Sunday, November 11, 2012

የቀለም ልዩነት(መድልኦ) በአገራችን ኢትዮጵያይህን ጽሑፍ ከላይ ርዕሱን አይታችሁ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? አሊያም ሁሌም ጠንካራ ጎናችን የሆኑትን መስማትና ማንበብ ስለለመድን ይህ ሐሳብ ግርታ የሆነ ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይችላል። ሐቅ ቢመርም መዋጥን መልመድ አለብና የተሰማኝን ጻፍኩት የሚሰማችሁን በጨዋ ደንብ አክሉበት። (ፀያፍ ካልተሳደቡ አስተያየት ያልሰጡ የሚመስላቸውን ታታሪ ተሳዳቢዎችን ነው ማሳሰቢያው የሚመለከተው!)

በኢትዮጵያችን ውስጥ ጥቁሩ ማኅበረሰብ (ከጠይም በላይ የጠቆሩትን ማለቴ ነው) በቆዳው ቀለሙ ብቻ መድልዖ ይደርስበታል የማግለልና በቀለም ብቻ የሚፈፀሙት በደሎችና መንስኤዋችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

፩፡-የሥራ ዕድል

ሥራ ለማግኘት ከትምህርትና  ከችሎታ መመዘኛዎች በተጨማሪ የምትጠየቀው ወይ የሚፈለግብህ/ ነገር አለ፡፡ የት አገር እንዳትሉኝ በእኛዋ ኢትዮጵያችን ውስጥ መልከ መልካም መሆን አሊያም ጠይም የቆዳ ቀለም ሚዛኑን ትደፉ ዘንድ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። የስራ አመራር፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ሹመቶች ወዘተ... ግርማ ሞገስና ውበት ከብቃት ይልቅ ሚዛን ይደፋሉ። የቤት ሠራተኝነት የምትቀጠር አንዲት ሴት ጠቆር ካለች የመጥፎ ገድ ምልክት ተደርጋ፣ ልጆቻችን ሊፈሩ ይችላሉ ተብሎ፣ ያቺ ምስኪን የሥራ ዋስትና ታጣለች። በተፈጠሩበት አገር ላይ መገለል ጉዳቱ ምን ያህል መሆኑን ከቀመሱት በላይ ማን ሊሰማው ይችላል?

(
አካላዊ ውበትና ቅርፅ የሚሹ የሥራ መስኮች የሉም እያልኩኝ ግን አይደለም!)

፪፡-የፍቅርና የትዳር አጣማጅ ማግኘት ጫናዎች

አንዲት የአገራችን ልጅ ከናይጀሪያዊ ጓደኛዋ ጋር በፍቅር ከነፈች ሲበዛ በጣም ትወደዋለች እሱም በጣም  ይሳሳላታል፣ የተማረ ስልጡን ባለሙያ ነው። በፍቅር የወደቀችለት ልጅን አግብቶ ቤተሰብ መመሥረት ይፈልጋል፤ እሷም ትፈልጋለች ግን ያደገችበት ማኅበረሰባዊና ቤተሰባዊ ጫና በትምህርት ያገኘችውን ዕውቀት በልጦ በጭንቀት ማዕበል ውስጥ በሰመመን እየተብከነከነች መኖርን አስመረጣት። ለምን እየወደደችው፣ እያፈቀረችው የትዳር አጣማጁ መሆንን አትሻም? መልሱ ቀላል ነው የቀለም ልዩነት ብቻ ነው። የቆዳው መጥቆር፣ የከንፈሩ መተለቅ አካላዊ ገፅታውን እሷ ብትወድለትም ቤተሰቦችዋ ግን እንደማይቀበሉት ታውቃለች፡፡ ያንንም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ነግረዋታል የመካነ አዕምሮ (ዩንቨርሲቲ) መምህሩ ወንድሟ በፌስቡክ ላይ ምስሉን አይቶ ዘራችንን ልታበላሺ ላልጠፋ ወንድ ባርያ ትይዣለሽ? በማለት አሸማቋታል (ይህ ሰው ለተማሪዎቹ ምን ይሆን የሚያስተምራቸው? የዘር፣ የቀለም ልዩነት ወንጀል በሆነበት ዘመን ያልተለወጠ ሰው በተለይ መምህር መሆኑ ጥፋቱን ያሰፋዋል!)
ሁለት አማራጮች ብቻ ነው ያላት የሥራና የፍቅር አጣምጅዋን የሕይወት አጋርዋ አድርጋ መቀጠልና ከቤተሰብ ጋር ያላትን ቁርኝት ማቆም፣ሁለተኛው ውስጧ እያነባ ውድዋን ትታ በቤተሰቦችዋ ሚዛን ውስጥ የሚገባ ባል ማግባት ሁለቱም ውሳኔዎች እጅጉን አስቸጋሪ ከባድ ውሳኔዎች ናቸው ለውቧ የአገሬ ጉብል አጣብቂኝ ውስጥ ሆና በእኸኸኸ ኑሮዋን ትገፋዋለች።

ስንቶቹ ዜጎቻችን ይሆኑ ይህን ፍራቻ ሽሽት ከሚወዱት ጋር መጣመር ፈርተው በብቸኝነት የሚማቅቁት? ቤት ይቁጠራቸው!

በተለይ ጫናው በሴት እህቶቻች ላይ ሲሆን ይበረታል።

፫፡-በቱሪዝም ገቢ ላይ

ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የሚባለው ቱሪዝም ላይ የቀለም ልዩነት (መድልኦ) እንከኖቻችን አሉታዊ ጫናችዎን ያሳርፋሉ። አንድ ጥቁር አሜሪካዊና ሌላው የአገሩን ልጅ ባለነጭ ቆዳውን በእኩል ዐይን የማየት ችግሮች አሉብን። በካፍቴሪያዎች፣መዝናኛ ቦታዎች ውስጥ ለነጭ ሲሆን ፈገግታውና መስተንግዶው ሽርጉዱን ላስተዋለ ያስደምማል። ነጮች የተሻለ ክፍያና ጉርሻ ስለሚሰጡ ነው ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳሳታችኋል፤ እጆቻቸው ባይፈቱም የቆዳቸው ቀለም ግን ደራጃቸውን ከፍ  ያደርግላቸዋል፡፡ የእነሱ ሕፀፅ አይደለም የኛ ደካማ የአስተሳሰብ ደረጃ ነው። በአንድ ወቅት በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ያደረ ኬክ በልቶ ሆዱ የታመመ ፈረንጅ ኬክ ቤቱን ከሰሰ ፍርድ ቤቱም የኬክ ቤቱን ባለቤት አስጠርቶ

"ለምን ያደረ ኬክ ለደንበኞችህ በመሸጥ ጤናቸውን ታሳጣለህ?" ሲባል።

"ክቡር ዳኛ የእኔ አይደለም ጥፋቱ የአስተናጋጆቹ ነው፡፡ ያደረ ኬክ ለፈረንጅ ሲሆን አትሽጡ ብያቸው ነበር ረስተው ነው የሰጡት ትዛዜን ባለማክበር.." በማለት ነበር ምላሹን የሰጠው። ከዚህ ምፀታዊ መልስ ጀርባ ግን መንስኤውን
የምናገኝበት ፍንጭ ይሰጠናል ለነጭ ያለን የተዛባ ግንዛቤን።

ሌላም ላክልላችሁ የአሜሪካ የዐውደ-ሰብ መድረክ አዘጋጅ (ቶክሾው) ኦፕራ ዊንፍሬይ አዲስ አበባ ስትደርስ እስዋን ቸል በማለት የስዋን ጠባቂዎች ሲንከባከቡ በማየትዋ የተሰማትን ቅሬታ በገሃድ ገልፃለች። ሌላም ሌላም ብዙ ማለት ይቻላል ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል!

በቆዳው ቀለም መንኳሰስ የደረሰበት ቱሪስት ተመልሶ አገራችን የመምጣት ዕድሉ ከመቀነሱም በላይ ለሌሎችም ስለ አገራችን ያለውን ተመክሮ ሲያካፍል መጥፎ ተመክሮውን ስለሆነ በቱሪዝም ላይና በመልካም ገፅታችን ላይ ጠባሳውን ያሳርፋልና ሳይውል ሳያድር መታረም አለበት። እንግዳ የማክበር ባሕላችን ለሁሉም የሰው ዘር በእኩል ያለማዳላት ሊሆን ይገባል። ማንም እራሱን የፈጠረ የለምና!

የቀለም መድልኦው ምንጮች

፩፡-ቤተሰብ

ብላቴናዎችን ከቤት ውስጥ ጀምሮ ወላጆች ሲያሳድጉዋቸው ከራሳቸው ልጆች ውስጥ ጠቆር ያለውን "ባሪቾ"፣ ነጣ ያለውን "ቀዮ" በሚሉ ተቀፅላዎች በመጥራት የቀለም ልዩነቱን ከቤት ያስጀምሩዋቸዋል። በዚህ አስተሳሰብ ያደገን ልጅ ጥቁር ማኅበረሰብ ውስጥ ገብቶ ሲኖር የመቀላቀል ችግሮች ይኖሩበታል ራሱን የተለየ ፍጡር አድርጎ ያስባልና!

፪፡-፡የአምልኮ ተቋማት

በአገራችን አንጋፋዎቹ የክርስትናና የእስልምና እምነቶች ውስጥ ቀደም ብሎ ለሃይማኖት ትምህርት ለቆሎ ተማሪነት፣ ለደረሳነት ቤተሰብ የመማር ዕድሉን ሲሰጥ መልከ መልካም የሆኑትን በመምረጥ ሰው ፊት ሲቆሙ ግርማቸው ይማርካል ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በፈጠረው እሳቤ በመነሳት ፈጣሪ በእኩል የፈጠራቸውን ልጆች ወላጆች ሲያበላልጡ የአምልኮ ማዕከላቱም ያንን የሚያርም አሠራር ስለሌላቸው እኩልነት በመድልኦ ሲቀየር ዝምታን መርጠዋል።

፫፡-ባሕላዊ እሴቶቻችን

የዐውድ ዓመት ክብረ በዐል ቀናት የሚገዙ የእርድ እንስሳት ሳይቀሩ በአገራችን ከስጋቸው ይልቅ የቆዳ ቀለማቸው ውበት የምርጫ መስፈርት በመሆኑ በዋጋ ላይም ከፍተኛ ልዩነት አለው። ጥቁር ወይ ዐይን ውስጥ የማይገባ ቀለም ያለው በግ ሆኖ ክብደቱ ከነጩ ወይ ከቀዩ በግ ቢበልጥም በገዢዎቹ ምርጫ ላይ የስጋው ጥራት ሳይሆን የቆዳው ቀለም ኅብር ዋጋውን ያወርደውና ተፈላጊነቱ ይቀንሳል፣ በዶሮ ሸመታው ላይ ገብስማ፣ ቀይና ነጭ ዶሮ ከሌላው በተሻለ ተፈላጊ በመሆናቸው ዋጋቸው የናረ ነው። ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። የቀለም ልዩነቱ በሰው ላይ ብቻ አይቆምማ ላባና ቆዳ የምንበላ ሕዝቦች እንመስላለን። በእህልና ጥራጥሬ ሰፈርም መድልዖው አለ በብረት ማዕድን የበለፀገው ጥቁር ጤፍ ከነጩ ጤፍ ዋጋው ያንሳል። ለምን ይመስላችኋል? ጣዕሙ ወይም የያዘው ንጥረ ነገር ከነጩ አንሶ አይደለም ጥቁር በመሆኑ ብቻ የልዩነቱ ሰይፍ ጥቁሩ ላይ አረፈ። ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል! እያለ የአገሬ ሰው በተሰመረ መም ላይ መጓዙን አልተወም። ትናንት ዛሬ አይደለምና ካለፉት ስህተቶች ተምረን የሚታረመውን ባሕላዊ እሴቶቻችንን አርመን የራሳችንን በማከል የተሻለ የአዲስ ትውልድ ጉዞ ማድረግ አለብን።

ወደኋላ ሄዶ በሃሳብ ከማለም፣
ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም፣ (ብሏልና ሙዚቀኛው)

-ማኅበረሰባችን

ማኅበረሰባችን በነጭ ቅኝ ያልተገዛችው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖሩም በሐሳብ ግን በገሃድ ሲታይ በቅኝ ከተገዙት አገሮች በላይ ጭንቅላታችን ተሰርቋል።

አንድ ጠይም ኳስ ተጫዋች ሲታይ "ኢትዮጵያዊ አይመስልም?" ስንል በአንፃሩ ጠቆር ያለ የአገራችን ተጫዋችን ግን "ከጋና ነው የመጣው?" የምንል ኢትዮጵያ የጠይም አሊያም የቀይ ዳማ አገር ብቻ እናስመስላታለን። ኢትዮጵያችን የጥቁር፣ የነጭ፣ የጠይሙ፣ የቀይዳማው የሁሉም አገር ናት፡፡ ማንኛችንም ለኢትዮጵያችን እኩል ልጆቿ ነን ይህንን መቀበል አለብን ሁላችንም ዜጎቿ። ጥቁርና ነጭ ገፅታን ሳይሆን የተዋበ አዕምሮን የማክበር ባሕል ብናዳብር ለራሳችንም ለአገራችንም ይበጃልና!

ሰላምና ፍቅሩን በብዛት ይስጣችሁ!!!

---
ጸሐፊውን ለማግኘት የኢሜይል አድራሻቸውን eyobebrehane@facebook.comን ይጠቀሙ፡፡

2 comments:

 1. It's probably more so on women than guys, but it is a sad truth! Well done Eyob

  ReplyDelete
 2. ፩)የሥራ ዕድል....
  *ሙያ፣ጥንቃቄ፤ሥነ-መግባር ፤ንፁህነት፤ግልፅነት፤ተጠያቂነት ያካከተተ እንጂ ቀለም አይወክልም!
  ፪)የፍቅር እና የጥዳር አጠማጅ የማግኘት...
  *ለምን ግለሰቡ እመጣበት ሀገር ይዟት አይሄድም? እዚያም ቤት እሳት አለ። ጎበዝ እየተስተዋለ!! ፫)በቱሪዝም ገቢ ላይ.. በእረግጥ በድሮ ዘመን ፈረንጅ እንደዛሬው እንደቻይና ዕቃና ዲቃላ ሜዳ ሙሉ ሳይሆን ክብርና አክባሪ የሆነች ሀገር ላይ እንግዳን አክብሩ ተብለናል።"ተወረወሩ" አልተባልንም!! ህፃናት ፈረንጅ(foreigner)ከረሜላ ሳነቲም እያሉ(ን)ስንከተል ትዝ ይለኛል፡፤ዛሬ እባካችሁ ፈረንጆች ውሰዱን ነው ። ሀ)ቤተሰብ የቀለም መድልዎ ምንጭ,,፣ አይሆንም ለመሆኑ አነድ እናት አመስት ልጆቿ በቀለም አንድ ሆኑ ልጆች ያሏት የት እና መቼ ነው? (የእናት ሆድ ዥንጉርጉር)የሚባለው በባህሪም በቀለምም ልዩነት ነው የራሷን የማታበላልጥ ሰውን አበላልጡ ስደቡ(አንቋሹ)አትልም።ጎበዝ አንዳንዴም በቀላሉ የሚታረምን የሰው አባባል ሰንጥቀን አናስፋው። ለ)የአምልኮ ተቋማት ሳይሆኑ በአብዛኛው ያደጉ ሀገሮችም ለአስተዳደር ለአመራር የሚመረጡበት ስለሆነ ሀገራችን ሀይማኖቶችን ሀጢያተኛ አድርጎ ማቅረብ በደንብ ካለማገናዘብ የመጣ ሊሆን ይችላል።
  ሐ) የዶሮ በግ ቀለም ድሮ ቀረ አልሰሜን ግባ በለው!እንኳን በቀለም አማርጦ በቀለም (በከለር እርሳስ ሥሎ)በቅርስንት ለማስቀመጥ ካሁኑ ሰዓሊያን ቢያስቡበት ይሻላል፡ ወይም ከለር ፎቶ ቢኖራቸው ይሻላል ቀድሞ የዶሮ ወጥ ሊቀር እንደሆነ አልሰማህም ወዳጄ?"ትናንት ዛሬ አይደለምና ካለፉት ስህተቶች ተምረን የሚታረመውን ባሕላዊ እሴቶቻችንን አርመን የራሳችንን በማከል የተሻለ የአዲስ ትውልድ ጉዞ ማድረግ አለብን"። እንደቃለህ ይደረግልህ ወደፊት የእባብ ሾርባ፤የአይጥ ጥብስ፤ የውሻ ቅቅል፤የድመት ቐንጣ፤የአህያና የፈረስ ቁርጥ፤የሩዝ ንፍሮ ባሕልህ ሊሆን ሥልጠና ላይ እንደሆንክ አላወከወም "ሐቅ ቢመርም መዋጥን መልመድ አለብህና የተሰማኝን ጻፍኩት የሚሰማችሁን በጨዋ ደንብ ሌሎችም አክሉበት።ፀሀፊውም ይመችህ።"ማኅበረሰባችን በነጭ ቅኝ ያልተገዛችው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖሩም በሐሳብ ግን በገሃድ ሲታይ በቅኝ ከተገዙት አገሮች በላይ ጭንቅላታችን ተሰርቋል። የተሰረቀብህ አዕምሮ ይመለስልህ ዘንድ የበለጠ ላመንበብ እና ለመረዳት ሞክር በለው!ከሀገረ ካናዳ በቸር ይግጠመን።>>>>>>>

  ReplyDelete