Friday, November 16, 2012

የዩንቨርስቲው ምህዳር

ከሀገራችን ዩንቨርስቲዎች በአንዱ ነው፤ ወቅቱም 1998 ዓ.ም የታህሳስ ወር መጀመሪያ ፡፡ የፈተና ወቅት እየተቃረበ በመሆኑ ተማሪዎች በየቦታው ይቻኮላሉ፡፡ አንድ አመሻሽ ላይ ግን ያልተጠበቀ ድምፅ ተሰማ፤ የጥይት ጩኽት፡፡ ከአሁን አሁን ይቆማል ብለው ቢያስቡም ተማሪዎች ጩኽቱ እየተበራከተ ሄደ፡፡ የተማሪዎች ጩኽትም ታክሎበት ጊቢው ተረበሸ፡፡ ተማሪዎች ከጊቢ ለመውጣት በየቦታው ይሯሯጣሉ፡፡ ‘እድለኛ የሆኑት’ ከጊቢ ለመውጣት ቻሉ፡፡ ‘እድለኛ ያልሆኑት’ ደግሞ በር ተዘግቶባቸው በየዶርማቸው ታግተዋል፡፡ የጩኽቱን መነሻ በተባራሪ ሲሰሙ የበለጠ ደንግጠዋል ታጋቾቹ፡፡ የጎሳ ፀብ ነበር፡፡ የአንድ ጎሳ ተማሪዎች ከሌላ ጎሳ ተማሪዎች ጋር ተጋጭተው ነው ሽብሩ የተነሳው የሚል ነበር ምክንያቱ፡፡ ለተከታታይ 3 ቀናት ከአንድ ጎሳ የመጡ ተማሪዎች ጊቢውን ተቆጣጥረው ተማሪዋች መታወቂያ እያሳዩ እንዲያልፉ በማድረግ ‘ተጣላተነዋል’ የሚሉትን ጎሳ ተማሪ ሲያገኙ እየደበደቡ ሰነበቱ፡፡ በመጨረሻም በፖሊስ ጣልቃ ገብነት ጉዳ ዘግይቶም ቢሆን ተረጋጋ፡፡


ይህ ከሆነ ከ6 ዓመታት በኋላ ሚያዚያ 2004 ዓ.ም በአንድ ሌላ የሀገራችን ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ይጮኻሉ/ይጨፍራሉ፡፡ መዝሙር የሚዘምሩም ይመስላሉ፡፡ ‹‹አሸዋ ለግንባታ፣ ጠጠር ለአርማታ›› እያሉ ያስተጋባሉ፡፡ የጩኸታቸው መነሻም  በዩንቨርስቲው የሚቀርብላቸው ምግብ ጥራት የለውም፣ እንጀራው አሸዋ አለበት፣ ወጡም ጠጠር ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ በመጨረሻም በልመና እና በፌደራል መንግስት ሃላፊዎች ጣልቃ ገብነት ጩኸታቸው ጋብ አለ፡፡

ትምህርት ስንል
ዶክተር እጓላ ገብረ ዩሃንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› ባሉት መፅሃፋቸው የትምህርትን ዓለማ ሲገልፁ፡
‹‹ትምህርት መጀመሪያ ሰብዓዊ ነው፡፡ ማለት ሰው ከሙሉ የሰውነት ማዕረግ የሚደርሰው በትምህርት ነው፡፡ ሁለተኛ ትምህርት መክሊታዊ ነው፤ ማለት ሰው በተፈጥሮው ዝንባሌ መሰረት አንድ ሀብት፤ ጥሪ፤ ወይም መክሊት አለው፤ በዚህ መክሊት መሪነት በማህበራዊ ኑሮ ውስት ተከፋፍለው ከሚገኙት ሥራዎች ላንዱ መሠልጠን መዘጋጀት አለበት፡፡ ሦስተኛው ትምህርት አዲስ ነገር ከማወቅ ከመመራመር የእስከ አሁኑን የዕውቀት ድንበር አልፎ ለመሄድ ከመጣጣር ጋር የተያያዘ ነው፡፡››

በማለት ነው፡፡ በአጭሩ ትምህርት ሙሉ ሰው የመሆኛ ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ ይነግሩናል ዶክተሩ፡፡

‹‹ሰማኒያ በሞላ በሶስተኛ ዓመት፣
ተማሪ አፈረሰው የተፈሪን ቤት፡፡››
መደበኛ የከፍተኛ ትምህርት በሀገራችን ከተጀመረ  ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል ማለት አይቻልም፡፡ ቀዳሚዎቹ ምሩቃን አውሮፓ እና አሜሪካ በመሄድ ትምህርታቸውን ተከታትለው ይመለሱ ነበር፡፡ በሚመለሱበት ወቅት ግን ሀገራቸው ትሰለጥን ዘንድ ቅናት አብሯቸው ይገባ ነበር፡፡ ይሄን ቅናታቸውንም ለማስታገስ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ይጀመር ዘንድ የንጉሱን ስርዓት መወትወታቸው አልቀረም፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያ የሚኖሩ ወንጌላዊ ካናዳዊያን ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ፈቃድ በመቀበል አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ኮሌጅን መሰረቱ፤ ከጥቂት አመታት በኋላም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ ተከፈተ፡፡ የዩንቨርስቲው መከፈት ለብዙ ኢትዮጵያዊያን መልካም ነገር የነበረ ሲሆን፤ ለንጉሱ ስርዓት ግን አበሳንም ይዞ እንደመጣ ይታመናል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ የተከፈተበት ወቅት በ1953 ዓ.ም ስኢረ መንግስት ማግስት መሆኑ ተማሪዎች ንጉሱ እና ስርዓታቸው ሊደፈሩ የሚችሉ እንደሆነ የተረዱበት ጊዜም ሆነ፡፡ ይባስ ብሎም በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጡ ኢትዮጵያዊያን በኮሚኒስታዊ ፀበል እየተጠመቁ ይገቡ ነበር፤ ኮሚኒዝምንም ይሰብኩ ጀመር፡፡ በነዚህ ተደራራቢ አጋጣሚዎች ያገኙት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ ተማሪዎችም ንጉሱ ስርዓታቸውን እንዲያስተካክሉ መገፋፋት አልፎ አልፎም መተንኮስ ጀመሩ፤ እንደነ ዩሃንስ አድማሱ ያሉት ተማሪዎች ንጉሱ በተገኙበት ሳይቀር፤ ባደባባይ ስርዓቱ ይቀየር ዘንድ ያውጁ ነበር፡፡ የስርዓቱ ባለስልጣናትም ‹‹እኛው አስተምረን በገዛ እጃችን ተማሪ ያንጓጥጠን ጀመር›› እያሉ በማስተማራቸው ቁጭት ውስጥ ገብተው ይብሰለሰሉ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ በ1960ዎቹ ይህ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሟ እየተጠናከረ ሄዶ የንጉሱ ስርዓት ግብዓተ መሬት ተፈፀመ፡፡

ትግል እንደገና
‹‹መሬት ላራሹ፣ ለላብ አፍሳሹ!›› ብለው የተነሱት ተማሪዎች የንጉሱን ስርዓት ተቃውመው የተነሱባቸውን አላማዎች በቀላሉ ማሳካት አልቻሉም፡፡  ይልቅስ ተማሪው የተሰለፈትን አላማ በወታደሩ ተቀማ ቢጨንቀውም፡

‹‹ጉድ ፈላ ዘንድሮ፣ ጉድ ፈላ ዘንድሮ፣
ምሁር ወደ ጫካ፣ ወቴ ወደ ቢሮ፡፡›› እያለ ሸፈተ፡፡

የወታደራዊው መንግስት ወደስልጣን መምጣት የተማሪዎቹን ህልውና በራሱ አደጋ ላይ ሊጥለው ቻለ፡፡ ከወታደራዊው መንግስት የተገኝው ትልቅ ‘ስጦታ’ ሊባል የሚችለው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲን ስም አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ብሎ መቀየሩ ነው፡፡ ከዛ ባለፈ ግን ግፍ እና ጭቆናው ተባብሶ ቀጥሎ ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ግፉ የበረታባቸው ተማሪዎችም ደብተር ጥለው ጫካ ገቡ፤ ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግስትም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም አልፎ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በአደባባይ ያስር፤ ይረሽን ጀመር፡፡

‹‹የተማሪ ደብተር፣ አልጠፋም ተገኝ፣
በየመሃል መንገድ፣ በደም እየዋኝ፡፡››

ተብሎ እስኪተከዝ ድረስ ‹‹ዘመቻ ተማሪ ማጥፋቱን›› ወታደራዊው መንግስት ቀጥሎበት፤ በመጨረሻም ሙሉ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎቸን አፍሶ ብላቴ ማሰልጠኛ ከተታቸው፤ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ይዋጉ ዘንድ፡፡ ነግር ግን ይህ የብላቴ ‘ምሁር ጦር’ አንድ ጥይት ሳይተኩስ ወታደራዊው መንግስት ከመንበሩ ተነሳ፡፡

'አዲስ ስርዓት'፤ 'አዲስ ዩንቨርስቲ'
ኢህአዴግ ስልጣን መያዙ የዩንቨርስቲዎቻችን እና ተማሪዎቻቸውን ሁናቴ መቀየሩን መታዘብ ይቻላል፡፡ ባንድ በኩል ተማሪው ከእታፈሳለሁ ስጋት ነፃ ሆነ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ በሃሳብ ያልተስማሙትን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህራን በአንድ አዳር አባሮ ከምሁራን ጋር ኩርፊያ ጀመረ፡፡ ይህ ሁለት መልክ ያለው ግንኙነት እንዳለ ሆኖ መንግስት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ሰፊ እና የማስፋፊያ ስራ መስራቱ እንደ ብርቅ ይቆጠር የነበረውን የዩንቨርስቲ ትምህርት ለብዙሃን ተደራሽ ሊያደርገው ቻለ፡፡

የትምህርት ዓላማ ሰብዓዊነት፣ መክሊታዊነት እና አዲስነት ነው እንዳልነው በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የመጀመሪያ አስር ዓመታት ተማሪዎችም ያገባናል በሚል መንፈስ በሀገሪቱ ባሉ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ነበሩ፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጉዳዩች እስከ የበጎ ፈቃድ አስተዋፅኦ ድረስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና መምህራን ያልገቡበት ጉዳይ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ንቁ ተሳትፎ መሃል ግን ከመንግስት ጋር በመብት ጉዳዮች ላይ መጋጨታቸው አልቀረም፡፡ ይባስ ብሎም ደም እስከመፋሰስ ድረስ ፀና፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በጎሳ ጎራ ለይቶ ዩንቨርስቲን ‹‹የጦር አውድማ›› ማድረግ አዲስ እውነታ ሆነ፡፡

የ1997 ዓ.ም ምርጫ ግን ለኢህአዴግ ትልቅ መልእክት አስተላለፈለት፡፡ ምርጫ በደረገባቸው ዩንቨርስቲዎች ውስጥ በሰፊ የድምፅ ልዩነት ተሸነፈ፤ እናም ተማሪ ጋር መተባበር (Cooperation) እንጅ መፋጠጥ (Confrontation) ዋጋ እንደሌለው ተረዳ ዩንቨርስቲዎችንም በስርዓቱ ፖሊሲዋች ማጥመቅ ያዘ፡፡ ይሄም ለዛሬዎቹ የዩንቨርስቲዎቻችን መልክ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይታመናል፡፡

ተማሪነት ዛሬ፣ አስተማሪነት ዛሬ፣ ዩንቨርስቲ ዛሬ
የትምህርት ጥራት መጓደል መንግስት የአጠቃላይ የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት ፈተና ነው ብሎ አውጇል፡፡ ይህ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ደግሞ የገዘፈ እና ለነገ ሊባል የማይችል ችግር እንደሆነ በተለያየ ወቅት የቀረቡ ሪፖርቶች አመላካች ናቸው፡፡ እንግዲህ  ከጥራት መጓደል ጋር ተያይዞ አላማቸወውን ማስተማር፣ መመራመር እና ህብረተሰቡን ማገልገል (Teaching, Research and Community Service) ለሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መፈተናቸው አልቀረም፡፡ እስኪ የአሁኖቹ ዩንቨርስቲዎች መልክ እና ቁመናን እንመልከት፡፡

1. ዋዘኛ እና ፈዛዛ
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ30 በላይ ዩንቨርስቲዎች አሉ፤ ይሄም ለከፍተኛ ትምህርት እድገት ታላቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን የነዚህ ዩንቨርስቲዎች ማህበረሰብ ዋዛ እና ፈዛዝነት በእጅጉ ያጠቃው እንደሆነ መረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ከአንጋፋዎቹ እስ አዳዲሶቹ ዩንቨርስቲዎች ዛሬ በጉጉት የሚጠበቁት ጉዳዩች እንደ Crazy Day, Color Day ወይም Valentines Day ያሉት ዋዘኛ ቀኖች እንጅ ትምህርት እና እውቀት አዘል ጉባኤዎች ወይም ውይይቶች አይደሉም፡፡ ትምህርት የትርፍ ጊዜ ሥራ እንደሆነ በብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንዲሁም አስተማሪዎች ዘንድ ግንዛቤ የተያዘ ይመስላል፡፡

አብዛኞቹ ተማሪዎች ከሚያነቡት Handout፤ መምህራንንም ከሚያዘጋጁት Handout ባለፈ ስለ ሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የማወቅ ፍላጎት አይታይባቸውም፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ፈዛዛ ነው ምንም መስማት አይፈልግም ማለት እንችላለን፡፡ በዩንቨርስቲዎች ውስጥ የመብት ጥያቄ ተነሳ ካልንም፤ መነሻዎቹ ወይ የምግብ ጉዳይ ነው አለዚያም እንደ የDSTV ካርድ የመጠቀሚያ ጊዜ ማለቅ ያሉ እዚህ ግባ ሊባሉ የማይችሉ ጉዳዩች ናቸው ፡፡

በአንድ ወቅት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች የንጉሱ ስርዓት በግዴታ ወደ ተላየዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንድንዘምት እያደረገን ነው ይሄ ደግሞ ከመብቶቻችን ጋር ይጋጫል በማለት የንጉሱን ስርዓት በፍርድ ቤት ከሰው አሸንፈውት ነበር፡፡ ዛሬ ይሄን ለመብት መታገል በዩንቨርስቲዎቻችን ውስጥ የሚፈልጉ ከሆነ፤ አዎ እርስዎ የትናንት ሰው ነዎት፡፡

2. ካድሬው ‘ምሁር’
ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ኢህአዴግ ትልቅ ትምህርት ቀሰመ ካልን፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ስርዓቱን ማጠንከርን ከቀዳሚዎቹ ትምህርቶች ማሰለፍ እንችላለን፡፡ በ1997 የክረምት ወራት የተጀመረው የመስመር ዝርጋታ ተጠናክሮ ፓርቲው በአዲስ ራእይ መፅሄቱ በ2003 ዓ.ም  በመላ ሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከ150,000 በላይ አባላት እንዳሉት እና በእያንዳንዱ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ህዋስ እንደዘረጋ ገልጿል፡፡ እንግዲህ ይህ ቁጥር እንደሚጠቁመን አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የስርዓቱ አካል እና አስፈጻሚ እንደሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዩንቨርስቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው አዲስ ገፅታ፤ የተማሪዎች ጊዜያቸውን በህዋስ ውይይት እና ግምገማ ማዋላቸው፣ ከአባላት ሁሉ ረዝሞ ለመታየት የሚደረግ ጥረት፣ ከትምህርት ውጤታቸው ይልቅ፤ በአባልነታቸው ወደሚሰጣቸውን ነጥብ  አብዝቶ ማተኮር፣ ሲብስም የትምህርት ጊዜያቸውን ለፓርቲ ተግባራት በማዎል የመጡበትን ዋነኛ አላማ መሸሽ ወ.ዘ.ተ የዛሬ የዩንቨርስቲ ተማሪነት መገለጫዎች ናቸው፡፡

3. የጎሳ 'ጠበቃ'
በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይእንደቀረበው ምሳሌ ያሉ ጎሳ ተኮር (Ethnocentric) ግጭቶች ሌላው የዩንቨርስቲዎቻችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ ነገሮችን በውይይት እና በሰከነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ጦር መስበቅ አዲሱ እውነታ ነው፡፡ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ከዩንቨርስቲ ፤ ዩንቨርስቲ ተሸጋጋሪ መሆኑ ነው፡፡ በአንድ ዩንቨርስቲ የተፈጠረ ግጭት አፍታም ሳይቆይ በሌላ ዩንቨርስቲ የሚገኙ ‘የጉዳዩ ባለቤቶች’ ጋር በመዳረስ እስከሞት የሚደርሱ ግጭቶችን ማየት ዛሬ ዛሬ ብዙም አስገራሚ ጉዳይ አይደለም፡፡

ይህ የጎሳ ጥብቅና ባስ ሲልበትም የመማሪያ መፅሃፍትን አስከ መምረጥ ይዘልቃል፡፡ ‹‹ይህ መፅሃፍ ለኔ ጎሳ አይስማማምና ከቤተ መፅሃፍት ይውጣልን!›› ብለው መፅሃፍ ላይ ፍርድ ሰጥተው፤ ውሳኔውን የሚያስፈፅሙ ተማሪዎች በየንቨርስቲዎቻችን እንዳሉ ማወቅ መራር እውነታ ነው፡፡

መምህራን እና የዩንቨርስቲዎች አስተዳደር አካላት ‘ለድቀቱ’ አስተዋፅኦ የላቸውም ማለት አይቻልም፡፡ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ስነምግባር ድረስ ከተማሪዎቻቸው የማይሻሉ መምህራን እንዳሉ ማወቅ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ የዩንቨርስቲዎች አስተዳደሮችም ሁሉም ጉዳዮች ‘ፖለቲካዊ ትርፍ’ ይገኝባቸው ዘንድ ሁሌም መትጋታቸው ከትምህርቱ ዋነኛ ዓላማ እንዲሸሹ አድርጓቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ከነዚህ እውነታዎች የምንረዳው ነገር፤ ተማሪዎች በዩንቨርስቲ የሚኖራቸው ቆይታ እንዲሁም አጠቃላይ የዩንቨርስተዎቻችን ምህዳር አሳሳቢ እንደሆነ ነው፡፡ አዎ የተማሪውን ደብተር በደም እየዋኝ ያየንበት ዘመን በማለፉ ደስ ይለናል፡፡ ነገር ግን ደስታችንን የሚገድብ አዲስ እውነታ ደግሞ ከፊታችን ይታያል፤ ደብተር የሌለው ‘ተማሪ’፡፡  ተማሪዎች የሚሟገቱለት ዓላማ (Cause) ምግብ እና ጎሳ ብቻ መሆኑ የት ያደርሰናል? ምንስ እናድርግ?


ማስታወሻ፡ በዚህ ፅሁፍ ‘የከፍተኛ ትምህርት ተቋማ’ት ወይም ‘ዩንቨርስቲ’ እያልን የገለፅናቸው ተቋማት በመንግስት የተቋቋሙትን የትምህርት ተቋማት ብቻ ያመለክታሉ፡፡

No comments:

Post a Comment