Thursday, October 18, 2012

መፅሃፍ፤ ከወዴት አለህ?


ባለፈው ሳምንት ፅሁፋችን አንባቢ ኢትዮጵያዊን ፍለጋ በሚል ርዕስ፤ ያለውን የንብብ ባህል ከመጽሃፍ ገበያው ጋር እንዲሁም ለምን ይህ ሆነ ብለን ጠይቀናል፡፡ በዛሬው ፅሁፋችን ደግሞ ምን ይፃፋል? እንዴትስ ይፃፋል? ለማን ይፃፋል? ብለን እንጠይቃለን፡፡
አንድ ፀሃፊ መፅሃፍ ሲፅፍ ብዙ አይነት አላማዎችን ይዞ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሀሳብን ከማስተላለፍ እራስን እስከማሻሻል ድረስ፡፡ ከዓማ ሁሉ ገዝፎ የሚታየውና የመፅሃፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ደግሞ መፅሃፉ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሳደረው ተፅዕኖ እና የሃሳብ አመንጭነቱ ነው፡፡ አንባቢውም መፅሃፉን ገዝቶ ሲያነብ አንድ ነገር መጠበቁ አይቀርም፡፡  እናም የደራሲው ዋና ሚና የሚጠበቀውን ተፅእኖ በተደራጀ እና በሚዋጥ መልኩ ለሚጠብቀው አንባቢ ማድረስ ነው፡፡

በሀገራችን አሁኑ ወቅት በተለይም በአማርኛ ቋንቋ ለአንባቢው እየቀረቡ ያሉ ፅሁፎች ከዚህ አንፃር እንዴት ይገመገማሉ ነው የፅሁፋችን ዋነኛ አላማ፡፡ ምንስ ችግሮች አሉም እንላለን፡፡ በዚህ ፅሁፍ ለማየት የሞከርኩት ሁሉም አይነት መፅሃፍት ውስጥ ለኔ ገዝፈው የታዩኝን ጉዳዮች ነው፡፡

The Zeitgeist is ‘Self-help’

በሀገራችን ዋና ዋና ከተሞች እግረኛ መንገድ እንዲሁም ብርቅ የሆኑትን የመፅሃፍት መደብሮች ተዘዋውሮ የተመለከተ ሰው፤ በአንድ ነገር ቀልቡ መሳቡ አያጠራጥርም፤ ‘የራስ አገዝ’ (Self-help) ወይም በተለምዶ ‘የስነ ልቦና’ መፅሃፍት የሚባሉት መፅሃፍት በገበያው ውስጥ ባላቸው ድርሻ፡፡ አዎ ገበያው ‘ምክር፣ ምክር’ ይሸታል፡፡ 

'ሀብታም የመሆኛ ሚስጥሮችን' ከSecrets Stock Market እስከ Save, Run & Invest ፣ 'ስኬታማነትን በአጭር ጊዜ ለመቀዳጀት' ይረዱ ዘንድ ከleadership እስከ Entrepreneurship፣ 'የወሲብ የፀደይ ወራትን' ይኖሩበት ዘንድ ከHow to Kiss a Breast እስከ Kamasutra ወ.ዘ.ተ በምክር መልኩ ተዘጋጅተው የመፅሃፉን ዓለም በአምባገነንነት ይዘውታል፡፡ ጥያቄው ግን እነዚህ አብዛኞቹ የትርጉም ስራዎች የሆኑ ራስ አገዝ መፅሃፍት አንደሚታሰበው የዜጎችን ንቃተ ህሊና ከፍ በማድረግ የግራ መጋባቱ መፍትሄ ይሆናሉ? እነዚህ ሲያሻቸው ከምዕራብ አለያም ከምስራቅ ፍልስፍና በትንሹ እየጨለፉ ስለማንኖርበት ህይወት የሚያስጎበኙን መፅሃፍት እውነተኛ ዋጋቸው ስንት ነው?

ይህ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እያደገ የመጣው የራስ አገዝ መፅሃፍት የገበያ አምባገነንነት ጫፍ (Apex) ላይ ደርሷል ማለት የሚያስችለን አሁን ያለንበት ወቅት ነው፡፡ ‘የራስ አገዝ’ መፅሃፍትን በሽሚያ ተሸጠው ማለቅ ስንመለከት፣ ጊዜው የነሱ ነው እንድንል ያደርገናል እናም የአምባገነንነታቸው መጨረሻ በቅርብ አልመስለን ይላል፡፡

የነጭ ሳሩ አንበሳ መሃል ፒያሳ ኬክ ቤት ውስጥ ምን ያደርጋል?

ደራሲ እና ሀያሲ መስፍን ኃ/ማርያም የአንዳንድ ድርሰቶች አኳኋን አላምር ሲለው ‹‹አንዳንዱ ደራሲ በጣም ያሰገርማል፤ ድርሰቱን አስከተወሰነ ቦታ ይወስደው እና መቋጫ ታሪክ ሲጠፋበት ዋናው ገፀ ባህሪ ’መሃል ፒያሳ ኬክ እየበላ እያለ፤ ከነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ አምልጦ የመጣ አንበሳ ገደለው’ በማለት ታሪኩን ይቋጨዋል፡፡›› ይለናል፡፡ እንግዲህ የስነፅሁፋችን ሌላው አዝማሚ አይረቤ ታሪክን በደረቀ ቋንቋ አጅሎ ‹‹ይህ እንደ ልቤ የማየውና ለ12 ዓመታት አምጨ የወለድኩት የበኩር ልጄ ነው፡፡ እነሆ ተቋደሱልኝ›› መባላችን ነው፡፡ 

በሀገራችን የተደራጀ የስነፅሁፍ ገምጋሚ አካል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ‘የደራሲያን’ መበራከት ለግልብ መፅሃፍት መንስኤ ተደርጎ መወሰድ ይችላል፡፡ 

ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‘ድርሰት’ የሚለውን ሀሳብ፡ ሐዲስ ጥበብን ፍልስፍናን […] በጽሕፈት መግለጥ በማለት ድርሰት የጥበብ ሽግግር እንደሆነ ይገልፃል፡፡ አያይዞም  ‘ደራሲ’ የሚባለው ማነው; ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ደራሲ ማለት፡ ጥበብን፣ ትምህርትን[ና] የዕውቀት መጻሕፍትን የሚደርስ ነው ይለናል። እንግዲህ አሁን ገበያውን ‘ከራስ አገዝ’ መፅሃፍት ጎን ለጎን እየገነኑበት ያሉት ‘ድርሰቶችስ’ የዕውቀት ሽግግር ላይ እንዴት ናቸው? ቋንቋን ለማሳደግስ ምን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው? ተነበው በልብ ይቀራሉ ወይስ ያቅራሉ? የነዚህ መፅሃፍት ‘ደራሲዎችስ’ እንደ ማእረግ ስያሜያቸው ጥበብን ያውጃሉ? ትምህርት እና ዕውቀትንስ ይሰብካሉን? አንባቢያቸውን ያዝናናሉ ወይስ ያሳዝናሉ? የዚህን ሁሉ ጥያቄ መልስ የአብዛኛውን መፅሃፍት ግማሽ ገፅ እንኳን ሳናገባድድ የምናገኝው ነው፡፡ ታዲያ ዘመኑን ማን እየደረሰው ነው? ብለን ስንጠይቅ ግን ድንጋጤ ሽው ይልብናል፡፡ ታዲያ ይሄን ሁሉ ዘመን ሸዋን የማያውቅ አንበሳ በጠራራ ፀሃይ ማሃል ፒያሳ ሲንጎማለል ላንደነግጥ ኑሯል?

Blurb እንደ ውዳሴ ከንቱ

መፅሃፍት ወደ ገበያው ከመውጣታቸው በፊት ለቅድሚያ ግምገማ ለአንዳንድ ሰዎች ሰጥቶ እርማት ማግኝት ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ ነገር ግን የግምገማው አላማ ገበያ ተኮር ሲሆን ነገሩ ወደሌላ አቅጣጫ ይመራናል፡፡ ይህ እንግዲህ በብዙ መፅሃፍት ላይ የሚታይ ‘አዲስ’ ሂደት ነው፡፡ ለብ ለብ የሆነች፣ መናኛ የግጥም መድብል ያሳተመ አንድ ጎረምሳ ከመፅሃፉ ጀርባ አንድ ታዋቂ ‘የስነ ፅሁፍ’ ሰው ‹‹ካይን ያውጣህ አንተ ልጅ፡፡ የቃላት አመራረጥህ የFrost ተፅእኖ እንዳለብህ ያሳያል፣ ከፑሽኪንም ጋር መንትያነትክን መመስከር ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ምን አለፋችሁ አሁን የማስተዋውቃችሁ የሸክስፒርን አኩያ ነው፡፡›› ብለው አስተያየት ሰጥተው አንባቢው ተሸምቶ ይገዛና፤ እንዴት ነው ነገሩ? ብሎ ይጠይቃል፡፡

ስለቁንጅና ውድድር ማሰልጠኛ ይሆን ዘንድ አንዲት 30 ገፅ የማትሞላ ፅሁፍ ከጀርባዋ ‹‹እንደ ሀሳቡ ጥልቅ ቋንቋ፣ እንደ ውበት ሰባኪነቷ ባህልን አክባሪነቷ ያሰደምማል፡፡ በሌላ ዳጎስ ያለ ስራሽ ለማየት ቸኩያለሁ›› የሚል የአንድ ጉምቱ ‘ምሁር’ አስተያየት አይታችሁ መፅሃፉን ስታዩት በሆሊውድ ተዋንያን ምስል የተሞላ አልበም ሲሆንባችሁ፤ ምንድነው ከማለት ሌላ ምን ትላላችሁ?
እናም እጠይቃለሁ በመፅሃፍ ላይ የሚሰጥ አስተያየት (Blurb) ለማን ነው? ምንድን ነው? ውዳሴ ከንቱውስ የት ያደርሰን ይሆን?

‹‹ዘመን አይሽሬ (Classic) መፅሃፍ ቁጠር ብለው፣ ዴርቶጋዳ አንድ አለ››

በሃገራችን የስነፅሁፍ ታሪክ አጭር ነው ማለት ሁላችንም የሚያሰማማ ሀሳብ ነው፡፡ ስነ ፅሁፉ አድጓል ወይስ አላደገም የሚለው ጥያቄ ግን እንደ ቀዳሚው ቀላል ካለመሆኑም በተጨማሪ አከራካሪም ነው፡፡ ከ1950ዋቹ መገባደጃ እስከ 1970ዎቹ መጀመሪያ ያሉትን 15 ዓመታት የኢትዮጵያ የአማርኛ ስነ ፅሁፍ የፍካት ጊዜ ነበር የሚለው  በብዙሃኑ ተሰሚነት አለው፡፡ በዚህ ወቅት ነበር እነፍቅር እስከ መቃብር፣ ሌቱም አይነጋልኝ፣ አደፍርስ፣ ከአድማስ ባሻገር፣ አልወለድም የመሳሰሉት ብሉይ (Classic) የአማርኛ ድርሰቶች  የታተሙት፡፡ እስከ አሁንም የአማርኛ ድርሰት መለኪያ ሆነው ይቀርባሉ፡፡

እንግዲህ ከዚህ የፍካት ዘመን ወደፊት 40 ዓመታትን ስንቆጥር አሁን ያለንበት ወቅት ላይ እንደርሳለን፡፡ እናም ዛሬስ ምን ይፃፋል? ብለን ለመተየቅ እንወዳለን? አዎ ‘ዴርቶጋዳ’ ተፅፏል፡፡ ግን ግን ልካችን ዴርቶጋዳ ነውን? ዴርቶጋዳን ለማጠልሸት ሳይሆን፤ በእውነት ስነፅሁፋችን ለመታዘብ ያክል ነው ይሄን ያልኩት፡፡ ዴርቶጋዳ የዘመኑ ብሉይ (Classic ) ስራ ነው ካልን የነ ‘አደፍርስ’ ምትኮች ከወዴት አሉ?  ስለ ምንኖረው ህይወት የሚፅፍልን ደራሲስ ከወዴት ነው?


No comments:

Post a Comment