Saturday, May 13, 2017

የአምስተኛ ዓመት ማስታወሻ…

‹ዞን ፱ የጦማሪዎች እና አራማጆች ስብስብ› ከተመሠረተ እነሆ አምስት ዓመቱ ዛሬ ሞላ፡፡ አምስት የተስፋ እና የስጋት ዓመታት ሔዱ፡፡ ብዙ ጊዜ፣ የተለያዩ ቦታዎች እንደሚነገረው ስብስቡን ለመመሥረት ያነሳሳን ተስፋ ነው፡፡ አዎ በይነመረብ ላይ ብቻ እንተዋወቅ የነበርነውን ዘጠኛችንን ያሰባሰበን ይህ ተስፋ ነው፡፡ ስብስቡ ከተመሠረተ በኋላ ታዲያ፣ ብዙ ጊዜ የበለጠ የሚያነሳሱ፣ አንዳንዴ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጡ እውነታዎችን ተጋፍጠናል፡፡

ያለፉትን ዓመታት መለስ ብለን ስናስታውሳቸው፣ በኢትዮጵያ ስለ ዜግነት ግዴታቸው እና ስለ መብታቸው እምቢ ባዮች የሚጋፈጧቸውን ፈተናዎች ከራሳችን ልምድ በመነሳት በአጭሩ ማካፈል አግባብ መስሎ ተሰማን፡፡

ሐሳብን በነጻነት በማስተናገድ ረገድ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዓለማችን አስቸጋሪ ከሚባሉት አገራት አንዷ መሆኗ እሙን ነው፡፡ እኛ ግን፣ አሁንም አሁንም እያነሳን የምንጥላቸው ጥያቄዎች፤ ‹እንዳሰቡት የሚጽፉ ጦማሪዎች ሕይወት በዚህች አገር ምን ይመስላል? የዴሞክራሲ አራማጆች የለት ተለት ፈተናቸውን እንዴት ነው የሚጋፈጡት?  ለምንድን ነው እያንዳንዱ ቀን ካለፈው ቀን የከፋ እየሆነ የሚመጣው? ለምንድን ነው የምንጽፈው? ጽሑፎቻችን አንባቢዎቻችን ላይ ምን ለውጥ አመጡ?› የሚሉ ናቸው፡፡

የየግል ጥረቶቻችን አሰባስበን ለመሥራት ጉዞ ስንጀምር፣ ሕልማችን ራሳችንን በስርዓት ማነፅ እና ማበልፀግ ነበር፡፡ ስለአገራችን ይበልጥ ማወቅ እና ዕውቀታችንን ማስፋት፡፡ ለዚህ ነው፣ የጡመራ እና አራማጅነት ስብስባችን ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች እኛው ራሳችን ነን የምንለው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በእኛ እርምጃ የተነሳሱ ወጣቶችን ንግግር/ጽሑፍ ስንሰማና ስናነብ - ደስታችን ወደር ያጣል፡፡ ሌሎችን እያነሳሱ የግል ፍላጎትን እንደማሟላት ያለ አስደሳች ነገር ጨርሶ የለም፡፡

የጦማር መድረካችንን ስንመሠርተው፣ ትልማችን የነበረው እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ትልቅ አገር ቀርቶ በትንንሽ ማኅበረሰቦች ሳይቀር ነባሪ የሆነውን ልዩነት የሚያስተናግድ ብዝኃ-ዕይታ የተሞሉ መጣጥፎችን ለማስተናገድ ነበር፡፡ ታዲያ ትልማችን ግቡን መታ? ባንድ ድምፅ የምንናገረው “ኧረ በፍፁም” ብለን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በከፊል - የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠሩት ሰዎች ለሐሳብ ገበያ እንቅፋት በመሆናቸው ነው፤ ከፊል ምክንያቱ ደግሞ እኛው ራሳችን አቅማችንን ሁሉ አሟጠን መሥራት ባለመቻላችን ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ጥቂትም ቢሆን ባደረግነው ጥረት ኩራት ይሰማናል፤ ዋናው ቁም ነገር አሁንም ቢሆን ከሞከርነው በላይ ለመሥራት ፍላጎቱ ያለን መሆኑ ነው፡፡

ጡመራ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ራስን በራስ የማከም ሚና አለው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ “ስለሚያገባን እንጦምራለን” የሚለው መፈክራችን በራሱ ይህንን ጡመራ በሕወታችን ያለውን ሚና ያሳያል፡፡ ስለ መብታችን ይገድደናልና እንጦምራለን፡፡ እኛ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ይህንን ተፈጥሯዊ እና አብሮን የተወለደ ሐሳባችንን የመግለጽ መብታችንን መገፈፋችን ስለሚያሳስበን እንጦምራለን፡፡ መጦመር እና ስለ መብቶቻችን መናገር የገዛ ራሱን ሕግ ማክበር በተሳነው አገረ-መንግሥት ውስጥ መኖር የሚያመጣውን ሕመም ስለሚያክምልን እንጦምራለን፡፡ በዚህ አባባላችን፣ ጡመራ ለጤናማ ማኅበረሰብ ፀር ለሆነው ጭቆና ማከሚያ መድኃኒቱ ነው፡፡

ጡመራ ሰፊ የወዳጅነት እና የመደጋገፍ የግንኙነት መረብ እንድንፈጥር ረድቶናል፡፡ እርስ በርስ በመወዳጀት እና በመገናኘታችን፣ የተቀናጀ የቡድን ሥራ አቅምን መረዳት ችለናል፡፡ ይህ ልምድ እንዲስፋፋ ነው ለአገራችን የምንመኝላት፡፡

መሰባሰብ እና መቧደን ግን ችግር አያመጣም ማለታችን አይደለም፤ ስበስቦች በአገዛዙ ዒላማ ውስጥ በቀላሉ ይገባሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ የጨቋኞች ዋና ጠላት የተደራጀ ጥረት እና ምክንያታዊ ሙግት/ትግል እንደሆነ አስተምሮናል፡፡ ትምህርቱን ማግኘታችን አበርትቶናል፡፡ ከእናንተ አንባቢዎቻችን የተቀበልነው ፍቅር እና ድጋፍም - እንዲሁ - በየቀኑ እያነሳሳን ቁስላችንም በቀላሉ እንዲሽር ረድቶናል፡፡

ዛሬ ላይ፣ ከጡመራ ባሻገር በሌሎች የአራማጅነት ኃላፊነቶች ተጠምደናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት - እኛ ስለ መብታችን የሚገድደን ዜጎች - እጅ ለእጅ ከተያያዝን እና ጥረታችንን ካጣመርን ለውጥ እንደምናመጣ ያለን እምነት ፅኑ ነው፡፡ ይህ ተስፋ እና እምነት ነው - በአምስተኛ ዓመታችን መታሰቢያ ዕለት ሁላችሁም የዞን ፱ ጦማር ተከታታዮች ለዚህ የጋራ ግባችን የበኩላችሁን እንድታበረክቱ የምንጋብዛችሁ፡፡

3 comments:

  1. The post is very nice, by the way, I want to share with you information about the best.

    ReplyDelete
  2. From the tons of comments on your articles, Thank you.

    ReplyDelete