በማሕሌት
ፋንታሁን
ጥቂት
ስለ ቃሊቲ የሴቶች መቆያ እና ማረሚያ ቤት
የማይቻል ነገር እንደሌለ በተግባር ለማየት
ከሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዱ የእስር ቤት ሕይወት ነው። እስር ቤት እንገባለን የሚል እሳቤ በአይምሯችን ውስጥ ስለማይኖር በአብዛኛው
ከተለመደው የኑሮ ዑደት (መወለድ፣ ማደግ፣ መማር፣ መሥራት፣ ማግባት፣ መውለድ፣ ማደርጀት እና መሞት) እና ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተን
ነው የግል አቋማችንን የምንቀርፀው። "ከሰው ጋር መተኛት አልወድም/አልችልም፤ እንቅልፍ አይወስደኝም"፣
"ስፕሪስ ሳልጠጣ መዋል አልችልም"፣ "የቀዘቀዘ ምግብ አልወድም"፣ "ሲጃራ ሳላጨስ መኖር
አልችልም"፣ "በቀን ቢያንስ ሁለት ፊልሞችን ካላየሁ አልደሰትም"፣ "እከሊትን/እከሌን ሳላይ መዋል
አልችልም"፣ "ጨለምለም ካላለ ወደ ቤት መግባት አልወድም"፣ "መብራት ካልጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም"
እና የመሳሰሉ የማይለወጡ የሚመስሉን አቋሞቻችን ፈተና ውስጥ የሚወድቁት የእስር ሕይወትን ‹ሀ› ብለን ስንጀምር ነው። ብዙ አልችልም
ብዬ የማስባቸውን ነገሮችን ችዬ ስለወጣሁበት ስለ ቃሊቲ የሴት እስረኞች ግቢ ጥቂት ልበላችሁ።
በቃሊቲ እስር ቤት ግቢ ውስጥ ከሚገኙት
8 ዞኖች ሁለቱ የሴት እስረኞች የሚኖሩበት ነው። በአንደኛው ዞን በቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሴቶች በሌላኛው ደግሞ የተፈረደባቸው ሴቶች ይኖሩበታል። ልዩ ጥበቃ ወይም የቅጣት ቤት የሚባሉ ቤቶች አሉ። ወይም በተፈለገበት ሰዓት ይሠራሉ። ለምሳሌ
ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከማንም እስረኛ ጋር እንዳትገናኝ 5ት ሰው ብቻ የሚኖርበት የቅጣት ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው። ISISን
በመቃወም ከተጠራው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ሚያዚያ ወር 2007 የታሰሩ ሴቶች ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ ለብቻቸው በተሠራላቸው ቤት
ይኖሩ ነበር።
በቀጠሮ ዞን ደግሞ 5 ቤቶች ያሉ ሲሆን
በፍርደኛ ግቢ 6 ቤቶች አሉ።አንድ ቤት ውስጥ ከ 40 እስከ 120 እስረኞች ይኖራሉ። ቀጠሮ ግቢ ከአንዲት አነስተኛ ሱቅ በስተቀር
ሌላ ምንም ስለሌለ የተለያዩ ነገሮችን ለመገበያየት እና ፀጉር ቤት
ለመጠቀም ፍርደኛ ግቢ መሄድ ግድ ይላል። ቤተሰብ መጠየቂያ ቦታው
የፍርደኛ ግቢን አቋርጦ የሚገኝ ቦታ በመሆኑ፤ በቤተሰብ መጠየቂያ ሰዓቶች (ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2:30 እስከ 6:00 ከሰዓት
ከ7:30 እስከ 10:00 እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ከ2:30 እስከ 6:00)፤ ቀጠሮ ክልል የሚገኙ እስረኞች ከፍርደኛ ክልል
ማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ይችላሉ። በቀጠሮ እና ፍርደኛ
ክልል መሐል 200 ሜትር ገደማ ርቀት ያለው ሲሆን በየግቢዎቹ በር እና ማማዎች ላይ ጠባቂ ፓሊሶች አሉ። ዞኖቹ (ቤቶቹ) ከአስተዳደር ጀምሮ በእስረኞች በተመረጡ የእስረኛ ኮሚቴዎች ይመራል። በየቤቱ
ለሊት የሚደረግ ጥበቃ አለ። ሮንድ ይባላል። እያንዳንዷ እስረኛ ተራዋ በደረሰ ቀን ለሁለት ሰዓት ከሌላ አንድ እስረኛው ጋር ይጠብቃል።
ከለሊቱ 5:00 ሰዓት እስከ 7:00 እና ከ7:00 ሰዓት እስከ 9:00 ሮንድ ተረኞች የሚጠብቁበት ሰዓት ነው። የእስረኞች ቆጠራ በቀን ሁለቴ ይካሄዳል። የጠዋት ገቢ ፓሊሶች ከጠዋቱ
12:00 ላይ፤ 11:30 ላይ ደግሞ የማታ ገቢ ፓሊሶች ቆጥረው ይረከባሉ።
የስድስት
ሰዓት ተጠያቂዎች
ከላይ የጠቀስኳቸው የእስረኛ
"መብቶች" እኛ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ጋር ሲደርስ ቅንጦት ይሆናሉ። እንኳን በውናችን በሕልማችንም አናስበውም።
"ይቺም ቂጥ ሆና ለሁለት ተከፈለች" ዓይነት ነገር ነው። ያም መብት ተብሎ ተሸራርፎ ሲሰጠን
እና ስንከለከል "All animals are equal but some are more equal" የሚለው አባባል ትዝ
ይለኛል። የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ማለት በሽብር ወይም በአመፅ ማነሳሳት የሚል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በቀጠሮ ክልል ሆነው
የሚከታተሉ ወይም ተፈርዶባቸው ፍርደኛ ክልል ያሉ ሴቶች ማለት ናቸው። ስያሜው የመጣው ከቤተሰብ ጋር ከምንገናኝበት ሰዓት የተወሰደ
ነው። የምንጠየቀው 6 ሰዓት ላይ ብቻ ሲሆን እኔ በቆየሁባቸው ጊዜያት ከ10 ደቂቃ እስከ 30 ደቂቃ ለሚሆን ቅፅበት ነበር። የመጀመሪያዎቹ
የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ለ5 ደቂቃ ብቻ ይገናኙ እነደነበር ሰምቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪም የምንጠየቀው በቅርብ ቤተሰቦች ብቻ ነው። ያለንበት ዞንም ሆነ ቤት በኮሚቴነት መመረጥም
መምረጥም አንችልም። ሮንድ ጥበቃ እኛን አያካትትም። ፍርደኛ ግቢ ሄዶ መገበያየት ይናፍቀናል። ቢበዛ የ6 ሰዓት ተጠያቂ ያልሆነ
(ኖርማል) እስረኛ እንድንልክ ቢፈቀድልን ነው። ሆኖም ግን አስጠጪ እስረኞች ሰበብ ፈልገው የሚላኩትን ኖርማል እስረኞች ለአሸባሪ
ይላላካሉ የሚል ክስ ስለሚያቀርቡባቸው፤ የሚላክልን ማግኘት እስቸጋሪ ነው።
ክሊኒክ እና ፀጉር ቤት ለመሄድ ስንፈልግ
ለብቻችን አጃቢ ተመድቦልን ነው። የምትመደብልን አጃቢ ፀጉር ቤት ውስጥ ገብታ ተሰርተን እስክንጨርስ ጠብቃ ይዛን ትመለሳለች። ይሄ
ሲገርመን የሆነ ጊዜ ላይ ፓሊሶች የሚሰሩበት ፀጉር ቤት እንድንጠቀም መመሪያ ተላለፈ። ይህ መመሪያ ከተላለፈ በኋላ የሆነ ቀን ጋዜጠኛ
ርእዮት አለሙ ፀጉር ቤት ለመሄድ ጠይቃ፤ አጃቢዋ እየወሰደቻት የተላለፈውን መመሪያ ስትነግራት "እኔ እስረኛ ነኝ። ለምንድነው የፓሊስ ፀጉር ቤት የምሰራው? ይቀራል
እንጂ!" ብላ ፀጉሯን መሠራቱን ትታ ተመለሰች። እስክትወጣ ድረስም በአቋሟ እንደፀናች ነበር። ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬም የሚደርስብንን
መገለል በመቃወም ፀጉሯን በመላጨት መልዕክት አስተላልፋአለች።


