Tuesday, August 28, 2012

የሳምቱ ጋዜጣና መጽሔቶች ከሰኞ እስከ ሰኞ - አሥራሁለት


(ከነሐሴ 14 እስክ ነሐሴ 21/2004)


ሳምንቱ በጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ዜና የተሞላ ነበር፡፡ የሞታቸው ዜና በቲቪ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ምላሾች የተስተናገዱ ሲሆን ጋዜጦች እና ህትመቶችም የዚሁ  አካላት ነበሩ፡፡ የፓትሪያርኩና የጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት ዜናዎች እና የሃዘን መግለጫዎች የጋዜጣዎችን ገጾች ያጨናነቁ ነበሩ፡፡

አዲስ ዘመን ጠ/ሚኒስትሩን ሲያስታውስ

በህትመቱ የፓትሪያርኩን ዜና እረፍት ሲያነሳ የነበረው አዲስ ዘመን የጠ/ሚኒስትሩን ሞት በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም "ኢትዮጵያ ታላቁን መሪ በሞት ተነጠቀች ከትላንትና ጀምሮም ብሔራዊ ሃዘን ታውጇል" ብሏል፡፡ በፊት ገጹ ሙሉውን የጠ/ሚኒስትሩን ምስል የያዘው አዲስ ዘመን በተከታታይ ሳምንታዊ እትሞቹ ሙሉውን (ገጽ 3ትን ጨምሮ) ለመለስ ማስታወሻነት እንዲውል አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፕረስ አሰሴሸን፣ ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ እና ልማት ባንክ ሃዘናቸውን ለመግለጽ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን ሳምንቱን ሙሉ የተለያዩ አካላት የሃዘን መግለጫ ሲያስተናግድ ከርሞአል፡፡ "የህዳሴው መሪ" "ለትውልዱ ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም" የሚሉ የተለያዩ ጽኁፎችን በፎቶ አጅቦ ያስተናገደው አዲስ ዘመን ምርጥ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግሮችን አቅርቦአል፡፡የተወሰኑትን እነሆ፡-

  • የግሌም ሆነ የድርጅቴ አቋም ህገ በመንግስቱ ሊሻሻል የሚችል ምንም አንቀጽ የለውም የሚል ነው፡፡ መለስተኛ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ይደረግ ቢባል ግን የሚያበሳጭ አይደለም፡፡
  • የመበታተን እና የመበጣጠስ አደጋ ጠፍቶ አሁን የፊዴራሊዝም ስርአት ሰፍኖ የብሄር የብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች መብትና እኩልነት መረጋገጡን ሳይ ደስታ ይሰማኛል፡፡በሃገራችን እየታየ ያለው የልማት እንቅስቃሴ እኛ ብቻ ሳይሆን በውጪ የሚገኙት መንግስታት ለስራም ሆነ ለስብሰባ ሲመጡ ከአመት አመት እየታየ ያለውን ለውጥ በማየት ይገርማቸዋል፡፡
  • ኢትዮጲያ ፌደራሊዝም ስርአቱን የጀመረችው ከቅርብ አመታት ወዲህ በመሆኑ የፊደራል ስርአትን አስቀድመው ከጀመሩ የምትማረው ብዙ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ኢትዮጲያ በስርአቱ ዙሪያ ለተቀሩት ሃገራት የሚተርፍ መልካም ተሞክሮ ያላት ሃገር ሆናለች፡፡

አዲስ ዘመን ከጠ/ሚኒስትሩ ሞት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ባለው እትሙ በገጽ ሶስት እትሙ ማህበራዊ ድህረ ገጽ መረጃዎች ተአማኒነት እና አጠቃቀማቸው በሚል ርእስ የማህበራዊ ድህረ ገጾች መረጃዎች ለአመኔታ እንደማይበቁ የሚዳስስ ጽሁፍም አቅርቦ ነበር፡፡



ፍኖተ ነፃነት በልዩ እትም

አርብ እለት በልዩ እትም የወጣችው ፍኖተ ነጻነት በአብዛኛው ከጠ/ሚኒስተሩ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን ይዛ ገበያ ላይ ውላለች፡፡የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን መታሰር በፊት ገጽ ላይ የተዘገበ ሲሆን የአንድነት ፓርቲ የሃዘን መግለጫም ተሳካቷል፡፡ የመለስ ዜናዊ ሁለቱ ገጾች በሚል ሰፊ ፍኖተ ነፃነት አራት የተለያዩ ሰፋፊ ጽሑፎችን አስነብባለች፡፡የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
  • መለስ ዜናዊ እና ሕገ መንግስቱ
  • አወዛጋቢው የመለስ ‹‹ጀግንነት››
  • የመለስ ዜናዊ ቅይጥ ትዝታዎች (ከዞን ዘጠኝ ተከታታይ ብሎጎች ለጋዜጣ እንዲመች ሆኖ የተዘጋጀ)
  • ከጠ/ሚኒስተር መለስ ሞት ጋር በተያያዘ የአንድነት አባላት እየታሰሩ ነው

ሪፓርተር በረቡዕ እና በእሁድ እትሞቹ

ሙሉ እረቡ እትሙን በአቶ መለስ ሞት ዙሪያ ያደረገው ሪፓርተር በፊት ገጹ የጠ/ሚኒስትሩ ፎቶ ይዞ የወጣ ሲሆን በቁጥራቸው በዛ ያሉ የሙሉ ገጽ የሃዘን መግለጫዎችን ሪፓርተር አስተናግዷል፡፡ በእሁድ እትሙ ደግሞ ሳያርፍ ያለፈው መለስ በሚለው ሰፋ ያለ ፅሁፍ ሪፖርተር ያልተሰሙ የመለስ ታሪኮች በሚል ርእስ ስር የሚከተለውን አስነብቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሽግግሩ ዘመን በሰጡት አንድ መግለጫ ላይ ባንዲራ ጨርቅ መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ንግግራቸውም በርካቶች መለስ የአገር ፍቅር እንደሌላቸውና ባንዲራውን እንዳዋደቁት ቆጥረዋቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተጠይቀው፣ ይቀርፃቸው የነበረውን ካሜራ አስጠፍተው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ባንዲራ ጨርቅ ነው፤ ይህ በሁሉም ሰው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ባንዲራ ጨርቅ ሆኖ ሳለ መለስ ሲለው ጨርቅ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ብለዋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብዙ ጊዜ ሲስቁ ስለማይታዩ፣ ለምን? እንደማይስቁ ተጠይቀውለምን እስቃለሁበማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡እኔ ቢሮ ውስጥ ሆኜ በየቀኑ የማነባቸው ደብዳቤዎች በሰቆቃ የተሞሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በደል ደርሶብኛል፣ ፍትሕ አጣሁ፣ ያሰርካቸውን ሰዎች ፍታ፣ የሚሉ በርካታ ይህን መሰል ደብዳቤዎች ይደርሱኛል፡፡ አብዛኞቹም ሁሉን ነገር የማደርገው እኔ እንደሆንኩ የሚገልጹ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ በአገሪቷና በአካባቢው ያሉትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት በየጊዜው እታገላለሁ፡፡ ታዲያ ምን የሚያስቅ ነገር ኖሮ ነው የምስቀው፤ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ
ሚኒስትር መለስ በሕይወታቸው አሳዛኝ ስለሚሏቸው ገጠመኝ ተጠይቀው ሦስት ነገሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡የመጀመሪያው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቀረበለትን የሰላም ሐሳብ አልቀበልም፣ አሻፈረኝ በማለቱ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተሰው ዜጐች ሁሌም ያሳዝኑኛል፡፡ ሁለተኛው በምርጫ 97 ጊዜ በተፈጠረው ግርግር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ናቸው፡፡ በወቅቱ እኔ እንደ ግለሰብ ብሞት እንኳን ምንም አይሰማኝም፡፡ ሆኖም እኔ የአገር መሪ እንደመሆኔ መጠን በሰላም ሳይሆን በእንደዚያ ዓይነት ግርግር ሥልጣን ብለቅ አገሪቱ ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር፡፡ በመሆኑም ውሳኔ ቢያሳዝነኝም ማንም በእኔ ቦታ ቢሆን የሚያደርገው ነገር ነበር፡፡ ሦስተኛ የሚያሳዝነኝ ጉዳይ የሕክምና ትምህርቴን ስከታተል አውቀው የነበረው አንድ ሻይ ቤት ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመልክቼው ምንም ዓይነት ለውጥ ባለማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ አገሪቱን ለመለወጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተረድቼ የበለጠ ለመሥራት ወስኛለሁ፤ብለዋል፡፡

ሳምንታዊው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ቋሚ አምዶቹን በሙሉ በማጠፍ ሙሉውን መጽሄቱን አቶ መለስን የተመለከቱ የተለያዩ ጽሁፎችን አስተናግዷል፡፡ በጥቁር የሽፋን ገጽ አቶ መለስን ፎቶ ይዞ የወጣው አዲስ ጉዳይ በመጨረሻ ገጹ ብቻ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ማናቸው የሚል አንድ ገጽ ጽሑፍ ከማስነበቡ ውጪ ሙሉውን አቶ መለስን በሚዘክሩ ጽሁፎች ነበር እሁድ እለት ገበያ ላይ የዋለው፡፡

ሀተታ ወ መለስ - የአቶ መለስን ታሪክ የዳሰሳ ጽሑፍ

ስለመለስ ከአራቱም ማእዘናት - የአቶ መለስ ሞት እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ዳሰሳ ጽሁፍ ሲሆን አብዛኛውን ጠንካራ ጎናቸውን ያወሱ ሚዲያዎችን ሪፓርት አካተዋል፡፡

የመለስን ጉዳይ መደበቅ ደግ ነበር ፓርቲውስ ከዚህ በኋላ አመኔታ ያጣበታል - የአቶ መለስን ህመም በተመለከተ ፓርቲው ያሳየውን ድብቅ ባህሪያ በዚህ ጽሑፍ በስሱ ተተችቶአል፡፡ በተጨማሪም፡-
·         የጥምረት መንግስት ቢቋቋም የተሻለ ነው - አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
·         አቶ መለስን የማገኛቸው ፓርላማ ውስጥ ነበር - ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (የአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ሊቀመንበር)
·         መልካም አስተዳደር ሊኖር የሚችልባቸው መንዶች ቢመቻቹ ጥሩ ነው - የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ (የመድረክ ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ)
·         አትሌቱን በመሸኘት እና በመቀበል ከፍተኛ የማበረታታት ስራ ሰርተዋል - አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ
 
አዲስ አድማስ በፊት ገጹን ሩብ የሚሸፍን የጠ/ሚኒስተሩን ፎቶግራፍ ይዞ ለንባብ የበቃ ሲሆን ለፓትያርኩ ቀብር ከሌሎች የህትመት ውጤቶች በተሻለ ሽፋን ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment