉዲና ከኢትዮ-ቻናል ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ›› - ኢትዮ-ቻናል መጋቢት 2005
6. ‹‹ዜጐች የተሰደዱት መንግስት የሥራ ዕድል ባለመፍጠሩ ነው›› - አዲስ አድማስ፤ ሕዳር 2006
7. ‹‹ሥልጣን ወይም ሞት’ ተብሎ የሚገፋበት መንገድ ማንንም አልጠቀመም›› - ዕንቁ መፅሔት፤ ሕዳር 2006
8. ‹‹ግድቡ አይሳካም፣ ተቃዋሚዎች ከግብጽ ሊተባበሩ ይችላሉ›› - አዲስ ዘመን፤ ሐምሌ 2006
9. ‹‹ከመድረክ መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ›› - ቪኦኤ፤ ሐምሌ 2006
10. ‹‹ኢሳት ጠመንጃ የለውም፣ የትጥቅ ትግልም እያካሄደ አይደለም›› - አዲስ አድማስ፤ ሕዳር 2007
11. ‹‹ከኦሮሚያ አንፃር፤ ከኢሕዴአግ ደርግ ይሻላል›› - ሰንደቅ፤ ታሕሳስ 2007
12. ‹‹ለ6 ወር ያስተማርኩበት ደሞዝ አልተከፈለኝም›› - አዲስ አድማስ፤ ጥር 2007
13. ‹‹ወጣቱ ትውልድ ፖለቲካውን መነገጃ እንዳያደርገው ሥጋት አለኝ›› - ሪፖርተር፤ ሚያዚያ 2007
14. ‹‹እድገት እየተባለ የሚለፈለፈው ካድሬ በሚሠራው ቤትና በሚያስገነባው ሕንጻ ቁጥር ነው፤ ሕዝቡ አንድ ክረምትም ያለችግር ማለፍ አልቻለም›› - የቀለም ቀንድ፤ ጥቅምት 2008
15. ‹‹በበኩሌ ከዚህ በኋላ ለማየት የምጓጓው ኦሕዴድ የሚባለው ድርጅት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር እንዴት እንደሚኖር ነው›› - የቀለም ቀንድ፤ ታሕሳስ 2008
16. ‹‹ከሁሉ በፊት ይህን ሁሉ አገራዊ ምስቅልቅል የፈጠሩት አካላት ተጠያቂ መሆን አለባቸው›› - የቀለም ቀንድ፤ መጋቢት 2008
17. ‹‹ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ስለ አዲሱ መጽሐፋቸው “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች” ይናገራሉ›› - ኤስቢኤስ አምሃሪክ፤ ሚያዚያ 2008
18. ‹‹ኢሳት በዚህ ሳምንት፡ ዶር መረራ ጉዲና›› - ኢሳት፤ ሐምሌ 2008
19. “EthioTube አፈርሳታ - Oromo Federalist Congress Chairman Dr. Merera Gudina” - EthioTube, August 2008
20. «ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም ምክንያቱ የኢህአዴግ ስውር እጆች ናቸው» - አዲስ ዘመን፤ ሕዳር 2009
Great article, a masterpiece. Thank you very much.
ReplyDeleteWow Zola
ReplyDeleteI believe this article is well written. The arbitrary arrest and solitary confinement of Dr. Merera Gudina is just the tip of an enormous iceberg. Thousands are languishing in awful prison conditions, many have been assassinated in broad daylight and still more are declared “disappeared” since the EPRDF seized power. There is an urgent need for political and social Justice for Ethiopia.
ReplyDeleteEyerusalem K Feysa
ጽሑፉን አነበብና ብዙ መረጃ አግኝቻለሁ. ይህ ታላቅ ጽሁፍ, ምርጥ ይዘት. ደራሲውን አመሰግናለሁ thuê xe đi du lịch ninh bình
ReplyDeleteI am reading this wonderful article to improve my know-how.
ReplyDeleteRelevant!! Finally I’ve found something that helped emergency. Thanks a lot!
ReplyDeleteThanks for a marvelous posting!
ReplyDeleteI seriously enjoyed reading it, you might
ReplyDeletebe a great author.
ReplyDeleteThankyou for this wonderful article. I regularly read your article, all are very amazing
Woah! It’s simple article, yet effective. Thanks for this
ReplyDeleteEverything is very open with a really clear explanation of the challenges.
ReplyDeleteMany thanks for sharing!
ReplyDeleteThis is incredibly charming substance! I have taken a lot of joy.
ReplyDeleteMany thanks for the efforts you have put into writing this site.
ReplyDeleteAn interesting discussion is definitely worth comment. Write more, All the best!!
ReplyDeleteValuable info. Thanks I discovered this awesome website here.
ReplyDeleteLot of informative blog are provided here, Happy to read this good post. Thanks a lot
ReplyDeleteType of fantastic informative web site, Awesomeness! Thanks
ReplyDelete
ReplyDeleteNice to meet you! I happened to know your blog while looking for the materials I needed.
Thank you for the good post.
ReplyDelete