Wednesday, April 27, 2016

We Thank You! እናመሰግናለን!

We Thank You!
We dedicate the recognition to all who sacrifice their personal security to the common cause of human rights respect in Ethiopia.

እናመሰግናለን!
ዕውቅናው ለኛ ብቻ ሳይሆን በአገራችን ለደኅንነታቸው ሳይሰጉ ለሰብኣዊ መብት መከበር ራሳቸውን አሳልፈው ለሰጡ እና እየሰጡ ላሉ ይሁንልን።

(We are named one of the three finalists of Martin Ennals' Award 2016 | የ2016 የማርቲን ኤናልስ ተሸላሚ ሦስት የመጨረሻ ዕጩዎች አንዱ ተደርገናል።)

Please find here the English presser.
በአማርኛ የተዘጋጀውን መግለጫ እዚህ ተመልከቱ!

Monday, April 25, 2016

የሁለት ሳምንታት ጓደኛዬ

በአቤል ዋበላ

ማዕከላዊ እንደገባኹኝ ከእኔ በፊት በዚያ የነበሩ ሠባት እስረኞች ተቀበሉኝ፡፡ ክፍሏ ከመጥበቧ የተነሳ እኔ እንድተኛበት ያመቻቹልኝ ቦታ ከሽንት መሽኛው ባሊ አጠገብ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ይመጣ ይሆን እያልን አንዳንዴ በድፍረት ብዙውን ጊዜ ደግሞ በፍራቻ የምንጠብቀው እስር ስለመጣ ይሆን ወይም ቀን በስራ የዛለው ሰውነቴ አላውቅም እንደገባኹኝ እንቅልፍ ጣለኝ፡፡ ስነቃ መንጋት አለመንጋቱን ማወቅ አልቻልኩም ነበር፡፡ ክፍሉ ጨለማ ነው፡፡

በመተላለፊያው ኮሪደር እና በኛ ሴል መሐል የምትገኝ አንዲት አምፑል የደከመ ብርሃኗ ይተየኛል፡፡ ወደክፍሉ ሳማትር ብርድ ልብስ ለብሰው የተጋደሙ ሰዎች፣ ኩርቱ ፌስታሎች እና በኋላ የሽንት መሽኛ ባሊ መሆኑን የተረዳኹት አንድ ነገር ይታዩኛል፡፡ ያለኹት ፌደራል ወንጀል ምርመራ መሆኑን ስረዳ ምን ያረጉኝ ይሆን የሚለው ስጋት ልቤን ይንጠው ገባ፡፡

አጠገቤ የተጋደመው ቀጭን ረጅም ሰው ብንን ብሎ ተነሳ፡፡ አነሳሱ ስላስደነገጠኝ ብበሽቅም ከማልወጣው የሀሳብ አዙሪት ስለገላገለኝ ደስታ ቢጤ ተሰማኝ፡፡ ፍራሽ ባልነጠፈባት ቀሪ ከሁለት ካሬ በምታንስ መሬት ላይ ቆሞ ይተጣጠብ ጀመር፡፡ ዑዱ እያደረገ መሆኑ ገባኝ፡፡ እኔ ጎን ወደሚገኘው ፍራሹ ተመልሶ ድምጹን ከፍ አድርጎ መስገድ ጀመረ፡፡ ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደከተተኝ ወያኔን እያማረርኩኝ ጸሎቱን እስኪጨርስ በትግስት መጠበቅ ጀመርኩኝ፡፡ ከአምላኩ ተገናኝቶ ሲጨርስ ወደግራ እና ቀኝ ተገላምጦ ሲያበቃ ባይተዋር ሰው በጭንቀት እየተመከተው እንደሆነ አስተዋለ፡፡ “አብሽር አብሽር” ብሎ ሰላም አለና ድንጋጤዬን አበረደው፡፡
 
ስሙ ዚያድ ያሲን ይባላል፡፡ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር  ወታደር ነው፡፡እየቆየው ከሌሌቹ እስረኞች ጋር ስግባባ አንድ ቶፊቅ ያሲን የሚባል አማርኛ፣ እንግሊዘኛ እና ኦሮምኛ አቀላጥፎ የሚናገር  አረብኛ ደግሞ በመጠኑ የሚሞክር ፋርማሲስት  በቆይታ ከዚያድ ጋር የፈጠሩትን የጋራ መግባቢያ በመንገር ወዳጅነታችን እንዲጎለብት አደረገው፡፡  ከሱማልኛ በቀር ሌላ ቋንቋ ባይችልም ሌበረሽን ፍሮንት ደጋግሞ ከአፉ የማይጠፋ ሁለት የእንግሊዘኛ ቃላት ናቸው፡፡ ቀብሪደሃር ነው የተወለደው፡፡ ገና ልጅ ሳለ ያጋጠመው ትዕይንት የህይወቱን መስመር ቀየረው፡፡ መንደራቸው በእሳት ሲቀጣጠል፣ ህጻናት እና ሴቶች ሲያለቅሱ፣ ወጣት ወንዶች እና ጉልማሳዎች በጥይት ተመተው ወድቀው ማየቱን ለማስረዳት እኔ የምረዳቸውን አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች አለማወቁ አላገደውም፡፡ የተለያዩ ድምጾችን እያወጣ፣ በሰውነቱ የተለያየ ቅርጽ እየሰራ የልጅነቱን ትዝታ ያካፍለኝ ጀመር፡፡ አብረውኝ ከታሰሩ ሰዎች ቀድሞ ወዳጅ አደረገኝ፡፡  ያ በልጅነቱ የተመለከተው ዕልቂት ሁሌም የንግግሩ ማጠንጠኛ ነው፡፡ እናም ያንን እንደተመለከተ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን ለመቀላቀል ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ያኔ የነበረው የፖለቲካ አመለካከት ጥቂት እንደሆነ እና መደበኛ ትምህርት እንዳልተማረ ፈገግ እያለ ያስረዳኝ ነበር፡፡ የማዕከላዊ መርማሪዎች የኦኤንኤልኤፍ አመራር አባል አድረገው ምንም ትምህርት የሌለውን ዚያድ መጠርጠራቸው ማዕረግ መደርደሪያ ትከሻውን እየደበደበ በድንቁርናቸው መገረሙን እየሳቀ ይነግረኛል፡፡ የሚገርመው ስለምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ እና ታሪክ ጥሩ ግንዛቤን ሰባት ዐመታት በፈጀው የደፈጣ ተዋጊነት ጊዜው አዳብሯል፡፡ መተኮስ ስለሚችላቸው ከባድ መሳሪያዎች አውርቶ አይጥግብም፡፡ በእኔ ምንም አለማወቅ ይገረም ነበር፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ እርሱም የኔን ታሪክ መጠየቅ ጀመረ፡፡ አየር መንገድ እንደምሰራ ለማሰረዳት ከባድ አልሆነብኝም የከበደኝ የእስሬን ምክንያት መግለጽ ነበር፡፡ እጄን የኮምፒዩተር ኪቦርድ እየደበደብኩኝ ሳስረዳው እስሬ ከኮምፒዩተር ጋር እንደተያያዘ ገባው፡፡ ኢንተርኔት የሚለው ቃል ከአፌ ሲወጣ ግን አደገኛ ሰው መሆኔን የገመተ መሰለኝ፡፡ በደፈጣ ተዋጊነቱ ዘመን ኦኔን ኤል ኤፍ የማረካቸውን ነዳጅ ሊቆፍሩ የመጡ ቻይናዎች ለመመለስ የተደራደረው ቻይኖቹ ለግንባሩ መጠቀሚያ የሚሆን የኢንተርኔት ማሽነሪዎች እንደሰጡ በማድረግ መሆኑን ያስታውሳል፡፡ ከትግል አጋሮቹ የተረዳው ኢንተርኔት ጠቃሚ የመታገያ መሣሪያ እንደሆነ ነው ፡፡  አለሙን በሞላ በወሬ እንደሚሞላም ግንዛቤም እንዳለው በሰፊው ከሚያወራጫቸው እጆቹ አወቅሁኝ፡፡
አንድ ሳምንት ከሌሎቹ እስረኞች ጋር ስምንት ሆነን ከዘለቅን በኋላ ሁሉንም ወደሌላ ክፍሎች ቀይረው እኔ እና ዚያድ ብቻችንን ቀረን፡፡ ወዳጅነታችን እጅግ ጠነከረ፡፡ አሁን ሳስታውሰው ያለቋንቋ እንዲያ መግባባታችን ይገርመኛል፡፡ ለዚያድ ባሬ ያለው ፍቅር፣ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ያለው ግንዛቤ፣ አምስቱ ሶማሌዎች ተሰብስበው እንዴት “ታላቋ ሶማሊያን” እንዴት እንደሚመሰርቱ፣ ይተነትንልኛል፡፡
በሶማሌ ላንዷ ሀርጌሳ ያሳለፈውን ጊዜ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳን በእጁ አንደጨበጠ በኩራት ደጋግሞ ይነግረኛል፡፡ ብቻችንን ስንቀር የኦጋዴን ነጻ  አውጪ ግንባር የትግል ዘፈኖች ይዘፍንልኝ ነበር፡፡ ቋንቋ በማይገድበው ዜማ የተበደለውን የኦጋዴን ህዝብ ጭቆና እና የታጋዮችን ቁርጠኝነት ያስረዳኝ ነበር፡፡ አንዳንዶችን አብሬው ለማንጎራጎር እሞክር ነበር፡፡ “ወያኖ” የሚል ቃል ያለው እንዴት ወያኔን አባረው የራሳቸውን ሀገር እንዴት እንደሚመሰርቱ የሚገልጽ ዘፈን ዜማው እስካሁን ድረስ በአእምሮዬ ያቃጭላል፡፡

ከዚያድ ጋር የምንጣላው አዲስ የምትመሰረተው ኦጋዴን የምትባል ናዝሬትን(አዳማ)፣  ሐዋሳ እና ድሬዳዋን እንደሚጠቀልል ሲነግረኝ ነው፡፡ “ይሄማ የኢትዮጵያ መሬት ነው” ስለው ሦስቱ ከተሞች ድሮ የሱማሌ መሆናቸውን እና ስያሜያቸው ሌላ እንዳነበረ ስያሜውን እየጠቀሰ ይነግረኛል፡፡ “ሂውማን ራይት” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ዚያድ በትክክል ተረድቶታል፡፡  ሂውማን ራይት ካለ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሐሳባቸውን ይቀይሩ እንደሆን እንደምንም ተፍጨርጭሬ ስጠይቀው እኔን ደስ እንዲለኝ ብቻ በሐሳቤ እንደተስማማ ይገባኛል፡፡

ዚያድ ሁሌ ደስተኛ ነው፡፡ ሁሌ ሰላቱን ይሰግዳል፤ ወያኔ በቅርብ ቀን እንደሚወድቅ ደስተኛ ነው፤ ያገኘውን ይበላል፤ እዛው ማዕከላዊ የተማረውን በተለምዶ ‘እንጀራ በወጥ’ የሚባለውን የካርታ ጨዋታ ብቻውን ይጫወታል፤ በየደቂቃው እየተነሳ በበሩ ትንሽ ቀዳዳ በመተላለፊያው ማን ወደ ምርመራ እንደሚሄድ ይመለከታል፡፡

ፀሐይ ስንወጣ ወይ አንዳችን ወደምርመራ ስንሄድ አንድ ባንድ ጓደኞቼን ለያቸው፡፡ ሁሉንም የራሱ የኮድ ስም ሰጣቸው፡፡ በአረብኛ ሳሂብ ማለት ጓደኛ መሆኑን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ዚያድ ይህንን ጓደኞቼ ከታሰሩበት ክፍል ቁጥር እና አንዳንድ ሁኔታዎች በማያያዝ የራሱን መለያ ፈጠረ፡፡ በቀዳዳው አጮልቆ “ሳሂብ ነምበር ናይን ፒው” ካለ በፈቃዱ ለምርመራ እንደተጠራ አውቃለው፡፡ ሳሂብ ነምበር ስሪ፣ ሳሂብ ነምበር ፎር ተስፋለም፣ ሳሂብ ነምበር ፋይቭ ዘላለም፣ እንደሆኑ አውቃለው፡፡ ጋዜጠኛው አስማማው ሀይለ ጊዮርጊስ ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከነበረው ኦኬሎ አኳይ ጋር በመታሰሩ ምክንያት ስሙ “ሳሂብ ኦኬሎ” ነበር፡፡ ከሁሉም የሚያስቀኝ ናትናኤል የነበረበት ክፍል ለመለየት የሚጠቀምበት ኮድ ነው፡፡ ናትናኤል ፈለቀ ታስሮ የነበረው ሽንት ቤት ጎን የሚገኝ ሰባት ቁጥር የሚል መለያ የነበረው ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ዚያድ ናትናኤልን እንደሌሎቹ ሳሂብ ነምበር ሰቭን ሊለው አልወደደም፡፡ ዚያድ ሁለት ሳምንቱን አብረን ቆይተን ወደ ሌላ ክፍል እስኪቀየር ድረስ የናቲ ስም “ሳሂብ ሽንት ቤት” ነበር፡፡

የእኔ እና ዚያድ አብሮነት ከሁለት ሳምንት በላይ አልዘለቀም፡፡ ከእኛ ቀድሞ ተከሶ ወደ ቅሊንጦ ወረደ፤ እኛ ስንከተል ደግሞ ዞን ተለያየን ፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ስንሄድ አግኝቸው የክፉ ቀን ጓዴን ሰላም ብዬዋለው እንደድሮው ግን ቋንቋ ሳያግደን የሆድ የሆዳችንን አልተጫወትንም፡፡ አሁን በተከሰሰበት መንግስት “የሽብርተኝነት” በሚለው እርሱ ደግሞ “የነጻነት ትግል” ብሎ በሚጠራው  ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ የሚቀጥሉትን አመታት በእስር ማሳለፉ አልቀረም፡፡ ማዕከላዊ በነበርን ጊዜ የነበራው ተስፋ እና ደስታ ሁሌም አብሮት እንዲቆይ ምኞቴ ነው፡፡

“ከመሞት መሰንበት” ~ መገርሳ

በበፍቃዱ ኃይሉ

ዓይን የሚፈታተን ደብዛዛ ብርሃን ያለበት ክፍል ውስጥ አስገብተው ከኋላዬ ወፍራሙን የብረት በር፣ ልብ በሚያደባልቅ ጓጓታ ድብልቅ አድርገው ዘጉት፡፡ ወደመታሰሪያ ክፍል የገባሁት እንዲህ ነበር፡፡ ሰዓቱ ከምሽቱ 3፡00 ወይም 4፡00 ሰዐት ገደማ ነው፣ ሚያዝያ 17፣ 2006፡፡ ከውስጥ መሬት ላይ የተኙ ሰዎች ይታዩኛል፡፡ በእጄ ያንጠለጠልኩትን ፌስታል እንደያዝኩ ተራ በተራ አየኋቸው፡፡ አንደኛው ከተኛበት ተነስቶ ቁጢጥ አለ፡፡ ‹ካቦው ይሄንኛው ነው ማለት ነው› አልኩ በልቤ፡፡ ‹የሻማ ሲጠይቁኝ ኪሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ሰጥቼ ለመገላገል ፈልጌያለሁ› እነርሱ ግን የሻማ አልጠየቁኝም፡፡ ‹አረፍ በል› አሉኝ፡፡ ጠርዝ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ‹ራት በልተሃል?› አሉኝ፤ ‹አዎ በልቻለሁ›፡፡

‹ምን አድርገህ ነው?›
‹ጸሐፊ ነኝ፡፡›
‹አሃ፣ ጋዜጠኛ ነህ?›
‹አይ፣ ኢንተርኔት ላይ ነው የምጽፈው፡፡›
‹ሙስሊም ነህ?›
‹አይ አይደለሁም፡፡›

የሚያስፈራ ዝምታ ሰፈነ፡፡ ‹እናንተስ?› አልኳቸው፤ ዝምታውን ለመስበር፡፡

ቁጢጥ ያለው፣ ‹እኔ እና እሱ› አለ ወደ አንደኛው ልጅ እየጠቆሙ ‹በሙስሊሞች ጉዳይ ነው፤ እነሱ› አለኝ ወደሌሎች ሦስት ልጆች እየጠቆመ ‹ከጋምቤላ ነው የመጡት፤ እኚህ ከሶማሊ ክልል ነው የመጡት፡፡ ያኛው› ወደጥግ ወዳለው እየጠቆመ ‹በግንቦት ሰባት ነው የተጠረጠረው› አለኝ፡፡ ሰባት ነበሩ፡፡ እኔ ስምንተኛ ሆንኩላቸው፡፡ በሳይቤሪያ የዘጠኝ ቁጥር እስረኛ ሆኜ ተቀላቀልኳቸው፡፡ ማብራሪያውን የሰጠኝ ረደላ ሸፋ ነበር፡፡ ሦስቱ አኙዋኮች ኡማን ኝኬው፣ ኡጁሉ ቻም እና ኝጎ ኩምቻሬ ነበሩ፡፡ ሶማሌው፣ እኔ በገባሁ በሁለተኛው ቀን ስለተፈታ ዘነጋሁት፡፡ የረደላ አባሪ ሐሰን ነው፡፡ ጥግ ላይ የነበረውና በክፍላችን ብቸኛው የግንቦት ሰባት ወታደርነት ተጠርጣሪ የነበረው አበበ ካሴ ነበር፡፡

ኒጎ ኩምቻሬ እሱ ተኝቶባት የነበረውን ፍራሽ ለቆልኝ እስከመጨረሻ ድረስ የቆየሁባትን ጥግ ላይ ያለች ምቹ ቦታ አወረሰኝ፡፡ ‹በቃ፣ አሁን ተኛ እና ነገ እናወራለን› አሉኝ፡፡ እሺ አልኳቸው፡፡ እነርሱ ተኙ፡፡

አበበ ካሴ እኔ በገባሁበት ሰዐት ምርመራ ጨርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን በአስፈሪ ዝምታ የተዋጠ ሰው ነበር፡፡ ተሰብስበን ኮንከር (ካርታ) ስንጫወት ብቻ፣ እየዳኘ በተራው ይጫወታል፡፡ እየቆየን ስንመጣ ግን ቀስ በቀስ ያዋራኝ ጀመር፡፡ ጠርጣራ ስለነበር፣ ድምፁን በጣም ዝቅ አድርጎ በእርጋታ ነበር የሚያዋራኝ፡፡ ምርመራ አምሽቼ ስመጣ፣ እልሄን የምወጣው እነሱ ጋር ነበር፡፡ ያሉኝን ብስጭቶችና ብሶቶች ሁሉ እነርሱ ላይ እዘረግፈዋለሁ፡፡ እነርሱም፣ አብዛኞቹ ምርመራቸውን ጨርሰው ክስ የሚጠባበቁ ስለነበሩ፣ እኔን ከበው ማፅናናት ብቻ ሆነ ሥራቸው፡፡ አበበ አንድ ቀን ማታ መጥቼ እንደለመድኩት ‹ሊገሉኝ ነው፤ ካልገደሉኝ አይለቁኝም› እያልኩ ሳማርር፡፡

‹አሁን ይቺን ተመታሁ ብለህ ነው?› አለኝ፡፡

በአባባሉ ተናድጄ መልስ ከመስጠቴ በፊት የእጆቹን አይበሉባ አሳየኝ፡፡ ‹ጥፍሮቼን እያቸው› አለኝ፡፡ ጥፍሮቹ ጣቶቹ ላይ የሉም፡፡ ‹እኔ እንኳን እንዲህ አድርገውኝ ዋጥ ነው ያደረግኳት፡፡ ወንድ ልጅ ቻል ነው ማድረግ ያለበት፡፡ ወንድ አደለህ እንዴ?› እኔ የወንድነት ጀብድ የምመኝበት ጊዜ ላይ አልነበርኩም፡፡ ይልቁንም እሱ እኔን ለመምከሪያ ያሳየኝ ጣቶቹ ማስፈራሪያ ሆነው አረፉት፡፡ እኔም ባለተራ ነኝ ብዬ አሰብኩ፡፡

አበበ ካሴ ቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበረ፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተዋጋ፣ ከዚያ በኋላ ግን ለቅቆ ግንቦት ሰባትን የተቀላቀለ ወታደር ነበር፡፡ ሲራመድ ያነክሳል፡፡ ‹ምን አርገውህ ነው?› ስለው ‹ምኑን አውቄ› አለኝ፡፡ ሲደበደብ ራሱን ይስት ነበር፡፡ አበበ ካሴ ከኤርትራ ጎንደር የዘመዱን ሠርግ ለመታደም መጥቶ ነው የተያዘው፡፡ በምርመራ ወቅት የግንቦት ሰባት ወታደር መሆኑን በፍፁም አላመነም ነበር፡፡ ያደገበት እና የኖረበት ኩራት በዱላ ፊት መንበርከክ አልፈቀደለትም፡፡ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ ግን ለፍርድ ቤቱ “አዎ፣ የግንቦት ሰባት ወታደር ነኝ፤ የሆንኩትም አምኜበት ነው” ብሏል፡፡

አበበ ካሴ ከኔ ክፍል ተቀይሮ ተስፋለም ታስሮበት ወደነበረው 4 ቁጥር የተዛወረው ከአጭር ቀናት በኋላ ነበር፡፡ ነገር ግን መልሰን ቂሊንጦ ዞን ሁለት ተገናኘን፡፡ አበበ መጀመሪያ የተከሰሰው በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ በአንቀጽ 4 ቢሆንም፣ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከተደመጡ በኋላ ተቀይሮለት 7/1 ሆኖለታል፡፡ የዛኔ ‹እንኳን ደስ አለህ› ልለው ክፍሉ ሄጄ ነበር፡፡ ሳቀብኝ፡፡ ‹ታስሬ እያለሁ ቁጥር ተቀነሰልኝ ብዬ የምደሰት ይመስልሃል?› ስሜቱን አላጣሁትም፡፡

እንደአበበ ካሴ በቂሊንጦ አስተዳደር የሚጠላ የፖለቲካ እስረኛ አልገጠመኝም፡፡ አበበ ሕክምና ተከልክሎ እግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸመቀቀ አጥሮ ግቢ ውስጥ በምርኩዝ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ብልቱ ላይ በምርመራ ወቅት በደረሰበት ጉዳት የሚያዥ ነገር ተከስቶበት ሕክምና ሲጠይቅ ተከልክሏል፡፡ በጥቅሉ የሰው ልጅ ላይ የሰው ልጅ ሊያደርስበት የሚችለው በደል ሁሉ እየደረሰበት ነው፡፡
አበበ ካሴ አሁን 7 ዓመት ከዘጠኝ ወር ፅኑ እስራት ተፈርዶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ገብቷል፡፡

እንደ አበበ ሁሉ አዱኛ እና መገርሳም በየቀኑ ሐሳቤ ናቸው፡፡ ማዕከላዊ ሳይቤሪያ የሚባለው ወንዶች ክፍል፤ ዘጠኝ ቁጥር ውስጥ ሁለት ሳምንት ከቆየሁ በኋላ ከክፍላችን የሚወጡ ሰዎች በዙ፡፡ ከሦስቱ የአኙዋ ልጆች አንዱ - ኝጎ ኩምቻሬ - ጓደኞቹ ላይ ሊመሰክር ተስማምቶ ወደጣውላ ክፍል ተዛወረ፡፡ ኡማን እና ኡጁሉ ክስ እስኪመሠረትባቸው ድረስ ወደሚቆዩበት ሸራተን ተዛወሩ፡፡ የሶማሊ ክልሉ ሰው ተፈታ፡፡ በምትካቸው ግን ብዙ ሰዎች መጡ፡፡

የአዳማ ዩንቨርስቲው አዱኛ ኬሶ መጣ፡፡ ገብረሚካኤል እና ሌላ ሥሙን የዘነጋሁት ሰው ከትግራይ ክልል መጡ፡፡ ሌላም ሰውዬ ከሶማሊ ክልል መጡ፡፡ አጀሌ ከቤንሻንጉል/ጉምዝ መጣ፡፡ ሁሉም የተጠረጠሩት በሽብርተኝነት ወንጀል ነው፡፡

ከሁሉም ሳቂታና ተጫዋች የነበረው አዱኛ ኬሶ ነበር፡፡ አዱኛ ከተያዘ 19 ቀናት እንደሆነው ነገረን፡፡ ‹የት ቆየህ?› አያውቀውም፡፡ ምክንያቱም፣ ወደቆየበት ቦታ ሲሄድም ሆነ ወደእኛ ሲመጣ ዓይኖቹ በጨርቅ ተሸፍነው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደሽንት ቤት ሲወሰድ እና ሲመለስ ዓይኖቹ በጨርቅ ይሸፈኑ ነበር፡፡ አዱኛ ወደኔ ክፍል ሲመጣ ግራ ዓይኑ ስር የበለዘ ነገር ነበረው፡፡ ‹ምንድን ነው?› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹ሲይዙኝ በቡጢ የነረቱኝ ነው› አለኝ፡፡ አሁን ድረስ ያ የቡጢ አሻራ ጠባሳ ሁኖ ቀርቷል፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ በፖሊስ ተደግፎ መጥቶ፣ በፖሊስ ተደግፎ 8 ቁጥር (የብቻ ጨለማ ቤት) ሲወጣና ሲገባ የቆየው መገርሳ ወደእኛ ክፍል ገባ፡፡ መገርሳ ወርቁ የሐሮማያ ዩንቨርስቲ ተማሪ ነበር፡፡ መገርሳ መጀመሪያ የተያዘው ሐረማያ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ቦምብ ተሳትፈሃል በሚል ተጠርጥሮ ነበር፡፡ መገርሳን ሐሮማያ ከተማ ተደብድቧል፡፡ ድብደባው እርቃን ነበር፡፡ እጆቹ በገመድ ተጠፍረው ጉልበቱን ያቅፍና በእጆቹ መታጠፊያ እና በቋንጃው መካከል እንጨት ያልፍና ይሰቀላል - ወፌ ይላላ፡፡ ከዚያ ይደበደባል፡፡ መገርሳ ይህንን ይነግረኝ የነበረው፣ እግሮቹ መታጠፊያ ላይ የቀረውን ሰምበር የመሰለ ነገር እያሳየኝ ነው፡፡ ‹ተንጠልጥዬ እየተሰቃየሁ ብልቴን ይጎትቱታል› ብሎኛል ሲነግረኝ፡፡ በመሐሉ ራሱን ይስታል፡፡ ‹ከዚያ ቅዝቅዝ ሲለኝ እነቃለሁ፤ ስነቃ አውርደውኝ አገኛለሁ፡፡ አሁንስ ታምናለህ አታምንም ይሉኛል፡፡ የማምነው ነገር እንደሌለ ሲያውቁ መልሰው ይሰቅሉኛል፡፡› አለ፡፡ በመጨረሻ ግን መገርሳ ተረታ፡፡
‹ሳስበው ከምሞት፣ ዕድሜ ልክ ተፈርዶብኝ በሕይወት ብኖር ይሻለኛል ብዬ አሰብኩ› አለ፡፡ ‹አዎ፣ እኔ ነኝ ቦንቡን የወረወርኩት› አላቸው፡፡ መርማሪዎቹ ተደሰቱ፡፡ ራቁቱን የሆነ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ አጋድመውት ሄዱ፡፡ ከዚያ ‹በሕይወቴ የማይዘነጋኝ ዘግናኝ ነገር ተከሰተ› ብሎ የሚከተለውን አጫወተኝ፡፡ ቤቱ ውስጥ የዶሮ ጫጩቶች ነበሩ (የአንዱ የደህንነት ሰራተኛ መኖሪያ ቤት ውስጥ ይመስለዋል ያለው)፡፡ ጫጩቶቹ መጥተው እየተራመዱ እላዩ ላይ ይወጡበታል፡፡ መገርሳ እነርሱን “እሽ” ብሎ የሚያባርርበት አቅም አልነበረውም፡፡ እግራቸው ይበላዋል፡፡ ሲነግረኝ ‹ጫጩቶቹን ጠላኋቸው› ነበር ያለኝ፡፡ ግን ምንም ሊያደርጋቸው አልቻለም፡፡

በማግስቱ በካሜራ ፊት ሐረማያ ዩንቨርስቲ ግቢ ውስጥ የፈነዳውን ቦምብ ያፈነዳው እሱ እንደሆነ አመነ፡፡ እሱ በወቅቱ ዩንቨርስቲው ግቢ ውስጥ አልነበረም፡፡ እንዲያውም የታቀደ ረብሻ እንዳለ መረጃው ቀድሞ ደርሶት ለዩንቨርስቲ ግቢው የኦሕዴድ ጽ/ቤት ደውሎ ማስጠንቀቁን ነግሮኛል፡፡ ያ ሁሉ አልፎ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ነገር ግን፣ እሱ ወደአዲስ አበባ እየመጣ እያለ ፖሊስ የእውነትም ቦንቡን ወርውሮታል ብሎ ያመነበትን ሰው ያዝኩኝ አለ፡፡ ነገር ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ ባይ መንግሥት መገርሳን ከመክሰስ አልተመለሰም፡፡ ጽፈኸዋል በተባለው ግጥም ክስ ተመስርቶበት ‹ተከላከል› ተብሎ፣ መከላከያ ምስክሮቹን አስደምጦ ‹የነጻ› ወይም ‹ጥፋተኛ› ብይን እየተጠባበቀ ነው፡፡ አዱኛ ኬሶም በተመሳሳይ መዝገብ ‹በቄሮ አባልነት› ተከላከል ተብሎ መከላከያ ምስክሮቹን እያስደመጠ ነው፡፡

ታስሮ መፈታት ቅጣት ነው፡፡ ሰቅጣጭ በደል በሚፈፀምባት ከተማ፣ አገር ሠላም ብሎ ከሚኖር ሰው ጋር ምንም እንዳላየ፣ ምንም እንዳልሰሙ መስለው የመኖር ቅጣት፡፡

ማዕከላዊ ምርመራ ወጥቼ ስገባ፣ መታሸት ሲያስፈልገኝ ሲያሸኝ፣ ጨዋታ ሲያመምረኝ ሲያጫውተኝ የነበረው ረደላ ሸፋ እና አባሪው ሀሰን ሁለቱም ‹ነጻ ለመውጣት ወይም ጥፋተኛ ለመባል ተከላከሉ› ተብለው መከላከያ ምስክሮቻቸውን ለማስደመጥ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ የቤንሻንጉሉ አጄላ አራት ዓመት ተፈርዶበት ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስዷል፡፡ አቦይ ገብረሚካኤል ‹ተከላከሉ› ተብለው መከላከያ ምስክር እያስደመጡ ነው፡፡ ኡማን እና ኡጁሉም ‹ጥፋተኛ› ተብለው ፍርዳቸውን ለመመቀበል ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡

እስረኞች ይመጣሉ፣ ከሰሜን ይመጣሉ፣ ከደቡብ ይመጣሉ፣ ከምሥራቅ ይመጣሉ፣ ከምዕራብ ይመጣሉ፡፡ በሕዝብ ጥቅም ሥም ጦር መዝዞ ሥልጣን የተቆጣጠረው መንግሥት ዛሬም የፖለቲካ እስረኞች የሉኝም ይላል፡፡

ኒምኦ እና ሂንዲያበማህሌት ፋንታሁን

በመጀመሪያ ጣውላ ቤት
 
ከታሰርኩበት ሚያዚያ 17/2006 አመሻሽ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሰማኒያ አራት ቀናት “የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ” (ማዕከላዊ) እኖርበት የነበረው ክፍል በተለምዶ ጣውላ ቤት ይባል ነበር። አምስት ክፍሎች አሉት። በፊት እነዚህ ክፍሎች የወንዶች እስረኞች ነበሩ። እኔ ከመግባቴ ከአራት ወር በፊት  እዛው አካባቢ የምትገኝ አንዲት ክፍል ውስጥ ነበር ሴት እስረኞች የሚኖሩት። ወይም ብቻቸውን እንዲሆኑ የሚፈለጉ ሴት እስረኞች ከአምስቱ በአንዱ ክፍል ለብቻቸው እንዲኖሩ ይደረጋሉ። ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ማዕከላዊ የቆየችባቸውን ጌዜ በሙሉ ከአምስቱ ክፍሎች  በአንዱ ብቻዋን ነበር የምትኖረው። ሴቶቹ የሚኖሩባት ክፍል ለእስረኞቹ  እየጠበበቻቸው ስትመጣ እዛ መኖራቸው ቀርቶ አምስቱ ክፍሎች ያሉበትን (ጣውላ ቤት) ሁለቱ (1 እና 2 ቁጥር) ተለይቶ በረንዳው ላይ በቆርቆሮ ተጋርዶ ፤ እንደታሳሪው ብዛት ሶስቱ ክፍል ላይ ሴቶች፤ ሁለቱ ላይ ወንዶች ወይም ሁለቱ ላይ ሴቶች ሶስቱ ላይ ወንዶች ይኖሩበታል። ጣውላ ቤት የሚኖሩ ወንድ እስረኞች በብዛት የመርማሪዎች ድብደባን መቋቋም ሲያቅታቸው በሌሎች እስረኞች ላይ (በተመሳሳይ የሽብርተንነት ወንጀል ተጠርጥረው ለታሰሩ) ለመመስከር በግዳጅ የፈረሙ ናቸው። አልፎ አልፎ አስም እና ተዛማጅ ህመሞች የሚጠቁ በሽብርተንነት የተጠረጠሩ እስረኞች ጣውላ ቤት እንዲኖሩ ይደረጋል። በአማካኝ 3 ሜትር በ4 ሜቴር ስፋት ያለው ሲሆን በመደበኛ ጊዜ ከ4 እስከ 20 እስረኞች ይኖሩበታል። 

ይድረስ ለአኙዋ ወዳጄ፤ ይነ ፑዋ! ኦሎ ቦንጎ!

በናትናኤል ፈለቀ

ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ ከቤት የሸከፍኩትን ጋቢ እና ቅያሪ ልብስ እንደያዝኩ ማዕከላዊ በተለምዶ ሳይቤሪያ በመባል የሚታወቀው የእስረኞች ማጎሪያ ሕንፃ 7 ቁጥር ገባሁ፡፡ ውስጥ 7 ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ 8ኛ ሆኜ ነው የተቀላቀልኳቸው፡፡ ምንም ሳልናገር ቆሜ ክፍሉን አየሁት፡፡ ሰዎቹን አየኋቸው፡፡

አንድም ቃል ሳንለዋወጥ አንደኛው “ኢትዮጵያ” ብሎ በሀዘኔታ ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡

ኦቻን ኦፕዮ የአኝዋክ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በ1996 በጋምቤላ የተቀሰቀሰውን ግጭት ሸሽተው ወደአሁኗ ደቡብ ሱዳን ከተሰደዱት ኢትዮጵያውያን መካከል ነበር፡፡ በወቅቱ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይፈፅም የነበረውን ግድያ በመሸሽ ለቀናት ጫካ ውስጥ ተደብቆ ከቆየ በኋላ ነበር ቀናትን የፈጀ የእግር ጉዞ አድርጎ ደቡብ ሱዳን የገባው፡፡ ከጁባ አቅራቢያ የአለ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ ከ8 ዓመት በላይ የቆየው ኦቻን ቤተሰብ መሥርቶ፣ ሁለት ልጆችን ወልዶ በጁባ የተረጋጋ ሕይወት መኖር ጀምሮ ነበር፡፡

የ1996ቱ የጋምቤላ ቀውስ በተቀሰቀሰበት ወቅት ክልሉን በርዕሰ ብሔርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ኦኬሎ ኦኳይ በደቡብ ሱዳን መንግሥት ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ሲሰጡ ከጁባ አብረዋቸው የታሰሩት የአኝዋክ ተወላጆች መካከል ኦቻን ኦፕዮ ነበር፡፡

ወደደቡብ ሱዳን ሲሸሽ ጫካ ውስጥ እሾሃማ የዛፍ ቅርንጫፍ የቀኝ ዓይኑን መቶት የማየት ችሎታውን ቢጋርድበትም የቀረችውን የማየት ችሎታውን በአኝዋክኛ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ የእስር ግዜውን ያሳልፋል፡፡ (በነገራችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደአኝዋ የተረጎሙት ኡመድ አግዋ በአሁኑ ወቅት በሽብር ወንጀል ተከሰው ቂሊንጦ ይገኛሉ፡፡)

ኦቻን ሲበዛ ሠላማዊ ሰው ነው፡፡ የሁለት ልጆቹ ነገር አብዝቶ ያሳሰበው ቀን ግን ከሰው ጋር መነጋገር አይፈልግም፡፡ አንድ ቀን ድንገት ብቻውን ስቅስቅ ብሎ ያለቅስ ጀመር፡፡ ሰባት ቁጥር በግዜው የቀረነው እሱ፣ እኔና ዘግየት ብሎ የተቀላቀለን ቢልሱማ የሚባል የሐሮማያ ዩንቨርስቲ ተማሪ ነበርን፡፡ ሁለታችን በጣም ተደናግጠን ምን እንደሆነ ጠይቀነው ሊነግረን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ቆይቶ ሲረጋጋ ልጆቹ እንደናፈቁት እና ምን አጥፍቶ እንዲህ ያለ ፈተና እንደገጠመው እንዳልገባው እያማረረ አጫወተኝ፡፡

በነኦኬሎ ኦኳይ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ ሆኖ ቀድሞ ቂሊንጦ የወረደው ኦቻን ነበር፡፡ ከጥቂት ግዜያት በኋላ እኔም በነሶልያና ሽመልስ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ ሆኜ ቂሊንጦ ስወርድ ኦቻንን ዞን3 አገኘሁት፡፡ እንደመጀመሪያው ሁሉ ተንከባክቦ ግቢውን አላመደኝ፡፡
ኦቻን የአኝዋ አስተማሪዬም ነበር፡፡ ለቤት የመጀመሪያ ልጅ መሆኔን ስለሚያውቅ በአኝዋ ባሕል እንደሚደረገው ኡመድ እያለ ነው የሚጠራኝ፡፡ ትንሽ የማይባሉ የአኝዋ ቃላትንም አስተምሮኛል፡፡

የአኙዋኩ ጓደኛዬ የተከፈተበት የሽብር ክስ የአገር ግዛት አንድነትን ለማፍረስ ሞክሯል በሚል ተቀይሮለት ጥፋተኛ ተብሎ ቂሊንጦ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ እስር ስገባ ያስተዋልኩት በሐዘን ተሞልቶ “ኢትዮጵያ!” ሲል ያማረረው ፊቱ እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ አብሮኝ ይዘልቃል፡፡ ይህችን አጭር ጦማር ያለህበት ድረስ መንፈስ ይዞት ይመጣ እንደሆን ይነ ፑዋ! ኦሎ ቦንጎ! ብዬሃለሁ፣ ኦቻን ኦፒዮ፡፡

“ጅሃዲስቱ” ከማዕከላዊ እስከ ቂሊንጦ

በአጥናፉ ብርሃኔ

አርብ ሚያዝያ 17፣ 2006 ዐሥር ሰአት አካባቢ ከጓደኛዬ በፍቃዱ ኃይሉ ጋር ከቀነኒሳ ሆቴል ወጥተን ትንሽ እንደተጓዝን የበፍቃዱ ስልክ ጠራ፤ ማነገር ጀመረ ቀስ እያለ ዓይኑ በድንጋጤ እየፈጠጠ ሲመጣ አየሁት ቀጥሎ “ምን?!” የሚል ድምፅ ተከተለ። ለበፍቃዱ በስልኩ የተላለፈለት አስደንጋጭ መልዕክት የእስር ወሬ መሆኑን በትንሹም ቢሆን ጠረጠርኩ። ወሩን ሙሉ በደኅንነት ተከበን ስንንቀሳቀስ ስለነበረ የፈራነው እንደደረሰ ገባኝ።

“ከማዕከላዊ ፖሊሶች መጥተው ማሂን ወሰዷት” አለኝ። ደነገጥኩ። ወድያው ሁለታችንም ስልካችን ላይ ተደፍተን ለተቀሩት ጓደኞቻችን መልእክት ለማስተላለፍ ስንፍጨረጨር አንድ ‘ሀይሉክስ ቶዮታ’ መኪና ከፊታችን ቆመ፤ ከመኪናው ውስጥ መደበኛ ልብስ የለበሱ ግለሰቦች ወርደው ስልካችንን በፍጥነት ተቀበሉን። በቆምንበት በፍጥነት ፎቶ አንስተውን ወደ መኪናው አስገቡን።
አስር የሚጠጉ ደህንነቶች የወላጆቼን ቤት በርብረው ከጨረሱ በኋላ ምሽት 3፡20 በፌደራል ፖሊሶች በታጨቀ ‘ፓትሮል’ መኪና ውስጥ ሆኜ በዝና ወደማውቀውና ባለፍኩ ባገደምኩ ቁጥር ቀና ብዬ ወደማየው “የስቃይ ማማ” ማዕከላዊ ገባሁ። ብርድ ልብስና ነጠላ ጫማዬን እንደያዝኩኝ ከመኪና እንድወርድ ተነገረኝ፡፡ ከዛም ወደ አንድ ክፍል አስገብተው ሙሉ ስሜንና ብሔሬን አስመዘገብኩ፡፡ በወቅቱ አርጌ የነበረውን የሸራ ጫማ ክር እንዳስረክብ ተጠየኩ፤ ቀበቶዬንም ተቀማሁ። ራሴን እንዳላጠፋ መሆኑ ነው። ማዕከላዊ ሞት የሚያስመኝ ቦታ መሆኑን ያወኩት ያኔ ነው። አቤልና ናትናኤል ተመሳሳይ ነገር አርገው ሲወጡ መንገድ ላይ ተገጣጠምን ሰለም ልንባባል ስንል “ዞር በል ከዚህ!” የሚል አንባራቂ ድምፅ ሰማሁ። ከዛም አንድ ኮማንደር ‘ሳይቤርያ’ ወደሚባለው የማእከላዊ ክልል ይዞኝ ሄደ። ድፍን ባለ ኮሪደር ውስጥ አስገብቶኝ በግራና በቀኝ ከተደረደሩት ክፍሎች በግራ በኩል ሶስተኛ ቤት የሆነውን ክፍል ቁልፍ መታገል ጀመረ። የክፍሉ በር በወፍራም ላሜራ የተሰራ ነው። የቁልፉ ብረትና በሩ ሲጋጩ የሚፈጥሩት ድምፅ ከአካባቢው ጨለማና ፀጥታ ጋር ተዳምሮ ጆሮ ያማል።

በሩ ተከፈተና ወደ ክፍሉ አስገባኝ፡፡ ዳር ላይ ቆምኩ። ያስገባኝ ኮማንደር በሩን እያንጋጋ ከጀርባዬ ዘጋው። ክፍሉ ውስጥ ትንሽዬ ጭል ጭል የምትል አንፖል ሰው ከማይደርስባት ዳር ላይ ተሰቅላለች፤ ግድግዳው በቁርአን ጥቅስ ተሞልቷል (ታሳሪዎች አሻራ ሰጥተው ሲመለሱ እጃቸው ላይ በተረፈው ቀለም ግድግዳው ላይ እንደሚፅፉ ጥቂት ቆይቶ ገባኝ)፤ መሬቱ አምስት ፍራሽ ያዘረጋል፤ በግራ በኩል አንድ ሰው ጥጉን ይዞ ቆሟል፤ አተኩሬ አየሁት በጣም አጭርና ጥቁር ነው። ልብሱ እላዩ ላይ የተበጫጨቀ፤ ጢሙ የረዘመና የራስ ፀጉሩ የገባ። ሙስሊም እንደሆነ ገፅታው ነገረኝ። ወድያውኑ ጭንቅላቴ እነ አቡበከር አህመድ ጋር ወሰደኝ። ከመታሰሬ በፊት በማዕከላዊ ምርመራ የደረሰባቸውን ስቃይ አንብቤ ነበር። ተስፋ ቆረጥኩ። የልጁ ፊት ላይ የሚነበበው የስቃይ ገፅታ “በቃ አለቀልኝ” ብዬ ለራሴ እንድነግረው አረገኝ። እቃዬን መጥቶ ተቀበለኝና አንዳርፍ ወደ ፍራሹ ጋበዘኝ ፣ ይህ ግለሰብ ሼህ ሳሂብ ይባላል ከጅማ ተይዞ የመጣ በግብርና የሚተዳደር የለየለት ‘ጅሃዲስት’ ነው።

የበሩ ጩኸት ተኝተው የነበሩ ሌሎች እስረኞች ከእንቅላፋቸው ቀሰቀሳቸው። በክፍሉ ውስጥ እኔን ጨምሮ አራት የሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጣሪዎች ስንኖር ሁለት በገንዘብ ነክ ወንጀል ተጠርጥረው የገቡም ነበሩበት። በሽብር ተጠርጥረን የገባነው ሁሴን አሊ (ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር አብሮ የታሰረና የቄራ መስጅድ ኢማምና በኋላም ከኮሚቴዎቹ ጋር 15 አመት ተፈርዶበት ቃሊቲ የሚገኘው የሰድ አሊ ወንድም) በጥሩ ሁኔታ አቀባበል ያረገልኝ፣ ኦታካ ኡዋር የሚባል የአኝዋ ተወላጅና ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚንቀሳቀሰው በዴቪድ ያው ያው የሚመራው ኮብራ አማፅያን ወታደርና በአሁኑ ወቅት በነ ኦኬሎ አኳይ መዝገብ ‘ጋምቤላን ከፌደሬሽኑ በትጥቅ ትግል ልታስገነጥል ሞክረሃል’ ተብሎ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለ፣ እንዲሁም ከላይ የገለፅኩላችሁ ሼኽ ሳሂብ የሚባል አገሪቷ በሸሪያ መተዳደር አለባት ብሎ የሚያምን ‘ጅሃዲስት’ አብረን ነበርን።

ግራ የገባው ‘ጅሃዲስት’?!

“አክራሪነትና ፅንፈኝነት” ለዘመናት ጆሯችንን ሲያደነቁሩ የከረሙ የመንግስት ፕሮፖጋንዳ ቁልፍ ቃላቶች ናቸው። “የሀይማኖት ነፃነት ይከበር፣ በሀይማኖቴ ጣልቃ አትግቡብኝ” ያለና “ኢትዮጵያ በሸርያ ነው መተዳደር ያለባት፣ ሌላ ሀይማኖት መኖር የለበትም፣ ግብር ለመንግስት አልከፍልም፤ ሀራም ነው” የሚል በመንግስት አይን እኩል ፅንፈኛና አክራሪ ተብለው የአሸባሪነት ካባ ያስደርባል።
ከሼህ ሳሂብ ጋር በማዕከላዊ በቆየሁባቸው ሁለት ሳምንታት በምን እንደታሰረና አላማው ምን እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ። ከቁርአን ትምህርት ውጪ ሌላ ትምህርት አልተማረም፤ መማር ለሱ ሀጥያት ነው። ጅማ ውስጥ ሚስትና ሶስት ልጆች አሉት። በእርሻ ላይ እንዳለ ፖሊሶች ሊይዙት ሲመጡ ለማምለጥ ቢሮጥም ጥይት ተኩሰው እንዳስቆሙትና ከተያዘም በኋላ ለማምለጥ በማስቸገሩ ጀርባው እስኪላጥ ድረስ እንደደበደቡት ጀርባውን ገልጦ ጠባሳውን አሳየኝ። ወደ ማእከላዊ ከገባም በኋላ በተለምዶነ‘ስምንት ቁጥር’ የሚባለው ቤት አንድ ሰው ብቻ የሚታሰርበት ክፍል ውስጥ ለሁለት ሳምንት እንዳቆዩትና ‘ምርመራም’ እንደጨረሰ በተኮላተፈው አማርኛ አስረዳኝ። እንደተግባባሁት ብዙ ታሪክ ከጀርባው እንዳለ ስላወኩ ጥያቄዎች አዘንብበት ነበር።

“ምርመራ ጨርሰሃል?”

“አዎ። ከገባሁ ሁለት ወር ሆኖኛል”

“በምን ጠርጥረው ነው የያዙህ?”

“በሽብር ነው። እስላማዊ መንግስት ልታቋቁም ነበር ነው የሚሉኝ።”

“አንተ እስላማዊ መንግስት ልታቋቁም ነበር?”

“አዎ። እኔ ምንም ወንጀል አልሰራሁም፣ ቁርአን ያዘዘኝን ነው ያረኩት።”

“እና ለመርማሪዎቹ ምን አልካቸው?”

“መሳርያ ይዘን ጫካ ለመግባት አላማ እንደነበረንና ይህን የምናረገው ኢትዮጵያ በሸርያ መተዳደር አለባት ብለን አስበን እንደሆነ ነው የነገርኳቸው።”

“አምነሃል ማለት ነው?”

“አዎ!”

“ደብድበውህ ነው ያመንከው?”

“የደበደቡኝማ መጀመሪያ ነው። ሲይዙኝ። እዚህ ከገባሁ በኋል ብዙ ልጆች ይደበደባሉ እኔን ግን አልደበደቡኝም”

“እዚህ ካመንክ እንደሚፈረድብህ ታውቃለህ አይደል? ብዙ ዓመት ነው የምትታሰረው።”

“አውቃለሁ። ግን መዋሸት አልፈለኩም። ይሄ ለእምነቴ የምከፍለው መስዋትነት ነው። አላህ ወደፊት ይከፍለኛል።”

“ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ህይማኖት ብቻ እንዲኖር ነው የምትፈልገው?”

“አዎ! እስልምና ብቻ ነው መኖር ያለበት፤ በመንግስት ሳይሆን በሸርያ ነው መተዳደር ያለብን”

“ሌላ  ሀይማኖት ያለው ሰው ታድያ ምን ልታደርጉት ነው?”

ይህን ጥያቄ ስጠይቀው ለመመለስ ትንሽ አቅማማ። በጣም ‘ዲፕሎማት’ በሆነ አነጋገር “ሙስሊም እንዲሆን ይደረጋል” አለኝ። ምን ማለት እንደሆነ ገብቶኛል። እሱ እና ግብር አበሮቹ ለዚህ ዓላማ ተግባራዊ መሆን ጅማ ጫካ ውስጥ ሲደክሙ የነበሩ ናቸው፡፡
ይህ ሰው ሁለት ሳምንት አብሮኝ ቆይቷል። ለኔ ክፉ አልነበረም፤ ተደብደቤ ስመጣ አሽቶኛል። ሐየማኖታችን ሳያግደን አብረን ከቤቴ የመጣውን ምግብ አብረን በልተናል። ምንም አይነት የቀለም ትምህርት አልወሰደም፡፡ በክርስትያን የተባረከ ምግብ ይበላል። ‘ለምን የክርስትዯን ስጋ ትበላለህ?’ ስለው “በአስቸጋሪ ሁኔታ ከሆንክ አይከለከልም” ይለኛል።

እኔንና ሼኽ ሳይብን ችግር በአንድ አልጋ ላይ እንድንተኛ አረገን እንጅ፤ ሰንቆት የነበረውንና ሊሰራው ሲዘጋጅ የነበረውን ድርጊት ሳስበው ይዘገንነኛል። ሼኽ ሳሂብ ድርጊቱን አምኖ እየተከራከረ ነው። ‘ፈጣሪ አዞኝ ነው ያደረኩት’ ብሎ ስለሚያምን “የጀነት” በር ወለል ብሎ እንደሚከፈትለት ያምናል። ከሼኽ ሳሂብ ጋር የነበረኝ የማዕከላዊ ቆይታ የበቃው በሁለት ሳምንት ውስጥ ነው። አንድ ቀን ጠዋት ኮተቱን ይዞ እንዲወጣ ተደረገና ‘ሸራተን’ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ወሰዱት። 

ሀምሌ 11፣ 2006 ዓለም ላይ ያሉ ወንጀሎች ተደፍድፈውብኝ ወደ ቂሊንጦ  እንድሄድ ከተደረኩ በኋላ ማዕከላዊ የማቀውን ሰው መፈለግ ጀመርኩ። ካገኝኋቸው ሰዎች መካከል ሸኽ ሳሂብ አንዱ ነው። በአንፃራዊነት የተሻለ ልብስ ለብሷል። “ኢስላማዊ መንግስት ልትመሰርት አስበሀል” ብለው በሽብርተኝነት ወንጀል እንደከሰሱት ነገረኝ። እኔም ከሱ እኩል መከሰሰ እየገረመኝ እሱ ከወጣ በኋላ ጨለማ ቤት ውስጥ ብዙ እንደቆየሁና ዱላቸውም ጠንክሮብኝ እንደነበር ነገርኩት። የደረሰብኝን ስነግረው አዘነልኝ። 

ቂሊንጦን ትንሽ ከተለማመድኩ በኋላ ግቢው ውስጥ ብቻዬን መንቀሳቀስ ጀመርኩ። አንድ ቀን አናት የሚተረትረውን የቂሊንጦ የስድስት ሰዓት ፀሀይ ሽሽት የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደሚሰግዱበት ቦታ ቁጭ አልኩኝ። ጥግ ላይ ወደ አራት የሚጠጉ ሙስሊሞች ይሰግዳሉ። ከመካከላቸው ሼህ ሳሂብ አለ። በቁጥር ማነሳቸው ገርሞኝል። ስግደት ከጨረሱ በኋላ ሸህ ሳሂብ ወደኔ መጣ።

“ዛሬ ምነው አነሳችሁ አልኩት?”

“እኛ ሁሌም እንደዚህ ነው የምንሰግደው።”

“ብቻችሁን?”

“አዎ”

“መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች አሉ አይደል እንዴ? ከነ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ጋር ለምን አትሰግዱም?” ስለው ጭንቅላቱን እየወዘወዘ “እነሱ ሙስሊሞች አይደሉም! ከነሱ ጋር መሆን አልፈልግም።” አለኝ። የሃይማኖት ነፃነት ይከበር በማለቱ የ22 ዓመት ፍርድ የተበየነበት (በኋላ ቢፈታም) ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በሼሕ ሳህብ አስተሳሰብ ሙስሊም አይደለም። ይህ ‘ጅሃዲስት’ ሰይፉን ሲስል የነበረው ለሙስሊሙም ለክርስትያኑም እንደነበር ገባኝ። 

አክራሪ፣ ፅንፈኛና አሸባሪ ተብለው እስር ቤት የተወረወሩት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በብዙ ‘ጅሃዲስቶች’ ይጠላሉ። ሙስሊሞች በጋራ በሚሰግዱበት ሰዓትም “ከክርስትያኖች ጋር አልሰግደም” የሚል ‘ጅሃዲስትም’ አለ። በሊቢያ በርሃ በአይሲስ አንገታቸው ስለተቀላ ኢትዮጵያውያን ሰምቶ አንጀቱ ቅቤ የጠጣ፣ “እሰይ!፣ አይሲስ እስላማዊ ያልሆነ ነገር ሲሰራ አላየሁትም” ያለ ‘ጅሃዲስትም’ አለ። ከንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር መታሰር ጭንቅላትን ይጎዳል። ከዚህ በባሰ ሁኔታ ግን ሕጉን በፈለገው መንገድ የሚጫወትበት መንግስት ትክክለኛ ጥያቄ “የእምነት ነፃነት ይከበር”  በማለት ያነሳውንና “አንድ ሀይማኖት ወይም ሞት” ብሎ ከንፁሃን አንገት በሚፈሰው ደም ለመፅደቅ ያሰበውን እኩል ይከሳል፣ እኩል ይፈርድባቸዋል። 

‘አቡሌ’ አብዱልከሪም


በዘላለም ክብረት

ረጅም ነው፡፡ ደረቱ ከልክ በላይ ሰፊ ነው፡፡ በደረቱ የጥይት እርሳስ አንጥሮ አንደሚመልስ በጉራ ሳቅ እያለ ይናገራል፡፡ ደረቱ ለምን እንደሰፋ ሲናገር ያለፈበትን ፈተና ያስተጋባል፡፡ ሸካራው እጁ እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ምን ቢሰራ ነው እንዲህ የጠነከረው? ያስብላል፡፡ እድሜውን በትክክል ባያውቀውም 29 ዓመቱ እንደሆነ ግን ይገምታል፡፡ አማርኛ መናገር ስለሚያስቸግረው ‘ተው ባክህ’ የሚል ሐረግ እዚህም እዚያም ጣል ያደርጋል፡፡ ሲናገር ፈገግታ ሁሌም ከፊቱ አይጠፋም፡፡ አፍንጫው በንግግሮቹ መሃል ይነፋል፡፡ የእጅ መሳሪያውና RPGው በአይኑ ላይ ውል ሲሉበት የመሳሪያ ድምፅ በአፉ እያወጣ፣ ጣቶቹን እንደ መሳሪያ ደቅኖ ትዝታውን ያስታምማል - አብዱልከሪም አብዱልሰመድ አብዱልቃድር፡፡

አብዱልከሪም የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ወታደር ነው፡፡ ቤሕነን አብዱልከሪም ደም ውስጥ ይራወጣል፡፡ ለብዙዎች የግንባሩ ስም አዲስ ቢሆንም ቤሕነን ግን ረጅም ታሪክ ያለው ሲሆን፤ ቤሕነንን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡም የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልልን የፖለቲካ ሁኔታ መረዳት አይቻልም፡፡

(ወታደራዊውን አምባገነን የደርግ መንግስት ለመጣል ወጣቶች ወደ ጫካ ገቡ፡፡ በኢሕአዴግ ቋንቋ ወታደራዊው መንግስት በወደቀበት ወቅት አስራ ሰባት የታጠቁ ሐይላት ራሳቸውን አስታጥቀው እየታገሉ ነበር፡፡ እንግዲህ ቤሕነን ከነዚህ አስራ ሰባት ድርጅቶች አንዱ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ስልጣን ይዞ በየክልሉ ስልጣን ለነዚህ አስራ ሰባት ድርጅቶች ማከፋፈል ጀመረ፡፡ ቤሕነንም የቀድሞው ክልል ስድስት፤ የአሁኑ ቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ደረሰው፡፡)

በ2002 በአንድ ሰበበኛ ቀን አብዱልከሪም ከጓደኞቹ ጋር በተለምዶ ‹የደማዚን እርሻ› እየተባለ ወደሚታወቀው የሱዳን እርሻ በቆሎ ለመሰብሰብ ይሄዳሉ፡፡ አብዱልከሪምና ጓደኞቹ ለጥቂት ቀናት በቆሎ ሲሰበስቡ ከቆዩ በኋላ ግን ሕይወት እንዳሰቡት አላዋለቻቸውም፡፡ ባላሳቡበት ቅጽበት ከየት መጡ ያላሏቸው የታጠቁ ሩጣና ቋንቋ ተናጋሪዎች (ሩጣና የበርታዎች ቋንቋ ነው) እሱንና ጓደኞቹን በመሳሪያ አስገድደው ወደ ሩቅና ወደማያውቁት ሐገር ሊወስዷቸው መኪና ላይ ጫኗቸው፡፡

(የደማዚን እርሻ (Al-Damazin Farms) ከኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገኝ እርሻ ሲሆን በርታዎች የደማዚን መሬት በሙሉ የበርታ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የደማዚን እርሻ በዓለማቀፍ ደረጃ ታዋቂነትትን ያተረፈ ቦታ ነው፡፡ ሟቹ የዓልቃዒዳ መሪ ኦሳማ ቢንላደን ከ1983 እስከ 1989 ድረስ ሱዳን በነበረበት ወቅት በባለቤትነት ያስተዳድረው የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ ቢንላደን የዓልቃኢዳ አባላትን በእርሻው ቦታ ያሰለጥንበት እንደነበረ ከታወቀ በኋላ የሱዳን መንግስት በደረሰበት ዓለማቀፍ ጫና ምክንያት ቢንላደንን ከሐገር ሲያባርር እርሻውን ደግሞ በመንግስት ቁጥጥር ስር አድርጎት ለረጅም ዓመታት ቆይቷል፡፡ በቅርቡ የግብፅ መንግስት ከዚሁ መሬት ላይ ‘ጥጥና ሱፍ አለማበታለሁ’ በማለት ሰፊ መሬት ወስዷል)

ከሶስት ቀናት አድካሚ ጉዞ በኋላ አብዱልከሪም እና ጓደኞቹ የማያውቁት በተራሮች የተከበበ በርሃማ ቦታ ላይ ወረዱ፡፡ በወቅቱ ግራ የተጋባው አብዱልከሪም ይህ ቦታ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት መኖሪያው እንደሚሆን በወቅቱ መገመት አልቻለም፡፡ ትንሽ እንዳረፉ ግን ስለ ቦታው ምንነትና እነሱ ለምን ወደቦታው እንዲመጡ እንደተደረጉ ገለጻ ተደረገላቸው፡፡ ያሉት በኤርትራ መሬት ላይ ሲሆን አሁን ያሉበት ቦታ ልዩ ስሙ ‘ሀሬና’ እንደሚባልና ከኢትዮጵያና ከሱዳን ድንበር እጅግ ቅርብ በሆነ አቀማመጥ ላይ የሚገኝ ቦታ እንደሆነም በተጨማሪ ተገለጻላቸው፡፡ ወደዚህ ቦታ እንዲመጡ የተደረጉትም የቤኒሻንጉል ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና በመቃወም ዳግም ወደ ጫካ የተመለሰውን የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) እንዲቀላቀሉ ታስቦ መሆኑን ተነገራቸው፡፡ ነገር ግን ከሶስተኛ ክፍል ያልዘለለ መደበኛ ትምሀርት ላልተማረው አብዱልከሪም በወቅቱ የተሰጠው ምክንያት ብዙም የሚገባው አልነበረም፡፡

(ቤሕነን ቤኒሻጉልን ለአምስት ዓመታት ከ1984 – 1988 ካስተዳደረ በኋላ፤ በ1988 ‘የታምራት ላይኔ መፈንቅለ መንግስት’ ብለን ልንጠራው በምንችለው ሂደት ኢሕአዴግ ‘አልተመቸኝም’ ያለውን በበርታዎች የበላይነት ሲመራ የነበረውን የክልሉን መንግስት ‘የአሶሳ ልጆች’ ከ ‘መንጌ ልጆች’፣ ‘የደጃዝማች ሸህ ሆጀሌ ቤተሰቦች’ ከ ‘የደጃዝማች ሙስጠፋ ቤተሰቦች’ በሚል በርታዎችን ከሁለት ከፍሎ አቶ ታምራት ላይኔ በመሩት ስብሰባ የጉምዞች የበላይነት የሰፈነበት መንግስት አቋቋመ፡፡ ፍክክሩንም “በርታዎች ከጉምዞች” የሚል አዲስ መልክ አስያዘው፡፡ ቤሕነንም ከአምስት ዓመታት ረፍት በኋላ በድጋሚ መሳሪያውን አንስቶ ጫካ ገባ፡፡)

ከዛን ጊዜ ጀምሮ አብዱልከሪም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀሬናን ጨምሮ በምዕራብ የኤርትራ በርሃዎች በየቀኑ የፕሮፓጋንዳ ትምህርትና ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰደ ከሌሎች ተዋጊ ቡድኖች ጋር ተቀራርበው እንደኖሩ ፈገግ እያለ ያስታውሳል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ አብዱልከሪም ለምን ታፍኖ ወደ ኤርትራ በርሃ እንደተወሰደ ይረዳል፡፡ አሁን የቤኒሻንጉል ሕዝብ ጥያቄም ለርሱ ግልፅ ነው፡፡ እንዲያውም ጥያቄውን በራሱ ቋንቋ በሩጣንኛና በአረብኛ በደንብ እንደሚተነትን ይናገራል፡፡ 

ከአምስት ዓመታት የበርሃ ስልጠና በኋላ አብዱልከሪምና ሌሎች ዘጠኝ ጓደኞቹ (ከዘጠኙ መካከል አብዱ ሐሚዝና ኢሳቅ ኢብራሒም የ16 እና የ17 ዓመት ልጆች ናቸው) ወደ ቤኒሻንጉል ተመልስው ገጠር በመግባት ሕዝቡን በፍትህና በዴሞክራሲ ጥያቄዎች ላይ ትምህርት እንዲሰጡ፤ ችግር ካጋጠማቸውም እንዲዋጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው በመጋቢት 2007 ከአድካሚና ረጅም ጉዞ በኋላ የቤኒሻንጉል ምድር ደረሱ፡፡ ነገር ግን ነገሮች እንዳሰቧቸው ቀላል አልሆኑም፡፡ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር በተደረገ አጭር የተኩስ ልውውጥ አንድ ጓደኛቸው ቢሞትባቸውም ከተኩስ ልውውጡ ይልቅ ፈተና የሆነችባቸው ግን ተፈጥሮ ነበረች፡፡ ውሃ ተጠሙ፡፡ ጫካ ውስጥ ያገኙትን ‘ውሃ ነገር’ ሁሉ ቢጠጡም የተፈጥሮ ጥያቄያቸውን መመለስ ግን አልቻሉም፡፡ ለዚህም መፍትሔ ሆኖ የታያቸው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ትጥቃቸውን ሁሉ ጫካ ውስጥ ደብቀው ሱዳን ውስጥ የሚገኝ በአቅራቢያቸው ያለ አንድ መንደር ውስጥ ውሃ ለመጠጣት መሔድ፡፡ ሐሳባቸውን ተግባራዊ አድርገውም ኩርሙክ አጠገብ የምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ውሃ አግኝተው እየጠጡ-እየተጫወቱ እያለ በድንገት ከየት መጡ ያላሏቸው የሱዳን ወታደሮች ከበቧቸው፡፡ ተያዙ፡፡ ወዲያው ለኢትዮጵያ ወታደሮች ተላልፈው ተሰጡ፡፡ 

(በ1988 ኢትዮጵያና ኤርትራ እፍ ያለ ፍቅር ውስጥ ነበሩ፡፡ ኤርትራ ሎዓላዊነቷ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሱዳን ጋር ፀብ ውስጥ ገባች፡፡ በወቅቱ በፀቡ ላይ ገለልተኝነት እንዲያሳይ በሱዳን መንግስት በጥብቅ ሲጠየቅ የነበረው ኢሕአዴግ በግልፅ የኤርትራ ወገንተኛ መሆኑን በማወጁ የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት እጅጉን ሻክሮ ነበር፡፡ ከዚህ ጋርና በደቡብ ሱዳን ከነበረው ሁኔታ ጋር ተያይዞም በቤኒሻንጉል በኩል በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የድንበር እሰጣ-ገባ ተነሳ፡፡ በወቅቱ በኢሕአዴግ አቋም የተበሳጩት ፕሬዘደንት ኦማር አልበሽር “ሰራዊታችን በሁሉም መልኩ ዝግጅቱን አጠናቆ የትግሬ ወታደሮችን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ እየጠበቀ ይገኛል” በማለት ሕወሃትን ብቻ ነጥለው መዛታቸውም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ አልበሽር በሱዳኑ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው “በአላህ ፈቃድ ዝም አንልም፡፡ አስመራ፣ አዲስ አበባና ካምፓላ ላሉት ተንኳሽ መንግስታት መልስ አንሰጣለን፡፡ ለተቃዋሚዎቻቸውም መሳሪያ እናስታጥቃለን፡፡” ብለውም ነበር፡፡ አሁን አልበሽር ከኢሕአዴግ ጋር ፍቅር በፍቅር ሆነው ያማራቸውን የውጭ ጉዞ ጥማት አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ አሶሳ፣ መቐለ … እየተመላለሱ እየቆረጡ ነው፡፡ እንደ አብዱልከሪም ያሉትን የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎችን ከሃያ ዓመታት በፊት አስታጥቃለው ካሉት ቃላቸው በተቃራኒው ይዘው ለኢሕአዴግ እያስረከቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የኤርትራን ኤርትራ ደግሞ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች እያሰለጠኑ ጸባቸውን አክርረው ቀጥለዋል፡፡)

አብዱልከሪምና ጓደኞቹ በተያዙበት ወቅት መጀመሪያ የተወሰዱት ወደ አሶሳ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ነው፡፡ በማታ ወደ ካምፑ ታስረው የገቡት እነአብዱልከሪም በሰራዊቱ አባላት አሰቃቂ ድብደባ የተፈፀመባቸው ሲሆን፤ በፌሮ ብረት ውሃ ላይ ሲደበደብ እንደቆየ የሚናገረው አብዱልከሪም በተያዙበት እለት ሌሊቱን ሙሉ አብዱልከሪም ብቻ ‘አንተ ነህ መሪው’ በሚል መነሻ በተለምዶ ‘ሒሊኮፍተር’ እየተባለ የሚጠራውን የግርፋት አይነት እንደሚገፈፍ በግ ተሰቅሎ ሲገረፍ እንዳደረ ይናገራል፡፡ ዝናብ ሌሊቱን ሙሉ እየዘነበበት ዛፍ ላይ በሒሊኮፍተር ቅርፅ ተሰቅሎ ሲሽከረከር ያደረው አብዱልከሪም ከስምንት ሰዓታት ስቅላት በኋላ መሬት ሲወርድ እጆቹ ሁሉ መንቀሳቀስ አቅቷቸው እንደነበር ሲያስታውስ ፊቱ ላይ ሐዘን ይታያል፡፡

(‘ሒሊኮፍተር’ የተባለው የማሰቃያ ዘዴ (Torture Method) በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ የገነነ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኤርትራ ዜጎቿን በዚህ አይነት የማሰቃያ ዘዴ እንደምታሰቃይ በተደጋጋሚ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያም በተለይም ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በዚህ የስቃይ አይነት ዜጎችን እንደምታሰቃይ አብዱልከሪምና መሰሎቹ ምስክሮች ናቸው፡፡)

አብዱልከሪምና ጓደኞቹ በግንቦት አጋማሽ 2006 ነበር ወደ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) የመጡት፡፡ በዛን ወቅት አብዱልከሪም እኔ ያለሁበት ክፍል ውስጥ (በተለምዶ ሳይቤሪያ 5 ቁጥር የሚባል ክፍል) ተመድቦ የመጣ ጊዜ በባዶ እግሩ በጣም የተዳከመ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ የገባ ሰሞን በጣም እንቅልፍ ይተኛ ነበር፡፡ እጅግ በጣም አድካሚ መከራና ስቃይ አልፎ እንደመጣም ያስታውቃል፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ማዕከላዊ ምንም እንኳን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ታሪኩን ደጋግሞ ቢነግራቸውም “የሕዳሴውን ግድብ ልናጠቃ ተልዕኮ ተሰጥቶን ነበር በማለት እመን፤ አመጣጣችሁን ዋሽተኸናል” እያሉ በየቀኑ ‘መርማሪ ፖሊሶቹ’ ይገርፉት ነበር፡፡ አብዱልከሪም ‘ለምርመራ’ ተጠርቶ ተደብድቦ ሲመጣ ድካሙ ስለሚብስበት ይተኛ ነበር፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነበር በጊዜው የነበረው፡፡ አንድ ቀን ማዕከላዊ ከጓደኞቹ ጋር ተጠርቶ ሲመለስ ‘ምን አሉህ?’ አልነው፤ እሱም ‘መሳሪያችን ከፊታችን አስቀምጠው ፎቶ አነሱን’ አለን፡፡ ለካ በቴሌቪዥን ካሜራ ቀርጸዋቸው በማታው የቴሌቪዥን ዜና ‘አስር አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ’ የሚል ዜና ተላልፎ ነበር፡፡ አብዱልከሪም ‘በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረሃል’ የሚለው ነገር ለረዥም ጊዜ ምን ማለት እንደሆነ አይገባውም ነበር፡፡ ‘ምንድን ነው ሽብርተኝነት?’ ይላል ሁሌ፡፡ ‘አሸባሪ እኔ እሆናለሁ እንዴ?’ እያለም ፈገግ ማለት የዕየለት ደንቡ ነበር፡፡ አያይዞም ‘እኔ ልማት የለም፣ ዴሞክራሲ የለም ብየ ለቤኒሻንጉል የታገልኩ ታጋይ ነኝ እንጅ አሸባሪ አይደለሁም’ ይላል በሚያስቸግረው አማርኛ፡፡ ፍርድ ቤት ቀርበው የሃያ ስምንት ቀን ቀጠሮ ሲሰጥ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት እጅግ ይቸግረው ነበር፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ያለአስተርጓሚ ስለነበር የሚቀርቡት ዳኛዋ ምን ትዕዛዝ እንደሰጠች እንኳን ማወቅ ሳይችሉ ይመለሱ ነበር አብዱልከሪምና ጓደኞቹ፡፡

(የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከሚታወቁት ሰላማዊ ግለሰቦችን ለማጥቂያ መሳሪያ ከመሆኑ ባሻገር፤ በዋናነት ሰለባ ያደረጋቸው የተለያዩ ብረት ያነሱ ኃይሎችን መሆኑ ክሶቹን ተመልክቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ የሕጉ ሰለባ ግለሰቦች አማርኛ ቋንቋ የማይናገሩ መሆናቸው ሕጉም ሆነ ክሳቸው ምን ማለት እንደሆነ ሳይገነዘቡ ለረጅም ዓመታት እስር መዳረጋቸው ደግሞ አሳዛኙ እውነታ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በአስተርጓሚ እጦት የሚቸገሩ ከመሆናቸውም ባለፈ ባብዛኛው አስተርጓሚ የሚባሉት ራሳቸው ‘መርማሪ ፖሊሶቹ’ ስለሚሆኑ እንደአብዱልከሪም ላሉ ተከሳሾች ጥላቻና ንቀት ያላቸው ናቸው፡፡)

እኔ መደበኛ ክስ ተመስርቶብኝ ወደ አዲስ አበባ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት (ቂሊንጦ) በሔድኩበት ወቅት አብዱልከሪም ምርመራ ጨርሶ የነበረ ቢሆንም ከቤኒሻጉል ተይዘው በመጡ አዲስ ተከሳሾች ምክንያት ዱላውና ድብደባው በአዲስ መልክ በርትቶበት ነበር፡፡ በጥቅምት 2007 ላይ አብዱልከሪም ከጓደኛው ፈተልሙላ አጣሂር ጋር እኔ ወዳለሁበት ቂሊንጦ ዞን አንድ ተመደበ እና በአጋጣሚ አንድ ቤት (ዞን አንድ፣ አንደኛ ቤት) አብረን ሆንን፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ማታ ማታ ሁሌ ብዙ ነገር እናወራ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን አዝኖ ቤተሰብም ሆነ ጠያቂ ስለሌለው ራሱን በትንሽ ገንዘብ (በወር 60 ብር) ለመደጎም የጀመረውን ለእስረኞች ወጥ የማመላለስ ስራ ፖሊሶች እንደከለከሉት ነገረኝ፡፡ ‘ለምን?’ ብየ ስጠይቀው ‘እነዚህ ጥቋቁር ልጆች ምንም ስራ እንዳይሰሩ፤ አሸባሪዎች ናቸው’ ብሎ አንድ ፖሊስ ከለከለኝ አለኝ፡፡ ልብን ይሰብራል፡፡ ከመከልከሉ ይልቅ የተከለከለበት ምክንያት ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ከዚህ የፖሊሶቹ ተግባር ባለፈ ረዘም ያሉና የቆዳ ቀለማቸው ጠቆር ያሉ ሰዎች ሁሉ የጋምቤላ ተወላጆች ለሚመስሉት አብዛኛው እስረኛ አብዱልከሪምን ‘ኡጁሉ’ እያለ የሚጠራው የነበረ ሲሆን፡፡ ገራገሩ አብዱልከሪም ግን ‘እኔ በርታ ነኝ፤ ምንድነው ኡጁሉ?’ እያለ ፈገግ ከማለት ውጭ አይከፋውም ነበር፡፡

(የቆዳ ቀለምን መሰረት አድርጎ የሚደረገው ፍረጃና ማግለል፤ በተለይም በጋምቤላ እና በቤኒሻጉል ክልሎች ላሉ የፖለቲካ ቡድኖች አንዱ የተቃውሟቸው መሰረት ነው፡፡ ቤሕነን በርታዎችን በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ከምትገፋ ኢትዮጵያ የራሱን ሀገር መመስረት እንደሚመርጥ በፕሮግራሙ የገለጸ ሲሆን፤ ይሄም መጀመሪያ በርታዎች ከቤኒሻንጉል ክልል ተነጥለው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ በሕገ መንግስት አንቀጽ 47 መሰረት የራሳቸውን ክልል ለማቋቋም ከጠየቁት ጥያቄ አንድ ርምጃ ወደፊት የሔደ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት ጥፋተኛ ተብለው ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዘደንት አቶ ኦኬሎ አኳይ ጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋዴን) የተባለ ተገንጣይ (secessionist) ፓርቲ ያቋቋሙበትን ምክንያት ሲያስረዱ “በአኝዋኮች ላይ ከሚደረገው የዘር ማጥፋት በላይ ‘ለማ’ እና ‘አዲስ ጎማ’ እተባልን በቆዳ ቀለማችን ምክንያት የምንገፋበት ሃገር ውስጥ መኖር አስፈላጊ አይደለም” በማለት ይገልጻሉ)

አንድ ቀን አብዱልከሪም አማርኛ ለማንበብ እየሞከረ ነበርና “‘ሕገ መንግስት’ የሚባለውን ‘ኪታብ’ ስጠኝ” ብሎኝ ሰጠሁት፡፡ እሱም ምንነቱን አይቶ ስለቤኒሻንጉል የሚያወራውን አንቀጽ እንዳሳየው ጠይቆኝ አንቀጽ 47/1/6 ላይ ከዘጠኙ ክልሎች አንዱ የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መሆኑን የሚጠቅሰውን ክፍል ሳሳየው ተገርሞ ‘እንዴት ጉሙዝ ይባላል? የቤኒሻንጉል ሕዝብ አንድ ነው እነሱ ለምን ጉሙዝን ለብቻ ሕገ መንግስት ላይ ይጽፋሉ?’ እያለ ተበሳጨ፡፡ እኔ ‘ሁለቱ ይለያያል ብለው ነው ይሄን ያደረጉት’ ብለውም ሊያምን አልቻለም፡፡ በርሃ እያለ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ሁሉ አንድ መሆኑን በደንብ ተነግሮታል፡፡ የጉሙዝ ልጆች ከበርታ ልጆች ጋር አንድ ላይ ብረት አንስተውም ተመልክቷል፡፡ ‘ታዲያ ሕገ መንግስቱ ለምን ይለያየናል?’ ማለቱ እንግዲህ ከዚህ የራሱ እውነት የሚመነጭ ነው፡፡

(የቤኒሻንጉል ክልልን ፖለቲካ ያጠኑ ሊቃውንት ይሄ ‘ጉምዝ ከበርታ’ የሚለው ምንታዌ የፖለቲካ አሰላለፍ ኢሕአዴግ የለመደውን ሕዳጣንን በብዙኃን ላይ የማንገስ ዘይቤ ተቀጥላ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም አሰላለፍ ያመች ዘንድ በክልሉ የሚኖሩ አምስቱም ነባር (indigenous) ሕዝቦች (በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮሞ) የየራሳቸውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመሰርቱ ያደረገው ኢሕአዴግ አንዱን የአንዱ አለቃ በማድረግ ክልሉን በሩቅ መቆጣጠር ችሏል፡፡)

አብዱልከሪም የምርጫ 2007 የፓርቲዎች የቴሌቪዥን ክርክርን እያየ ‘ወላሂ ሽማግሌው ጎበዝ’ ነው ይላል ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲናገሩ ከት ብሎ እየሳቀ፡፡ መረራ የሕዝቡን ችግር ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ መንገራቸው ነው ለአብዱልከሪምና መሰሎቹ መረራን እንዲወዱ ያደረጋቸው፡፡ ቤኒሻንጉልን የተመለከተ ዜና ሲመለከት ልቡ የሚሰቀለው አብዱልከሪም፤ የሕዳሴው ግድብ ለቤኒሻንጉል ሕዝብ ምን ጥቅም እንደሚሰጠው ብዙም አይገባውም፡፡ ‘ልማት ማፍረስ የቤሕነን አላማ አይደለም’ የሚለው አብዱልከሪም ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር የሚባለው ነገር አይገባውም፡፡ ‘እውነትን ብቻ መናገር ያስፈልጋል’ የሚለው አብዱልከሪም ‘መከራከር በመሳሪያ ነው’ ብሎ ያምን እንደነበር እየሳቀ ይናገራል፡፡ ‘አዎ እኔ የቤሕነን ወታደር ነኝ፤ ለልማትና ዴሞክራሲ ታግያለሁ፤ ልማት ላጠፋ ግን አልመጣሁም’ ብሎ ውሸት በማያውቀው አንደበቱ ንጽህናው ተናግሯል፡፡ ከሳሹ ግን ‘አይ ግድቡንም ሊያጠቁ ነበር’ ብሎ ከመካከላቸው ያስቀረውን ጓደኛቸውን ለምስክርነት አቅርቦባቸዋል፡፡ ነገር ግን ውሸትን ከሚጸየፉት የበርታ ልጆች አንዱ የሆነው የከሳሽ ምስክር ‘እኛ ግድብ ልናፈርስ አልመጣንም’ በማለት መስክሮ የነአብዱልከሪምን እውነት አረጋግጧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁሉንም ተከሳሾች በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀጽ 7/1 መሰረት ጥፋተኛ በማለት የአራት ዓመታት ጽኑ አስራት በሰኔ ወር 2007 መጀመሪያ ላይ ፈርዶባቸዋል፡፡

አብዱልከሪም ተፈርዶባቸው የተመለሱ እለት አራት ዓመት ማለት ምን እንደሆነ በቅጡ አልተረዳውም፡፡ ሁሌም የማይለየውን ፈገግታው ፊቱ ላይ ብትን አድርጎ ‘አቡሌ አይዞህ’ ይለኛል እኔኑ፡፡ ‘አቡሌ’ ማለት በበርታ ቋንቋ ‘ጓደኛዬ’ ማለት እንደሆነ ስንቴ ነግሮኛል? አብዱልከሪምን ሲፈታ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ በጠየኩት ቁጥር ‘አሁን ረፍት ያስፈልጋል’ ይለኛል፡፡ ቤኒሻንጉል ውስጥ ወደ ትውልድ ቦታው ‘ቁቆ’ ተመልሶ በልጅነቱ ይወዳት የነበረችውን ‘ለይላ’ የምትባል ወዳጁን አግብቶ ማረስ እንደሚፈልግና ከዛ ትምህርት መማር እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ይነግረኝ ነበር፡፡ ከእርሻ ቦታ ታፍኖ ወደ ጦር ካምፕ የተወሰደው አብዱልከሪም እናቱን ከተለያቸው ስምንት ዓመታት እንደሆኑ እየገለጸ በሕይወት መኖራቸውን እንኳን እንደማያውቅና ሲፈታ ግን እንደሚያገኛቸው ተስፋ አለው፡፡ ተወዳጁ ጓደኛዬ አብዱልከሪም ከታሰረ ሁለተኛ ዓመቱ ሲሆን፤ ወደ በርሃማው ‘የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት’ ከሔደ ደግሞ አንደኛ ዓመቱ፡፡  

Wednesday, April 6, 2016

ኢትዮጵያና የአስር ዓመታት የኢንተርኔት አፈና

በአጥናፉ ብርሃኔና በዘላለም ክብረት

ሐሙስ ጠዋት ግንቦት 10፣ 1998 መንግስታዊው የቴሌኮም ድርጅት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ በጊዜው አሉኝ ካላቸው አንድ መቶ አስራ ሶስት ሽህ የኢንተርኔት ደንበኞቹ መካከል ጥቂቶቹ ከምርጫ 97 ማግስት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በተወሰደው አፈና ምክንያት አማራጭ እየሆኑ ከመጡት ጥቂት ጦማሮችና የዜና ድረ ገፆች ላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለማየት ከኮምፒውተሮቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ቢሞክሩም አብዛኞቹ ሊሰሩላቸው አልተቻላቸውም ነበር፡፡ በጊዜው  በአንድ ሌሊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ከተዘጉት አስር ገደማ ጦማሮችና ድረ ገፆች መካከል አንዱ የሆነው ሰምና ወርቅ ጦማር ግንቦት 09፣ 1998 አመሻሹ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ሰምና ወርቅ ጦማርን ጨምሮ ሌሎች ጦማሮችንና ድረ ገፆችን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረጉን ገልፆ ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከአስር ዓመታት በኋላ አያንቱ የተባለውና የኦሮሞ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚፅፈው ድረ ገፅ የካቲት 24፣ 2008 ባወጣው ፅሁፍ ምንም እንኳ እየጨመረ የመጣውን የአንባቢዎቹን ቁጥር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ አቅሙን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ከየካቲት 23፣ 2008 ጀምሮ ድረ ገፁ በኢትዮጵያ ውስጥ በድጋሚ እንዳይታይ መታገዱን ዘግቦ ፅፏል፡፡

የኢንተርኔት አፈናው (Internet Censorship) ከተጀመረ አስር ዓመታት ቢያስቆጥርም ትናንት ዛሬን፣ ዛሬ ደግሞ ትናንትን በእጅጉ ይመስላሉ፡፡

የአፈናው አፍሪካዊ ፈር ቀዳጅ

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓለም ጭራ ሀገራት አንዷ እንደሆነች ዓለማቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (International Telecommunication Union) በየዓመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት ብቻ በመመልከት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሃያ አመታት ውስጥ ከሶስት በመቶ በላይ መሔድ ያልቻለው የኢትዮጵያዊያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ሀገሪቱ በዚህ ዘርፍ ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ የሚገልፅም ነው፡፡

ምንጭ፡ ዓለማቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (International Telecommunication Union)
ነገር ግን በዚህ ትንሽ የተጠቃሚዎች ቁጥር ላይ ያለው ቁጥጥርና ክልከላ ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የበለጠ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ከአስር ዓመታት በፊት በግንቦት 1998 የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ አመለካከታቸውን ያልወደዳቸውን ድረ ገፆች በሀገር ውስጥ እንዳይታዩ በማገድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የመጀመሪያዋ የኢንተርኔት አፋኝ ሀገር  ያደረጋት ሲሆን፤ ዓለም ላይ ደግሞ ከቻይና እና ከሳኡዲ አረቢያ ቀጥሎ በሶስተኝነት የኢንተርኔት አፈናን በመጀመር የአፈናው ፈር ቀዳጅ ሁኗል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ሚንስትር የነበሩት አቶ ብርሃነ ሐይሉ  ሰጡት መልስ ‹በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታይ የተደረገ ምንም አይነት ድረ ገፅም ሆነ ጦማር የለም› የሚል ሲሆን፤ ይሄም ከእውነታው ጋር በግልፅ የሚጋጭ ነበር፡፡

ድረ ገፆቹ ለምን ይታፈናሉ?

የተለያዩ ሃገራት በተለያዩ ምክንያቶች አንዳንድ ድረ ገፆች በሀገራቸው እንዳይታዩ ያደርጋሉ፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥም ሐይማኖታዊና ግብረ ገባዊ ምክንያቶች (religious and moral reasons) የብዙ ሀገራት መነሻዎች ሆነው ይታያሉ፡፡ ሀገራት ‹አንድ ድረ ገፅ ሐይማኖቶችን ያጎድፋል፤ የሕብረተሰቡን ስነ ምግባር ደንብም ያውካል› በሚሉ ምክንያቶች የተለያዩ ድረ ገፆች በሀገራቸው ዜጎች እንዳይታዩ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ጥቂት አምባገነን መንግስታት በፖለቲካዊ ምክንያት የተቃውሞ ድምፀት ያላቸውን ድረ ገፆች በሃገራቸው ዜጎች እንዳይታዩ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ድረ ገፆቹን ለመዝጋት ምንም ያስቀመጠው ግልፅ ፖሊሲ ካለመኖሩም ሌላ በግልፅ የሚታወቀውን የኢንተርኔት አፈና የለም በማለት ሁሌም ይክዳል፡፡ ነገር ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆችን ጦማሮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ መደረጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፖለቲካ ቀመስ ድረ ገፅ   ሳይበር  ኢትዮጵያን ከሌሎች ዘጠኝ ድረ ገፆች ጋር ግንቦት 09/1998 በኢትዮጵያ እንዳይታዩ በማድረግ በየተጀመረው አፈና እያደገ መጥቶ ማንኛውንም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚዘግብ ድረ ገፅ እስከ መዝጋት ድረስ ሂዷል፡፡ አፈናው ጣራ በነካበት  2005 በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን (የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ድረ ገፆች ተዘግተው የነበረ መሆኑን ልብ ይሏል) ድረ ገፆች ሳይቀር በሃገር ውስጥ እንዳይታዩ በማድረግ አይን ያወጣ አፈና ይካሄድ ነበር፡፡

ከዚህም ተነስተን በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ዋነኛ የኢንተርኔት አፈና የሚያተኩረው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ድረ ገፆች፣ ጦማሮች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አድራሻዎች ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ ይሄም በዋናነት መሰረት የሚያደርገው ዜጎች አማራጭ ሃሳቦችን እንዳይሰሙ በማድረግ እና የፖለቲካ ትርክቱን መቆጣጠርን ነው፡፡ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ ተቋማትም ‹የአፈናው ዋነኛ መገለጫ ፖለቲካ ነው› በማለት በየዓመቱ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ይገልፃሉ፡፡


የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊዎች መጋቢት 27/2008 ባደረግነው ሙከራ ከላይ በምስሉ ለናሙና የተመለከቱትን http://aayyantuu.comhttp://ethsat.comhttp://gadaa.com እና http://zehabesha.com ጨምሮ ሌሎች ብዙ ድረ ገፆችን ጦማሮች በአዲስ መልክ በመዝጋት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ መደረጋቸውን ለመገንዘብ ችለናል
ነገር ግን አፈናዎቹ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ኢላማ ማድረጋቸው ደግሞ የአፈናው ሌላው ገፅታ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ድረ ገፆች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ በተደረገበት በግንቦት 1998 የአፈናው ዋነኛ ዓላማ የምርጫ 97 የፖለቲካ ትኩሳት ላይ ውሃ መቸለስ መሆኑ ግልፅ ነበር፡፡ አፈናው ለአምስት ዓመታት ብዙም ለውጥ ሳያሳይ ቀጥሎ በአረቡ ዓለም አቢዮት ማግስት ግን እጅግ በተጠናከረና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ባካተተ መልኩ በ2004 እና በ2005 በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆችንና ጦማሮችን በማፈን ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ ይሄም እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስት ተመሳሳይ የለውጥ እንቅስቃሴ ይደረጋል የሚል ስጋት ይዞት እንደነበር ያሳያል፡፡

ምርጫ 2007 መዳረሻ ላይም እንዲሁ ድረ ገፆቹና የጦማሮቹ አፈና ከፍ ብሎ እንደነበር ጉዳዩን በቅርቡ የሚከታተሉ ዓለማቀፍ ተቋማት ዘግበውት ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ከሕዳር ወር የጀመረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ አስመልክቶ የተለያዩ ድረ ገፆችን በኢትዮጵያ እንዳይታዩ ከመደረጋቸውም በላይ፤ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊዎች በምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ተንቀሳቅሰን ለማረጋገጥ እንደቻልነው ባለፉት አራት ሳምንታት ውስጥ ይሄ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ውስጥ መተግበሪያዎችን (Applications) ተጠቅሞ ድረ ገፆችን መጎብኝት እንዳይቻል ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም መጋቢት 21 እና 22/2008 ምሽት በመላው ሀገሪቱ ለተከታታይ አስር ሰዓታት እነዚህ መተግበሪያዎች ተጠቅሞ ድረ ገፆችን መጎብኝት አይቻልም ነበር፡፡ ይሄም የኢንተርኔት አፈናው እያደገ እና በቴክኖሎጅም በእጅጉ እየተራቀቀ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ከዚህ ተነስተን የምንደርስበት ድምዳሜም በኢትዮጵያ ያለው መንግስት መሬት ላይ ያለን ማንኛውንም አይነት የፖለቲካ ትኩሳት ለማዳፈን ሲባል የመረጃ ስርጭትን መገደብን እንደ ውጤታማ አካሔድ እየተጠቀመበት እንደሆነ ነው፡፡

ድረ ገፆቹን ማን ነው የሚዘጋቸው?

አስር ዓመታት ያስቆጠረው የኢንተርኔት አፈና እጅግ እየጠነከረና የተለያዩ ሰበቦችን እየያዘ ቀጥሏል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስት ይሄን ግልፅ አፈና እንኳን ለማመን አይፈልግም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡትም ምላሽ ‹ቴክኒካል ችግር ሊሆን ይችላል እንጂ እኛ አልዘጋንም› የሚል ነው፡፡ ግልፅ የኢንተርኔት የሳንሱር ፖሊሲ በሌለበት (በመስከረም 2004 ወጣው ‹የኢፌዴሪ ሃገራዊ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ፖሊሲ› በጉዳዩ ላይ ምንም የሚለው ነገር የለም) ሁኔታ ድረ ገፆቹና ጦማሮቹ በሀገር ውስጥ እንዳይታዩ የሚያደርጋቸው አካል ይሄ ነው ብሎ ለመደምደም ቢከብድም ያሉትን የሕግ ማዕቀፎች እና አንዳንድ ተግባራትን ተመልክተን ግን ለእርግጠኝነት የቀረበ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡

የኢትዮጵያን የኢንተርኔት አፈና ገና ከጅምሩ ጀምሮ ሲከታተሉ የነበሩ ዓለማቀፍ ተቋማት አፈናውን የሶስት ተቋማት ተግባር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ አፈናውን የሚመራው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ሲሆን፣ በሃገሪቱ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ደግሞ የአፈናው ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ተቋማት ጉዳዩ ዋነኛ ተጠያቂ ተጠሪነቱን በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረገው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ኢትዮጵያ ድረ ገፆችን ማፈን ከጀመረችበት ግንቦት 1998 ስድስት ወራት በኋላ በሕዳር 1999 የተቋቋመው ኢመደኤ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢንተርኔት የመረጃ ፍሰት የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶትና ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 130/1999 ተመስርቷል፡፡ ኢመደኤ በተመሰረተበት ደንብ መሰረት ዓላማው ‹ … ሀገሪቱ የኢንፎርሜሽንና የኢንፎርሜሽን መረብ ቴክኖሎጅንና ቴሌኮሙኒኬሽንን ለብሄራዊ ደህንነቷ ስጋት ሳያስከትል የሰላም የዴሞክራሲና የልማት መርሃ ግብሮቿን ተግባራዊ ለማድረግ እንድትጠቀምበት ማስቻል … ›  እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህ ዓላማ ከለላ ስር ሆኖም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የተቃውሞ ድምፀት ያላቸውን ድረ ገፆች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ 

ኢመደኤ የአረቡ ዓለም አብዮት በተፋፋመበት ወቅት በነሃሴ 2003 በድጋሚ በደንብ ቁጥር 250/2003 በመመስረቻ ደንቡ አለው ከተባለው ዓላማ በተጨማሪ ‹በሀገሪቱ ጥቅሞች ላይ የሚሰነዘሩ የኢንፎርሜሽን ጥቃቶችን መከላከልና አፀፋዊ ምላሽ መስጠት› የሚል አላማ ደርቦ በድጋሚ ተመስርቷል፡፡ በዚህ ወቅት ኢመደኤ ከአረቡ ዓለም አብዮት ጋር በተያያዘ ዘገባ የሚሰሩ ዓለማቀፍ የዜና ተቋማትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆችንና ጦማሮችን እንዲሁም የማህበራዊ ድረ ገፅ አድራሻዎችን በፀና ሁኔታ (aggressively) በኢትዮጵያ እንዳይታዩ እገዳ ማድረግ ችሏል፡፡ ይሄም ጊዜ መንግስት የኢንተርኔት ምህዳሩንየስልጣን ስጋቱ እንደሆነ የፈረጀበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢመደኤን በድጋሚ የመሰረተው ደንብም ኤጀንሲው ተግባሩን ሲፈፅም ማንኛውም አካል የመተባበር ግዴታ እንዳለበት ማስፈራሪያ አዘል አንቀፅን ጨምሮ የመጣ ሲሆን፤ የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትርም የአፈናው ተሳታፊነት ከዚህ የደንቡ ክፍል የመነጨ ይመስላል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 808/2006 በታህሳስ 2006 የተመሰረተው ኢመደኤ ስልጣኑን እጅግ አስፋፍቶ መጥቷል፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ የተመሰረተው ኢመደኤ ለየት የሚያደርገው ድረ ገፆችን ከማፈን ባለፈ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን የጥቃት ኢላማ አድርጎ አስፈሪ አካሔድ መጀመሩ ነው፡፡ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Without Borders) በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2013 ባወጣው ‹የኢንተርኔት ጠላቶች› (Enemies of the Internet) ሪፖርት፤ ዓለም ላይ ለኢንተርኔት ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው በማለት ከጠቀሳቸው አምስት ድርጅቶች ማለትም የእንግሊዙ Gamma Group፣ የጀርመኑ Trovicor፣ የጣሊያኑ Hacking Team፣ የፈረንሳዩ Amesys  እና የአሜሪካው Blue Coat System መካከል የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ (Gamma GroupTrovicor እና Hacking Team) ለኢመደኤ የተለያዩ የስለላ (surveillance) መሳሪያዎችን በማቅረብ ለአፈናው ዋነኛ ተባባሪዎች እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ተመልክቶ ነበር፡፡ ኢመደኤ በአሁኑ ወቅት ድረ ገፆችን ከመዝጋት ባለፈ እጁን አስረዝሞ የግለሰቦችን መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል አቅም ለመገንባት እጅግ ውድ የሆኑ መሳሪያዎችን እየሰበሰበ ይገኛል፡፡

ከዳታ ክልከላ ወደ ድምፅ እቀባ

የህንድ ትልቅ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ (Internet Service Provider) የሆነው ኤርቴል (Airtel) በታሕሳስ 2006 ደንበኞቹ እንደ Skype, WhatsApp, Viber, imo ወዘተ አገልግሎቶችን ኢንተርኔት ተጠቅመው ለሚያገኙት ማንኛውም የድምፅ አገልግሎት (Voice over Internet Protocol - VoIP) ተጨማሪ ክፍያ ማስከፈል በወራት ውስጥ እንደሚጀምር ገልፆ ነበር፡፡ ከመግለጫው በኋላ ግን የወርልደ ዋይድ ዌብ (World Wide Web) ፈጣሪ የሆነውን ቲም በርነርስ ሊን ጨምሮ ከመላው ዓለም ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ የተቃውሞው ዋነኛ መነሻም ‹የዚህ አይነት ተግባር የመረብ ገለልተኝነት መርህን (The Principle of Net Neutrality) የሚጥስ ነው› የሚል ነበር፡፡ የመረብ ገለልተኝነት (Net Neutrality) በተለያዩ ፀሃፍት የተለያየ ትርጉም የሚሰጠው ሲሆን ሁሉም የሚስማሙበት ግን ‹የኢንተርኔት አቅራቢዎች ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን አይነት አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ እቀባም ሆነ ለይተው ተጨማሪ ክፍያ ሊጠይቁ አይገባም፤ ገለልተኛ መሆን አለባቸው› የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ የህንድን የቴሌኮም አገልግሎት የሚያስተዳድረው ‘Telecom Regulatory Authority of India (TRAI)’፤ ይሄን የኤርቴል መግለጫ ተከትሎ ሕንዳዊያን በሃሳቡ ላይ እንዲወያዩ የውይይት ሰነዶችን ከበተነ በኋላ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተቃውሞ ኢሜሎችና የተለያዩ ዘመቻዎችን ተገንዝቦ ከሁለት ወራት በፊት ጥር 30፣2008 የመጨረሻ ሃሳቡን ‹ማንኛውም የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጭ ተቋም የመረጃ መረብ ገለልተኝነትን (Net Neutrality) በሚጋፋ መንገድ እቀባም ሊያደርግ አይችልም፤ ተጨማሪ ክፍያም መጠየቅ አይገባውም› በማለት ብዙሃኑን የሕንድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚያስፈነድቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ኢንተርኔት ካመጣቸው ፀጋዎች አንዱ የስልክ አገልግሎትን በርካሽ መልክ እንድንጠቀም ማድረጉ ነው፡፡ ይሄም መደበኛውን ለኢንተርኔት አገልግሎት የሚከፈል በአንፃሩ አነስተኛ ዋጋ በመክፈል የስልክና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማግኝት ያስችላል፡፡ አግልግሎቱ በተለምዶ ‹ኦቨር ዘ ቶፕ› (Over-the-top - OTT) አገልግሎት እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ዓላማውም የቆዩትን የመደበኛ ስልክ አሰራሮች የበለጠ ማቅለልና በርካሽ ዋጋ ማቅረብ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተመሳሳይ በ2004 የመጨረሻ ወራት የኢትዮጵያን ማህበራዊ ድረ ገፆችን አጣቦ የነበረው “ኢትዮጵያ አፋኝ የሆነ የቴሌኮም አዋጅ ልታፀድቅ ነው” እና ‹አዋጁ ፀድቆ ሊተገበር ነው› የሚሉ ለኢንተርኔትተጠቃሚዎች አስደንጋጭ የሆነ ወሬዎች ነበሩ። (በጊዜው በጉዳዩ ላይ የዞን ዘጠኝ ጦማር ይሄን ፅሁፍ ፅፎ ነበር) በወቅቱ ቢቢሲንና አልጀዚራን ጨምሮ ዓለማቀፍ የሚድያ አውታሮች ‹‹ኢትዮጵያ ስካይፒን የመሳሰሉ በኢንተርኔት የድምፅ አገልግሎት (Voice over Internet Protocol- VoIP) የሚጠቀሙ ሰዎችን፤ እንዲሁም በቴሌኮሙ ያልታወቀ ግንኙነት መሳሪያ የያዙ ግለሰቦችን ለረጅም ዓመታት እስርና ለገንዘብ መቀጫ የሚዳርግ አዲስ አዋጅ አረቀቀች” የሚሉ ሰፋፊ ዜናዎችን ሲያስነብቡ፤ ሀሳብን በነፃነት መብት ላይ የሚሰሩ እንደ የጋዜጠኞች ጠባቂ ድርጅት (Committee to Protect Journalists)፣ አርቲክል 19 (Article 19) እና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Reporters Without Borders) የመሳሰሉ ዓለማቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በበኩላቸው ‹የኢትዮጵያ መንግስት ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትና ጋዜጠኞችን ለማፈን ሆን ተብሎ የወጣ አዋጅ ነው› ሲሉ ኮንነውት ነበር፡፡ በወቅቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማል ‹አዋጁ የስካይፒን የድምፅ ግንኙነት አያግድም፤ ይልቅም ይህ አዋጅ በ1994 የወጣውን የስካይፕ ተጠቃሚነትን የሚከለክል ህግ እንዲሻር አድርጓል› ብለው ነበር።

አወዛጋቢው አዋጅም ከረቂቁ ምንም መሻሻል ሳይደረግበት በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ከነሃሴ 2004 ጀምሮ አዋጅ ቁጥር 721/2004 በመሆን በተግባር ላይ ውሏል፡፡ በአዋጁን አንቀፅ 10 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ ‹‹ኢንተርኔትን በመጠቀም የስልክ ጥሪ አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ 3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ አምስት እጥፍ የሚሆን መቀጮ ይቀጣል› ተብሎ መደንገጉም የብዙዎቹ ስጋት እውነትነት ያዘለ እንደነበር አመላክቶ ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከሶስት ዓመታት በኋላ በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ ሃላፊዎች በአገሪቱ ብቸኛ የሆነውና በመንግስት ደረጃ ‹እንደማትነጥፍ ላም› የሚቆጠረው የቴሌኮም ድርጅት የድምፅ ግንኙነት አገልግሎት የሚሰጡ (VoIP) ወይም የሚጠቀሙ ደንበኞቹን ተጨማሪ ገንዘብ ለማስከፈል የሚያስችል ቴክኖሎጂ በስራ ላይ ሊያውል እንደሆነ እየገለፁ ይገኛል፡፡ በተለምዶ ይሄን የድምፅ አገልግሎት የሚጠቀሙ እንደ Skype፣ WhatsApp፣ Viber፣ imo ወዘተ ያሉ የኮምፒውተር ወይም የስልክ መተግበሪያዎች (Applications) ለመጠቀም የዳታ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ደንበኞች ይህን አገልግሎት ለማግኘት ለቴሌኮም ድርጅቱ ይከፍላሉ። ኢትዮ ቴሌኮም አሁን አገልግሎት ላይ ላውለው ተዘጋጅቻለው የሚለው ቴክኖሎጂ ደንበኞች ለኢንተርኔት ከሚከፍሉት በተጨማሪ የድምፅ አገልግሎት ለሚሰጡ መተግበሪያዎች በመጠቀማቸው (over the top) ብቻ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ ማለት ነው።

ይሄን አስመልክተው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አንዷለም አድማሴ ለካፒታል ጋዜጣ  ሲገልፁ ድርጅቱ እነዚህን አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት ዕቅድ እንደሌለው፤ ነገር ግን እነዚህን አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞችን ‘Policy Charge and Control system (PPC)’ በተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ አማካኝነት እንቆጣጠራለን ብለዋል። የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዱረሒም አሕመድ በበኩላቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሰኞ መጋቢት 26/2008 እንደተናገሩት ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ ገቢው ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ገቢውን የሚያገኝው ከመደበኛ የስልክ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹ከኢንተርኔት አገልግሎት የሚገኝው ገቢ ግን ሃያ በመቶው ብቻ ነው› ብለዋል፡፡ ‹በመሆኑም ይሄን ገቢ ለማሳደግ አዲስ አይነት የአገልግሎት አሰጣጥ እንጀምራለን› በማለት የዋና ሃላፊውን ሃሳብ አጠናክረዋል፡፡

(በጉዳዩ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ዘግየት ብሎ ‹ሐላፊው ይሄን አልተናገሩም፤ የተጠቀሱት አገልግሎቶችም ክፍያ ሊጠየቅባቸው አልታሰበም› በማለት ጉዳዩን ይዞት የወጣው ጋዜጣ (ካፒታል ጋዜጣ) እርማት እንደሚያደርግ  ቢገልፅም፤ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊዎች በስልክ ለማረጋገጥ እንደቻልነው እስከ አሁን ድረስ (እስከ ዛሬ ጠዋት መጋቢት 28/2008) ከኢትዮ ቴሌኮም ለካፒታል ጋዜጣ የደረሰ ምንም አይነት የእርማት ጥያቄ እንደሌለና፤ ጋዜጣውም የሐላፊውን ንግግር የድምፅ ቅጅ እንዳለው ጠቅሶ የሚታረም ነገር እንደሌለ ለማወቅ ችለናል)

ይሄም ጉዳይ አገልግሎቶቹን ሙሉ ለሙሉ ከማገድ ይልቅ በተዘዋዋሪ ታሪፍን በመጨመር የዜጎችን ከአግልግሎቶቹ ተጠቃሚነት ማስቆምን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ከላይ ያነሳነውን የመረብ ገለልተኝነት (Net Neutrality) መርህንም አፈር ድሜ የሚያበላ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ አንድ ሲም ካርድ ለአንድ የተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ እንዲሰራ የሚያደርግ ኢክዊፕመንት አይደንቲቲ ሪጂስተር (Equipment Identity Register - EIR) የተባለ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን ሐላፊዎቹ ገልፀዋል። ይህ ቴክኖሎጂ በእያንዳንዱ የስልክ ቀፎ ላይ የሚገኘውን የመለያ ቁጥር እየመዘገበ አንድ ሲም ካርድ ለአንድ ቀፎ ብቻ እንዲሰራ የሚያደርግ ነው፡፡ ቴክኖሎጅው የትኛው ግለሰብ የትኛው የሞባይል ቀፎን እንደሚጠቀም የሚየሳውቅ ነው ማለት ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ለዚህ ቁርጠኝነቱም ‹አሁን ገበያ ያሉ ያልተመዘገቡ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ሰብስቤ የራሴን አዳዲስ ስልኮች ለተጠቃሚዎች አድላለሁ› እስከማለት ደርሷል፡፡ ነገር ግን መንግስት የሚታማበትን ዜጎችን የመሰለል ተግባር ያቀላጥፍለታል የሚለው ደግሞ አዲስ ስጋት ነው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ‹ይህን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ የምናደርገው ሳይቀረጡ የገቡ ስልኮችን አገልግሎት እያንዳይሰጡና የሞባይል ስልክ ስርቆትን ለመቀነስ ነው› ቢሉም፤ ካለፈው ልምድ ተነስተን ‹የቁጥጥር አባዜ ያለበት በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ዜጎቹን መሰለያ አዲስ መረብ እየዘረጋ ነው› ብንል ስህተት አይሆንም፡፡

እንግዲህ ‹የጀመርናቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች የምንደጉምበት ስለሆነ ለግል ተቋማት ክፍት አናደርገውም› ተብሎ በመንግስት በኩል የሚሞካሸው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ብቸኛ በመሆኑ የሚያስተዳድረው አካልም (Regulatory Organ) ሆነ ‹ተው› የሚለው የበላይ የሌለበትና ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር እንደፈለገ የሚሰራ ተቋም ነው ማለት ነው፡፡

መጭው ዘመን

የቴክኖሎጂው ተደራሽነት እየጨመረና እየረከሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያዊያንም የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ቀስ በቀስ እያደገ ነው፡፡ ምንም እንኳ የተጠቃሚው ቁጥር ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር አሁንም እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ሁሉንም ተቃውሞ በወንጀልነት ለሚፈርጅ መንግስት የሚያስደነግጥ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለዛም ነው የድረ ገፅ አፈናው በአስር ዓመቱ እጅግ ገዝፎና አስፈሪ ሁኖ የሚታየው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከአራት ወራት ለሚልቅ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ በይነ መረቡ (በተለይም ማሕበራዊ ሚዲያዎች) ትኩስ መረጃን በርካሽ ዋጋ ተጠቅሞ የሕዝብ ጥያቄን ዓለም ላይ እንዴት ማድረስ እንደሚቻል ያስገነዘበ ሂደት ነው፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው ተቃውሞዎች የተዘገቡት በማሕበራዊ ሚዲያዎች ቢሆኑም መንግስት ግን በኢትዮጵያ እንዲታዩ ትቷቸው የነበሩትን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚፅፉ ድረ ገፆችን (በተለይም የኦሮሚያውን ተቃውሞ ላይ ትኩረት አድርገው ሲዘገቡ የነበሩ ድረ ገፆችን) በድጋሚ እንዳይታዩ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ዝነኛ የሆኑ የማሕበራዊ ድረ ገፆችን በተለመደው መልኩ መጠቀም እንዳይቻል ከአንድ ወር ለሚልቅ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተደረገው እቀባ ግን የአፈናውን ሌላ ጎን ይነግረናል፡፡ መንግስት አሁን ትኩረቱን ወደ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማድረጉን፡፡


አሁን አፈናው እጅግ ብዙ ዘርፎችን ይዟል፡፡ በአንድ በኩል የተለመደውና የተቃውሞ ድምፀት ያላቸውን ድረ ገፆችንና ጦማሮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረጉ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማሕበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎችን በመዝጋት እና አሁን ደግሞ የድምፅ አገልግሎት የሚሰጡ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ግለሰቦች ከሌሎች አገልግሎቶች በተለየ (discriminatory) ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ ለማድረግ አዲስ አሰራር በመዘርጋት ላይ መሆኑን በመግለፅ የመረጃ ፍሰቱን ማስተጓጎል ተጀምሯል፡፡ ከዚህ ዜጎች መረጃ እንዳያገኙ ከሚደረገው የመከላከያ (defensive) የአፈና ስልት ባለፈ ደግሞ፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ምስጢራት ለመበርበር የሚያስችሉ መሳሪያዎችን እና ዘዴዎችን ከውጭ ድርጅቶች በውድ ዋጋ በመሸመት የማጥቃት (offensive) ስልት በመጠቀም የአፈናውን ስልት ከፍ ብሏል፡፡ ይህን የአፈና ስልት ለማለፍ እንደ ኢንክሪፕሽን ያሉ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ግለሰቦችን ደግሞ ወደ እስር በመወርወር የኢንተርኔቱን ምሕዳር ጠቅልሎ የመያዝ ስልት አስፋፍቶ እናገኛለን፡፡ አሁን ዓለምን የበለጠ እያገናኝ እና ክፍት እያደረገ ያለው ኢንተርኔትም በኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ታላቅ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ከዚህም ተነስተን ዜጎችን መጠበቅ ሲገባው በሚያጠቃው መንግስት ምክንያት መጭው ጊዜ ለኢትዮጵያዊያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ፈታኝ መሆኑን መገንዘብ ብዙ የሚቸግር ጉዳይ አይደለም፡፡ 

***
የፅሁፉን የራስጌ ምስል ያገኝነው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Without Borders) ካወጣው የ2014 ‹የኢንተርኔት ጠላቶች› ሪፖርት ነው::