Monday, August 6, 2012

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ማኅበር ዛሬ

በናትናኤል ፈለቀየ1997ቱን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ መገለጫ ነው ከተሰኙት እና ከትልቅ ጉሩምርምታ በኋላ ከጸደቁት ሕጎች መካከል ይመደባል - የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እና የሙያ ማኅበራትን ለማስተዳደር የወጣው አዋጅ ቁጥር 621/2009፡፡ እንደ አብዛኞቹ ተመሳሳይ አዋጆች ሁሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ይህንንም አዋጅ የሚያዩት መንግስት በቀላሉ መቆጣጠር የማይችላቸውን ድርጅቶች ወይ ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አልያም በቁጥጥሩ መዳፍ ስር እንዲወድቁ ያስገደደበት መሣሪያ አድርገው ነው፡፡ የመንግስት ጥርስ ውስጥ ባልተፈለገ አዝማሚያ መግባት ከአዋጁ አንቀፅ እንደሚያስመዝዝ የተረዱ ብዙ ማህበራት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ‹‹ወደቀፏቸው›› ተመልሰዋል ቢባል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እንቅስቃሴያቸው እና ውሳኔያቸውም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት መንግስት እንዴት ሊረዳው ይችላል ከሚል እይታ መተንተኑ  የሥራችን አንዱ አካል ሆኖ እስከመቆጠር ደርሷል ብለው የሚናገሩም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በሀገራችን ካሉ ጠንካራ ከሚባሉ የሙያ ማኅበራት መካከል የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ ማኅበሩ በገለልተኛ የሞያ ማኅበርነት ከሚጠቀሱ ማኅበራት አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የነበረው ጥንካሬ ከሌሎች ተመሳሳይ ማኅበራት ጋር በንፅፅር ሲታይ  ጥንካሬውን አሁንም ይዞ መቀጠል ችሏል ለማለት ያስደፍራል፡፡ እንደ ብዙዎች ግምት ግን፣ የኢትዮጵያ  ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ሕጉ እንዲጠነሰስ ምክንያት ከሆኑ ጥቂት ማኅበራት እና የበጎአድራጎት ድርጅቶች ዋነኛው ነበር፡፡

ጠንካራነቱን እንደያዘ መቀጠል ችሏል የሚባለውን የዚህን ማኅበር የዕድገት ዝግመተ ለውጥ (Evolution) በቅርብ የተከታተሉ ሰዎች ማኅበሩ የዕድገት ጡዘት ጫፍ ማየቱንና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ መሰረቱን ያስጨበጡት የሀገሪቱ አንጋፋ የምጣኔ - ሐብት ባለሙያዎች ከማኅበሩ ጎን መሸሻቸውን ይናገራሉ፡፡ እንደማሳያ አድርገው የሚያነሱትም የማኅበሩ አንጋፋ መስራቾች እና አባላት በነበሩበት ወቅት ይካሄዱ የነበሩ ሕይወት ያላቸው ውይይቶች አለመኖር እና ማኅበሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት በሕዝብ ዘንድ የነበራችውን ቅቡልነት መቀነስ ነው፡፡ እንደነዚህ ሰዎች ማብራሪያ ማኅበሩ አሁን የሚመሰገንባቸው ምርምሮች፣ የህትመት ውጤቶች እና ሌሎችም ተግባራት አንጋፋዎቹ በነበሩበት ወቅት በእነሱ ጥረት የተጀመሩ ናቸው፡፡

በአንጋፋዎቹ አመራር ወቅት ከተጀመሩት ተግባራት አንዱ የሆነው በኢትዮጵያ ምጣኔ -  ሐብት ላይ በየአመቱ የሚያካሂደው አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ከሐምሌ 12-14 ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ በሚገኘው የማኅበሩ ባለአራት ፎቅ  ህንፃ ላይ ለሦስት ቀናት ተካሂዷል፡፡ በኮንፍረንሱ ማጠቃለያ ላይ እንደቀረበው ግምገማ ከሆነ ኮንፍረንሱ ላይ እንዲቀርቡ እቅድ ተይዞላቸው ከነበሩት  89  የምርመምር ውጤቶች መካከል  84ቱ በተሳካ ሁኔታ መቅረባቸውንና (በማኅበሩ የፌስቡክ ገፅ ላይ ዘግይቶ የወጣው መረጃ የቀረቡትን የጥናት ውጤቶች 95 ያደርሳቸዋል፣) ተሳታፊዎችም ባመዛኙ የቀረቡት የጥናት ውጤቶች በዳሰሷቸው ጉዳዮች ደስተኛ መሆናችውን መስክረዋል፡፡
የአንጋፋ መስራች አባላትን ከማኅበሩ መራቅ እና በማኅበሩ አዘጋጅነት ይካሄዱ የነበሩትን ሕይወት ያላቸው ክርክሮች መቋረጥን አስመልክቶ የአዲስ ነገሩ ዘሪሁን ተስፋዬ የማኅበሩ የምርምር ክፍልን በዳሬክተርነት የሚመሩትን ዶ/ር አሰፋ አድማሴን ከዓመታት በፊት ጠይቋቸው ሲመልሱ፤ ‹‹ብዙዎቹ ምሁራን ማኅበሩን ሸሽተዋል፡፡ በአንጻሩ ወጣቱ ትውልድ በተሳትፎ ጥሩ ለውጥ እያሳየ ነው… ብዙዎች እንደቀድሞው ሞቅ ሞቅ ያሉ  (Sensetional) ጉዳዮችን እንድናነሳ ይሻሉ፡፡ እኛ ግን ከስሜት ይልቅ ምክንያትን እናስቀድማለን፤›› ብለው ነበር፡፡

ለአሥር ተከታታይ ዓመታት የተካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ለዶ/ር  አሠፋ መከራከሪያ ጥሩ ማሳያ የነበረው ይመስላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኮንፍረንሱ ላይ ተገኝቶ የታደማቸው  9  መድረኮች ላይ ከቀረቡት ወደ  29  የሚጠጉ የጥናት ውጤቶች መካከከል ዕድሜያቸው በግምት  ከ40  የሚዘሉት አቅራቢዎች ከ4 አይበልጡም ነበር፡፡ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መሳተፍን በተመለከተ ግን ዶ/ር አሰፋ የአቋም ማስተካከያ ያደረጉ ይመስላል፡፡ የ2003 ዓ.ም የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ በተካኼደበት ወቅት ከአባላት ‹ለምን በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት እስክትጠየቁ ድረስ ትጠብቃላትሁ፤ ማኅበሩ በሀገሪቷ ምጣኔ-ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ ለምን የነቃ ተሳትፎ አያደርግም?› የሚል ጥያቄ ያስተናገዱት ዶ/ሩ ‹‹የሀገሪቷን ሁኔታ የምታውቁት ነው፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት ህልውናችን ይቀድማል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ያንን እንድናደርግ አይፈቅድልንም›› ሲሉ መልስ ሰጥተው ነበር፡፡

‹‹የማኅበሩ መግስትን ደፍሮ መተቸት አቁሟል የሚሉ ትችቶች ከዚህም ከዚያም በርትተዋል፡፡ መተቸቱን ማቆሙን ግን ከጥፋት መቁጠር አግባብነት የለውም›› ይላሉ በኮንፍረንሱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንድ ግለሰብ፡፡ ቀጥለውም ‹‹ማኅበሩ ከመንግስት ጋር ፊት ለፊት ከመጋጨት ይልቅ በስልታዊ መንገድ ተጉዞ ቀጣይነቱን ቢያረጋግጥ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችልበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡›› ይላሉ፡፡ አቋማቸውን በምሳሌ ለማስረዳትም ማኅበሩ  ለ2012  የፈረንጆቹ አመት የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ያቀረበውን አጠቃላይ ዘገባ ይጠቅሳሉ፡፡ በምጣኔ-ሃብት ዘገባው ማኅበሩ የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ዕድገት መጠን በተመለከተ የራሱን ቁጥር ከመጠቀም ይልቅ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትርን ቁጥር መጠቀም መርጧል፡፡  ‹‹መንግስት በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ስሱ (Sensative) ነው፡፡ ማኅበሩ የራሱን ቁጥሮች ቢጠቀምና ዕድገቱ  ከ11.4 በመቶ በታች ነው ብሎ ቢዘግብ ኖሮ፤  አይደለም የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዲኤታው መጥተው የመክፈቻ ንግግር ሊያደርጉ ይቅርና የጥናት ውጤታቸውን ያቀረቡትን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን ጥናታቸውን እንኳን እንዳያቀርቡ ይከለክሏቸው ነበር›› ይላሉ እኝሁ ተሳታፊ፡፡

ለዘብተኝነትን መርጧል የተባለው ማኅበር ግን በዘገባው እንዲህ ብሏል፤

“While one can sense that there are signs of high economic growth episodes in the country, the deterministic nature of the growth shades doubt on the accuracy of measuring the GDP in the sense that labour, capital, technology and most importantly nature cannot be so perfect to give a highly predictable constant rate of growth such as this [more than 10% growth rate for consecutive 8 years]. This happens in spite of the fact that a number of the fact that a number of shocks such as draught and international financial crisis put the economy on the test.” EEA Annual Report on the Ethiopian Economy 2012 pp. 4

‹‹[በኢትዮጵያ ውስጥ] ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እንዳሉ ግልፅ ቢሆንም ተመዘገበ የተባለው የዕድገት መጠን ወጥነት (አለመዋዠቅ)፣ የአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት (GDP)  የተለካበትን መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ ይከተዋል ምክንያቱም ከተፈጥሮ የሚገኙትን የምርት ግብአቶች ጨምሮ ሁሉም ልክ እንደሚፈለገው ሆነው እንደዚህ ዓይነት ወጥነት ያለው ከፍተኛ የዕድገት መጠንን ሊደግፉ የሚችሉበት አጋጣሚ እጅግ ጥቂት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ወጥነት ያለው ዕድገት እንዳስመዘገበ የተዘገበው ደግሞ በድርቅ እና በአለም አቀፉ የፋይናንስ ቀውስ በሚፈተንበትም ወቅት ነው፡፡›› የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባከሙያዎች ማኅበር - የ2012 የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሃብት ዓመታዊ ዘገባ ገፅ 4፣ (ትርጉም የራሴ)

ምንም እንኳን አንጋፋዎቹ መስራቾች እና ማኅበሩን በአመራርነት ያገለገሉት አባላት መሸሽ በማኅበሩም ጭምር የታመነ እውነታ ቢሆንም 10ኛው ዓመታዊ ኮንፍረንስ ግን 17 የሚሆኑ መስራች እና 3 ልዩ አስተዋፅዎ ያደረጉ አባላትን የኮንፍረንሱ አንድ አካል አድርጎ አክብሯቸዋል፡፡

አሁን ማኅበሩ የያዘው የማመቻመች መንገድ የት ያደርሰው ይሆን? ዘላቂነቱን አረጋግጦ የሀገሪቷን ምጣኔ ሃብት ወደ ብርሃን የሚመሩ ምርምሮችን የሚያፈልቅ እና በመንግስት እና በህዝብ ከምር የሚወሰድ ተቋም የሚሆንበትስ ጊዜ ምን ያህል ቅርብ ይሆን? ጊዜ ብቻ መልስ አለው፡፡

No comments:

Post a Comment