ዓለምን እንዲሁ ልናውቃት አንችልም፡፡ ዓለሚቱን ለመገንዘብ ብዙ ግብዓቶች ያስፈልጉናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ዓለምን ሙሉ ለመሉ አናውቃትም፡፡ ስለ ዓለም ጥሩ የሆነ ግንዛቤ
ያለው ሰው፤ ስለምድሪቱ ከሌሎች የተሻለ መረጃ አለው ማለት ነው፡፡ መረጃን ማግኛ መንገዶች ደግሞ ከሰው ሰው፣ ከቦታ ቦታ፣ ከጊዜ
ገዜ ይለያያሉ፡፡ ፅሁፍ ከሰው ልጅ ቀደምት የመረጃ ማግኛ ዘዴዎች
አንዱና ዋነኛው ነበር/ነው፡፡ ፅሁፍ በአንድ ላይ ተጠርዞ ለአንባቢው ሲቀርብ ደግሞ መፅኃፍ የሚል ስያሜን ያገኛል፡፡
እንግሊዛዊው ባለቅኔ ጆን ሚልተን (1608 - 1674) እንዲህ ይላል ‹‹Who kills a man kills a reasonable
creature, God's image; but he who destroys a […] book, kills reason itself,
kills the image of God, as it were in the eye.›› መፅኃፍ ማለት ምክንያት ማለት ነው እንደ ማለት፡፡
ያለምክንያት ህይወት እንዴት ይሆናል?
መፅኃፍ መረጃን መስጠት አንዱ አላማው
ቢሆንም ከዚህ ጋር ተያይዞ ማዝናናት እና ማበልፀግን እንደ ግብ አድርጎ መመልከትም ይቻላል፡፡
አለማቀፉ የመፅኃፍት እና የአንባቢ
ግንኙነት
አል አረቢያ ቴሌቪዥን ባለፈው ሃምሌ
ወር ሮይተርስን በመጥቀስ ያዎጣው ዜና የአረቡ አለም በንባብ ባህል በኩል በጣም
ደካማ እንደሆነና ከምዕራብ ሀገሮች ጋርም ሲነፃፀር በጣም ያነሰ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ ይሄም በአረቡ አለም ዘንድ አስገራሚ ተብሎ
ነበር፡፡ በተጠቀሰው የምርምር ስራ መሰረት አንድ አረብ በዓመት ስድስት ገፅ ብቻ የሚያነብ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ አንድ አሜሪካዊ
በዓመት አስራ አንድ መፅኃፍት እንዲሁም አንድ እንግሊዛዊ በዓመት ሰባት መፅሃፍት ያነባል በማለት ፡፡ ‹‹እኛ የአረቡ አለም ነዋሪዎች
ልጆቻችን በዓመት ስድስት ደቂቃ ብቻ ለልጆቻችን የንባብ ጊዜ ስናበረክት፤ በአንፃሩ ምዕራባዊያን ቤተሰቦች ደግሞ በዓመት አስራ ሁለት
ሽህ ደቂቃዎችን ለልጆቻቸው የንባብ ጊዜነት ያውሉታል›› ይላል፡፡
ይህ የሚያሳየው የንባብ ባህል መኖር
በእድገት እና በብልፅግና ላይ የሚያደርሱት ተፅእኖ ትልቅ መሆኑን ነው፡፡ አዎ Readers are Leaders.
ኢትዮጵያዊው መፅሃፍ
ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ፤
ያለውን የንባብ ባህል በምርምር ስራ አስደግፎ ያቀረበ ምርምር ስራ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ ሊያገኝ አልቻለም ወይም ያሉትም የአንድ በጣም
የተወሰነ ሁኔታን ብቻ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ነገር ግን ተያያዥ ሁኔታዎችን አብረን በማየት ያለውን የንባብ ባህል እና የመፅኃፍ ስርጭት
የሚያመለክት ስዕል ማስቀመጥ እንችላለን፡፡
ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ስልጣን
በያዘ ማግስት አላማው ማርክሲስት-ሌኒኒስት ሕብረተሰብን ለመገንባት በማሰብ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ካወጀ በኋላ፤ ማሀይምነትን
ለማጥፋት በሚል ግብ በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የሚገኙ መሀይማንን ቁጥር ወደ ሀያ አራት በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ ለዚህም ስኬት በመላ
ሀገሪቱ ከሰባት ሽህ በላይ ቤተ መፅኃፍት ተገንብተው እንደነበር በጊዜው የወጡ ሪፖርቶች ይገልፃሉ፡፡ ይሄም የማንበብ ባህልን ከማሳደግ
አኳያ ታላቅ እምርታ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
ነገር ግን በወታደራዊ ዘመን የመፅኃፍት
ሳንሱር በእጅጉ የበረታ ከመሆኑ የተነሳ መንግስታዊ ርዕዮተ ዓለም ከሆነው ማርክሲዝም- ሌኒኒዝም ውጭ ሌሎች ሀሳቦችን የሚያንፀባርቁ መፅሃፍት ‘የአድሃሪያን’ ናቸው፣ ‘የኢምፔሪያለዝም
ጭምቅ መርዞች’፣ ‘የአቢዮት ቀልባሾች ማንፌስቶ ናቸው’ ወ.ዘ.ተ በሚሉ አልባሌ ምክንያቶች የሚታተሙት መፅኃፍት በእጅጉ በተወሰኑ
ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ ነበሩ፤ ይሄም የንባብ ባህሉን እና የሀሳብ እንሽርሽሪቱን (Discourse) እድገት አንቆ
ይዞት ነበር፡፡
ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ የኢትዮጵያ
ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተርን አፀደቀ፡፡ ቻርተሩ ከያዛቸው ዋነኛ ነጥቦች መካከል
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ያፀደቀውን እና ኢትዮጵያም ፈራሚ የነበረችበትን ‹‹አለማቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ(UDHR) ሙሉ ለሙሉ ተቀብላለች›› የሚለው ሃሳብ ይገኝበታል፡፡ ከነዚህ መብቶች አንዱ ሀሳብን በፈለጉት መንገድ የመግለፅ ነፃነት ነው፡፡ ይሄም
በንባብ ባህሉ ላይ በአጠቃላይ፣ በመፅኃፍ ገበያውን ላይ ደግሞ በተለይ በአዎንታዊ መልኩ ተፅዕኖ እንደሚሳርፍበት በወቅቱ ተገጿል፡፡ ለዛም ይመስላል በኢህአዴግ
መጀመሪያ የስልጣን አመታት በደርግ ጊዜ ታፍነው የነበሩ ድምፆች መተንፈስ የጀመሩት፡፡ ነገር ግን ከመፅኃፍት ገበያው ጎን ለጎን
የግል ጋዜጦች ወደ ገበያው መግባታቸው አንባቢዎችን ከጠጣር (Hard) ወደ ስስ እና ለብ ለብ (Soft) የንባብ ባህል እንዲነዱ
ተፅእኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይሄም መፅኃፍ ከጋዜጣ የደረሰበት የመጀመሪያው ጠንካራ ቡጢ ነበር፡፡
እንደዛም ሆኖ በነዚህ ዓመታት የመፅኃፍት
ገበያው መልካም በሚባል ሁኔታ ላይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሂደት ግን የመፅኃፍት ገበያው እየተቀዛቀዘ መጣ፡፡ በ2001 ዓ.ም
አካባቢ በሚዩዚክ ሜይ ዴይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ውስጥ የመማሪያ መፅኃፍትን ጨምሮ በቀን በአማካኝ አምስት
መፅኃፍት ለህትመት ይበቃሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው በዓመት በመላ ሀገሪቱ በሁሉም ቋንቋዎች፤ በሁሉም ርእሰ ጉዳዮች ላይ የትርጉም
ስራዎችን ጨምሮ ወደ 1800 አካባቢ መፅኃፍት ይታተማሉ ማለት ነው፡፡ ይሄን ቁጥር ለምሳሌ በአሜሪካ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010
ዓ.ም በአሜሪካ ከታተሙት ሶስት መቶ ሃያ ስምንት ሽህ ሁለት መቶ
ሀምሳ ዘጠኝ (328,259) መፅኃፍት ጋር ስናነፃፅረው በሀገራችን
የሚታተሙትን መፅሃፍት ቁጥር አናሳነት እንረዳለን፡፡
እንግዲህ ከ80 ሚሊዮን በላ ህዝብ
ለሚኖርባት ሀገር ይህ ቁጥር እጅግ ትንሽ ቁጥር ከመሆኑም በላይ፡፡ የአንባቢውን ውስንነት እና የንባብ ባህሉን ውድቀት ያሳያል፡፡
ለመሆኑ መፅኃፍ ለምን ተዘነጋ?
መሀይምነት
ከ84 በመቶ በላይ ህዝብ በገጠር
በሚኖርባት ኢትዮጵያ የመሃይሙ መጠንም በዚያው ልክ ብዙ እነደሚሆን መገም አያዳግትም፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2005 ዓ.ም፤
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) በወጣው ሪፖርት መሰረት 45 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ብቻ የተማሩ (Literate) እንደሆኑ
ሲገልጽ፤ ቀሪዎቹ 55 በመቶዎቹ ደግሞ ያልተማሩ (Illiterate) ናቸው ይላል፡፡ ይሄም የሚያሳየው ከግምሽ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን
አያነቡም አይፅፉምም ማለት ነው፡፡ በጣም የሚያስገርመው በመሰረተ ትምህርት ዘመቻ አመካኝነት ማንበብ እና መፃፍ ይችሉ የነበሩ አንዳንድ
ሰዎች ዝንጋኤ ውስጥ (Memory loss) ሆነው የተማሩትን መዘንጋታቸው ነው፡፡ እናም የመሃይሙን ቁጥር ከፍ አድርጎታል፡፡
እንግዲህ በሀገሪቱ የመሃይማኑ ቁጥር
ከተማረው ይልቅ ማየሉ በንባብ ባህሉ እና በመፅኃፍ ገበያው ላይ የሚያስከትለው ተፅእኖ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሄን ስንል
ግን ተምረው - ያልተማሩትን (Functionally Illiterate) ማለትም ፊደል የቆጠሩ ነገር ግን ስለመፅኃፍ ምንም ሀሳብ
የሌላቸውን ዜጎች ሳንጨምር ነው፡፡
ዕውቀት ተኮር ህብረተሰብ ወዴት ነው?
የመሃይማኑ ቁጥር ከላይ እንደተቀስነው ከተማረው ዜጋ ቁጥር በላይ ቢሆንም፤ በተማረው ህብረተሰብ
ዘንድ ያለው የመፅኃፍ ግንዛቤም ሌላው ከንባብ ባህሉ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የንባብ ምሽቶች፣ የማንበቢያ ቦታዎች (Reading Buzz) መኖር፣ ህፃናት ለማንበብ ያላቸው
ተነሳሽነት እንዲጨምር እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ወ.ዘ.ተ ስንመለከት የችግሩ ስር ወዴት ሊሄድ እንደሚችል መገመት ያስችለናል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ
ባህሉ እድገት የሰጡት ትኩረት ምን ያህል ነው? በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉት ንባብ ተኮር ዝግጅቶች ምን ያክል ናቸው? ተማሪዎች
‘የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን’ እንዲመለከቱ ትኩረት ተሰጥቶ በሚሰራበት መጠን፤ ለመፅኃፍ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግስ ይደረጋል ሆይ?
እያልን ስንጠይቅ፤ መልሱን ለጥያቄዎቹ ከምንሰጠው መልስ ጀርባ እናገኝዋለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ በሞቱ ወቅት
የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር እና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ
መኮንን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በእውቀት የተመሰረተ ህብረተሰብን ገንብተዋል›› ብለዋል፡፡ ይሄ እንዴት ይለካል? ነው ጥያቄው፡፡ ምን ማለትስ ነው?
‘የስክሪን ትውልድ’
ሌላው መፅኃፍን ያስረሳው ጉዳይ
አዳዲስ ‘አማራጮች’ መስፋታቸው ነው፡፡ ከነዚህ አዳዲስ ክስተቶች አንዱ እና ዋነኛው የሲኒማው ዓለም ዘመነኝነት እና ተደራሽነት
ናቸው፡፡ በአጭር ጊዜ፣ በግሩም ቴክኖሎጂ እና በተለያየ መልኩ የሚቀርቡት ሲኒማዎች ትውልዱ ለመፅኃፍ ጀርባውን እንዲሰጥ አድርጎታል፤
የሚለው መከራከሪያ ደግሞ በአንድ በኩል ይቀርባል፡፡ ግን ሲኒማ መፅኃፍን የማስረሳት አቅም አለው ማለት ይቻላል? አንዳንዶች ዘመነኞቹ
መረጃን በቀላልና ክሽን ባለ መልኩ (Cooked) መፈለጋቸው ወደሲኒማው ዓለም እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡
ነገር ግን እስኪ ስንቱ ሲኒማ ተመልካች
ነው “Twilight” መጀመሪያ መፅኃፍ እንደነበር የሚያውቀው? ማነው “Avatar” አይቶ ከመፅኃፍ ላይ የተወሰደ ታሪክ እንደሆነ
የሚያስተውለው? “Harry Potter” ተከታታይ ሰኒማን ተመልክቶ መፅኃፍ፤ በምእራቡ ዓለም እንደ ቅዱስ መፅኃፍ የሚመለክ መሆኑን
ልብ ያለ ስንቱ ይሆን?
እንግዲህ ‘የስክሪን ትውልድ’ ተብሎ
የተፈረጀው ዘመነኛ አይኑ ቴሌቪዥን ላይ እንደተተከለ መፅኃፍ አንብበው ሲኒማውን የሰሩትን ሰዎች እንዳደነቀ እዛው ሶፋ ላይ ይተኛል፡፡
እንዴት ነው?
የቀበሌው ‘ድራፍት ቤት’
መንግስትም እንደዋነኛ ባለድርሻ
የመፅኃፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን ይሰራ ዘንድ ከሚጠበቁ አካላት አንዱ ነው፡፡ በየምንኖርበት አካባቢ ያለውን ‘የድራፍት
ቤት’፣ ካለው የቤተ መፅኃፍት ቁጥር ጋር አነፃፅረነው እናውቅ ይሆን? በመንግስት ድጋፍ የሚቋቋሙ ‘የድራፍት ቤቶች’ እንዳሉ ሁሉ፤
ምን ያክል ቤተ መፅሃፍተስ እንዲሁ ይቋቋማሉ? ብለን መጠየቅ መንግስት ለዘርፍ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቷል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ
ያስችለናል፡፡
‘ድራፍት ቤቶች’ መኖራቸውን ልቃዎም
አይደለም፡፡ ነገር ግን በነሱ ትይዩስ ምን እየቀረበ ነው? ነው ጥያቄው፡፡ መንግስት በተለያዩ ፖሊሲዎቹ ትኩረት የሚሰጠው ልማት
የአእምሮ ልማትን በቅጡ ያካተተ ነው ወይስ አይደለም?
ይሄን ፅሁፍ ስንጀምር ከእንግሊዊው
ባለቅኔ ጆን ሚልተን ‹‹መፅኃፍ ምክንያት ነው፤ መፅኃፍ ከሌለ ምክንያት የለም ››የሚለውን ሀሳብ ተንተርሰን ነበር፡፡ እናም የእኛ
ምክንያታዊነትስ እያደገ ነው ወይስ በተቃራኒው? ብለን በመጠየቅ ሳባችን እንቋጭ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
Lasebewe yemechelewen endewem keza belaye askemetehewal!! Thank you Mr.Zola!
ReplyDeleteManbeben susey lemadrege terete laye nege Yekenahe beleng!!