Tuesday, April 25, 2017

#ኢትዮጵያ: እውነትም ዞን 9!

ባለፈው ወር (መጋቢት 28/2009)፣ በዞን ዘጠኝ ጦማርያን ጉዳይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት "የመሠረትኩትን የሽብርተኝነት ክስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጉ አግባብ አይደለም" ብሎ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበው የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ብይን ሲያገኝ፣ ዳኞች የወሰኑት ብይን ላይ ‘ዞን 9 የጦማርያን ስብስብ’ ኢትዮጵያን በሰፊ እስር ቤት መመሰሉ በራሱ ‘የሕዝቡን እምነት ዝቅ ለማድረግ’ ለረዥም ግዜ ወንጀል መሰናዶ የተፈጠረ ሥያሜ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ሰፊ እስር ቤት መሆኗን በከፊል ማስረዳት ነው።
"አርብ-አርብ ይሸበራል… የጦማሪው ልብ"
አርብ አርብ ልቡ የማይሸበር የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ማግኘት ይቸግራል። ያለምክንያት አይደለም። ምክንያታችን እንዲገባችሁ የእኔኑ በማጫወት ልጀምራላችሁ።
ከዞን ዘጠኝ ወዳጆቼ ጋር አንድ ዓመት ከስድስት ወር ታስሬ የተፈታሁት አርብ፣ ሚያዝያ 17, 2006 ተይዤ ነው። በኋላ አርባ ቀን "ታድሼ" የወጣሁት አርብ፣ ሕዳር 2, 2009 ታስሬ ነው። ብቻ የሆነ ነገር የጻፍኩ፣ የሆነ ዲፕሎማት ወይም ጋዜጠኛ ያናገርሁ ሰሞን አርብ እስኪያልፍ ጭንቅ ነው። በሌላ አነጋገር ሁሉም አርብ እስኪያልፍ ጭንቅ ነው። አርብ ቀን ለእስር በፖሊሶች የምትመረጠው ቅዳሜና እሁድ እስረኛውን ፍርድ ቤት ለማቅረብ ስለማይገደዱ ነው። ነገር ግን ሰው በማይኖርበት እሁድ ቀን ለማቅረብ እንዲመቻቸውም ጭምር ነው። ስለዚህ አርብ አርብ እኛን አለማየት ነው።
የሥነ ልቦና ሐኪሞች በፈረንጅ አፍ "Post Traumatic Stress Disorder (PSTD)" ይሉታል። ከሆነ ክፉ ገጠመኝ በኋላ የሚከሰት "የደግሞ ይከሰታል ጭንቅ" የሚያመጣው የሥነ ልቦና መዛባት። እኛ አገር እንደችግራችን የሥነ ልቦና ሕክምና ማግኘት የተለመደ አይደለም። ነገር ግን የPSTD ተጠቂ መሆናችንን መጠርጠራችን አልቀረም።
ከመታሰራችን በፊት የብዙአየሁ “ሳላይሽ” አልበም ተወድዶ በየታክሲው፣ በየካፌው ሲጫወት ነበር። ዛሬ ግን የብዙአየሁ ዘፈኖች ለማሕሌት ፋንታሁን የእስር ነጋሪት ናቸው። የእርሱ ዘፈን በተከፈበት ታክሲ እንድትሔድ፣ የእርሱ ዘፈን የተከፈተበት ካፌ ውስጥ እንድትቀመጥ ከተፈለገ ዘፈኑ መዘጋት አለበት። አለበለዚያ አትችልም።
ናትናኤል ፈለቀ የታሰረ ዕለት ከቢሮው በሆኑ ፀጉረ ልውጥ እንግዶች ትፈለጋለህ ተብሎ ነው። ዛሬም ድረስ፣ ቢሮው በር ላይ ፀጉረ ልውጥ ሰዎች በተከሰቱ ቁጥር ከመደንገጥ አርፎ አያውቅም። በተለይ "ናትናኤልን ፈልገን ነው" ካሉ የልብ ደላቂው አካል አታሞውን ይመታል።
ከአዋሽ 7 መልስ በወዳጆቼ ውትወታ የሥነ ልቦና ሐኪም ማየት ጀምሬ ነበር። ምናልባት PSTDው ጎድቶኝ ከሆነ በአፍላነቱ ልድረስበት በሚል ነበር ሐኪም ለማየት የተስማማሁት። ሐኪሜ አንድ ቀን "እስኪ በየቀኑ የሚገጥሙህን የሚያስደነግጡህን ነገሮች ጽፈህ አምጣ" እስከምትለኝ ድረስ በየቀኑ፣ ያን ያክል ጊዜ እየተረበሽኩ እንደምውል አስቤው አላውቅም ነበር። በማግስቱ ልደታ ፍርድ ቤት አንድ ችሎት ለመከታተል ሔድኩኝ። ፍርድ ቤቱጋ አንድ የፖሊስ ፓትሮል መኪና ቆሟል። ፖሊስ ስናይ ማተኮራችን የተለመደ ነው። እነሱን እያሰብኩ ስሻገር ፊትለፊቴ ወደኔ እያዩ የሚያወሩ ፖሊሶች ጋር ዓይን ላይን ተገጣጠምኩ። ልቤ በአስደናቂ ፍጥነት ድርርርርርም እያለ መምታት ጀመረ። አልፌያቸው ስሔድ በሰከንድ ውስጥ ራሴን አረጋጋሁ። የዛኑ ዕለት ተመሳሳይ ነገር ረፋዱ ላይ ተፈጠረ። ይህ የሆነው ከማሕሌት ጋር ከልደታ ፍርድ ቤት ስንወጣ ጊቢ ውስጥ ቆሞ የነበረ የፖሊስ ፓትሮል ከጎናችን ተንቀሳቅሶ አብሮን በመውጣቱ ነው። “አርብ ነው እንዴ ዛሬ?” ተባባልን። የዛኑ ዕለት ምሽት አቤል ዋበላ የጻፈውን የታሰርን ዕለት የነበረውን ውሎ የሚተርክ ጽሑፍ እያነበብኩ እያለ ልክ አሁን የሚሆን ይመስል እፈራለሁ፤ ልቤ ድርድድው፣ ድርድድው ይላል።
ታዲያ ሰፊ የእስርቤት ዞን ውስጥ አይደለንም ማለት ይቻላል? ይህ የኛ የግል ጉዳይ፣ በገዛ ቅብጠታችን ያመጣነው ጦስ የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉ አላጣሁትም። በእርግጥ እኛ እንዲህ ዓይነቱ ሰቀቀን ውስጥ የገባነው ሐሳባችንን በነጻነት በመግለጻችን፣ መብታችንን በመጠየቃችን ብቻ መሆኑን መዘንጋት ተገቢ አይደለም።
ልዩነቱ የዲግሪ ነው እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህ ፍራቻ አለበት። ብዙኃኑ ኑሮውን መግፋት የሚፈልገው መብቱን እስከጥግ እየጠየቀ አይደለም። ለአካላዊ ነጻነቱ የተወሰኑ መብቶቹን አሳስሯል።
ፍርድ ቤት ፈትቶን፣ በአንፃራዊ የአካላዊ ነጻነት እየተንቀሳቀስን መሆኑን እያወቁ በርካታ ወዳጆቻችን ሸሽተውናል። የሸሹት እኛን አይደለም። እስርን ነው። ከእኛ ጋር መሆናቸው ያለምንም ወንጀል በመንግሥት ዒላማ ውስጥ የሚያስገባቸው ከመሰላቸው፣ መንግሥት ያለወንጀል እንደሚያስር ያምናሉ ማለት ነው። ያለወንጀላቸው ሊታሰሩ እንደሚችሉባት የሚያስቧት አገር ደግሞ "ሰፊ እስር ቤት” ነች።
ወዳጆቻችን ብቻ አይደሉም። ሌሎችም ለጊዜያዊነት የሚያገኙን ሰዎች እንዲሁ ይፈሩናል። “የምትሠራው ሥራ የተባረከ ነው። ግን አገሩ ኢትዮጵያ ነው” ዘወትር የምንሰማው ምክር ነው። አይበሉት እንጂ “አገሩ እስር ቤት ነው” ብለው ማሰባቸውን ማሳያ ነው። ለምሳሌ ከላይ የጠቀስኳት ሐኪሜ ይህንኑ ፈርታ ወደሷ ስሔድ ስልኬን አጥፍቼ እንድሔድ፣ ለሰው እንዳልናገር ደጋግማ ታስጠነቅቀኝ ነበር። ግንኙነታችን የሕክምና እርዳታ የሚፈልግ እና የሚሰጥ ሰው ቢሆንም ያሳስረኛል ብላ ትፈራለች። የምትፈራው እኔን አይደለም። እኔንማ በወዳጅነት ስሜት ስጋቴን የምጋፈጥበትን መንገድ እያስተማረችኝ ነበር። የምትፈራው ያለሰበብ የማሰር ሥልጣን ያለውን የሰፊው እስር ቤት ዋርድያ - መንግሥትን ነው።

No comments:

Post a Comment