Tuesday, October 11, 2016

የማርቲን ኤናልስ ሽልማት የ2016 ሎሬት ታወቀ


10 ዕውቅ የዓለም የሰብኣዊ መብቶች ድርጅቶች የሚያዘጋጁት ዓመታዊው የማርቲን ኤናልስ የሰብዓዊ መብት የ2016 የመጨረሻ ሦስት ዕጩዎች መካከል ዞን 9 የጦማሪዎች እና አራማጆች ስብስብ አንዱ መሆኑ ግንቦት ወር ላይ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ከዞን 9 በተጨማሪ የእድሜ ልክ እስራት ፍርደኛው ቻይናዊው ኢልሃም ቶቲ እና በሶሪያ አማፅያን የተጠለፈችው ሶሪያዊቷ ራዛን ዛይቱን መታጨታቸው ይታወቃል፡፡

ዛሬ አመሻሹ ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አሸናፊ ኤ.ኤፍ.ፒ. የተባለው የዜና ወኪል ቀድሞ አሸናፊውን በመግለጹ ማርቲን ኤናልስም ይፋ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ቻይናዊው የዊጉር ሕዝብ የመብት ታጋይ ኢልሐም ቶቲ የዚህ ዓመት ሎሬት በመሆን ተመርጧል፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ ዛሬ ምሽት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ይከናወናል፡፡
የመጨረሻ ዕጩዎቹ አጭር መግለጫ

አሸናፊው፤ ኢልሃም ቶቲ (ከቻይና)

ኢልሃም ቶህቲ በዊጉር እና ሃን ቻይኖች መካከል ጤናማና ሠላማዊ ውይይት እንዲዳብር ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የደከመ ምሁር ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ምክንያት ከፍተኛ የመንግሥት ክትትል እና እንግልት የገጠመው ሲሆን በጃንዋሪ 15፣ 2015 በከፋፋይነት ክስ እና በሁለት ቀን ችሎት የዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶበታል፡፡በተጨማሪም የሚከተሉት የመጨረሻ ዕጩዎች ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡

ራዛን ዛይቱን (ከሶሪያ)

ራዛን ሕይወቷን ሙሉ የፖለቲካ እስረኞችን፣ የመብት ጥሰቶችን እና ሌሎች ራሳቸውን ነጻ እንዲያወጡ በመርዳት የኖረች ሰው ነች፡፡ የመብት ጥሰቶች መመዝገቢያ ማዕከል (ቪዲሲ) አቋቁማ በሶሪያ ያሉ እስረኞች ላይ የሚደርሱ እንግልቶችን እና የሞት እንዲሁም የመሰወር ዝርዝሮችን እየመዘገበች ይፋ አድርጋለች፡፡ ራዛን በዲሴምበር 9፣ 2013 ጭምብል ባጠለቁ ሰዎች ከሁለት ባልደረቦቿ እና ባለቤቷ ጋር ከቢሮዋ ታግታ ከተወሰደች በኋላ እስካሁን የት እንዳለች አይታወቅም፡፡ የዞን 9 ጦማሪያን እና አራማጆች ስብስብ

የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና አራማጆች ስብስብ (ከኢትዮጵያ)

ቃሊቲ ማረሚያ ቤት 8 ዞኖች አሉት፡፡ ዞን 9 በሚል ሥም የተሰባሰቡት ወጣት ጦማሪዎች የጦማሩን መጠሪያ ያገኙት ኢትዮጵያ ሰብኣዊና ፖለቲካዊ መብቶች የተገደቡባት ትልቅ እስር ቤት ናት ከሚለው ነው፡፡ የዞን 9 ጦማሪያን የሰብኣዊ መብት ጥሰትን እና የፖለቲካ እሰስረኞች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ይጽፋሉ፡፡ ስድስቱ የስብስቡ አባላት ታስረው የተፈቱ ሲሆን፣ ሦስቱ አሁን በስደት ላይ ናቸው፡፡ ታስረው ከተፈቱት ውስጥ አራቱ ይግባኝ ተብሎባቸው እና የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው፡፡


ዞን 9 ለሽልማቱን አሸናፊ የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፣ ሽልማቱም ኢልሐም እንዲፈታ ጫና ያሳድራል ብሎ ያምናል፡፡ ለወደፊቱ መልካም ዕድል እንዲገጥመው ይመኛል፡፡ 

No comments:

Post a Comment