Saturday, August 11, 2012

እንዴት እንደመጥ?በስካይፕ ካንድ ወዳጄ ጋር በማውራት ላይ እያለን እንዳጋጣሚ ሆኖ በኔ በኩል ያለው ማይክ መስራት አቆመ፡፡ የነበርኩበት ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ፣ ስካይፕ ለማስጠቀም አገልግሎት የሚሰጡ ውስን ቦታዎች ሁሉም ስለተያዙና መቀየር ባለመቻሌ እዚያው የነበርኩበት ቦታ ሆኜ የወዳጄን ወሬ በጆሮዬ እየሰማሁ ምላሼን በጽሑፍ ለማድረግ በመወሰን ወሬያችንን ቀጠልን፡፡ እሱ በቃላት ለሚያወራልኝ ነገር እኔም በጽሑፍ እየመለስኩ ጥቂት እንደቆየን የኔ የጽሑፍ ምላሽ እሱ ለሚያወራልኝ ነገር ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት እንደማይችል ገባኝ፡፡ የሚያበሳጭ ነገር ሲያወራ እኔ ከዚህ በኩል ሆኜ እንዴት በብስጭት እንደማወራ አይሰማኝም፤ እንደማይሰማኝ እያወኩም የምፅፈውን ብስጭቴን ጮክ ብዬ ማለቴም አልቀረም፡፡ የሚያስደስትና የሚያስቅ ነገር ሲናገርም እንዲሁ ባለሁበት ሆኜ እደሰታለሁ እስቃለሁ፡፡ እሱ ግን አይሰማኝም፡፡ለተናገረው ነገር ምላሽ ፅፌ ሳልጨርስ ሌላ ወሬ ይጨምራል፡፡ ለሌላኛውም ምላሽ ልሰጥ ስሞክር ሌላ ንግግር፡፡ በዚህ ምክንያት ምንም ሳንግባባ እኔም ምንም ተመጣጣኝ ምላሽ መልስ ሳልሰጥ በሌላ ቀን ለመገናኘት ተቀጣጥረን ተለያየን፡፡

የነበርኩበትን ሁኔታ የተሰማኝን ስሜት እንደኔ አጋጥሟችሁ የምታቁ በጣም ትረዱታላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከወዳጄ ጋር ከመጨረሳችን በፊት በዚህ ተስማማን-----ለካ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች በእንዲህ ባለ መልኩ ለመግባባት እየሞከሩ ነው - የህዝብ ጩኸት ሊደመጥ ያልቻለው፡፡ በትርጉም ደረጃ መንግስት ማለት ህዝብ እንደሆነ ነው የምናቀው፡፡ መግባባት ባለመቻላችን ግን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ተለያይተናል ብዬ አምናለሁ፡፡የህዝብ ተወካይ ተብለው ምክር ቤቶችን ጨምሮ በተለያየ ቦታ የሚገኙ ሰዎች ጥረታቸው ገዢው ፓርቲው የሚለውን ሁሉ ለህዝብ ለማሳመን እንጂ የወከላቸውን ህዝብ ሃሳብ ለመንግስት ሲያቀርቡ አይደለም፡፡ በስም ብቻ የህዝብ ተወካይ ተባሉ እንጂ በስራቸው የገዢው ፓርቲ ተወካዬች ናቸው ማለት ነው፡፡  

ስለዚህም መንግስት እነዚህ ወኪሎቹን እንደልሳንነት እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲሁም 99% የሚሆነው ሚዲያ ተጨማሪ የመንግስት ልሳን በመሆን ያገለግላል፡፡ የመንግስት ልሳን ደግሞ የሚያወራው ወላጅ  ለልጁ አበላ፣ አጠጣና አለበሰ ዓይነት ወሬዎችን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ወሬዎች እንዴት ዜና ሆነው ወይም እንደ ተአምር ተቆጥረው በተደጋጋሚ እንድንሰማቸው ሲደረግ ይገርመኛል፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ ጋዜጦች በስተቀር ሬድዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ በዚህ ተግባር የተጠመዱ ናቸው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በጣት የሚቆጠሩት ጋዜጦች በአብዛኛው የመንግስትን አግባብ ያልሆኑ ስራዎችንና የህዝብን አቤቱታ ወይም በደል በማሰማት ብቻ የተወሰኑት፡፡ በነዚህ ውስን ጋዜጦችና ፓርላማ ባለ አንድ የህዝብ ተወካይ አማካኝነት ሃሳቦቻችንን ለመግለፅ ቢሞከርም ከመንግስት ልሳን ጋር ተወዳድሮ ተደማጭነትን ማግኘትና መፍትሄ ማሰጠት መቻል የህልም እንጀራ የሆነብን ነገር ነው፡፡“ጉድ” አንድ ሰሞን ነው?

ጋዜጦቹ በሳምንት በሚወጡበት ጊዜ ብዙ አዳዲስ ዜናዎችን፣ ክስተቶችን እና ትችቶችን ይዘው ይወጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ቢሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወቅታዊ ጉዳይን እስመልክቶ የሚሰጡትን መግለጫ ወይም ተቃውሞ ያቀርባሉ፡፡ በተደጋጋሚም መንግስት ህገመንግስቱን አክብሮ እየሰራ እንዳልሆነ፤ እራሱ እንድንመራበት ቀን ከለሊት እየተናገረ ነገር ግን ተግባር ላይ እያዋለው እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ግን መቼም ጊዜ መንግስት ጆሮ ገብተውና ምላሽ ተሰጥቷቸው አያቁም፡፡ እነዚሁ ጉዳዮች  በፌስቡክና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆችም ያንድ ሰሞን ጉዳይ ሆነው ለውይይት ይቀርባሉ፡፡ የማበራዊ ድረገፅ ተጠቃሚዎች ባላቸው እውቀት እና ችሎታ ተጠቅመው በጉዳዩ ላይ ገለፃቸውን እና ትንታኔያቸውን ያካሂዳሉ፡፡ ሌላ አጀንዳ ሲመጣ ደግሞ የፊተኛው ይረሳና ስለ አዲሱ ጉዳይ ብቻ ይሆናል ወሬው፡፡

ጉዳዮቻችን በተቻለ ፍጥነት ምላሽ ወይም እርምት ሊሰጥባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ሆነው ሳለ መንግስት ግን ከዝምታ የዘለለ ምላሽ ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ ምላሽ ተሰጠም ከተባለ ፓርላማ ውስጥ እንደምናየው የተድበሰበሰ ወይም ጥያቄውን ሳይሆን ጠያቂውን በመዝለፍ ወይም ደግሞ ኢ-ተአማኒ የሆነ ማስተባበያ በመስጠት ይሆናል፡፡ ፓርላማውማ የሹፈት መድረክ ከሆነ ቆይቷል፡፡ የጠ/ሚኒስቴሩን ኩምክና እንጂ ለተነሱት ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሾችና ማብራሪያዎች ሰምተን አናውቅም፡፡ ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ሲከሰትም እንዲሁ ይፃፋል፣ ይተቻል፣ ይተነተናል ወይም ፓርላማ ይቀርባል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ተድበስብሶ ወይም ‹ምላሽ ተሰጠ› ተብሎ ይታለፋል፡፡  አንዳንድ ጌዜ ደግሞ ትችቱ ወይም ጥያቄው አዲስ በወጡ አዋጆች ላይ ይሆንና ከተጠበቀው በላይ ጥያቄዎች ሲኖሩ የሚሰጡት ምላሾች የሚገርሙ ናቸው፡፡ አንደኛው ምላሽ ጥፋት እንደተሰራ ማመን እና አዋጁ ሲረቀቅ ህዝብ ማሳተፍ እንደነበረበት ወደፊት እንዲህ ዓይነት አዋጅ ሲወጣ ተመሳሳይ ጥፋት እንደማይሰራ ይነገረናል፡፡ ጥፋትን ማመን ምላሽ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ልክ ‹አዎ የመንግስት ሌቦች አሉ› እንደተባልነው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ሌላኛው አዋጁ ከወጣና ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ህዝብ እንዲወያይበት ማድረግ በሚል ውይይት ሳይሆን ተሰብሳቢወቹ አዋጁን ተምረው እንዲወጡ የሚደረግበት አካሄድ ነው፡፡   

በጋዜጦቹ ላይ የምናነባቸው ትችቶች ወይም የሚነሱ ጥያቄዎች የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ርዕስ ከመሆን አልፈው መፍትሄ ወይም እርምጃ ተሰጥቶባቸው አያውቁም፡፡ ይህ በሃገራችን የተለመደ ዑደት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ ዑደት ለመውጣት ጥረት ሲያደርግ አይታይም፡፡ በተቃራኒው በተገኘው አጋጣሚ እንዲህ ዓይነት ትችት የሚፅፉትን ማሰር፣ እንዲሰደዱ መገፋፋት እና ህትመቱ እንዲቆም ሲያደርግ ነው የምናየው፡፡ በማህበራዊ ድረገፆች የሚደረጉትን ትንታኔዎችና ውይይቶችንም ለመገደብ ድረገፆቹ በሃገር ውስጥ እንዳይታዩ ማገድ ዋነኛ ተግባሩ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ጩኸታችን መሰማት በማይቻል መጠን ሆኖ ሳይሆን መንግስታችን ካሉት የስሜት ህዋሳት ጆሮውን ሊሰጠን አለመፈለጉን ነው፡፡ እንዲያውም ዝም ብንል እንደሚመርጥ በተለያየ መልኩ እየገለፀልን ነው፡፡


አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደሚባለው መንግስት ሆን ብሎ እያወቀ ‹‹አልሰማም!›› ከሆነ ያለን መቼም የሚሰማን አይመስለኝም፡፡ ጆሮው ለሚሰማ ሰው ስንናገር የማይመልስልን ምን ሲሆን ነው? ምንም እንደማናመጣ ሲያስብ፣ መልስ ሲያጣ እና ለኛ ግድ ሳይሰጠው ሲቀር (ሲንቀን) ነው፡፡ መንግስትም የኛንም ጩኸት ሰምቶ ምላሽ የማይሰጥበት ምክንያት ከዚህ ውጪ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ምንም አታመጡም እየተባልን ነው ወይም ለጥያቄዎቻችን መልስ የለውም ወይም ንቆናል ወይንም ሁሉንም፡፡ እና መፍትሄው ምን ይሁን ትላላችሁ? እስቲ እንምከርበት፡፡
No comments:

Post a Comment