Thursday, August 2, 2012

የበይነመረብ ደህንነት (Internet Security) አንድምታዎች!

እንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል እና በፍቃዱ ኃይሉ

“ኢትዮጵያውያን በይነመረብ ላይ መታየት ጀምረዋል” የሚባሉበት ደረጃ ላይ ናቸው እንጂ “በይነመረብ እየተጠቀሙ ነው” ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡ የሲአይዬ የአገራት ጥሬ ሐቅ ብሎ ያስቀመጠው ቁጥር እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ ከበይነበመረብጋ የተገናኙ ኮምፒዩተሮች ቁጥር 447,300 (እ.ኤ.አ. 2009) እንደሆነ ነው፡፡ ይህም አገሪቱን ከ231 አገራትና ግዛቶች አንጻር በ202ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል፡፡ ፌስቡክ ደግሞ የኢትዮጵያ ተጠቃሚዎቼ ቁጥር 618400 ደርሷል፣ ባለፈው ስድስት ወር ብቻ ከ120ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን አግኝቻለሁ የሚል ሪፖርት አለው፡፡

ቁጥሩ ከሕዝብ ብዛቱ አንፃር በጣም ትንሽ መሆኑ ግን ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን አያስክደውም፡፡ በኢትዮጵያ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኗቸው ከፍተኛ የሆኑ ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን በየነበመረብ ተጠቃሚያን ናቸው፣ አብዛኛዎቹም የፌስቡክ እና ትዊተር ማሕበራዊ አውታሮች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በርግጥ በኢትዮጵያ የሚገኙት ቴሌቪዥኖችም ቁጥር ከዚሁ የበለጠ እንዳልሆነ ቆየት ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች ተፅዕኖ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጠቃሚዎች አይተናነስም ብለን በመደምደም እንጀምር፡፡

ለመሆኑ ኢንተርኔት የማነው?
“የበይነመረብን መሰረተ ልማት ሽርፍራፊ በባለቤትነት የያዙ በርካታ ድርጅቶች፣ ኮርፖሬሽኖች፣ መንግስታት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ግለሰቦች እና አገልግሎት ሰጪዎች አሉ፤ ነገርግን ማንም በሙሉ ባለቤትነት አልያዘውም፡፡” ይላል webopodia የተሰኘ ኢንሳይክሎፔዲያ፡፡ አንድ ግለሰብ በሙሉ ባለቤትነት አልያዘውም ማለት ግን በበይነመረብ እና ተጠቃሚዎቹ መረጃ ላይ ስልጣን ያላቸው ቡድኖች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አይፒ አድራሻ የመስጠት ስልጣን ያላቸው (እንደነ ኢትዮቴሌኮም)፣ የድረአምባ ስያሜ ሰጪዎች (ቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ እልፍ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች)፣ እና እነ የበይነመረብ አርክቴክቸር ቦርድ ቢፈልጉ ተባብረው መግደል፣ አልያም ደግሞ በነጠላ ማቁሰል ይችላሉ፡፡

ግን አስፈሪው ጉዳይ ይህ አይደለም፡፡ የድረአምባ (website) ባለቤቶች መረጃዎቻችንን አሳልፈው ለሌላ ወገን ቢሰጡብንስ የሚል ስጋት ይኖር ይሆን? ለምሳሌ የጉግል ኩባንያ በየ6 ወሩ ይህንን መረጃ አጥፋልን  እና የግለሰቦችን መረጃ ስጠን የሚሉ ጥያቄዎችን ከየትኞቹ መንግስታት እንደተቀበለ ሪፖርት የማውጣት ባሕል እንዲፈጥር ያደረገው ይሄው ጫና ነው፡፡ እርግጥ ነው በጉግል መረጃ ላይ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በማቅረብ አልተጠቀሰችም፡፡ ይህ ግን ከመንግስቱ ፍላጎት ጋር የሚገጥም አይመስልም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን መረጃ አስወግድልኝ ብሎ አለመጠየቁን በጥርጣሬ ለመመልከት የሚያስችሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ዋነኛው በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበቡ ካልታገዱት የጦማሮች ቁጥር የታገዱት የመብለጣቸው ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የታገዱትን ድረአምባዎች እና ጦማሮች በኢትዮጵያ ለማንበብ የሚረዱ ፕሮክሲዎችን በጉግል አማካይነት ከበይነመረብ ላይ ለማውረድ ፈልግ የሚለውን ስትጫኑ “Sorry! The page cannot be displayed.” የሚል ለማግኘት ትገደዳላችሁ፡፡

በበይነመረብ ላይ እነዚህ ዓይነቶቹ እገዳዎች መኖራቸው አገራችንን እንደነፃ ፕሬሱ ሁሉ “ነፃ ያልሆነች” አሰኝተዋታል፡፡ ፍሪደም ሐውስ “ነፃ ያልሆነች” ሲላት፣ ኦፕንኔት ኢኒሼቲቭም በበኩሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጽሑፎችን “በአሳሳቢ ደረጃ የሚያጠሉ (Substantial filtering)” አገራት ምድብ ውስጥ አስቀምጧታል፡፡

ስለዚህ ብቸኛው የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮቴሌኮም (በመንግስት ይዞታ ስር) ያለ እንደመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በይነመረብ የመንግስት ነው ብሎ ማለት ድፍን ስህተት አይሆንም፡፡ አንድባንድ ከማገድ እስከ ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት አቅም እና ስልጣን አላቸውና!

ማሕበራዊ አውታሮች፤ አውጪ መሳሪያ ወይስ መታሰሪያ?
በተለይም ከአረቡ ዓለም የፀደይ አብዮት ወዲህ ፌስቡክና ትዊተርን ጨምሮ ሌሎችም ማሕበራዊ አውታሮች እንደ ነፃ አውጪ መድረኮች መታየት ጀምረዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንም ቢሆን ፌስቡክን በአዲስ አብዮት ተስፋ ይመለከቱታል፡፡ የዚሁ ውጤት ነው በመቶዎች የሚቆጠሩ አብዮት ናፋቂ የፌስቡክ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ ማሕበራዊ አውታሮችን ተጠቅመው ተመሳሳይ ግብ ያላቸውን ሰዎች ከመቀስቀስ እስከ መረጃ መለዋወጥ ድረስ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ “ለመንበሩ ቀናኢ ነው፣ ከአርባ ዓመት ወዲህ አውራነቱን አሳልፎ አይሰጥም” እየተባለ የሚታማው የገዢው ፓርቲም ነገሩን በንቀት አልተመለከተውም፡፡ እንዲያውም የፌስቡክ የቡድን ገጾችን አንድ በአንድ እየተከታተለ ማገዱን ተያይዞታል፡፡ በዚህ መሃል ታዲያ ገና ለገና ‹ኢትዮጵያ› የሚል ቅጽል ብቻ ስላለው ‹ደጉ ኢትዮጵያ› በሚል ስም ለበጎ አድራጎት የተፈጠረ የፌስቡክ ቡድን ገፅ ሳይቀር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበብ ተደርጓል፡፡ ይህ እያግበሰበሱ የማገድ እርምጃ ሌላ ጥያቄ ወልዷል፡፡ ገዢው ፓርቲ እየተቃወሙኝ ነው ወይም ተቃውሞ እያስተባበሩኝ ነው ያላቸውን ግለሰቦች በዚህ አማካይነት ቢከታተላቸውስ?

የማሕበራዊ አውታር ተጠቃሚዎች አውታሩን የሚቀላቀሉበት የመጀመሪያው ዓላማ ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት በመሆኑ በርካታ የግል መረጃዎቻቸውን በግልጽ ማስቀመጣቸው የተለመደ ነው፣ ነገር ግን በፖለቲካ ቅኝቱ እየተማረኩ በሚገቡበት እና ከማያቁት ሰው ጋር በሚመሰርቱት ምናባዊ ወዳጅነት (virtual friendship) በቀላሉ ግላዊ መረጃዎቻቸውን ሊያጡ ወይም አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ግዜ የውሸት ስሞች ያሏቸው (anonymous) ሰዎች አሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት የነፃ አውጪ ታጋዮች ቢኖሩም፣ በተቃራኒው ሰላዮችም ይኖራሉ፡፡

የቴሌኮም አዋጁስ ምን ይነግረናል?
የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ በቅርቡ ፀድቋል፤ አዋጁ ‹ስካይፕ መጠቀም ይከለክላል፣ አይከለክልም› በሚሉ አጀንዳዎች ተሸፍኖ ለሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች ቁብ መስጠት አለመስጠቱ ሳይታወስ ታልፏል፡፡ በመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂ (Information and Communication Technology) የበለፀጉ አገራት የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጆቻቸው ላይ፣ የግለሰቦችን ደህንነት (privacy)፣ የንብረት ባለቤትነት (intellectual property)፣ የኮምፒዩተር ሰርጎገብነት (hacking)፣ የወሲብ ቪዲዮዎች (pornography) እና የሕፃናት ስነልቦናዊ ጥቃትን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር ሲወጡ፣ በእኛ አገሩ የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ግን ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ሕዝብን እና እሴትን ከአደጋ ስለሚከላከሉ ጉዳዮች አንዳችም ያነሳው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ‹በአገር ደህንነት› ስም የገዢውን ፓርቲ ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ድምጾችን በማፈን በተዘዋዋሪ የበይነመረብ ላይ ሐሳብን በነፃ የመግለፅ መብት የሚነፍጉ አንቀጾች ተሰግስገውበታል፡፡ ይህም ማሕበራዊ አውታሮች፣ በተለይም በአገራችን ከነፃ መድረክነታቸው ይልቅ አጋላጭነታቸው እያየለ እንደመጣ ሌላ ምስክር ነው፡፡

የተመስገን  ደሳለኝ ገጠመኝ (እና ፍቺው)
ፍትህ ጋዜጣ ላለፉት ወራቶች በስርጭት ብዛት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ጋዜጣ ነበር፡፡ ጋዜጣው ሙሉ ለሙሉ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ የገዢውን ፓርቲ በመንቀፍም ይታወቃል፡፡ ሆኖም ጋዜጠኞቹ በተደጋጋሚ እንደገለፁት እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹አጀንዳ› አምድ ላይ ብዙ ጊዜ እንደተነበበው ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው፡፡ አሁን ደግሞ ከናካቴው ጋዜጣው እንዳይታተም በፍትህ ሚንስትር ታግዷል፡፡

ጋዜጣው ከመታገዱ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ሁለት ደብዳቤዎችን በኢሜይል አድራሻው እንደተቀበለ ጽፏል፡፡ የመጀመሪያው ደብዳቤ የተጻፈው ራሱን የአልሻባብ መልዕክተኛ ብሎ ከሚጠራ ሰው ሲሆን፣ እንደተመስገን አገላለጽ አልሻባብ እና ፍትህ ጋዜጣ የኢትዮጵያ መንግስትን እያጥላሉ ለመስራት ስምምነት ያላቸው አስመስሏል፡፡ በሁለተኛው ደብዳቤ ደግሞ ሌላ የአልሻባብ ተወካይ ነኝ ባይ ተመስገን የመጀመሪያውን ደብዳቤ የተቃወመው የወሰደውን ገንዘብ ላለመመለስ ፈልጎ እንደሆነ ለማስመሰል ሞክሯል፡፡ ተመስገን፣ እነዚህ ደብዳቤዎች የተጻፉት ከመንግስት ካድሬዎች እንደሆነ እና ክስ ለመመስረቻ ሰበብ እያሴሩ እንደሆነ ያለውን እምነት አትቶ ገልጧል፡፡

በርግጥ ይህ ዓይነቱን ደብዳቤ አስመስሎ በመጻፍ እና በማሴር የመንግስት አቃቤሕግ ክስ ሊመሰርትበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂው ለበጎም ለክፉም መዋል የሚችል ነውና (ወይም በሌላ አነጋገር ለማንም አይወግንምና) ኢሜይሉ፣ ከየት እንደተላከ በዝርዝር ማወቅና ክሱ የተሳሳተ እንደሆነ ሊታወቅባቸው የሚችላቸው በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ የኢሜይል አገልግሎት ሰጪዎች የተላኩልንን ደብዳቤዎች ምንጭና ዝርዝር መረጃ የሚሰጡ መሆኑ በቂ ምሳሌ ነው፡፡ እንደምሳሌም የዋና፣ ዋና ኢሜይል አገልግሎት ሰጪዎቸን የኢሜይል ላኪ መረጃ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል እዚህ መመልከት ይቻላል፡፡

እኛና ኬንያ
ከሀገራችን የዝብ ብዛት ከግማሽ በታች የምታንው ጎረቤታችን ኬንያ ከ11 ሺህ በላይ ጦማሪዎች እንዳሏት ይገመታል:: በኢትዮጵያ ያሉት ጦማሪዎች እና ጦማር ቁጥር በጣት የሚቆጠሩ ቢሆንም እነርሱም በአዝጋሚው የበይነመረብ አገልግሎት የተሰላቹና በአፈናው የተሳቀቁ ናቸው፡፡ በይነመረብ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎችን ብንመለከት በአገራችን አንድ ለናቱ የሆነው ኢትዮቴሌኮምን ብቻ ስናገኝ፣ በትንሽዋ ኬንያ ግን ከአራት ያላነሱ አንራዊ በሆነ መልኩ የተሻለ አገልግሎትን ረከስ ባለ ዋጋ የሚያቀርቡ የበይነመረብ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎችን ይገኙባታል:: ኬንያ በICTእና ተያያዥ ግልጋሎቶች በርካታ የሚያስቀኑ ውብ የሆኑ ድገቶችን ከዕለት ዕለት በማስመስገብ ላይ ያለች ገር ነች:: ገራችን ውስጥ የሚገኙ የሶፍትዌር ኩባንያዎችን ከጎረቤታችን ኬንያ የሶፍትዌር ኩባንያዎች ጋር ስናወዳድር የኛዎቹ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም፡፡ በይነመረብ የገቢምንጭ መሆን እስካሁን አልቻለም፣ የዜና አውታሮችም በይነመረብን በሙሉ ልባቸው አልተቀላቀሉትም፡፡

ኬንያውያን እ.ኤ.አ. በ2008 ያካሄዱትን ምርጫ ተከተሎ የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ እና አለመረጋጋት በጥራት ለመዘገብ በሚል ያቋቋሙትን በስዋሂሊ ቋንቋ ‹‹ኡሻሂዲ›› ብለው የሰየሙትን ኩባንያ እንመለከት:: ይህ ኩባንያ በበጎ ፍቃደኞች አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ሲሆን  በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት በሚገባ በማጋለጥ እየቀነሰው ይገኛል:: የፈጠራ ራን ማበረታት እና ማስፋፋት ለምሳሌ የማፕ ኬብራ ፕሮጀክት ወጣቶች በጋራ በመሆን በኬንያ ካርታ ላይ ከ1 ሚሊዮን ዝብ በላይ የሚርበትን የሆች መንደር እንዲተወቅ እና ተገቢውን ኩረት እንዲያገኝ አድርገዋል:: ኬንያውያን በእንደዚህ ዓይነት ሥራዎቻቸው ለዴሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደር እና ልማታዊ መቀላጠፍ አገራቸውን አብቅተዋታል፡፡ ይህ የሆነው በቂ የበይነመረብ እና ቴክኖሎጂ ነፃነት በመኖሩ ነው፡፡

በተቃራኒው ቻይናውያን በዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ በኢንተርኔት ጠላትነት ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንኑ ሞዴል በመውሰድ የቻይና ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ ጦማሮችን እና ድረአምባዎችን በማገድ የበይነመረብ ማጥለል ሥራውን በሰፊው እና በገሃድ ተያይዞታል፡፡

አጭር ደመደሚያ
ግብጻዊው ዊኤ ጎሆኒም በ2010 የግብዊያን አመጽ ወቅት ለሲኤንኤን እንዲህ ሲል ተናግሯል “If you want to liberate a society just give them the Internet” (አንድ ማኅበረሰብ ነፃ እንዲወጣ ከፈለጋችሁ በይነመረብ ስጡት) እኛም ይህንኑ እንደግማለን፤ ሕዝቦች ነፃ ካልወጡ ዴሞክራሲም፣ መልካም አስተዳደርም፣ ዕድገትም የለምና!

1 comment:

  1. I like the assessment! Especially the part that points out the shortcomings of Telecom Proclamation.

    ReplyDelete