Friday, August 10, 2012

‘ተቃዋሚ’ ስንል

ሕይወት በአንድ ቦይ አትፈስም፡፡ ሕይወት ፍኖተ ብዙ ናት፡፡ አለምም በተቃርኖ የተሞላች ናት፡፡ ለእያንዳንዱ ጫላ ፣ ጫላቱ አለችው፤ ለእያንዳንዱ በለጠ ፣ በለጡ አለችው፡፡ ማህበራዊ ሕይወታችን፣ የፖለቲካው መንገድ፣ ኢኮኖሚያዊ ሀሳቡ ሁሉ በአማራጭ የተሞላ ነው፡፡ ስለ አይዲዎሎጂ ስታነሱ ካፒታሊዝም ወይስ ኮሚኒዝም ትባላላችው፣ ስለ ዕምነት ስታነሱ አንድ አምላክ ወይስ ብዙ ወይስ ምንም የሚል ሀሳብ ይነሳል፣ ስለ መብት ስታነሱ የግለሰብ መብት ወይስ የቡድን መብት ሲባል ትሰማላችሁ፡፡ ማለቂያ የለውም ተቃርኖው፡፡

ሕይወት ማለትም እነዚህን ተቃርኖዎች ስንመርጥ፣ ስንጥል፣ ስናሻሽል መኖር ነው፡፡

የፖለቲካ ተቃርኖ

ፖለቲካም ከዚህ የሕይወት ሕግ የተለየ መንገድ የለውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ፤  ሁለት ፖለቲከኞች አሉ እንበል ሁለቱም ሕዝቡ እንዲወዳቸው ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አንዱ ለሕዝቡ ‹‹የህብረተሰቡ ዋነኛ ችግር የእንቅልፍ ማጣት ስለሆነ እኔን ከመረጣችሁ የምን መጨናነቅ ከውጭ ሀገር ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ የስነ-ልቦና ባለሙያ  አስመጥቼ በመቅጠር የዕንቅልፍ ችግርን በ7 ቀናት ውስጥ አስወግዳለሁ›› እያለ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ ሌላው በበኩሉ ‹‹የከተማዋ ህብረተሰብ እንቅልፍ አጥቶ መሰቃየቱ የኔ የእናንተ መልካም አገልጋይም ስቃይ ነው፡፡ እኔን የመረጣችሁ ጊዜ ግን መለኮታዊ ሀይል ከእንቅልፍ እጦት እንደሚገላግላችሁ አትጠራጠሩ›› እያለ ለምርጫው ሊተጋ ይችላል፡፡ ለእንቅልፍ እጦቱ የቀረቡት መፍትሄዎች የተለያዩ መሆናቸው ህዝቡ አማራጭ እንዲያገኝ እና ያመነበትን እንዲመርጥ ያስችሉታል፡፡ 

በነገራችን ላይ በከተማዋ ውስጥ ያለው የእንቅልፍ እጦት ችግር ዋነኛ መነሻ ከተማዋ ውስጥ የተተከለ ትልቅ የቆዳ ፋብሪካ የሚያወጣው ድምፅ ሊሆንም ይችላል፡፡ ፖለቲከኞቹም ይሄን ችግር ሊስቱት ይችላሉ፡፡ ዋነኛው የሕዝቡ ስቃይም ችግሩን የሚረዳለት ሰው ሲያጣ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ

ኢትዮጵያ  ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ከተጀመረ ገና 50 ዓመት እንኳን አልሞላውም፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ምን አበርክተዋል የሚለው እጅግ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡

የንጉሳዊ ስርዓቱ በመውደቂያው ዋዜማ ብቅ፣ ብቅ ያሉት ፖለቲካ ፓርቲዎች ንጉሱ እንደ ወደቁ ወደ ስልጣን መንበሩ ቀረብ ቀረብ ማለት ጀመሩ፡፡ ያሳዝናል! በመጀመሪያ ሁሉም ግራ ዘመም ፓርቲዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ሲከተልም ለህዝቡ ያቀረቡለት ሀሳብም ‹‹እኔ ከእርሱ የበለጠ ግራ ዘመም ነኝ›› እያሉ ለህዝቡ እንግዳ የሆኑትን እነ ማርክስን ካላመለክ፣ እነ ሌኒንን ካላወደስ አንተማ ኢምፔሪያሊስት ነህ እየተባባሉ አንድ ሁለት ያሉት ፓርቲዎች ፍፃሜያቸው አሳዛኝ ሆኖ አለፈ፡፡ አሸናፊው ቡድንም ሀገሪቱን በመሳሪያ አስተዳድራለሁ ብሎ ታገለ፡፡ ብሎ፣ ብሎ ግን እሱም  ወደቀ፡፡  

ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዱ ከስኬቶቹ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ነው፡፡ ይሄንም ተከትሎ በዛ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ መድረኩ ብቅ፣ ብቅ አሉ፡፡    

ተቃዋሚው ከየት ወደየት

ዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊነት በምስራቅ/ምእራብ ክፍፍል ማግስት ሶስተኛው ማዕበል (The Third Wave) ተብሎ ብቅ ካለ በኋላ የፓርቲ ፖለቲካ የዲሞክራሲው ማሳያ ተደርጎ ለህዝቡ እንዲቀርብ አስችሏል፡፡ ኢህአዴግም የዚህ የታሪክ አካል በመሆን የተቃውሞ ፖለቲካን የዲሞክራሲው መገለጫ እንዲሆን ከፈቀደ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየሰፈሩ ብቅ፣ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ገና ከመጀመሪያው ኢህአዴግን ሊቀናቀን ይችላል የተባለው ኦነግ አልቻልኩም ብሎ፡

‹‹እልም ያለው ጫካ፣ እልም ያለው ዱር፣
ሲነጋገር ያድራል ከመውዜሩ ጋር፡፡››

እያለ ጫካ ገባ፡፡

ከዛ በመቀጠል አንዳንድ በተለይም ዘውግ ተኮር ፓርቲዎች ብቅ፣ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ የዘውግ ተኮር ፓርቲዎች ወደ ፖለቲካው መምጣታቸው ያስደነገጣቸው ግለሰቦች ‹‹የቅይጥ ብሄር ብሄረሰቦች ፓርቲ›› ብለው ፓርቲ እስከ መመስረት ደርሰዋል፡፡ ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የስልጣን ሽኩቻው አልለቃቸው ብሎ ግንባር ሲፈጥሩ እና በግንባራቸው ሲደፉ ሁለት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች አለፉ፡፡

ሶስተኛው ሀገረ አቀፍ ምርጫ ግን የተቃማዊውን ጎራ በተለየ መሰረት ላይ አስቀመጠው፡፡ የህዝቡን አመኔታም አስገኙ በምርጫውም አስገራሚ ድል አገኙ፡፡ ምርጫውን እንዳሸነፍ ተናገሩ፣ ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ግን ‹‹ከበፊቱ የተሻለ ድል አምጥታችኋል፣ ነገር ግን ያሸነፍኩት እኔ ነኝ›› ብሎ ድል አወጀ አለማቀፍ ታዛቢዎችም ምርጫው አለምአቀፍ መለኪያዎችን ያላሟላ ነው አሉ፡፡

ከዛም ለትንሽ ጊዜ ብልጭ ያለው ጠንካራ የተቃውሞ ሀይል እያነሰ፣እያነሰ መጥቶ አሁን ሞተ ሊባል ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡
ለመሆኑ የተቃውሞ ሀይሉ አሁን ላይ ሆኖ ምን አላማ ይዟል?ቁርጠኝነቱስ? መጨረሻውስ ምን ይሆን? አንዳንድ አመላካቾችን አንመልከት እስኪ፡፡

የተቃውሞው አላማ

አንዳንዱ የተቃዋሚ ሀይል ተቃውሞውን የሚጀምረው ‘ተቃዋሚ’ ልንባል አይገባም በማለት ‘ተቀናቃኝ’ በሉን በሚል ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹ተቃዋሚ ማለት ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲን ፖሊሲዎች በመቃወም ለመተካት እራሱን የሚያዘጋጅ ማለት ነው በሌላ ሀገርም በተመሳሳይ ነው Opposition Party ነው የሚባለው›› ሲባል የለም ስሜን ቀይሩ አጀንዳ አንድ ሆኖ ይመዘገባል፡፡

ሲቀጥል አብዛኛው ፖለቲካ ፓርቲ አላማ አንድን የተወሰነ ሕዝብ ብቻ በመወከል መነሳቱ እይታውን ከመንደር ውስጥ የስልጣን ፍላጎት በላይ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጥርሰ ፍንጭት* ሰዎች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢጥፍሰዲድ) ተቋቋመ እንበል፡፡ እንግዲህ ዋነኛ አላማው ጥርሰ ፍንጭት ሰዎችን በጥርሳቸው እንደ ፈለጉ እንዲስቁበት ለማድረግ ሊሆን ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ በመጀመሪያ ጥርሰ ፍጭት ሰዎች እንደፈለጉ እንዳይስቁ  የመብት ክልከላ አለ ወይ? የሚል ሲሆን በማስከተልም የመብት ጥሰቱስ ካለ የጥርሰ ፍንጭት ሰዎችን መብት ብቻ ለማስከበር መነሳት እና ተሳክቶለት በጥርሳቸው እንደ ፈለጉ እንዲሆኑ ቢያደርግ መብቸው ሙሉ ሊሆን ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄንም መመለስ የሚችል አይመስልም ይህ ‘የአንድ ወንዝ ፓርቲ’፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በይፋ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች 76 እንደሆኑ የቦርዱ ዌብሳይት ያመለክታል ከነዚህ ውስጥ ከ53 የሚሆኑት ለአንድ ዘውግ (በተለምዶ ብሄር) መብት መከበር የሚታገሉ ሲሆኑ፤ ይሄም ከላይ ያነሳናቸው ጥያቄዎች በወሳኝነት መላሽ እንደሚስፈልጋቸው ያስገነዝበናል፡፡

ሌላው ከአላማቸው ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ግልፅ አላማ ያለው ፓርቲ ስንት ነው? ብለን ስንጠይቅ ነው፡፡ በምርጫ 2002 በአስገራሚ ሁኔታ  ‹‹ፖሊሲ የለንም፣ ፖሊሲ የምንቀርፀው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመረጠን በኋላ ከህዝቡ ጋር አብረን መክረን ነው፡፡›› የሚል ‘ፓርቲ’ ህዝቡን ‘ነፃ’ ለማውጣት እንደተሰለፈ አይተናል፡፡ ለመሆኑ ስንቱ ፓርቲ ነው አላማ ቀርፆ ህዝቡን አላማየን አይታችሁ ምረጡኝ የሚለው? ቢሮውን መኖሪያ ቤቱ ውስጥ አድርጎ አባላትን በዘመድ አዝማድ እየመለመለ ህዝብን እመራላው፣ እኔ ነኝ ትክክለኛ አማራጭ ቢል ህዝቡስ ምን አይቶ ይቅረበው? ለነገሩ ይሄስ ቢሆን የምርጫ ሰሞን ግርግር አይደል?
ለመሆኑ 31,869 ለሚሆነው የሀረሪ ሕዝብ 3 የተለያዩ ፓርቲዎች እኔ እሻልኻለው ብለው ሲቀርቡለት ምን አይነት የአላማ ልዩነት ይዘው ነው? ነው ዙፋን ጉዳዩ ነው ? እንድንል ያደርገናል፡፡

ቁርጠኝነት

ከላይ እንደ አየነው የአላማ አለመኖር፣ መደብዘዝ ወይም መጥበብ የተቃዋሚው ጎራ የመጀመሪያው ፈተና ነው፡፡ እሽ አላማው እንዳለ ሆኖ ፓርቲዎች ያስቀመጡትን አላማ ለማስፈፀም ምን ያክል መሰጠቱ (Submission) አላቸው? የሚለው ደግሞ ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ከላይ ያነሳነውን ምሳሌ እዚህም እናምጣው፡፡ የኢትዮጵያ ጥርሰ ፍንጭት ሰዎች  ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢጥፍሰዲድ) የተቋቋመለት አላማ ጥርሰ ፍንጭቱ ህዝብ በጥርሱ እንደፈለ እንዲሆን ማድረግ ነው እንበል፡፡ ፓርቲው ምን ያክል ከጥርሰ ፍንጭቱ የህብረተሰብ ክፍል ጋር አብሮ እየሰራ ነው? ለአላማውስ እስከ ምን ድረስ ነው የሚታገለው? ‹‹እኔ ድራፍት እየጠጣው ነው መታገል የምፈልገው›› እያለ ለሚታገልልት አላማ ሲል ከብርሌ አንገት እንኳን መራቅ የማይፈልግ ነው ወይስ እስከ ከርቸሌ ለመሄድ የወሰነ ነው?  በምንዳ ተታሎ የጥርሰ ፍጭቱን ሕዝብ መብት ይሸጣል ወይስ በአቋሙ ይፀናል? እነዚህ ጥያቄዎች ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ካሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በየጊዜው የምንሰማቸው ዋነኛ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ዲሞክራሲ ሲሉ

የኢትየጵያ ምርጫ ቦርድ በአሁኑ ወቅት በመዝገቡ ውስጥ ካካተታቸው 76 ፓርቲዎች ውስጥ 55ቱ ‘ዲሞክራሲያዊ’ ወይም ‘ዲሞክራቲክ’ የሚል ቅፅል በስያሜያቸው ውስጥ አካተዋል፡፡ ለምሳሌ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ፣ የጠምባሮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ  ሕብረት፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ የደንጣ፣ ዱባሞ ክንችችላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ  ድርጅት፣የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ  ንቅናቄ፣ የሲዳማ ሀዲቾ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ  ድርጅት እያለ ዝርዝሩ  ይቀጥላል፡፡ ለመሆኑ ስንቶቹ ፓርቲዎች ናቸው እንደ ስማቸው ዲሞክራሲያዊ የሆኑት? ውስጠ ዲሞክራሲ (Democratic Centralism) በስንቶቹ ፓርቲዎች ውስጥ አለ? ከተመሰረተ አስራ ምናምን አመት የሆነው ‘ዲሞክራሲያዊ’ ፓርቲ እንዴት አንዴ እንኳን የድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አይጠራም?

እንዴት አንድ የፓርቲ መሪ ራሱ ገንዘብ ሰብሳቢ፣ ራሱ ገንዘብ ያዥ፣ ራሱ ኦዲተር፣ ራሱ የፓርቲው አመታዊ ሪፖርት አዘጋጅ እና አፅዳቂ ይሆናል? ምን አይነትስ ‘ዲሞክራሲ’ ለማምጣት ነው የሚታገለው?

የፓርቲ አባላት ‹‹ይሄ ነገር መልካም አይደለም ስለዚህ እንዲህ ይደረግ ሲሉ›› ከመንግስት ጋር ወግናችኋል፣ የስልጣን ጥመኞች ናችሁ፣ አድማ በፓርተው ውስጥ ለመምታት አቅዳችኋል እያሉ ማውገዝ እና ከፓርቲው  ማባረር የተቃውሞው ጎራ ልማዳዊ ተግባር ሆኗል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከነ መሪ ግለሰቦቻቸው ነገ ስልጣን ቢይዝ የሚያመጡት ዲሞክራሲያዊ ለውጥስ ምን አይነት ይሆን? አዎ፤ ፈተናው ብዙ ነው፡፡

ለመሆኑ የተቃውሞውን ሀይል እንዲህ በሞት አፋፍ ላይ ያስቀመጠው ማን ነው? ወደፊትስ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? የሚለውን ለማየት በቀጣይ ፅሁፍ እንመለስበታለን፡፡

·       *  ፍንጭት ማለት የፊት ጥርሱ ክፍት  የኾነ ማለት ነው።

No comments:

Post a Comment