Wednesday, April 23, 2014

በሕገመንግሥታዊ መብቶቻችንን ተጠቅመን ስለሕገመንግሥታዊነት መነጋገራችንን እንቀጥላለን!

ዞን ዘጠኝ ከተመሠረተ ድፍን ሁለት ዓመት ሊሞላው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ቀረ፡፡ ከዞን 9 ነዋሪዎች ለመጨረሻ ጊዜ ከዞኑ ጽሑፍ ያነበቡት ደሞ የዛሬ ስድስት ወራት ገደማ ነው፡። ዳግመኛ በብርታት መመለሳችንን ልናሳውቅ ስንነሳ ምነው ‹እስከዛሬ የት ነበራችሁ?› የሚል ጥያቄ መነሳቱ ስለማይቀር አጭር መልስ ለመስጠት መሞከራችን አግባብ ነው፡፡
የመጥፋታችን አንዱና ትንሹ ምክንያት የግል ቁርጠኝነታችንን በነበረበት ሁኔታ መቀጠል አለመቻሉ ነበር፡፡የቡድን አራማጅነት ሙሉ በሙሉ የበጎ ፍቃደኝነት ስራ እንደመሆኑ መጠን በግል ህይወታችንና በበጎ ፍቃደኝነት በምንሰራው የቡድን አራማጅነታችን መካከል ሚዛን መጠበቅ ከብዶን አንገዳግዶናል፡፡ ይህ ተግዳሮት ግን ብቻውን አልነበረም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሚገባ የሚታፈንባቸው አገራት አንዷ መሆኗን ከዚህ ቀደም ከምናውቃቸው ምሳሌዎች በተጨማሪ በተለይ ባለፋት ስድስት ወራት በተግባር አይተነዋል፡፡
ለነገሩ የዜጎች ሐሳብን መግለጽ በገዢዎቻችን ዓይን የነውር ያክል እንደሚቆጠር የተረዳነው ገና ቡድናችን ሥራውን በይፋ የጀመረ ሰሞን አንድ ዞን ዘጠኛዊ ላይ በደረሰ ግልጽ ማስፈራሪያ ነበር፡፡ ከማኅበራዊ አውታሮች እምብዛም ያልወረዱ እንቅስቃሴዎችን ዝም ብለን ስንቀጥል፣ በከፊል የተረሳን መስሎንም ነበር፡፡ ከወራት በፊት መልሶ የት ወጡ፣ የት ገቡ፣ ምን አደረጉ የሚሉ ጥያቄዎች እና ክትትሎች በዙሪያችን እየተደረጉ እንደሆኑ እና በአንድም በሌላም መንገድ፣ ከዞኑ አባላቶችና ወዳጆችም ጭምር ከ‹‹ደኅንነቶች›› በመጡ መልዕክቶች የማናውቀው ስህተት እየተፈለገብን እንደሆነ አውቀናል፡፡
ይህም እስከዛሬ የምናወቀውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ አፈናን በተቋማትና በባለሞያዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ዞን ዘጠኝ ባሉ እጅግ በጣም ኢመደበኛ በሆኑ የግለሰቦች ስብስቦችን ሰለባ የማድረግ አቅም እንዳለው እንድንረዳ እድል ሰጥቶናል፡፡ በዚህ እውነታውን የማየት፣ የማሰብና የሥራችንን ዓላማ በስህተት የተረዱ ናቸው ብለን ካሰብናቸው አካላት ጋር ካደረግነው ውይይት በመነሳት ‹ዝምታ ወርቅ› አለመሆኑን አውቀን ተመልሰናል፡። ከዚህ በኋላ የሚከሰቱ እና ከእንቅስቃሲያችን የሚያርቁንን የግል፣ የቡድን ወይም የውጪ ግፊት ጉዳዮችን በፍጥነት ለዞን ዘጠኝ ነዋሪያን ከነዝርዝር ምክንያቱ ለማቅረብ ቃል እንገባለን፡፡
ሁለቱ አመት ጉዞአችን እንዳደረግነው ሁሉ የተለያዩ ጽሁፎችን ማቅረብ ዘመቻዎችን በማዘጋጀት የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ማወያየታችንን እንቀጥላለን፡፡ በሚቀጥለው የሦስተኛ ዓመት የመነሻ ጉዞአችን የተለመዱ የዞኑን ስራዎች ጨምረን አዳዲስ እና ትኩረት የሚገባቸው ወቅታዊ ሥራዎችን ለውይይት ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን፡፡ ሦስተኛ ዓመታችን ከሚጀምርበት ጊዜ አንስቶ እንደተለመደው በወቅታዊ ጉዳዎች ላይ የሚያተኩሩ ሦስተ ዘመቻዎችን እና ተያያዥ ሥራዎችን ይኖሩናል። ዓመቱ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ዓመት በመሆኑም ጭምር የሥራዎቻችን ትኩረት ወደዚያ ቢሳብ ነዋሪዎች እንደሚረዱት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ብዙ የዞኑ ነዋሪያን እንደሚያስታውሱትና ዞኑ ዋና እሴት የሆነው የንግግርና ተዋስኦን ለማበረታታት እና ትውልዱ የራሱ ትርክት እንዲኖረው የበኩላችንን አስተዋእጾ ለማድረግ የምናደርገው ጥረትም ይቀጥላል፡፡ በዚህም መሠረት ጽሑፎቻችሁን ብታጋሩን ለነዋሪያን የመወያያ ርዕስ ለማድረግ መሞከሩን ሥራ አጠናክረን እንገፋበታለን ፡፡ ሁላችንም የዞን9 አባላት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ መብት ፣ ለዴሞክራሲ ውይይትና ለሰብአዊ መብት አራማጅ መሆን ህገ ወጥና ሊደበቅ የሚገባው ተግባር ነው ብለን ስለማናምን የአራማጅነት ሚናችን በመጪው ሶስተኛ አመትም እንደበፌቱ ይቀጥላል፡።
መጥፋታችን ያሳሰባቸው፣ የዞን 9 አስተዋእጾን በበጎ የሚያስታውሱ ምክንያት እስከመጠየቅ ጀምሮ እስከማበረታቻ ድረስ ሲለግሱ የነበሩ ግለሰቦችን በማመስገን የምንጀምረው የእናንተ አስተያየት ለመመለስ ካሰብንበት ጊዜ ጀምሮ አንዱ ማበረታቻ መሆኑን ስለምናምን ነው፡፡ ጥያቄዎች ጠይቃችሁ ያልመለስንላችሁ፣ እንደተለመደው ጽሑፎቻችሁን ልካችሁ ያላስተናገድናቸው፣ ለኢሜይል መልእክቶቻችሁ ምላሽ ላልሰጠናችሁ ምናልባትም ብዙ ጠብቃችሁን በቦታው ላላገኛችሁን ሁሉ ይቅርታችሁ ይገባናል፡፡
አሁንም፤ ስለሚያገባን እንጦምራለን!!

No comments:

Post a Comment